ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጋና ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጋና ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጋና ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ጋር በጁብሊ ሀውስ በሁለትዮሽ እና በጋራ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ከአፍሪካ ኅብረት የጤና ዘርፍ ልዩ የመሪዎች የጤና ጉባኤ በተጓዳኝ፣ ከጋና ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ጋር በጁብሊ ሀውስ በሁለትዮሽ እና በጋራ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጋና ጋር ከፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መነሻ ጀምሮ ለዘለቀው ታሪካዊና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነቷ ትልቅ ሥፍራ ትሰጣለች ሲሉም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው አዲሱ የጋና ኤምባሲ ሕንፃ መጠናቀቅም የሁለቱ አገራት የማይናወጥ ወዳጅነት ምልክት መሆኑን በውይይታችን አንስተናል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ፕሬዝዳንት ማሃማ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነትና የአንድነት አርማነቷን እንደጠበቀች፣ አሁን ደግሞ በአረንጓዴ አሻራና በሌሎች የልማት ዘርፎች እያስመዘገበቻቸው ባሉ አበረታች ለውጦች እና ስኬቶች በእጅጉ መደነቃቸውን ገልጸውልኛል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሀገራችን ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄደውን የጣና ፎረም ለማዘጋጀት እያከናወነችው ያለችውን የቅድመ ዝግጅት ስራ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል ሲሉም ጠቁመዋል።
በፎረሙ ቦርድ ላይ እያበረከቱ ላሉት እጅግ የላቀ አመራርም የከበረ ምስጋናችንን አቅርበንላቸዋል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመልዕክታቸው።