ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ስንት ዓይነት የአዕዋፍ ዝርያዎች አሉ? 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአዕዋፍ ኑሮ ምቹ እና ተስማሚ ሁኔታዎች ካሉባቸው ሀገራት አንዷ ናት። 

በፈረንጆቹ 2024 እና 2025 የተደረጉ የጥናት ውጤቶች እንዳመላከቱት፤ በኢትዮጵያ ከ881 እስከ 926 የሚደርሱ የአዕዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ። 

ይህ አሃዝ ነዋሪ እና ፍልሰተኛ የአዕዋፍ ዝርያዎችን እንደሚያካትት በኢትዮጵያ ዱር እንስሣት ጥበቃ ባለሥልጣን የጥበቃ ቦታዎችና የብሔራዊ ፓርኮች ዋርደን ፋንታዬ ነጋሽ ለኢዜአ ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ ለአዕዋፋት ኑሮ ምቹና አስፈላጊ ከሆኑ ሀገራት መካከል እንደምትመደብም ጠቅሰዋል። 

639 ነዋሪዎችን እና 224 ወቅታዊ ፍልሰተኞችን ጨምሮ 926 የአዕዋፍ ዝርያዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ባሳለፍነው ነሐሴ ወር ላይ የተደረገ ጥናት ውጤት አመላክቷል ነው ያሉት። 

ከእነዚህ መካከል በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙት የአዕዋፍ ዝርያዎች ቁጥራቸው ከ18 እስከ 20 እንደሚደርስ ጠቁመዋል። 

አማካኝ የወፎች ዕድሜ እንደ ዝርያ፣ መጠን እና አካባቢ ስለሚለያይ ለሁሉም ወፎች አንድ አማካይ ዕድሜ አለመኖሩንም አንስተዋል። 

ትንሽ ዕድሜ የሚኖሩት የድንቢጥ ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቅሰው አማካኝ ዕድሜያቸውም ሦስት ዓመት መሆኑን ተናግረዋል። 

እንደ አልባትሮስ (Albatrosses and Some Parrots) ያሉ ትላልቅ የአዕዋፍ ዝርያዎች እና አንዳንድ በቀቀኖች ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሊኖሩ እንደሚችሉ አመላክተዋል። 

መጠን፣ ዝርያ እና የመኖሪያ አካባቢ በአዕዋፍ የሕይወት ዘመን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩም አስገንዝበዋል። 

በዚህም መሠረት ትልልቅ ወፎች ከትንንሽ ወፎች የበለጠ ረጅም ዕድሜ ይኖራሉ ብለዋል። 

እንደ ዝርያቸው የሚወሰን ቢሆንም አዕዋፋት ከቀዝቃዛ እስከ ሞቃታማ የአየር ንብረት ያላቸው አካባቢዎች ላይ መኖር እንደሚችሉም አንስተዋል። 

አንድ ተመራጭ የአየር ንብረት የላቸውም፤ አብዛኞቹ የአዕዋፍ ዝርያዎች የተረጋጋ፣ አስተማማኝ የምግብ አቅርቦት ለማግኘት እና ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ተስማሚ ሁኔታዎችን የሚቸር የአየር ሁኔታን ይመርጣሉ ነው ያሉት። 

በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ 11 ሺህ 100 የሚጠጉ የአዕዋፍ ዝርያዎች እንዳሉም ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም