ባጃጅ ላይ ወድቆ የተገኘው የአደራ ገንዘብ- 82 ሺህ 265 ብር - ኢዜአ አማርኛ
ባጃጅ ላይ ወድቆ የተገኘው የአደራ ገንዘብ- 82 ሺህ 265 ብር

በአማራ ክልል ዋግኸምራ አስተዳደር የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው ባለባጃጅ ወጣት ሠለሞን ቢምረው ተሳፋሪ ደንበኞቹን ከቦታ ቦታ በማዘዋወር ዕለታዊ ተግባሩን ይከውናል።
ዛሬ ማለዳ ታዲያ በሰቆጣ ወረዳ የሰርክ ተግባሩን እያከናወነ ሳለ በድንገት ከአንድ ተሳፋሪ የተረሳ በኬሻ የተቀመጠ ንብረት ባጃጁ ውስጥ ያገኛል።
ሰለሞን ቢምረው ማንነቱን ባላወቀው ተሳፋሪ የተረሳው ምንነቱን ያላወቀው በኬሻ የተቋጠረ ንብረት ገንዘብ መሆኑን ያወቀው ከደቂቃዎች በኋላ ነበር።
'ታማኝነት ለራስ ነው' የሚለው ወጣት ሰለሞን፥ ከተሳፋሪ ደንበኛ የተረሳን መጠኑን ያላወቀው ገንዘብ ለመመለስ ተጣደፈ።
ተሳፋሪውን በእግር በፈረስ ማፈላለግ ይጀምራል።
በሌላ በኩል የሰቆጣ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘር ኃይሌ በአደራ የተረከቡትን በኬሻ የተቋጠረ 82 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ፌርማታ ላይ ከባጃጅ ሲወርዱ መርሳታቸውን ካወቁበት ቅጽበት ጀምሮ በደንጋጤ ድባቴ ውስጥ ገብተዋል።
ጉዳያቸውን ለፖሊስ አሳውቀው የአደራ ገንዘባቸውን በይገኛል ተስፋ እና ጭንቀት የባጃጅ አሽከርካሪውን ፍላጋ በየፌርማታው እየኳተኑ ነው።
ተሳፋሪ እና አሳ'ፋሪ በየፊናው መፈላለጉን ተያያዙት።
በዚህ መሀል የባጃጅ አሽከርክሪው ሰለሞን ቢምረው ወደ ተሳፋሪዋ ወይዘር ኃይሌ ድንገት ከተፍ ይላል።
የወይዘሮ ወይዘር ደስታ ወደር አጣ።
አሳፋሪው ሰለሞንም እፎይታ ተሰማው። በተለይ የአደራ ገንዘብ መሆኑን ሲረዳ።
ባጃጅ አሽከርክሪው ሰለሞን እና ተሳፋሪዋ ወይዘሮ ወይዘር በፖሊስ ፊት ንብረት ተረካከቡ።
ወጣቱ ሰለሞን እንደገለጸው የተሳፋሪ ንብረት በመመለሱ ደስተኛ ነው።
ለወይዘሮ ወይዘር አደራ ያስረከበችው የገንዘቡ ባለቤት ወይዘሪት ወለለ ንጉስ፤ በሰለሞን ቢምረው ነባይነት(ታማኝነት) እንዳስገረማቸው ይናገራሉ።
በዚህ ወቅት ይህን ያህል ገንዘብ አግኝቶ መመለስ በዕውነቱ በነፍስም በስጋም የሚያስመሰገን በጎ ምግባር ነው ስትል አመስግናለች።
የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ደሳለኝ አባተ ወጣት ሰለሞን ከአሁን ቀደምም ሞባይል ጥለው የሄዱትን ለባለቤቱ በታማኝነት መመለሱን አስታውሰዋል።
አሁን ደግሞ በኬሻ የተቋጠረን 82 ሽህ 265 ብር ከግል ይልቅ የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ለግለሰቧ በታማኝነት ማስረከቡን አረጋግጠዋል።
ይህን መሰል በጎ ምግባር በሁሉም የማህበረሰብ ዘንድ በአርዓያነት ሊወሰድ የሚገባው ነው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።