በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወፎች በፍልሰት ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ - ኢዜአ አማርኛ
በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወፎች በፍልሰት ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፡- በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ፍልሰተኛ ወፎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል።
የዓለም የስደተኛ ወፎች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ "ምቹ የመኖሪያ ቦታ፤ ለአዕዋፋት አኗኗር ምቹ የሆኑ ከተምች እና ማኅበረሰብ" በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ በመላው ዓለም እየተከበረ ነው።
በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የጥበቃ ቦታዎችና የብሔራዊ ፓርኮች ዋርደን ፋንታዬ ነጋሽ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የዓለም የፍልሰተኛ ወፎች ቀን የሚከበረው ስለ ፍልሰተኛ ወፎች ያለ የማኅበረሰብ ግንዛቤን ለማሳደግ እና በእንቅስቃሴያቸው ወቅት ተገቢ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጎልበት ነው።
ለምግብና ለመራባት በይበልጥ ምቹ ሁኔታ በመፈለግ ብሎም ከወቅታዊ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች (ቅዝቃዜና ሙቀት ) ለማምለጥ ወፎች ምቹ ወደሚሉት አካባቢ እንደሚፈልሱ አንስተዋል።
በዚህም መሠረት ከአውሮፓ፣ እስያ፣ ከተለያዩ የአፍሪካ እና ባልካን ሀገራት በየዓመቱ በተለያዩ ወቅቶች በሚሊየን የሚቆጠሩ ወፎች በፍልሰት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።
አንዳንድ ፍልሰቶች አጭር መሆናቸውን ገልጸው፤ አኅጉራትን፣ በረሃዎችን እና ውቅያኖሶችን ማቋረጥ የግድ የሚሆንባቸው ረጅም ርቀት የሚሸፍኑ ፍልሰቶች እንዳሉም አስገንዝበዋል።
ትክክለኛ ዓመታዊ ቆጠራ ላይ የተመሠረተ አሀዛዊ መረጃ ማግኘት ቢያዳግትም፤ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ መስመር አማካኝነት በየዓመቱ በርካታ ፍልሰተኛ ወፎች ወደ ኢትዮጵያን ይመጣሉ ብለዋል።
በዚህም መሠረት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚልቁ ፍልሰተኛ ወፎች በኢትዮጵያ በኩል የሚያልፈውን የስምጥ ሸለቆ መስመር ይጠቀማሉ ነው ያሉት።
በተጨማሪም 199 ገደማ ዝርያዎች ከአውሮፓና እስያ እንዲሁም 47 ዓይነት ዝርያዎች ከአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት በፍልሰት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ እና ከወራት ቆይታ በኋላ ወደተለያዩ አቅጣጫዎች ተመልሰው እንደሚሄዱም አንስተዋል።
እንደዝርያቸው ቢወሰንም ከቅዝቃዜ እስከ ሞቃታማ የአየር ንብረት ያላቸውን አካባቢዎች በማካለል የሚኖሩት እነዚህ ፍልሰተኛ ወፎች ቋሚ የመኖሪያ ሥፍራ እና ወጥ የአየር ንብረት የላቸውም ብለዋል።
ነገር ግን አብዛኞቹ የወፍ ዝርያዎች ለአስተማማኝ የምግብ አቅርቦትና ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ተስማሚ የአየር ንብረት ወዳላቸው አካባቢዎች ርቀው በመሄድ አስቸጋሪ ወቅቶች እስከሚያልፉ ይጠብቃሉ ነው ያሉት።