በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፋችን ታላቅ የዜግነት ኩራት ይሰማናል-በጎ ፈቃደኞች - ኢዜአ አማርኛ
በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፋችን ታላቅ የዜግነት ኩራት ይሰማናል-በጎ ፈቃደኞች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የነገ ዕጣ ፋንታን በጋራ በሚቀርጸው ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፋቸው ታላቅ የዜግነት ኩራት እንደሚሰማቸው ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የዋናው የምክክር ጉባኤ በጎ ፈቃደኞች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መከፈቱ ይታወሳል።
ለዘመናት የዘለቁ ልዩነቶችን በውይይትና በመግባባት ለመፍታት የተጀመረው ይህ ሂደት ለትውልድ የሚተላለፍ አኩሪ ሀገራዊ አሻራ እንደሚሆንም ይጠበቃል።
ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ዜጎች በንቃት በሚሳተፉበት በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ፣ የስነ-ስርዓት ማስተባበር፣ የተሳታፊዎች መረጃ አገልግሎት፣ ድጋፍና አጠቃላይ የአስተናጋጅነት ሥራዎችን በበጎ ፈቃድ የሚያከናውኑ ወጣቶች የሂደቱ የማይታይ ግን ወሳኝ አካል ሆነዋል።
በጎ ፈቃደኛ አቶ ዮሐንስ ግርማ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ሀገርን በሚመለከት ታሪካዊ ሂደት ውስጥ በፈቃደኝነት ማገልገል ከፍተኛ ኩራትን የሚፈጥር ነው።
ሀገሬ ምን አደረገችልኝ ከሚለው አስተሳሰብ ይልቅ እኔ ለሀገሬ ምን አበረከትኩ ወደሚለው የዜግነት ኃላፊነት መሸጋገር ትልቅ የውስጥ እርካታን እንደሚሰጥና የጋራ ኃላፊነትን እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሀገር ፍቅርን በተግባር የሚያሳይ ከፍተኛ የዜግነት መገለጫ ነው።
በጎ ፈቃደኛ መቅደስ መዝገቡ በበኩላቸው፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰብአዊነት ከፍተኛ እሴት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ወሳኝ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ህዝብንና ሀገርን ማገልገል የሚፈጥረው ስሜት እጅግ ልዩ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተመካካሪዎች ተገቢውን እገዛ በማድረግ፣ የመረጃ አገልግሎት በመስጠት እና የጉባኤው ሂደት በተሳለጠ ሁኔታ እንዲካሄድ ድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከአፋር ክልል የመጡት በጎ ፈቃደኛ አህመድ አለዉ በበኩላቸው፣ በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ኩነት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸው ከፍተኛ ኩራት እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።
የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በዜጎች መካከል መተማመንን በማጠናከር፣ ዘላቂ ሰላምን በማስፈንና የኢትዮጵያን የጋራ የወደፊት ራዕይ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።
በጎ ፈቃደኞቹ የሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያን የነገ ዕጣ ፈንታ በጋራ ባለቤትነት የሚቀርጽ ታሪካዊ አጋጣሚ በመሆኑ፣ የዚህ ሂደት አካል መሆናቸው ለሕይወታቸው የማይረሳ ትዝታና ለሀገራቸው የሚያበረክቱት ታላቅ አሻራ መሆኑን ገልጸዋል።