ቀጥታ፡

ስር የሰደዱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ምክክር እያደረግን ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ምክክሩ ስር የሰደዱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና የተሻለች አገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል ምክክር እያደረግን ነው ሲሉ በምክክሩ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ አባላት ገለፁ።      

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክክር የሚደረግባቸውን ስምንት አጀንዳዎች ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በአጀንዳዎቹ ላይም 4 ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ምክክር ማድረግ ጀምረዋል።    

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጰያዊያን እንዳሉትም፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ግልጽና ተስፋ ሰጪ በሆነ መንገድ እየተካሄደ ነው።              

ምክክሩ የመደማመጥና የጋራ መግባባት ባህልን በማጠናከር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ ዕድል መሆኑንም ጠቅሰዋል።       

ከተመካካሪዎች መካከል አገርነሽ ሃይሌ በሰጡት አስተያየት፤ የምክክር ሂደቱ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና ሌሎችንም የህብረተሰብ ክፍሎች ማካተቱ እጅግ አሳታፊ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል። 

ለምክክር ሒደቱ ስኬታማነት የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።   

ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም እና ልማት ቅድሚያ በመስጠት በምክክር ሂደቱ ስኬታማነት አዎንታዊ ሚናችንን መጫወት ይኖርብናል ብለዋል፡፡    

ተመካካሪ ወይዘሮ ፎዚያ ሁሴን በበኩላቸው፤ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፉ አጀንዳዎች ላይ እየተወያየን በመሆናችን ነገን በሚያሻግር መልኩ የተሰጠንን አደራ በከፍተኛ ኃላፊነት እንወጣለን ብለዋል፡፡

ሁላችንም የተሰጠንን ይህንን ታሪካዊ አደራ በከፍተኛ ኃላፊነት በመወጣት፣ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም እና አንድነት በጋራ መቆም አለብን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም