ቀጥታ፡

ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል የጀመራቸው ተጨባጭ ለውጦች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2018 (ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል የጀመራቸው ተጨባጭ ለውጦች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።

ብልፅግና ፓርቲ በፓርቲና በመንግሥት የተቀናጀ አመራር የስራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋት፣ የገበያ መረጋጋትን ለማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የጀመራቸው ተጨባጭ ሥራዎች በሕዝብ ሕይወት ላይ የሚታዩ ለውጦችን እያስመዘገቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

አቶ አደም ፋራህ ይህንን የተናገሩት በ2018 በጀት ዓመት በፓርቲና በመንግሥት ቅንጅት በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በገበያ ማረጋጋትና በኑሮ ውድነት ቅነሳ ዙሪያ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት በተገመገመበት መድረክ ማጠቃለያ ላይ ነው።


 

የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የገበያ መረጋጋትና የኑሮ ውድነት ቅነሳ የመንግሥት መደበኛ ፕሮግራሞች ብቻ ሳይሆኑ የፓርቲው ዋና ዋና የፖለቲካ ተልዕኮዎች በመሆናቸው በሁሉም የአመራር እርከኖች በንቅናቄ ተመርተዋል ብለዋል።

ይህም ከዕቅድ አፈጻጸም ባለፈ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን አመልክተዋል።

በሁሉም ክልሎች በስራ ዕድል ፈጠራና በኑሮ ውድነት ቅነሳ ዘርፎች የሚታዩ መሻሻሎች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ ያለውን የሀገሪቱን አቅምና የሕዝቡን ፍላጎት ከግምት በማስገባት ከዚህ በላይ ሊሠራ የሚገባ ብዙ ሥራ እንዳለ አስገንዝበዋል።

ሁለቱንም የትኩረት መስኮች በሕዝብ ንቅናቄ በመምራታችን ጉዳዩን እስከ ቀበሌ ድረስ የአመራር አጀንዳ ማድረግ ችለናል፤ ይህም ተጨባጭ ለውጥ አስገኝቷል ነው ያሉት።

አሁን ያለውን ጅምር ማጠናከርና ወደ ከፍተኛ ውጤት ማሸጋገር ይጠበቃል ሲሉም አቶ አደም አስገንዝበዋል።

የፓርቲ አደረጃጀቶችና አባላት በዘርፉ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ በማሳሰብ፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።


 

የእያንዳንዱን አካባቢን የልማት አቅምና የገበያ እውነታ መሠረት በማድረግ ለሕዝቡ ቀጥተኛ ጥቅም የሚያስገኙ ምርቶችን በመለየት የኑሮ ሁኔታን ማሻሻል የቀጣይ ትኩረት መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

እንዲሁም የሕዝብ ባለቤትነትንና የተደራጀ ተሳትፎን በማጠናከር፣ ከአሰራር፣ ከአመለካከትና ከአስተሳሰብ ጋር የተያያዙ ማነቆዎችን በመፍታት ሥራዎቹን ዘላቂ፣ ተቋማዊና ሥርዓታዊ በሆነ አግባብ ማስቀጠል እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዶች በተሻለ አፈጻጸም እንዲተገበሩ ሁሉም የፓርቲ መዋቅሮችና የመንግሥት ተቋማት በቅንጅት፣ በተጠያቂነትና በውጤት ተኮር አሰራር ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተካሄደው የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ የውይይት መድረክ፣ በቀጣይ የሕዝብን የኑሮ ሁኔታ የበለጠ ማሻሻል የሚያስችሉ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መጠናቀቁ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም