ቀጥታ፡

ፈተናዎችን ወደ ዕድል የቀየረው የለውጡ ዓመታት የኢንዱስትሪው ዘርፍ እመርታ

በሙሴ  መለሰ

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የተከናወኑ ሁለንተናዊ የፖሊሲና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ አዲስ መነቃቃትንና ተጨባጭ ስኬቶችን አስመዝግበዋል።መንግስት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳን ቀርፆ ወደ ተግባር በመግባት፣ የግል ዘርፉን በማበረታታት እና የአምራች ኢንዱስትሪውን በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል።

ይህ መዋቅራዊ ሽግግር የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ ከማመጣጠን ባለፈ፣ በሁሉም ንዑሳን የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ተስፋ እንዲፈነጥቅ አድርጓል። የለውጡ ዓመታት የኢንዱስትሪ ስኬቶች መካከል በዋንኛነት የሚጠቀሰው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዚያ ወር 2014 ዓ.ም ይፋ የተደረገው የ “ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።

ይህ ንቅናቄ በፋይናንስ፣ በግብዓት እና በኃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት ተዘግተው የነበሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎችን ዳግም ወደ ሙሉ ማምረት አቅማቸው እንዲመለሱ አድርጓል።

ንቅናቄው በተጀመረባቸው የመጀመሪያዎቹ ተከታታይ ዓመታት ብቻ የአገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ በርካታ የውጭ ምንዛሬ የሚያስወጡ የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የተቻለ ሲሆን፣በተለይም በጨርቃ ጨርቅ፣በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ እንዲሁም በምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎች ላይ ከፍተኛ የምርት ዕድገት ተመዝግቧል።

ይህም የሀገሪቱን የአምራች ኢንዱስትሪ አማካይ የማምረት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚያዚያ ወር 2018 ዓ.ም ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን እንደ ኮሮና ወረርሽኝና የአጎዋ (AGOA) ስረዛ ያሉ ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ችላለች።

የኢንዱስትሪ መሪነቱን ከመንግሥት ወደ ግሉ ዘርፍ የማሸጋገር ሥራን ጨምሮ በተቀረጹ ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች አማካኝነት፣ ቀደም ሲል 8 ሺህ ገደማ የነበሩት አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በአሁኑ ወቅት ከ26 ሺህ በላይ መድረሳቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ ማነቆዎች ሥራ አቁመው የነበሩ 800 ገደማ ፋብሪካዎች አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ማምረት መመለሳቸውንና ይህም የኢንዱስትሪዎችን አማካይ የማምረት አቅም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ሂደትም እስካሁን ለውጭ ምርት ይወጣ የነበረውን 3.6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ በሎጂስቲክስና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ታላላቅ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን በወቅቱ ገልጸው ነበር።

የኢትዮጵያን ግብርና ከኢንዱስትሪ ጋር ለማስተሳሰር የተከናወኑት ተግባራት ሌላኛው የለውጡ ማሳያ ነው።

በይርጋለም፣ቡሬ እና ቡልቡላ የሚገኙ የተቀናጁ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ሙሉ ስራ መግባት አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ለፋብሪካዎች እንዲያቀርብና እሴት የተጨመረበት ምርት ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ መንገድ ከፍቷል።

ይህ ስትራቴጂ የገጠር የስራ ዕድል ፈጠራን ከማሳደጉም በላይ የኢንዱስትሪዎቹን የጥሬ ዕቃ ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ትልቅ እገዛ አድርጓል።ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኬሚካል፣ በፋርማሲዩቲካል እና በሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶች ማምረቻ ዘርፍ የታየው ስኬት ለሀገሪቱ የጤና ዋስትና ትልቅ ምሰሶ ሆኗል።

ከዚህ ቀደም አብዛኛው የመድኃኒት ፍላጎት በከፍተኛ ወጪ ከውጭ የሚገባ ሲሆን፣ በለውጡ ዓመታት ግን የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች አቅም እንዲጎለብትና አዳዲስ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የፋርማሲዩቲካል ፋብሪካዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ ተደርጓል። ይህም ለአገር ውስጥ ገበያ ጥራት ያላቸው መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ አስችሏል።

በሌላ በኩል፣በኮንስትራክሽን እና ማዕድን ኢንዱስትሪ ላይ የታየው መነቃቃት የሀገሪቱን የመሠረተ ልማት ፍላጎት በራስ አቅም ለመደገፍ አስችሏል። አዳዲስ የሲሚንቶ እና የብረት ፋብሪካዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉ እና ነባሮቹ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ መደገፉ፣ በሀገሪቱ ለሚታዩት ሰፊ የኮሪደር ልማት እና የዘመናዊ ከተሞች ግንባታ ፕሮጀክቶች የአገር ውስጥ ግብዓትን በበቂ ሁኔታ ለመጠቀም አስችሏል።

ማዕድናትን በተመለከተም፣ ጥሬ ግብአት ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ የመላክ ፖሊሲ በመተግበሩ የዘርፉን የሀገር ውስጥ ገቢ ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል።

ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መፋጠን ሌላው ዋነኛ አስደጋፊ የሆነው የኢነርጂ እና ታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የውሃ፣ የንፋስ እና የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጠናቀቅና ወደ ሥራ መግባት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያገኙትን የኃይል አቅርቦት እንዲያድግ አስችሏል።

ይህ የአረንጓዴ የኃይል አቅርቦት የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ከማሳደጉም በላይ፣ የኢትዮጵያን ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ (Eco-friendly) እንዲሆኑ አድርጓል።

ከነዚህ ዘርፎች ባሻገር፣ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር ተከትሎ በቴክኖሎጂው እና በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ አበረታች ስኬቶች ተመዝግበዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የሞባይል ስልኮች እና የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች የመገጣጠም ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።በተለይም ደግሞ ለአካባቢ ጥበቃና ለነዳጅ ወጪ ቅነሳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EVs) በአገር ውስጥ በስፋት መገጣጠም መጀመራቸው ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ ራሷን እንድትችል እና ለሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ዘላቂ የስራ ዕድል እንዲፈጠር መሰረት የጣለ እርምጃ ሆኗል።

በአጠቃላይ፣ የለውጡ ዓመታት በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር የተደረገባቸው ነበሩ ሊባል ይችላል።

ከፖሊሲ ማሻሻያ ጀምሮ እስከ መሬት ወርደው የተተገበሩ ሀገራዊ ንቅናቄዎች ድረስ የተከናወኑት ተግባራት ሀገሪቱ በምርት ራሷን እንድትችል እና የውጭ ምርት ጥገኝነትን እንድትቀንስ አግዘዋታል። እነዚህ የተመዘገቡ ስኬቶች የኢትዮጵያን የነገ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ጠንካራ መሰረቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም