ቀጥታ፡

ቱሪዝም- የኢትዮጵያ የማከናወን አቅም ማሳያ

በዮሐንስ ደርበው

“ሀገራችን ከቱሪዝም ልታገኛቸው የምትችላቸውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና አካባቢያዊ ጥቅሞች ሁሉ ከቀረው ዓለም ጋር ተወዳድራ እንድታገኝ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ ወደ ሀገራችን መሳብ አለብን። ለዚህም የተለያዩ ስልታዊ መላዎች ነድፈን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን (የመደመር መንግሥት 273)።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የለውጡ መንግሥት እመርታዎችን ካስመዘገበባቸው ዘርፎች አንዱ ነው።

መንግሥት ከአምሥቱ የትኩረት መስኮች አንዱ አንድርጎም በጥናት፣ አካባቢያዊ ፀጋን ዐውቆና ለይቶ በተደመረ ዐቅም ባከናወናቸው ሥራዎች በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር፣ በገበታ ለትውልድ፣ በኮሪደር ልማት፣ በወንዝ እና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት እሠየው ያሰኙ ተግባራት አከናውኗል።

በገበታ ለሸገር የተገለጠው የተደመረ ዐቅም - ለኢትዮጵያ ስኬቶች እንደማሳያ

የመልከ መልካሟ ብዙ መልኮች

ለአስም በሽታ አጋላጭ ምክንያቶችና ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀው ከእንጦጦ - ቀበና የተከናወነው የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክትም ለጎብኚም ለነዋሪም ምቹ ከባቢን በመፍጠር ረገድ እየተደረገ ያለውን ትጋት ያስረዳል።

ምረቃውን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባጋራው መረጃ፤ “መቆሸሽ እኛ አይገባንም፣ መጠልሸት እኛ አይገባንም፣ ማነስ እኛ አይገባንም! ሠርተን እንደምንችል ማሳየት ያስፈልጋል” ሲል የሥራውን ማራኪነትና ውበት ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚሁ ወቅት፤ የተሰጠንን ሕዝባዊ አደራ በታማኝነት፣ በጽኑ ትጋት እና በቅንነት በመፈጸም የዜጎቻችንን የኑሮ ጥራት ለማሻሻልና መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የጀመርነውን ጉዞ አበክረን እንቀጥላለን ሲሉ በቀጣይ ካለፈው የበለጠ እንደሚሠራ አመላክተዋል።

ገንዘብን፣ ዕውቀትን፣ ጉልበትን፣ ሐሳብን፣ የአመራር ብቃትን ስንደምር የሚከሰተው ነገር እንደዚህ ያለው ውበት ይሆናል ሲሉም አስገንዝበዋል።

በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው (ገጽ 256) ላይም፤ “የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሀገራት በዘመናቸው ሁሉ የሠሩትንና ተፈጥሮ ያደለቻቸውን መልካም ገጽታ በኩራት ለዓለም የሚያስተዋውቁበት፣ ‘ሀገሬ ይሄንን ትመስላለች’ የሚሉበት መድረክ ነው። ሀገርን በሚያኮራና ለሌሎች ለመጋበዝ በማያሳፍር መልኩ መገንባት፣ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ መሠረቱ ነው።” ያሉትም የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በቁጭት መነሳታቸውን ይገልጻል።

ነገን ዛሬ እየሠራች ያለችው ኢትዮጵያ ካላት ላይ ሳትነፍግ የገንዘብም ሆነ የሰው ኃብቷን ቱሪዝም ላይ ስታውል፤ አንድም የኢንዱስትሪውን ዐዋጭነት ብሎም የዜጎቿን በየዘርፉ ዘላቂ ተጠቃሚነት በመገንዘብ ነው። እዚህ ላይ ለሀገር ገቢ በማስገኘት እና የሥራ ዕድል በመፍጠር ዘርፉ የሚያበረክተውን ጥቅም ማጤን ይገባል።

በአዲስ አበባ ከተከናወኑ ቁልፍ የቱሪዝም ልማቶች መከካከል፤ የመስቀል ዐደባባይ ቅርስን ማንበርና ማዘመን፣ ከአዲስ አበባ ልማት ጋር ተሣሥሮ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ በአዲስ መልክ የታደሠው ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት፣ የአምሥቱ ዕውቀት ተኮር ማዕከላት (አብርኾት ቤተ-መጻሕፍት፣ ሳይንስ ሙዝየም፣ የሀገር በቀል ዕጽዋት ማሳያ፣ የአንድነት ቤተ-መዛግብት እና የማዕድን ሙዝየም) ግንባታ፣ የአዲስ አበባ ኮንቬንሽን ማዕከል እና ሌሎችም ይገኙበታል።

በሌላ በኩል ደግሞ ጎብኚዎች የሚያርፉበት ሎጂና ሆቴሎች ግንባታም በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።

ገበታ ለሸገር ብሎ ከአዲስ አበባ የተነሳው የቱሪዝም ልማት በገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ወደ ክልሎች ተስፋፍቶ ደረጃቸውን የጠበቁ ሎጂዎች እንዲገነቡ አስችሏል። የተገነቡት ሎጂዎች ደግሞ ለጎብኚዎቹ ምቾትን የሚያስጠብቁ መሠረተ-ልማቶችን ስበዋል።

በርካታ ጎብኚ መሳብና ገቢን ማሳደግ፣ በጎ ገጽታን መሸጥ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የበለጸገች ኢትዮጵያ ዕውን ማድረግ እየተከናወኑ ላሉ ተግባራት ሁሉ ግቦች ናቸው።

መንግሥት ዕምቅ የጎብኚዎች መስኅብ ዐቅም የሆኑና አቧራ ለብሰው የተደበቁትን ፀጋዎች ውበታቸውን ገላልጦ እያሳዬ ያለውም ለዚህ ነው።

ቱሪዝም በቀጥታ ዜጎች (ሰዎች) የሚጠቀሙበት ኢንዱስትሪ ነው። ለዚህ ደግሞ ሰዎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና መጠበቅ ይኖርባቸዋል።መሠረተ-ልማቶችን በመጠበቅ እንዲሁም ከመንግሥት ጎን በመሆን በሚፈለጉበት ሁሉ ንቁ ተሳትፎ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል።

#የኢትዮጵያ_ዜና_አገልግሎት #Ethiopian_News_Agency #ቱሪዝም #PMOEthiopia #በኢዜአ_ዐይን #PMOEthiopia #EthiopiaDelivers

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም