ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት፡ የኢትዮጵያ ግብርና በአዲስ ምዕራፍ

በሳባ ስለሺ

መግቢያ

ኢትዮጵያ ለዘመናት የነበራትን የግብርና እምቅ ሀብት ወደ ተጨባጭ የምግብ ዋስትና ለመቀየር ተግዳሮት ሆኖባት የቆየ ቢሆንም፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመንግስት በተጀመረው ዘርፈ-ብዙ የሪፎርም ጉዞ የዘርፉ ታሪክ በተጨባጭ እየተቀየረ ነው። የዚህ ለውጥ አብይ ማሳያ የሆነውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ይፋ የሆነው "የሌማት ትሩፋት" መርሃ ግብር አንዱ ነው። ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ የሀገሪቱን የግብርና እና የእንስሳት ሀብት ልማት ጉዞ በአዲስ ምዕራፍ የቃኘ ነው።

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ሲሆን፣ በዋናነት በእንስሳት ሀብት እና ተያያዥ ዘርፎች ላይ ያተኩራል።በእንስሳት ሀብት ልማት ረገድ  የወተት ላሞችን፣ የዶሮ (ሥጋ እና እንቁላል)፣ የንብ ማነብ (ማር) እና የዓሣ እርባታን በስፋት የሚያካትት ነው።የመርሃ ግብሩ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያን ከምግብ ሸማችነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ነው። በተለይም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን በማቃለል፣ የአርሶና አርብቶ አደሩን ገቢ በማሳደግ እንዲሁም ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የምግብ ሉዓላዊነትን እውን ለማድረግ ያለመ ነው።

የሌማት ትሩፋት ለምን አስፈለገ? ፡- የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር፣ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል በመጠቀም፣ ለዘመናት የዘለቀውን የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትና ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተነደፈ ነው። መንግስት ለዚህ መርሃ ግብር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት የሚገኘውም፣ ሀገሪቱ ያላትን ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት በቴክኖሎጂ በመደገፍ ወደ ተጨባጭ እሴትና የሀገር ውስጥ ተጠቃሚነት ለመቀየር እንዲሁም የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ነው።

ባለፉት አራት ዓመታት ምን ተከናወነ?፡- ባለፉት አራት ዓመታት በተተገበረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የወተት፣ የእንቁላል፣ የሥጋ፣ የዓሣ እና የማር ምርቶችን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ተከናውኗል። ለዚህ ስኬት በቂና ጥራት ያለው የእንስሳት ተዋጽኦ ለማቅረብ የሚያስችሉ ሰፊ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻልና የማዳቀል ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ የአዳቃይ ቴክኒሻኖችን አቅም መገንባት፣ የፈሳሽ ናይትሮጂን አቅርቦትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለዘርፉ ተዋናዮች ማስተላለፍ ተችሏል። እንዲሁም የእንስሳት መኖ አቅርቦትንና ተደራሽነትን በማስፋፋት፣ የእንስሳት እርባታ ደህንነታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን በማድረግ እና አስፈላጊውን መሰረተ ልማት በማሟላት ረገድ ላለፉት አራት ዓመታት ቅድሚያ ተሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።

በመስኩ ምን ተጨባጭ ውጤት ተገኘ ?፡- የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የሀገሪቱን የምግብና ስነ-ምግብ ደህንነት ከማረጋገጥ ባለፈ፣ በዜጎች ዘንድ የቆየውን አመለካከት በመቀየር ረገድ ከፍተኛ ለውጥ አስመዝግቧል። በተለይም በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል ብቻ ተወስኖ የነበረውን የግብርና እንቅስቃሴ ወደ ከተሞች በማስፋት፣ ህጻናት፣ እናቶች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከእንስሳት ተዋጽኦ ማግኘት የሚገባቸውን አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች እንዲያገኙ አስችሏል። ይህ ተነሳሽነት የከተማ ግብርናን በማስተዋወቅ ዜጎች በቤታቸው እንስሳትን በማርባት ከራስ ፍጆታ ባለፈ ምርቶቻቸውን ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

በመሆኑም፣ ባለፉት ዓመታት በመስኩ የተመዘገቡት ስኬቶች እንደሚያሳዩት፣ መርሃ ግብሩ ዜጎች በተቋማት ተቀጥረው ከመስራት ይልቅ በዘርፉ ተሰማርተው የራሳቸው ስራ ኖሯቸው ለሌሎችም የስራ እድል እንዲፈጥሩ አድርጓል። ይህ የመንግስት ያላሰለሰ ጥረት፣ የዜጎችን የስነ-ምግብ ፍላጎት ከማሟላት አልፎ፣ ጤናማ እና ሁለንተናዊ ብቃት ያለው ትውልድ በመገንባት ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በአሀዛዊ መረጃ  የተደገፉ የዘርፉ ስኬቶች ፡- የግብርና ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በተጀመረ በአራት ዓመታት (2014 ዓ.ም -2018 ዓ.ም) ውስጥ በእንስሳት ምርታማነት አስደናቂ ለውጥ ተመዝግቧል።

በወተት ምርት፦ መርሃ ግብሩ ሲጀመር የነበረው 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሊትር የማምረት አቅም፣ በአሁኑ ወቅት ወደ   15 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሊትር አድጓል።

በእንቁላል ምርት፦ ከነበረበት 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ፣ ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ከፍ ብሏል።

በዶሮ ሥጋ ምርት፦ በ2014 ዓ.ም 90 ሺህ ቶን የነበረው የማምረት አቅም፣ በ2018 ዓ.ም ወደ 253 ሺህ ቶን ከፍ ብሏል።

በማር ምርት፦ በ2014 ዓ.ም 146 ነጥብ 7 ሺህ ቶን የነበረው የማምረት አቅም፣ በ2018 ዓ.ም ወደ 428 ሺህ ቶን ከፍ ብሏል።

በአሳ ምርት፦ የውሃ አካላትንና ሰው ሰራሽ ኩሬዎችን በአግባቡ በመጠቀም የተከናወነው የአሳ ጫጩት ስርጭት፣ ከ300 ሺህ ወደ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን አድጓል።

ይህ ውጤት ሀገሪቱ በእንስሳት ተዋጽኦ ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም በጥቂት ዓመታት ውስጥ እንዴት ማጎልበት እንደተቻለ በግልጽ ያሳያል።

ዘርፉ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ምን አበረከተ?፡- የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የሀገር ውስጥ የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ኢትዮጵያ ከእንስሳት ተዋፅኦ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ብቻ 24 ነጥብ 2 ሺህ ቶን የተቀነባበረ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ 128 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት ተችሏል።

ማጠቃለያ፦ በዘርፉ የተመዘገበውን  ስኬት ዘላቂ ለማድረግ አርብቶ አደር እና አርሶ አደሩ ከተለመደው ባህላዊ የእንስሳት አረባብ ዘዴ ለማላቀቅ የተጀመሩ ስራዎችን ማስቀጠል፣ የእንስሳት መኖ አቅርቦትንና ጤና አገልግሎትን የማዘመን፣ እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅና የማምረት አቅም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። በተጨማሪም የመንግስት፣ የግሉ ዘርፍ እና የማህበረሰቡን ቅንጅት ማጠናከር፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አሰራር መዘርጋት፣ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ያለው የገበያ ትስስር መፍጠርና የደላሎችን ጣልቃ ገብነት ማስወገድ እንዲሁም አምራቹና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ለተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ጠንካራ መሰረት ማኖር ይቻላል።


በአጠቃላይ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የግብርና እምቅ ሀብት ወደ ተጨባጭ ሀገራዊ ብልፅግና ለመቀየር የተጀመረ ውጤታማ መንገድ መሆኑን ባለፉት አራት ዓመታት አሳይቷል። ይህ ከተጠናከረ ሀገሪቱ የምግብ ሉአላዊነቷን ለማረጋገጥ ያለመችውን ትልም ከማሳካት የሚያስቆማት ነገር እንደማይኖር አመላካች ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም