የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ በአልሸባብ ጥቃት በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ በአልሸባብ ጥቃት በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገለፁ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2016 (ኢዜአ)፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ አሸባሪው አልሸባብ ከሰሞኑ በሶማሊያ በፈፀመው የሽብር ጥቃት በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሃዘን ገለፁ።
አምባሳደር ታዬ ባስተላለፉት የሃዘን መልዕክት በሽብር ቡድኑ ጥቃት ምክኒያት በደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት እና አካል ጉዳት ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸው ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ እንዲሁም በራሳቸው ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ለሶማሊያ መንግስት እና ህዝብ የገለጹት ሚኒስትሩ ፤ በልምምድ ወቅት ወታደራዊ መኮንኖችን ኢላማ በማድረግ የተፈፀመውን ጥቃት የወንጀል ተግባር ነው ብለዋል።
የወንጀል ተግባሩን ኢትዮጵያ በፅኑ እንደምታወግዘውም ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል።
ጥቃቱ አልሸባብ የሽብር ቡድን በሶማሊያ እና በክፍለ አህጉሩ ደህንነት አደጋ መደቀኑን በግልፅ ያረጋገጠ መሆኑን በመግለፅ ፥ የአካባቢው ሀገራት በፀረ ሽብር የሚያደርጉትን ትብብር ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የሶማሊያን ሰላም እና ደህንነት በጋራ ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ትብብሯን አጠናክራ በቁርጠኛነት እንደምትቀጥልም ባስተላለፉት የሃዘን መልዕክት ማስታወቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።