በኢትዮጵያና ሩስያ መካከል የዳበረውን ባህላዊና ኪነ ጥበባዊ ትስስር ይበልጥ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ሰኔ 22/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያና ሩስያ መካከል የዳበረውን ባህላዊና ኪነ ጥበባዊ ትስስር ይበልጥ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑ የሀገራቱ ተወካዮች ገለጹ።

'የሩስያ ባህል ቀን በኢትዮጵያ' በሚል መሪ ሃሳብ የሀገሪቱን ባህል የተመለከተ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ የሩስያ ኤምባሲ አዘጋጅነት አዲስ አበባ በሚገኘው የሩስያ የሳይንስና ባህል ማዕከል/ፑሽኪን/ ተካሂዷል።

የሩስያን ባህል የሚያስቃኝ የኪነ ሕንጻ ዐውደ ርዕይ በማዕከሉ የተከፈተ ሲሆን በሁለቱ ሀገራት ባህላዊና መንፈሳዊ ቅርሶችና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።


 

የኢትዮጵያና ሩስያ ታሪካዊ ግንኙነት በርካታ ምዕተ ዓመታትን ቢያስቆጥርም ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው ግን በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት እንደሆነ ይነገራል።

125ኛው ዓመቱን ያስቆጠረው የሁለቱ ሀገራት ዘመናትን የተሻገረ ጽኑ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ከፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ባሻገር ባህላዊና መንፈሳዊ ትስስሮችም እንደጎለበቱ ይወሳል።

በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኢያቭገኒ ተርኪን እንዳሉት ዘመናትን በጽኑ ወዳጅነት የዘለቀው የኢትዮ-ሩስያ ዲፕሎማሲያዊ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር በባህላዊና መንፈሳዊ ቅርርብ ያዳበረ ነው።


 

በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዘመናት የዳበሩ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ኪነ ጥበባዊ እና ታሪካዊ ግንኙነቶችና ትብብሮች ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጭው ሕዳር ወር ዕውቅ የሩስያ ድምጻዊያንን ያካተተ ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ስራውን እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

ከዚህም በሻጋር የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ሙያተኞች ወደ ሩስያ በመሄድ የኢትዮጵያን ባህል የሚያስተዋውቁብትን ዕድል ለማመቻቸት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር  አበባው አያሌው በበኩላቸው የሁለቱን ወዳጅ አገሮች ባህል ልውውጥ ይበልጥ ለማጎልበት የሚያግዙ ዝግጅቶች በአዲስ አበባ ፑሽኪን ማዕከል ጋር በመተባበር እንደሚዘጋጁ ጠቁመዋል።


 

የኢትዮ-ሩስያ ባህላዊ ትስስር ለማጠናከር በኪነ ሕንጻ፣ በስነ ጥበብ እና በሌሎች ኪነ ጥበብ ዘርፎች ላይ በስፋት እንደሚሰራ አረጋገጠዋል።

ኢትዮጵያ ባህላዊና መንፈሳዊ ቅርሶቿን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የሚዘክር የአርኪኦሎጂና የቨርቹዋል ሪያሊቲ ቋሚ ዐውደ ርዕይ በላሊበላ መከፈቱን ገልጸዋል።

”ላሊበላ በእምነት የታነፀ” በሚል መሪ ሀሳብ የተከፈተው ዐውደ ርዕይ በቀጣይ ሩስያን ጨምሮ ወደ አውሮፓ ሀገራት እና ሰሜን አሜሪካ የመውሰድ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 የሩስያ ዘመናዊ ሥነ-ጽሁፍ አባት የሚሰኘው ዕውቁ ሩስያዊ ባለቅኔ አሌክሳንደር ፑሽኪን 225ኛ ልደት በዓል በቀጣይ ዓመት በድምቀት እንደሚከበር ተገልጿል።

በአሌክሳንደር ፑሽኪን ልደት ቀን የተሰየመው የሩስያ ቋንቋ ቀን በቅርቡ በአዲስ አበባ መዘከሩም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም