ለላቀ ውጤት - የተማሪ መምህርና ወላጆች ጥምር ጥረት

በሃብታሙ ገዜ

ስልጡን የመንገድ ጠበብቶች በጥንቃቄ የከተማ ውብ ገፅታ አልበሰው ባነጿት ከዚራ አካባቢ የሚገኘው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አዳራሽ በሰው ተሞልቷል። የተሰበሰቡት ወጣት ተማሪዎች፣ የድሬደዋ አመራሮች፣ የትምህርት ዘርፍን የሚመሩ አካላትና ወላጆች በፈገግታ ተሞልተዋል። ይበልጥኑ ከወጣቶቹ ገፅታ የሚንፀባረቀው የደስታ ፈገግታ ለአዳራሹ የተለየ ብርሃን ደርቦለታል።  

የደስታቸው ምንጭ ደግሞ አምና የተፈተኑትን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በላቀ ውጤት አልፈው ሽልማት በመቀበል ላይ መሆናቸው ነው።

የአዳራሹን የሽልማት መርሃ ግብር የሚመራው ሰው ድንገት "የዛሬው ልዩ ክስተት ከሚሸለሙት ተማሪዎቻችን መካከል ከ600 በላይ ውጤት በማምጣት ከወንድሞቿ ጋር ሦስት ሆነው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ የአንድ ቤተሰብ አባላት መገኘታቸው ነው" ሲል ተናገረ። ይሄኔ አዳራሹ በጭብጨባ ተናጋ፤ ሁሉም ተሰብሳቢ በአንድነት ቆሞ ጭብጨባውን አቀለጠው።

ለሽልማት ወደ አደባባዩ የመጡት በደስታ ፀዳል የወረዙት የወላጅ ተወካይ እንጂ የድሉ ባለቤት የሆኑት እነዚህ ሦስት ተማሪዎቹ አይደሉም። 

በአዳራሹ የተሰባሰቡት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሃርና የካቢኔ አባላት እንዲሁም ተሸላሚዎቹ ተማሪዎች "የዓመቱ የተለየ ክስተት የሆኑትን ተማሪዎች" ለማየት ዓይኖቻቸው ቢባዝንም አልተሳካም። ለምን ካላችሁ ተማሪዎቹ ወደ ተመደቡበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጓዛቸው ነው።

የመድረኩ የድምፅ ማጉያ ባለቤትም ሆነ ተሰብሳቢዎቹ የዓመቱ ክስተት የሆኑት ኒያ ሰላሃዲን 602፤ አሊ ሰላሃዲን 556፣ አማን ሰላሃዲን 526 ያመጡት ተማሪዎች መንትዮች መሆናቸውን ቢያውቁ ኖሮ አዳራሹ ሌላ የግርምት ደስታን ባስተናገደ ነበር።

ሽልማቱን ያበረከቱት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሃር ተሸላሚዎች በጥረታቸው በትጋታቸው ባመጡት ውጤት መደሰታቸውን አብስረዋል። አገር በዜጎች አንድነትና መተባበር እንደሚፀናው፤ የተማሪዎች ውጤትም በተማሪዎችና በመምህራን ጥረት ብቻ ሳይሆን በወላጆች ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ ጭምር የሚመጣ ነው።

"በተለይ ከአንድ ቤተሰብ የበቀሉት ተማሪዎችና የዛሬው ሽልማት እና ውጤት ያስተማረን ይህንኑ ነው" ብለዋል ከንቲባው።

በዚህ አደራሽ ውስጥ የሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ርዕሰነ-መምህራን ታድመዋል። እንደ ድሬደዋ አስተዳደር ከተፈተኑት ከ3 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች መካከል በቀጥታ ያለፉት 250 ተማሪዎች ብቻ ናቸው። ለመጣው ውጤት ተሞጋሹም ተወቃሹም የዘርፉ አመራሮች፣ ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች ናቸው። 

የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ "ለመጣው ዝቅተኛ ውጤት በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ያለነው በሙሉ ተጠያቂዎች ነን" ብለዋል።

ኃላፊዋ ሌላውም ከዚህ ትምህርት መውሰድ እንዳለበት ነው የገለጹት። እንደ አስተዳደሩም የትምህርት አመራሮች፣ ርዕሳነ መምህራን፣ መምህራንና ወላጆች ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የተቀናጀ እንቅስቃሴ መጀመሩን አውስተዋል።

በመንግስት የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን ከኩረጃ ነፃ ለማድረግ የተወሰደው እርምጃ ተማሪዎች በጥረታቸውና በብቃታቸው የልፋታቸውን ውጤት እንዲያገኙ ያስቻለ ነው። የፈተና አሰጣጡና ውጤቱ እንደአገር ያለንበትን አዘቀት አስተምሮ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ፤ ብቁና በራስ የሚተማመን ዜጋ ለማዋለድም ጥርጊያ መንገድ ሆኖ አልፏል ማለት ይቻላል።

መንግስት የትምህርት ጥራትን ከታችኛው እርከን ጀምሮ ለማረጋገጥም በዘርፉ ሙሁራን ጥልቅ ጥናት ላይ ተመስርቶ ያዘጋጀውን የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት ያደረገ ስርዓተ ትምህርት ቀርጾ ዘንድሮ እስከ 8ተኛ ክፍል ተግባራዊ አድርጓል። ለመማር ማስተማሩ መጻህፍት ተዘጋጅተው ለመምህራን ስልጠና በመስጠትም ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። በሚቀጥለው ዓመትም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው።

በሽልማት ሥነስርዓቱ ላይ እንደታየው ለተማሪዎች ውጤት ማማር የወላጆች ሚና የጎላ ነው። ወላጆች ተገቢውን ድጋፍ እና ጥብቅ ክትትል ካደረጉ የሚፈልገው ለውጥና ውጤት ማምጣት ይቻላል።

ወይዘሮ ሙሉካ በአትኩሮት ከገለጹት ሃሶቦች መካከል ዋናዎቹን ሰበዞች መዝዤ፤ "ተጠያቂዎቹ እኛው ነን" የሚለውን ሃሳብ አንግቤ ለድሬዳዋና ለአገር ከፍ ሲል ለዓለም ህዝብ ጭምር በየዘርፉ ታላላቅ ሙሁራን ወደ አፈሩት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አመራሁ።

ድንገት ሃሳቤን ቀለበስኩት። 

መነሻዬ የወላጆች ኃላፊነት እና ድጋፍ መሆኑን መርሳት ዞሮ ዞሮ የምፅፈው መዳረሻ መርሳት ይሆንብኛል ብዬ ነው።

እናም ወደ ሦስቱዎቹ፤ የዓመቱ  ክስተቶች አባት አመራሁ።

ድሬዳዋን ለሁለት እኩሌታ የሚከፍላትን የደቻቱን ድልድይ ተሻግሬ ወደአንድ የግል የሕክምና አገልግሎት መስጫ ሆስፒታል ገባሁ። አምሮ በተሰናዳው ሆስፒታል ውስጥ ሙያዊ ኃላፊነታቸው እየተወጡ አገኘኋቸው፤ የማህፀንና የፅንስ ስፔሻሊስት ዶክተር ሰላሃዲን ዩሱፍን።

የውጤታማ ተማሪዎቹ ወላጅ ናቸው፤ በ1970 ዎቹ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መዝለቅ በመርፌ ቀዳዳ የመሹለክ ያህል በሚቆጠርበት ዘመን በከፍተኛ ማዕረግ አልፈው በቀሰሙት ዕውቀትና ጥበብ የሰዎችን ሕይወት እየታደጉ ይገኛሉ።

ዶክተር ሰላሃዲን ለትምህርት ጥራት መውደቅ ወደ ዩኒቨርሲቲ በስርቆትና ኩረጃ የመግባት ዝንባሌዎች እንደሆኑና ይሄም ሁሌም የሚያንገበግባቸው ጉዳይ መሆኑን አጫወቱኝ።

መንግስት በተለይ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ባልደረቦቻቸው በሁለተኛ ደረጃ የፈተና አሰጣጥ ላይ የወሰዱት እርምጃ አስደስቷቸዋል። "በተለይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ከሚያሳልፉት ጊዜ በበለጠ ከወላጆቻቸው ጋር ያላቸው ጊዜ ይበልጣል። ከሁሉም ነገር በላይ ለትምህርት ትኩረት ማድረጋቸውን መከታተልና መደገፍ የኛ ፋንታ ነው፤ አንዴ መስመር ከያዙ የሚመልሳቸው ችግር አይኖርም" ይላሉ።

ሦስቱ ልጆቻቸውን በዚህ መንገድ በመደገፍ እና ከትምህርት ቤታቸው ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ አስችለዋል። 604 ያመጣችው ስኮላርሽፕ ሺፕ አግኝታ ወደ ውጭ ሄዳለች፤ ሁለቱ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ናቸው።

"ለልጆቼ የፈለጉትን የማድረግ አቅም ቢኖረኝም ያለትምህርት የሚፈጠር አንዳች ነገር እንደሌለ ገብቷቸው ለውጤት በቅተዋል" ይላሉ ዶክተር ሰላሃዲን።

ብዙ የመስራት እንጂ ብዙ የመናገር ዝንባሌ የማይታይባቸው እኚህ የታታሪዎች አባት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ እና ውጤታማ ተማሪዎችን ለማፍራት በሚደረግ ጥረት የወላጆች ክትትልና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ነው በአፅንኦት ያሳሰቡት።

"የሽልማቱ መርሃ ግብር ወደሌላ አካባቢ በሄድኩበት አጋጣሚ በመካሄዱ ሳልገኝ ቀረሁ፤ በጣም የቆጨኝና ቅር ያለኝ ዕለት ሆኖ አልፏል" ብለዋል።

እሳቸውን ጨምሮ አንቱ የተሰኙ ሙሁራን ያፈራው የድሬዳዋ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ፍቃዱ ሰንበቶ፤ የማርያም ሰፈር አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ኢጀታ መኮንን ካለፈው ክፍተት በመማር ዘንድሮ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ የተማሪዎች አመለካከት ላይ ለውጥ እና እችላለሁ የሚል መርህ የማስረጽ ሥራ ተሰርቷል ብለውኛል።

ለውጤቱ ቀዳሚ ባለቤት ተማሪዎች ቢሆኑም ከወላጆቻቸው ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር የተለያዩ የማካካሻና ለፈተና ዝግጁ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ነው ርዕሳነ መምህራኑ የገለጹት።

ቅኝቴን በመቀጠል ሽቅብ ወደ ሳብያን ሁለተኛ እና የመሰናዶ ትምህርት ቤት አመራሁ። ይህ ትምህርት ቤት በከተማዋ ካሉት ትምህርት ቤቶች በውጤታማነት እና በብዛት ተማሪዎችን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማሳለፍ ረገድ ወደር አልነበረውም፤ ባለፉት ዓመታት።

ከተመሠረተ 22 ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ትምህርት ቤት በምክትል ርዕሰ መምህርነት የሚመሩት አቶ በፍቃዱ ወልደሰማያትን አገኘኋቸው። ትምህርት ቤት በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ካስፈተናቸው ከ800 በላይ ተማሪዎች መካከል ያለፉት 20 ናቸው።

የመጣው ውጤት ያለንበትን ደረጃ ፍንትው አድጎ ያሳየን መሆኑን ተከትሎ መሠረታዊ የሆኑት ችግሮች በጋራ ተነቅሰው ለመጪው ጊዜ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ተገብቷል።

አቶ በፍቃዱ እንዳሉት ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር የጋራ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ትምህርት ቤቱን ሞዴል ትምህርት ቤት ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን ለዘንድሮው ተፈታኞች ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ነው። እነዚህን ሥራዎች የተማሪ፣ መምህርና ወላጅ ህብረት በቅርበት እንዲከታተል ተደርጓል።

ለተማሪዎች ውጤት ማማር የወላጆች የቅርብ ክትትልና ደጋፍ መሠረታዊ ጉዳይ ነው የሚሉት አቶ በፍቃዱ፣ ለዚህ ጉዳይ ትምህርት ቤቱ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ነው የገለጹት። "በተለይ ወላጆች በትምህርት ውጤታማነት ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ልክ እንደ ዶክተር ሰላሃዲን አይነት ቤተሰቦች ተሞክሮ የማስፋት ሥራ ለመስራት ትምህርት ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል" ብለዋል።

"ፍቃደኛ ከሆኑ የመጀመሪያው እንግዳችን ዶክተር ሰላሃዲን በማድረግ ለወላጆች ህብረት ተሞክሮን እንዲያካፍሉ እናደርጋለን " ብለዋል።

በድሬዳዋ ታሪክ ከፍ ሲልም እንደ አገር በ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከ1990 ዎቹ ዘመን ጀምሮ እንዲህ አይነት ዝቅተኛ ውጤት አለመምጣቱን የሚገልጹት ደግሞ የትምህርት ቤቱ አንጋፋ መምህር እዮብ ረታ ናቸው።

የፊዚክስ መምህሩ እንደሚሉት የአምናው ክፍተት በሰከነ መንፈስ ታይቶ ዘንድሮ የተሻለ ሥራ ለመስራት መምህራን በጥሩ መንፈስ ጉዞ ጀምረዋል። ወላጆችም ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክ ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለት ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው የገለጹት።

"የተማሪዎች የትምህርት ቤት ቆይታ ለሰዓታት ብቻ የተወሰነ መሆኑን በመረዳት ወላጆች በስነ ምግባር የታነፀ በራስ የሚተማመን ዜጋ ለማፍራት የተጀመረውን ጉዞ መደገፍ አለባቸው" 

በትምህርት ቤቱ የዘንድሮው የ12ተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪ ረደኤት ገነሙ በበኩሏ "እንደአገር በዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረው የፈተና አሰጣጥ ኩረጃን የሚጠየፍ በራሱ ጥረት ውጤት ለማምጣት የሚተጋ ትውልድ ለመፍጠር ያግዛል" ብላለች።

በትምህርት ቤቱ የተጀመረው ልዩ ዕገዛ መጠናከርና መቀጠል እንዳለበት የምትገልጸው ተማሪ ረድኤት ወላጆቿ ተገቢውን ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ከመምህራን ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር የልጆቻቸውን ትምህርት ሊከታተሉ እንደሚገባ አውግታኛለች።

እኔም ሆንኩ የዘንድሮ ተፈታኞች ትምህርት ቤታችንንና ድሬዳዋን በውጤት ለማስጠራት ጠንክረን እያጠናን ነው ብላለች።

ከገጠር ከተማ ተጉዞ የሚማረው የድሬዳዋ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  የዘንድሮ  ተፈታኝ ተማሪ አላሙዲን አልይ በበኩሉ፤ መንግሥት የፈተና ኩረጃን ለማስቀረት የጀመረውን ተግባር ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ነው የገለፀው።

"የዘንድሮ የመምህራን ድጋፍ የተለየ ነው፤ እኛም ልዩ የጥናት ጊዜ እንዲጀመር ጫና እየፈጠርን ነው፤ ወላጆቼም በአቅማቸው እየደገፉኝ በመሆኑ ቀሪው ሥራ የኔ ጥረትና ብርታት ይሆናል፤ ልፋቴ ውጤት እንዲያስገኝ የስርቆትና የኩረጃ ሂደት መወገድ አለበት" ብሏል ተማሪ አላሙዲን።

ከሳብያን ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ግቢ ለቅቄ ስወጣ ዶክተር ሰላሃዲን ዩሱፍ ያሉኝ ትዝ  አለኝ።

"ለተሞክሮ የሚሆን ነገር እኔ ጋር ካለ ያለችኝን ጊዜ አብቃቅቼ ለዘንድሮው ተፈታኞች ሃሳቤን ለማካፈል ዝግጁ ነኝ" ያሉኝ በአዕምሮዬ ደጋግሞ እያቃጨለብኝ ጉዞዬን ቀጠልኩ።

ለመውጫ ያህል፤

በድሬዳዋ አስተዳደር ዘንድሮ በመንግሥት እና በግል 22 ትምህርት ቤቶች ከ5 ሺህ በላይ ተፈታኞች በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው። እነዚህ ተፈታኞች በራሳቸው ጥረት የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በየአቅጣጫው የተቀናጀ ድጋፍ የማድረግ  ጅምር ተግባራት ተስተውለዋል፤ ይሄ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ይህን ዙሪያመለስ ድጋፍ በማጠናከር ተማሪዎቹን ለውጤት ማብቃት በሁሉም ዘንድ ለአፍታ መዘንጋት የለበትም። መድረሻውን ለማሳመር መነሻውን አድምቶ ማበጃጀት ግድ እንደሚልም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም