የአረንጓዴ ዐሻራ፤ ከሥነ-ምኅዳር ዘብ እስከ ዓለም የልማት ተምሳሌት - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ፤ ከሥነ-ምኅዳር ዘብ እስከ ዓለም የልማት ተምሳሌት
በመጽሔት አንለይ
በወሳኝ ሀገራዊ የልማት ውይይቶች ላይ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸው፣ በዚህም በርካታ ሚሊየን ሄክታር መሬት መታደሱ በአበይት ጉዳይነት ይነሳሉ።
ኢትዮጵያ እየተገበረችው ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአርሶ አደሩ ምርታማነት ማደግ፣ የወጣቱ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን፣ የእናቶች የኑሮ መሻሻልና የተፈጥሮ ሃብት መጠበቅ መቻሉ እንዲሁም የአየር ንብረት መዛባትን ማስተካከልና የደን ሽፋንን ማሳደጉ ለመርሃ ግብሩ ውጤታማነት በአብነትነት ይጠቀሳሉ።
በዚህ አተያይ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከተራ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ባሻገር በአካባቢ ጥበቃ፣ በግብርና፣ በምግብ ዋስትና፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ልማት ዘርፎች መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት አንጸባራቂ ውጤት እያሰገኘ ነው።
የዓለም አየር ንብረት ጉዳይ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ባለበት ወቅት፣ አፍሪካ የችግሩ ተጠቂ ብቻ ሳትሆን ለመፍትሄውም የራሷን ልምድና አቅም ማበርከት እንደምትችል እያሳየች ይገኛል። የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሀገራዊ ንቅናቄም ለአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃ ጥረት አዲስ የተግባር ልምድ እየሆነ መጥቷል።
የአረንጓዴ ዐሻራው ልዩነት በተተከሉ ችግኞች ቁጥር ብቻ አይለካም። በተራቆቱ መሬቶች ላይ የተመለሰው ሕይወት፣ በገጠር የተፈጠሩ የኢኮኖሚ ዕድሎች፣ የተጠበቁ የውሃ ሀብቶችና ለወደፊት ትውልድ የተገነባው የአካባቢ መሠረት ዋናው ውጤቱ ነው።
አረንጓዴ ዐሻራ፤ ከርዕይ ወደ ተግባር!!
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በሀገራዊ ለውጥ ማግስት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሕዝባዊ ተሳትፎ የተጀመረ ሲሆን፤ እስካሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ከዚህ በፊት የነበረው የተፈጥሮ ሃብት መራቆት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ብቻ ሳይሆን በዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይም ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ ነበር።
የአፈር መሸርሸር፣ የደን መጥፋትና የድርቅ ተጋላጭነቶችም የገጠር ሥነ-ምኅዳራዊ ሕይወትን ሲፈታተኑ ቆይተዋል። ይህን ምላሽ ለመስጠትም የአረንጓዴ ዐሻራ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማትና የደን ሽፋንን ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
የአረንጓዴ አሻራ የኢኮኖሚ ዐሻራ፡- የአረንጓዴ ዐሻራ ትርጉም በአካባቢ ጥበቃ ብቻ አይወሰንም። በኢኮኖሚውም ውስጥ አዲስ የልማት መንገድ እየፈጠረ ይገኛል። በጥምር ግብርና (Agroforestry) አማካኝነት ቡና፣ ፍራፍሬና ሌሎች የኢኮኖሚ ዋጋ ያላቸው ምርቶች ከደን ልማት ጋር እንዲሰናሰሉ አድርጓል።
ይህም የገቢ ምንጭን ከማስፋት ባሻገር የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ አስተዋፅዖ አድርጓል። በተለይ የቡና ዘርፍ ከሚሊዮን ወደ ቢሊዮን ዶላር ደረጃ መሻገሩ የዚህ ጥምረት ውጤት አንዱ ማሳያ ነው። የአቮካዶ ምርት ለወጪ ንግድ የፈጠረው ዕድልም አንዱ የአረንጓዴ ዐሻራ ውጤታማነት አብነት ሆኗል። በሌሎች የፍራፍሬ ምርቶች ላይ የመጣው ዕድገት ኢትዮጵያን በዓለም ገበያ የተሻለ ተወዳዳሪ የምትሆንበትን ዕድል ፈጥሯል።
ከአፈር ጥበቃ እስከ ምግብ ዋስትና፡- የአረንጓዴ ዐሻራ በአፈር ጤናማነት ላይ ያመጣው ለውጥ የግብርና ምርታማነትን ከፍ አድርጓል። የአፈር ኦርጋኒክ ካርቦን መጨመር፣ የውሃ ማቆየት አቅም መሻሻልና የተፋሰስ ልማት በኢትዮጵያ የመስኖ ልማትና የምግብ ምርት ዕድገት መሠረት ጥለዋል። የስንዴ ምርታማነት ዕድገት እና የቤተሰብ ብልፅግናን የሚያረጋግጥ ስኬታማ ጉዞም የአረንጓዴ ዐሻራ ተጠቃሽ ውጤቶች ናቸው።
የተፈጥሮ ጋሻነት፡- ኢትዮጵያ ለድርቅ፣ ለጎርፍና ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናት። ዛፎችና ስሮቻቸው አፈርን በመያዝ መሸርሸርን ይቀንሳሉ፤ የውሃ ሃብቶችን ጠብቆ በማቆየትና በማሻሻል የድርቅ ተጋላጭነትን የመቋቋም አቅም እየገነባ ነው።
በተለይም በርካታ የኃይል ማመንጫ ግድቦችንና የውሃ ሃብቶችን ከደለል አደጋ ለመጠበቅ የደን ልማት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ እሙን ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም የተፈጥሮ አደጋዎችን በመቀልበስ የተፈጥሮ ጋሻነቱን እያረጋገጠ ይገኛል።
የትውልድ ሐውልትና የልማት ውርስ የሆነው አረንጓዴ ዐሻራ!!
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የመንግሥትና የሕዝብ የጋራ ተሳትፎ ውጤት መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ በአንድ ወቅት ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻም፣ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደው ዘመቻ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ተሳትፈውበታል። ይህም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪክ በመፃፍ በልማት መስክ አስደናቂ የትብብር መንፈስ እንዲገነቡ አስችሏል።
የመርሃ ግብሩ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አረንጓዴ ዐሻራ የደን ውድመትን በመከላከል የተፈጥሮ ሃብትን ለመጠበቅ፣ የድርቅና የበረሃማነት ተጋላጭነትን ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እያስገኘ ነው።
የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተፅዕኖ መቋቋም አዲስ የዲፕሎማሲ ሚና!!
በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መድረክ የአፍሪካ ዋና ጥያቄ የአየር ንብረት ፍትሐዊነት ነው። አህጉሪቱ በአነስተኛ የካርቦን ልቀት ላይ ብትገኝም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ከባድ ጫናን እየተጋፈጠች ይገኛል። በዚህ አውድ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራን እንደ ሀገራዊ ፕሮጀክት በመውሰድ ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር የሚጋራ ተሞክሮ ፈጥራለች።
የአፍሪካ አህጉራዊ የአየር ንብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱም ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ያላትን ተሳትፎና አመራር ያሳየ ክስተት ነው። ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአየር ንብረት ውይይት ማዕከል እንድትሆን ከማገዙም በላይ የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መድረኮችን ለማስተናገድ ያላትን አቅም በተግባር አሳይቷል።
ማጠቃለያ፡- የተተከለ ችግኝ፣ የተገነባ ተስፋ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ዳርቻ ''ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፤ በዚህ ዓመት ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ግብ ተቀምቷል። በዚሁ ወቅትም ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ወደ 65 ቢሊዮን ችግኞች ግብ የመድረስ ትልማችንን ለማሳካት በፅናት እየገሰገስን እንገኛለን ብለዋል፡፡
ዘንድሮም የተያዘውን የስምንት ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብ ለማሳካት በሚደረገው ብሔራዊ የንቅናቄ ስራ ላይ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ መትከል ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ የወደፊት የዕድገትና ብልፅግና ማሳኪያ የልማት ትልም እንጂ። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም ከአንድ ችግኝ ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መድረክ የደረሰ የሀገር ተሞክሮ ነው። የተተከሉት ችግኞች ዛሬ የአካባቢ ጥበቃ ዘብ ሲሆኑ፣ ነገ ደግሞ የኢኮኖሚ ዕድል፣ የምግብ ዋስትና፣ የኃይል ዘላቂነትና የትውልድ ተስፋ ይሆናሉ።
የተተከለው ችግኝ ነገ የሚሆነው ዛፍ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር የኢኮኖሚ ጥንካሬ፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ጋሻና ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ሕያው ቅርስ ነው።
አረንጓዴ ዐሻራ ዛሬ የሚተከል ተስፋ፣ ነገ የሚሰበሰብ ብልፅግና ነው፤ ተስፋን እንትከል!!!