ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት መሰረት የሚጥል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት መሰረት የሚጥል ነው
ደሴ ፤ሐምሌ 16/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት መሰረት የሚጥል መሆኑን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሐይማኖት አባቶች ገለጹ።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ባሰባሰባቸውና በተለዩ ስምንት አጀንዳዎች ላይ የዋናው የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢትዮጵያን የቆዩ ችግሮች በምክክር በመፍታትና ለሁሉም የምትመች ጠንካራ ሀገር የመገንባት ትልም ተይዞ እየተሰራ ነው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የባቲ ከተማ የሃይማኖት አባት መላከ ፀሐይ ሰምረ አስቻለው እንዳሉት፥ ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ለማምጣት መሰረት የሚጥል ነው ።
በምክክሩ የመደማመጥ እሴትን በመጠቀምና በማጎልበት ለችግሮች መፍትሄ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።
ለምክክሩ በአጀንዳነት የተመረጡ ጉዳዮችም ችግሮቹን ለመፍታት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ጠቁመው፥ለጉባኤው ስኬት ሁሉም ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ መክረዋል።
ሌላው የሰንበቴ ከተማ የሐይማኖት አባት ሸህ ኡመር ሸህ መሀመድ በበኩላቸው፣ የምክክር ኮሚሽኑ እየሄደበት ያለው እርቀት በኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ስኬት ነው ብለዋል።
በምክክሩ የሚነሱ ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙበት ከመሆኑ ባለፈ ለመጪው ትውልድ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ለማስተላለፍ የሚያግዝ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤው በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ መፍትሄ በማምጣት የሕዝቦችን አብሮነት ያጠናክራል ብለው ተስፋ ማድረጋቸውን የሀይማኖት አባቶቹ አመላክተዋል።