ቀጥታ፡

የኢትዮ-ቴሌኮም ቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚና መወጣት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ቴሌኮም ቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚና መወጣት የሚያስችል መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የ2018 በጀት ዓመትና የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ አፈፃፀም ላይ በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ሰባት ዓመታት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በትጋት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።


 

ባለፈው ዓመት የተጀመረውና ለሦስት ዓመታት የሚተገበረው"ቀጣዩ አድማስ" ስትራቴጂ፣ ሁለንተናዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማፋጠን ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ስትራቴጂው ተቋሙ በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የድርሻውን እንዲወጣ ከማስቻሉም በላይ፣ለአፍሪካ አጀንዳ 2063 እና ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬት ጠንካራ መሠረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።

በስትራቴጂው የአንድ ዓመት አፈፃፀምም በርካታ የኔትወርክ ማስፋፊያና የማዘመን ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም 603 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰው፣ ይህም አጠቃላይ የሞባይል ጣቢያዎችን ቁጥር ወደ 10 ሺህ 613 ከፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም 195 የገጠር ሞባይል ጣቢያዎች መገንባታቸውን ገልጸው፣ በዚህም 117 ወረዳዎች የቴሌኮሙ አገልግሎት ተደራሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይህም የአገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ዲጂታል አካታችነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።


 

በ2018 በጀት ዓመት የኔትወርክ ማሻሻያና ማስፋፊያ ሥራዎች በስፋት መከናወናቸውን ጠቅሰው፣ 264 ተጨማሪ ከተሞች የአራተኛ ትውልድ (4ጂ) አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የ4ጂ ኔትወርክ ሽፋን ያላቸው ከተሞች ቁጥር ወደ 1 ሺህ 200 ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሰባት አዳዲስ ከተሞች የአምስተኛ ትውልድ (5ጂ) አገልግሎት በማግኘታቸው፣ የ5ጂ ተጠቃሚ ከተሞች ቁጥር 33 መድረሱን አስታውቀዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት 215 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ በማስመዝገብ የዕቅዱን 99 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካቱንም ገልጸዋል።

ይህም ከ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ33 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂና በመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች የተመዘገበውን ውጤት መሠረት በማድረግ፣የኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 90 ነጥብ 1 ሚሊዮን መድረሱን ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ 475 አዳዲስና የተሻሻሉ ምርቶችና አገልግሎቶች ለደንበኞች ማቅረብ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የቴሌብር ተጠቃሚዎች ቁጥር 60 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም