ስፖርት
የ33ኛው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርዓት እየተካሄደ ነው
Jul 26, 2024 171
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦በፓሪስ የሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርዓት በመከናወን ላይ ይገኛል። በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ቶማስ ባክ፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የተለያዩ የሀገራት መሪዎችና ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። የዘንድሮው ኦሊምፒክ መክፈቻ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስታዲየም ውጪ በወንዝ ላይ እየተደረገ ነው። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ 10 ሺህ 500 ስፖርተኞች በሰሜናዊ ፈረንሳይ በሚገኘው ሴይን ወንዝ ላይ በመርከብ የ3 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር በማቋረጥ የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ የሚካሄድ ይሆናል። የመክፈቻ ስነ ስርዓቱን 300 ሺህ ተመልካች በስፍራው በመገኘት እንደሚከታተለው ይጠበቃል። በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከ203 ሀገራት የተወጣጡ 10 ሺህ 500 አትሌቶች በ32 የስፖርት አይነቶች እንደሚወዳደሩ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል። ከሀገራቱ በተጨማሪ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር ገለልተኛ አትሌቶችና የኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድን ይሳተፋሉ። ኢትዮጵያም በአትሌቲክስና በውሃ ዋና የስፖርት ዓይነቶች በ38 ስፖርተኞች የምትካፈል ሲሆን አትሌቶቹ ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም አንስቶ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል። 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።
በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላ ምርመራ ተደርጓል
Jul 26, 2024 116
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላ ምርመራና የክትትል ስራ መከናወኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን አስታወቀ። ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የፀረ-አበረታች ቅመሞች አማካሪ ቡድን ውስጥ አፍሪካን በብቸኝነት መወከሏንም ገልጿል። 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ በፓሪስ የሚጀመር ሲሆን የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በውድድሩ አበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር የተለየ ትኩረት ሰጥቷል። በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የአበረታች ቅመሞች ምርመራ እንዲያደርግ ፈቃድ የተሰጠው ተቀማጭነቱን በስዊዘርላንድ ሉዛን ያደረገው ' ኢንተርናሽናል ቴስቲንግ ኤጀንሲ' የተሰኘው ገለልተኛ ተቋም ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል የዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ(ዋዳ) ባስቀመጠው አሰራር መሰረት በውድድሩ ለሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአበረታች ቅመሞች ምርመራ መደረጉን ገልጸዋል። ባለስልጣኑ ስፖርተኞቹ ከአበረታች ቅመሞች የጸዱና ነፃ ሆነው እንዲወዳደሩ የቅድመ መከላከልና የቁጥጥር ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከአበረታች ቅመሞች የፀዳ ስፖርት እንዲፈጠር በትኩረት እየሰራች መሆኗን ጠቅሰው፤ በኦሊምፒክ ጨዋታዎችም ላይ ያለው መልካም ተሞክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊ ጥረት መደረጉን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት። ምርመራዎቹ ለስፖርተኞች የተከለከሉ ብሎ የለያቸው ቅመሞችን መሰረት በማድረግ መከናወኑና ሁሉም አትሌቶች ነጻ መሆናቸውን አመልክተዋል። ከክትትልና ቁጥጥር ስራው በተጨማሪ ለአትሌቶች የአበረታች ቅመሞችን አስመልክቶ የግንዛቤ መፍጠር ስራ ማከናወኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይም ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች በጉዞና በውድድር ወቅት አበረታች ቅመሞችን አስመልክቶ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። በተያያዘም በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ(ዋዳ) ባቋቋመው አማካሪ ቡድን ውስጥ አፍሪካን የወከለች ብቸኛ ሀገር መሆኗን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ አፍሪካን በወከል የአበረታች ቅመሞች ክትትልና ቁጥጥር ስራ ላይ እንደምትሳተፍና ለዋዳ የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችን እንደምታቀርብ ተናግረዋል። የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአበረታች ቅመሞች ላይ ከሚያደርገው ቁጥጥርና ክትትል በተጨማሪ ስፖርተኞችን የማስተማር ስራ ያከናውናል። የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የዓለም አቀፉ የፓራኦሊምፒክ ኮሚቴ ከእ.አ.አ 1960ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ የአበረታች ቅመሞች ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርጉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ዛሬ በፓሪስ በሚጀመረው በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በእያንዳንዱ ውድድር በሚደረግበት ስፍራ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ቁጥጥር ቦታ ተዘጋጅቷል። በዚህም 360 የሚሆኑ ግለሰቦች የአበረታች ቅመሞች ናሙና በመውሰድ ምርምራ ያደርጋሉ፣ የአትሌቶችን በውድድር የመሳተፍ ተገቢነትም ያረጋግጣሉ ተብሏል። ኢትዮጵያ በዘንድሮው የፓሪስ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክስና ውሃ ዋና የስፖርት ዓይነቶች በ38 ስፖርተኞች ትወከላለች።  
ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በኦሊምፒክ የመክፈቻ ስነ ስርዓት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በመያዝ ከፊት ይሰለፋል
Jul 26, 2024 139
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦በፓሪስ የሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ በይፋ ይጀመራል። አትሌት ቀነኒሳ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ታሪክ ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈ አንጋፋ አትሌት ሆኗል። የኦሊምፒኩ መክፈቻ በውድድሩ የ128 ዓመት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስታዲየም ውጪ በወንዝ ላይ ይደረጋል። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ 10 ሺህ 500 ስፖርተኞች በሰሜናዊ ፈረንሳይ በሚገኘው ሴይን ወንዝ ላይ በመርከብ የ3 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ጉዞ በማድረግ የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ይከናወናል። ኢትዮጵያ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች 15ኛ የውድድር ተሳትፎዋን ታደርጋለች። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ1956 በአውስትራሊያ ሜልቦርን በተካሄደው 16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ነበር። 12 አትሌቶችን በአትሌቲክስና ብስክሌት ስፖርተኞች አሳትፋለች። አትሌት አበበ ቢቂላ፣ አትሌት ማሞ ወልዴ፣ አትሌት ፊጣ ባይሳ፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ምሩጽ ይፍጠር፣ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣ አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣ ቦክሰኛ አቤል አፈራልኝ፣ ዋናተኞቹ ያኔት ስዩም፣ ሮቤል ኪሮስና አብዱልመሊክ አዲስ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻና መዝጊያ ስነ ስርዓቶች ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ የመያዝ እድል ያገኙ ስፖርተኞች ናቸው። በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርዓት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሚይዘው ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ነው። አትሌት ቀነኒሳ በቻይና ቤጂንግ እ.አ.አ በ2008 በተካሄደው 29ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በመዝጊያ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ የመያዝ እድል አግኝቶ ነበር።   በስኬትና በድል የታጀበ የአትሌቲክስ ሕይወት ያለው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው እ.አ.አ በ2004 በግሪክ አቴንስ በተካሄደው 28ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ነበር። ቀነኒሳ በውድድሩ በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ እና በ5 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ አግኝቷል። በቻይና ቤጂንግ እ.አ.አ በ2008 በተካሄደው 29ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ አትሌቱ በ10 ሺህ እና 5 ሺህ ሜትር ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ለሀገሩ አኩሪ ታሪክ ሰርቷል። አትሌት ቀነኒሳ በኦሊምፒክ ተሳትፎው 3 የወርቅና 1 የብር ሜዳሊያ አግኝቷል። አትሌቱ በዘንድሮው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያን ወክሎ ይሳተፋል። የ42 ዓመቱ አትሌት በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፎ ታሪክ በእድሜ ትልቁ ተወዳዳሪ ክብረ ወሰንን ይዟል። ቀነኒሳ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በተካሄደው የለንደን ማራቶን 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ15 ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት ያስመዘገበው ጊዜ "እድሜው ከ40 ዓመት በላይ የሆነ አትሌት በማራቶን ያስመዘገበው የምንጊዜውም ፈጣን ሰዓት" በሚል ተመዝግቦለታል። በአሜሪካው የስፖርት ቴሌቪዥን ጣቢያ 'ኢኤስፒኤን' ከሳምንት በፊት የ21ኛው ክፍለ ዘመን 10 ታላላቅ አፍሪካውያን ስፖርተኞችን ዝርዝር ይፋ ሲያደርግ አትሌት ቀነኒሳ በቀለን አካቶታል። አንጋፋው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በሚሳተፍበት የማራቶን ውድድር የተሻለ ውጤት ያስመዘግባል የሚል የቅድሚያ ግምቶችን ከወዲሁ እያገኘ ነው።                          
በፓሪስ ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ለሚሮጠው ኤርሚያስ ይርጋ ሽኝት ተደረገለት
Jul 26, 2024 146
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሻምበል አበበ ቢቂላን ፈለግ በመከተል በኦሎምፒክ መድረክ በባዶ እግሩ ለሚሮጠው ኤርሚያስ ይርጋ ሽኝት አድርጎለታል። የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በሽኝቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በሮም ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ስሟ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ካደረጉ የኦሎምፒክ ጀግኖች መካከል ቀዳሚው አበበ ቢቂላ ነው። የእሱን አርአያነት በመከተል በባዶ እግር በመሮጥ የሀገርን ስም ለማስጠራት እና ሻምበል አበበ ቢቂላን በሚያስታውስ መንገድ ለመሮጥ ወደ ፓሪስ በሚደረገው ጉዞ እንዲቀናውና በድል እንዲመለስም መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል። በአለም አደባባይ በባዶ እግር በመሮጥ ኦሎምፒክ ያሸነፈ ብቸኛው አፍሪካዊ ብሎም ኢትዮጵያዊ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላን ገድል መዘከር የሁሉም ትውልድ ሃላፊነት እንደሆነ የገለፁት የስፖርት ዘረፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ናቸው። በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬም በባዶ እግር መሮጥ እንደሚቻል እና የቀደምት ጀግና ታሪክን ይዞ ለማስቀጠል ወደ ፓሪስ በማቅናት በባዶ እግሩ ለሚሮጠው ኤርሚያስ ይርጋ ክብር ይገባዋል ብለዋል። የቀድሞ ሞተር ስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤሪሚያስ ይርጋ በበኩሉ በሮም፣ በአቴንስ፣ በደቡብ ኮሪያና በእንግሊዝ በተካሄዱ ኦሎምፒኮች ላይ በባዶ እግር በመሮጥ ሻምበል አበበ ቢቂላን ማስታወስ እንደቻለ መግለፁን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ግዙፉ የስፖርት ሁነት የፓሪስ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራል 
Jul 26, 2024 117
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ በፓሪስ የሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ በይፋ ይጀመራል። የዘንድሮው ኦሊምፒክ መክፈቻ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስታዲየም ውጪ በወንዝ ላይ ይደረጋል። በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከ203 ሀገራት የተወጣጡ 10 ሺህ 500 አትሌቶች በ32 የስፖርት አይነቶች እንደሚወዳደሩ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል። ከሀገራቱ በተጨማሪ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር ገለልተኛ አትሌቶችና የኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድን ይሳተፋሉ። ኢትዮጵያም በዋናነት በተለያዩ ርቀቶች በሚደረጉ የአትሌቲክስ የስፖርት ውድድሮች በ39 ስፖርተኞች የምትካፈል ሲሆን አትሌቶቹ ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም አንስቶ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ፈረንሳይ የኦሊምፒክ ተሳታፊ ሀገራትን ቀይ ምንጣፍ በመዘርጋት እየተቀበለቻቸው ሲሆን ለታላቁ ድግስ 9 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንዳደረገች መረጃዎች ያመለክታሉ። የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርዓት በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ30 አንስቶ የሚከናወን ሲሆን የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ በኦሊምፒክ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስታዲየም ውጪ በወንዝ ዝላይ ይደረጋል። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ 10 ሺህ 500 ስፖርተኞች በሰሜናዊ ፈረንሳይ በሚገኘው ሴይን ወንዝ ላይ በመርከብ የ3 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ጉዞ በማድረግ የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ይከናወናል። አትሌቶች የመርከብ ጉዟቸው ከኦስተርሊትዝ ድልድይ ጀምረው በኖትሬ-ዳም ካቴድራል፣ ሉቭር ሙዚየም ፣ 'ፓላስ ዴላ ዲ ኮንኮርድ' እየተባለ በሚጠራው የሕዝብ አደባባይ፣ ጥንታዊ ሕንጻዎች ባሉበት 'ኢንቫሊዴስ' መንደርና ታሪካዊውን ኤይፍል ታወር አቋርጠው 'ትሮካዴሮ' የተሰኘው ስፍራ ላይ መዳረሻቸውን ያደርጋሉ።   "የብርሃን ከተማ" እየተባለች የምትጠራው ፓሪስ በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ በብርሃን የደመቀ ዝግጅት ታሳያለች ተብሎ ሲጠበቅ በስነ ስርዓቱ ላይ ሙዚቀኞችና 400 ዳንሰኞችን ጨምሮ 3 ሺህ ሰዎች ስራቸውን በቦታው ያቀርባሉ። የማሊና የፈረንሳይ ጥምር ዜግነት ያላት የ29 ዓመቷ ድምጻዊና የዜማ ደራሲ አያ ናካሙራ በመክፈቻው ስነ ስርዓት ስራዋን ታቀርባለች። አሜሪካዊቷ ሌዲ ጋጋና ካናዳዊቷ ኮከብ ሴሊን ዲዮን የሙዚቃ ስራቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የመክፈቻ ስነ ስርዓቱን 300 ሺህ ተመልካች እንደሚከታተለው የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል። እስከ አሁን ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ የኦሊምፒክ ችቦውን ይለኩሰዋል ተብሎ እንዲሚጠበቅ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው። ከኦሊምፒክ መክፈቻ ስነ ስርዓቱ በፊት ባሉት ቀናት የወንዶችና የሴቶች የእግር ኳስ ውድድር፣ ራግቢ፣ የእጅ ኳስና የኢላማ ተኩስ ስፖርቶች ተጀምረዋል። 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።              
ስፖርት አንዱ የልማት ዘርፍ ነው - አቶ ተመስገን ጥሩነህ
Jul 25, 2024 116
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ ስፖርት እንደ ሀገር አንዱ የልማት ዘርፍ ከመሆኑም በላይ መንፈሰ ጠንካራ፣ ንቁና ጤነኛ ዜጋ ለመፍጠር ሁነኛ መሳሪያ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ተቀዛቅዞ የቆየውን የብሄራዊ ስፖርት ምክር ቤት ወደ ስራ ማስገባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል። ዛሬ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አመራሮች ጋር ባደረግነው ውይይት ለሀገራችን ስፖርት ዕድገት የሚጠቅሙ በርካታ ሀሳቦች ላይ በመወያየት ችግር ፈቺ መንገዶችን ለይተናል ብለዋል፡፡ ስፖርት እንደ ሀገር አንዱ የልማት ዘርፍ ከመሆኑም በላይ መንፈሰ ጠንካራ፣ ንቁና ጤነኛ ዜጋ ለመፍጠር ሁነኛው መሳሪያ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ የብሄራዊ ስፖርት ምክር ቤት አደረጃጀትን በመፈተሸ መልሶ ለማደራጀትና ተቀዛቅዞ የነበረውን ብሄራዊ ስፖርት ምክር ቤት ወደ ስራ ማስገባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አቅጣጫ አስቀምጠናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የተጨዋቾች ዝውውርና የክለቦች የክፍያ አስተዳደር መመሪያ በማያከብሩ የሊጉ ክለቦች ላይ እርምጃ ሊወስድ ነው
Jul 24, 2024 223
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የተጨዋቾች ዝውውርና የክለቦች የክፍያ አስተዳደር መመሪያን በሚጥሱ የሊጉ ክለቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳሰበ። የ2017 ዓ.ም.የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተጨዋቾች ዝውውርና የክለቦች የክፍያ አስተዳደር መመሪያ አፈጻጸምን አስመልክቶ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሮችን የተመለከተ ጥናት ከሁለት ዓመት በፊት ማስጠናቱ የሚታወስ ነው። ከጥናቱ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ ክለቦች ያላቸው የፋይናንስ አስተዳደር እንዲሻሻል ምን መደረግ አለበት? የሚለው ላይ ሲሆን ጥናቱን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የክፍያ ሥርዓት አስተዳደር መመሪያ ተዘጋጅቷል። ይህ መመሪያ በሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም ማኅበሩ ባካሄደው 4ኛው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ጸድቋል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፤ መመሪያው ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ከተጀመረው የ2017 ዓ.ም.የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ጀምሮ ተፈጻሚ መሆኑን ገልፀዋል። በመመሪያው አማካኝነት ክለቦች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዝውውር ውል ሳያጸድቅ ለተጨዋቾች አስቀድመው የቅድመ ክፍያ መፈጸምና በቼክ ገንዘብ መክፈል እንደማይችሉ አመልክተዋል። በተጨማሪም ክለቦች በዓመት ለተጨዋቾችና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ደመወዝና ጥቅማጥቅም ከ57 ሚሊየን 750 ሺህ ብር በላይ ክፍያ መፈጸም አይችሉም ብለዋል። የሊጉ ክለቦች የተቀመጡትን አሠራሮች የሚጥሱ ከሆነ ከገንዘብ ቅጣት አንስቶ ውድድር መታገድ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ነው ሰብሳቢው የገለጹት። ክለቦች በመመሪያው ላይ ያላቸውን ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉበት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው፤ በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች ተጨዋቾችን ሲያስፈርሙ ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች አስመልክቶ ገለፃ አድርገዋል። ክለቦች አንድ ተጨዋች ሲያስፈርሙ ፌዴሬሽኑ ዝውውሩ የተሟላ መሆኑን ይፋ የሚያደርገው የሕይወትና የአደጋ ጊዜ ኢንሹራንስ፣ የሕክምና ሰርቲፊኬት፣ የልደት ሰርቲፊኬትና በፊት ከሚጫወትበት ክለብ መልቀቂያ(ክሊራንስ) ሲያሟሉ ብቻ ነው ብለዋል። ፌዴሬሽኑ በመመሪያው አፈጻጸም ላይ ላይ ከሊጉ አክሲዮን ማኅበሩ ጋር በትብብር እንደሚሰራም አመልክተዋል። መመሪያው ለተጨዋቾችና ለአሰልጣኞች በግል የሚከፈላቸው ክፍያ ላይ ገደብ እንደማያስቀምጥና ዋንኛ ትኩረቱ ዓመታዊ ጥቅል የክለቦች ክፍያ ጣሪያ እንደሆነና ከደመወዝና ጥቅማጥቅም ክፍያ ውጭ በሌሎች ወጪዎች ላይ ገደብ እንደማያስቀምጥ የአክሲዮን ማኅበሩ መረጃ ያመለክታል። ማኅበሩ የተጨዋቾችና አሰልጣኞችን አጠቃላይ ዓመታዊ ክፍያ የሚቆጣጠር ኮሚቴ ወደ ሥራ ማስገባቱ የሚታወስ ነው። የ2017 የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ እስከ መስከረም 26 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ በምድብ 1 ተደለደለ
Jul 24, 2024 174
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በ2024/25 የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ዞን ማጣሪያ በምድብ 1 ተደልድሏል። ​​​​የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ዛሬ በተቋሙ ዋና መቀመጫ ግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ ላይ አከናውኗል። ኢትዮጵያን በሴካፋ ዞን ወክሎ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በምድብ 1 ከኬንያው ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ ፣ከሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ፣ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስና ከዛንዚባሩ ዋሪየር ኩዊንስ ጋር ተደልድሏል።   የታንዛኒያው ሲምባ ኩዊንስ፣ የብሩንዲው ፒቪፒ ቡዬንዚ፣ የዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊምና የጅቡቲው ፋድ በምድብ 2 የተደለደሉ ክለቦች ናቸው። የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከነሐሴ 11 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው። ንግድ ባንክ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሲሳተፍ የዘንድሮው ለአራተኛ ተከታታይ ዓመት ነው። ክለቡ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ሶስት ተሳትፎዎች በሁለቱ ፍጻሜ ደርሶ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ባስመዘገባቸው ውጤቶች ለካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማለፍ አልቻለም። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአራተኛ ተሳትፎው የማጣሪያ ውድድሩን ካሸነፈ ለመጀመሪያ ጊዜ በሻምፒዮንስ ሊጉ ይሳተፋል። ካፍ በዘንድሮው የማጣሪያ ውድድር 38 ክለቦች በስድስት ዞኖች ተከፍለው ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ አስታውቋል።ክለቦቹ የካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ መስፈርቶችን ማሟላታቸውንም ገልጿል። በስድስቱ ዞኖች የሚያሸንፉ 6 ሀገራት፣ የወቅቱ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሳንዳውንስና የውድድሩን የመጨረሻ ዙር የሚያዘጋጀው ሀገር ቡድን ጨምሮ 8 ክለቦች እ.አ.አ በ2025 ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማሉ። የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የተጀመረው እ.አ.አ በ2020 ነው። የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሳንዳውንስ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ያነሳ ሲሆን የሞሮኮው ኤኤስ ፋር ራባት ውድድሩን አንድ ጊዜ አሸንፏል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወንዶችም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ እንደሚሳተፍ ይታወቃል።
የ33ኛው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ዛሬ ይጀመራል 
Jul 24, 2024 154
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2016(ኢዜአ)፦በፓሪስ የሚካሄደው 33ኛው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ጅማሮውን ያገኛል። በውድድሩ ላይ 16 ሀገራት 4 ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ሁሉም ተሳታፊ ብሔራዊ ቡድኖች የመክፈቻ መርሐ ግብራቸውን ዛሬ ያከናውናሉ። በምድብ 3 ኡዝቤኪስታን ከስፔን እንዲሁም በምድብ 2 አርጀንቲና ከሞሮኮ በተመሳሳይ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በምድብ 1 ጊኒ ከኒውዝላንድ፣ በምድብ 3 ግብጽ ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ በተመሳሳይ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ከምሽቱ 2 ሰዓት በምድብ 2 ኢራቅ ከዩክሬንና በምድብ 4 ጃፓን ከፓራጓይ የሚጫወቱ ሲሆን በምድብ 1 አዘጋጇ ሀገር ፈረንሳይ ከአሜሪካና በምድብ 4 ማሊ ከእስራኤል በተመሳሳይ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ መርሐ ግብራቸውን የሚያካሂዱ ይሆናል። የወንዶች የእግር ኳስ ውድድር እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል። በተያያዘ ዜና የ33 ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ መርሐ ግብር ነገ ይጀመራል። በውድድሩ ላይ 12 ሀገራት በ3 ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በምድብ 1 አዘጋጇ ሀገር ፈረንሳይ ፣ ኮሎምቢያ ፣ ካናዳና ኒውዝላንድ እንዲሁም በምድብ 2 አሜሪካ ፣ ጀርመን ፣ አውስትራሊያና ዛምቢያ ተደልድለዋል። ብራዚል ፣ ስፔን፣ ጃፓንና ናይጄሪያ በምድብ 3 የተደለደሉ ሀገራት ናቸው። የሴቶች የእግር ኳስ ውድድር እስከ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል። በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የራግቢ ስፖርት ውድድር ዛሬ የተጀመረ ሲሆን ከኦሊምፒክ መክፈቻ ስነ ስርዓት በፊት የእጅ ኳስና ኢላማ ተኩስ ውድድሮች እንደሚጀመሩ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል። የ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርዓት ከነገ በስቲያ ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ ከ206 ሀገራት የተውጣጡ እንዲሁም በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር የሚወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶችና የኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድን ጨምሮ 10 ሺህ 714 ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋሉ። የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።            
በፓሪስ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ ስፖርተኞች የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት እና የቱሪዝም ሀብቶች ለአለም እንዲያስተዋውቁ ጥሪ ቀረበ
Jul 23, 2024 182
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2016(ኢዜአ)፦ በፓሪስ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ ስፖርተኞች የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት እና የቱሪዝም ሀብቶች ለአለም እንዲያስተዋዉቁ የቱሪዝም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ። ቱሪዝም ሚኒስቴር በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የሽኝት መርሐ ግብር አካሂዷል። በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በዚሁ ጊዜ ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በሚካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ በተለያዩ ስፖርቶች እንደምትሳተፍ ገልጸዋል። በዚህም ውድድር የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ልጆች አሸናፊነት በአለም ህዝብ ዘንድ የሚጠበቅ ነው። ይህም ከትውልድ ትውለድ ሲተላለፍ ከመጣው የአሸናፊነት ታሪክ በመሆኑ ነው ብለዋል። ይህንን መልካም ዕድል በመጠቀም የኢትዮጵያ መለያዎችንና መታወቂያዎችን ለአለም ህዝብ እንዲያስተዋውቁ ጠይቀዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ምድረ-ቀደምትነት የቡና፣ የአለም ትልቁ ወንዝ መገኛ፣ የአፍሪካ ነጻነት ምልክት መሆኑን በውድድሩ ወቅት እንዲያንፀባርቁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ለዚህም የሚሆን የተለያዩ የህትመት ስራዎች እና አልባሳት በቱሪዝም ሚንስቴር አማካኝነት እንደተዘጋጀ ተናግረዋል። አትሌቶቻችን በሚያደርጓቸው ውድድሮች ካሸነፉ በኋላ ለ1 ደቂቃ ያህል በስታዲየሞች ውስጥ የሚከፈት የኢትዮጵያን ምድረ-ቀደምትነት የሚገልፅ ሙዚቃ እና ምስልም ለልዑክ ቡድኑ ተወካዮች አስረክበዋል። አምባሳደር ናሲሴ አትሌቶች፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፓሪስ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማስተዋወቅ ከወዲሁ እያደረጉት ላለው ዝግጅት አመስግነዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን የታዳጊዎች የክረምት በጎ ፍቃድ ስልጠና አስጀመረ
Jul 23, 2024 205
አሶሳ፤ ሐምሌ 16/2016 (ኢዜአ)፦ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ከበጎ ፍቃደኛ አሰልጣኞች ጋር በመተባበር የክረምት በጎ ፍቃድ የስፖርታዊ ስልጠና አገልግሎት አስጀምሯል። የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዩሱፍ አልበሽር እንዳሉት ታዳጊዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በስፖርት እንዲያሳልፉ እና የክረምት ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል። በመርሃ ግብሩ ታዳጊዎቹ እግርኳስ፣ ቮሊቦል፣ ወርልድ ቴኳንዶ እና የቦክስ ስልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን፤ መደበኛው የታዳጊ ፕሮጀክት ስልጠናም የሚቀጥል መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። በብልጽግና ፓርቲ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኡስማን አህመድ በበኩላቸው የዘንድሮው የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሁሉንም ዘርፎች ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።   አቶ ኡስማን እንዳሉት ታዳጊዎችን በስፖርት ዘርፍ በበጎ ፍቃደኝነት ሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች የነገ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ወጣቶችን ለማሳደግ በበጎ ፈቃደኝነት መነሳሳታቸው ያስመሰግናቸዋል ብለዋል። ለታዳጊዎቹ የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በቀጣይም በስፖርቱ ዘርፍ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሁሉም ቦታዎች እንደሚቀጥል ተገልጿል። የስፖርት ስልጠና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን የሚሰጡት በአሶሳና አካባቢዋ በሙያው የተሻለ ልምድ እውቀት ያላቸው በጎ ፈቃደኛ አሰልጣኞች መሆናቸውም ታውቋል።  
አትሌቶች ወደ ፓሪስ ይዛችሁ የምትሄዱት ኢትዮጵያን በመሆኑ ለስኬት መትጋት ይጠበቅባችኋል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
Jul 22, 2024 404
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፦አትሌቶች በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከምንም በላይ ኢትዮጵያን በማስቀደም ሀገራቸውን ስኬታማ ለማድረግ መትጋት እንዳለባቸው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ። በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የሽኝት መርሐ በብሔራዊ ቤተ መንግስት እየተካሄደ ይገኛል። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አትሌቶች በተለያዩ የዓለም መድረኮች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይም ኢትዮጵያ ብዙ ሜዳሊያዎችን እንደምታመጣ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡ አትሌቶች ኢትዮጵያን በማስቀደም በጠንካራ የቡድን መንፈስና ትብብር ሀገራቸውን ውጤታማ ለማድረግ መስራት እንደሚኖርባቸውም ተናግረዋል። ማንም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ክብር አይደራደርም፤ ኢትዮጵያዊነት በጋራ የመቆም አቅምና መንፈስን የሚያጎናጽፍ ማንነት ነው ብለዋል። አትሌቶች ሀገርን ከማስጠራት ጎን ለጎን በስፖርታዊ ጨዋነት ውድድራቸውን እንዲያደርጉም ነው ጥሪ ያቀረቡት። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አስረክበዋል። 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በፓሪስ ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ ከ206 ሀገራት የተወጣጡ (በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር የሚወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶችና የኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድን ጨምሮ) 10 ሺህ 714 ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋሉ። ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ፣ ውሃ ዋናና ቦክስ በ39 ስፖርተኞች ትሳተፋለች።
በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ሽኝት እየተደረገለት ነው
Jul 22, 2024 223
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፡- በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ሽኝት እየተደረገለት ይገኛል። በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ተሳታፊ ስፖርተኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በፓሪስ ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ ከ206 ሀገራት የተወጣጡ (በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር የሚወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶችና የኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድን ጨምሮ) 10 ሺህ 714 ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋሉ። ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ፣ ውሃ ዋናና ቦክስ በ39 ስፖርተኞች ትሳተፋለች።
የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ይፋ የሚደረግበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ዓለም አቀፍ የቦክስ ሻምፒዎና ሊካሄድ ነው
Jul 19, 2024 482
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ይፋ የሚደረግበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ዓለም አቀፍ የቦክስ ሻምፒዎና ሊካሄድ ነው። የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ውድድሩ "አፍሪካ ዩናይት" በሚል መሪ ሃሳብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልጿል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የኢትዮጵያ ቦክስ በየጊዜው እድገት እያሳየ በአህጉርና ዓለም አቀፍ መድረኮች በውጤት መታጀብ ጀምሯል ብለዋል። በተለይ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት መቀመጫ ኢትዮጵያ መሆኗን ተከትሎ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ጽህፈት ቤቱ በአዲስ አበባ በይፋ እንደሚከፈት አስታውቀዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍ ደረጃ የአመራርነት ሚናዋ ዛሬም የጎላ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ገልፀዋል። የጽህፈት ቤቱ በአዲስ አበባ መከፈት ለሀገሪቱ የስፖርት ዕድገት መነቃቃት እንደሚፈጥር በማስታወቅ በተጨማሪም በሀገር ገፅታ ግንባታ እና በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ እምርታ ያመጣል ብለዋል። የመገናኛ ብዙሃንም የጽሕፈት ቤቱን መከፈት እና የዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድሩን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያ ገፅታን የሚገነቡ ተግባሮችን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል። የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን በበኩላቸው የኮንፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ መከፈቱ ኢትዮጵያ አህጉር አቀፍና ዓለማቀፍ ውድድሮችን እንድታስተናግድ ያግዛትል ሲሉ ገልፀዋል። በዚህም ምክንያት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ዓለምአቀፍ የቦክስ ሻምፒዮና እንደሚከናወን ተናግረዋል። የዓለምአቀፉ ቦክስ አሶሴሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚስተር ክርስቶፈር ሮበርትስ ኢትዮጵያ የተሰጣትን ኃላፊነት በሚገባ እንደምትወጣ እምነት እንዳላቸውና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። ዓለምአቀፍ የቦክስ ሻምፒዮናው በስምንት የተለያዩ የኪሎግራም ምድቦች ተክፍሎ እንደሚካሄድ ተገልጿል። በሴቶች በ60 ኪ.ግ ሚሊየን ጨፎ ከኢትዮጵያ እና ሀድጅላ ከሊፍ ከአልጀሪያ የሚወዳደሩ ሲሆን በ54 ኪ.ግ ውድድር ደግሞ ውዳድ በርታል ከሞሮኮ እና ሳራ ሀግሂግሃት ጆ ከሴራሊዮን ይወዳደራሉ። በ75 ኪ.ግ ፓትሪሺያ ምባታ ከናይጄሪያ እና ራዲ አዶንሲንዳ ግራማኒ ከሞዛምቢክ እንዲሁም በወንዶች 92 ኪ.ግ ፒተር አቡቲ ከኬኒያ እና አሎሬ አድማስ ከናይጄሪያ የሚወዳደሩ ይሆናል። በ75 ኪ.ግ ደግሞ ያሲኔ ኢሎረዝ ከሞሮኮ እና ቲያንጎ ሙታንጋ ከሞዛምቢክ ይወዳደራሉ። በ60 ኪ.ግ አቡበከር ሴፈን ከኢትዮጵያ እና ራሺድ ኦማሪ ከሶማሌያ ሲወዳዳሩ፤ በ80 ኪ.ግ ፒታ ካቤጂ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የሱፍ ቻንጋላዊ ከታንዛኒያ የሚወዳደሩ ይሆናል። በ51 ኪ.ግ ፓትሪክ ችንየምባ ከዛምቢያ እና ዴቪድ ፒና ከኬፕቨርዴ በውድድሩ እንደሚፋለሙ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ካወጣው መርሐ ግብር መረዳት ተችሏል።  
የደራርቱ ቱሉ ስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩት ስፖርትን በሳይንሳዊ መንገድ መምራት የሚያስችል ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ 
Jul 18, 2024 388
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ11/ 2016 (ኢዜአ)፡- የደራርቱ ቱሉ ስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩት ስፖርትን በሳይንሳዊ መንገድ መምራት የሚያስችል መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ። የክልሉ መንግሥት በሱሉልታ ከተማ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባው የደራርቱ ቱሉ ስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩት ተመርቋል። ፕሮጀክቱን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ-ልማትን በማስፋፋት ለዘርፉ እድገት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የስኬት ተምሳሌት በሆነችው ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ስም ተገንብቶ የተመረቀው ኢንስቲትዩትም የዚሁ ሥራ ማሳያ ነው ብለዋል።   ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ለስምንት ዓመታት በግንባታ ላይ ቆይቶ በተለያዩ ችግሮች ሳይጠናቀቅ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ለስፖርቱ የላቀ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል። ኢንስቲትዩቱ ስፖርቱን በሳይንሳዊ መንገድ በመምራት ዓለም አቀፍ ተፎካካሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል። በአንድ ጊዜ በ16 የስፖርት አይነቶች 800 ስፖርተኞችን ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም ያለው መሆኑ ተገልጿል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፤ የስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩቱ ብቁ አትሌቶችን ከማፍራት ባለፈ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስችል መሆኑን ገልጻለች። ለሀገር ላበረከተችው አስተዋጽዖ እውቅና በመስጠት ኢንስቲትዩቱ በስሟ በመሰየሙ የላቀ ምስጋናዋን አቅርባለች። “ኢንስቲትዩቱ ከሰራሁት በላይ ታሪክ ያለው ለወጣቱ ትውልድ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል፤ ዜጎች ለሀገራቸው በቻሉት አቅም ሊያገለግሉ ይገባል” በማለትም መልዕክቷን አስተላልፋለች። በክልሉ ከዚህ በፊት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ካሉት መካከል የአምቦ ጎል (ፊፋ) እግር ኳስ አካዳሚ፣ የቦቆጂ እና ቦሬ አትሌቲክስ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት ይገኙበታል፡፡    
በቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ለሚገነባው ስታዲየም የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
Jul 17, 2024 443
ሆሳዕና፣ሐምሌ 10/2016 (ኢዜአ )፡-የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በሃላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ ለሚገነባው ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ። አቶ እንደሻው በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ የስታድየሙ መገንባት በክልሉ ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን በማውጣት በአገር አቀፍ ደረጃ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችል ነው። ስታዲየሙ የግንባታ ሥራው በሦስት ምዕራፍ ተከፋፍሎ እንደሚከናወንና ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበት ገልጸዋል።   ለመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግም በመርኃ ግብሩ ላይ ተገልጿል። የሀላባ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታገል ጌታቸው በበኩላቸው፤ አካባቢው ለስፖርት ዘርፍ ጥሩ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶችና ማህበረሰብ ያሉበት መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ የወጣቶችን የስፖርት ዝንባሌ ወደ ውጤት ለመቀየር የስፖርት መሰረተ ልማት ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጹት። በዞኑ በዘርፉ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብም በቁሊቶ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ለመገንባት የዝግጅት ሥራው ተጠናቆ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን ተናግረዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ በመጀመሪያ የስታዲየሙ ግንባታ ምዕራፍ የሰው ሰራሽ ሜዳና መሰል ሥራዎች ይከናወናሉ።   በሁለተኛውና በሦስተኛው ምዕራፍ የመሮጫ መም እና የመብራት እንዲሁም ሌሎች ሥራዎች እንደሚከናወኑ አቶ ታገል ገልጸው፣ ግንባታው በዞኑ ህዝብ ተሳትፎ እንደሚከናወን ተናግረዋል። ስታድየሙ ለተጫዋቾች የሚሆን መታጠቢያ ቤቶች፣ የልብስ መቀየሪያ እና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች እንደሚኖሩትም አመልክተዋል። የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ በተዘጋጀ ስነ ስርአት ላይ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የክልል እና የዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የእግር ኳስ ቤተሰቡ ተገኝተዋል።    
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀጣይ ዓመት መስከረም 10 ይጀመራል
Jul 17, 2024 418
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 10/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀጣዩ የውድድር ዓመት መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጀምር የሊጉ አክሲዮን ማኅበር አስታወቀ። ማኅበሩ ውድድሩን በተጠቀሰው ጊዜ እንደሚጀመር ለተሳታፊ ክለቦች ማሳወቁን ገልጿል። በቀጣዩ የውድድር ዓመት 19 ክለቦች ተሳታፊ ናቸው። የትግራይ ክለቦች በ2017 ዓ.ም ውድድር ከማቆማቸው በፊት ወደነበሩበት ሊግ እንዲመለሱ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ስሑል ሽሬና መቀሌ ሰብዓ እንደርታ በሊጉ ላይ ይሳተፋሉ። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉት አርባ ምንጭ ከተማና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በቀጣይ ዓመት በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ናቸው። በ2017 ዓ.ም የውድድር ዘመን በ19 ክለቦች መካከል ውድድር ተደርጎ 5 ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ እንደሚወርዱ ተገልጿል። በ2018 የውድድር ዓመት ሁለት ክለቦች ደግሞ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንደሚያድጉም እንዲሁ። ይህንንም ተከትሎ በ2018 ዓ.ም ሊጉ ወደነበረበት 16 ክለቦች እንደሚመለስ ነው ማኅበሩ ያስታወቀው። የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም መጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድሩ አሸናፊ መሆን ችሏል።      
ስፔን የአውሮፓ ዋንጫን ለአራተኛ ጊዜ በማንሳት አዲስ ታሪክ ጻፈች
Jul 15, 2024 435
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2016 (ኢዜአ)፦ በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን 2 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች። በበርሊን ኦሊምፒክ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ከእረፍት መልስ በ47ኛው ደቂቃ ከላሚን ያማል የተሻገረለትን የ22 ዓመቱ የአትሌቲኮ ቢልባኦ የክንፍ ተጫዋች ኒኮ ዊሊያምስ ከመረብ ላይ በማሳረፍ ስፔንን መሪ አድርጓል። ይሁንና ተቀይሮ የገባው የ22 ዓመቱ የቼልሲ የአጥቂ አማካይ ኮል ፓልመር በግሩም ሁኔታ ያስቆጠራት ግብ እንግሊዝን አቻ አድርጓል። ፓልመር ግቧን ያስቆጠረው በኮቢ ሜይኖ ተቀይሮ በገባ በሶስት ደቂቃ ውስጥ ነው። በ86ኛው ደቂቃ ማርክ ኩኩሬያ በግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው የ27 ዓመቱ የሪያል ሶሴዳድ አጥቂ ማይክል ኦያርዛባል ከመረብ ላይ ያሳረፋት ጎል ስፔንን አሸናፊ አድርጋለች። ውጤቱን ተከትሎ ስፔን የአውሮፓ ዋንጫን ለአራተኛ ጊዜ በማሸነፍ አህጉራዊውን ዋንጫ ለበርካታ ጊዜ ያነሳች ሀገር መሆን ችላለች። ስፔን በውድድሩ ያደረገቻቸውን 7 ጨዋታዎችን አሸንፋለች። ስፔን በጨዋታው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራት ሲሆን በርካታ የግብ ሙከራዎችን አድርጋለች። እንግሊዝ በሁለት ተከታታይ የአውሮፓ ዋንጫ ውድድሮች ለፍጻሜ ብትደርስም በሁለቱም አጋጣሚዎች ድል አልቀናትም። ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት በበርሊን የኦሊምፒክ ስታዲየም ደማቅ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ተካሄዷል። 18ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በእንግሊዝ ፣ስኮትላንድ፣ዌልስ፣ አየርላንድና ሰሜን አየርላንድ ጣምራ አዘጋጅነት እ.አ.አ በ2028 ይከናወናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም