ምክክር-ለኢትዮጵያ ብሩህ ነገ - ኢዜአ አማርኛ
ምክክር-ለኢትዮጵያ ብሩህ ነገ
ምክክር-ለኢትዮጵያ ብሩህ ነገ
(በቀደሰ ተክሌ ከኢዜአ-ሚዛን አማን ቅርንጫፍ)
ጥቃቅን ችግሮች እያደጉ ሔደው ሀገር የማፍረስ አደጋን ከመደቀናቸው በፊት ከሥር መሠረቱ ማስተካከያ ማድረግ ብቸኛው መንገድ ሁሉን አካታች ሀገራዊ ምክክርን ማካሔድ ነው። በዚህም ራሳቸውን ከመጥፋት ታድገው ሀገር በሚል ስያሜ ሕልውናቸውን ያቆዩ ሀገራት አሉ። ከእነዚህም መካከል በአካታች ምክክር ከግጭት ወደ ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተሸጋገሩትን ማንሳት ይቻላል።
ለአብነት የቱኒዚያ ሀገራዊ ምክክር በዓለም ላይ ካሉ የቅርብ ጊዜ ስኬታማ ተሞክሮዎች ቀዳሚው ነው። እ.አ.አ በ2011 የ"አረብ አብዮት" መነሻ የነበረችው ቱኒዚያ፣ የፖለቲካ መሪዎች መገዳደል እና ከፍተኛ አለመረጋጋት ገጥሟት ነበር። አራት የሲቪክ ማህበራት (የሰራተኞች ማህበር፣ የጠበቆች ማህበር፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የነጋዴዎች ማህበር) በጋራ በመሆን "የቱኒዚያ ብሔራዊ ምክክር ኳርትት አቋቋሙ። ፖለቲከኞችን አስገድደው በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጡ አደረጉ። በዚህም ሳቢያ ሀገሪቱ አዲስ እና ሁሉን አቀፍ ህገ-መንግስት ቀረጸች፤ ሰላማዊ ምርጫ ተካሄደ፤ ሀገሪቱ ወደ ለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ከመግባት ዳነች። ይህንን ምክክር የመሩት አራት ድርጅቶችም እ.አ.አ በ2015 የኖቤል የሰላም ሽልማትን አግኝተዋል።
ደቡብ አፍሪካም ለዘመናት የዘለቀውን የዘረኝነት እና የአፓርታይድ ስርዓት ያቆመችው በጦርነት ሳይሆን በሁሉን አካታች ብሔራዊ ምክክር ነው። በኔልሰን ማንዴላ የሚመራው ኤ.ኤን.ሲ እና የነጮች ገዥ ፓርቲ በጥላቻ ፋንታ "ለነገዋ ሀገር" በሚል ይቅርታን እና ድርድርን አስቀደሙ። በምክክሩ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና የነገዶች ተወካዮች በሙሉ ተሳትፈዋል። ያለምንም ደም መፋሰስ የስልጣን ሽግግር ተደረገ፤ በአለም ላይ እጅግ ተራማጅ የሚባል አዲስ ህገ-መንግስት ተቀረጸ፤ "የእውነትና የእርቅ ኮሚሽን" በማቋቋም ያለፈው ቁስል እንዲሻር ተደረገ።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሁዋን ማኑኤል ሳንቶስን የኖቤል ተሸላሚነት ያበቃው ምክክር የተካሄደው በኮሎምቢያ መንግስት እና በኤፍ.ኤ.አር.ሲ አማፂያን መካከል ለአምስት አስርት ዓመታት የዘለቀው እና ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ላለቁበት ጦርነት እልባትን ሰጥቷል። ምክክሩ ከሀገር ውጭ (በኩባ እና ኖርዌይ) በተደረጉ ድርድሮች የተደገፈ ሲሆን፣ ዋናው ትኩረቱ ግን የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ፣ የፖለቲካ ተሳትፎ እና የአደንዛዥ ዕፅ ንግድን ማቆም ላይ ያተኮረ ነበር አማፂያኑ ሙሉ በሙሉ ጦርነቱን አቁመው ነፍጣቸውን አስረክበው፤ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲነት በመቀየር ሰላማዊ ትግላቸውን እንዲቀጥሉ ያስቻለ ነው።
ኢትዮጵያም ዛሬ ለዘመናት ሲንከባለል የመጣን ዕዳ በጫንቃዋ ላይ ተሸክማ ቆማ ያንን አሳራፊ መድኃኒት ሽታለች። በዘመነኛው ዓለም ውስጥ ሆና በትላንት በሽታ ትታመማለች። የቀደሙት የጣሉት የስህተት እርሾ ዛሬም ከሊጥ ጋር እየተቦካ የኮመጠጠ የአኗኗር ሥርዓትን ትውልዱ እንዲጋፈጥ ምክንያት መሆን ከጀመረ ከራርሟል። ይህም የማይነጋ ሌሊት መስሎ ታይቶ ብዙዎችን ለቀቢጸ-ተስፋ ዳርጓል። የሰላም በር ዘግቶ ሰላም መፈለግ፣ መክፈቻ ቁልፍ በእጅ ይዞ ወደ ሌላ ማማተር ሆነና ነገሩ፤ ችግሩ ከነግሳንግሱ እያደገ ጥቁር ደመናን በሀገሬ ሰማይ ላይ ለመጋረድ አቅሙን ተጠቀመ።
ሆኖም እንደተባለው የማይነጋ ሌሊት፣ የማይፈታ ሕልም የለም። "ፈጣሪም ሀገርን ያለ አንዳች አይተውም" ነውና ቃሉ፤ የተስፋ ብርሃን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ፈነጠቀ። ወደ ውስጥ የሚመለከት፣ የራስ ማንነትን በኢትዮጵያዊ ቀለም የሚፈትሽ፣ ችግርን ሳይሆን መፍትሔን አነፍንፎ ገሃድ የሚያወጣ፣ ሀገር በቀል ዕውቀትን ያከበረና መልካም የሆኑ ነባር እሴቶችን ለችግሮቻችን ወጌሻ ያደረገ የለውጥ ተስፋ ከተፍ አለ። የመጋቢት ብስራት ኢትዮጵያን ወደ ፍካት ለመለወጥ በሀገር ፍቅር ስሜት አዳዲስ የሰላም መንገዶችን መክፈት ጀምሯል።
ከመገፋፋት ይልቅ መደመርን፣ ከመካሰስም ይቅርታን የሚያስቀድመው የመደመር መንግሥት ሁሉንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ ሀሳብ ይዞ የምክክር ኮሚሽንን በማቋቋሙ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስብል ተግባር በኢትዮጵያ ተወጠነ። በፖለቲካ እሳቤም ሆነ በሐሰት ትርክት አልያም የማያግባባ የትኛውንም ጉዳይ በመምዘዝ አኩርፎ ነፍጥ ማንገብን ልምድ ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት ባለበት፤ በአንጻሩ አቅም ኖሮት ሥልጣን የጨበጠ በሀሳብ የተቃረነውን በሚኮንንበትና ቀፍድዶ በወህኒ ቤት በሚያሰቃይባት ምድር በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መመካከር ትልቅ ትርጉም አለው። ይህ በደማቅ የታሪክ ቀለም የሚመዘገብ ክስተትም ነው። ምክክር በባህላችን አብሮን የኖረ የማንነታችን አካል የሆነ እሴታችን ቢሆንም ለፖለቲካው ሜዳ ግን እንግዳ ነገር ነውና።
ጠላቶቻችን የኢትዮጵያን ሰላምና ዕድገት ማየት አይሹምና ሂደቱን ለማደናቀፍ ጥረዋል። በዚህም የመለወጥ መንገዳችንን ለመዝጋት ብዙ ጉድጓዶችን ምሰዋል። ጉድጓድ ለማዘጋጀት ከሩቅ ያመጡት ቁሳቁስ የለም፤ ከራሳችን ጋር አብሮ ባደገው የዘርኝነት፣ የጽንፈኝነትና አክራሪነት ገሶ (ትልቅ የጉድጓድ መቆፈሪያ) ነው እንጂ። በተለይ የኢትዮጵያ ጌጥ የሆነው ብዝኃ-ብሔር እና ሃይማኖት ብዙ ሳይደክሙ ያጠመዷቸው ፈጣን ውጤት የሚያስገኙላቸው ወጥመዶች ነበሩ። የወል ትርክት በሐሰተኛ ትረካ ተሞልቶ ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት መንስኤ ሆነ። ጠንካራዋ ሀገር ኢትዮጵያ ግን መሠረቶቿ ዓለት ላይ ስለሆኑ ይህ ሁሉ የጥፋት ጎርፍና ነፋስ ሊያነቃንቃት አልቻለም። ይልቁንም በጽናት ቆማ ወጀብ ማዕበሉን ጸጥ የሚያደርግ ሀገርኛ መሣሪያ ታጥቃለች - የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን!
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ አማረ ፈንታው (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋምና በአግባቡ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን አጠናቆ አጀንዳ መለየት መቻሉ የኢትዮጵያውያንን የሥነ-ልቦና እና የሞራል ከፍታ ማሳያ ነው። ለዚህም አመክንዮ ሲያስቀምጡ፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለችግር መፍቻ ወደ ጠረጴዛ ሳይሆን ወደ ጫካ የሚሮጥ የፖለቲካ ሥርዓትን ነው ስታስተናግድ የቆየችው ብለዋል። ዛሬ ላይ ግን ያ ልክ አለመሆኑን የተረዳ ትውልድ በስብዕና ሞራል ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖን አሳድሮ በጥይት ሳይሆን በሀሳብ ለማሸነፍ ራሱን አዘጋጅቷል። በጦር ግንባር ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሔ ሊያገኝ ከራሱ ጋር ተስማምቷል። ይህ የመማርና የማደግ ውጤት ነው። የትናንት አካሔድ ሞትና ችግርን እንጂ ብልጽግናን አላተረፈም። መመካከር በእጃችን የነበረ አውጥተን ያልተጠቀምንበት ሀብታችን ነው። እንደ ተፈጥሮው ሁሉ እሴታችን የተሸፈነበት አቧራ በምክክር ተራግፎ በአብሮነት እና ዘላቂ ሰላም የምንደምቅባትን ጀንበር ልናይ ንጋት ላይ ተቃርበናል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ትልቅ ተስፋ የጣለበት ጉዳይና ውጤቱን አጥብቆ የሻተበት አጀንዳ ምን ይሆን ተብሎ ቢጠና፤ "የምክክር ኮሚሽን ወደ ተግባር መግባት" ከሚለው በላይ ሌላ አጀንዳ ይኖራል ብሎ በልበ-ሙሉነት መግለጽ አይቻልም። ያለ ልዩነት ሁሉም ደግፎ በብርቱ ናፈቀው። የጥንት የአያት ቅድመ-አያቱ ወግ ነባርና አዲስ ሳይሆንበት በብርሃን ፍጥነት ዓላማውን ተረዳ። ተረድቶም ሳይቀር ተስፋውን ወደ ሚጨበጥ ውጤት ለመቀየር ባለው አቅም ሁሉ ለመደገፍ ተረባረበ። ዕድል የገጠመውም በቁርጠኝነት ሂደቱ ላይ ተሳተፈ። የዚህ ድምር ውጤት የምክክር ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ የነበሩ አለመግባባቶች ቁልፍ መፍቻዎች ናቸው ያላቸውን 8 ዋና ዋና የምክክር አጀንዳዎችን በስኬት ለመለየት አበቃው።
የምክክሩ አጀንዳ ልየታ ሥርዓት ከአጀንዳ መለየት ያለፈ ትርጉም ያለው ነው። ስኬታማ የተቋም ግንባታ አንጸባራቂ ክስተት ጭምር እንጂ። አካታችነትን ባረጋገጠ መልኩ የሁሉንም አካባቢ ወግ፣ ባህልና ሥርዓት ተገንዝቦ ለሀገር የሚሆን አጀንዳ በስኬት መሰብሰብ የተቋማዊ ብቃት ማሳያ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ማድረግ የምትችል መሆኗን ገላጭ ሌላኛው የድል ገጽ ቢባል ግነት አይሆንም። አጀንዳዎቹ የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ ናቸው። ኃይል የተሞላበት የፖለቲካ ሥርዓትን በመገርሰስ ወደ ዴሞክራሲያዊ እና የተሟላ የሰላም ደሴት የሚያሸጋግር አጋጣሚ እንደሚሆንም ዶ/ር አማረ ይገልጻሉ። ምክክሩ ለኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ ሲሆን በታሪክ ድርሳን የምናስቀምጠውና ወደፊት መጪው ትውልድ የሚያወሳው ኩነት ነው ብለዋል።
መምህር ቢመርቅ በርሁን በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ናቸው። እርሳቸው የምክክር ኮሚሽንን ተግባር ለኢትዮጵያ ያለውን መልካም ዕድልነት ሲገልጡ፤ ስር የሰደዱ ችግሮችን ከሥር የሚነቅል መሣሪያ ብለውታል። ከግለሰቦች የፖለቲካ ትርክት ተላቆ ወደ ተቋማዊ አሠራር መሸጋገሪያ ድልድይም እንደሆነ እንዲሁ። ኢትዮጵያ በበርካታ ነጠላ ትርክቶች ለሰላም እጦት ተዳርጋለች፣ በግለሰቦች ግላዊ ፍላጎት ብዙዎች ሕይወታቸውን ገብረዋል። ይህ የመጠፋፋት ሰንሰለት ይበጠስ ዘንድ ምክክሩ አስፈላጊ ነው።
ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተግባራት ስኬት አካታችነት ትልቅ አቅም እንደሆነውም መምህር ቢመርቅ ያነሳሉ። በኮሚሽኑ የተሠራው የአጀንዳ ማሰባሰብና ልየታ እንዲሁም የምክክሩ ተሳታፊ መረጣ ሂደት በተማሩ ኃይሎች አልያም በፖለቲካ ልሂቃን ላይ ብቻ መሠረት ያደረገ አይደለም። በታችኛውም እርከን ወርዶ አርሶ አደሩን፣ አካል ጉዳተኛውንና ሌሎችንም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን የጉዳዩ ባለቤቶች ናችሁ ብሎ ማሳተፉ በጎ ውጤት አመልካች ቅድመ-ሂደት ነበር ነው ያሉት።
የአካታችነቱ ወሰን መስፋት ሰፊውን የማኅበረሰብ ጥያቄ ይዞ ለመነሳት አስችሎታል። የሁሉም ጥያቄ በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ማለትም፦ በሀገር ግንባታ፣ በመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ እንዲሁም በፖለቲካ ሥርዓት፣ በፖለቲካ ውክልና እና በምርጫ ሥርዓት፣ በፌዴራል ከተሞች (የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የድሬዳዋ አስተዳደር) ጉዳይ፣ በሃይማኖት ጉዳዮች፣ በተቋማት ግንባታ፣ በሕግ የበላይነት እና በሰብዓዊ መብቶች፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ በሙስና እና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በሰላም ግንባታ አጀንዳዎች ሥር ተጠልሏል።
እነዚህ አጀንዳዎች በአንድም በሌላም የመከፋፈል፣ በጎሪጥ የመተያየትና የጥርጣሬ መንፈስን በመንዛት ዜጎች እርስ በእርስ ከመተማመንና በአብሮነት ከመቀጠል ይልቅ "የኔ" የሚል አጥር ውስጥ እንዲገቡ ያደረጉ ናቸው። በሌላ በኩል "ተበደልኩ"ን ወልደው ኩርፊያን አስፍተዋል። ይህም በአንድ ወገን ሳይሆን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በተለያየ መጠን የሚንጸባረቅ ችግር ነው። አሁን የመጣ ሳይሆን ትናንት የነበረ፣ ለዛሬ የተዘራና እንክርዳድ እያበቀለ ያለ የግጭት ዘር ነው። ሀገራዊ የሆኑ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የአስተዳደር ሥርዓት ፈትሾ እውነትን እና ለነገ የሚበጀውን የወል ትርክት በሕዝብ ይሁንታ ሊያጸና ቀጠሮ የያዘው ኮሚሽኑ፤ በሁሉም ዜጎች ትብብር ሀገራዊ ድልን ያጎናጽፋል። ሰላምና ስኬት ለኢትዮጵያችን! አበቃሁ!!