ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን በመጠበቅ ለሀብት ምንጭነት ለማዋል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን በመጠበቅ ለሀብት ምንጭነት ለማዋል እየተሰራ ነው
ጎንደር፤ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ጥንታዊ ቅርሶችን በመጠገን፣ በማደስና በዘመናዊ ሥርዓት በመያዝ የሃብት ምንጭ ሆነው እንዲቀጥሉ እየተሰራ ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለጹ።
የባለስልጣኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በጎንደር ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ነባር ቅርሶችን በማደስና አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎችን በማልማት የሀብት ምንጭ የማድረግ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
በዚህም ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማደስ የኢኮኖሚ ምንጭ የማድረግ ፍልስፍናው በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የጎንደር አብያተ መንግስታትን፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጅማ አባጅፋር ቤተ መንግስትን፣ የሐረር ቅርሶችንና የነቀምት የቁምሳ ሞረዳ ቤተመንግስት እድሳት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በዋና ዋና የቅርስ መገኛ አካባቢዎች ሙዚየሞችን በማስገንባት እና ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን ለጎብኝዎች ክፍት በማድረግ የሀብት ምንጭ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የአዝማሪ ጨዋታዎችን ጨምሮ የሀገር ባህል ዘፈኖችና ጭፈራዎችን ወደ አደባባይ በማውጣት የገጠሩን ቱሪዝ ልማት በማሳደግ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የጎንደር ከተማ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ማርያም ካሳሁን እንደገለጹት፣ በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማትና የታሪካዊ አብያተ መንግስታት እድሳት የቱሪዝሙ ዘርፉን እንዲነቃቃ አድርጓል።
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት አንድ ሺህ 914 የነበረው የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥር በ2018 በጀት ዓመት ወደ ስድስት ሺህ 420 ማደግ መቻሉን በማሳያነት አቅርበዋል።
ባለስልጣኑም በጎንደር ከተማ ለሚገኘው የደብረ ብርሃን ሥላሴ ጥገና በመጀመሪያው ምእራፍ 30 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቁመው ሌሎች ቅርሶችንም ደረጃ በደረጃ እንደሚታደሱ ነው የተናገሩት።
ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ በቅርቡ የታደሰው የፋሲል አብያተ መንግስትን ጨምሮ ሌሎች በከተማዋ የሚገኙ የመስህብ ህብቶችን ጎብኝተዋል።