የሃሳብ መቀራረብን በማጠናከር የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ የሚገነባ ምክክር እያደረግን ነው - የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሃሳብ መቀራረብን በማጠናከር የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ የሚገነባ ምክክር እያደረግን ነው - የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 16/2018 (ኢዜአ) ፦ በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ያለምንም ገደብ የሃሳብ መቀራረብንና የጋራ መግባባትን በማጎልበት የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ የሚገነባ ምክክር እያደረጉ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።
ከሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች በንዑስ ቡድኖች ተከፋፍለው በተመደቡባቸው አጀንዳዎች ላይ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተመካከሩ ነው።
የምክክር ጉባኤው ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ያለመግባባት ጉዳዮችን ለመፍታት በተሰባሰቡ የሕዝብ ወኪሎች እየተካሔደ ያለው ምክክር ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሠረት የሚጥል ነው።
በምክክር ጉባኤው ላይ የሚመከርባቸው አጀንዳዎችም የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ በማጎልበት ሀገራዊ አንድነትን፣ መከባበርንና ዘላቂ መግባባትን የሚያጠናክሩ እንደሆኑም ገልጸዋል።
ተመካካሪ ሊቀ ካህናት መልዓከ ሰላም ጌታሰው በላይ እንዳሉት፤ የምክክር ጉባኤው የሁሉም ዜጎች የሕዝብ ወኪሎች በአንድ መድረክ ተሰባስበው እየመከሩበት የሚገኝ ታሪካዊ ዕድል ነው።
ስለ ሀገር አንድነት፣ ሰላምና መግባባት እየመከርን ነው ያሉት ሊቀ ካህናት መልዓከ ሰላም ጌታሰው በላይ፣ በቀጣይም ጠንካራ ሀገራዊ መግባባት እንዲገነባ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ ፓስተር ጻዲቁ አብዶ በበኩላቸው፣ ምክክር በኃይማኖታዊ አስተምህሮ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው እሴት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤም ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ጠቃሚ ትምህርት የሚያስተላልፍ የኢትጵያዊያን የጋራ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ የሐሳብ መሸናነፍ ሳይሆን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን የጋራ አሸናፊ ለማድረግ የሚያስችል የመግባባት ሂደት መሆኑንም አመልክተዋል።
ተመካካሪ አባገዳ ደቻሳ ወዳጆ በበኩላቸው፣ ምክክሩ ለትውልድ ተስፋ የሚጣልበት ታሪካዊ የተሞክሮ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡም በተስፋ የሚጠብቀው ሂደት በመሆኑ ስለ ኢትዮጵያ ቀጣይ ዕድገትና ልማት በማሰብ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ በበኩላቸው፣ በምክክሩ የሕዝብ አጀንዳዎችን በነፃነትና በተገቢው መንገድ የሚያቀርቡበት ምቹ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
በዚህም በተመረጡት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ጥልቅና ገንቢ ምክክር እያካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሀገራችን ይጠቅማሉ ብለን በምናምንባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ወደ መግባባት ለመድረስ እየሠራን ነው ብለዋል።
ተመካካሪ አቶ ሳይመን ቶት በበኩላቸው፣ ምክክሩ የመወያየትና የመደማመጥ ባህልን ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፍ ጠንካራ መሠረት በመጣል መግባባት የሰፈነባትን ሀገር ለመገንባት አስፈላጊ ነው ብለዋል።