ENA - ኢዜአ አማርኛ
አርእስተ ዜና
የግብፅ የውሃ አባካኝነት እና ያረጀው የቅኝ ግዛት እሳቤ
Sep 22, 2026 26
ግብፅ ለዓባይ ወንዝ ፍሰት ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የሌላት ብትሆንም፣ የዓባይን ውኃ በማባከን ትታወቃለች። ይህ በዓባይ ወንዝ እውነት ላይ ያለ አስገራሚ ተቃርኖ ነው። በርካታ የውሃ ሃብት ተንታኞችና ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ በግብፅ ግድቦች ውስጥ የሚከማቸው ውኃ ሀገሪቱ ባላት እጅግ ሞቃታማ የአየር ንብረት ምክንያት በትነት ይባክናል። የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ውኃዎች እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ (GERD) አማካሪ ቡድን ሰብሳቢ፣ እንዲሁም የምሥራቅ ናይል አህጉራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ እንደሚገልጹት፣ የታላቁ አስዋን ግድብ የፈጠረው የናስር ሀይቅ የሚገኘው በዓለም ላይ በጣም ሞቃት እና ደረቅ ከሆኑት የሰሃራ በረሃ ክፍሎች ውስጥ ነው። በዚህም አስዋን ግድብ በየዓመቱ በትነት ምክንያት ብቻ ከ15 እስከ 16 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ያጣል። ከዚህ በተጨማሪ በግብፅ የዓባይ ሸለቆ እና ዴልታ አሁንም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የግብርና መሬት የሚጠጣው በባህላዊ የጎርፍ/የቦይ መስኖ ዘዴ ነው። ይህም ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን በትነት፣ በመሬት ሰርገት እና ባልተጣጠመ ስርጭት ምክንያት ያባክናል። በግብጽ እንደ ጠብታ መስኖ እና ረጭ መስኖ (Sprinkler) ያሉ ዘመናዊና ውሃ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች ትግበራ አሁንም አነስተኛ ነው። በሌላ በኩል በረሃን ወደ እርሻ መሬት ለመቀየር የተቀረፁ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በረጅም ክፍት ካናሎች ውሃን ወደ በረሃ በመሳብ ለማልማት የሚደረገው ጥረት፣ ውሃው ክፍት በሆኑ ካናሎች በሚጓዝበት ወቅት በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በትነት እና ወደ አሸዋማ መሬት በመስረግ ከፍተኛ ውሃም ለዘመናት እያባከነች ትገኛለች። ይህ አልበቃት ብሎ ግብፅ በደረቅና ከፍተኛ የትነት መጠን ባላቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የውሃ ፍጆታ ያላቸውን ሰብሎች በስፋት ታመርታለች። እንደ ሩዝ እና የሸንኮራ አገዳ ያሉ ከፍተኛ ውሃ የሚፈልጉ ሰብሎችን በበረሃማ የአየር ጠባይ ውስጥ በጎርፍ መስኖ ማልማት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሜትር ኪዩብ ውሃን ታባክናለች። በተቃራኒው ውኃን በኢትዮጵያ ጥልቅ፤ ጠባብ ሸለቆዎች ውስጥ እና አመቺ የአየር ንብረት ባለበት አካባቢ ማከማቸት የትነት መጠንን ለመቀነስ እጅግ ከፍተኛ ሚና አለው። ዋናው የውኃ ማከማቻ በኢትዮጵያ መሆኑ በሙቀት ሊባክን የሚችለውን በርካታ መጠን ያለው ውኃ ከማዳኑም በላይ፣ ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚለቀቀውን የውኃ መጠን አስተማማኝና የተረጋጋ እንዲሆን ያደርገዋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበት ቦታ ቀዝቃዛና ጥልቅ ሸለቆ በመሆኑ፣ ውሃን በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ ከሚገኘው የአስዋን ግድብ ይልቅ እዚያ መያዝ በትነት የሚባክነውን የውሃ መጠን በእጅጉ ይቀንሳል። ይህም ለግብፅም ጭምር ውሃን የሚቆጥብ ሳይንሳዊ እውነታ ነው። ሳይንሳዊ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግብፅ አሁንም ያረጀና የፈጀ የቅኝ ግዛት እሳቤን በመያዝ በዓባይ ወንዝ ላይ የተሳሳተ አቋም ማራመዷን ቀጥላለች። ግብፅ አሁንም በ1929 እና 1959 በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረጉ፣ ኢትዮጵያን ያገለሉ ፍትሃዊ ያልሆኑ ውሎች ላይ በመመስረት የከልካይነት መብት አለኝ የሚል ጊዜ ያለፈበት እሳቤ ለማራማድ እየጣረች ነው። የኢትዮጵያን ዕድገትና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ለግብፅ እንደ ስጋት አድርጎ በመሳል፣ የዓባይን ጉዳይ የደህንነት ስጋት በማስመሰል ጫና ለመፍጠር የምታደረግው ከንቱ ሙከራም ከዚህ ካረጀ እሳቤ የመነጨ ነው። ነገር ግን ካይሮ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ መብት ላይ ጫና ለማሳደር ከምታደርገው ከንቱ ጥረት ይልቅ፣ የራሷን የውሃ አጠቃቀም ማዘመን፣ ዘመናዊ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ጥቅም እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትብብር ማድረግ የረጅም ጊዜ መፍትሔ ነው።
የከምባታ ዘመን መለወጫ በዓል "መሳላ" በአብሮነትና በትብብር የመሥራት እሴት ጎልቶ የሚታይበት በዓል ነው- አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ
Sep 22, 2026 28
ዱራሜ ፤ መስከረም 12/2019(ኢዜአ) ፦የከምባታ ዘመን መለወጫ በዓል "መሳላ" በአብሮነትና በትብብር የመሥራት እሴት ጎልቶ የሚታይበት በዓል መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ገለፁ። የከምባታ ዘመን መለወጫ "መሳላ" በዓል በዱራሜ ሁለገብ ስታዲየም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። ዋና አፈ ጉባኤዋ በወቅቱ እንዳሉት፤ የከምባታ ዘመን መለወጫ በዓል "መሳላ" በአብሮነትና በትብብር የመሥራት እሴት ጎልቶ የሚታይበት በዓል ነው። "መሳላ" የመደጋገፍና የአንድነት እሴቶችን ከማጠናከር ባለፈ ለክልሉ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማዋል እንደሚገባ አመልክተዋል። በዓሉ ወደ አዲስ ዘመን የመሻገር ምልክት ከመሆኑም በተጨማሪ ባህላዊ ክዋኔዎቹ፣ የመደጋገፍና የአብሮነት እሴት ጎልቶ የሚታይበት ነው ብለዋል። እንዲሁም የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተራራቁ የሚቀራረቡበት በመሆኑ እሴቱን አስጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አስገንዘበዋል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው፤ የ"መሳላ" በዓል ከክረምት ወቅት ወደ ሌላ የመሻገር ምልክት ብቻ ሳይሆን የመተሳሰብና የመደጋገፍ እሴት የሚጎለብትበት መሆኑን ተናግረዋል። በዓሉ ጥላቻና ቂምን በማስወገድ ሰላምን በማፅናት፣ በአብሮነትና በመረዳዳት የሚከበር መሆኑንም አክለዋል። የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ፤ "መሳላ" የአዲስ እሳቤ ማስጀመሪያ በመሆኑ በተለየ መንገድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው ብለዋል። የበዓሉን እሴቶች በማጎልበት ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በበዓሉ አከባበር ላይ የክልሉ፣ የዞንና የዱራሜ ከተማ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የባህል ሽማግሌዎችና ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተጋባዥ እንግዶች ታዳሚ ሆነዋል።
በሐረሪ ክልል በኢንዲስትሪ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ናቸው
Sep 22, 2026 30
ሐረር፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ):-በሐረሪ ክልል በኢንዲስትሪ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካላት ገለጹ። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና የኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤልን ጨምሮ የክልሉ አመራር አካላት በሐረሪ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ኢንዱስትሪ ልማት እና ሌሎች ስራዎችን ጎብኝተዋል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና የኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በሀረሪ ክልል በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጪ ምንዛሬን የማስቀረት ስራ በስፋት ስለመከናወኑ መመልከታቸውን ተናግረዋል። በዚህም ኢንዱስትሪው የሚያመርተው የመብራት ምሰሶ ለኮሪደር ልማት ስራ በማዋል ከተማዋን ውብና ማራኪ ማድረጉን በምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል። በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች በአንድ ቦታ የተለያዩ አገልግሎት በማግኘት ወጪና ጊዜን ባግባቡ እንዲጠቀሙ እያደረገ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል። በአካባቢው የሚገኙ ሃብትንና ጥበብን በመጠቀም የሚገነቡት የገጠር ሞዴል መንደሮችም የሚበረታቱ መሆኑንም አንስተዋል። እንደ አቶ ስንታየሁ ገለጻ በክልሉ በኢንዲስትሪ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ናቸው። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ናትናኤል ሚሊዮን በበኩላቸው በክልሉ ጥንታዊ እና ታሪካዊ እሴቶችን በያዘ መልኩ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች ሳቢና ማራኪ ናቸው ። በመሰረተ ልማት ግንበታ፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት አሰጣጥ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚከናወኑ ተግባራት ዓርዓያነት ያላቸውና ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገቡ ናቸው ብለዋል። በጉብኝቱ ላይ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር እና ሌሎች የክልሎቹ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች ተዘርግተዋል - ጤና ሚኒስቴር
Sep 22, 2026 41
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች በጤና ተቋማት መዘርጋታቸውን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ። የጤና ሚኒስቴር ሀገር አቀፍ የሁለተኛው ብሔራዊ ከወሊድ በኃላ የሚከሰት የደም መፍሰስ እና የእናቶች ጤና ፖሊሲ ሰነድ ላይ ያተኮረ ምክክር "ከቃል ኪዳን ወደ ተግባር" በሚል መሪ ሃሳብ እያካሄደ ይገኛል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በመደመር እሳቤ በሁሉም መስክ በከፍተኛ የብልፅግና ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል። በጤናው ዘርፍም በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተው፤ይህም በሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የተገኘ ነው ብለዋል። በሚኒስቴሩ እና በሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ በተሰራው ስራ የእናቶች ሞት መጠን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ መጠን መቀነስ መቻሉን አንስተዋል። ይህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት የእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ላይ በትኩረት ከሚሰሩ ቀዳሚ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያስቻለ መሆኑን በመግለጽ። በቀጣይ በ2030ዓም ይህን የእናቶች የሞት መጠን መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና ለስኬታማነቱም በሚቀጥሉት 3 እና 4 ዓመታት ከፍተኛ ሥራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ለዚህም ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች በጤና ተቋማት መዘርጋታቸውን ተናግረዋል። መድረኩ የተዘጋጀው የእናቶች እና የሕፃናት ጤናን የበለጠ ለማሻሻል፣ እስካሁን ያሉትን ስኬቶች እንደ ወረት ለመውሰድ፣ ቀሪ ስራዎችን ደግሞ በመገምገም የማሻሻያ ተግባራት ማከናወን የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ሰነዶችን ይፋ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። የፖሊሲ ሰነዶቹ የጤና ባለሙያዎች የበረታ የደም መፍሰስን በጊዜ ለይተው ወደሚቀጥለው ተቋም ሪፈር ማድረግና አስፈላጊው ግብዓት እንዲሟላ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል። በተጨማሪም እናቶች ሙሉ በሙሉ በጤና ተቋማት መቆየት እንዲችሉ የምክር አገልግሎት የሚሰጡበት መሆኑን ጠቁመው ለፖሊሲው ተግባራዊነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በኢሉባቦር ዞን ከቡና ምርት የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቡና ጥራት አጠባበቅ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል
Sep 22, 2026 54
መቱ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ):- በኢሉባቦር ዞን ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢና የአካባቢውን አምራቾች ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ በቡና ጥራት አጠባበቅና አያያዝ ላይ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ገለጹ። በኢሉባቦር ዞን የ2019 ዓ.ም የቡና ምርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በመቱ ከተማ ተካሄዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ እንዳስታወቁት፤ ባለፉት ዓመታት በዞኑ የቡና ምርት ጥራትን ለማረጋገጥ በየደረጃው ሰፋፊ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። በእነዚህ የተቀናጁ ስራዎችም አመርቂና ጥሩ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በዘርፉ የተመዘገቡ አመርቂ ውጤቶችን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማሳደግ የሚያስችሉ ጥረቶች አሁንም በላቀ ትጋት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል። ዋና አስተዳዳሪው አክለው እንደገለጹት፤ የምርት ጥራትን ከመጠበቅ ጎን ለጎን ሕገወጥ የቡና ዝውውርን መከላከል እና ምርቱን በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ የዞኑ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ነው። በመሆኑም ከቡና አምራቾች እስከ ላኪዎች እና አመራር አካላት ድረስ ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለእነዚህ ነጥቦች ትኩረት በመስጠት የተቀናጀ ቁጥጥርና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተጨማሪም የቀይ ቡና መፈልፈያ ፋብሪካዎች ቀድመው አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ፋብሪካዎቹ በቴክኒክና በአሰራር ረገድ ቀድመው በመዘጋጀት ከዞኑ ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን የቡና ምርት ጥራትና መጠን ለማሳደግ የሚጠበቅባቸውን ሚና በብቃትና በኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አቶ እንዳልካቸው ጠቁመዋል። የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳሙ ታከለ በበኩላቸው በ2019 የምርት ዘመን ከዞኑ 62 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እቅድ መኖሩን ገልጸው፤ ለዚህ እቅድ ስኬታማነት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል። በምክክር መድረኩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ በ2019 ዓ.ም የምርት ዘመን የቡና ጥራትን አስተማማኝ በሆነ ደረጃ ለማስጠበቅ የገበያ ሰንሰለቱን ማስተካከልና የምርት አያያዝን ማዘመን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። በቡና ንግድ የተሰማሩት አቶ በፈቃዱ ገምቴሳ የቡና ምርት ጥራትን የማረጋገጥ ጉዳይ የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን የሁሉንም አካላት ከፍተኛ ተሳትፎና ትኩረት የሚጠይቅ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የክትትል ሰንሰለቱ ጥብቅ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ተሳታፊው፤ ለቡና ምርት አያያዝም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። የቡና ጥራትን የማስጠበቅ ስራ በሁሉም ደረጃዎች ተመሳሳይ ትኩረት ካላገኘ በተወሰኑ ሂደቶች ብቻ ሊረጋገጥ እንደማይችል ያነሱት ደግሞ አቶ ስባቱ በቀለ ናቸው። አያይዘውም የቡና ጥራት ከምርቱ የሚጠበቀውን ተጠቃሚነት የሚወስን ዋና ምክንያት በመሆኑ፣ ባለድርሻ አካላት በየደረጃው በሚከናወኑ የጥራት ማስጠበቅ ተግባራት ላይ በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ፖለቲካ
የካይሮ እውነተኛ ገጽታ-ከውሃ አባካኝነት እስከ ቀጣናዊ የሰላም ጠንቅ
Sep 22, 2026 191
ግብፅ በዓለም አቀፍ መድረክ የምታቀርበው "የውሃ እጥረት ስጋት አለብኝ" የሚል ተበዳይ አስመስሎ የመቅረብ ትርክት፣ ከጀርባው ያለውን እውነተኛ የስግብግብነትና የቀጣናዊ የበላይነት ፍላጎት ለመሸፈን የተዘጋጀ ጭምብል ነው። ካይሮ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የሚበቃት ግዙፍ የከርሰ ምድር ውሃ እያላትና የዓባይን ውሃ በበረሃ ላይ በማፍሰስ፣ በሌላ በኩል ግን ኢትዮጵያውያን ለዕለት ጉርሳቸውና ለቤታቸው መብራት እንኳ ውሃ እንዳይጠቀሙ፣ የታችኛው የተፋሰስ ሀገራትም በድህነት እንጂ በዕድገት እንዳይገለፁ ትታገላለች። ግብጽ ለዘመናት የሚበቃ የከርሰ ምድር ውሃ አላት። በኢትዮጵያ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ዝናብ ቢቋረጥ እንኳ ግብጽ ለዘመናት የሚበቃት የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ይዛለች። ግብጽ ውሃ ታባክናለች፤ አጠቃቀሟም እጅግ የከፋ ነው። ግብፅ ሰፊ ረግረጋማ መሬት ያላት በማስመሰል የሸንኮራ አገዳ እና ሩዝ ታመርታለች። ነገር ግን እሷ የውሃ ማባከኗን ለማስቀጠል ሌሎች ንጹሕ ውሃ እንኳ እንዳይጠጡና የጓሮ ጎመን እንዳያመርቱ መሻቷ ነው። ግብፅ የዜጎቿን የተደላደለና ቅንጡ ሕይወት ለማስጠበቅ ስትል፣ ኢትዮጵያ ልማቷን ገትታ በድህነት እንድትማቅቅ ትፈልጋለች። በበረሃ ውሃ እያፈሰሰች ኢትዮጵያውያን መብራት እንዳያገኙ ትቃወማለች፡ አዳዲስ የቅንጦት ከተሞችን በመገንባት ፤ በሌላ በኩል ግን ኢትዮጵያውያን በቤታቸው መብራትና ማብሰያ ምድጃ እንኳ እንዳይኖራቸው ትሰራለች። ግብፃውያን የውኃ እጥረት እንዳለባቸው ያስመስላሉ ነገር ግን የዓባይን ውሃ ፍሰት ለመጠበቅ ከ50 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን እየተከለች ያለቸውን ኢትዮጵያን ለማመስገን አይፈልጉም። ይልቁንም ግብፅ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማናጋት ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። ግብጽ የሱዳንን ሉዓላዊነትና አንድነት አትሻም። ሱዳንን እንደ ገለልተኛ አገር ሳይሆን እንደ እራሷ ጥገኛ ሀገር አድርጋ ስለምትቆጥራት በውስጥ ጉዳዮቿ እንደፈለገች በመግባት እና ቅጥረኞችን በመጠቀም ሱዳንን ለማፍረስና ኢትዮጵያን የማዳከሚያ መተላለፊያ ለማድረግ እየሰራች ነው። ግብጽ በቀይ ባሕር ያለ ማንኛውም አገር እንዲበለጽግና እንዲያድግ አትፈልግም። ይህ እጅግ አደገኛ የሆነ የአጥፊነትና የቀጣናው ሰላም ጠንቅ የሆነ የፖለቲካ ሴራ ነው!
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ እገዳ ጣለ
Sep 21, 2026 559
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በትግራይ ቴሌቪዥን (Tigray TV) ላይ ላልተወሰነ ጊዜ እገዳ መጣሉን አስታወቀ። በኢፌዴሪ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል በፕሬቶሪያ የተፈፀመውን የሰላም ስምምነት ተከተሎ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ባደረገው ውይይትና በተደረሰበት ስምምነት መሠረት፣ቀደም ሲል በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነስቶ ወደ ሥራ መመለሱን በመግለጫው አስታውሷል። ከዚህም በተጨማሪ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች የሰላም ግንባታና የሙያ ብቃት ማሳደጊያ ሥልጠናዎችን በመስጠት ሚዲያው ወደ ሕገ-መንግሥታዊና ሙያዊ መስመር እንዲመለስ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክቷል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትግራይ ቴሌቪዥን በተሰጠው ዕድል ተጠቅሞ እና የሙያ ሥነ-ምግባር አክብሮ አገልግሎት መስጠት ሲገባው፤ የሀገርንና የህዝብን ደህንነት እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ወደ ግጭት የሚገፋፉ እና ፅንፈኝነት የሚያበረታቱ መልእክቶች በተከታታይ እየተላለፉበት እንደሚገኝ የባለሥልጣኑ የሚዲያ ይዘት ክትትል ግምገማ ውጤት እንደሚያሳይ ተጠቅሷል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በህግ የተጣለበትን ኃላፊነት መሠረት በማድረግ፣ ከዛሬ ጀምሮ በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ላልተወሰነ ጊዜ እገዳ መጣሉን ገልጿል። ማንኛውም ዲጂታል፣ የብሮድካስትም ሆነ የሕትመት ሚዲያ የትግራይ ቴሌቪዥንን እንደ መረጃ ምንጭ መጠቀም ወይም የቴሌቪዥን ጣቢያው በህገወጥ መንገድ የሚያሰራጫቸውን ይዘቶች አሰራጭቶ ወይም አስተጋብቶ መገኘት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን አስገንዝቧል። ይህንን መመሪያ ተላልፎ በሚገኝ ማንኛውም ሚዲያ ላይ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንደሚወስድ በጥብቅ አሳስቧል።
ግብፅ ከፍተኛ የውሃ ሀብት እያላት ደካማ የውሃ አስተዳደር የምትከተል ሀገር ናት - አቶ ጌታቸው ረዳ
Sep 19, 2026 1129
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- ግብፅ ከፍተኛ የውሃ ሀብት እያላት ደካማ የውሃ አስተዳደር የምትከተል ሀገር መሆኗን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ገለጹ። አቶ ጌታቸው ረዳ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ግብፅ የዓባይ ወንዝን የራሷ ብቻ አድርጎ የመመልከት ኋላ ቀር አካሄድ እንደምትከተል ተናግረዋል። የግብፅ አቋም የወንዙን እውነተኛ ምንጭ ጨምሮ ፍጹም ሐቅን የሚክድ የድፍረት አካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ደግሞ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብለዋል። ግብፅ ሳይንስን በተቃረነ መልኩ በዓባይ አጠቃቀም ዙሪያ የምታራምደው የተሳሳተ አካሄድ ግብፃዊያን “ታሪካዊ መብቶች” በሚል የተሳሳተ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል ብለዋል። “ታሪካዊ መብት” የሚለው ሀሳብ ውሃውን ቀድሞ መጠቀም የጀመረ አካል ለዘላለም መቆጣጠር አለበት ከሚል ስግብግብ አስተሳሰብ የመነጨ መሆኑን አመልክተዋል። ግብጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች የምታራምደው የ“ውሃ ደህንነት” ጽንሰ ሀሳብ የዚሁ ጊዜ ያለፈበት የአንድ ወገን የበላይነት ፍላጎት አካል መሆኑንም አቶ ጌታቸው አብራርተዋል። ይህ ሆን ተብሎ ለፖለቲካዊ ትርፍ የተፈጠረ አሳሳች ትርክት እንደሆነም ነው የተናገሩት። ግብፅ በዓለም ላይ ደካማ የውሃ አስተዳደር ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት ያሉት አቶ ጌታቸው በበረሃማ አካባቢዎች የሚገኙት እንደ ቱሽካ ያሉ ከፍተኛ የውሃ መጠን የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች የዚሁ ብክነት የተሞላበት አጠቃቀም ማሳያ ናቸው ብለዋል። በግብፅ በሚገኘው የአስዋን ግድብ የሚከሰተው ዓመታዊ የውሃ ትነት መጠን፣ በኢትዮጵያ የውሃ ማከማቻዎች ውስጥ ከሚቀመጠው የውሃ መጠን በእጅጉ የሚበልጥ መሆኑንም ተናግረዋል። የዓባይ ወንዝ ዋና ምንጭ በሆነችው ኢትዮጵያ እና ሰፊ የመስኖ አቅም ያላት ሱዳን መካከል ሰላም እንዳይኖር ግብፅ ስትሰራ መቆየቷን አንስተው በሱዳን ያለው ቀውስ ሀገሪቱ ውሃውን እንዳትጠቀም ለማድረግ ግብፅ የምታራምደው ስትራቴጂ ነው ብለዋል። ግብፅ ያላት ብቸኛው መንገድ ጊዜው ያለፈበትን አካሄድ በመተው ከነባራዊው እውነት ጋር መታረቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በቅንጅት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-የሰላም ሚኒስቴር
Sep 19, 2026 952
ባሕርዳር፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶችና ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት የሚያከናውኗቸው ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አመለከተ። የሰላም ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። የሰላም ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የሚኒስትሩ ተወካይ አቶ መብራቱ ካሳ በመድረኩ እንደገለፁት፤ኢትዮጵያ በተለያየ ወቅት የገጠሟትን ፈተናዎች በፅናት እየተወጣች ትገኛለች። በተለይ በአማራ ክልል አጋጥሞ የነበረውን የሰላም እጦት መላ ህዝቡ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅተው በከፈሉት ዋጋ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እየተረጋገጠ እንዲመጣ መሰረት መጣሉን ገልፀዋል። የመድረኩ አላማም በክልሉ እየተረጋገጠ የመጣውን ሰላም በቀጣይም በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን አብራርተዋል። የፀጥታ ኃይሉ፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ሌሎች በጋራ ያመጡትን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል የጀመሩትን ሰላምን የማፅናት ተግባር አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል። የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በተደረገ የጋራ ጥረት ሰላሙ እየተረጋገጠ መምጣቱን ገልፀዋል። በተለይ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና ፅንፈኛ ኃይሎች ክልሉንና ኢትዮጵያን ለመበተን ያደረጉትን ጥረት በፀጥታ ኃይሉና በህዝቡ የጋራ ቅንጅት ማክሸፍ መቻሉን ተናግረዋል። ሰላም ለሰው ልጆች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ነው ያሉት እሸቱ (ዶ/ር) ሰላምን ማጽናት ለመንግስትና ለፀጥታ ተቋማት ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁላችንም በጋራ የምናረጋግጠው ተግባር መሆኑን አንስተዋል። በመሆኑም የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የህይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች ፣ሴቶችና ወጣቶች፣ ከመንግስትና ከፀጥታ ኃይሉ ጋር የጀመሩትን ሰላም የማረጋገጥ ስራ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል። ሰላም የሚገነባው በጋራ ችግሮቻችን ላይ የጋራ መፍትሄ ማስቀመጥ ሲቻል ነው ያሉት ዶክተር እሸቱ በመድረኩም የግጭት መንስኤዎችን ለይቶ በመገምገም ዘላቂ እልባትና መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የሃይማኖት አባቶች የሃይማኖት እሴትን፣ የሃገር ሽማግሌዎች የገጠመንን ፈተና በመቀልበስ፣ ሴቶች ጥበብን፣ ወጣቶች የመሪነት ሚናን በመላበስ የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። ሚኒስቴሩና የክልሉ ፀጥታ ቢሮ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ከክልሉ የጸጥታ ተቋማት፣ ከሴቶችና ከወጣቶች አደረጃጀቶች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከሃገር ሽማግሌዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
ኮሞሮስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት አላት
Sep 19, 2026 953
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- ኮሞሮስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደር ዩሱፍ ሞንዶሃ አሱማኒ ገለጹ። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን በኢትዮጵያ የኮሞሮስ አምባሳደር እና የአፍሪካ ህብረት ቋሚ መልዕክተኛ ዩሱፍ ሞንዶሃ አሱማኒ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል። ሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን ለመመስረት የሚያስችል ስምምነትን ለመፈራረም የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ ትብብሩን የበለጠ ለማጎልበት እንደሚያስችልም አመልክተዋል። የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር የሁለቱ ሀገራት የቅድሚያ ትኩረት እንደሆነም ነው ያነሱት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ መስፋት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ትብብር መጠናከር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል። አየር መንገዱ ወደ ኮሞሮስ መብረር የጀመረበትን የ10ኛ ዓመትን በጋር ለማክበርም ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል። በሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እየተሰጠ ያለው የረጅም ጊዜ ስልጠና የኮሞሮስን ብሔራዊ አቅም በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት። የኮሞሮስ የንግድ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ አቻ ተቋማት ጋር ያላቸውን የንግድ ትስስር በየሀገራቱ የንግድ ምክር ቤቶች በኩል ይበልጥ ለማጠናከር የሚችሉባቸው እድሎች እንዳሉም ነው አምባሳደሩ ያነሱት። የፀጥታ ትብብሩን ለማጠናከር የኮሞሮስ ፖሊስ ተቋም ከፍተኛ አመራሮችን ያቀፈ ልዑክ ኢትዮጵያን መጎብኘቱን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ ልዑኩ በተደራጀ ወንጀል እና በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር መከላከል ዙሪያ የኢትዮጵያን ልምድ መቅሰሙን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የኢነርጂ ልማት ለአፍሪካ ልማት እና ለቀጣናው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽነት ወሳኝ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አመልክተዋል። የኢትዮጵያን ሀገራዊ የምክክር ሂደት ያደነቁት አምባሳደሩ ሰላምና መረጋጋት ለአፍሪካ ልማት ጉልህ አበርክቶ እንዳለውም ገልጸዋል። ኮሞሮስ የምታስተናግደውን የህንድ ውቅያኖስ ደሴቶች ጨዋታዎችን ጨምሮ በቱሪዝም፣ በአገልግሎት ዘርፍ እና በስፖርት ሁነቶች ዝግጅት ከኢትዮጵያ ልምድ የመቅሰም ፍላጎት እንዳላት ነው የገለጹት። በአጠቃላይ ኮሞሮስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት እንዳላት አምባሳደሩ ተናግረዋል። ኮሞሮስ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ከከፈተችበት ከእ.ኤ.አ 2011 አንስቶ እያደገ የመጣው ግንኙነት አሁን ላይ ትብብሩን በተለያዩ ዘርፎች ይበልጥ ለማጠናከር ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ በሚኖራት ሚና ላይ ያለው ዓለም አቀፍ መግባባት እያደገ መጥቷል
Sep 18, 2026 1290
አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ባላት ሚና ዓለም አቀፋዊ መግባባት እየተፈጠረበትና አጀንዳው ተቀባይነቱ እያደገ መምጣቱን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተመራማሪ ግዛቸው አስራት (ዶ/ር) ገለጹ። የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ፍላጎት ለቀይ ባህር ቀጣና ትልቅ እድል መሆኑንም ከፍተኛ ተመራማሪው ለኢዜአ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ፍትሃዊ እና ተቀባይነት ያለው ስትራቴጂካዊ መብት መሆኑንም ገልጸዋል ። የሀገሪቱ የህዝብ ቁጥር ማደግ፣ የኢኮኖሚው እየሰፋ መሄድ፣ የንግድ ልውውጥ ማደግ እንዲሁም ሀገራዊ እና ቀጣናዊ የጸጥታ ዋስትናን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆን ለዚህ ጥያቄ ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሆኑ ነው ያብራሩት። ሀገሪቱ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ጂኦግራፊያዊ ቅርበት እና ከቀጣናው ወደቦች ጋር የነበራት ታሪካዊ ትስስር ዘላቂ የባህር መውጫ ለማግኘት ለምታነሳቸው ጥያቄዎች ጠንካራ መሰረት እንደሆነም አንስተዋል። የኢትዮጵያ በባህሩ አቅራቢያ መገኘት እና በኢኮኖሚውም ሆነ በጸጥታው መስክ ትልቅ ሚና መጫወት እንዳለባት የጋራ ግንዛቤ እንዳለም ነው የገለጹት ከፍተኛ ተመራማሪው። ለዚህ ስኬትም ጎረቤት ሀገራት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጋራ መተማመንና በትብብር መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል። የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ እውነተኛ ዓላማ በግልጽ መረዳት እንደሚገባ ተመራማሪው አንስተዋል። የጂኦ-ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ከየብስ እስከ ባህር የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ቀጣናዊ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም የየብስና የባህር ደህንነትን ነጣጥሎ ከማየት ይልቅ፣ በጋራ ስጋቶችና ጥቅሞች ላይ ያተኮረ ትብብር መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ወደ ባህር በር መመለስ ለቀጣናው ሰላም፣ ለቀጣናዊ ትስስር እና ለምስራቅ አፍሪካ የጋራ ደህንነት ወሳኝ መሆኑን አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያን በቀይ ባህር መድረክ ላይ መሳተፍ ለቀጣናው ትልቅ እድል ነው ሲሉም አክለዋል። ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እና የፀጥታ ስርዓት ጋር ያላት ቁርኝት ጥልቅ በመሆኑ፣ በቀይ ባህር እና የባህር መስመሮችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በባለቤትነት መሳተፍ እንዳለባት አሳስበዋል። ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት፣ በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ እና ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ በምስራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባህር የባህር ፀጥታን ለማስጠበቅ የግድ ሊሟላ የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ከፍተኛ ተመራማሪው አስገንዝበዋል።
የሕወሃት ቡድን ለትግራይ ህዝብ ከጥፋት ውጪ ሊሰጠው የሚችለው አንዳች ነገር የለውም -አቶ ጌታቸው ረዳ
Sep 18, 2026 1220
አዲስ አበባ ፤መስከረም 8/2019 (ኢዜአ)፦የህወሃት ቡድን ከጥፋትና ከመከራ ውጪ ለትግራይ ሕዝብ ሊሰጠው የሚችለው አንዳችም አዲስ ነገር እንደሌለው የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ገለጹ። የትግራይ ሕዝብና ወጣቶች የሕወሃትን አጥፊ ቡድን በመታገል ክልሉን ወደ ሰላምና ልማት መመለስ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል። የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ህወሃት ባለፉት ዓመታት የትግራይን ህዝብ ማለቂያ የሌለው መከራ እና የጥፋት አዙሪት ውስጥ ከመክተት ውጪ የፈየደለት ነገር እንደሌለ ነው የተናገሩት። የቡድኑ አጥፊ አካሄድ የትግራይ ሕዝብ ከልቡ ከሚሻው እውነተኛ የሰላም እና የመረጋጋት ፍላጎት ጋር ፍጹም የተቃረነ መሆኑን አመልክተዋል። የሀገርና የዓለም ሁኔታ በተለወጠበት በአሁኑ ወቅት የህዋሃት መሪዎች በአሮጌ እና በጠባብ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተዘፍቀው እንደሚገኙ አመልክተዋል። ባለፉት ዓመታት በክልሉ የደረሰው ጥፋት ከህወሃት ቡድን የተሳሳተ ውሳኔ የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል። አመራሮቹ ሁልጊዜ ራሳቸውን ትክክለኛ አድርጎ የማሰብ አባዜ፣ የህዝቡን እውነተኛ ስቃይ እንዳይረዱት አድርጓቸዋል ነው ያሉት። በአሮጌ የትጥቅ ትግል ስልት የታወሩ እና ዕድሜያቸው የገፋ ጥቂት የቡድኑ አመራሮች የትግራይን ህዝብ ዕጣ ፈንታ በብቸኝነት ለመቆጣጠር መነሳታቸው ፍጹም ስህተት ነው ብለዋል። ዛሬ ላይ ያለው ትውልድ አዲስ አስተሳሰብ እና እውነተኛ የሰላም ፍላጎት እንዳለው ገልጸው ይሁንና የቡድኑ አመራሮች ጊዜው ባለፈበት እሳቤ ህዝቡን ወደ ሌላ የትርምስ አዙሪት ውስጥ ለመክተት እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል። የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የተፈረመው ጦርነትን ለማስቆም እና ሕዝቡን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ እንደነበር አስታውሰው፤ ይሁን እንጂ የህወሓት አመራሮች ስምምነቱን የራሳቸውን ስልጣን ለማስቀጠል ሲሉ ሂደቱን ሆን ብለው ማደናቀፋቸውን ተናግረዋል። ከቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ጭምር ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ በመከልከል ለፖለቲካ ንግድ መጠቀሚያ ማድረጋቸውን አመልክተዋል። ሰላም የማይፈልጉት የህወሃት ቡድን አመራሮች ሕዝቡን በችግር ላይ ጥለው፣ ከቀውሱ ትርፍ ለማግኘት በሕገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድና የወርቅ ዝውውር ላይ ተሰማርተዋል ሲሉ ገልጸዋል። የትግራይ ወጣቶች በቡድኑ በሚደርስባቸው ግፍና ጭቆና ተማረው ክልሉን ጥለው እየተሰደዱ ስለመሆኑም ነው የገለጹት። አሁን ላይ ደግሞ የቡድኑ አመራሮች የትግራይን ህዝብ ደህንነትና ጥቅም ወደ ጎን በመተው ከትግራይ ህዝብ ጠላቶች ጋር አዲስ የፖለቲካ ጥምረት መፍጠራቸው እጅግ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል። የሕወሃት አመራሮች ውድቀትን እንደ ብቃትና ድል አድርገው የማየት አባዜ የተጠናወታቸው ጸረ ህዝብ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፤ ቡድኑ አጥፊ ስህተቶቹን አምኖ ከመቀበል ይልቅ ራሱን ትክክለኛ በማስመሰል ህዝቡን በማሳሳት ዘመቻ አሁንም መቀጠሉን ገልጸዋል። የህወሓት ቡድን ለትግራይ ሕዝብ ከጥፋት፣ከስደት፣ ከስቃይ እና ከመከራ ውጪ ሊሰጠው የሚችለው አንዳችም አዲስ ነገር የለም ብለዋል። እውነተኛ ሰላም ሊመጣ የሚችለው ይህንን አጥፊ ቡድን በቁርጠኝነት በመታገል ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል። ከዚህ አኳያ የትግራይ ሕዝብና ወጣቶች የጥቂቶች መጠቀሚያ የሆነውን ይህንን አጥፊ ቡድን በመታገል ክልሉን ወደ ሰላምና ልማት መመለስ እንዳለባቸውም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደባባይ በዓላትን ያለምንም ችግር ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል-ፖሊስ
Sep 18, 2026 1072
ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደባባይ በዓላትን ያለምንም ችግር ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። በኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀልና የትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ኮማንደር ደግፌ ደበላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቀጣይ ቀናት የሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ያለምንም ችግር እንዲከበሩ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በክልሉ በቀጣይ ቀናት በወላይታ ጊፋታ፣ በጋሞ ዮ ማስቃላ፣ በጎፋ ጋዜ ማስቃላ እና በሌሎችም አካባቢዎች የአደባባይ በዓላት እንደሚከበሩም ገልጸዋል። በክልሉ በአደባባይ ለሚከበሩ በዓላት ሰላማዊ ክንውን ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የተሟላ እና የተቀናጀ ስምሪት ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። የትራፊክ እንቅስቃሴን ከማሳለጥ ጀምሮ በዓላቱ በሚከበሩባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ቁጥጥርና ጥበቃ ሥራዎች በተጠናከረ ሁኔታ ማከናወን በሚያስችል መልኩ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል። በግብይት ወቅት ሕብረተሰቡ ከሐሰተኛ ገንዘብ ስርጭት እና ባዕድ ነገሮችን ቀላቅለው ከሚሸጡ ህገወጦች ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል። አሽከርካሪዎችም የትራፊክ አደጋን በመከላከል የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው በአፅንኦት ተናግረዋል። ሕብረተሰቡ ከመደበኛ እንቅስቃሴ የተለየ ነገር ሲመለከት እና የወንጀል ሥጋቶች ሲኖሩ በአቅራቢያ ለሚገኝ ፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ሊተባበር እንደሚገባም አመልክተዋል።

ማህበራዊ
የከምባታ ዘመን መለወጫ በዓል "መሳላ" በአብሮነትና በትብብር የመሥራት እሴት ጎልቶ የሚታይበት በዓል ነው- አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ
Sep 22, 2026 28
ዱራሜ ፤ መስከረም 12/2019(ኢዜአ) ፦የከምባታ ዘመን መለወጫ በዓል "መሳላ" በአብሮነትና በትብብር የመሥራት እሴት ጎልቶ የሚታይበት በዓል መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ገለፁ። የከምባታ ዘመን መለወጫ "መሳላ" በዓል በዱራሜ ሁለገብ ስታዲየም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። ዋና አፈ ጉባኤዋ በወቅቱ እንዳሉት፤ የከምባታ ዘመን መለወጫ በዓል "መሳላ" በአብሮነትና በትብብር የመሥራት እሴት ጎልቶ የሚታይበት በዓል ነው። "መሳላ" የመደጋገፍና የአንድነት እሴቶችን ከማጠናከር ባለፈ ለክልሉ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማዋል እንደሚገባ አመልክተዋል። በዓሉ ወደ አዲስ ዘመን የመሻገር ምልክት ከመሆኑም በተጨማሪ ባህላዊ ክዋኔዎቹ፣ የመደጋገፍና የአብሮነት እሴት ጎልቶ የሚታይበት ነው ብለዋል። እንዲሁም የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተራራቁ የሚቀራረቡበት በመሆኑ እሴቱን አስጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አስገንዘበዋል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው፤ የ"መሳላ" በዓል ከክረምት ወቅት ወደ ሌላ የመሻገር ምልክት ብቻ ሳይሆን የመተሳሰብና የመደጋገፍ እሴት የሚጎለብትበት መሆኑን ተናግረዋል። በዓሉ ጥላቻና ቂምን በማስወገድ ሰላምን በማፅናት፣ በአብሮነትና በመረዳዳት የሚከበር መሆኑንም አክለዋል። የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ፤ "መሳላ" የአዲስ እሳቤ ማስጀመሪያ በመሆኑ በተለየ መንገድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው ብለዋል። የበዓሉን እሴቶች በማጎልበት ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በበዓሉ አከባበር ላይ የክልሉ፣ የዞንና የዱራሜ ከተማ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የባህል ሽማግሌዎችና ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተጋባዥ እንግዶች ታዳሚ ሆነዋል።
በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች ተዘርግተዋል - ጤና ሚኒስቴር
Sep 22, 2026 41
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች በጤና ተቋማት መዘርጋታቸውን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ። የጤና ሚኒስቴር ሀገር አቀፍ የሁለተኛው ብሔራዊ ከወሊድ በኃላ የሚከሰት የደም መፍሰስ እና የእናቶች ጤና ፖሊሲ ሰነድ ላይ ያተኮረ ምክክር "ከቃል ኪዳን ወደ ተግባር" በሚል መሪ ሃሳብ እያካሄደ ይገኛል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በመደመር እሳቤ በሁሉም መስክ በከፍተኛ የብልፅግና ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል። በጤናው ዘርፍም በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተው፤ይህም በሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የተገኘ ነው ብለዋል። በሚኒስቴሩ እና በሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ በተሰራው ስራ የእናቶች ሞት መጠን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ መጠን መቀነስ መቻሉን አንስተዋል። ይህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት የእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ላይ በትኩረት ከሚሰሩ ቀዳሚ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያስቻለ መሆኑን በመግለጽ። በቀጣይ በ2030ዓም ይህን የእናቶች የሞት መጠን መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና ለስኬታማነቱም በሚቀጥሉት 3 እና 4 ዓመታት ከፍተኛ ሥራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ለዚህም ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች በጤና ተቋማት መዘርጋታቸውን ተናግረዋል። መድረኩ የተዘጋጀው የእናቶች እና የሕፃናት ጤናን የበለጠ ለማሻሻል፣ እስካሁን ያሉትን ስኬቶች እንደ ወረት ለመውሰድ፣ ቀሪ ስራዎችን ደግሞ በመገምገም የማሻሻያ ተግባራት ማከናወን የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ሰነዶችን ይፋ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። የፖሊሲ ሰነዶቹ የጤና ባለሙያዎች የበረታ የደም መፍሰስን በጊዜ ለይተው ወደሚቀጥለው ተቋም ሪፈር ማድረግና አስፈላጊው ግብዓት እንዲሟላ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል። በተጨማሪም እናቶች ሙሉ በሙሉ በጤና ተቋማት መቆየት እንዲችሉ የምክር አገልግሎት የሚሰጡበት መሆኑን ጠቁመው ለፖሊሲው ተግባራዊነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
"ማሽቃሮ" የአብሮነት መገለጫ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
Sep 22, 2026 145
ቦንጋ፣ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ የካፋ ዘመን መለወጫ "ማሽቃሮ" በአል አብሮነት የሚጠናከርበትና በጋራ የተሻለ ለመስራት የሚታቀድበት መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ። የካፋ ዘመን መለወጫ የ"ማሽቃሮ" በአል በቦንጋ ከተማ በቦንጊ ሸምበቶ የበአሉ መክበሪያ ስፍራ በድምቀት ተከብሯል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት የካፋ ዘመን መለወጫ "ማሽቃሮ" ወንድማማችነት የሚጎለብትበትና አብሮነት የሚጠናከርበት በዓል ነው ። በዓሉ በአብሮነትና በሰላም አዲስ አመትን በመቀበል የተሻለ ለመስራት የሚታቀድበት መሆኑን ተናግረዋል ። የ"ማሽቃሮ" በዓል የአዝመራ መድረስን ተከትሎ በአብሮነትና በፍቅር የሚከበር መሆኑንም አመልክተዋል። ይህም ባህላዊ ዕሴቶች የሚገለጽበት ከመሆኑም በላይ ለኢኮኖሚያዊ እድገት መሰረት የሚሆንበት አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል። ወጣቶች የባህሉን ታሪካዊ ዳራ ጠብቀው እንዲያከብሩና ምሁራንም በጥናታዊ ስራዎች በማገዝና በመሰነድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። የክልሉ መንግስት የባህል ሀብቶችን በማጥናትና በማስተዋወቅ ለትውልድ እንዲሸጋገሩና የቱሪዝም ስበት ማእከል ለማድረግ መሰራቱንም አስታውቀዋል። የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ በበኩላቸዉ፣ የ"ማሽቃሮ" ባህላዊ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል። በዓሉ ከትዉልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገርና በማይዳሰስ ቅርስነት በዩኒስኮ እንዲመዘገብ የተጀመረዉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል። የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻዉ ከበደ እንደገለፁት፣ የ"ማሽቃሮ" የዘመን መለወጫ በይቅርታና በተስፋ ወደ አዲስ አመት የሚሻገሩበት መሆኑን ጠቅሰዋል። በዓሉ በእርሻና አከባቢ ጥበቃ እንዲሁም በሰላምና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት የሚገመገሙበት እንዲሁም የሰራ የሚሸለምበትና ደካማው የሚወቀስበት በመሆኑ የስራ ባህልን የሚያበረታታ ነው ብለዋል ። በበዓሉ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።
የዘንድሮ ኢሬቻ መስከረም 23 እና 24 ይከበራል
Sep 22, 2026 87
ቢሾፍቱ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ የዘንድሮ ኢሬቻ መስከረም 23 እና 24 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚከበር የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት አስታወቀ። በዚሁ መሰረት የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ መስከረም 23 ቀን፣ እንዲሁም የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ መስከረም 24 ቀን እንደሚከበር ተገልጿል። የኢሬቻ በዓል የምስጋና፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የህዝቦች አብሮነት በዓል በመሆኑ፣ ባህሉንና እሴቱን ጠብቆ የሀገርን ገጽታ በሚያጎላ መልኩ መከበር እንዳለበት ተገልጿል። የ2019 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል "ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሐሳብ ይከበራል።
ኢኮኖሚ
በሐረሪ ክልል በኢንዲስትሪ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ናቸው
Sep 22, 2026 30
ሐረር፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ):-በሐረሪ ክልል በኢንዲስትሪ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካላት ገለጹ። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና የኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤልን ጨምሮ የክልሉ አመራር አካላት በሐረሪ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ኢንዱስትሪ ልማት እና ሌሎች ስራዎችን ጎብኝተዋል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና የኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በሀረሪ ክልል በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጪ ምንዛሬን የማስቀረት ስራ በስፋት ስለመከናወኑ መመልከታቸውን ተናግረዋል። በዚህም ኢንዱስትሪው የሚያመርተው የመብራት ምሰሶ ለኮሪደር ልማት ስራ በማዋል ከተማዋን ውብና ማራኪ ማድረጉን በምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል። በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች በአንድ ቦታ የተለያዩ አገልግሎት በማግኘት ወጪና ጊዜን ባግባቡ እንዲጠቀሙ እያደረገ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል። በአካባቢው የሚገኙ ሃብትንና ጥበብን በመጠቀም የሚገነቡት የገጠር ሞዴል መንደሮችም የሚበረታቱ መሆኑንም አንስተዋል። እንደ አቶ ስንታየሁ ገለጻ በክልሉ በኢንዲስትሪ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ናቸው። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ናትናኤል ሚሊዮን በበኩላቸው በክልሉ ጥንታዊ እና ታሪካዊ እሴቶችን በያዘ መልኩ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች ሳቢና ማራኪ ናቸው ። በመሰረተ ልማት ግንበታ፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት አሰጣጥ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚከናወኑ ተግባራት ዓርዓያነት ያላቸውና ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገቡ ናቸው ብለዋል። በጉብኝቱ ላይ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር እና ሌሎች የክልሎቹ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በኢሉባቦር ዞን ከቡና ምርት የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቡና ጥራት አጠባበቅ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል
Sep 22, 2026 54
መቱ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ):- በኢሉባቦር ዞን ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢና የአካባቢውን አምራቾች ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ በቡና ጥራት አጠባበቅና አያያዝ ላይ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ገለጹ። በኢሉባቦር ዞን የ2019 ዓ.ም የቡና ምርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በመቱ ከተማ ተካሄዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ እንዳስታወቁት፤ ባለፉት ዓመታት በዞኑ የቡና ምርት ጥራትን ለማረጋገጥ በየደረጃው ሰፋፊ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። በእነዚህ የተቀናጁ ስራዎችም አመርቂና ጥሩ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በዘርፉ የተመዘገቡ አመርቂ ውጤቶችን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማሳደግ የሚያስችሉ ጥረቶች አሁንም በላቀ ትጋት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል። ዋና አስተዳዳሪው አክለው እንደገለጹት፤ የምርት ጥራትን ከመጠበቅ ጎን ለጎን ሕገወጥ የቡና ዝውውርን መከላከል እና ምርቱን በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ የዞኑ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ነው። በመሆኑም ከቡና አምራቾች እስከ ላኪዎች እና አመራር አካላት ድረስ ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለእነዚህ ነጥቦች ትኩረት በመስጠት የተቀናጀ ቁጥጥርና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተጨማሪም የቀይ ቡና መፈልፈያ ፋብሪካዎች ቀድመው አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ፋብሪካዎቹ በቴክኒክና በአሰራር ረገድ ቀድመው በመዘጋጀት ከዞኑ ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን የቡና ምርት ጥራትና መጠን ለማሳደግ የሚጠበቅባቸውን ሚና በብቃትና በኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አቶ እንዳልካቸው ጠቁመዋል። የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳሙ ታከለ በበኩላቸው በ2019 የምርት ዘመን ከዞኑ 62 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እቅድ መኖሩን ገልጸው፤ ለዚህ እቅድ ስኬታማነት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል። በምክክር መድረኩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ በ2019 ዓ.ም የምርት ዘመን የቡና ጥራትን አስተማማኝ በሆነ ደረጃ ለማስጠበቅ የገበያ ሰንሰለቱን ማስተካከልና የምርት አያያዝን ማዘመን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። በቡና ንግድ የተሰማሩት አቶ በፈቃዱ ገምቴሳ የቡና ምርት ጥራትን የማረጋገጥ ጉዳይ የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን የሁሉንም አካላት ከፍተኛ ተሳትፎና ትኩረት የሚጠይቅ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የክትትል ሰንሰለቱ ጥብቅ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ተሳታፊው፤ ለቡና ምርት አያያዝም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። የቡና ጥራትን የማስጠበቅ ስራ በሁሉም ደረጃዎች ተመሳሳይ ትኩረት ካላገኘ በተወሰኑ ሂደቶች ብቻ ሊረጋገጥ እንደማይችል ያነሱት ደግሞ አቶ ስባቱ በቀለ ናቸው። አያይዘውም የቡና ጥራት ከምርቱ የሚጠበቀውን ተጠቃሚነት የሚወስን ዋና ምክንያት በመሆኑ፣ ባለድርሻ አካላት በየደረጃው በሚከናወኑ የጥራት ማስጠበቅ ተግባራት ላይ በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ገቢን አሟጦ የመሰብሰብ አቅምን ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ ነው
Sep 22, 2026 76
ባህር ዳር፤ መስከረም 12/2019(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋት የገቢ አሰባሰብ አቅምን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ። በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ወራት ከ18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ። የቢሮው የግብር ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዘባቸው ጣሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የገቢ አሰባሰብ አቅምን ከፍ በማድረግ በራስ አቅም የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በተለይም ክልሉ የሚያመነጨውን ኢኮኖሚ የሚመጥን ገቢ ያለምንም ማንጠባጠብ ለመሰብሰብ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት የመዘርጋት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ166 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል። ቀሪውን ዕቅድ ለማሳካትም አዳዲስ ግብር ከፋዮችን ወደ ግብር መረብ ከማስገባት ባሻገር ገቢ የመሰብሰብ አቅምን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በክልሉ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን በማሳደግ በራስ አቅም የሕዝብን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የመመለስና የመሥራት ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም አብራርተዋል። ህብረተሰቡ ለገዛው ዕቃና ላገኘው አገልግሎት ደረሰኝ የመቀበልና የመጠየቅ ልማድን በማዳበር የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። ቢሮው በቀጣይም የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ይበልጥ ዘመናዊ፣ ፍትሐዊና ቀልጣፋ በማድረግ ክልሉ የሚያመነጨውን ኢኮኖሚ የሚመጥን ገቢ ለመሰብሰብ ጠንክሮ እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል። በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት በተከናወነ የገቢ አሰባሰብ ሂደት ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሎ እንደነበርም ከዳይሬክተሩ ገለጻ ለማወቅ ተችሏል።
የግብጽ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቦታ የሌለው ኋላቀር አካሄድ ነው
Sep 22, 2026 176
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ የግብጽ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እና የውሃ የበላይነት ህልም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈጽሞ ቦታ የሌለውና ኋላቀር አካሄድ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። ኢትዮጵያ ዓባይን ጨምሮ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶቿን የማልማት እና የቀጣዩን ትውልድ ፍላጎት የማሟላት ሉዓላዊ መብቷን በአግባቡ እንደምትጠቀምም ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል። ኢትዮጵያ ዓባይን ጨምሮ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶቿን የማልማት ሉዓላዊ መብቷ የተጠበቀ መሆኑንም አመልክቷል። በቅርቡ የግብፅ የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ኢትዮጵያውያንን በመዝለፍ የሰጡት አስተያየት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ግብጽ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት የምትከተለውን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በግልጽ ያሳየ መሆኑን አመልክቷል። ግብጽ ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሀብታቸውን የሚጠቀሙት እሷን ጠይቀውና ፈቃድ አግኝተው ብቻ ነው ብላ ማመኗ ሁልጊዜም የበላይ ልሁን ከሚለው ኋላ ቀር እሳቤዋ የሚመነጭ መሆኑን ገልጿል። ይህ የግብጽ አቋም ከእውነት የራቀ እና ፍጹም አስመሳይነት የተሞላበት መሆኑን ሚኒስቴሩ ጠቁሟል። ግብፅ ከዚህ ቀደም የትኛውንም የተፋሰሱ ሀገራት ፈቃድ ሳትጠይቅ የአስዋን ታላቁን ግድብ መገንባቷን መግለጫው አውስቷል። የግብፅ ባለሥልጣናት የሚያሰሙት ጥላቻ የሞላበት ንግግር እና የሚከተሉት አሻሚ አካሄድ፤ በተፋሰስ ሀገራት መካከል ሊኖር ከሚገባው የትብብር መንፈስ ጋር ፈጽሞ የሚቃረን መሆኑ ተመላክቷል። ኢትዮጵያ ዓባይን ጨምሮ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶቿን የማልማት እና የቀጣዩን ትውልድ ፍላጎት የማሟላት ሉዓላዊ መብቷ የተጠበቀ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል። ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የአለመግባባትና የንትርክ ምንጭ ሳይሆን ትብብርን፣ የጋራ እድገትንና የቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ መሆን እንዳለባቸው በጽኑ ታምናለች ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው። አንዱ አካል ብቻ ተጠቃሚ የሚሆንበት እና የተፋሰሱ ሀገራትን መብት ነፍጎ የበላይነትን በጉልበት ለመጫን የሚደረግ ጊዜ ያለፈበት አካሄድ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ሲል ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል። አንዳንድ አካላት የዓባይን ወንዝ እንደ ጸጥታና ግጭት አጀንዳ ብቻ ማየትን ሲመርጡ፣ ኢትዮጵያ ግን የተፋሰሱን የረጅም ጊዜ ደህንነትና ዘላቂነት ለማረጋገጥ ሰፊ ተግባራትን ማከናወኗን ገልጿል። ኢትዮጵያ በውሃ ተፋሰስ አካባቢዎች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ማድረጓን፣ ሰፊ የችግኝ ተከላና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማከናወኗን እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በዘላቂነት እየሰራች እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። የኢትዮጵያ አዎንታዊ እርምጃ ከግብጽ ጠላትነት ከሞላበት የተሳሳተ ትርክት አንጻር ሲታይ ፍጹም የተለየ እና የሰለጠነ አካሄድ መሆኑን አመልክቷል። በመሆኑም ግብጽ ጊዜው ካለፈበት ፖሊሲ ወጥታ፣ ጉዳዩን በጋራ መከባበርና የሁሉንም ወገኖች የረጅም ጊዜ ጥቅም በሚያከብር የ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ልትመለከተው ይገባል ብሏል። ግብጽ አሮጌና ጊዜ ያለፈባቸውን የበላይነት ህልሞች በመተው፣ አዲሱን የትብብር እውነታ መቀበል የሚገባበት ጊዜ አሁን መሆኑን ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
ሳይንስና ቴክኖሎጂ
ዩኒቨርሲቲው የሚያካሄደው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው
Sep 21, 2026 261
ሮቤ፤ መስከረም 11/2019 (ኢዜአ)፦ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የሚያካሄዳቸው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው የጭብጥ ተኮር የምርምርና ማህበረሰብ ልማት ንድፈ ሀሳቦችን የሚገመግም የአቅም ግንባታ ዐውደ ጥናት እያካሄደ ነው። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ለማህበረሰቡ ችግሮች መፍትሔ የሚያመላክቱ ምርምሮችን እያካሄደ ይገኛል። በተለይም የዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል የሆኑት የግብርና፣ ጤና፣ ቱሪዝም፣ ብዝሃ-ሕይወትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዘርፎች ዋና ዋና የምርምር ትኩረት መስኮች መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው ምሁራንም ባለፉት ዓመታት ባካሄዷቸው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች የበርካታ ዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እመርታዊ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል። በተለይም በግብርናው የኩታ-ገጠም አሰራር፣ በካንሰር ህክምናና ህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸው የምርምርና ማህበረሰብ ልማት አገልግሎቶች የህዝብን ችግሮች በተሻለ ሁኔታ ለመፍታት እንዲችሉ በዘርፉ ለተሰማሩ ተመራማሪዎችና ገምጋሚዎች የሚሰጠው ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠናም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንቱ አውስተዋል። የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት በዛብህ ወንድሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአቅም ግንባታ ዐውደ ጥናቱ በምርምር ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመለየት የተሻለ ተፅዕኖና ውጤት የሚያመጣ ምርምር ለማከናወን እንደሚረዳ ገልጸዋል። በተለይም ተመራማሪዎቹ በስልጠናው ቆይታቸው በጭብጥ ተኮር የምርምር ንድፎች ምንነትና አዘገጃጀት፣ በማህበረሰብ ተኮር ልማት ስራዎች ንድፈ-ሀሳብ አዘገጃጀትና በዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ በቂ ግንዛቤ እንደሚያገኙ ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በ2018 የበጀት ዓመት በተለያዩ የትኩረት መስኮች ላይ ያተኮሩ ከ24 በላይ ምርምሮችን ማካሄዳቸውን በማስታወስ፤ በአዲሱ የበጀት ዓመት ደግሞ 96 የምርምር ንድፈ-ሀሳቦች ለግምገማ መቅረባቸውን አመልክተዋል። ዩኒቨርሲቲው የሚያካሄዳቸው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች የአካባቢውን ህብረተሰብ ችግሮች በመቅረፍ ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።
በክልሉ ተቋማት ላይ ተግባራዊ የተደረገው የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የተገልጋይን እርካታ እያረጋገጠ ነው
Sep 19, 2026 374
ባህር ዳር፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- በአማራ ክልል ተቋማት ላይ ተግባራዊ የተደረገው የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የተገልጋይን እርካታ እያረጋገጠ መሆኑ ተገለፀ። በክልሉ በመጀመሪያው ዙር ወደ መንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የገቡ ስምንት ተቋማት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሄዷል። በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ሪፎርም አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሪፎርሙ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር የተገልጋይን እርካታ እያረጋገጠ መምጣቱን ገልጸዋል። ይህም የመንግሥትን ተቋማት ነፃና ገለልተኛ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር የሠራተኛውን ችሎታና ብቃት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል። በተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ የዲጂታል አሠራርን እውን በማድረግ ፈጠራና ፍጥነት የታከለበት አገልግሎትን በፍትሐዊነት ተደራሽ መሆኑ ውጤት እያስገኘ ነው ያሉት። በተለይም የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ማስቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም በስድስት ማዕከላት በተሰጠ አገልግሎት የተገልጋይ እርካታን 99 ነጥብ 7 በመቶ ማድረስ እንደተቻለም ገልጸዋል። የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ባንችአምላክ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ ሪፎርሙ የመንግሥትን አገልግሎትና አስተዳደር በውጤታማነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል። በተለይም ከዚህ ቀደም በተቋማት ይስተዋሉ የነበሩ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ወጪ ቆጣቢ በሆነ አግባብ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን ማስቻሉን ጠቁመዋል። ሪፎርሙ አሠራሮችን ዲጂታል በማድረግ ሥራን የማቅለልና የማዘመን ብሎም ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል መገንባትን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። እስካሁን በተደረገ ጥረት ተቋማትን ለአሠራር ምቹ ከማድረግ ባለፈ የሕግ ማዕቀፎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል። በክልል ደረጃ 69 ተቋማት 361 አገልግሎቶቻቸውን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ከ183 ሺህ 300 በላይ ደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። በሪፎርሙ የግዥ፣ የንብረት አስተዳደርና የክፍያ ሥርዓትን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ የገቢ ሥርዓቱን ከማኑዋል ወደ ዲጂታል በማሳደግ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከፍ እንዲል ማድረጉን አብራርተዋል። ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ ፕላንና ልማት እና ሥራና ክህሎት ቢሮዎች ሪፎርሙን በመተግበር የተሻለ ሥራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል። የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከርም በየደረጃው የተሻለ ግንዛቤ ተፈጥሮ ወደ ተሟላ አፈጻጸም ለመግባት በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል። በመድረኩ በሪፎርሙ ወደ ተግባር የገቡ ተቋማት አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን የየተቋማቱ የሪፎርም አፈጻጸም ግምገማ ተካሄዷል።
መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት መንግስት ለህዝብ የሰጠው ፈጣንና ቁርጠኛ ምላሽ
Sep 18, 2026 327
አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ):- መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት መንግስት ለህዝብ የሰጠውን ፈጣን እና ቁርጠኛ ምላሽ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ። መንግስት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ባደረገው ጥረት ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ተቋማትን በመገንባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ለዚህም ማሳያ የሆነው የመሶብ አገልግሎት እጅግ ፈጣን እና ቀልጣፋ በመሆኑ በዜጎች ዘንድ ትልቅ እርካታን ፈጥሯል። በተለይም የተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት ነዋሪዎች ወደ መንግስት ተቋማት መሄድ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት አካባቢ ሆነው ጉዳያቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈጽሙ ምቹ ሁኔታን መፍጠር የቻለ ነው። የተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት በአካባቢያቸው ሲያገኙ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎችም መንግስት ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በፍጥነት መቅረፉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል። ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ታምሩ አሰፋ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረው የመንግሥት አገልግሎት ረጅም ጊዜ የሚወስድና ለእንግልት የሚዳርግ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ አሠራሩ እጅግ ዘመናዊ በመሆኑ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል። በተለይ የተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት በመኖሪያ አካባቢዎቻቸው የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት መቻሉ የበለጠ እርካታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ታምራት ከበደ በበኩላቸው፤ የተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት አሰጣጡ ከአቀባበል ጀምሮ ያለው መስተንግዶ ቀደም ሲል ከነበረው አሠራር ፈጣን እና ቀልጣፋ መሆኑን ጠቁመው፣ በተሰጣቸው አገልግሎት እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል። በተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ መገልገላቸውን የተናገሩት አቶ ዋበላ ሐጂከድር፤ አገልግሎቱን ባጠረ ጊዜ እና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። መንግሥት ለህዝብ ፈጣን አገልግሎት በመስጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎት ተንቀሳቃሽ አገልግሎት የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ካውንተር ባለሙያ ደርቤ ፋንታሁን፤ ቀደም ሲል ተገልጋዮች አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋሙ በአካል ለመሄድ ይገደዱ እንደነበር ያስታውሳሉ። አሁን በተዘረጋው ተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎት በሰለጠኑ ባለሙያዎች በመታገዝ በርካታ ተቋማትን ባቀናጀ መልኩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። በኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎት ተንቀሳቃሽ አገልግሎት የሁሉ አገልግሎት ባለሙያ ሃና ተፈራ፤ እስካሁን ድረስ ወደ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በመንቀሳቀስ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የተገልጋዮችን እርካታ እያረጋገጥን እንገኛለን ብለዋል። የኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ ዓለማየሁ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል ተበታትነው የነበሩ የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ በአንድ ማዕከል ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው የመሶብ አገልግሎት ከፍተኛ ሀገራዊ ውጤት እያስመዘገበ ነው። ይህም በመሶብ ማዕከላት በአካል በመሄድ መገልገል ለማይችሉ ዜጎች መኖሪያ አካባቢያቸው ድረስ ሄዶ ማገልገል የሚቻልበት ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል። ይህ አሠራር በአካል መገኘት ለማይችሉ ዜጎች ትልቅ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ በቀጣይም አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ አቶ ዮናስ ዓለማየሁ አረጋግጠዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ተማሪዎች በፈጠራ ስራዎች ላይ በስፋት እንዲሳተፉ እያገዘ ነው
Sep 18, 2026 872
ጅማ ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ):-የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ተማሪዎች በዘርፉ ያላቸውን እውቀትና ግንዛቤ በማሳደግ በምርምርና በፈጠራ ስራዎች ላይ በስፋት እንዲሳተፉ እያገዘ መሆኑን ገለጸ። በአሁኑ ወቅት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ፣ በጤና፣ በእርሻ እና በትምህርት ዘርፎች ፈጣን ለውጥ እያመጣ የሚገኝ ቁልፍ የፈጠራ መሳሪያ ነው። በኢትዮጵያም ሀገራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እቅድን ለማሳካት እና የኢንዱስትሪ አብዮት ተሳትፎን ለማሳደግ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አቅም ያላቸውን ወጣቶች ማፍራት ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል። የጅማ ዩኒቨርሲቲም ይህንን ዓለም አቀፋዊ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ሀገራዊ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የተማሪዎችን የፈጠራና የምርምር አቅም ለማጎልበት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል አቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ማዕከሉ ተማሪዎች የንድፈ ሐሳብ እውቀትን ከተግባራዊ ልምድ ጋር እንዲያናብቡ፣ በችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ እንዲሰማሩ እና በዲጂታል ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ ነው። በዩኒቨርሲቲው የማዕከሉ ዳይሬክተር ኢንጂነር ጃርሚያ ባይሳ እንዳሉት፤ የዩኒቨርሲቲው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ተማሪዎች በዘርፉ የሚያሳዩትን እውቀትና ግንዛቤ ለማጎልበት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። ማዕከሉ ተማሪዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረቱ የፈጠራ ስራዎችንና ሶፍትዌሮችን እንዲያበለጽጉ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ። እንዲሁም ልዩ ልዩ እውቀትና ግንዛቤ ያላቸው ተማሪዎች በአንድ የስራ ቦታ በመሰባሰብ ልምድ የሚለዋወጡበት እድል ማመቻቸቱን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ተማሪዎች በማዕከሉ የስራ ላይ ልምምድ የሚያደርጉበትን እድል በመፍጠር፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመስራት ተግባራዊ ልምድና እውቀት እንዲገበዩ እያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በዓመት ሁለት ጊዜ ደግሞ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዙሪያ የሃካቶን ውድድር በማዘጋጀት፣ ተማሪዎች በፈጠራ እንዲወዳደሩና የልዩ ልዩ ሽልማቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል እያመቻቸ እንደሚገኝም ገልጸዋል። የማዕከሉ እንቅስቃሴዎችም በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ብቻ የተገደቡ አለመሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ተማሪዎችና መምህራን በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ ተጨባጭ የማህበረሰብ ችግሮችን የሚፈቱ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ላይ በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከተከናወኑ የፈጠራ ስራዎች መካከል በቡና ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን ቀድሞ ለመለየት፣ መፍትሄ ለመስጠት እና የቡና ደረጃን ለመወሰን የሚያገለግለው "ደቦ ቡና አፕ" ፈጠራን ለአብነት አንስተዋል። እንዲሁም ባህላዊ ጨዋታዎችን በሮቦቲክስ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት በማቀናጀት የሚያቀርብ ፕሮጀክት፣ የአፈርን ይዘት በመለየት ተስማሚ የምርት አይነት የሚያመላክተው "ኦሚሽቱ ጆይ አፕ" እና የእንስሳትን ጤና እና በሽታ ለመከታተል የተሰሩ ፈጠራዎች እንደሚገኙበትም አመልክተዋል። በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ እነዚህና ሌሎች ፕሮጀክቶች በተማሪዎችና መምህራን ንቁ ተሳትፎ የሚከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ስራዎቹ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሽልማቶችና እውቅናዎችን ማጎናጸፋቸውን ጠቁመዋል። ማዕከሉ በቀጣይም ተማሪዎች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች በዘርፉ የታገዙ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን እንዲያከናውኑና በርካታ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረቱ ጀማሪ ድርጅቶች (ስታርት አፕስ) እንዲቋቋሙ በትኩረት እንደሚሰራ ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የተመረቀችውና በተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ላይ ስትሳተፍ የቆየችው ወጣት ኢክራም አልቃድር፣ በማዕከሉ የነበራት ቆይታ ከፍተኛ እውቀትና ልምድ እንድታካብት እንደረዳት ገልጻለች። በአሁኑ ወቅትም በግል ተቋም ውስጥ በዘርፉ ተሰማርታ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች። ሌላኛው ወጣት አደም ሰይድ በማዕከሉ ያገኘውን እውቀትና ልምድ በመጠቀም 'ክሬቲቭ ሀብ' በተሰኘ ተቋም ውስጥ በመስራት ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በሶፍትዌር ማበልፀግ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ የገለጸው ወጣቱ፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ለስኬቱ ትልቅ መሰረታዊ እውቀት እንዳበረከተለት ጠቅሷል።
ስፖርት
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን አቀባበል ተደረገለት
Sep 22, 2026 88
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ በዴንማርክ ኮፐንሃገን በተካሄደው ሁለተኛው የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ሩጫ ሻምፒዮና ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል። ልዑኩ ቡድኑ አዲስ አበባ ሲደርስ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን እና የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኮሙኒኬሽን ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም ምሩፅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በኮፐንሃገን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ በማድረግ ሀገራችሁን አኩርታችኋል ሲሉ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው አንድ የወርቅ፣ ሁለት የብር እና አንድ የነሐስ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ሻምፒዮናውን አጠናቃለች።
ማንችስተር ዩናይትድ ከፉልሃም ጋር አቻ ተለያየ
Sep 20, 2026 395
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2019 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ማንችስተር ዩናይትድ እና ፉልሃም ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ማምሻውን በክራቫን ኮቴጅ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በ63ኛው ደቂቃ በራሱ መረብ ላይ ያስቆጠረው ግብ ፉልሃምን መሪ አድርጓል። ማትያስ ኩንሃ በ89ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ባሳረፈው ጎል ዩናይትድ አቻ ሆኗል። ከአምስት የሊጉ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፈው ማንችስተር ዩናይትድ በአምስት ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ ያገኘው ፉልሃም በበኩሉ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ዛሬ በተደረጉ ሌሎች መርሐ ግብሮች ማንችስተር ሲቲ ሰንደርላንድን 5 ለ 3 በማሸነፍ የሊጉን መሪነት አጠናክሯል። ሊቨርፑል ቦርንማውዝን 1 ለ 0 ሲረታ ሊድስ ከክሪስታል ፓላስ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። ጨዋታዎቹን ተከትሎ አምስተኛ ሳምንት ተጠናቋል። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ምክንያት የሚቋረጥ ሲሆን መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም በስድስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ይመለሳል።
አትሌቲኮ ማድሪድ ሪያል ማድሪድን አሸነፈ
Sep 20, 2026 348
አዲስ አበባ፤መስከረም 10/2019 (ኢዜአ):- በስፔን ላሊጋ ተጠባቂ በነበረው የማድሪድ ደርቢ ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ ሪያል ማድሪድን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በጨዋታው የአትሌቲኮ ማድሪድን የድል ግቦች አሌክስ ግሪማልዶ እና ጆናታን ዴቪድ ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ለሎስ ብላንኮዎቹ (ሪያል ማድሪድ) ብቸኛዋን ግብ አንቶኒዮ ሩዲገር ማስቆጠር ችሏል። ይህንን ውጤት ተከትሎ ሪያል ማድሪድ በውድድር ዘመኑ ሁለተኛ የላሊጋ ሽንፈቱን አስተናግዷል። በአሁኑ ሰዓት በላሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ አትሌቲኮ ማድሪድ በ16 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ሪያል ማድሪድ በ15 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በሊጉ ያደረጋቸውን ተከታታይ 7 ጨዋታዎች ያሸነፈው የካታላኑ ክለብ ባርሴሎና ላሊጋውን በ21 ነጥቦች ይመራል።
ማንችስተር ሲቲ መሪነቱን ሲያጠናክር፣ ሊቨርፑልም ድል ቀንቶታል
Sep 20, 2026 328
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2019 (ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማንችስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል። ማንችስተር ሲቲ ከሰንደርላንድ ጋር ባደረገው የሊግ ጨዋታ 5 ለ 3 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። የማንችስተር ሲቲን የድል ግቦች ሴሜንዮ (ሁለት ግቦች)፣ ኤርሊንግ ሀላንድ፣ ሪያን ሼርኪ እና ኢንዞ ፈርናንዴዝ ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ለሰንደርላንድ ብሮቤይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል። ይህንን ድል ተከትሎ ማንችስተር ሲቲ በፕሪሚየር ሊጉ አምስተኛ ተከታታይ ድሉን በማስመዝገብ በ15 ነጥብ የሊጉን መሪነት አጠናክሮ መቀጠል ችሏል። በሌላ በኩል ሊቨርፑል ከሜዳው ውጪ ከቦርንማውዝ ጋር ባደረገው ጨዋታ በአሌክሳንደር አይሳክ ብቸኛ ግብ ታግዞ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
አካባቢ ጥበቃ
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር የብዝሃ ሕይወትና ሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን በማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እያስገኘ ነው
Sep 21, 2026 487
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2019 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የብዝሃ ሕይወትና ሥነ-ምኅዳር ደኅንነት በማስጠበቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝኅ ሕይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በ2011 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የጀመረችው ታሪካዊ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ትልቅ አርአያ መሆን ችሏል። በዚህ ግዙፍ ሀገራዊ ተነሳሽነት አማካኝነት ባለፉት 8 ዓመታት ውስጥ 56 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለው የሀገሪቱ ስነ-ምህዳር እና ብዝሃ ህይወት በዘላቂነት እንዲጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ መሰረት ተቀምጧል። ይህ ሁሉን አቀፍ ጥረት ሀገሪቱ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን ጠብቃ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ብሩህ ጉዞ ጠንካራ እና አዲስ መሰረት ጥሏል። የኢትዮጵያ ብዝኅ ሕይወት ኢንስቲትዩት የደንና ግጦሽ መሬት ዕፅዋት ብዝሀ ህይወት ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበራ ስዩም ለኢዜአ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በዓለም ከታወቁት ከፍተኛ የብዝሃ ሕይወት ሀብት ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት። እስካሁን በተደረጉ ጥናቶች ከ6 ሺህ በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች መለያታቸውንና ከ10 እስከ 12 በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ ዝርያዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል። ይህ እምቅ የብዝሀ ህይወት ሀብት መኖር ሀገሪቱ የተለያዩ የምግብ ስርዓቶች እንዲኖራት መደላደል የፈጠረ ከመሆኑም በላይ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል። የብዝሀ ህይወት ሀብቶች ለውሃ ሀብት፣ ለስነ ምህዳር መጠበቅ፣ ለባህላዊና ዘመናዊ ህክምና መድኃኒትነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት በመዋል ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል። በመሆኑም የብዝሀ ሕይወት ሀብቶቻችንን ጠብቆ ማቆየት ለሀገር ህልውና ወሳኝ በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ነው ብለዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተጀመረው አርአያነት ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ብዝሃ ህይወትን በመጠበቅ እና የአየር ንብረት ለውጥን በብቃት በመቋቋም ረገድ ከፍተኛ ሚና በመወጣት ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ስኬታማ መርኃ ግብር በመጀመሩ ምክንያት ቀደም ሲል የተራቆቱ ቦታዎች እንዲያገግሙ የተደረገ ሲሆን፣ በሂደትም የጠፉ ዝርያዎች ተመልሰው መተካት በመጀመራቸው የተጎዳው ስነ-ምህዳር እየተስተካከለ መጥቷል ብለዋል። ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት ተግባራት ኢንስቲትዩቱ 26 ሚሊዮን የሚደርሱ የሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን በማዘጋጀት ማሰራጨቱን ተናግረዋል። በዚህም የሀገሪቱን የምግብ ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ አቅም እየገነባ ይገኛል ነው ያሉት። በቀጣይም ለትውልድ የሚተርፍ አረንጓዴ ሀብት የመገንባት ሥራውን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ውጤታማ የፖሊሲ እርምጃ በአርአያነት የሚወሰድ ነው - የዘርፉ ሙያተኞችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት
Sep 19, 2026 280
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2019 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ውጤታማ የፖሊሲ እርምጃ የአፍሪካና የዓለም ሀገራት በአርአያነት ሊወስዱት የሚገባ መሆኑን የዘርፉ ሙያተኞችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ። የአፍሪካን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር ከኖርዲክ ሀገራት የቴክኖሎጂና የኃይል ልማት ልምድ ጋር የሚያገናኘው የኖርዲክ-አፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል። በጉባኤው የተገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የወሰደችው የፖሊሲ እርምጃ እና እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ ለአፍሪካና ለቀሪው ዓለም በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል። በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን፣ ግንኙነትና መሠረተ ልማት ክፍል ዳይሬክተር ሮበርት ታማ ሊሲንጌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአህጉራችን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መስክ ውጤት እያመጡ ያሉ ሀገራት እንደ ኢትዮጵያ ግልጽ ራዕይ፣ ስትራቴጂና የትግበራ እቅድ ያላቸው ናቸው። ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ልምድ በመውሰድ በበቂ መሠረተ ልማትና የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች አቅም ግንባታ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዘርፍ እያደረገች ያለው ሽግግር ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነትን የሚያሳይና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ የፊንላንድ ኤምባሲ የንግድና ልማት ሃላፊ ቶሚ ሳርኬ፤ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ውጤታማ ሥራ እሰራች ነው ብለዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዘርፍ የታዩት ለውጦች እጅግ ማራኪ መሆናቸውን ገልጸዋል። የተወሰዱት የፖሊሲ እርምጃዎችና የመሪዎችን ቁርጠኝነት ህዝቡ ለራዕዩ መሳካት በጋራ እንዲንቀሳቀስ ትልቅ መነሳሳት መፍጠራቸውንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የምታደርገው ፈጣን ሽግግር የሀገሪቱን ብሩህ የወደፊት አቅጣጫ የሚያመላክት እንደሆነም ተናግረዋል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ በስፋት እየገቡ ነው ያሉት ደግሞ የኖርዲክ-አፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጉባኤ የሀሳብ መሪ ሚከል ቤከር አከርቪክ ናቸው። ይህ ታላቅ ስኬት በአውሮፓና በሌሎች ዓለም ሀገራት በዘርፉ ላይ ለሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ትልቅ የአጋርነት ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል። በአረንጓዴ ትራንስፖርትም በአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ላይ የበለጠ ለመስራት የኢትዮጵያ እንዲሁም የአፍሪካ ጊዜ አሁን በመሆኑ ሁሉም የዚህ አረንጓዴ ሽግግር አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በጋምቤላ ክልል በሚቀጥሉት ወራት መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ይጠበቃል
Sep 18, 2026 333
ጋምቤላ ፤መስከረም 8/ 2018 (ኢዜአ) ፡-በጋምቤላ ክልል በሚቀጥሉት ወራት መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ሊኖር እንደሚችል በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዮት የጋምቤላ ክልል የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል አስታወቀ። በክልሉ የሚኖረው የዝናብ ስርጭት ለእርሻ ስራ አወንታዊ ሚና እንዳለው ሁሉ ቅጽበታዊ ጎርፍ በመፍጠርም አሉታዊ ተጽኖ ሊኖረው እንደሚችል ማዕከሉ ገልጿል። የማዕከሉ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋሁን ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተያዘው መስከረም አጋማሽ ጀምሮ በቀጣዮቹ ወራት መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ሊኖር እንደሚችል የአየር ትንበያ መረጃዎች ያመለክታሉ ። በክልሉ በተለይም በጥቅምትና ህዳር 2019 ዓም መደበኛና ከመደበኛ በላይ ጠንከር ያለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ገልጸዋል። በክልሉ ሊኖር የሚችልው የዝናብ ስርጭት ዘግይተው ለሚዘሩና ለረጅም ጊዜ ሰብሎች አመች ሁኔታ እንደሚኖረው ተናግረዋል። እንዲሁም ለበጋ የግብርና ልማት ስራዎች እርጥበታማ አፈርን በመፍጠርና የውሃ አቅሞችን በማሳደግ ረገድ አዎንታዊ አስተዋፆ እንደሚኖረው ገልጸዋል። በአንፃሩ የክልሉ መልከአ ምድራዊ አቀመማጥ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአጎራባችና በአካባቢው የሚጥለው ጠንክር ያለ ዝናብ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ይችለል ብለዋል። በተለይም ባሮን ጨምሮ ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ አራት ታላላቅ ወንዞች ሞልተው በመፍሰስ ለጎርፍ ሊያጋልጡ ስለሚችሉ በወንዞች አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል። በተጨማሪም የዝናቡ ስርጭት ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥርና የወባ በሽታ ሊጨምር ስለሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዘርፉ ልማት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ ነው- የውጭ ሀገራት ተመራማሪዎች
Sep 18, 2026 292
ሀዋሳ፤ መስከረም 8/2019 (ኢዜአ) :- የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስደናቂና በዘርፉ ልማት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን የተለያዩ ሀገራት የደን ዘርፍ ተመራማሪዎች ገለጹ። ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት በድምሩ 56 ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል በዘርፉ ልማት የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ ቀጥላለች። የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ለምግብ ዋስትናም መሰረት እያኖረ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ሀገራት የዘርፉ ባለሙያዎች፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት አስደናቂ የልማት ስራ መሆኑን ገልጸዋል። ኒዘርላንዳዊው የዘርፉ ተመራማሪ አልበርት ስቼንክ፤ ኢትዮጵያ የዓለም ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ በመካላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን በተግባር እያሳየች መሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስደናቂና በዘርፉ ልማት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድና ሁሉም ሊደግፈው የሚገባ መልካም ተግባር መሆኑን አንስተዋል። የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ጉዳይ የሁሉም ሀገራት የጋራ ሃላፊነት መሆኑን የተናገሩት ተመራማሪው ሀገራት የኢትዮጵያን ፈለግ መከተል ይገባቸዋል ብለዋል። የተፈጥሮ ሀብትና ደንን ለመንከባከብ የሚደረግ ጥረት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በአረንጓዴ ልማት ላይ የሚውል ጉልበትና ገንዘብ መልሶ የሚከፍል ሀብት በመሆኑ ሊተኮርበት እንደሚገባ አሳስበዋል። ሌላኛው ኡጋንዳዊው የደን ሃብት ልማት ተመራማሪ ሮበርት አቱጎንዛ፤ በደን ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ኢትዮጵያ ትልቅ እቅድ ሰንቃ እየሰራችና በተግባርም እያሳየች ትገኛለች ብለዋል። የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የዓለም ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ጥረት፣ የተፈጥሮ ሃብትን የመጠበቅና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ መሰረት ሆኖ መቀጠሉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም የአፍሪካ ሀገራት በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ልምድ በመቀመር በተባበረ አቅም የልማት ስራውን ማስቀጠል ይኖርባቸዋል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል። በታንዛኒያ የደን ጥበቃ ፕሮግራም አስተባባሪና የደንና የተፈጥሮ ሀብት ተመራማሪ አልማስ ካሽንዲዬ፤ በኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ ስራ የህዝብ አጀንዳ ሆኖ የቀጠለ አስደናቂ መርሃ ግብር ነው ሲሉ ተናግረዋል። የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅና መንከባከብ የብዝሃ ህይወትንና የውሃ አካላትን መጠበቅ፤ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከልና የምግብ ዋስትና መሰረት በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ሲሉ አስረድተዋል። የዘርፉ ምሁር የሆኑት ቦሊቪያዊው ሁምቤርቶ ጎሜዝ፤ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከሏቸው ችግኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ትልቅ ትርጉም ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያና ዜጎቿ በአረንጓዴ አሻራ ልማት እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ዜናዎች
የአፍሪካ ህብረት እና ተመድ ያላቸውን የጋራ ውጥኖች በቁርጠኝነት ለመተግበር እንደሚሰሩ ገለጹ
Sep 21, 2026 388
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2019 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰላም፣ ኢኮኖሚና ፍትሃዊ ዓለምን ለማስፈን በጋራ እያከናወኑ የሚገኘውን ስራ ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ። 81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከመስከረም 8 ቀን 2019 ዓ.ም አንስቶ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ይገኛል። “መተማመንን ዳግም መገንባት እና አዳዲስ ለውጦችን በአግባቡ መምራት፣ ለሁሉም የሚሰራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መፍጠር” የጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በጉባኤው ላይ ለመታደም ኒው ዮርክ ይገኛሉ። ከጠቅላላ ጉባኤው ጎን ለጎን ስትራቴጂካዊ ትብብር ማጎልበት፣ የሰላምና ደህንነት ማዕቀፎችን ማጠናከርና አፍሪካን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ሪፎርሞች ላይ ያተኮረ ከፍተኛ የምክክር መድረክ ተካሄዷል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና የተባበበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ መድረኩን በጋራ መርተውታል። ስብስባው ሁለቱ ተቋማት አፍሪካ መዋቅራዊ ፈተናዎችን ለመፍታት እያደረገች ያለቻቸውን ጥረቶች ለመደገፍና ፍትሃዊ የዓለም ስርዓትን ለመፍጠር ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት ይበልጥ ያረጋገጠ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል። የዓለም አቀፍ የፋይናንስ አወቃቀርን ማሻሻል፣ ዘላቂ የእዳ አስተዳደር እና የአፍሪካ ሀገራት ከቁልፍ የማዕድን ሀብቶች ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ ውይይት ከተደረገባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ሁለቱ ወገኖች በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ህብረት እና የተመድን ትብብር ያለውን ስትራቴጂካዊ ፋይዳ አጽንኦት ሰጥተዋል። የተቋማቱ ሶስት ነባር የትብብር ማዕቀፎች በአዲስ መልክ ለማደስ እና እ.አ.አ በ2026 ትግበራው የሚጠናቀቀውን የጋራ ፍኖተ ካርታ የተፈጻሚነት ገደብ ለማራዘም መስራት እንደሚገባ ተመላክቷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአፍሪካ ያሉ የሰላም እና የደህንነት ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአፍሪካ ህብረት ቁልፍ አጋር ሆኖ እንደሚቀጥል ዳግም አረጋግጧል። የአፍሪካን የሰላምና ደህንነት መዋቅር ማጠናከር፣ ግጭትን አስቀድሞ የመከላከል ዲፕሎማሲና የእርቅ ሂደትን በሚገባ መተግበርና ለአፍሪካ ፈተናዎች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ማረጋገጥ የሚያስችል በቂ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ በስብሰባው ላይ ተነስቷል። በውይይቱ በሳሄል ቀጠና፣ በሊቢያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮችና የሰላም ጥረቶች ተገምግመዋል። በስብስባው ላይ ግጭቶች፣ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የተፈጠሩ መስተጓጎሎች እና የባህር በር መስመሮችን መዝጋትን ጨምሮ ሌሎች ውጫዊ ሁኔታዎች በአፍሪካ ኢኮኖሚ እና ምግብ ዋስትና ላይ ተጨማሪ ጫና እየፈጠሩ መሆኑ ተነስቷል። የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለው ጉዳትም ምክክር ተደርጎበታል። ሁለቱ ወገኖች በውይይቶች ጠንካራ የጋራ ግብረ መልስ መስጫ ማዕቀፍ ለመፍጠር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። የአፍሪካ ህብረት እና ተመድ ፍኖተ ካርታ ዝግጅን ለማጠናቀቅ፣ በአፍሪካ ሀገራት የሰላም ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር፣ የምግብ ዋስትና ተግዳሮቶችን ለመፍታትና ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ የአሰራር ማዕቀፎችን ለመቅረጽ በቅርበት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል። 81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እስከ መስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
በቀጣናው ያሉ ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገራት የጋራ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው - ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)
Sep 15, 2026 745
አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ)፦ በቀጣናው እያጋጠሙ የሚገኙ ፈተናዎች በዘላቂነት እንዲፈቱ የአባል ሀገራት አብሮነትና የጋራ ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ። የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት 74ኛው አስቸኳይ ስብሰባውን ዛሬ በጅቡቲ አካሂዷል። በስብሰባው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮች ተሳትፈዋል። በቀጣናው ሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎች አበይት ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በቀጣናው እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመቋቋም የአባል ሀገራት አብሮነትና የጋራ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው። በኢጋድ ሴክሬታሪያት በኩል የተከናወኑ የልማትና የሰላም ሥራዎች አበረታች ውጤቶችን እያስገኙ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ተቋሙ ለቀጣናው ህዝቦች ብልጽግና መረጋገጥ የጸና አቋም እንዳለው አመልክተዋል። ምንም እንኳን የተለያዩ ጂኦፖለቲካዊ ፈተናዎች ቢኖሩም፣ የኢጋድ ሴክሬታሪያት ያለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸም አበረታች የሚባል መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣናዊ መሠረተ ልማት እና የጤና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን ያነሱት ዋና ፀሐፊው፤ የቀጣናው የከርሰ ምድር ውሃ መረጃ ሥርዓት የአገልግሎት ተደራሽነት የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል። እንዲሁም የቀጣናው ዓለም አቀፍ የጤና ሽፋን መረጃ ጠቋሚ (ኢንዴክስ) ከ60 ወደ 65 በመቶ ከፍ ማለቱንና ይህም እ.አ.አ በ2027 70 በመቶ ለማድረስ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ነው ያነሱት። በሌላ በኩል ሱዳን ወደ ኢጋድ ሙሉ አባልነቷ መመለሷ የቀጣናውን ትብብርና አንድነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል። ዋና ፀሐፊው እ.አ.አ ጁላይ 2026 ወደ ሱዳን ባቀኑበት ወቅት የኢጋድ የሱዳን ልዑክ ቢሮ በድጋሚ በይፋ መከፈቱን አስታውሰው ይህ እርምጃ ከቀጣናው ሕዝቦች ጋር ያለውን ቀጥተኛና ዘላቂ ትስስር አጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑን አመላክተዋል። ኢጋድ ከአፍሪካ ሕብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች እና ከሌሎች ስትራቴጂካዊ አጋሮች ጋር ያለው ግንኙነት ለቀጣናው ዘላቂ ልማት ወሳኝ ነው ብለዋል። አጋርነቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን አቅም በማጠናከር ረገድ የጎላ ድርሻ እንደሚያበረክትም ነው ያነሱት። በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን በማጠናከር ለመቋቋም የሚያስችሉ አሰራሮች እየተቀረፁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሀገራት የኤልኒኖ (El Niño) የአየር ንብረት መዛባት የሚያስከትለውን ስጋት ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል። በሌላ በኩል ቀጣናውን ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር ለማስተሳሰርና በቴክኖሎጂ የታገዘ የልማት መሠረት ለመጣል የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸዋል። ስብሰባው የቀጣናውን ሰላም፣ ደህንነት እና ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን በሚያስችሉ ሀገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በመምከርና ውሳኔዎችን በማሳለፍ መጠናቀቁን ኢዜአ ከኢጋድ ሴክሬተሪያት ያገኘው መረጃ ያመለክታል። የኢጋድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተቋሙ ቁልፍ የፖሊሲ አደረጃጀቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የድርጅቱን ሥራዎች በመምራትና በአባል ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና የሚጫወት ነው።
አፍሪካ በዓለም ፊት ቦታ ለማግኘት አትማጸንም ፤ ይልቁንም የሚገባትን ስፍራ በባለቤትነት እየያዘች ነው
Sep 9, 2026 634
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2018 (ኢዜአ):- አፍሪካ በዓለም ፊት ቦታ ለማግኘት አትማጸንም ፤ የሚገባትን ስፍራ እና ክብር በራሷ እያረጋገጠች ነው ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ። የአፍሪካ ህብረት ቀን ዛሬ እየተከበረ ይገኛል። የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ቀኑን በማስመልከት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ሊቀ መንበሩ የአፍሪካ ህብረት ቀን እ.አ.አ በ1999 የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለመተካት ይፋዊ ውሳኔ የተላለፈበት የሰርጥ ድንጋጌ (Sirte Declaration) የሚታወስበት እንደሆነ ገልጸዋል። በዚያን ወቅት የአፍሪካ መሪዎች አህጉራዊ ትስስርን ለማፋጠን እና የአፍሪካን ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ለማድረግ የአፍሪካ ህብረትን ለመመስረት ወሳኝ እና ታሪካዊ እርምጃ የወሰዱበት ምዕራፍ ነው ብለዋል። የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት ቀን ለአህጉሪቱ እጅግ ልዩ ትርጉም ባለው ወቅት ላይ እየተከበረ እንደሚገኝ አውስተዋል። ከጥቂት ቀናት በፊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የአፍሪካን እውነተኛ ቁመና እና ትክክለኛ መጠን የሚያሳይ የዓለም ካርታ አጠቃቀምን የሚደግፍ፣ በአፍሪካ መሪነት የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ አፅድቋል። በቶጎ ሃሳብ አመንጪነትና በአፍሪካ ህብረት ድጋፍ እውን የሆነው ይህ እርምጃ ከቀላል የካርታ ማስተካከያ በላይ ትርጉም አለው ብለዋል ሊቀ መንበሩ። አፍሪካ በዓለም ፊት እንዴት እንደምትታይ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን እና አፍሪካ ራሷን የምትገመግምበትንና የምታሳይበትን ትርክት ራሷ መቅረጽ እንዳለባት አበክሮ የሚያስታውስ ነው። ይህ ውሳኔ አፍሪካ በዓለም ፊት በምን መልኩ መታየት እንዳለባት ከማሳየቱም በላይ፤ አፍሪካ ራሷን የምትመዝንበትንና እውነታዋን ለዓለም የምታሳይበትን ትርክት በራሷ መቅረጽ እንዳለባት በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ነው ያነሱት። የአፍሪካ እጣ ፈንታ የሚወሰነው በአፍሪካውያን የራሳቸው እይታ ነው። አፍሪካን በእውነተኛ ቁመናዋ፣ኃይሏ እና አቅሟ የምንመለከትበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል። የኮሚሽኑ ሊቀመንበር አያይዘውም ካርታውን የማስተካከል እርምጃ አፍሪካ ወደ ላቀ የጋራ ራዕይ የምታደርገው አህጉራዊ ጉዞ አካል መሆኑን አንስተዋል። ይህም በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጠና (AfCFTA) አማካኝነት የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከርን፣ ሰላም እና ፀጥታን ማረጋገጥን፣ ዘላቂ ልማትን እውን ማድረግን እና በዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪ አካላት ውስጥ የአፍሪካን ተሳትፎ ማሳደግን እንደሚያካትት በዝርዝር አስረድተዋል። የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 የተሳሰረች፣ የበለጸገች እና ሰላማዊት አፍሪካን ለመገንባት የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። ሰላም እና ፀጥታን ማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ ትስስርን በማፋጠን እና የአፍሪካን ዓለም አቀፍ ተሰሚነት መጨመር የአፍሪካ ህብረት ቀዳሚ ትኩረቶች ናቸው ብለዋል። አፍሪካ በዓለም ፊት እውቅና ለማግኘት አትለምንም፤ ይልቁንስ በዓለም አቀፍ መድረክ የሷ የሆነውን ትክክለኛ ስፍራ በራሷ ባለቤትነት እየያዘች ነው። አሁን የሚጠበቅብን ይህንን ጠንካራ እምነት ወደ ህብረት፣ ሀብትና ብልጽግና፣ ሰላም እና ተደማጭነት መለወጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ሊቀመንበሩ አፍሪካ የምታስመዘግበው እድገት በዓለም አቀፍ መድረኮች በሚኖራት ውክልና ብቻ ሳይሆን፣ በዜጎቿ ላይ የኑሮ ጥራት መሻሻል ጭምር መለካት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። በዚህም መሰረት የአፍሪካ ህብረት የ2026 ዓመት ትኩረቱን በዘላቂ የንጹህ ውሃ አቅርቦት እና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አገልግሎት ላይ ማድረጉ፣ ህብረቱ አህጉራዊ ራዕዮችን ከዕለት ተዕለት የዜጎች ህይወት ጋር ለማያያዝ ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አመልክተዋል። በአፍሪካ ህብረት ቀን አከባበር አባል ሀገራት፣ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ የአፍሪካ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ሴቶች እና ወጣቶች ተባብረው ይበልጥ የተሳሰረች፣ በራሷ አቅም የምትተማመን እና የራሷን እጣ ፈንታ በራሷ መወሰን የምትችል አፍሪካን እንዲገነቡ ሊቀመንበሩ ጥሪ አቅርበዋል። የምንፈልጋት አፍሪካ የሚለውን አህጉራዊ ራዕይ እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ እና የሰርት ድንጋጌ ለቀጣዩ የአፍሪካ ትውልድ ዘላቂ የትምህርት እና የዕድገት መሰረት ሆኖ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። የነገዋ አፍሪካ በካርታ ላይ ብቻ የተሻለ ውክልና ያላት ብቻ ሳትሆን፤ በዓለም አቀፍ መድረክ ሉዓላዊነቷ የጸና፣ ጠንካራ ውስጣዊ አንድነት ያላት፣ ለህዝቦቿም ዘላቂ ብልጽግናን የምታጎናጽፍ አህጉር መሆን ይኖርባታል ነው ያሉት። የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ለመላው አፍሪካውያን እና በውጭ ሀገር ለሚገኙ የአፍሪካ ዳያስፖራዎች ሰላማዊ እና የትብብር መንፈስ የተሞላበት የአፍሪካ ህብረት ቀን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ህብረት እና አሜሪካ አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ
Sep 4, 2026 822
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2018 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ህብረት እና አሜሪካ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን እና ሁሉን አቀፍ ትብብራቸውን የበለጠ ለማላቅ እንደሚሰሩ አስታወቁ። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሺያን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ውይይቱ በአፍሪካ ህብረትና አሜሪካ መካከል ያለውን ለረጅም ጊዜ የቆየ አጋርነት ማጠናከር እና በአህጉሪቱ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። የኮሚሽኑ ሊቀመንበር የአፍሪካና አሜሪካን ትብብር ታሪካዊ መሆኑን አውስተው በህብረቱ፣ በአባል ሀገራት እና በአሜሪካ መካከል የሁለቱንም ወገኖች ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ጠንካራ አጋርነት መገንባት እንደሚገባ አሳስበዋል። በምስራቅ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሱዳን እየተደረጉ ላሉ አፍሪካ መር የሰላም ጥረቶች አሜሪካ እያደረገች ላለው ገንቢ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሺያ በበኩላቸው አፍሪካ አሜሪካ ቀዳሚ ትኩረት የምትሰጣት አህጉር እንደሆነች ገልጸዋል። የጋራ ፍላጎቶችንና ግቦችን ከህብረቱ ኮሚሽንና ከአባል ሀገራት ጋር በመሆን ለማሳካት ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በዲፕሎማሲ፣ እንዲሁም በሰላምና ጸጥታ ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል። በውይይቱ ላይ በሱዳን ጉዳይ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ የሰብአዊ እርዳታ ያለ ገደብ እንዲገባ እና በሲቪሎች የሚመራ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት እንዲጀመር አጽንዖት ተሰጥቷል። በአፍሪካ ባለቤትነት የሚመሩ የሰላም ጥረቶች እና አሜሪካ የምትደግፋቸው የሰላም ሂደቶች በተቀናጀ መልኩ ለመተግበር ከስምምነት ላይ ተደርሷል። በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመሰረተ ልማት እና በሰላም መስኮች የሁለቱን ወገኖች ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ የትብብር መስኮች ተገምግመዋል። ሁለቱ ወገኖች በአፍሪካ ህብረትና በአሜሪካ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት ማዕቀፍ ውስጥ የተደረጉ ስምምነቶችን ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። በሊቢያ ጉዳይ ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሄ ማግኘት እንደሚያስፈልግም ተነስቷል። የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር እና ረዳት ሚኒስትሩ የሁለቱን ወገኖች ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከርና የትብብር አድማሱን ለማስፋት የጋራ ቁርጠኝነታቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሐተታዎች
ነገን የዋጀ የኢትዮጵያ ጉዞ
Sep 22, 2026 123
ኢትዮጵያ የዛሬን ተፎካካሪነት ብቻ ሳይሆን የነገውን ዓለም አሻግራ በመመልከት፣ አርቆ አሳቢነት በተሞላበት መንገድ የዲጂታል ምህዳሯን በጽኑ መሠረት ላይ እየገነባች ትገኛለች። ይህ "ነገን የዋጀ የልማት ጉዞ" በቃላት ሳይሆን በተጨባጭ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና በዕውቀት በተደገፉ የቴክኖሎጂ እርምጃዎች እየተረጋገጠ ይገኛል። ወጣቶችን በኮዲንግ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በዲጂታል ክህሎት ማበቃት የነገዋን ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ማዕከል የማድረግ ትልቅ ራዕይ መገለጫ ነው። የ"5 ሚሊዮን ኮደርስ" ኢኒሼቲቭ በአሁኑ ወቅት ከታቀደው በላይ ተሳክቶ ወደ 7 ሚሊዮን ኮደርስ ማደጉ የወደፊቷን ሀገር በሰው ሀብት የመታደግ አርቆ አሳቢነት ማሳያ ነው። ይህም ነገ የአፍሪካን የዲጂታል ገበያ በበላይነት የሚቆጣጠሩ አቅም ያላቸው ወጣቶችን የማፍራቱን ስራ በጽኑ መሰረት ላይ እያስቀመጠው ነው። ለዲጂታል ትስስርና ለገበያ ተሳትፎ ዋነኛ መሠረት የሆነው የቴሌኮም ተመዝጋቢ ደንበኞች ቁጥር ሀገራዊ ለውጡ ሲጀመር ከነበረበት ከ37 ነጥብ 9 ሚሊዮን ወደ 85 ሚሊዮን በላይ ማደጉ፣ የኢትዮጵያውያንን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት አዲስ ደረጃ ላይ አሸጋግሮታል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የተመዘገቡ ሲሆን፤ ይህም የገበያ ምዝገባ እና የማረጋገጫ ወጪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ለአገልግሎቶችና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ትልቅ ምቾትና እምነት ፈጥሯል። እንደ "መሶብ" ያሉ የዲጂታል አገልግሎት መስጫ ተቋማት በአጭር ጊዜ ውሰጥ በሁሉም የኢትዮጵያ ከባቢዎች እየሰፉ ሲሆን፤ ዲጂታል ግብይትም በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ትልቁን ስፍራ እየያዘ ይገኛል። ይህ አሰራር አገልግሎትን ለማቀላጠፍ ከማስቻሉ ባሻገር፣ ጥሬ ገንዘብ ለማተም እየወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ እያስቀረ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ዓመታዊ የዲጂታል ግብይት መጠን 24 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር መድረሱ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ስኬታማነት ማረጋገጫ ነው። መደመር ያለፉ እውቀቶችን፣ የዛሬ አቅሞችንና የነገ ተስፋዎችን አዋህዶ ሀገርን የማነፅ ፍልስፍና ነው። በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሚከናወኑት እነዚህ የሰው ሀብት ልማት፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የፋይዳ መታወቂያና የዲጂታል ግብይት ስኬቶች በሙሉ "በመደመር" መርህ የወጣቶችን እውቀትና ሀገራዊ አቅምን ለመገንባት የተለሙ ናቸው። ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ እያከናወነች ያለችው ሥራ የዛሬ ፍላጎቶችን የመመለስ ያህል፣ ነገ የሚገጥማታን ዓለም አሻግራ የመመልከትና ለዲጂታሉ ዘመን ተወዳዳሪ ሆኖ የመቅረብ ጥበብ ነው። ይህ ጉዞ ነገን ዛሬ የመገንባት፣ የትውልድን ተስፋ የማረጋገጥና የኢትዮጵያን ብልፅግና የማስቀጠል የጋራ ስኬታችን ማሳያም ጭምር ነው።
"ያሆዴ"- ከፉሊት ታኮ ብስራት እስከ ዘራሮ ይዞ ጥየቃ
Sep 21, 2026 169
(በማሙሽ ጋረደው ከኢዜአ ሆሳዕና ቅርንጫፍ) በሀዲያዎች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው "ያሆዴ" የመተሳሰብና የመረዳዳት ተምሳሌት ነው። በዓሉ ማኅበራዊ መሠረትን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል። "ያሆዴ" አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲስ ዘመን የሚቀበሉበት፣ የመጻኢ ተስፋ ብስራትና የልምላሜ ምልክት ተደርጎም ጭምር ይቆጠራል። በመሆኑም በዓሉ ሲቀርብ የሀዲያ ተወላጆችና የበዓሉ ተሳታፊዎች ከሀገር ውስጥም ሆነ ከወጭ ከያሉበት ወደ አካባቢያቸው ይሰባሰባሉ። የያሆዴን ባህላዊ ክዋኔዎች ለመከወን እንዲመች ታስቦ በተዘጋጀው ስፍራ (ሀድይ ነፈራ) ተሰባስበው በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ። በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ ትምህርት መምህርና የበዓሉ ተመራማሪ መምህር ታረቀኝ ኑክሮ እንደሚናገሩት፣ የሀዲያ የዘመን መለወጫ በዓል "ያሆዴ" የመተሳሰብና የመረዳዳት ተምሳሌት ነው። በዓሉ የብሩህ ተስፋ፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የረድኤትና የበረከት ተምሳሌት በመሆኑ የተለየ ትርጉምና ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል። በዓሉ ሲከበር በተለያዩ ምክንያቶች ተራርቀው የሚኖሩ የቤተሰብ አባላት ከያሉበት እንደሚሰበሰቡም አመልክተዋል። በዓሉ ባማረ መልኩ እንዲከበርም ሁሉም የቤተሰብ አባላት የየራሳቸውን የሥራ ድርሻ የሚያከናወኑ ሲሆን፣ አባወራዎች ለበዓሉ ሠንጋ መግዣ የሚሆን ገንዘብ "በቱታ" ወይም በቅርጫ ቡድናቸው አማካኝነት እየቆጠቡ ይቆያሉ። እንዲሁም ለእንስሳት የሚሆን የግጦሽ ሣር የሚያበቅል ቦታ ከልለው ያዘጋጃሉ። ይህ የሚሆነበት ምክንያት ደግሞ በዓሉ በሚከበርበት ሰሞን የሰው ልጅ ይቅርና እንስሳትም መጥገብ አለባቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው። እናቶች በዓሉ ከመቃረቡ ከ3 እና 4 ወራት አስቀድመው ለሥጋ መብያ የሚሆን እንሰት በመፋቅ ቆጮ፣ ቡላና የቅቤ እቁብ (ዊጆ) በመግባት ቅቤ የማጠራቀም ኃላፊነታቸውን በመወጣት ቅድመ ዝግጅት ያደርጋሉ። ለበዓሉ ማድመቂያ የሚሆን ጠጅና ቦርዴን ጨምሮ ሌሎች መጠጦችን ማዘጋጀትም የእናቶች ድርሻ ነው። በዚህ ወቅት ወጣቶችም የራሳቸው የሆነ የሥራ ድርሻ አላቸው። ወጣት ሴቶች የቤቱን ወለል ይደለድላሉ፣ ያሰማምራሉ፤ የተለያዩ ውበት በሚሰጡ ቀለማት በመጠቀም የቤቱን የውስጥና የውጭ ግድግዳዎች በተለያዩ ጌጦች ያስውባሉ። ወጣት ወንዶች ደግሞ ከነሐሴ መግቢያ ጀምሮ በወላጆቻቸው የተለየላቸውን ግንድ ቆርጠው ለምግብ ማብሰያነት የሚውል የማገዶ እንጨትና ለችቦ (ሳቴ) እንጨት ማዘጋጀት ደግሞ ተግባርና ኃላፊነት ነው። በተጨማሪም አቅመ ደካማ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተናጠልና በቅንጅት የተሟላ ድጋፍ የማድረጉ ሥራ በማኅበረሰቡ ከሚደረጉ የቅድመ ዝግጅት ሂደቶች አንዱና ዋነኛው ነው። እንደ መምህር ታረቀኝ ማብራሪያ፣ ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ የዋሽንት (ገምባቡያ) ድምፅና በታዳጊ ልጆች "ኦሌ... ኦሌ" የወጣቶች ጭፈራ መሰማት ከጀመረ፣ በሀዲያዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የዘመን መለወጫ "ያሆዴ" በዓል የመቃረቡ ምልክት ነው። ይህ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓት የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ (ፉሊት ታኮ) ይባላል። ይህም በዓሉ መቃረቡን ተከትሎ የሚፈጸም ባህላዊ ክዋኔ ነው። ማኅበረሰቡ አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ሲያከናውን የነበረውን ቅድመ ዝግጅት ይበልጥ በማጠናከር መነቃቃት የሚፈጠርበት የብስራት ወቅት ነው። ወጣቶች "ኦሌ... ኦሌ" እየጨፈሩ በየቤቱ እየዞሩ አዲሱ ዓመት መቃረቡን ያበስራሉ፤ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፤ እንዲሁም የተለያዩ ስጦታዎችን ይቀበላሉ። ይህም ወጣቶቹ ወላጆቻቸው ለዋዜማው በመድረሳቸው መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹበት ወቅትም ነው። ከበዓሉ ዕለት በፊት ያለው የመጨረሻ ገበያ "የእብድ ገበያ" (መቻዕል ሜራ) የሚል ስያሜ አለው። ስያሜው በዓሉ ሲቃረብ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚፈጠረውን ውጥረት ለማሳየት ያለመ ሲሆን፣ ገበያው በማለዳ ጀምሮ እኩለ ቀን ላይ ይጠናቀቃል። ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለመግዛትና የያሆዴ በዓል ከተከበረ በኋላ ለአንድ ወር ገበያ ስለማይኖር፣ ይህን ታሳቢ ያደረገ ግብይት ለመፈጸም የግብይት ሂደቱ ጥድፊያ የበዛበት ሆኖ ይታያል። በዚህ ገበያ አባወራዎች በቅርጫ ማኅበራቸው አማካኝነት ያጠራቀሙትን ገንዘብ በመያዝ የእርድ በሬ ይገዛሉ። በዚህ ወቅት ገንዘብ ማጠራቀም ያልቻሉ የቅርጫ አባላት እህል በሚደርስበት ወቅት ለመክፈል ተስማምተው በሬውን በዱቤ (አባ) እንዲገዙ ይደረጋል። ይህም የሚሆነው በ"ያሆዴ" በዓል አንዱ ሲበላ ሌላው ተመልካች መሆን ስለሌለበት ነው። የ"ያሆዴ" በዓል መከበር የሚጀምረው በአተካን ሂሞ ወይም በአተካና ምሽት ሲሆን፣ ይህም ከበዓሉ አንድ ቀን በፊት ያለው ምሽት ነው። በሀዲያዎች ዘንድ ቂምና ጥላቻን ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር ፈጽሞ የማይቻል በመሆኑ፣ ይህንን የበዓል ዋዜማ እርቀ-ሰላም የሚፈጽሙበትና ተራርቀው የቆዩ የአካባቢው ተወላጆች በናፍቆት የሚገናኙበት በመሆኑ ዕለቱን የተለየ ያደርገዋል። "አተካና" በሀዲያዎች ዘንድ ለክብር እንግዳና በዘመን መለወጫ በዓል ወቅት የሚዘጋጅ ምግብ ነው። አተካና ከወተት፣ ከአይብ፣ ከቡላ፣ ከቅቤና ከሌሎች የቅመማ ቅመም ውጤቶች የሚዘጋጅ ሲሆን፣ በጣም ጣፋጭና የምግብ ፍላጎትን የሚጨምር ምግብ ነው። ሀዲያዎች በበዓሉ ዋዜማ ይህንን የተለየ ምግብ ተሰባስበው በአብሮነት በመመገብ በደመቀ መልኩ በዓሉን ማክበር ይጀምራሉ። የአካባቢው አባቶች በወጣቶች የተዘጋጀ የማቀጣጠያ እንጨት (ሳቴ) ይዘው ትልቅ በሚባሉ አባወራዎች ቤት ደጃፍ ወደ ተዘጋጀው የችቦ ደመራ (ጦምቦራ) ቦታ ይመጣሉ። የሀገር ሽማግሌዎች አዲሱ ዓመት የብርሃን ዓመት እንዲሆን፣ ለሀገርና ለሕዝቦቿ ሰላም እንዲጸና፣ አብሮነት እንዲጠናከር፣ ሰላምና ፍቅር እንዲነግሥ ፈጣሪያቸውን ከተማጸኑ በኋላ ችቦውን በእሳት ይለኩሳሉ። ችቦው ከተለኮሰ በኋላ የአካባቢው ወጣቶች ተሰባስበው "ያሆዴ... ያሆዴ!... ያሆዴ!... ሆያ!... ሆ!" በማለት እየጨፈሩ ያነጋሉ። በሀዲያዎች ዘንድ "ያሆ" ማለት የአዲስ ዓመት መግባትን ተከትሎ የሚደረግ ማብሰሪያ ጭፈራ ሲሆን፣ "ኤዴ" ማለት ደግሞ አገናኝ ማለት ነው። በ"ያሆዴ" በዓል የእርድ ሥነ-ሥርዓት ለማከናወን ነዋሪዎች የሚሰበሰቡበት ስፍራ "ነፈራ" የሚል ስያሜ አለው። ይህም የተለያዩ ማኅበራዊና ባህላዊ ክዋኔዎችን ለመከወን እንዲመች ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ሰፋ ያለ ቦታ ሲሆን፣ በተለያዩ የጥላ ዛፎች የተዋበና ለዚሁ ተግባር የተዘጋጀም ነው። በዕለቱ ለእርድ የተዘጋጀው ሠንጋ ከቀረበ በኋላ የባህል ሽማግሌዎች የበሬውን ሻኛ በሰርዶ ሣር ለጋ ቅቤ ይቀባሉ፤ ወተትም ያፈሱበታል። ይህ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓት "ጋቢማ" የሚባል ሲሆን የመልካም ምኞት መግለጫ ሥነ-ሥርዓት ነው፦ "ክፉ ቀን አይምጣ፣ ራብና ሰቀቀን ይጥፋ፣ ጥጋብ ይስፈን፣ በአካባቢውና በሀገሩ ጥጃ ይቦርቅ፣ ልጅ ይፈንጭበት፣ ሀገር ሰላም፣ ገበያ ጥጋብ ይሁን፣ ሰማይና ምድሩ ይታረቁን" እያሉ በአባቶች ምርቃት ከተካሄደ በኋላ የእርድ ሥነ-ሥርዓቱ ይከናወናል። የእርድ ሥነ-ሥርዓቱ የተከናወነበት ቤት እማወራ አስቀድመው ባደረጉት ዝግጅት መሠረት ቅቤ፣ (ቦርዴ፣ ቃሪቦ፣ ጠጅ፣ ብርዝ) እንዲሁም ከታረደው የበሬ ሥጋ አርዚ ማራ (የቅምሻ ሥጋ) ይወሰድና ክትፎ ከተዘጋጀ በኋላ በጋራ እየበሉና እየተጫወቱ ይውላሉ። በዚህም በቅርጫ ሥጋው ላይ ከሚሳተፉት የቤተሰብ አባላት ውጭ በአካባቢው የሚገኙ አቅመ-ደካማ ወገኖች ጭምር አብረው በመብላትና በመጠጣት በዓሉን በአንድነት ያሳልፋሉ። ቀሪውን የቅርጫ ሥጋም አባላቱ ተከፋፍለው ወደየቤታቸው ይወስዱታል። በዓሉ አብሮ የመብላት፣ የመጠጣት፣ የመጠያየቅ፣ ችግርንና ግጭትን በጋራ ተወያይቶ የመፍታት፣ መፈቃቀርና መተሳሰብን የሚፈጥር፣ አቅመ-ደካሞችና የተቸገሩ የሚረዱበት የአብሮነት መገለጫ በመሆኑ በተለየ መልኩ ይከበራል። ከእርድ ሥርዓቱ በኋላ በማግስቱ ልጆች አደይ አበባ (ዘራሮ) ይዘው ወደ ወላጆቻቸው እየጨፈሩ ይመጣሉ። ሥርዓቱም "ሚክር ከጃ" ይባላል። "እንደ መስቀል አበባ ፈክታችሁ ኑሩ" ተብለው ይመረቃሉ። ከሥጋው፣ ከቦርዴውና ከአተካናውም እንዲመገቡ ይደረጋል። በ"ያሆዴ" የዘመን መለወጫ በዓል ትዳር የያዙ የቤት እመቤቶች ከባሎቻቸው ጋር ሆነው ወደ ወላጆቻቸው ምግብ ሠርተው፣ የሹልዳ ሥጋና አደይ አበባ ጭምር ይዘው ይሄዳሉ። በዓሉ ያላገቡ ወጣቶች የሚተጫጩበትና ለአዲስ ሕይወት ጅማሬ የሚያበስሩበት በመሆኑ የተለየ ድባብም አለው። የመተሳሰብና የመረዳዳት ተምሳሌት የሆነው የዘንድሮው የ"ያሆዴ" በዓል መስከረም 11 እና 12 ቀን 2019 ዓ.ም. በሆሳዕና ከተማ በተለያዩ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓቶች ታጅቦ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።
"ዮ ማስቃላ"--ከእንጊጫ እስከ ጮዬ
Sep 19, 2026 325
(በሳሙኤል አየነው -ከኢዜአ አርባምንጭ ቅርንጫፍ) የጋሞ ማህበረሰብ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር፣ ባህልና ቋንቋ አለው። ከእነዚህም የሰላም፣ የአብሮነትና የይቅርታ እሴትን አቅፎ የያዘው የዘመን መለወጫ በዓል "ዮ ማስቃላ" በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችል ሲሆን በትውልድ ቅብብሎሽ ሲወርድ ሲዋረድ እየተከበረ ዛሬ ላይ ደርሷል። ማህበረሰቡ ዘመን ተሻጋሪ የጋራ እሴት ያለው ጠንካራ ባህል የገነባ በመሆኑ በአብሮነት፣ በሰላም፣ በአንድነት፣ በፍቅርና በይቅርታ ተቻችሎና ተከባብሮ ዘመናትን ተሻግሯል። አሁንም ይህንኑ እሴቱን በማጠናከር ቀጥሏል። ከጋሞዎች የዘመን መለወጫ በዓል ''ዮ ማስቃላ'' እሴቶችና ሌሎች ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ ኢዜአ ከዞኑ ባህልና ስፖርት መምሪያ የባህል እና ታሪክ ጥናት ልማት ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ወንድይፍራው ከተማ ጋር ቆይታ አድርጓል። አስተባባሪው እንደገለጹት፤ ጋሞዎች የዘመን መለወጫ በዓላቸው ''ዮ ማስቃላ'' ከመከበሩ አስቀድሞ አባቶች ለእርድ ከብት፣ ለአልባሳትና ጌጣጌጥ መግዣ እናቶች ደግሞ ለባህላዊ ምግብና መጠጥ እንዲሁም ቅመማ ቅመም የሚሆን የገንዘብ ቁጠባ ያደርጋሉ። ጋሞዎች ቁጠባን የለመዱት ከጥንት አባቶች በተረከቡት የዘመን መለወጫ ቅርስ ጀምሮ ሲሆን ዛሬ ላይ ኑሮን ለማሸነፍ ቁጠባ በሁሉም አካባቢ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። የበዓሉ ዝግጅት ምዕራፍ በአካባቢው አጠራር "እንጊጫ" ይባላል፤ በዓሉ ሲቃረብ በተቆጠበው ገንዘብ በመስከረም ወር ከመጀመሪያው ሣምንት ጀምሮ አባወራዎችና እማወራዎች በየገበያው የተለያዩ የበዓል ቁሳቁሶችንና የፍጆታ ዕቃዎችን መሸመት ይጀምራሉ። በዚህም ወቅት አባወራው ለበዓሉ የሚሆን ሠንጋ፣ ለመላው ቤተሰብ አልባሳት እና ለእማወራዋ ጌጣጌጥ የማቅረብ ኃላፊነቱን ሲወጣ፤ በአንጻሩ እማወራዋ ቅቤ፣ ለቅመማ ቅመምና ለባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች ትኩረት በመስጠት ዝግጅት ታደርጋለች። በበዓሉ ጅማሮ እንደየ አመቺነቱ ሁሉም ከቤተዘመድና ከጎረቤት ጋር በመሆን አማካይ በሆነ ስፍራ ከብቶችን የሚያርዱ ሲሆን፤ በስፍራው ከየሥጋው ዓይነት ያዘጋጁትን ከቀማመሱ እና በቦርዴ ካወራረዱ በኋላ የድርሻቸውን ሥጋ ይዘው ወደ የቤታቸው በማቅናት ቁርጥ እና ጎረድ ጎረድ ጥብስ ሥጋ በቅቤ ተለውሶ በትልቅ ወጭት ላይ ቀርቦ ይመገባሉ። ከባህላዊ ምግቦች መካከል የገብስ ቅንጬ፣ የቡላ ቆጮ እና ከገብስ የሚዘጋጅ ቂጣ፣ የቡላ ፍርፍር፣ ሐረግ ቦዬ ሲሆኑ፤ ከመጠጥ ደግሞ ቦርዴ፣ የማርና የቦርዴ ውህድ የመሳሰሉ ባህላዊ መጠጦችም በስፋት ይቀርባሉ። "ዮ ማስቃላ" ለሰላም እሴት ግንባታ የራሱ የሆነ ጉልህ ፋይዳ አለው፤ በጋሞዎች ዘንድ አዲሱን ዓመት ቂም፣ ቁርሾ እና ሐዘን ይዞ መሻገር ነውር በመሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተጣሉት ይታረቃሉ፤ ይቅር ይባባላሉ፤ ያዘኑት ደግሞ ሐዘናቸውን በመተው በአዲስ መንፈስ ይጽናናሉ። በተለያዩ ስፍራዎች ተራርቀው በናፍቆት የቆዩ ዘመድ አዝማድ እና ወዳጆች ተሰባስበው በዓሉን በጋራ ማክበር የ"ዮ ማስቃላ" ሌላኛው የመደመር፣ የአብሮነትና የአንድነት ገጽታ ነው። "ዮ ማስቃላ" ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም የደስታና የጥጋብ ጊዜ ተብሎ የሚታሰብ በመሆኑ የቤት እንስሳትን ቀደም ሲል ተከልለው በለሙ የግጦሽ ስፍራዎች እንዲሰማሩ በማድረግ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድ ልብ ፊታቸውን ወደ በዓሉ ያዞራሉ። ከጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት አሜሌ አልቶ፤ የመስቀል ዳመራ ችቦ ሥርዓት፣ የአባቶች ምርቃት እና ባህላዊ ጨዋታዎች እንዲሁም አብሮ መብላትና መጠጣት ከ"ዮ ማስቃላ" ዘመን መለወጫ በዓል አበይት ኩነቶች እንደሚጠቀሱ አጫውተውናል። ችቦ የሚወጣበት ሰዓት ሲደርስ አባት የራሱን ችቦ ለኩሶ የቅቤ ምንቸቱን፣ የቤቱን ምሰሶ፣ የከብቶቹን በረት እና የበር ጉበኖችን ግራ እና ቀኝ በችቦው ጫፍ በማነካካት ቀጥታ ወደ ደመራ ሥርዓት እንደሚያመሩ ጋሽ አሜሌ አንስተዋል። በዚህም ወቅት ወንድ ልጆች የየራሳቸውን ችቦ ተራ በተራ እየለኮሱ አባታቸውን ተከትለው "ዮ..ዮ..ማስቃላ" እያሉ በመጨፈር ወደ ደመራው ቦታ ከደረሱ በኋላ አባት በቀዳሚነት፣ ልጆች ደግሞ በተከታይነት ደመራውን ይለኩሳሉ። በ"ዮ ማስቃላ" ከታቀፉ እሴቶች መካከል የመደጋገፍ፣ አብሮ የመብላት፣ አብሮ የመጠጣትና አብሮ የመጨፈር አንዱ ሲሆን፤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች በዓሉን ለማክበር አይጨነቁም። ምክንያቱም ለበዓሉ የተዘጋጀው ምግብና መጠጥ ደሃ፣ ሀብታም ሳይባል ካለምንም ልዩነት ያላቸው ከሌላቸው ጋር ተጠራርተው በአብሮነት የሚደሰቱበት ልዩ ጊዜ ነው። በዓሉ ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእንስሳት እና ለአእዋፋትም ጭምር የደስታ ጊዜ ተብሎ የሚታመን በመሆኑ በወቅቱ ምግብ ከሰው አልፎ ለእንስሳት እና ለአእዋፋትም ይትረፈረፋል። አዲስ ዓመት እንደመሆኑ ሁሉም የቤተሰብ አባላት በአዲስ አልባሳት የሚያሸበርቁ ሲሆን፤ እናት ደግሞ በጌጣጌጥም ደምቃ የቤቱ ንግስት መሆኗን ታሳያለች። በ"ዮ ማስቃላ" ጊዜ ተጋቢ ጥንዶች በይፋ ማኅበራዊ ዕውቅና የሚያገኙበት ልዩ አጋጣሚ መሆኑንም ጋሽ ዓመሌ ይናገራሉ። የአንቱታን ክብር የሚጎናጸፉት በአልባሳትና ጌጣጌጥ ተውበው ከቤተሰብ፣ ሚዜዎችና አጃቢዎች ጋር ገበያ ወጥተው ራሳቸውን ካሳዩ በኋላ ነው። በተጨማሪም ማኅበራዊ ግዴታዎችን ለመወጣትም ሆነ ለኃላፊነት የሚታጩት ያን ሥርዓት ከፈጸሙ በኋላ ሲሆን፤ በዚህም ጊዜ እንስቷ ማህፀኗ ጽንስ መሸከም እንዲችል በሚል ለወራት ተቀልባና ታርሳ ትወጣለች፤ ይህ በአካባቢው ቋንቋ የ"ሶፌ" ሥርዓት ይባላል። የማኅበረሰቡ የጋራ የሆኑ የሰላም፣ የእርቅና የአብሮነት እሴቶች ደግሞ የማኅበረሰቡን አንድነት ከማጽናት ባለፈ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የማይነጥፍ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። እንደ "ዮ ማስቃላ" ያሉ የሕዝብና የሀገር አንድነትን የሚያጸኑ የአደባባይ በዓላት ሳይበረዙና ሳይከለሱ ለትውልድ ተጠብቀው እንዲቆዩ የመንግሥት አካላት፣ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች እየተወጡ ያለውን ሚና በማጠናከር የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል። ጋሞዎች "ዮ ማስቃላ"ን በወርሃ መስከረም ብቻ አክብረው የሚያበቁ ሳይሆን ከዕለት ተዕለት የኑሮ እንቅስቀሴን ጎን ለጎን የበዓሉ ድባብ ሳይደበዝዝ እስከ ታህሳስ ወር መገባደጃ በማክበር፣ በመጨረሻም የሽኝት (ጮዬ ማስቃላ) በየስፍራው ተዘጋጅቶ ከተገባበዙ በኋላ በአባቶች ተመራርቀው ይለያያሉ። "ዮ ማስቃላ" የአብሮነትና የአንድነት እንዲሁም ሰርቶ የመለወጥ የተስፋና የብርሃን ምልክትና ካስማ ተደርጎ የሚወሰድ በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሴቶችን በውስጡ የያዘ ሀብት ነው። የዘንድሮ የ"ዮ ማስቃላ" በዓል በመስከረም 11 እና 12/2019 ዓ/ም በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድምቀት ይከበራል።
"ጊፋታ"- ከጅምሩ እስከ ጋዜ ኦሩዋ
Sep 18, 2026 211
(በማስረሻ ሀብታሙ ከኢዜአ ወላይታ ሶዶ ቅርንጫፍ) የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" ሕዝቡ ለዘመናት ሲያከብረው የኖረ ደማቅ ባህላዊ እሴት ነው፡፡ ጊፋታ የተጣሉና የተኮራረፉ የሚታረቁበት እንዲሁም የሕዝቦች አንድነትና አብሮነት ይበልጥ የሚጠናከርበት የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡ ጊፋታ አዲስ ተስፋና ብርሃን ጭምር ነው፡፡ አሮጌው አልፎ አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስና መነሳሳት የሚቀበሉበት በጉጉት የሚጠበቅ በዓል ነው፡፡ ጊፋታ ለአብሮነትና ለሰላም እንዲሁም ለልማትና ብልጽግና በመዘጋጀት የሚቀበሉት ልዩ በዓልም ነው፡፡ በዓሉ ማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ የሕይወት ዑደትን የሚማርበት፣ ከትናንት በመማር ለነገ የሚዘጋጅበት፣ የአብሮነትና የትስስር እሴት ነው፡፡ ያነጋገርናቸው የወላይታ ባህል፣ ታሪክና ቅርስ ባለሙያ አቶ አዳነ አይዛ እንደሚሉት፤ ጊፋታ ታላቅ፣ በኩር፣ የመጀመሪያ፣ መሻገር የሚል ትርጓሜ አለው፤ ይህም ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገርን የሚያሳይ ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው ይህ በዓል በወላይታ ባህላዊ የጊዜ አቆጣጠር የመጀመሪያው ወር መሆኑን ያብራራሉ። ዕለቱም የጨረቃንና የፀሐይን እንቅስቃሴ መሰረት ያደረገውን የወላይታዎች ባህላዊ የጊዜ አቆጣጠርን በመከተል የሚከበር መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ ረጅም የመዘጋጃ ጊዜን የሚወስደው የጊፋታ በዓል ከአባቶች እስከ ሕፃናት በበዓሉ ዝግጅት ላይ የየራሳቸው የሥራ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፤ የቅድመ ዝግጅት ሥራው በአብዛኛው በደቦ ይከወናል። በዓሉ በሚቃረብበት ወቅት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል እርቅ ዋናው መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው፤ በዚህ ወቅት የተጣሉ ሰዎች እርስ በርሳቸው ታርቀው እና ጥላቻን ረስተው የጊፋታን በዓል እንደሚያከብሩ አውስተዋል፡፡ የተበደሩትን ዕዳ መክፈል ሌላኛው የጊፋታ በዓል ቅድመ ዝግጅት እንደሆነ እና ዕዳን ሳይከፍሉ ጊፋታን ማለፍ የተወገዘ ተግባር እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ጊፋታ ከመድረሱ ሦስት ወር ቀደም ብሎ ከአሮጌው ዓመት ጉሌ ወር ላይ ወጣቶች ተሰባስበው በአካባቢው የወደቁና ከጥቅም ውጭ የሆኑ እንጨቶችን በመልቀም በአንድ ቦታ ላይ በማከማቸት በዓሉን በእሳት ብርሃን እንደ ወደፊት ተስፋ በመውሰድ ያከብራሉ፡፡ እንዲሁም በዓሉ ሲቃረብ የመታደስ ምልክት የሆነውን አካባቢያቸውን የማጽዳት ሥራ የሚያከናውኑ ሲሆን፤ መኖሪያ ቤታቸውን የማሳደስና የተለያዩ ያረጁ ቁሶችን በአዲስ የመተካት ተግባር ያከናውናሉ፡፡ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አበሻ ሺርኮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዓሉ የሁለት ወር ጊዜ ሲቀረው አባወራዎች የእርድ በሬ በመግዛት ለተመረጠ ቤተሰብ በማስረከብ ከብቱ እንዲደልብና በደረቅ የኮባ ቅጠል በተሸፈነ ልዩ በረት በልዩ እንክብካቤ እንዲቀለብ ያደርጋሉ። በጊፋታ በዓል ዝግጅት አባቶችና ታላላቅ ወንድ ልጆች የጉሊያ እንጨት በማሰባሰብ፣ ማቆምና የማገዶ እንጨት መፍለጥ፣ ቆጮ መቁረጥ እና ሌሎችንም ሥራዎች ይሠራሉ። እናቶች እና ሴት ልጆቻቸው ደግሞ ለተለያዩ ባህላዊ ምግቦች እንሰትን መፋቅ፣ የማሽላና የበቆሎ ዱቄት፣ ዳጣ በርበሬ የማዘጋጀት፣ የተለያዩ ባህላዊ መጠጦችን እንደ ቦርዴና ጠላ ያሉትን በትላልቅ እንስራ ያዘጋጃሉ። የጊፋታ በዓል የሚከበርበት የአዲሱ ዘመን የመጀመሪያ ቀን ከሆነው እና እርድ ከሚከናወንበት የእሑድ ቀን በፊት ቅዳሜ (በወላይታ አቆጣጠር የአሮጌው ዓመት መጨረሻ ቀን) ላይ ሁሉም ሰው ንጽሕናውን የመጠበቅ ሥራ ያከናውናል፡፡ ይህ የሚደረገውም ከአሮጌው ዓመት እድፍና ቆሻሻ ጋር ወደ አዲሱ ዓመት መሻገር አያስፈልግም በሚል ነው፡፡ የእርድ ዕለት እሑድ (የወላይታ ዘመን መለወጫ) ጠዋት ወፎች ዜማቸውን እንዳሰሙ የእርድ ተግባሩ መከናወን ይጀምራል፤ በዚሁ ወቅትም እናቶች ያዘጋጁት መጠጥ እና ምግብ በእርዱ ለሚሳተፉት ሰዎች ይቀርባል። አባወራዎች ሥጋውን ተከፋፍለው ወደ ቤታቸው ከመውሰዳቸው በፊት ሁሉም በአንድ ላይ ይበላሉ፤ ይጠጣሉ። ይህም ፍቅራቸውን ከአንድ ማዕድ በመቁረስ የሚያድሱበትና አዲሱን ዓመት የሚያበስሩበት እንደሆነ አበሻ (ዶ/ር) ይገልጻሉ። በቀጣይም ዕጣ በመጣጣል ሥጋውን ተከፋፍለው ለጊፋታ ተብሎ በሚገዛ አዲስ ቅርጫ ሥጋውን ይዘው ወደ ቤታቸው እንደሚወስዱ እና እናቶች በቤት ውስጥ የመጣውን ሥጋ ባልተበሳሳ ኮባ ቅጠል ላይ ዙሪያውን በማስቀመጥ በቆጮ፣ በቂጣ፣ በዳጣ በርበሬ አድርገው ሲያቀርቡ፤ አባት ደግሞ እማወራዋን በማጉረስ እንደሚጀምሩ ያስረዳሉ። በጉሊያ ወር በወጣቶች የተሰበሰበው እንጨት (ጉሊያ) ለጊፋታ በዓል ሁለት ሳምንት ሲቀረው እንዲቆም የሚደረግ ሲሆን፤ በዕለቱ አመሻሽ ላይ ሁሉም በተሰበሰቡበት አባወራው ጉሊያውን በእሳት ይለኮሳሉ፡፡ ወጣቶችም ዙሪያውን በመክበብ ባህላዊ ጭፈራ ይጨፍራሉ። በቀጣዩ ቀንም በቤት ውስጥ የተረፈው ሥጋ ተዘልዝሎ ይጠበስና ማባያ ተዘጋጅቶ ሁሉም ተሰብስበው በመመገብና በመዝናናት በአንድነት ያሳልፋሉ። ከጊፋታ ቀጥሎ የሚመጣው ሦስተኛው ቀን ወይም ጪሻ ጋላሳ ደግሞ በጊፋታ ወቅት ብቻ የሚፈካ፣ በወላይታዎች አባባል ኮርማ-ጪሻ የሚባለውን ነጭ አበባ ወይም የጊፋታ አበባ ይዞ በመሄድ ዘመድ የሚጠያየቅበት ዕለት ይሆናል። ከጊፋታ ሦስተኛው ቀን ጀምሮ ደግሞ በተከታታይ ለሁለት ሳምንታት ወጣት ወንዶችና ወጣት ሴቶች በአካባቢው ታዋቂ ሽማግሌ ደጃፍ ተሰብስበው በጋዚያ ጨዋታ ያሳልፋሉ፡፡ ይህም ጋዜ ኦሩዋ በመባል ይታወቃል። ለረጅም ጊዜ የቆየው የበዓል ዝግጅትና አጠቃላይ የጊፋታ በዓል ሥነ ሥርዓት የጋዜ ኦሩዋ ጨዋታ ሲጠናቀቅ ጉሊያ በማቀጣጠል ለሚመጣው ዓመት በዓል በሰላም እንዲያደርሳቸው በመመኘት ይሸኛሉ። ታዲያ ይህ የወላይታ ብሔር አዲስ ዓመት በዓል የሆነው "ጊፋታ" በ2018 ዓ.ም ታኅሣሥ ወር ላይ በሕንድ ሀገር ኒው ዴልሂ ከተማ በተካሄደው በ20ኛው የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ጥበቃ የመንግሥታት ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት በተባበሩት መንግሥታት ትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግቧል። በዓሉ ዕድሜ፣ ጾታ፣ ሃይማኖትና ማኅበራዊ ደረጃን ሳይለይ የሚያሳትፍ መሆኑ፣ ቅርሱ ተላልፎ ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ እንዲሁም በትምህርት ቤቶችና በሚዲያዎች ለትውልድ በመሸጋገር ላይ የሚገኝ መሆኑ እና ሌሎች መመዘኛዎችን በማሟላቱ ነው በዩኔስኮ መመዝገብ የቻለው። "ጊፋታ" የዓለም ሕዝብ ሀብት ሆኖ በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ የሚከበረው የዘንድሮ መርሃ ግብር በወላይታ ዘመን አቆጣጠር መሰረት የወላይታ ዘመን መለወጫ ወይም "ጊፋታ 1" ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም በድምቀት ይከበራል።
ትንታኔዎች
የግብፅ የውሃ አባካኝነት እና ያረጀው የቅኝ ግዛት እሳቤ
Sep 22, 2026 26
ግብፅ ለዓባይ ወንዝ ፍሰት ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የሌላት ብትሆንም፣ የዓባይን ውኃ በማባከን ትታወቃለች። ይህ በዓባይ ወንዝ እውነት ላይ ያለ አስገራሚ ተቃርኖ ነው። በርካታ የውሃ ሃብት ተንታኞችና ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ በግብፅ ግድቦች ውስጥ የሚከማቸው ውኃ ሀገሪቱ ባላት እጅግ ሞቃታማ የአየር ንብረት ምክንያት በትነት ይባክናል። የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ውኃዎች እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ (GERD) አማካሪ ቡድን ሰብሳቢ፣ እንዲሁም የምሥራቅ ናይል አህጉራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ እንደሚገልጹት፣ የታላቁ አስዋን ግድብ የፈጠረው የናስር ሀይቅ የሚገኘው በዓለም ላይ በጣም ሞቃት እና ደረቅ ከሆኑት የሰሃራ በረሃ ክፍሎች ውስጥ ነው። በዚህም አስዋን ግድብ በየዓመቱ በትነት ምክንያት ብቻ ከ15 እስከ 16 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ያጣል። ከዚህ በተጨማሪ በግብፅ የዓባይ ሸለቆ እና ዴልታ አሁንም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የግብርና መሬት የሚጠጣው በባህላዊ የጎርፍ/የቦይ መስኖ ዘዴ ነው። ይህም ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን በትነት፣ በመሬት ሰርገት እና ባልተጣጠመ ስርጭት ምክንያት ያባክናል። በግብጽ እንደ ጠብታ መስኖ እና ረጭ መስኖ (Sprinkler) ያሉ ዘመናዊና ውሃ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች ትግበራ አሁንም አነስተኛ ነው። በሌላ በኩል በረሃን ወደ እርሻ መሬት ለመቀየር የተቀረፁ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በረጅም ክፍት ካናሎች ውሃን ወደ በረሃ በመሳብ ለማልማት የሚደረገው ጥረት፣ ውሃው ክፍት በሆኑ ካናሎች በሚጓዝበት ወቅት በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በትነት እና ወደ አሸዋማ መሬት በመስረግ ከፍተኛ ውሃም ለዘመናት እያባከነች ትገኛለች። ይህ አልበቃት ብሎ ግብፅ በደረቅና ከፍተኛ የትነት መጠን ባላቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የውሃ ፍጆታ ያላቸውን ሰብሎች በስፋት ታመርታለች። እንደ ሩዝ እና የሸንኮራ አገዳ ያሉ ከፍተኛ ውሃ የሚፈልጉ ሰብሎችን በበረሃማ የአየር ጠባይ ውስጥ በጎርፍ መስኖ ማልማት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሜትር ኪዩብ ውሃን ታባክናለች። በተቃራኒው ውኃን በኢትዮጵያ ጥልቅ፤ ጠባብ ሸለቆዎች ውስጥ እና አመቺ የአየር ንብረት ባለበት አካባቢ ማከማቸት የትነት መጠንን ለመቀነስ እጅግ ከፍተኛ ሚና አለው። ዋናው የውኃ ማከማቻ በኢትዮጵያ መሆኑ በሙቀት ሊባክን የሚችለውን በርካታ መጠን ያለው ውኃ ከማዳኑም በላይ፣ ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚለቀቀውን የውኃ መጠን አስተማማኝና የተረጋጋ እንዲሆን ያደርገዋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበት ቦታ ቀዝቃዛና ጥልቅ ሸለቆ በመሆኑ፣ ውሃን በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ ከሚገኘው የአስዋን ግድብ ይልቅ እዚያ መያዝ በትነት የሚባክነውን የውሃ መጠን በእጅጉ ይቀንሳል። ይህም ለግብፅም ጭምር ውሃን የሚቆጥብ ሳይንሳዊ እውነታ ነው። ሳይንሳዊ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግብፅ አሁንም ያረጀና የፈጀ የቅኝ ግዛት እሳቤን በመያዝ በዓባይ ወንዝ ላይ የተሳሳተ አቋም ማራመዷን ቀጥላለች። ግብፅ አሁንም በ1929 እና 1959 በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረጉ፣ ኢትዮጵያን ያገለሉ ፍትሃዊ ያልሆኑ ውሎች ላይ በመመስረት የከልካይነት መብት አለኝ የሚል ጊዜ ያለፈበት እሳቤ ለማራማድ እየጣረች ነው። የኢትዮጵያን ዕድገትና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ለግብፅ እንደ ስጋት አድርጎ በመሳል፣ የዓባይን ጉዳይ የደህንነት ስጋት በማስመሰል ጫና ለመፍጠር የምታደረግው ከንቱ ሙከራም ከዚህ ካረጀ እሳቤ የመነጨ ነው። ነገር ግን ካይሮ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ መብት ላይ ጫና ለማሳደር ከምታደርገው ከንቱ ጥረት ይልቅ፣ የራሷን የውሃ አጠቃቀም ማዘመን፣ ዘመናዊ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ጥቅም እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትብብር ማድረግ የረጅም ጊዜ መፍትሔ ነው።
የዓባይ እናት ኢትዮጵያ የጠላትን ሰንሰለት እየበጣጠሰች ጉዞዋን ትቀጥላለች
Sep 22, 2026 62
86 በመቶ የሚሆነውን የዓባይ ውሃ አመንጭታ የምታፈሰው ኢትዮጵያ ለዘመናት ልጆቿ በጥም፣ በጨለማና በድህነት ሲማቅቁ ዝም ብላ እንድታይ ተፈርዶባት ነበር። በአንጻሩ በዓለም አቀፍ መድረኮች «የውሃ እጥረት ስጋት አለብኝ» እያለች የምትለፈልፈው ካይሮ፣ ተበዳይ መስሎ የመቅረብ ትርክቷ ከጀርባ ያለውን እውነተኛ የስግብግብነትና የቀጣናዊ የበላይነት ፍላጎት ለመሸፈን የተበጀ ጊዜ ያለፈበት ጭንብል ነው። ካይሮ ውሃ እያባከነች፣ ኢትዮጵያውያን የጓሮ አትክልት እንዳያለሙ ለመከልከል ተሞክሯል። ያ የጠላት ሰንሰለት ግን በሕዳሴ ግድብ ተበጣጥሷል። በነገራችን ላይ ግብፅ ለምዕተ ዓመታት የሚበቃት ግዙፍ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት አላት። በኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት ዝናብ ቢቋረጥ እንኳ የማይነጥፍ ተፈጥሯዊ የውሃ ክምችት ይዛ ሳለች፣ የዓባይን ውሃ በግዴለሽ አጠቃቀም ታባክናለች። ይህ ደግሞ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። በየበረሃው ቅንጦተኛ ሰፊ ረግረጋማ መሬት እንዳላት በማስመሰል ከፍተኛ ውሃ የሚጠቀሙትን ሸንኮራ አገዳና ሩዝ ታመርታለች። አዳዲስ የቅንጦት ከተሞችንና የመዝናኛ ገንዳዎችን እየገነባች ውሃ ታባክናለች። በሌላ በኩል ግን ኢትዮጵያውያን ለዕለት ጉርሳቸውና ለቤታቸው መብራት እንኳ ወንዞቻቸውን እንዳያለሙ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ያለማቋረጥ ትነዛለች። ሌሎች የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በድህነት እንዲማቅቁም ቀን ከሌሊት ታሴራለች። በዚህም ግብፅ የራሷን የቅንጦት አኗኗር እያስፋፋች የሌሎችን ህልውና ለማነቅ ከምታደርገው የሚልቅ ፍርደ ገምድልነት የለም። የዓባይን ውሃ ፍሰት ለመጠበቅ ከ50 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን እየተከለች ያለችውን ኢትዮጵያን ማመስገን ሲገባት፣ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማናጋት የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም። ቅጥረኞችን በመጠቀም ሱዳንን ለማፍረስና ኢትዮጵያን የማዳከሚያ መተላለፊያ ለማድረግ ትሰራለች። በቀይ ባሕር አካባቢ ያለ ማንኛውም ሀገር እንዲበለጽግና እንዲያድግ አትፈልግም። ለዚህም ባንዳ እየመለመለች የቀጣናው ሰላም ዋና ጠንቅና የጥፋት መሪ ሆናለች። ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገራት በሉዓላዊ ሀብታቸው ላይ መወሰንና ማልማት ጀምረዋል። ይህ ደግሞ ውሃ አባካኝነቷን የረሳችውን ግብፅ የጣረ ሞት ጩኸትና ቅዠት ውስጥ ከቷታል። የውሃ ሚኒስትሯና ሌሎች የዘርፉ ሃላፊዎች ደግሞ ሙሾ አውራጅ ሆነው መጥተዋል። ለዓባይም ሆነ ለናይል ጠብታ አበርክቶ የሌላት ግብፅ የላይኛውን ተፋሰስ ማለትም የወንዙን መፍለቂያ ሀገራትን ሳታስፈቅድ አስዋንን የገነባችው ካይሮ፣ ዛሬ በሰው ቤት ፈትፋች ልሁን፣ ግድብ ስትገነቡም እኔን ፈቃድ ጠይቁ ብትልም፤ ጊዜውም ሁኔታውም አልፈቀዱም ወደፊትም አይፈቅዱም። ጭንብሏም ካባዋም ከላይዋ ላይ እየወለቁ የእውነትና የፍትሕ መንገድ እየተጠረገ መጥቷል። የኢትዮጵያ የመልማት እቅድና የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀም ጽኑ ፍላጎት በምንም ዓይነት የዛቻና የከሰረ ፕሮፓጋንዳ ጋጋታ አይገታም። ጊዜው ተቀይሯል፤ የኃይል ሚዛኑም በጽናትና በፍትሃዊነት ተተክቷል። የዓባይ እናት በልማት ሰልፍ ላይ ናት። የሕዳሴ ግድብ ደግሞ በዓባይ ላይ የመጀመሪያው ሆኗል። ይቀጥላል።
የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ትንሳኤ ፤ከትናንት ፈተናዎች ወደ ዛሬ ድሎች
Sep 21, 2026 279
ዘመን ሲለወጥ ወቅቶች ሲተኩ ሁልጊዜም አዳዲስ ተስፋዎች እና እቅዶችን ይዘው ይመጣሉ። ይህ ለውጥ ከቀናት አቆጣጠር ከዘመናት ሽግግር የተሻለ ፋይዳ እንዲኖረው ወቅቱን የሚዋጅ ስራ ማከናወን የግድ ይላል። ወቅቱ ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት የገነባችውን ሁለንተናዊ የለውጥ ምዕራፍ እና ከማሽቆልቆል ወደ ከፍታ የተደረገውን ድል አድራጊ ጉዞ በግልጽ የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያ ጉዞ በኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረዶች እና በዓለም አቀፍ ጫናዎች የተሞላ ነበር። ኢትዮጵያን ትናንት የገጠሟት ፈተናዎች ሀገሪቱን ወደ አስቸጋሪ አዙሪት ውስጥ ከተዋት ቆይተዋል። የዛሬው እውነታ ግን ከትናንቱ ፈተና ፈጽሞ የተለየ ነው። የቁልቁለቱ ጉዞ ሙሉ በሙሉ ተቀልብሶ ሀገሪቱ በሁሉም ዘርፎች ወደ እውነተኛ የማንሰራራት ከፍታ ተሸጋግራለች። የዘመን ንጽጽር ማዕቀፉ ትናንት በስጋትና በቁጭት የታጀበውን ጉዞ ከዛሬው የብልጽግና ተስፋ ጋር በማቀናጀት ነገን ብሩህ እያደረገ ይገኛል። በኢኮኖሚው መስክ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለዚህ ታሪካዊ ከፍታ ትልቅ መሠረት የጣለ ዋናው ምዕራፍ ነው። ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት ሲተገበር የነበረውና ለኮንትሮባንድ እንዲሁም ለጥቁር ገበያ መፋፋም ምክንያት ሆኖ የቆየው የምንዛሬ ተመን ተቀይሯል። በገበያ የሚመራ የምንዛሬ ሥርዓት በይፋ መዘርጋቱ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የወጪ ንግድን ለማንሰራራት የሚያስችል ሰፊ በር ከፍቷል። የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወር ሂደትም ሌላኛው የገበያ ተወዳዳሪነት ማሳያ ነው። የቴሌኮም ዘርፍ ለውጭ ውድድር ክፍት መደረጉ እና የኢትዮ ቴሌኮም ከፊል አክሲዮን ለሕዝብና ለውጭ ኩባንያዎች መሸጡ የቀድሞውን የቁጥጥር ስርዓት ሰብሮታል። ይህ እርምጃ የአገልግሎት ጥራትን ከማሻሻል ባለፈ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አዲስ ንቃት ፈጥሯል። የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን ዲጂታላይዝ ማድረግ ሌላው የለውጥ ምሰሶ ነው። እንደ ሲቢኢ ብር እና ቴሌብር ያሉ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች ከመንግሥት አገልግሎቶች ጋር በመቀናጀታቸው የገቢ አሰባሰብ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ አሳድገዋል። በዚህም የተነሳ በውጭ ዕርዳታ እና ብድር ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የነበረው የሀገሪቱ ገጽታ ተለውጦ የውስጥ አቅምን ማዕከል ያደረገ ፋይናንስ እውን ሆኗል። ከኢኮኖሚ ማሻሻያው ጎን ለጎን በግብርናው ዘርፍ የታየው እመርታ ሀገሪቱን ከምግብ ዋስትና እጥረት ራስን ወደ መቻልና የምግብ ሉዓላዊነትን ወደ ማረጋገት አሸጋግሯታል። በኢትዮጵያ የመስኖ ልማት ጉዞ ቀደም ሲል ከነበረበት መጓተት ወጥቶ የመስኖ ሽፋን ከነበረበት 490 ሺህ ሄክታር ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ከፍ ማለቱ ታሪካዊ ስኬት ነው። በበጋ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ድል ሀገሪቱ ከውጭ ታስገባው የነበረውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ ማስቆም እንድትችል አድርጓታል። ከዚህም አልፎ ምርቱን ለጎረቤት ሀገራት መላክ መጀመሯ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን በተግባር ያረጋገጠችበት ማሳያ ነው። ግብርናው ከባህላዊ የዝናብ ጥገኝነት ተላቆ የሀገሪቱ የዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር ወደመሆን እየተሸጋገረ መጥቷል። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ከፍታ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ባለፉት ስምንት ዓመታት 56 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ ይህ መርሐ ግብር ለፍራፍሬ ልማት እና ለቡና ምርታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጉ የገበሬውን ገቢ አሳድጓል። ተራቁተው የነበሩ መልክዓ ምድሮች አረንጓዴ እና ለምለም ገጽታን ተላብሰዋል። የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርም የእንስሳት ተዋጽኦን በቤት ውስጥ ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን አረጋግጧል። ወተት፣ ሥጋ፣ ማር እና እንቁላል እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎች በስፋት እንዲመረቱ በማድረግ የዜጎችን የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለማሳደግ ተችሏል። በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ያመጣው ለውጥ የላቀ ነው። ቀደም ሲል በጥሬ ዕቃ እጥረትና በኃይል መቆራረጥ አሽቆልቁለው የነበሩ የአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች በፋይናንስና በፖሊሲ ተደግፈዋል። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወደ ሙሉ ማምረት አቅማቸው በመመለሳቸው የሀገር ውስጥ ምርት እያደገ መጥቷል። በከተሞች የተከናወነው የኮሪደር ልማት የዕድገቱ ሌላኛውመገለጫ ነው። በአዲስ አበባ የተጀመረውና ወደ ክልል ዋና ዋና ከተሞች የተሻገረው ይህ ልማት የከተማ መሠረተ-ልማትን አዘምኗል። የእግር መንገድ፣ የብስክሌት መስመር፣ አረንጓዴ ስፍራዎች እና ውብ መዝናኛዎች መዘርጋታቸው ከተሞችን ለኑሮ፣ ለንግድ እና ለቱሪስት መስህብነት ምቹ አድርጓቸዋል። በዲፕሎማሲው መስክም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያሳየችው ተፅዕኖ ፈጣሪነት የላቀ ከፍታ ላይ ደርሷል። ሀገሪቱ በዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢኮኖሚዎች ስብስብ የሆነው የብሪክስ አባል መሆኗ የመደራደር አቅሟን አጠናክሮታል። የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እና ተጠናክሮ የቀጠለው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የቀጣናው የትስስር ማዕከልነቷን አረጋግጧል። የፖለቲካው ትርክት ከብሔር ማዕከልነት ወደ ሃሳብ እና መርህ መር ፖለቲካ መሸጋገሩ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን አጽንቷል። ይህ የሐሳብ እና የፖለቲካ ሽግግር ዜጎች በልዩነት ውስጥ በአብሮነት እንዲቆሙ እና ለሀገራዊ የጋራ ግቦች እንዲሰለፉ ትልቅ እገዛ አድርጓል። አዲሱ ዓመት አዲስ መንግስት የሚደራጅበት፣ አዳዲስ ሀገራዊ ግቦች የሚቀመጡበት እና የኢትዮጵያ ህዝብ ለላቀ ውጤት ራሱን የሚያዘጋጅብበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው። ሕዝቡ ባለፉት ዓመታት የጣለውን የሰላም እና የልማት መሠረት በማስቀጠል፣ ለሀገሩ የብልጽግና ጉዞ እየሰራ ይገኛል። ይህ የዘመን ሽግግር የትናንቱን ታሪካዊ ቁልቁለት ሰብሮ ኢትዮጵያን ወደ ብሩህ የማንሰራራት እና የብልጽግና ከፍታ የወሰደ እውነተኛ የድል ማሳያ ነው። ሕዝብ እና መንግስት በጋራ በመሰለፍ የነገዋን የኢትዮጵያ ከፍታ እውን እያደረጉ ይገኛሉ።
የዓለም አቀፍ ዲጂታል ሽግግር ፈጣን አብዮት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ፍኖት!!
Sep 19, 2026 355
በታዬ ለማ ዓለም ከኢንዱስትሪ አብዮት ወደ ዲጂታል፣ ከዲጂታል አብዮት ደግሞ ወደ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተጓዘችበት ፈጣን ሽግግር የሰውን ልጅ የኑሮ፣ ሥራና የሀሳብ ምኅዳር እየቀየረ ይገኛል። ዛሬ ላይ ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚደግፍ አንድ ዘርፍ ብቻ አይደለም፤ የምርታማነት፣ የፈጠራ፣ የውድድርና የሀገራዊ አቅም መሠረት እየሆነ መጥቷል። በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ሽግግር አዲሱ የዕድገት ሞተር ሲሆን የጤና፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ዲጂታል ግብይት፣ ትምህርትና የመንግሥት አገልግሎቶችን መደገፍ ከጀመረ ሰነባብቷል። ስለዚህ የወቅቱ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር በተሻለ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ ነፃነት እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እውነት ጋር የተጣጣመ ትግበራን ማዕከል ያደረገ ሆኗል። ይህ የዓለም አቀፍ ሽግግር ለአፍሪካ በርካታ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል። አህጉሪቱ በአንድ በኩል የዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የኤሌክትሪክና የኢንተርኔት ተደራሽነት፣ የዳታ አቅምና የሰው ኃይል ክፍተቶች አሏት። በሌላ በኩል ወጣት የሰው ኃይል፣ ታዳጊ የቴክኖሎጂ ገበያና በብዙ ዘርፎች አሁንም ያልተሟሉ ፍላጎቶች ስላሏት የፈጠራ ዕድልን ያበረታታል። ይህንን እውነት የተገነዘበው የአፍሪካ ሕብረት በ2024 የአህጉራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ስትራቴጂን ቀርጿል። ስትራቴጂውም የሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) በአፍሪካ የልማትና የሕዝቦቿ ፍላጎት እንዲሁም በአህጉሪቷ እውነታ ላይ የተመሠረተ ሆኖ እንድትጠቀምበት የሚያበረታታ ነው። በዚህም አፍሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን በዳታ፣ በምርምር፣ በሶፍትዌር፣ በሰው ኃይልና በአፍሪካዊ መፍትሔዎች ላይ የራሷን አቅም የምትገነባበትን ዕድል ይፈጥራል። በ2025 በአዲስ አበባ በተካሄደው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ልማትና ቁጥጥር ከፍተኛ ደረጃ ውይይት ላይ የአፍሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ስትራቴጂክ ልማት የዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የዳታ ጥራት፣ የክህሎትና ምርምር አቅምን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ተሰጥቷል። ኢትዮጵያ፤ ከዲጂታል 2025 ወደ ዲጂታል 2030 ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍና የአፍሪካን ፈጣን የዲጂታል ሽግግር በመገንዘብ የዲጂታል ዘርፍ የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት አካል በማድረግ መጓዝ ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ዋና ትኩረቱን የዲጂታል ምኅዳር ግንባታ፣ የዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ የዲጂታል ክፍያንና የመንግሥት ዲጂታል አገልግሎትን ማጠናከር ማዕከል በማድረግ በሁሉም ዘርፍ የታለመለትን ዓላማ በማሳካት ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ተሸጋግሯል። ይህ ሽግግር ከአንድ ስትራቴጂ ወደ ሌላ የሚደረግ የስያሜ ለውጥ ብቻ አይደለም። ከዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ጥልቀት የሚደረግ ሽግግር እንጂ። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም የዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋፋትን፣ የመረጃ አስተዳደርን፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) እና የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን በቁልፍ ግብ ይዟል። በዚህም በሁሉም ዘርፍ ተጨባጭ ውጤቶች ማስገኘቱን ቀጥሏል። የዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ፤ የኢትዮጵያ ሽግግር አስቻይ ምኅዳር!! የዲጂታል አቅም በመተግበሪያና ሶፍትዌር ልማት ብቻ የሚገነባ አይደለም። የኃይል፣ ኢንተርኔት፣ ዳታ ማዕከላት፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የሳይበር ደኅንነት መሠረተ ልማቶች ግንባታም መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው። በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተፋጠነው የግንኙነት መሠረተ ልማት እመርታ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን በጽኑ መሠረት አንጾ አልፏል። ለአብነትም በፈረንጆቹ 2025 መጨረሻ 97 ሚሊዮን የሞባይል ተመዝጋቢዎች፣ 57 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችና 1 ሺህ 30 ከተሞች የ4G የኢንተርኔት መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ሆነዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል፤ የመንግሥት አገልግሎት ወደ ዜጎች በር እና የእጅ ስልክ የዲጂታል ሽግግር የመጨረሻ ትርጉም ዜጎች በሚያገኙት አስቻይ የአገልግሎት ምኅዳር ላይ ይመዘናል። በዚህም የመሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ከተለያዩ ተቋማት የሚገኙ አገልግሎቶችን በአንድ የዲጂታል ምኅዳር ለማቀናጀት የሚያግዝ እርምጃ ሆኖ ከመጣ ሰነባብቷል። ይህ ዲጂታል ምኅዳር የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶች በአንድ ላይ በማቀናጀት ዜጎች ያለ እንግልት በቀላሉ የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል ፈጥሯል። የዲጂታል ሽግግሩ ዋና ዓላማ የሕዝብን እርካታ ማረጋገጥ ነው። በዚህም የመሶብ መርሃ ግብር በአካል በመሶብ የአንድ ማዕከላት፣ በጋዝና ኤሌክትሪክ በሚሠሩ መኪኖች በተንቀሳቃሽና የተቀናጀ አገልግሎት በሞባይል መተግበሪያ የመንግሥት አገልግሎቶች ለሕዝብ ቅርብ ሆነዋል። ይህም የሕዝብን እንግልት በማስቀረት የመንግሥት አሠራር ግልጽነትንና መልካም አስተዳደርን በማስፈን በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ተጨባጭ ለውጥ እመጣ ይገኛል። በዚህም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በዲጂታላይዜሽን፣ በፋይዳቨርስና ኢትዮ-ኮደርስ በሕዝብና መንግሥት መካከል መተማመንን በማጎልበት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማት መስክ አስቻይ የፈጠራና ክህሎት ምኅዳር እየፈጠረ ይገኛል። ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI)፤ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል መፍትሔን የማፍለቅ ህልም ዓለም በዲጂታል ሽግግር አዲስ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። በተለይም ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ከቴክኖሎጂ ዘርፍ አልፎ በኢኮኖሚ፣ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በፋይናንስና በመንግሥት አገልግሎት የአሠራር ሥርዓቶችን በማቀላጠፍና በማዘመን ጉልህ ሚና እየተወጣ ነው። አፍሪካም ከዓለም አቀፍ የውድድር ምኅዳር ውጭ አይደለችም። ይህም ከአህጉሪቷ ፍላጎትና ነባራዊ እውነታ ጋር የተቆራኘ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መፍትሔን ማፍለቅ እንደሚያስፈልግ የሚጠይቅ አዲስ ምዕራፍ ነው። ኢትዮጵያም የዲጂታል ሽግግርን ከአገራዊ የልማት ግቦቿ ጋር በማስተሳሰር በእመርታዊ ለውጥ እየተጓዘች ይገኛል። ለዚህም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሁነኛ መሠረትን ጥሏል። የኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ጉዞም በዲጂታል 2025 የተጣለውን መሠረት ወደ ዲጂታል 2030 በማሸጋገር ጭምር ፈጠራና ክህሎትን የሚያበለጽግ ምኅዳርን ፈጥሯል። ይህም የዲጂታል 2030 ራዕይና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማት (AI) በአንድ ሰንሰለት የሚገነቡበትን አዲስ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ ከፍቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው መሾማቸው ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለውን ስኬት አሳይቷል። የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ፤ የኢትዮጵያ አዲስ አህጉራዊ የልህቀት ማዕከልነት ራዕይ የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁ ተሰይሞ ወደ ሥራ የሚገባ የይስሙላ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም አይደለም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የምርምር፣ ክህሎትና የፈጠራ ማዕከል በማድረግ የመጪው ዘመን ፍኖት የሚያበስር ተቋም ነው። ተቋሙም ከኢትዮጵያ ባሻገር በአፍሪካውያን ቋንቋዎችና የማኅበረሰብ ዕውቀቶች ላይ የተመሠረተ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI)፣ ሀገር በቀል መፍትሔ አመንጪ ምርምሮች፣ የዲጂታል ትስስርና ፈጠራን የሚያበረታታ ወሳኝ የመጪው ዘመን የተስፋ ብርሃንን ያነገበ ነው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ፤ ኢትዮጵያ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ በሰጠችው ትኩረት የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ እንዲወለድ ያደረገ ነው። የአፍሪካን አህጉር በይበልጥ የሚያግዙ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቶችን በማበልጸግ ኢትዮጵያን አህጉራዊ የዘርፉ የልህቀት ማዕከል የሚያደርጋት ነው። ለዚህም ከብሪክስ አባል ሀገራት የትምህርት፣ የቴክኖሎጂ እና የምርምር ተቋማት ጋር ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ጉዞ መነሻውን ከሀገራዊ የዲጂታል ሽግግር አጀንዳ በማድረግ ወደ አህጉራዊ የቴክኖሎጂ ትብብር የሚሸጋገር ተስፋን የሰነቀ ነው። የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲም የዚህ ጉዞ ተቋማዊ መገለጫ ሆኗል። ይህም ኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የቴክኖሎጂ ፈጠራ ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን ለአፍሪካ እውነታ የሚመጥኑ መፍትሔዎችን የምታመነጭ የምርምርና የፈጠራ ማዕከል የመሆን ራዕይ የሚያጠናክር ይሆናል፡፡
ልዩ ዘገባዎች
በታዳጊው የተሰራችው መኪና
Jun 17, 2026 13604
ለአዳዲስ ፈጠራ የማይታክተው ልጅዓለም ንጉሱ ትውልድና እድገቱ በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ወረዳ ፀመራ ቀበሌ ነው። ከሕጻንነቱ ጀምሮ ፈትቶ መግጠምና አፍርሶ መስራትን እየተለማመደ የመጣው ልጅዓለም፤ ከቤት እስከ ትምህርት ቤት ያልተቋረጠ ፈጠራውን አጠናክሮ ቀጥሏል። ከዚህ ቀደም ለሚማርበት ፀመራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከወዳደቁ ቁሶች የተለያዩ ቅርፃ ቅርፆችን በመስራት የፈጠራ አሻራውን አኑሯል። በትምህርትና በፈጠራ ሥራው ገፍቶበት አሁን ላይ የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ልጅዓለም እንጨት ገጣጥሞ መኪና በመስራት ያለውን የጥበብና ፈጠራ ክህሎት አሳይቷል። በታዳጊው የተሰራችውና በፔዳል የምትነዳው መኪና ሁለት ሰዎችን የማያዝ አቅም አላት። በቀጣይ ተጨማሪ ቁሶችን በማቅረብና በተለያየ መንገድ የሚያግዘው ካገኘ መኪናዋ በዲናሞ እንድትንቀሳቀስ ለማድረግ መዘጋጀቱን ተናግሯል። የተሽከርካሪውን አካል የገጣጠመው በአካባቢው አጠራር "እንቋ" የተሰኘ ዛፍ እንጨትን በመጠቀም ሲሆን የተሽከርካሪውን እግር ለማዘጋጀት ደግሞ የዋርካ ዛፍ ተጠቅሟል። በዚህም መሰረት የልጅዓለም መኪና የመብራትና የመሪ ስራዋ ተጠናቆ ሁለት ሰዎችን ጭና መንቀሳቀስ እንደምትችል በተግባር አሳይቷል። "በቀጣይ የሚያግዘኝና የሚደግፈኝ ካገኘሁ በዲናሞ የሚሰራ ተሽከርካሪ ለመስራት ዝግጁ ነኝ" ያለው ጥበበኛው ተማሪ ወደ ፊት ለሀገሬ ብዙ የመፍጠር ህልም አለኝ ብሏል። የፀመራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ግርማ ጌቴ፤ ከዚህ በፊት ተማሪ ልጅዓለም በትምህርት ቤቱ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች እንዳሉት አስታውሰው ትምህርቱንም ፈጠራውንም አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል። የፈጠራ ክህሎቱን፣ ተሰጥኦውንና ፍላጎቱን ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ ተከታትያለሁ ያሉት መምህሩ የሳይንስ ትምህርቱንና የግል ክህሎቱን ደምሮ ለአዳዲስ ሥራዎች እየተጋ መሆኑን አንስተው፣ የመኪና ፈጠራውም ይህንኑ በተግባር ያሳየበት ነው ብለዋል። የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ ከተደረገለት የተሻለና ውጤታማ ሥራ መስራት እንደሚችል ገልጸው ለሚፈጥሩ ወጣቶች በጥሩ ምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል። በእንጨት የተገጣጠመችው መኪና በሁላችንም ድጋፍ የዲናሞ፣ የብረትና ሌሎች አስፈላጊ ቁሶች ከተሟሉላት በታዳጊው ጥበብ የተሻለች መኪና ሆና ልትሰራ ትችላለች ሲለም እምነታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ስንት ዓይነት የአዕዋፍ ዝርያዎች አሉ?
Oct 13, 2025 22633
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአዕዋፍ ኑሮ ምቹ እና ተስማሚ ሁኔታዎች ካሉባቸው ሀገራት አንዷ ናት። በፈረንጆቹ 2024 እና 2025 የተደረጉ የጥናት ውጤቶች እንዳመላከቱት፤ በኢትዮጵያ ከ881 እስከ 926 የሚደርሱ የአዕዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ። ይህ አሃዝ ነዋሪ እና ፍልሰተኛ የአዕዋፍ ዝርያዎችን እንደሚያካትት በኢትዮጵያ ዱር እንስሣት ጥበቃ ባለሥልጣን የጥበቃ ቦታዎችና የብሔራዊ ፓርኮች ዋርደን ፋንታዬ ነጋሽ ለኢዜአ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለአዕዋፋት ኑሮ ምቹና አስፈላጊ ከሆኑ ሀገራት መካከል እንደምትመደብም ጠቅሰዋል። 639 ነዋሪዎችን እና 224 ወቅታዊ ፍልሰተኞችን ጨምሮ 926 የአዕዋፍ ዝርያዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ባሳለፍነው ነሐሴ ወር ላይ የተደረገ ጥናት ውጤት አመላክቷል ነው ያሉት። ከእነዚህ መካከል በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙት የአዕዋፍ ዝርያዎች ቁጥራቸው ከ18 እስከ 20 እንደሚደርስ ጠቁመዋል። አማካኝ የወፎች ዕድሜ እንደ ዝርያ፣ መጠን እና አካባቢ ስለሚለያይ ለሁሉም ወፎች አንድ አማካይ ዕድሜ አለመኖሩንም አንስተዋል። ትንሽ ዕድሜ የሚኖሩት የድንቢጥ ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቅሰው አማካኝ ዕድሜያቸውም ሦስት ዓመት መሆኑን ተናግረዋል። እንደ አልባትሮስ (Albatrosses and Some Parrots) ያሉ ትላልቅ የአዕዋፍ ዝርያዎች እና አንዳንድ በቀቀኖች ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሊኖሩ እንደሚችሉ አመላክተዋል። መጠን፣ ዝርያ እና የመኖሪያ አካባቢ በአዕዋፍ የሕይወት ዘመን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩም አስገንዝበዋል። በዚህም መሠረት ትልልቅ ወፎች ከትንንሽ ወፎች የበለጠ ረጅም ዕድሜ ይኖራሉ ብለዋል። እንደ ዝርያቸው የሚወሰን ቢሆንም አዕዋፋት ከቀዝቃዛ እስከ ሞቃታማ የአየር ንብረት ያላቸው አካባቢዎች ላይ መኖር እንደሚችሉም አንስተዋል። አንድ ተመራጭ የአየር ንብረት የላቸውም፤ አብዛኞቹ የአዕዋፍ ዝርያዎች የተረጋጋ፣ አስተማማኝ የምግብ አቅርቦት ለማግኘት እና ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ተስማሚ ሁኔታዎችን የሚቸር የአየር ሁኔታን ይመርጣሉ ነው ያሉት። በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ 11 ሺህ 100 የሚጠጉ የአዕዋፍ ዝርያዎች እንዳሉም ነው ያስረዱት።
በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወፎች በፍልሰት ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ
Oct 11, 2025 15651
በዮሐንስ ደርበው በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ፍልሰተኛ ወፎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል። የዓለም የስደተኛ ወፎች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ "ምቹ የመኖሪያ ቦታ፤ ለአዕዋፋት አኗኗር ምቹ የሆኑ ከተምች እና ማኅበረሰብ" በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ በመላው ዓለም እየተከበረ ነው። በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የጥበቃ ቦታዎችና የብሔራዊ ፓርኮች ዋርደን ፋንታዬ ነጋሽ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የዓለም የፍልሰተኛ ወፎች ቀን የሚከበረው ስለ ፍልሰተኛ ወፎች ያለ የማኅበረሰብ ግንዛቤን ለማሳደግ እና በእንቅስቃሴያቸው ወቅት ተገቢ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጎልበት ነው። ለምግብና ለመራባት በይበልጥ ምቹ ሁኔታ በመፈለግ ብሎም ከወቅታዊ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች (ቅዝቃዜና ሙቀት ) ለማምለጥ ወፎች ምቹ ወደሚሉት አካባቢ እንደሚፈልሱ አንስተዋል። በዚህም መሠረት ከአውሮፓ፣ እስያ፣ ከተለያዩ የአፍሪካ እና ባልካን ሀገራት በየዓመቱ በተለያዩ ወቅቶች በሚሊየን የሚቆጠሩ ወፎች በፍልሰት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ጠቁመዋል። አንዳንድ ፍልሰቶች አጭር መሆናቸውን ገልጸው፤ አኅጉራትን፣ በረሃዎችን እና ውቅያኖሶችን ማቋረጥ የግድ የሚሆንባቸው ረጅም ርቀት የሚሸፍኑ ፍልሰቶች እንዳሉም አስገንዝበዋል። ትክክለኛ ዓመታዊ ቆጠራ ላይ የተመሠረተ አሀዛዊ መረጃ ማግኘት ቢያዳግትም፤ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ መስመር አማካኝነት በየዓመቱ በርካታ ፍልሰተኛ ወፎች ወደ ኢትዮጵያን ይመጣሉ ብለዋል። በዚህም መሠረት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚልቁ ፍልሰተኛ ወፎች በኢትዮጵያ በኩል የሚያልፈውን የስምጥ ሸለቆ መስመር ይጠቀማሉ ነው ያሉት። በተጨማሪም 199 ገደማ ዝርያዎች ከአውሮፓና እስያ እንዲሁም 47 ዓይነት ዝርያዎች ከአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት በፍልሰት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ እና ከወራት ቆይታ በኋላ ወደተለያዩ አቅጣጫዎች ተመልሰው እንደሚሄዱም አንስተዋል። እንደዝርያቸው ቢወሰንም ከቅዝቃዜ እስከ ሞቃታማ የአየር ንብረት ያላቸውን አካባቢዎች በማካለል የሚኖሩት እነዚህ ፍልሰተኛ ወፎች ቋሚ የመኖሪያ ሥፍራ እና ወጥ የአየር ንብረት የላቸውም ብለዋል። ነገር ግን አብዛኞቹ የወፍ ዝርያዎች ለአስተማማኝ የምግብ አቅርቦትና ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ተስማሚ የአየር ንብረት ወዳላቸው አካባቢዎች ርቀው በመሄድ አስቸጋሪ ወቅቶች እስከሚያልፉ ይጠብቃሉ ነው ያሉት።
ባጃጅ ላይ ወድቆ የተገኘው የአደራ ገንዘብ- 82 ሺህ 265 ብር
Mar 5, 2025 21400
በአማራ ክልል ዋግኸምራ አስተዳደር የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው ባለባጃጅ ወጣት ሠለሞን ቢምረው ተሳፋሪ ደንበኞቹን ከቦታ ቦታ በማዘዋወር ዕለታዊ ተግባሩን ይከውናል። ዛሬ ማለዳ ታዲያ በሰቆጣ ወረዳ የሰርክ ተግባሩን እያከናወነ ሳለ በድንገት ከአንድ ተሳፋሪ የተረሳ በኬሻ የተቀመጠ ንብረት ባጃጁ ውስጥ ያገኛል። ሰለሞን ቢምረው ማንነቱን ባላወቀው ተሳፋሪ የተረሳው ምንነቱን ያላወቀው በኬሻ የተቋጠረ ንብረት ገንዘብ መሆኑን ያወቀው ከደቂቃዎች በኋላ ነበር። 'ታማኝነት ለራስ ነው' የሚለው ወጣት ሰለሞን፥ ከተሳፋሪ ደንበኛ የተረሳን መጠኑን ያላወቀው ገንዘብ ለመመለስ ተጣደፈ። ተሳፋሪውን በእግር በፈረስ ማፈላለግ ይጀምራል። በሌላ በኩል የሰቆጣ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘር ኃይሌ በአደራ የተረከቡትን በኬሻ የተቋጠረ 82 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ፌርማታ ላይ ከባጃጅ ሲወርዱ መርሳታቸውን ካወቁበት ቅጽበት ጀምሮ በደንጋጤ ድባቴ ውስጥ ገብተዋል። ጉዳያቸውን ለፖሊስ አሳውቀው የአደራ ገንዘባቸውን በይገኛል ተስፋ እና ጭንቀት የባጃጅ አሽከርካሪውን ፍላጋ በየፌርማታው እየኳተኑ ነው። ተሳፋሪ እና አሳ'ፋሪ በየፊናው መፈላለጉን ተያያዙት። በዚህ መሀል የባጃጅ አሽከርክሪው ሰለሞን ቢምረው ወደ ተሳፋሪዋ ወይዘር ኃይሌ ድንገት ከተፍ ይላል። የወይዘሮ ወይዘር ደስታ ወደር አጣ። አሳፋሪው ሰለሞንም እፎይታ ተሰማው። በተለይ የአደራ ገንዘብ መሆኑን ሲረዳ። ባጃጅ አሽከርክሪው ሰለሞን እና ተሳፋሪዋ ወይዘሮ ወይዘር በፖሊስ ፊት ንብረት ተረካከቡ። ወጣቱ ሰለሞን እንደገለጸው የተሳፋሪ ንብረት በመመለሱ ደስተኛ ነው። ለወይዘሮ ወይዘር አደራ ያስረከበችው የገንዘቡ ባለቤት ወይዘሪት ወለለ ንጉስ፤ በሰለሞን ቢምረው ነባይነት(ታማኝነት) እንዳስገረማቸው ይናገራሉ። በዚህ ወቅት ይህን ያህል ገንዘብ አግኝቶ መመለስ በዕውነቱ በነፍስም በስጋም የሚያስመሰገን በጎ ምግባር ነው ስትል አመስግናለች። የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ደሳለኝ አባተ ወጣት ሰለሞን ከአሁን ቀደምም ሞባይል ጥለው የሄዱትን ለባለቤቱ በታማኝነት መመለሱን አስታውሰዋል። አሁን ደግሞ በኬሻ የተቋጠረን 82 ሽህ 265 ብር ከግል ይልቅ የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ለግለሰቧ በታማኝነት ማስረከቡን አረጋግጠዋል። ይህን መሰል በጎ ምግባር በሁሉም የማህበረሰብ ዘንድ በአርዓያነት ሊወሰድ የሚገባው ነው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
መጣጥፍ
ከጨበራ እስከ ጎርጎራ
Sep 22, 2026 142
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ)፦ከጨበራ እስከ ጎርጎራ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጸጋዎች እንዲሁም በታሪክ፣ በባህል እና በታሪካዊ ቅርሶች የታደለች ሀገር መሆኗ ይታወቃል። ይሁን እንጂ እነዚህ እምቅ ሃብቶች ለበርካታ ዓመታት ተገቢውን ትኩረት ሳያገኙ፣ ሳይለሙና የሀብት ምንጭ ሳይሆኑ ተዘንግተው መቆየታቸው የሚታወቅ ነው። የመደመር መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ትኩረት ዘርፉ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ከተካተቱ አምስት ሴክተሮች አንዱ ሆኖ መተግበር ጀምሯል። በዚህም በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማሻሻልና አዳዲስ መዳረሻዎችን የማልማት ስራ በስፋት ተከናውኗል፤ እየተከናወነም ይገኛል። በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑ የ"ገበታ ለሸገር"፣ "ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" የልማት መርሃ-ግብሮች የቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ እመርታና ማንሰራራት አምጥተዋል። በእነዚህ ኢንሸቲቮች ተደብቀው የቆዩና በሁሉም ማእዘናት የነበሩ መሠረተ ልማቶችን በማልማት ጥቅም ላይ ማዋል ተችሏል። ለኢትዮጵያ ተፈጥሮ የለገሳትን ውብ መልክዓ ምድሮች፣ ሀይቆች፣ ብሔራዊ ፓርኮች እና ታሪካዊ ስፍራዎች ይበልጥ በማልማት የዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም መዳረሻነቷን ከፍ አድርጓል። የቱሪዝም ልማቱ ሀገርን እና ትውልድን መሰረት አድርጎ በሁሉም አካባቢዎች በርካታ ግንባታዎችን እውን አድርጓል። ከቀድሞው የተገደበ የቱሪስት እንቅስቃሴ ወጥቶ፣ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችንና ሪዞርቶችን በመገንባት ረገድ አስደናቂ ስራዎች ተከናውነዋል። በጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ የተገነባው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ለቱሪስቶች ምቾትና ለሐይቁ ውበት ግርማ ሞገስ ሆኖ የተገነባ ነው። የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ጋር ተሰናስሎ የተገነባው ሎጅም የተፈጥሮን ውበት ከዘመናዊ የቅንጦት አገልግሎት ጋር ያሰናሰለ አስደናቂ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል። የ«ገበታ ለትውልድ» ሁለተኛ ምዕራፍ ማሳያ የሆነው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ደግሞ የወሎን ማህበራዊ መስተጋብር እና የአብሮነት እሴት የሚያጎለብት፣ ለአይን ማራኪ እና ዘመናዊ መዝናኛ ሆኖ የታነጸ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ትኩረት ከሰበሰቡ አዳዲስ የቱሪዝም እና የልማት መዳረሻዎች መካከል ቤኑና መንደር አንዱ ነው። የ«ይቻላል» እምነት ቋሚ ምስክር ተብሎ የሚታወቀው ይህ አካባቢ፣ አካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ስበት በመጠቀም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶችን ትኩረት የሳበ ውብ መናኸሪያ ሆኗል። በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተፈጠረው እና ውብ ውበቱን የያዘው የወንጪ ሐይቅ፣ ዛሬ ላይ ከማህበረሰቡ ጋር በተቀናጀ መልኩ በለማው ኢኮ-ሎጅ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያገኘ መዳረሻ መሆኑ ይታወቃል። በሶማሌ ክልል ከጅግጅጋ ከተማ በ385 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ታላቁ የሸበሌ ሪዞርትም የክልሉን የቱሪዝም ልማት በእጅጉ ያነቃቃ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል። የዳናክል በረሃ እና ኤርታአሌ ያሉ ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋዎችን የያዘው የአፋር ክልል ቱሪዝምን ለማነቃቃትና የጎብኚዎችን ቆይታ ለማራዘም "ከፈንታሌ እስከ ኤርታአሌ" የተሰኘ የቱሪዝም ልማት ፕሮጀክት ጨምሮ ዘመናዊ ሪዞርቶችና መዳረሻዎች እንዲስፋፉ ተደርጓል። በድምሩ ከጨበራ እስከ ጎርጎራ፣ ቤኑና፣ ወንጪ፣ ሎጎ ሃይቅ እንዲሁም የሀሮ ደንዲ ሎጅ የሀገሪቱን ገጽታ የቀየሩና የቱሪዝም ዘርፉን እድገትና ማንሰራራት እውን ካደረጉት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የህዳሴ ግድብም ከሃይል ልማት ባለፈ አይነተኛ የቱሪዝም መሰህብ ስፍራ ሆኖ የንጋት ሃይቅ ዓሳ የሚመረትበትና ቱሪስቶች የሚስተናገዱበት ተመራጭ ስፍራ ሆኗል። በመደመር መንግስት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ባለፈ የቆዩትን የማደስና ቅርሶችን የመጠበቅ እንዲሁም የመንከባከብ ስራ በስፋት ተከናውኗል። በሁሉም ክልሎች እምቅ ሃብቶችን በመለየት የማልማትና የነበሩትን የመጠበቅ ስራ ተሰርቷል። ለትውልድ የሚሻገር የቅርስ ጥበቃና መዳረሻዎችን የማልማት ተግባር የኢትዮጵያን ብዝሃ-ሃብት በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ኢኒሼቲቮች በተለይም በቱሪዝም ሴክተር መሰረታዊ ለውጥና ስኬት ማስመዝገብ የቻሉ ተጨባጭ ውጤቶችም ያመጡ መሆናቸውን መናገር ይቻላል።
ጊፋታ እና ኮርማ ጪሻ
Sep 17, 2026 496
"ጊፋታና ኮርማ ጪሻ" (በማስረሻ ሐብታሙ ከኢዜአ ወላይታ ሶዶ ቅርንጫፍ) የወላይታ ዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓል ሲደርስ ሜዳና ጋራው በአበቦች ይደምቃል። የአበቦቹ መዓዛ አካባቢውን ያውዳል። ሕዝቡም የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ በዐይነ-ሕሊናው እያሰበ ዕለቱን በናፍቆት ይጠብቃል። ከአበቦች መካከልም ከሁሉ ቀድሞ የሚፈካው "ኮርማ ጪሻ" ወይም "የጊፋታ አበባ" በሰፊው መስክ ላይ ሌላ ውበትና ድምቀት ይፈጥራል። ''ኮርማ ጪሻ'' በወላይታዎች ዘንድ የጊፋታ በዓል ዋዜማና የመምጫ ወቅት መጠቆሚያ ከሆኑት የተፈጥሮ ምልክቶች አንዱ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ''ኮርማ ጪሻ'' ከአደይ አበባ የሚለይ ሲሆን፤ ነጭ ቀለም እና ትናንሽ ቅጠሎች ያሉት የአበባ ዓይነት ነው። በወላይታ ዘመን አቆጣጠር መሠረት "ኩሻ አጊና" ወይም ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ በጊፋታ ወር መባቻ ላይ በአካባቢው በስፋት በማበብ ለእይታ ድምቀት የሚሰጥና የወላይታ አዲስ ዓመት መቃረቡን የሚያበስር ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ ነው "ኮርማ ጪሻ" ወይም "የጊፋታ አበባ"። በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ታሪክ ተመራማሪ አቶ አዳነ አይዛ እንደሚያስረዱት፤ ቀደምት የወላይታ ሥነ-ፈለግ አዋቂዎች ዘመንን ለመቁጠር ከፀሐይ፣ ጨረቃ እና ከዋክብት እንቅስቃሴ በተጨማሪ፣ የተፈጥሮ ለውጦችን ከመልክዓ-ምድሩ ውበትና ከተፈጥሯዊ ምልክቶች ጋር አጣምረው ይጠቀሙ እንደነበር አውስተው፤ ይህ ''ኮርማ ጪሻ'' ትልቁ ማረጋገጫ ስለመሆኑም ይገልጻሉ። "ጊፋታ" ሲቃረብ የወላይታ ሕዝብ ለበዓሉ ሙሉ ዝግጅት የሚያደርግበት አያሌ የተፈጥሮ ምልክቶች እንዳሉት ተመራማሪው ይናገራሉ። ወላይታዎች የዝናብና የአየር ንብረት ለውጥን መሠረት በማድረግ ጊዜን የሚቆጥሩ ሲሆን፤ የክረምቱ ከባድ ዝናብና ጨለማ ወቅት አልፎ ሙሉ የፀሐይ ብርሃን መተካት ''ቦቃልሳ'' ማለትም ''ኦፊንታ'' (የፀደይ ወቅት) ሊጀምር ሲል ለጊፋታ በዓል ጥቂት ቀናት ብቻ መቅረቱን በማጥናት አንዱ ከአንዱ መረጃ መለዋወጥ ይጀምራሉ ብለዋል። የወንዞች ሙላትና መጉደልም እንደ አንድ ምልክት የሚወሰድ ሲሆን፤ ለሦስት ወራት ምድርን አጨልሞ የነበረው ጭጋግና የጉም ወቅት አልፎ በክረምቱ ጎርፍ ሞልተው የነበሩ ወንዞች ጊፋታ ሲቃረብ እየጎደሉ ይመጣሉ። ጨረቃም በአዲስ መልክ ለመውጣት በአሮጌው ዓመት በጨለማ ውስጥ ለቀናት ቆይታ ''ጤሩዋ'' ወይም መውጫ ጊዜዋ ሲደርስ በ''ግሩዋ'' (በሥነ-ፈለግ አዋቂዎች) ዓይን ከታየች፤ አዲስ ዓመት መቃረቡን በአዋጅ ሳይነገራቸው እንዲሁ በተፈጥሮ ምልክት ብቻ ዝግጅት ማድረግ ይጀምራሉ። ይህ ብቻ አይደለም፤ የጊፋታ መምጣትን ጠቋሚ የሆነው የነጭ ቢራቢሮ መንጋ የወላይታን ምድር በመውረር ከአንድ አቅጣጫ ወደ ሌላኛው አቅጣጫ መብረር ሲጀምርም ጊፋታ መቃረቡን አመልካች መሆኑን አቶ አዳነ ይገልጻሉ። በዚህ ወቅት ልጆች የቢራቢሮ መንጋ ለማደን ወደ መስክ ወጥተው የሚያደርጉት ጨዋታ የጊፋታ መምጫን ልዩ ያደርገዋል፤ የበዓሉ መቃረብ ደወል ተደርጎም ይወሰዳል። በዚህ ትይዩ ወቅት የሚያብበው ''ኮርማ ጪሻ'' የክረምቱ ጨለማና ያ ከባዱ ዝናብና ጉም አልፎ ወደ ፀደይ ብርሃን በሚሸጋገርበት ወቅት የፀሐይን መውጣት ተከትሎ የሚመጣ ጊዜ ወይም ''ቦቃልሳ'' የሚባለው ወቅት ሊገባ ሲል መሆኑንም የዘርፉ ሊቃውንት ይናገራሉ። በወላይታ ባህል "ኮርማ ጪሻ" ሲያብብ ኅብረተሰቡ የጊፋታ በዓል ዝግጅቱን በይፋ የሚያጧጧፍበት ልዩ የተፈጥሮ ጥሪ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረው፤ ሳይሸራረፍ ዘመናትን እየተሻገረ ይኸው ለዛሬው ትውልድ መድረሱን የገለጹት ደግሞ በወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል፣ የታሪክና ቅርስ ተመራማሪ አቶ ግርማ ገነነ ናቸው። "ኮርማ ጪሻ" በወላይታዎች ዘንድ ለጊፋታ በዓል "እንኳን አደረሰህ / አደረሳችሁ!" ተብሎ የሚበረከት የመልካም ምኞት መግለጫ የአበባ ስጦታ መሆኑንም አመልክተዋል። ''ኮርማ ጪሻ'' በወላይታ የዘመን አቆጣጠር እና ተፈጥሯዊ ቀመር ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ምስጢራዊ አበባ መሆኑን የገለጹት አቶ ግርማ፤ ወደ አዲስ ዘመን መሻገሪያ ምልክት፣ የተስፋ እንዲሁም ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን የሚያበስርና ለመንፈስ እርካታን የሚሰጥ ነው ብለዋል። የወላይታ የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት በጨረቃ እና በፀሐይ ዑደት ላይ የተመሠረተ ሆኖ በዓሉ የሚከበርበትን ትክክለኛ ቀን፤ "አዋቂዎች" ከሚያደርጉት ስሌት ጎን ለጎን፣ የተፈጥሮ ጸጋ የሆነው ኮርማ ጪሻ ወይም የጊፋታ አበባ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። አበባው የወቅቱን መለወጥና የአዲሱን ዓመት መባቻ በተፈጥሯዊ ቋንቋ የሚነግር ነው። የዚህን አበባ ምስጢር ታላቅነት የሚያብራሩት ከሀገር ሽማግሌዎች አንዱ የሆኑት አቶ ኢያሱ ጋጃቦ በበኩላቸው፤ ይህ አበባ ለ"ጊፋታ" ወይም ለአዲስ ዘመን በዓል መግቢያ አንድ ወር ጊዜ ብቻ ሲቀረው የሚበቅልና ቀናት ሲቀሩት የሚያብብ ድንቅ የተፈጥሮ ፀጋ መሆኑን ይናገራሉ። ኮርማ ጪሻን ከጊፋታ በዓል መምጫ ወቅት ውጭ በዓመት ውስጥ ፈልጎ ማግኘት እንደማይቻል ገልጸው፤ ይህንን ተፈጥሮ በመተርጎም ረገድ የቀደምት አባቶች አእምሯዊ ጥበብ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል። ''ኮርማ ጪሻ'' ወይም የጊፋታ አበባ ከጊፋታ በዓል ማግስት ባለው ማክሰኞ ዕለት ወደ አማች ቤት ወይም ወደ አበልጅ ቤት "ዮዮ ጊፋታ" በማለት ይዞ በመሄድ ለአባዎራው ይሰጣል። በዚህ ጊዜ አባወራው "ዮዮ ዮዮ" በማለት ተቀብሎ ከምሰሶ ጋር አስሮ ያስቀምጣል። ይህም የቤቱ መሶብ፣ በረከትና አዲሱ ዘመን እንደ ምሰሶው ጸንቶ እንዲኖር የሚደረግበት የአዲሱ ዓመት መቀበያ ምልክትና ምርቃት ነው፡፡ በዚህም ወቅት አባዎራው ''ጊፋታይ እንተና ቆዶፖ፤ እንቴ ጊፋታ ቆዲቴ'' ወይም "ዘመን እናንተን አይቁጠራችሁ፤ እናንተ ዘመናትን እየቆጠራችሁ ኑሩ" በማለት ይመርቃል። "ኮርማ ጪሻ" የወላይታ ነባር የሥነ-ፈለግ እውቀት የሚገለጥበት ተፈጥሯዊ እውቀት መሆኑንም ተናግረዋል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" ዘንድሮ በ"ጊፋታ አጊና" ወይም መስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም ተወላጆችና የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።