ቀጥታ፡

የዓለም አትሌቲክስ የአትሌት ትዕግስት አሰፋ የሴቶች ብቻ የማራቶን የዓለም ክብረ ወሰንን አፀደቀ 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የዓለም አትሌቲክስ የኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ የሴቶች ብቻ (women’s only) የማራቶን የዓለም ክብረ ወሰንን ዛሬ ማፅደቁን ይፋ አድርጓል።
 
አትሌት ትዕግስት እ.አ.አ አፕሪል 26 / 2026 በለንደን ማራቶን 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ41 ሴኮንድ በመግባት እ.አ.አ በ2025 በራሷ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በዘጠኝ ሴኮንድ በማሻሻል አሸንፋለች።
 
የዓለም አትሌቲክስ የአትሌቷን የሴቶች ብቻ የዓለም ክብረ ወሰን ዛሬ ማፅደቁን አስታውቋል።
 
የሴቶች ብቻ (women’s only) የዓለም ክብረ ወሰን ሴቶች ብቻ በሮጡበት ውድድር ብቻ የተመዘገበ የዓለም ፈጣን ሰዓት ማለት ነው።
 
የዚህ የዓለም ክብረ ወሰን አመዘጋገብ በሴቶች ውድድር ላይ የወንድ አሯሯጮች ወይም ወንዶች ተቀላቅለው ሲሮጡ (አጠቃላይ ሩጫ) ከሚመዘገበው የዓለም ክብረ ወሰን ጋር የሚለያይ ነው።
 
ወንዶች በሴቶች ውድድር ላይ መኖራቸው የውድድሩን አዝማሚያ እና ሴቶች የሚያስመዘግቡት ሰዓት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።

ሴት እና ወንድ ተደባልቀው በሚሮጡበት አጠቃላይ የሴቶች ማራቶን ውድድር የዓለም ክብረ ወሰንን (Overall women's world record) የያዘችው ኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቼፕጌቲች ናት።
 
ሩት እ.አ.አ በ2024 በቺካጎ ማራቶን 2 ሰዓት ከ9 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ በመግባት ክብረ ወሰኑን ጨብጣለች።
 
የዓለም አትሌቲክስ ከአትሌት ትዕግስት በተጨማሪ ሰባት የዓለም ክብረ ወሰኖችን ማጽደቁን አስታውቋል።
 
እውቅናና ፈቃድ በተሰጣቸው ውድድሮች ላይ ማሸነፍ፣ የውድድር ሜዳዎቹ የሚፈለገውን መስፈርት ያሟሉ መሆንና አትሌቶች በአበረታች ቅመም ምርምራ ውጤት ጤነኛ መሆናቸው መረጋገጥ አትሌቶች የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት የሚሆኑባቸው ዋነኛ ቅደመ-ሁኔታዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም