አረንጓዴ ዐሻራ የሥነ-ምኅዳር ደህንነትን በማስተካከል ዕድገትን በማፋጠን ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ የሥነ-ምኅዳር ደህንነትን በማስተካከል ዕድገትን በማፋጠን ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የሥነ-ምኅዳር ደኅንነት በማስተካከል ዕድገትን የሚያፋጥን ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሁመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን "ተስፋን እንትከል" መሪ ሃሳብ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ዳርቻ በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
በዚሁ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይም፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ብልጽግና የሚያረጋግጥ ብሔራዊ የልማት ትልም መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮው መርሃ ግብር ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ሁሉም የማኅብረሰብ ክፍል በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚሁ መሠረትም የተለያዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞችና የማኅበረሰብ ክፍሎች በየአካባቢያቸው ችግኝ በመትከል ዐሻራቸውን እያኖሩ ይገኛል።
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አመራርና ሠራተኞችም በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጎሮ የወንዝ ዳርቻ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል።
በዚሁ ወቅት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሁመድ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የሥነ-ምኅዳር ደኅንነት በማጠናከር ዘላቂ ልማትን የሚያፋጥን ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መርሃ ግብሩ በ2011 ዓ.ም ከተጀመረ ወዲህ ባሉት ሰባት ተከታታይ ዓመታት በርካታ ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል።
መርሃ ግብሩ የሥነ-ምኅዳር ሚዛንን ከማስጠበቅ ባለፈ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ዛፍ መትከል ለሰው ልጆች የአዕምሮ እርካታና የልብ ደስታን በመፍጠር ተስፋን የማለምለም አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የተተከሉ ችግኞች ፀድቀው ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ መንከባከብና በቀጣይነት መከታተል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል።
በመርሃ ግብሩ የተሳተፉት የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተረፈ በዳዳ በበኩላቸው፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከሰው ልጆች ሕይወት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው የልማት ተግባር ነው ብለዋል።
በዚህ ብሔራዊ ዘመቻ ላይ በመሳተፍ አሻራ ማኖር፣ በሀገር ልማትና በትውልድ ተስፋ ላይ አሻራ የማኖር ዕድል መሆኑንም ገልጸዋል።
ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መሳተፋቸውን የገለፁት ደግሞ ሌላኛዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የብዝኅነትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር መንደሪን ማርቆስ ናቸው።
መርሃ ግብሩ ለቀጣዩ ትውልድ ልምላሜን የተላበሰች ኢትዮጵያ ለማስረከብ ያለመ በመሆኑ፣ እስካሁን የተከሏቸውን ችግኞች በመንከባከብ እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ የትራንስፖርት ባለሙያ አቶ ኬኔዲ መላኩ በበኩላቸው፣ ከልጅነት ጀምሮ ችግኝ የመትከል ልምድ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ይህም ለተፈጥሮ ጥበቃና ለችግኝ እንክብካቤ ያላቸውን ግንዛቤ የበለጠ እንዲጎለብት አስችሎኛል ብለዋል።