የፅዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ከተሞችን ውብ፣ ፅዱ፣ ለኑሮ እና ለቱሪዝም ፍሰት የተመቹ እንዲሆኑ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የፅዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ከተሞችን ውብ፣ ፅዱ፣ ለኑሮ እና ለቱሪዝም ፍሰት የተመቹ እንዲሆኑ አድርጓል
ባህር ዳር ፤ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፡-የፅዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ከተሞችን ውብ፣ ፅዱ ፣ ለኑሮ እና ለቱሪዝም ፍሰት የተመቹ በማድረግ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ማድረጉን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለፀ።
''ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ'' በሚል መሪ ሀሳብ የሦስተኛ ዙር ክልል አቀፍ የአካባቢ ብክለት መከላከል ዘመቻ የንቅናቄ ማስጀመሪያ ፕሮግራም በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በመድረኩ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ ይገኛል።
በተለይ ከለውጡ ዓመታት ወዲህ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል የሚያስችሉ ወሳኝ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችን፣ መመሪያዎችንና ደንቦችን አውጥቶ በመተግበር ውጤታማ ስራ ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅትም በከተሞች በስፋት እየተከናወነ ያለው የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት፣የአረንጓዴ አሻራና መሰል የልማት ስራዎች ለፅዱ ኢትዮጵያ መጠናከር ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በሃይቆች፣ ወንዞችና ሌሎች የውሃ አካላት ብሎም በመኖሪያ አካባቢዎች ለማሕበረሰቡ ጤና አደገኛ የሆኑ የፕላስቲክ ውጤቶችን በማስወገድ በኩል ምሳሌ የሚሆን ስራ መሰራቱን አረጋግጠዋል።
መንግስት የአካባቢ ጥበቃን ለዘላቂ ልማትና መጭውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለበለጠ ውጤታማነት በተሻለ ትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።
''ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ'' ሦስተኛው ዙር ንቅናቄ የፕላስቲክ ውጤቶችን በማስወገድ፣ የድምፅ ብክለትን በመከላከል እና የብዝሃ ህይወት መመናመን እና የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ህብረተሰቡን እያሳተፈ ይገኛል።
የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ በልስቲ ፈጠነ በበኩላቸው፤ በፅዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቨ በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን ተችሏል።
በተለይም ጣና ሀይቅንና ሌሎች የውሃ አካላትን ከፕላስቲክ ቆሻሻና ሌሎች በካይ ነገሮች በማፅዳት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት።
አሁን ላይ የፕላስቲክ ውጤቶችን በመሰብሰብና መልሶ መጠቀም የሀብት መፍጠሪያ መሆኑን አመልክተው ፤የአካባቢ ብክለትን በዘላቂነት በመከላከል ምቹ የኑሮ አካባቢ በመፋጠር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናከረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
መንግስት በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ከሀገር አልፎ ለአህጉርና ዓለም አቀፋ መድረክ ምሳሌ የሚሆን ስራ እየሰራ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ይትባረክ አወቀ ናቸው።
በፅዱ ኢትዮጵያ ከተሞችን በመግለጥና ለቱሪዝም ዘርፉ ማደግ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅስው ይህ ንቅናቄም በተገቢው መንገድ እንዲተገበርና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
በመድረኩ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ባለሙያዎች ብሎም ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በባህር ዳር ከተማ የፅዳት ዘመቻና የፓናል ውይይት ተከናውኗል።