ቀጥታ፡

የአፍሪካን አንድነት የበለጠ በማጎልበት የበለፀገች አህጉር መገንባት አለብን-መሐሙድ አሊ ዩሱፍ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦የአፍሪካን አንድነት የበለጠ በማጎልበት የበለፀገች አህጉር መገንባት እንደሚያስፈልግ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።

63ኛው የአፍሪካ ቀን ''የ63 ዓመታትን ዓመታት አንድነት፣ ትስስርና ልማት፤ አብረን እናክብር” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።

በዝግጅቱም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ጨምሮ የሕብረቱ አባል ሀገራት ዲፕሎማቶችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አፍሪካ በዓለም መድረክ ያላት ሚና በየ ጊዜው እየታደሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

የአህጉሪቷ የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገትም በጥቂት ዓመታት ውስጥ የአፍሪካን ጥቅል የሀገር ውስጥ ዕድገት ምጣኔ 10 ትሪሊዮን ዶላር ያደርሰዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ወጣቶችም ሌሎች አህጉራት ጭምር የሚመኟቸው የአህጉሪቷ ዕድገትና ብልፅግና አቅም መሆናቸውን አንስተዋል።

በቀጣይም የአፍሪካዊያንን የአንድነት ኃይል የበለጠ በማጎልበት የአህጉሪቱን ዕምቅ ፀጋዎች ለሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና መቀየር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ በበኩላቸው፥የአፍሪካዊያን ባህልና ዕሴት ለአህጉሪቷ መፃኢ ዕድል፣ ዕድገትና ብልፅግና የሚተርፍ የጥንካሬ ምንጭ ነው ብለዋል።

የአፍሪካን የትብብር አቅም በማጎልበት የአህጉሪቷ ዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የራስን የተሻለ ዕድል መቅረፅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለዚህም በሁሉም ዘርፍ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስፋት የአህጉሪቱን ዕምቅ የልማት ፀጋ ወደ ዘላቂ ብልፅግና መቀየር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአህጉሪቷ ላይ የደረሱ በደሎች ፍትሕ እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገርም ለአጀንዳ 2063 ስኬት በቁርጠኝነት በመስራት የወደፊት እጣ ፋንታ መወሰን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በየዓመቱ የአፍሪካ ቀን መከበር የጀመረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁን የአፍሪካ ህብረት እ.ኤ.አ በ1963 መመስረቱን እንደሆነ ይታወቃል።

የዘንድሮው የአፍሪካ ቀንም የህብረቱ ኮሚሽን ከህብረቱ ሰራተኞች ማኅበር፣ አባል ሀገራት፣ ከህብረቱ አደረጃጀቶችና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ጋር በመተባበር ተዘጋጅቷል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም