ቀጥታ፡

የኢትዮጵያዊያን ምክክር፤ የጋራ ነገን የሚያሻግር የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ ድልድይ

 በሚኪያስ ጎቡ

መግቢያ፡- ሀገራት ከጦርነት በላይ የሚፈትናቸው ጠላት አለ፤ እርሱም በአንድ ሀገር ልጆች መካከል የሚፈጠረው የመተማመን መሰናክል ነው። መሣሪያ የፈጠረውን ጉዳት እንደገና መገንባት ይቻላል። የተሰበረ ልብና የጠፋ መተማመን ግን በጉልበት አይመለስም። ለዚህም ነው ብዙ ሀገራት ከግጭት በኋላ ወደ ምክክር የሚመለሱት።

ብሔራዊ ምክክር የአንድ መንግሥት ፕሮጀክት ወይም የፖለቲካ ውድድር አይደለም። የአንድ ትውልድ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው የሰላም ውርስ ነው። የሚጋጩ ሃሳቦች በጠመንጃ ሳይሆን በቃል ሲገናኙ፣ የተለያዩ ትርክቶች በመደማመጥ ሲቀራረቡ፣ ልዩነቶችም የጥላቻ ምንጭ ሳይሆኑ የመግባባት መነሻ ሲሆኑ ነው እውነተኛ ሀገራዊ ምክክር የሚፈጸመው።

የዓለም ተሞክሮ እንደሚያሳየው ብሔራዊ ምክክር አንድ ዓይነት ቀመር የለውም። እያንዳንዱ ሀገር በታሪኩ፣ በባህሉ፣ በፖለቲካዊ እውነታውና በማኅበራዊ መዋቅሩ መሰረት የራሱን መንገድ ይመርጣል። ነገር ግን የሁሉም ግብ አንድ ነው፤ ግጭትን በመግባባት፣ ጥላቻን በመተማመን፣ ፍርሃትን በተስፋ መተካት።

በአውሮፓ ከኮሙኒዝም ውድቀት በኋላ፣ በአፍሪካ ከአምባገነናዊ አስተዳደሮች ሽግግር ወቅት፣ በደቡብ አሜሪካ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ሂደቶችና በዓረቡ ዓለም ከፖለቲካ አብዮቶች በኋላ የተካሄዱ ምክክሮች አንድ ትልቅ ትምህርት ይሰጣሉ። ምክክር ሲታመን ሀገር ያድናል፤ ለፖለቲካ ጥቅም ሲውል ግን ቀውስን ያባብሳል።

ይህ የኢትዮጵያም ትልቁ ፈተና ነው። ሀገራዊ ምክክር የአንድ ተቋም ወይም የአንድ ወገን ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነት ነው። የምንናገረው ቃል፣ የምንጽፈው ሐሳብ፣ የምናዳምጠው አቋምና የምንቀበለው ልዩነት የነገዋን ኢትዮጵያ ይቀርጻሉ። ምክክር የሚጀምረው በአዳራሽ ሳይሆን በሰዎች ልብ ውስጥ ነው፤ የሚሳካውም ከመናገር በላይ በመደማመጥ ሲቻል ነው።

ስለዚህ የዛሬው ጥያቄ "ምክክር ይካሄድ ወይ?" የሚል አይደለም። "ምክክሩን ለሀገር የሚበጅ፣ ለትውልድ የሚተርፍ፣ ለታሪክ የሚያስከብር እንዴት እናድርገው?" የሚለው ነው። መልሱም በአካታችነት፣ በእውነት፣ በመከባበርና በሀገርን ከግል ጥቅም በላይ በማስቀደም ውስጥ ይገኛል።

ምክክር፤ የሀገር መድኃኒት ወይስ የትውልድ ፈተና? 

ምክክር ለምን ያስፈልጋል?፡- ማንኛውም ሀገር የሚያድገው በሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ግንባታ ብቻ አይደለም። በሕዝቦቿ መካከል በሚኖረው መተማመን ጭምር እንጂ። መንገድ፣ ድልድይና ፋብሪካ መገንባት ይቻላል፤ ነገር ግን የተሰበረ ማኅበራዊ ትስስር ካልተጠገነ የልማቱ መሠረት ይናወጣል። ስለዚህ ብሔራዊ ምክክር የፖለቲካ መድረክ ብቻ ሳይሆን የሀገር የወደፊት ዕጣ ፋንታ የሚወሰንበት የጋራ አስተሳሰብ ሂደት ነው።

የምክክሩ ዋና ዓላማ አሸናፊና ተሸናፊ መፍጠር አይደለም። ይልቁንም ሁሉም ወገኖች የራሳቸውን እውነት እየገለጹ፣ የሌላውንም እውነት በማዳመጥ የጋራ መግባባት የሚፈጥሩበት ሂደት ነው። እውነተኛ የምክክር ድል የሚለካውም የማን ሃሳብ አሸነፈ ሳይሆን ለሀገር ምን ያህል ሰላምና መተማመን ፈጠረ በሚለው ነው።

የዓለም ተሞክሮ የሚያስተምረን፡- የታሪክ ገጾች እንደሚያሳዩት ሀገራት የብሔራዊ ምክክርን መንገድ የመረጡት ሌሎች አማራጮች ሲያቅቷቸው ነው። አንዳንዶቹ የረዥም ጊዜ የፖለቲካ ቀውስ ነበራቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ በዘር፣ በሃይማኖት ወይም በሥልጣን ሽኩቻ ተከፋፍለው ሲራኮቶ የሰነባበቱ ናቸው። ነገር ግን የተሳካላቸው ሀገራት አንድ የጋራ መርህ ነበራቸው፤ የሀገርን ጥቅም ከፓርቲ፣ ከቡድንና ከግል ጥቅም በላይ አስቀድመዋል።

ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ወደ ዴሞክራሲ የተሸጋገረችው በበቀል ሳይሆን በሰለጠነ ምክክር ነው። ፖላንድና ሀንጋሪ የፖለቲካ ሽግግራቸውን በየጠረጴዛ ዙሪያ ምክክር አሳልፈዋል። ላይቤሪያና ሊባኖስ የጦርነት ቁስላቸውን ለማዳን የመደማመጥን መንገድ መርጠዋል።

በተቃራኒው ግን ምክክርን ለፖለቲካ ሕጋዊነት ማግኛ፣ ለሥልጣን ማራዘሚያ ወይም ለውጭ ጫና ማስታገሻ ብቻ ያደረጉ ሀገራት የበለጠ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል። ይህም አንድ ግልጽ ትምህርት ይሰጠናል፤ የምክክር ስኬት የሚወሰነው በመድረኩ ሳይሆን በተመካካሪዎች ቅንነት መሆኑን ያስረዳናል።

ምክክር የሚጠይቀው ከባድ ኃላፊነት፡- ሀገራዊ ምክክር የኮሚሽን ወይም የመንግሥት ሥራ ብቻ አይደለም። የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነትን የሚጠይቅ የጋራ ነገ አሻጋሪ ድልድይና የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ ነው። ፖለቲከኛው የሀገርን ጥቅም ማስቀደም፣ የሚዲያው እውነትን በሚዛናዊነት ማቅረብ፣ የሲቪክ ማኅበራት የተገለሉ ድምፆችን ማሰማት፣ የኃይማኖት ተቋማት ይቅርታና መቻቻልን ማስፋፋት፣ ወጣቱ ከጥላቻ ይልቅ ውይይትን መምረጥና ምሁራን በማስረጃ የተደገፈ ሃሳብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

ማንም ወገን የራሱን አቋም ብቻ ለማስገደድ ከሞከረ፣ ምክክሩ ወደ ክርክር ይቀየራል። ሁሉም ለመረዳት እንጂ ለማሸነፍ ካልመጡ ደግሞ የምክክሩ መንፈስ ይጠፋል። የሀገራዊ ምክክር ትልቁ ድል የሌላውን አቋም መለወጥ ሳይሆን፣ የሌላውን ህመም መረዳት ነው።

ምክክር፣ ውይይት፣ ድርድርና ክርክር፤ ልዩነታቸው ምንድን ነው?፡- ብዙ ጊዜ ምክክር፣ ውይይት፣ ድርድርና ክርክር የሚሉት ቃላት በአንድ ትርጉም ይጠቀሳሉ። ነገር ግን በፖለቲካዊና በማኅበራዊ ሂደቶች እያንዳንዳቸው የተለየ ዓላማና ባህሪ አላቸው። ይህንን ልዩነት አለማወቅ ሀገራዊ ምክክርን ከመጀመሪያው ሊያዛባው ይችላል። ውይይት የሐሳብ ልውውጥ ነው። ሰዎች ስለ አንድ ጉዳይ አመለካከታቸውን ይገልጻሉ፣ ይደማመጣሉ። ሁልጊዜ ውሳኔ ላይ ላይደርስ ይችላል። ክርክር የሚያተኩረው የማን ሃሳብ ትክክል እንደሆነ ላይ ነው። የራስን አቋም በማስረጃ ለማስረዳት ይደረጋል፤ አንድ አሸናፊና አንድ ተሸናፊ ሊኖር ይችላል። ድርድር ደግሞ የጥቅም ግጭትን በመካከለኛ መፍትሔ ለመፍታት የሚደረግ ሂደት ነው። እያንዳንዱ ወገን ከአቋሙ በመቀነስ የጋራ መፍትሔ ለማግኘት ይሞክራል። 

ሀገራዊ ምክክር ግን ከእነዚህ ሁሉ የላቀ ሂደት ነው። ዓላማው ማንንም ማሸነፍ ወይም ማስሸነፍ ሳይሆን የሀገር የወደፊት አቅጣጫ ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር ነው። በምክክር ውስጥ የሚሸነፍ ሰው የለም፤ የሚያሸንፈው ሀገር ነው።

የኢትዮጵያ ልዩ እውነታ፡- ኢትዮጵያ ሦስት ሺህ ዘመናትን የተሻገረ በሕብር ያሸበረቀ ታሪክ፣ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ኃይማኖት ያላት ሀገር ናት። ይህ በሕብር ያሸበረቀ ልዩነት የኢትዮጵያ ጥንካሬ መሆን ሲገባው በተለያዩ ወቅቶች የፖለቲካ አለመግባባቶችና የታሪክ ትርክቶች የመከፋፈል መሣሪያ ሆነው ቆይተዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ፈተናም ይህ ነው። ሁሉም የራሳቸውን ታሪክ ይዘው ወደ ጠረጴዛው ይመጣሉ፤ ነገር ግን ከጠረጴዛው የሚወጡት አንድ የጋራ የወደፊት ርዕይ ይዘው መሆን አለባቸው። ይህ ቀላል አይደለም። ስለዚህ ምክክሩ ከቃላት በላይ በተግባር የሚገለጥ ቅንነትን ይፈልጋል። የዋናው ምክክር ጉባኤ የህዝብ ወኪል ተመካካሪዎችም ሀገርን የማስቀደም ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ስኬታማ ምክክር የሚመሰረትባቸው አምስት ምሰሶዎች፡- ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን ቢያንስ አምስት መሠረታዊ ምሰሶዎች ሊኖሩት ይገባል። እነሱም መተማመን፣ አካታችነት፣ እውነት፣ ፍትሕና የጋራ ርዕይ ናቸው። ከሁሉም ክልሎች፣ ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እና በውጭ ከሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበራሰብ የሕዝብ ወኪል 4 ሺ ተመካካሪ ኢትዮጵያዊያንም በሀገር ግንባታ ጉዳይ፣ የመንግስት አደረጃጃትና ስርአት ጉዳይ፣ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባ እና ድሬድዋ ከተሞች ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ ሙስናና የመልካም አስተዳዳር ጉዳዮች፣ የሰላም ግንባታ ጉዳዮች በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽ ማዕከል እየመከሩ ይገኛል። ሀገራዊ ምክክር ያለፈውን ለመቁጠር ሳይሆን፣ የወደፊቱን ለመገንባት የሚደረግ የጋራ ጉዞ ነው። የኢትዮጵያ መንገድም የልዩነት ግድግዳን የሚያፈርስ የትውልድ አደራና የብሔራዊ መግባባት ማሰሪያ ጥበብና ትልም ሆኖ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር፤ የተገኙ ዕድሎች፣ ዋና ፈተናዎች እና የወደፊት አቅጣጫ

በታሪክ ጉዞዋ ውስጥ ኢትዮጵያ ብዙ የፈተና ዘመናትን አልፋለች። አንዳንዶቹ ፈተናዎች ከውጭ ጥቃት የመጡ ቢሆኑም፣ አብዛኞቹ ግን ከውስጣዊ አለመግባባቶች፣ ከተለያዩ የታሪክ ትርክቶች፣ ከፖለቲካ ፉክክርና ከመተማመን እጥረት የተፈጠሩ ናቸው። ስለዚህ የዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት የዛሬን ችግር ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፣ የትውልድ ዕዳን ለማቃለል የተጀመረ ታሪካዊ ሂደት ነው።

ይህ ሂደት ቀላል አይደለም። በርካታ ዓመታት የተከማቹ ቅሬታዎች፣ የተለያዩ እውነታዎች፣ የተቃራኒ ትርክቶችና የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎቶች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ መገናኘታቸው በራሱ ትልቅ ፈተና ነው። ነገር ግን ከዚህ በላይ ትልቁ ፈተና ልዩነትን ወደ መግባባት መቀየር ነው።

ዕድሎች፤ ሊጠቀሙባቸው የሚገቡ ወሳኝ መስኮቶች፡- የሀገራዊ ምክክር ሂደት ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ የምታነሳበት ትልቅ አጋጣሚ ነው። የታሪክ አተረጓጎም፣ የማንነት ጥያቄዎች፣ የሥልጣን ክፍፍል፣ የሀብት አጠቃቀም፣ የፍትሕ ጉዳዮችና የአብሮነት ዕሴቶች በጦርነት ሳይሆን በሐሳብ የሚፈቱበት ዕድል ይፈጥራል።

ከዚህም በላይ ምክክሩ የፖለቲካ ባህልን ለመቀየር የሚያስችል ዕድል ነው። ለብዙ ዓመታት "አሸናፊና ተሸናፊ" በሚለው አስተሳሰብ የተመራውን ፖለቲካ ወደ "አብሮ ማሸነፍ" የሚሸጋግር ከሆነ እውነትም የኢትጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ ጠንካራ መሠረት ያገኛል።

በሂደቱ ፊት የሚቆሙ ፈተናዎች፡- ማንኛውም ሀገራዊ ምክክር ከፍተኛ ተስፋ እንደሚፈጥር ሁሉ ከባድ ፈተናዎችንም ይዞ ይመጣል። የመጀመሪያው ፈተና የመተማመን እጥረት ነው። ለብዙ ዓመታት የተገነባ ጥርጣሬ በጥቂት ወራት አይጠፋም። ስለዚህ የምክክሩ ተዓማኒነት በእያንዳንዱ እርምጃ ሊገነባ ይገባል። ሁለተኛው ፈተና የተለያዩ የታሪክ ትርክቶች ናቸው። 

አንድ ክስተት በአንዱ ወገን የድል ታሪክ ሲሆን፣ በሌላው ወገን የመከራ ታሪክ ሊሆን ይችላል። ይህን ልዩነት በክብር መቀበል እንጂ መግፋት አይቻልም። በሌላ መልኩም የጥላቻ ንግግርና የሐሰት መረጃ ስርጭት ነው። በዲጂታል ዘመን አንድ ያልተረጋገጠ መረጃ በጥቂት ደቂቃዎች ሺዎችን ሊደርስ ይችላል። ስለዚህ የሚዲያ ተቋማትና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሚወስዱት ኃላፊነት ከመቼውም በላይ ወሳኝ ይሆናል።

የምሁራንና የመገናኛ ብዙኅን ሚና፡- በብሔራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ምሁራን ስሜትን ሳይሆን ማስረጃን ማቅረብ አለባቸው። የማኅበረሰብ ችግሮችን በሳይንሳዊ ጥናት መተንተን፣ ከሌሎች ሀገራት ልምድ መማርና አማራጭ መፍትሔዎችን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። መገናኛ ብዙኅንም በዚህ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና አላቸው። መገናኛ ብዙኅን ወሬን ከማባዛት ይልቅ እውነትን ማጣራት፣ ልዩነትን ከማባባስ ይልቅ መግባባትን ማጎልበት፣ ስሜትን ከማቀጣጠል ይልቅ እውነታን ማቅረብ አለበት። ምክክሩን የሚያጠናክር የመገናኛ አውታር ታሪክ ይሠራል፤ የሚያደናቅፍ ደግሞ በታሪክ ይጠየቃል።

ሀገራዊ ምክክር በአንድ ቀን የሚጠናቀቅ ክስተት አይደለም። ምክክር በትውልድ የሚገነባ የፖለቲካ ባህል ነው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራውን ሊጨርስ ይችላል፤ ነገር ግን የመደማመጥ ባህል በሕዝብ ውስጥ ካልሰረጸ የምክክሩ እውነተኛ ዓላማ አይሳካም።

የዛሬ ውሳኔ፤ የነገ ኢትዮጵያ፡- አንዳንድ የታሪክ ወቅቶች በየቀኑ አይመጡም። አንዳንድ ውሳኔዎችም የአንድ መንግሥት ዘመንን ብቻ ሳይሆን የትውልዶችን ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ። ሀገራዊ ምክክር የእነዚህ ታሪካዊ ውሳኔዎች አንዱ ነው። ዛሬ በምንመርጠው የምክክር ባህል፣ በምንገነባው መተማመንና በምናሳየው የፖለቲካ ብስለት ላይ የነገዋን የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ተምሳሌት ኢትዮጵያ ያንፃል።

ምክክር ሁሉንም ችግር በአንድ ጊዜ የሚፈታ አስማታዊ መፍትሔ አይደለም። ነገር ግን ጦርነትን ከውይይት፣ ጥላቻን ከመቻቻል፣ መከፋፈልን ከመተባበር የሚተካ ብልህ መንገድ ነው። የሚያደርገውም ልዩነቶችን ማጥፋት ሳይሆን ልዩነቶችን በአንድ ሀገር ጣሪያ ስር እንዴት እንደሚኖሩ የጋራ ሕግና ሥርዓት መፍጠር ነው።

በእርግጥ ኢትዮጵያ ከባድ ፈተናዎችን አሳልፋለች። የፖለቲካ አለመተማመን፣ የማንነት ጥያቄዎች፣ የፀጥታ ችግሮች፣ የኢኮኖሚ ጫናዎችና የማኅበራዊ ስብራቶች በቀላሉ የሚያልፉ አይደሉም። ይሁን እንጂ እነዚህን ችግሮች በጥይት ከመፍታት ይልቅ በምክክር ለመፍታት መሞከር በራሱ የታሪክ ለውጥ ነው።

ይህ ጉዞ ግን የአንድ ተቋም ብቻ አይደለም። የመንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙኅን ተቋማት፣ የምሁራን፣ የወጣቶች፣ የሴቶችና የእያንዳንዱ ዜጋ የጋራ ኃላፊነት ነው። የሀገር ዕጣ ፋንታ ለአንድ ቡድን ብቻ የሚተው አይደለም፤ በጋራ የሚገነባ እንጂ።

ከምክክር ወደ ባህል፡- ምክክሩ ተጠናቀቀ ማለት የሀገሪቱ ችግሮች ተፈቱ ማለት አይደለም። እውነተኛው ስኬት የሚለካው የመደማመጥ ባህል በማኅበረሰቡ ውስጥ ሲሰርጽ ነው። በትምህርት ቤቶች፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በመገናኛ ብዙኅን፣ በፖለቲካ ተቋማትና በየቤቱ የመነጋገር ባህል ካልጠነከረ፣ ምክክሩ የሰነድ ውጤት ብቻ ሆኖ ይቀራል።

የእውነተኛ ዴሞክራሲ መሠረት ተመሳሳይ አስተሳሰብ መኖር አይደለም፤ የተለያዩ አስተሳሰቦችን በሰላም የመቀበል ባህል መኖር ነው። ልዩነት የችግር ምንጭ ሳይሆን የጥንካሬ ምንጭ ሲሆን ነው አንድ ሀገር ዘላቂ ሰላም የምታገኘው።

የማጠቃለያ፡- የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሚያስፈልገው ብልህ አመራር ብቻ አይደለም፤ ታጋሽ ዜጎችንም ይፈልጋል። ሀገር የምትገነባው በግንብ ሳይሆን በመተማመን ነው። ሰላም የሚጸናውም በፍርሃት ሳይሆን በፍትሕ ነው።

ዛሬ የምንመርጠው የምክክር መንገድ ነገ ለልጆቻችን የምንተወው ታሪክ ይሆናል። ስለዚህ በኢትዮጵያን ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተደራጅተው የሚመከርባቸው ስምንት ዐበይት አጀንዳዎች የዛሬ አጀንዳ ብቻ አይደሉም፤ የነገዋን ኢትዮጵያ የሚቀርጽ የትውልድ አደራ እንጂ። የዋናው ምክክር ጉባኤ ተመካካሪ የሕዝብ ወኪሎችም ከግልና ቡድን ፍላጎት ይልቅ የቀጣዩን ትውልድና ሀገርን ማስቀደም ይጠበቅባቸውል። 

ምክክር የቃላት ልውውጥ ብቻ አይደለም፤ የተሰበረ መተማመንን የሚጠግን፣ የተከፋፈለ ማኅበረሰብን የሚያቀራርብ፣ የትውልድ ታሪክን በአዲስ ተስፋ የሚጽፍ ሀገራዊ ጥበብ ነው። የምንወስነው ዛሬ የምንወርሰውን ነገ ይበይናል። 

ምክክር የሀገር መድኅን ነው፤ ኢትዮጵያም እየመከረች ነው። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም