በተያዘው የክረምት ወቅት ከ256 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በተያዘው የክረምት ወቅት ከ256 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል
ባህር ዳር ሃምሌ 17/2018;-በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በተያዘው የክረምት ወቅት ከ256 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ አንዱዓለም አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተያዘው የመኸር ወቅት ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየተሰራ ነው።
በአጠቃላይ በተያዘው መኸር የምርት ዘመንም 412 ሺህ 480 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማምረት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
በመኸር እርሻው ከ187 ሺህ በላይ የዞኑ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን እስካሁን ባለው 256 ሺህ 249 ሄክታር መሬት በቆሎ ፣ ጤፍ ፣ ዳጉ ሳ፣ ስንዴ ፣ ሰሊጥ ፣ ሩዝ ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎች በዘር መሸፈን ተችሏል።
በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥም ከ169 ሺህ 790 ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የተዘራ መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ ገበያ ተኮር የሆኑ የቅባት ሰብሎችን በማምረት ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለገበያ ለማቅረብ እንዲቻል እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግም ለተያዘው እቅድ ስኬትም 484 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና ከ28 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።
የተሰራጨው የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት በሔክታር የተገኝውን 41 ኩንታል ምርት ወደ 43 ነጥብ ስምንት በመቶ ለማሳደግ የሚያስቸል ነው ብለዋል።
እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካትም ከዞን እስከ ቀበሌ ያለው አመራርና ባለሙያ ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል።