ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል ባሻገር ለትውልድ የሚተርፍ አርዓያነት ያለው ተግባር ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል ባሻገር ለትውልድ የሚተርፍ አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ የዘንድሮውን የክረምት አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በቤላ 18 ቀበሌ የወንዝ ዳርቻ አካሂዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለመጪው ትውልድ ታሪክ የምናኖርበት አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የችግኝ ተከላው የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም እና የግብርና ምርታማነትን ከማሻሻል አንጻር ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል።

በመሆኑም ትኩረታችን ችግኝ መትከል ላይ ብቻ ሳይወሰን፤ የተተከሉትን  በማሳደግ፣ በመንከባከብ እና የፅድቀት መጠናቸውን በማረጋገጥ ላይ ሊሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።


 

መርሃ ግብሩ ለምግብ ዋስትና የሚረዱ የፍራፍሬ እና ለአካባቢ ጥበቃ ጠቀሜታ ያላቸው የዛፍ ዝርያዎችን ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙሃን መረጃን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ሀገራዊ የደን ሽፋን ጥረትን ለመደገፍ ያላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ባለሥልጣኑ በ8ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 45 ሺህ 125 ችግኞችን ለመትከል አቅዶ እየሰራ ሲሆን፣ እስካሁን በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ከ43 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸው ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም