ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሕብረት ለታዳጊው ዓለም የፍትህ ድምፅ እና ለባለብዙ ወገን ግንኙነት ዋነኛ መገለጫ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሕብረት ለታዳጊው ዓለም የፍትህ ድምፅ እና ለባለብዙ ወገን ግንኙነት ዋነኛ መገለጫ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰላም፣ በጸጥታ፣ በዘላቂ ልማት እና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ተቋማዊ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፈርመውታል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዚሁ ወቅት በሰጡት መግለጫ፣ የአፍሪካ ህብረት ለታዳጊው ዓለም የፍትህ ድምፅ እና ለባለብዙ ወገን ግንኙነት ዋነኛ መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።

አጋርነታቸውን ይበልጥ ተቋማዊ የሚያደርገው ይህ ስምምነት በቁልፍ ዘርፎች ላይ የተመዘገቡ ስኬቶችንና የወደፊት ዕቅዶችን መነሻ ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ በቋሚ አባልነት አለመካተቷን ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነት ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ ይህም የምክር ቤቱን ተቀባይነትና ውጤታማነት እንደሚጎዳው አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ሊስተካከል እንደሚገባ ጠቅሰው አፍሪካ ከጥሬ ዕቃ አቅራቢነት ወጥታ ለአረንጓዴ ኢነርጂ ሽግግር የማምረቻና የማጣሪያ ማዕከል መሆን እንዳለባት ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው፣ የአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳ እና የተባበሩት መንግሥታት የ2030 አጀንዳ የተጣጣሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ፈተናዎችን ለመፍታት በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ ተደርጎ የአፍሪካ ሀብቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በናይሮቢ የተካሄደው የ"አፍሪካ ፎርዋርድ" (Africa Forward) ጉባኤ ውጤቶች ክትትል እንዲደረግባቸው አሳስበዋል፡፡

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብትን ጨምሮ ቋሚ መቀመጫና ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖራት የሚለውን የአህጉሪቱን ጥያቄ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ይህ ስምምነት በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ያለውን ስልታዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ይጠበቃል።

10ኛው የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የከፍተኛ ደረጃ ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም