አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት ማድረግ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ኢ-ፍትሐዊነት የሚያንጸባርቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት ማድረግ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ኢ-ፍትሐዊነት የሚያንጸባርቅ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፦ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት ማድረግ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ኢ-ፍትሐዊነት የሚያንጸባርቅ ተግባር መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ገለጹ።
የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 10ኛ ዓመታዊ ኮንፍረንስ በአፍሪካ ሕብረት እየተካሄደ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የመንግስታቱ ድርጅት በሁሉም ዘርፎች ቀዳሚ ተግባር አፍሪካን የማድረግ የፖለቲካም ሆነ የሞራል ግዴታ አለበት።
አፍሪካ አህጉራዊ ግጭቶችን በማርገብ፣ አህጉራዊ ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን በመግለጽ፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናና ሌሎች የሰላምና ጸጥታ ኢኒሼቲቮች አስደናቂ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አፍሪካ በዓለም ሁለንተናዊ እንቅስቀሴ ላይ ያላት ሚና የጎላ መሆኑን እንገነዘባለን ያሉት ዋና ጸሀፊው፤ በታሪክና በዓለም ኢ-ፍትሐዊ አሰራር የደረሰባትን በደል ለመቀልበስ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ባልወጡበት ወቅት የተቋቋሙ ዓለም አቀፍ ተቋማት አህጉሪቱ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት ማድረጋቸው ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።
አፍሪካ ባልተሳተፈችበት የተቋቋሙ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኢ-ፍትሐዊነት አፍሪካን ብዙ አሳጥቷታል ያሉት ዋና ጸሀፊው፤ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካ ለመፍታት የተጀመሩ ኢንሼቲቮችን መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት አፍሪካዊ ግጭቶች በአፍሪካ ማዕቀፍ እንዲፈቱ በመሪነት ከመሳተፍ ባለፈ የአፍሪካ ሕብረትን ጥረት እንደሚደግፍ ጠቁመዋል።
አፍሪካ በወሳኝ ማዕድናትና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትልቅ አቅም እንዳላት ገልጸው፤ ሀብቷን እሴት በመጨመር ለዓለም ገበያ የምታቀርብበትን መንገድ መቀየስ ይገባል ብለዋል።