ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት - የሕዝብ ድምጽ

ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት - የሕዝብ ድምጽ

ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ፍኖቷ ለአፍሪካ አርአያ ሆና አሳይታለች...

የአፍሪካውያን ቀንዲል ናት። የክፉ ቀን መሸሸጊያቸው፣ የመከራ ጊዜ መጽናኛቸው፣ የነጻነት ተምሳሌትና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በረጅም ዘመናት ታሪካዊ መስተጋብር የተፈጠረ የሀገረ መንግሥት መዋቅር ባለቤት ናት። በተፈጥሮ ጸጋዎች፣ ምድሯን ሰንጥቀው በሚያልፉ ወንዞቿ የምትታወቅ አገር ናት። የተለያዩ ማዕድናት በብዛት የሚገኙባት ከመሆኗም በላይ፣ የበርካታ ብሔረሰቦች ባህልና እሴቶች ሕብር ሠርተው፣ ተስማምተው የሚኖሩባት የታሪክ ማህደር ናት። ይሁን እንጂ ይህ ታሪካዊ ግርማ ሞገስና የነጻነት አርማነት፣ በውስጣዊ የፖለቲካ ጉዞዋ ውስጥ ካጋጠሟት መዋቅራዊ ስብራቶችና የሥልጣን ፍትጊያዎች ሊታደጋት አልቻለም።

ለዘመናት በሀገሪቷ የሰፈነው የሥልጣን ሥርዓት የሰፊውን ሕዝብ ፍላጎትና ተሳትፎ ያገለለ፣ በጥቂት የሕብረተሰብ ክፍሎችና ልሂቃን ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረተ ነበር። ይህ አካሄድ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ አንዱን ሥርዓት በሌላው እየተካ፣ የተተካው አገዛዝ ደግሞ የባሰ ጭቆናን ይዞ የሚመጣበትን አዙሪት ፈጥሯል። ከብዙ መቶ ዓመታት የዘውድ አገዛዝ በኋላ የመጣው ወታደራዊ ሥርዓት፣ በመቀጠልም ለ30 ዓመታት ገደማ የዘለቀው የአንድ ወገን የበላይነት የሰፈነበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሀገሪቱንና ዜጎቿን ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርገው አልፈዋል። ይህ ዓይነቱ የመከራና የጭቆና ሰንሰለት ግን በ2010 ዓ.ም በተቀጣጠለው ሀገራዊ ለውጥ ተገርስሶ ወደ አዲስ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ምሕዳር ተሸጋግሯል።

ያለፉትን ስምንት ዓመታት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ጉዞ ስንመረምር፣ ሀገሪቷ ከአሮጌውና ከተለመደው የአፈና ሥርዓት ወጥታ አዲስ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ አቅም ይዛለች። ይህ ወቅት የዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ መብት በተግባር የተረጋገጠበትና የሐሳብ ብዝኃነት የተስተናገደበት ምዕራፍ ነው። ከዚህ ቀደም የሥልጣን ማራዘሚያ ሆነው ያገለግሉ የነበሩ ዋና ዋና ተቋማት ገለልተኛና ነፃ ሆነው እንዲደራጁ መደረጉ የለውጡ ትልቁ ስኬት ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል።

በዚህ የሽግግር ሂደት ውስጥ የለውጡ የመጀመሪያ ፍሬ የታየው በ2013 ዓ.ም የተካሄደው ስድስተኛው ምርጫ ነበር። በወቅቱ የነበሩትን ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቆቁሞ ሕዝቡ ያሳየው የባለቤትነት ስሜት የዴሞክራሲ ናፍቆቱን በግልጽ ያሳየ ነው። ይህንን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ፣ በዘንድሮው የ2018 ዓ.ም የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይበልጥ የነቃ አስደናቂ የፖለቲካ ተሳትፎ አሳይቷል።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው ይህ ታሪካዊ መድረክ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን የማይናወጥ አቋም አሳይተውበታል። ከንጋት እስከ እኩለ ሌሊት ረጅም ሰዓታትን ተሰልፈው የተፈጥሮ የአየር ንብረት ተጽዕኖዎችንና ልዩ ልዩ ፈተናዎችን በሙሉ በትዕግሥት በመሻገር ድምፃቸውን ሰጥተዋል። ይህ ሂደት የሚያሳየው ሕዝቡ የሥልጣን ምንጭነቱን በተግባር የተረዳበትና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰነበት ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ነው።

በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞና የውስጥ መረጋጋት ሁልጊዜም በከፍተኛ ትኩረት የሚከታተሉት ጉዳይ ነው። ላለፉት ዓመታት በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሚነሱ ሥጋቶችና የጂኦፖለቲካ ጫናዎች ቢኖሩም፣ ይህ በስኬት የተጠናቀቀው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሀገሪቷን የውስጥ ጥንካሬና ሉዓላዊነት በተግባር ያስመሰከረ ሆኗል። በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በነፃነትና በሰላም ድምፅ የሰጡበት ይህ ሂደት፣ ኢትዮጵያ የራሷን የውስጥ ጉዳይ በራሷ ዜጎች ፍላጎት የመወሰን ሙሉ አቅም እንዳላት ለዓለም አሳይቷል። ምርጫው ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ታላቅ ታሪካዊ ክስተት ነው። ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን በመስጠት የሀገሩን ሉዓላዊነትና አንድነት አስከብሯል። የፖለቲካ ሥልጣን የሚገኘው በጠመንጃ አፈሙዝ ወይም በሁከት ሳይሆን በሕዝብ የላቀ ውሳኔ ብቻ መሆኑን በማረጋገጥ፣ ሀገራችን ካለፈችባቸው የፖለቲካ ስብራቶች በላይ ከፍ ብላ እንድትቆም አድርጓታል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተደማጭነትና የድርድር አቅም ከፍ የሚያደርግ ነው። የምርጫው ዝርዝር ስኬቶች ምን ምን ናቸው የሚለውን ስንመለከት፦

👉የአፈሙዝ ድምፅንና የጽንፈኛ ዛቻን ያሸነፈው የሕዝብ ጽናት

ግንቦት 24 ታሪካዊ ቀን ናት። በዚህች ታሪካዊ ዕለት፣ በየምርጫ ጣቢያው በነቂስ ወጥቶ ድምፁን የሰጠው ሕዝብ ያሳየው የነጻነት፣ የሉዓላዊነት እና የጽናት ማረጋገጫ ነው። ምርጫውን ለማደናቀፍና ሕዝቡን ለማስፈራራት የተቃጡ የአፈሙዞች ድምፆችና የሁከት ዛቻዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ሕዝብ ከመምረጥ አላፈገፈገም። መራጮች የጽንፈኛ ኃይሎችን ዛቻ ወደ ጎን ትተው፣ የአካላቸውን ሕመም፣ የበሽታን ሥቃይ፣ አልፎ ተርፎም የወሊድ ምጥንና የቅርብ ዘመድ ሞት ያመጣውን ጥልቅ ሐዘን በሕሊናቸውና በሥጋቸው ተሸክመው ነበር ረጅሙን ሰልፍ ተሰልፈው ይበጀኛል ያሉትን በካርዳቸው የመረጡት። ይህ የሚያሳየው እውነት ለኢትዮጵያውያን የምርጫ ካርድ ሰላማቸውን የሚገዙበት፣ መብታቸውን የሚያስከብሩበትና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን በገዛ እጃቸው የሚወስኑበት ብቸኛ የነጻነት አዋጃቸው መሆኑን ነው።

ሕዝቡ ከምርጫ ውጭ በሆነ መንገድ፣ በኃይል ወይም በሁከት ሥልጣን ለመያዝ ምኞትና የቆየ የሥልጣን ናፍቆት ላላቸው ወገኖች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግልጽና የማያሻማ መልዕክት አስተላልፏል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የኃይልና የሁከት አካሄድን እንደማይቀበል፣ በድምፅ ላይ ብቻ የተመሠረተ ሕጋዊ ሥርዓትን ለማፅናት እንደሚታገል አረጋግጧል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በአፅንኦት ሲያነሱ፤ "የዘመናችን ዲሞክራሲ አስተምህሮቱ ሰላምና ዕድገት፣ ቋንቋው ደግሞ መምረጥና መመረጥ ብቻ በመሆኑ የፖለቲካ ቅኝታችሁንና አካሄዳችሁን ከዚሁ ስልጡን መስመር ጋር ማስተካከል ይበጃችኋል። ካሁን በኋላ የሕዝብ ድምፅ ያልጎበኘው፣ የምርጫ ካርድ ያልዳሰሰው የፖለቲካ ሥልጣን መያዣ መንገድ በኢትዮጵያ ዝግ መሆኑን እነሆ እንዳየነው መሠረት የጣለ ስለሆነ ይህኑ ስልጡን መንገድ ለመቀበል የማትፈቅዱ ሁሉ ግን ግፋ ቢል የዘመናችን የፖለቲካ ድርሳን ሲጻፍ ልትሆኑ የምትችሉት የግርጌ ማስታወሻ ብቻ ነው።" ብለዋል።

ስለሆነም ከዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ሕጋዊ አካሄድ ውጭ የሚደረግ ሙከራ የጥፋት ተዋናይ ከመሆን ባሻገር ለሀገር የሚያተርፈው አንዳች ነገር እንደሌለ በዚህ ስሑት መንገድ ላይ የሚገኙ አካላት ሊገነዘቡ ይገባል።

1. ምርጫው በቁጥሮች ሲገለጽ

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በጉልህ የሚጠቀሱ አኃዛዊ መረጃዎች አሉት። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ንዋይ እንደገለጹት፤ ቦርዱ ከ120 ሚሊዮን በላይ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በውጭ ሀገር አሳትሞ ካስመጣ በኋላ፣ ከምርጫው 4 ቀናት በፊት በሀገሪቱ ባሉት ከ52 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች በታማኝነትና በጥንቃቄ ማድረስ ተችሏል። ይህንን እጅግ ግዙፍና ውስብስብ የሎጂስቲክስ ሥራ ሙሉ በሙሉ ያከናወኑት የቦርዱ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ብቻ መሆናቸው ተቋማዊ አቅሙ ምን ያህል እንደጎለበተ ማሳያ ነው።

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ እንደተናገሩት፤ የቦርዱ ሠራተኞችና የምርጫ አስፈጻሚዎች በዕረፍት ቀናትና በሌሊት በመጋዘን ውስጥ ጭምር እያደሩ የቁሳቁስ ማሸግ ሥራዎችን በትጋት አከናውነዋል። ሩቅና ተደራሽነታቸው አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ደግሞ ቁሳቁሶችን በእግር፣ በእንስሳት ጀርባና በጀልባ ጭምር በማጓጓዝ፣ ወንዞችን ለመሻገር የራሳቸውን የፕላስቲክ ጀልባ ሠርተው ሀገራዊ አደራቸውን ተወጥተዋል። በድምፅ መስጫ ቀን ሥራቸውን ከንጋት እስከ ንጋት በልዩ ብርታት ፈጽመዋል። ይህ ልብ የሚነካ እውነታ የሚያሳየው፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና የሕዝብ ድምፅ እንዲከበር የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ዋጋ ያለው የተናጥልና የጋራ ትጋት የሚጠይቅ መሆኑን ነው።

    ሰፊ ተሳትፎ፦ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎችና 80 የግል ዕጩዎች ተሳትፈዋል። 10 ሺህ 438 የፖለቲካ ፓርቲና የግል ዕጩዎች ተወዳድረዋል። ቦርዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውን ለሕዝብ የሚያስተዋውቁበት የክርክር መድረክ ያዘጋጀ ሲሆን፤ ይህ ተግባር ፓርቲዎች ከምርጫው ውጭም ራሳቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበትን ባህል ያዳብራል።

    የመራጮችና አስፈጻሚዎች ቁጥር፦ በአጠቃላይ 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 861 መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፤ ምርጫውን ለማስፈጸም ከ350 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል።

    ታዛቢዎችና ወኪሎች፦ ከ260 ሺህ በላይ የፖለቲካ ፓርቲ ወኪሎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያሰማሯቸው ከ60 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች፣ እንዲሁም 63 የአፍሪካ ኅብረት እና 26 የኢጋድ ታዛቢዎች ተሳትፈዋል። ለመራጩ ሕዝብ የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ለመስጠት መስፈርቱን ላሟሉ 169 ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ተሰጥቷል። እንዲሁም 21 ሚሲዮኖችና አንድ የውጭ ሀገር የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ምርጫውን ተመልክተዋል።

    የአየር ሰዓት አጠቃቀም፦ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች ነፃ የአየር ሰዓት የማግኘት መብት ስለነበራቸው ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 752.5 ነፃ የሬዲዮ ሰዓት፣ 57.5 ነፃ የቴሌቪዥን ሰዓትና 576 የጋዜጣ ኮለምን በዘመናዊ የዕጣ ማውጣት ሥርዓት ተደልድሎ እንዲጠቀሙ ተደርጓል።

    መገናኛ ብዙኃን፦ 73 የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃንን የወከሉ 1 ሺህ 827 የሀገር ውስጥና 45 የውጭ ጋዜጠኞች ለዘገባ ሥራ ተሰማርተዋል።

    የሕግ ማሻሻያ እና ዲጂታላይዜሽን፦ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ተሻሽሎ በአዋጅ ቁጥር 1394/2017 ተተክቷል። ቦርዱ 10 አዳዲስ መመሪያዎችን አጽድቋል።

    የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር፦ ለመጀመሪያ ጊዜ በገለልተኛ ባለሙያዎች የሚመራ፣ እያንዳንዳቸው 2 ሰዓት የሚወስዱ 19 የክርክር መድረኮች በቦርዱ ተዘጋጅተዋል። 14ቱ በአማርኛ፣ 5ቱ በክልል ቋንቋዎች (አፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛ፣ ሲዳምኛ፣ አፋርኛ) ተካሂደው በሰባት መገናኛ ብዙኃን በፕራይም ታይም ተላልፈዋል።

    አካታችነት፦ 28 ሺህ 632 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ከ20 ሺህ በላይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በልዩ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲመዘገቡ ተደርጓል።

    የቅሬታ አፈታትና ክትትል፦ የቅድመ አደጋ ማሳወቂያ ሥርዓት (Early Warning System) ተዘርግቷል። 663 የምርጫ ክልል ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎችና ልዩ የአጣሪ ጉባኤ ተደራጅተው 129 አቤቱታዎችን መርምረዋል። የሕግ ጥሰት በተገኘባቸው ጣቢያዎች ውጤት እንዲሰረዝ እና በፈጻሚዎች ላይ አስተዳደራዊና የወንጀል ተጠያቂነት እንዲኖር ተወስኗል።

2. ጠንካራና ገለልተኛ ተቋም፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሀገር ውስጥ አቅም

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ መጠነ ሰፊ ተቋማዊና ሕጋዊ ማሻሻያዎች የተደረጉበት ከመሆኑም በላይ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ ሀገራዊ አቅምን በተግባር ያሳየ ነበር። የዚህ ምርጫ ትልቁ ትርፍ ጠንካራና የማይናወጡ ብሔራዊ ተቋማትን መገንባት መቻላችን ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳየው ፍጹም ገለልተኝነት፣ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ብቃት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የመተግበር አቅም፣ ተቋማት ከግለሰቦችና ከፖለቲካ ጫና በላይ መሆናቸውን ያስመሰከረ ነው። ይህም ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገር አስተማማኝ የመንግሥት መዋቅር መሠረት ነው።

ለምርጫው ስኬት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መራጮችን በትዕግሥት በማስተናገድ፣ ብቁ አስፈጻሚዎችን በማሰማራትና ሂደቱን በታማኝነት በመምራት ረገድ ቦርዱ አድናቆት የተቸረው ሥራን ፈጽሟል። የሠራተኞቹ ቀንና ሌሊት መትጋት እንዲሁም በግንባር ቀደምትነት የሚመሩት አመራር አባላት ያሳዩት ቁርጠኝነት የላቀና ለሀገር ኩራት የሆነ ተግባር ነው።

በዚህ ምርጫ ውስጥ ትልቁን ትኩረት የሳበውና ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው የዲጂታል የመራጮች ምዝገባ ሥርዓት ነው። ይህ ዘመናዊ አሠራር ለምርጫው ከተመዘገቡ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች መካከል ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በአካል መጓዝ ሳይጠበቅባቸው፣ ባሉበት ቦታ ሆነው በነፃነት እንዲመዘገቡ ዕድል ፈጥሯል። ቴክኖሎጂው የመራጮችን ማንነት በፎቶግራፍ ጭምር በማረጋገጡ በድምፅ መስጫ ቀን ሊፈጠሩ የሚችሉ ግድፈቶችንና ማጭበርበሮችን በከፍተኛ ደረጃ መከላከል ተችሏል። የዚህ ሥርዓት ዋነኛውና ትልቁ ድል ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወጣት ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የበለጸገ መሆኑ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ የዚህን የቴክኖሎጂ ስኬት አስፈላጊነት ሲያብራሩ፤ "እነዚህ የዲጂታል የምዝገባ ሥርዓቶች በውጭ ሀገር አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች የለሙ ሳይሆን በራሳችን ወጣት ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የተገነቡ ናቸው። ይህም ተቋሙን ከውጭ አቅራቢዎች ጥገኝነት ነፃ በማድረግ በራሱ አቅም እንዲቆምና ለወደፊቱ ማሻሻያዎችን በራሱ እንዲያከናውን መሠረት ጥሏል።"

ይህ እርምጃ ቦርዱ የውጭ የቴክኒክ ጥገኝነትን በመቀነስ የሀገር ውስጥ አቅምን ለመገንባትና የሉዓላዊነትና የደኅንነት ዋስትናን በራስ ቴክኖሎጂ ለማረጋገጥ የቻለበትን ስትራቴጂካዊ አካሄድ በግልጽ ያሳያል። በተጨማሪም በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በውጭ ዜጎች ይሠራ የነበረው የቴክኒክ ድጋፍ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ሠራተኞች መተካቱ የተሳካ የእውቀት ሽግግር መኖሩን አሳይቷል።

3. ሕጋዊ ማሻሻያዎች፣ አካታችነትና ተጠያቂነት

ዴሞክራሲ እውነተኛ ትርጉም የሚኖረው ዜጎች፣ በተለይም ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ያለ ፍርሃትና ጫና፣ ደኅንነታቸው ተጠብቆ በፖለቲካዊ ሂደቶች እኩል መሳተፍ ሲችሉ ነው። ይህንን እውን ለማድረግ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር በታዛቢነት በመሳተፍ፣ ሴቶች የዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በነፃነት እንዲጠቀሙና በሂደቱ በንቃት እንዲሳተፉ አስችሏል።

ቦርዱ የሴቶችን መብት ከማስከበር ባለፈ፣ ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳን ለመከላከል የሚያስችል ፖሊሲ ቀርጾ ተግባራዊ አድርጓል። ከዚህም በላይ በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ግብረ ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ አቋቁሟል።

በተጨማሪም የምርጫውን ግልጽነትና ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ቀድሞ የነበረው አዋጅ ቁጥር 1162/2011 በአዋጅ ቁጥር 1394/2017 እንዲተካ የተደረገ ሲሆን፣ ቦርዱ ይህንን መነሻ በማድረግ 10 አዳዲስ መመሪያዎችን አጽድቋል። በነዚህ ማሻሻያዎች ውስጥ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደ ዋና መርህ የተወሰደ ነው።

4. ፈተናዎችን መጋፈጥና ገለልተኝነትን ማስከበር

ይህ ሁሉ ስኬት ግን ያለ ፈተና አልመጣም። ምርጫው በተያዘለት ጊዜ አይካሄድም የሚሉ ጥርጣሬዎችና የተሳሳቱ መረጃዎች ተቋሙን ፈትነውት ነበር። ሆኖም ቦርዱ ጫናዎችን በመቋቋም ሕግና መርህን ብቻ ተከትሎ በመሥራት ምርጫውን ለስኬት ማብቃቱን ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ያረጋግጣሉ።

ቦርዱ በምርጫው ወቅት የተቋሙን ነፃነት ከማንኛውም ዓይነት ጫናና ጣልቃገብነት በመጠበቅ በሕግና በመርህ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ ቆይቷል። በምርጫ አፈጻጸም የአሠራር ግድፈቶች እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡ ቅሬታዎችን በመመርመር በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች በድምፅ መስጫው ቀን ጭምር አስፈጻሚዎችን አሰናብቷል፤ በምርጫ ውጤቶች ላይም ውሳኔ ሰጥቷል። ይህም ቦርዱ ለሕግ የበላይነትና ለምርጫ ታማኝነት ያለውን ጽኑ አቋም ያሳያል።

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት በአንድ ተቋም ወይም በጥቂት ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ መራጮች በፀሐይና በዝናብ ሳይበገሩ በትዕግሥት የሰጡት ድምፅ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች (እንደ አፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ) እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የጋራ ጥረት ውጤት ነው።

5. የምርጫው ግልጽነትና ዓለም አቀፍ እውቅና

የምርጫውን ታሪካዊ ሂደትና ተዓማኒነት ለማረጋገጥ የሀገር ውስጥና የውጭ አካላት በሰፊው ተሳትፈዋል። ሂደቱን ለመዘገብ 73 ለሚሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 1 ሺህ 827 ጋዜጠኞች የዘገባ ሥራቸውን አከናውነዋል። ከ260 ሺህ በላይ የፖለቲካ ፓርቲ ወኪሎች እና ከ64 ሺህ በላይ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎች በሂደቱ ላይ ተሳትፈዋል።

በተለይም በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተሰጣቸው 55 የሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች 60 ሺህ 277 ታዛቢዎችን በማሰማራት ሂደቱን የተከታተሉ ሲሆን፤ 169 ድርጅቶች ደግሞ ለመራጮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል። በአህጉር ደረጃም የኬንያ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመሩትና ከ60 በላይ ታዛቢዎችን ያቀፈው የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን እና 26 የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ታዛቢዎች ሂደቱን በታዛቢነት ተከታትለዋል። ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫው ግልጽ፣ አሳታፊና ተዓማኒ ሆኖ በስኬት መካሄዱንም አረጋግጠዋል።

👉የአፍሪካ ህብረት እና የኢጋድ ታዛቢ ቡድኖች ምስክርነት

የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በሰጡት መግለጫ፣ የምርጫው ዕለት ሰላማዊ፣ ሥነ ሥርዓት የሰፈነበት እና ግልፅነት የታየበት መሆኑን ነው ያረጋገጡት። በቴክኖሎጂ የታገዘ የመራጮች ምዝገባ መተግበሩ ወጣቶችን መሳቡን፣ ዜጎች በትዕግሥት ሰልፍ በመያዝ ጥልቅ ፍላጎታቸውን ማሳየታቸውን፣ የሎጂስቲክስ ዝግጅቱ የተሟላ መሆኑንና የምርጫ ሰዓት መራዘሙ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል። በመስተንግዶ ረገድም ወንበሮችና የምግብ አቅርቦቶች መኖራቸው ረጅሙን ሰልፍ ታጋሽ እንዳደረገውና ለአረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ቅድሚያ መሰጠቱን አረጋግጠዋል።

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ለኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልዕክት "ቅኝ ግዛትን በአንድነት የተከላከለች Couch፣ ለአፍሪካ ነፃነት የቆመች እና የአህጉሪቱ ዋና ከተማ በሆነች ሀገር ውስጥ የተደረገው ይህ ምርጫ ትልቅ ምዕራፍ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ሊኮሩ ይገባል፤ ወደፊት ለመራመድም በሕዝቦች መካከል ያለውን የፖለቲካ እና የማኅበረሰብ ውይይት ይበልጥ ማሳደግ፣ ወደ ኋላ የተተዉ የሚሰማቸውን አካላት ወደ መድረኩ በማምጣት እና አካታችና የተባበረች ኢትዮጵያን መገንባት ያስፈልጋል" ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ የኡጋንዳ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ የሚመራው የኢጋድ (IGAD) የምርጫ ታዛቢ ቡድን በሰባት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች 28 ጣቢያዎችን በመጎብኘት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን አውጥቷል። ቡድኑ ጣቢያዎቹ በሰዓታቸው መከፈታቸውን፣ በቂ ቁሳቁስና አስፈጻሚዎች እንደነበሩ፣ የሳጥኖች አስተሻሸግ የድምፅ ምስጢራዊነትን ያረጋገጠ መሆኑንና የድምፅ አሰጣጡ ያለምንም መሰናክል በጥሩ ሁኔታ መካሄዱን በመታዘብ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ለአረጋውያን፣ ሕፃናት ለያዙ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ቅድሚያ መሰጠቱንና መራጮች የሚቀመጡባቸው ወንበሮች መኖራቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በማዘጋጀትና በመምራት ረገድ ከፍተኛ አስተዳደራዊና ኦፕሬሽናል አቅም ማሳየቱን አጉልቷል።

የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ለሰላማዊና ተዓማኒ ምርጫ የተደረገውን የጋራ ቁርጠኝነት ያደነቀ ሲሆን፣ "ይህ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ እና ምርጫ ዕድገት ላይ በተለይም የምርጫ አስተዳደርን ለማሻሻል፣ አካታችነትን እና ተዓማኒነትን ለማሳደግ የተነደፉ ዋና ዋና ቴክኖሎጂያዊ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች የተስተዋሉበት ትልቅ ምዕራፍ ነው" ሲል ቡድኑ ምስክርነታቸውን በአፅንኦት የገለጹት።

የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ "ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው። በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ይበልጥ እንዲጠናከርና ቀጣይነት ያለው መሻሻል እንዲመዘገብ አብረን ለመሥራት ያለንን ጽኑ ቁርጠኝነት እናረጋግጣለን።" ሲሉ ነው የተደመጡት።

6. የምርጫው ውጤት፣ የሕዝቡ ጽናትና የአሸናፊው ፓርቲ ከባድ ሸክም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት፣ ብልፅግና ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 438 መቀመጫዎችን በማግኘት አሸንፏል። በሌላ በኩል ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎችም በምክር ቤቶቹ ወንበሮችን ማግኘት የቻሉ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) 13፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ስድስት፣ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሦስት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሦስት፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ሦስት፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ሁለት ወንበሮችን አሸንፈዋል።

በሌላ በኩል ኦብነግ፣ ጉህዴን፣ አርጎባ አንድነት ጀበርቲ፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ፣ የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የሶማሌ ፌዴራሊስት ፓርቲ፣ ኅብረት ለዴሞክራሲና ለነጻነት፣ ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት፣ የጌዴዮ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እያንዳንዳቸው አንድ ወንበር ሲያገኙ 8 የግል ተወዳዳሪዎችም ምክር ቤት ለመግባት አሸንፈዋል።

ይህን ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ከሌሎች ጊዜያት ለየት የሚያደርገው ታላቅ ክስተት፣ መራጩ ሕዝብ በታጋሽነት ተሰልፎ የመምረጥ መብቱን ለመጠቀም ያሳየው ወደር የለሽ ጽናት ነው።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ይህንን የሕብረተሰብ አደራ "አሸናፊው ፓርቲ ትልቅ ሀገራዊ ሸክም የተጣለበት መሆኑን ብልፅግና ፓርቲ በሚገባ ይረዳል። ፓርቲያችን በማኒፌስቷችንና በአጠቃላይ በምርጫ ቅስቀሳችን ወቅት ለሕዝብ ቃል የገባናቸውን በተግባር ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይንቀሳቀሳል" ብለዋል፡፡

👉የፉክክርና የትብብር ሚዛን

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምሕዳር በቀጣይነት ሊመራበት የሚገባው ስልጡን መስመር በፉክክርና በትብብር መካከል ያለውን ሚዛን ጠብቆ መጓዝ ነው። ብልፅግና ፓርቲ ከሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በሀገር ግንባታ ላይ ሚና ካላቸው አካላት ጋር በብሔራዊ ጥቅም ላይ በትብብር ለመሥራት ያለው አቋም የጸና መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በሰጡት አስተያየት፤ "ባለፉት ዓመታት የጀመርነውን በፉክክርና በትብብር መካከል ሚዛን ጠብቆ የሚሄድ ጥረታችንን በቀጣይ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል። በምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉ ሕዝቡን በማሳተፍ፣ በየጊዜው የሕዝቡን ግብረ መልስ በመስማት፣ ያንን እንደ ግብዓት ተጠቅመን የእቅድ አካል አድርገን ወደ ተግባር ለመተርጎም በቁርጠኝነት እንንቀሳቀሳለን።" ብለዋል።

ይህ ዕይታ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሕዝብን ድምፅና ግብረ መልስ በየጊዜው የሚያዳምጥ፣ እንዲሁም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለሀገር ጥቅም በጋራ የመሥራትን ስልጡንና አካታች የአሠራር ሥርዓት መከተል መጀመሩን ያሳያል።

7. ዴሞክራሲና ምርጫው የሚገለጽባቸው አራቱ ምሰሶዎች

ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ማለት አማራጭ የሌለው የህልውና ጉዳይና የሁለንተናዊ ብልጽግናችን መሠረት ነው። ብዝኃነትን በአግባቡ ማስተናገድ፣ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥና ጠንካራ ሀገር መገንባት የሚቻለው በዴሞክራሲያዊ ምሰሶዎች ላይ በመመሥረት ብቻ ነው። መንግሥት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሲሠራ ቆይቷል።

በዚህ ሂደት ውስጥ የሲቪል ማኅበራት ሚና የማይተካና አዎንታዊ ሚና አላቸው። መራጩን ሕዝብ ከማስተማር፣ ሕገ መንግሥታዊ የመምረጥ መብቱን እንዲጠቀም ከማስቻል፣ እስከ ሰላም እሴት ግንባታና በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ድልድይ በመሆን የዜጎችን ባለቤትነት ከማረጋገጥ አኳያ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ እንደገለጹት፣ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት በአራት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ የቆመ ነው።

    አንደኛው ምሰሶ፦ ምርጫ የሰላም ዋስትና መሆኑን መረዳት ነው። ሕዝቡ ልዩነቶችን በፀብና በአምባጓሮ ከመፍታት አዙሪት ተላቆ፣ በሰላማዊ መንገድ የመሻገር ባህልን መርጧል። በነቂስ ድምፁን መስጠቱ ኋላ ቀር የአመፃ መንገድን ለሚከተሉ ሁሉ "በቃችሁ" የሚል መልዕክት ያስተላለፈበት ሲሆን፣ የሰፊው ሕዝብ ማዕበላዊ ድምፅ ከአሮጌው የብጥብጥ ባህል መላቀቅ እንደሚፈልግ ማረጋገጫ ነው።

    ሁለተኛው ምሰሶ፦ የምርጫ ውግንና ከሕዝብ ጋር መሆኑን ማወቅ ነው። የምርጫ ተዓማኒነትና ክብሩ የሚገለጠው ሥልጣን ከሚመነጭበት ከሰፊው ሕዝብ ሉዓላዊ መብትና ፍላጎት ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ነው። ምርጫ ከሚሰጠው ኃላፊነት በላይ ለእያንዳንዱ ዜጋ የዕለት ተዕለት ሕይወት መሻሻልና ከሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ሕዝቡ በትክክል ተገንዝቧል።

    ሦስተኛው ምሰሶ፦ የምርጫው የፖሊሲ ሐሳቦችና አማራጮች ከፍታ የታየበት ነው። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የክርክር መድረኮች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያነሷቸውን የፖሊሲ አማራጮች ሕዝቡ በጥንቃቄ አዳምጧል። እነዚህ ሐሳቦች ለሀገር ዕድገት፣ ለጠንካራ መንግሥትና ለሰከነ የፖለቲካ ባህል ግንባታ መሠረት እንዲሆኑ በእያንዳንዱ ዜጋ ሕሊና ማስረፅ፣ በሰነድ በማዘጋጀትም መተግበር ይገባል።

    አራተኛው ምሰሶ፦ ምርጫ እንደ ማኅበራዊ ሀብት፤ ምርጫ ፖለቲካዊ ኩነት ብቻ ሳይሆን ትልቅ ማኅበራዊ ሀብት መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የዚህን ማኅበራዊ እሴት አንድምታ ሲያብራሩም "ሕዝባችን ስለ ኢትዮጵያዊ ቀናነቱና ፍቅሩ ጩኸቱን ሳይሆን የምርጫ ካርድ ድምፁን፣ ስላቅና ሃኬትን ሳይሆን ትሑትነቱን፣ የትኛውንም የፖለቲካ ሐሳብ ቢያራምድ እንኳን ማኅበራዊና ሀገራዊ ፍቅሩን ከጎኑ ላለው ወገኑ አለመንፈጉን ያየንበት እጅግ የተዋበ መድረክ ነበር። ስለዚህ የኢትዮጵያ ምርጫ ከፖለቲካዊ ፋይዳው ባልተናነሰ ሁኔታ ማኅበራዊ ፋይዳውም ከፍ ያለ ትልቅ የማኅበራዊ መሠረትን የሰጠው ነው።" ብለዋል።

8. የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ታሪካዊ ሚና፦ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራቶች የመፈወስ ዕድል

ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥትና የፖለቲካ ሥርዓት ጉዞዋ ውስጥ በርካታ አኩሪ ታሪኮችን ብታስመዘግብም፣ በሂደቱ ውስጥ የተፈጠሩና ዛሬም ድረስ ሀገራዊ አንድነቷን፣ ሰላሟንና የዴሞክራሲ ግንባታዋን እየተፈታተኑ ያሉ ሥር የሰደዱ የፖለቲካ ስብራቶች መኖራቸው አይካድም። እነዚህን ለዘመናት የዘለቁ ስብራቶች በመጠገን ረገድ ይህ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሀገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ሊያሻግር የሚችል ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ዕድል ይዞ መጥቷል። ምርጫው በበሰለና አካታች መንገድ በመመራቱ በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ላይ ጉልህና አዎንታዊ አሻራ ማሳረፍ የሚችልባቸው ዋና ዋና አቅጣጫዎች አሉት። እነዚህም፦

    የቅቡልነት ስብራትን ማከም፦ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመንግሥታት ሥልጣን አመጣጥ አብዛኛውን ጊዜ ከኃይል ፖለቲካ ወይም ሙሉ በሙሉ ነፃ ካልሆኑ ምርጫዎች ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ የመንግሥት ሕዝባዊ ቅቡልነት ማጣት ለግጭቶች መነሻ ሲሆን ቆይቷል። ይህ ምርጫ ነፃና ታማኝ ሆኖ መካሄዱ አሸናፊው አካል ከሕዝብ የሚሰጠው እውነተኛ የሥልጣን አደራ እንዲኖረው ያደርጋል፤ ይህም በገዥው አካልና በሕዝቡ መካከል ያለውን መተማመን በማደስ ረገድ ትልቅ ዕድል ይሰጣል።

    የሰላማዊ ሥልጣን ሽግግር ባህልን መገንባት፦ ሥልጣንን በአፈሙዝ የመያዝ ልምድ ሀገሪቱን በተደጋጋሚ ለድቀት የዳረጋት መሆኑ ብዙ ትምህርት ሰጥቷል። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሁሉም ወገኖች የሕዝብን ድምፅ አክብረው የሚቀበሉበት ድባብ መፈጠሩ ምርጫን ብቸኛ የሥልጣን መያዣና መልቀቂያ መንገድ የማድረግ አዲስና ጤናማ የፖለቲካ ባህል በሀገሪቷ ውስጥ እንዲለመድ ያደርጋል።

    በተቋማት ላይ ያለውን አመኔታ ማደስ፦ ሕዝቡ እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶችና የዴሞክራሲ ተቋማት ባሉ ገለልተኛ መሆን በሚገባቸው ተቋማት ላይ ያለው እምነት መሸርሸሩ ሌላው ስብራት ሲሆን፣ ይህንንም ምርጫ በስኬትና በገለልተኝነት ማካሄድ መቻሉ የተቋማቱን ነፃነትና ብቃት በተግባር የሚያሳይ በመሆኑ ዜጎች በሀገሪቷ የሕግ የበላይነት ላይ ያላቸው እምነት መልሶ እንዲያገግም ያደርጋል።

    ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር፦ አካታች የሆነ ምርጫ ማካሄድ መሣሪያ ያነሱ ወይም በሰላማዊ መንገድ የሚያምፁ የፖለቲካ ኃይሎች ቅሬታቸውን በሕዝብ ድምፅ እንዲፈትሹ በር ይከፍታል። ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን የዘመናት የፖለቲካ ስብራቶች ለመፈወስ የራሱ አሻራ ሊያኖር የሚችለው ሂደቱ ፍትሐዊ፣ ግልጽና በርካታ የፖለቲካ ኃይሎችን ያሳተፈ፣ ከ54 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በንቃት የተሳተፈበት በመሆኑ ነው። በዚህም ምርጫው በተሳካ ሁኔታ መካሄዱ በራሱ ወደ ሰፊው ብሔራዊ ምክክር ለመሻገር እንደ ትልቅ መነሻ ሆኖ ያገለግላል።

ማጠቃለያ፦ ምርጫው ለአፍሪካ ዴሞክራሲ የብርሃን ፍኖት

አፍሪካ በፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች፣ በወታደራዊ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ኢ-ሕገመንግሥታዊ መንገድ መምራት፣ የመንግሥት ግልበጣዎች እየተፈተነች ባለችበት በዚህ የታሪክ ምዕራፍ፣ ኢትዮጵያ በሰላማዊና ስልጡን መንገድ ምርጫዋን ማጠናቀቋ ለአህጉሪቱ አዲስ ፍኖተ ዴሞክራሲ ሆና እንድትወጣ አድርጓታል። 'የአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካውያን መፍትሔዎች' የሚለውን መርህ በተግባር በማሳየት፣ የራሳችንን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በራሳችን አቅም መቅረጽ እንደምንችል ለዓለም አሳይተናል። በዚህ አስቸጋሪ አህጉራዊ ድባብ ውስጥ፣ የፓን አፍሪካኒዝም ማዕከልና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊና ፍትሐዊ መንገድ በስኬት ማጠናቀቋ ለአፍሪካ ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ ነው። ኢትዮጵያ ለጫናዎች ሳትበገር፣ በራሷ ሁለንተናዊ አቅም ያከናወነችው ይህ ታሪካዊ መድረክ ሀገር በቀል ዴሞክራሲን እና አህጉራዊ ሉዓላዊነትን ያረጋገጠ በመሆኑ ለመላው አፍሪካ ኩራትና ተምሳሌት ሆኗል።

የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፤ አህጉሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ዲሞክራሲ አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን ገልጸው፤ ሰላምና ልማት ሊመጡ የሚችሉት በጠመንጃ ኃይል ሳይሆን ሕዝብ በነፃነት የራሱን መሪ በሚመርጥበት ስልጡን መንገድ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። ኮሚሽነሩ አክለውም፦ "አህጉራችን ከዲሞክራሲ ውጭ ሌላ ምርጫ የላትም። ወደፊት ለመራመድ፣ ዕድገትን ለማረጋገጥና በተለይም ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ዴሞክራሲ ብቻ ነው" ሲሉ በአፅንኦት ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ ኢትዮጵያ ተቋማዊ አቅሟንና ሕጋዊ መሠረቷን በማጠናከር ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የተሻገረችበት እና የጋራ የትብብር አቅምን ያሳየችበት አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ በስኬት ተጠናቋል። ለዚህም ስኬት በየሚናቸው አስተዋጽኦ ላበረከቱ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዕጩዎች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የጸጥታ ኃይሎች፣ የአፍሪካ ኅብረትና የኢጋድ ታዛቢ ቡድኖች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እንዲሁም ሀገር በቀል ታዛቢ ድርጅቶች በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል።

በምርጫው ወቅት የተሰጠው የሕዝብ አመኔታና ድምፅ ለተመራጮች ትልቅ አደራና ኃላፊነትን ጥሏል። ያሸነፉ ፓርቲዎችና ዕጩዎች ይህንን ታሪካዊ አደራ በመሸከም ለሕዝብ ፍላጎት ቅርብ የሆነ አገልግሎት በመስጠት፣ በታማኝነት፣ በቅንነትና ንጹሕ በሆነ ሕሊና በመሥራት የሕዝቡን ተስፋ ወደ ተጨባጭ ውጤት የመቀየር ግዴታ አለባቸው። የምርጫው ትልቁና የመጨረሻው ስኬት የሚለካው በተመራጮችና በሕዝብ መካከል በሚገነባው መተማመን፣ በሚረጋገጠው ዘላቂ ሰላምና ለሁሉም ተጠቃሚነትን በሚያሰፍነው ሀገራዊ ዕድገትና ብልጽግና ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም