ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤና ወረርሽኞችን በመከላከል ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን አቅም ገንብታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤና ወረርሽኞችን በመከላከል ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን አቅም ገንብታለች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ፣ በወረርሽኞች መከላከልና ለአደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆን ጠንካራ አቅም መገንባቷን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።
የአፍሪካ ሀገራት የማይበገር የጤና ስርዓት ለመገንባት በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ፣ በሰው ሀይል አቅም ግንባታና በዘላቂ የጤና ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።
በኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነቻቸው የሚገኙ ተግባራት ሀገሪቱ በዘርፉ ለዓለም ተጨማሪ አበርክቶ እንዳላት የሚያሳዩ ናቸው።
በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አማካኝነት የእናቶችና የሕጻናት ሞትን በመቀነስ የተገኘው ውጤት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚሆንም ጠቅሰዋል።
በዚህም የዓለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያን በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ የልህቀት ማዕከልነት እውቅና ለመስጠት ሂደት መጀመሩን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም በላቦራቶሪ አቅም፣ በዲጂታል የወረርሽኝ ክትትል፣ በሰው ሀይል አቅም ግንባታና በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ በአፍሪካ ካሉ ጠንካራ የሕብረተሰብ ጤና ተቋማት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በቀጣይ ከሕክምና አገልግሎት ባለፈ በበሽታ መከላከል ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልጸው፤ የአካባቢ ጥበቃና ፅዳት አገልግሎትን ማሻሻል ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት መርሃግብሮችን በመተግበር የከተሞችን ገጽታ ከማስዋብ ባለፈ የህዝብ ጤናን ለማሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ዲጂታል ጤና ለበሽታዎች ቅድመ ትንበያ፣ ለጤና ዕቅድ ዝግጅትና ለአገልግሎት አሰጣጥ መዘመን ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
የዓለም ጤና ድርጅትም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ሀገሪቱ የዲጂታል ጤና እያከናወነችው ያለውን ተግባር ለማጠናከር እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የአፍሪካ ሀገራት የመቋቋም አቅም ያለው የጤና ስርዓት ለመገንባት በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ፣ በሰው ሀይል አቅም ግንባታ፣ በተቀናጀ ሪፈራል ሥርዓትና በዘላቂ የጤና ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ከ1947 ጀምሮ የዓለም ጤና ድርጅት መስራች አባል በመሆን በዓለም አቀፍ የጤና ፖሊሲዎች ቀረጻ ላይ ከ79 ዓመታት በላይ አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች።