ቀጥታ፡
ማህበራዊ
ለመንግሥት ገቢ መሆን የነበረበትን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰወር ወንጀል የተጠረጠሩ የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር ዋሉ
Nov 27, 2025 203
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ ለመንግሥት ገቢ መሆን የነበረበትን ከ100 ቢልዮን ብር በላይ በመሰወር ወንጀል የተጠረጠሩ የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል። የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶችና ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር በሚባሉ የገንዘብ ክፍያ ስርዓት አቅራቢ ተባባሪ ተቋማት ዙሪያ ጥናትና ክትትል ሲከናወን ቆይቷል፡፡ ፈቃድ ያላቸውና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በገቡት ውል መሰረት የማይሠሩ ፤ በሕገ-ወጥ ድርጊት ተሰማርተው በመገኘታቸው ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው እንዲሁም ምንም አይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው በስፖርት አወራራጅነት ተሰማርተው የነበሩ አካላት በዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ትስስር አማካይነት በሕገ-ወጥ ድርጊት ተሰማርተው የተገኙ ሲሆን፤ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታ አካላት እንዲሁም በኅብረተሰቡ ትብብር አማካኝነት 24 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አስታውቋል፡፡ በተለይ በሕጋዊነት ሽፋን ፈቃድ ያወጡት ድርጅቶች ላይ ክትትል ለማድረግ ሙከራ በተደረገበት ወቅት ሁሉም ፈቃድ ሲያወጡ ይዘውት ከነበረው ቢሮ መልቀቃቸውና አድራሻቸውን መሰወራቸው ተረጋግጧል፡፡ የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር ተብለው ከሚጠሩ የፋይናንስ ስርዓቶችን ከሚያሳልጡላቸው የሀገር ውስጥ የክፍያ ስርዓት አቅራቢ ተቋማት ጋር በመመሳጠር በአጠቃላይ ሲያንቀሳቅሱት ከነበረው የገንዘብ መጠን መንግሥት በተለያዩ የገቢ አማራጮች ማግኘት የነበረበትን 100 ቢልዮን ብር በላይ መሰወራቸው እንደተደረሰበት አመልክቷል፡፡   የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ በተለያዩ የገንዘብ ክፍያ ስርዓቶች አማካይነት የሚሰበስቡትንና የሚያዘዋውሩትን የገንዘብ መጠን ያማከለ ግብር አለመክፈላቸው እንደተደረሰበት የጠቆመው መግለጫው፤ በክሪፕቶከረንሲ እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሃዋላ ገንዘብ ማስተላላፊያ አማራጮች አማካኝነት የሚያገኙትን ገቢ በውጭ ምንዛሪ በመቀየር ሲሰውሩና ከሀገር እንዲወጣ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውቋል፡፡ ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር የሚባሉት የሀገር ውስጥ የገንዘብ ክፍያ ስርዓት አቅራቢ ተቋማቱ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በመውሰድ የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም፤ የደንበኛን ምስጢር መጠበቅ የሚል ሙያዊ አሠራርን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች የሚያንቀሳቅሱትን የገንዘብ መጠን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አስፈፃሚ ተቋማት በመደበቅ ወይም አሳንሶ በማቅረብ በግብር ስወራ እንዲሁም ከፍተኛ የሀገር ሀብትን ወደ ውጭ በማሸሽ ወንጀል ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መግለጫ አመልክቷል፡፡ የተለያዩ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ግለሠቦች ጭምር ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው ሀገር ውስጥ ለሚገኙ ተባባሪዎቻችው ውክልና በመስጠት ሕገ-ወጥ ድርጊቱን ሲፈጸሙ መቆየታቸው እንዲሁም ውጭ ሀገር የበለጸጉ ሶፍትዌሮች ጥቅም ላይ መዋላቸውና ድርጅቶቹ ቋሚ አድራሻ የሌላቸው መሆኑ ወንጀሉን ውስብስብና ለቁጥጥር አስቸጋሪ አድርጎት ቢቆይም የደኅንነት ተቋሙ ከሌሎች የመረጃና የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ባደረጉት ስምሪት ተጠርጣሪዎቹ መያዛቸው ተመላክቷል፡፡ በሕገ ወጥ ድርጊቱ ከሀገር ሲሸሽ የነበረው ከፍተኛ ገንዘብ ሽብርተኝነትንና ጸረ ሰላም ቡድኖችን በገንዘብ ለመደገፍ፤ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ለማስመሰል እንዲሁም ለኮንትሮባንድ ንግድ ማካሄጃ እንደሚውል የጠቆመው መግለጫው፤ ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በመጻረር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ስጋት ላይ ለመጣል የሚደረግ እንቅስቃሴ አካል በመሆኑ ዜጎች ማንኛውም አይነት ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች ሲመለከቱ ለደኅንነትና ጸጥታ አካላት የሚሰጡትን ጥቆማ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ የላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል 
Nov 27, 2025 63
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ምጣኔ ባለባቸው አካባቢዎች ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ያለው የወባ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ። የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚያካሂደው አራተኛው ዙር የወባ ጠቋሚ ጥናት ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በቢሾፍቱ ተካሂዷል።   የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት የበሽታ መከላከልን መሰረት ባደረገ ስራ የኤች አይ ቪ፣ ወባና ቲቢ በሽታ የስርጭት ምጣኔ ላይ መቀነስ ታይቷል። ሆኖም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች በአንዳንድ አካባቢዎች የወባ ምጣኔ ከፍ ማለቱን ተከትሎ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል። የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ፣ የአልጋ አጎበር ስርጭትና የፀረ-ወባ ኬሚካል ርጭት ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ገልፀዋል። በዚህም የወባ ስርጭት ምጣኔ አምና ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር በ40 በመቶ መቀነስ ችሏል ነው ያሉት። የወባ ከፍተኛ ምጣኔ ባለባቸው አካባቢዎች ትኩረት ተደርጎ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የወባ ጠቋሚ ጥናት በሁሉም ክልሎች እንደሚካሄድ ተናግረዋል። ጥናቱ እስካሁን የወባ በሽታን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ውጤታማነት የሚገመግምና ለቀጣይ ዓመታት የሚሰራባቸውን ስትራቴጂዎችና የመንግስት እቅድ የሚያመላክት የመረጃ ምንጭ እንደሚሆን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም የምርምር ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።   አራተኛው ዙር የወባ ጠቋሚ ጥናት ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራት ጥንካሬና ድክመትን ለመለየትና ቀጣይ አቅጣጫን ለማሳየት የሚረዳ መሆኑንም ገልፀዋል። የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ዶክተር አዱኛ ወዬሳ በበኩላቸው ጥናቱ ቤት ለቤት የሚካሄድና በ268 መረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎች የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።   ከ14ሺህ በላይ አባወራዎችና እማወራዎች የሚሳተፉበት ጥናቱ ዓለም አቀፋዊ መስፈርቶችን የተከተለ መሆኑንም አስረድተዋል።
 ህብረ ብሄራዊ አንድነትን  ለመገንባት የሕዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስር ማጠናከር ላይ ትኩረት ተደርጓል 
Nov 27, 2025 64
ሚዛን ፤ ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ ብዝሀነትን ለማጎልበትና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለመገንባት የሕዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር ማጠናከር ላይ ትኩረት መደረጉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አስታወቀ። "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በክልል ደረጃ ሚዛን አማን ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።   በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ጌታቸው ኬኒ እንዳሉት፤ በሕዝቦች መካከል መቀራረብን ለማጠናከር የቀኑ መከበር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው። ብዝሀነትን ለማጎልበትና ህብረ ብሄራዊነት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጽናት የህዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስር ማጠናከር ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።   ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንን በአግባቡ መጠቀምና ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ድሎችን በጋራ በመከወን እንደሃገር የተያዘውን የብልጽግና ጉዞ ማሳካት ይገባል ብለዋል፡፡ የክልሉ ብሔረሰቦች ባህል፣ ቋንቋና ወግ እንዲለማ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል። የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው፤ አንድነት ኃይል መሆኑን ተገንዘብን በኅብረት መቻልን በተለያዩ ፕሮጀክቶች እያሳየን ነው፣ ወደ ፊትም እንቀጥላለን ብለዋል።   በዞኑ የሕዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር በአብሮነትና መቻቻል እሴት ላይ ተመሥርቶ በሁሉም የልማት ዘርፎች በአንድነት በመቆም ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ጉጣ ብዙአየሁ፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዘቦች ቀን መከበር የተለያዩ ባህሎችን ወደ አደባባይ በማውጣት የኢትዮጵያን ቱባ ባህል ለዓለም እንዲታይ አስችሏል ብለዋል፡፡   ወይዘሮ ደብሪቱ ኃይሉ በበኩላቸው፤ የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት አብሮነታችንን እናጠናክራለን ብለዋል ።   ልዩነቶችን ውበት በማድረግና መቀራረብን በማጠናከር አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ እናተኩራለን ሲሉም አክለዋል ። የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ፍትኃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ነው ያሉት ደግሞ ከጋምቤላ ክልል በመድረኩ የተገኙት ተሳታፊ አቶ ጆንማያንግ ኩን ናቸው።   በዓሉ የመተዋወቅ ዕድልን በመፍጠር ወንድማማችነትን የሚያጎለብት ስለሆነ በጋራ ቀኑን የማክበሩ ልምድ ዳብሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከርና ለሀገር ግንባታ የሚተጋ ትውልድ የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
Nov 27, 2025 47
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከርና ለሀገር ግንባታ የሚተጋ ትውልድ የማፍራት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር) ገለጹ። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ 20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት ከበዓሉ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይትና የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር አካሂዷል። በተማሪዎች መካከል በተካሄደው የጥያቄና መልስ ውድድር አሸናፊ የሆኑ ተማሪዎች የአጋዥ መጽሐፍት፣ የታብሌትና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር)፥ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያውያንን አብሮ የመኖር እሴት የሚያጎለበት መሆኑን ተናግረዋል። ይህ የአብሮ መኖር ህብረ ብሔራዊ እሴት ከትውልድ ወደ ትውልድ በአግባቡ እንዲተላለፍ የትምህርት ተቋማት ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል። ሀገርን የሚገነባ ትውልድ ማፍራት ላይ አበክሮ መስራት ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት። ለዚህም ከመደበኛው ትምህርት ባለፈ በልዩ ልዩ መንገዶች ተማሪዎች ስለ ኢፌዲሪ ህገ መንግስት የተሻለ ግንዛቤ የሚያገኙበትን መድረክ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል። ህብረ ብሔራዊ አንድነትንና አብሮነትን የሚያጠናክሩ እንደ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አይነት ሁነቶች ላይ ትውልዱን ማሳተፍ የኢትዮጵያን ብዝኃነትና የአብሮነት እሴቶች የተገነዘበ ሀገር ወዳድ ዜጋ ማፍራት ያስችላል ብለዋል።   የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ፋይዛ መሃመድ በበኩላቸው፥ 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያውያን የሀገር ፍቅር ስሜትና ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የምናጸባርቅበት ነው ሲሉ ገልጸዋል። ትውልዱ ስለ ሀገሪቱ ህገ መንግስታዊ ስርዓት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ምቹ አጋጣሚ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አንስተዋል። የትምህርት ማህበረሰቡ ቀኑን በተለያዩ ሁነቶች ማክበሩ ስለብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ስለብዝኃነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ጠንካራ ግንዛቤ ያለው ትውልድ መገንባት የሚያስችል በመሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።   በመድረኩ የተሳተፉት የክሩዝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዓለም ባንክ ቅርንጫፍ ርዕሰ መምህር ሱራፌል ዐቢይ፥ ተማሪዎች ከህገ መንግስት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች እንዲሁም ሀገራችን ያላትን ባህልና ወግ እንዲገነዘቡ ከመደበኛው ትምህርት ባለፈ በክበባት አማካኝነት የማስረፅ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።   የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር ማድረጋቸው የተሻለ ግንዛቤ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ሊጠናከሩ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የአየር አምባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ከበደ አሰፋ ናቸው።   በተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር አንደኛ የወጣችው የክሩዝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳራ አህመዲን በውድድሩ አንደኛ በመውጣቷ መደሰቷ ገልጻ፥ ስለ ሀገሯ ህብረ ብሔራዊነት፣ ስለ ዴሞክራሲ ስርዓትና ስለ ህገመንግስቱ እውቀት መቅሰሟን ተናግራለች። በውድድሩ ሁለተኛ የወጣችው የእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪዋ ሰሚራ ንጋቱ በበኩሏ፥ በውድድሩ ህገመንግስቱንና የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘቷን ገልጻለች።
 በኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ
Nov 27, 2025 60
አዶላ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ በህብረተሰብ ተሳትፎ የታገዘ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ማሳደጊያ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡   የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ግርማ ሮቤ እንዳሉት በትምህርት ለሁሉም ኢንሸቴቭ የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላትና የህብረተሰብ ተሳትፎን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። ለአብነትም ባለፈው አመት ግንባታቸው የተጀመሩ 14 ትምህርት ቤቶች ተጠናቀው ስራ መጀመራቸውን አንስተዋል። ግንባታቸው ተጠናቆ የመማር ማስተማር ስራን ከጀመሩ መካከል ሶስቱ መደበኛ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። ትምህርት ቤቶቹ የመምህራን፣ የአስተዳደር ጽህፈት ቤቶችና የስፖርት ማዘውተሪያንም ያካተቱ መሆናቸውን አክለዋል፡፡ የትምህርት ቤቶቹ መገንባት 3 ሺህ 500 አዳዲስ ተጨማሪ ተማሪዎችን ለመቀበል ከማገዛቸው ባለፈ በክፍል ጥበት የሚፈጠረውን የመማር ማስተማር እንከን እንደሚፈቱም አክለዋል። ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ህብረተሰቡ 75 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት፣ የጉልበትና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡ በወረዳው የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከአዳዲስ ግንባታዎቹ በተጨማሪ የ89 መማሪያ ክፍሎች እድሳት፣ 81 የመምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታ እንዲሁም የምድረ ግቢ ውበትና የአጥር ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡ ለትምህርት ጥራት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ፣ የውሃ፣ የመብራትና የመንገድ መሰረተ ልማት የማሟላት ስራም እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም በህብረተሰቡ ተሳትፎ የ25 የገጠር ትምህርት ቤቶች ደረጃ መሻሻሉንና መሰረተ ልማት መሟላቱን አስታውሰዋል። የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደ ክልል የተነደፈውን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን የማስፋት ስራንም እውን የማድረግ ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል፡፡ በሻኪሶ ወረዳ የበቴ ትምህርት ቤት መምህር ብርሃኑ ተሾመ እንዳሉት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ህብረተሰቡ የድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡ በተለይም በህዝብ ተሳትፎ እየተሰሩ ያሉ ትምህርት ቤቶችና የመምህራን መኖሪያዎች የመምህሩን የስራ ተነሳሽነት ማሳደጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል በእውቀት የበቁ ተማሪዎችን ለማፍራት የማይተካ ሚና በመኖሩ ወላጆች ከመንግስት ጋር በመተባበር እያካሄዱት ያለው ተግባር ምስጋና የሚቸረው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ መምህር ገመዳ ጉድሩ በበኩላቸው የመማሪያ ክፍል መሰራታቸው የተማሪዎችን መጨናነቅ በማቃለል ለበርካታ ህጻናት የመማር እድል እንዲያገኙ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎቸ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡  
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያግዛል
Nov 27, 2025 57
ጅግጅጋ፤ ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ድርሻ መጫወቱን የሱማሌ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አያን አብዲ ገለጹ። 20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ’’ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ሀሳብ በሱማሌ ክልል ደረጃ ጅግጅጋ ከተማ ተከብሯል።   የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ አያን አብዲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ለሀገር የልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በአንድነትና አብሮነት ላይ የተመሰረተ መግባባትን መመስረት አስገዳጅ ነው። ህብረ ብሄራዊነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባትና የጋራ እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል። የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ድርሻ ተጫውቷል ያሉት አፈጉባዔዋ፤ የዘንድሮውም በዓል ብዝሃነትን በሚገባ በሚያንፀባርቅ መልኩ እየተከበረ መሆኑን አንስተዋል። የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ብዝሃ ባህልና እምነት ያላት አገር በመሆኗ የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን በጋራ በማክበር ላይ እንገኛለን ብለዋል።   ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በሱማሌ ክልል የተገኘው ሠላም የክልሉ ህዝብ በሙሉ አቅሙ በልማቱ ላይ እንዲያተኩርና ከልማቱም ተጠቃሚ እየሆነ ነው ብለዋል። በበዓሉ የታደሙት ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሐመድ በበኩላቸው ፤ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የህዝቦች አንድነት የሚጠናከርበት፣ ባህልና ቋንቋቸውም ይበልጥ የሚንፀባረቅበት ቀን ነው ብለዋል።   ክልሉ በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት መግባቱን የተናገሩት ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሐመድ፤ በሀገር ደረጃ የተጀመሩ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችም የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ መሆናቸውን አንስተዋል። በመድረኩ በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሌን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። የደም ልገሳ፣ የችግኝ ተከላና ሌሎች መርሃግብሮችም የበዓሉ አካል ነበሩ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ75ኛ ዓመት በዓሉን ትናንት፣ ዛሬና ነገን በሚያሳዩ መርኃ ግብሮች ሊያከብር ነው
Nov 27, 2025 54
አዲስ አበባ፤ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ የምስረታ በዓሉን ያለፈበትን ታሪክ፣ አሁን ያለበትን ሁኔታ እንዲሁም የመጪ ዘመን ራዕዩን በሚያሳይ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሃና ደምሴ፣ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች ኔትወርክ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር መሳይ ገብረማርያምና የቴአትር መምህር ዘርይሁን ብርሃኑ የበዓሉን የአከባበር ዝግጅት በተመለከተ ማብራሪያ ስጥተዋል። የኮሙኒኬሽን አማካሪዋ ሃና ደምሴ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ለ75ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ዩኒቨርሲቲው ያለፈበትን ታሪክ፣ አሁን ያለበትን ሁኔታ እንዲሁም የመጪ ዘመን ራዕዩን የሚያሳዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል።   በዓሉ “ያለፈውን በማክበር የተሻለ ነገን ማለም” በሚል መሪ ሀሳብ በልዩ ልዩ መርኃ ግብሮች እንደሚከበርም ጠቁመዋል። ዝግጅቶቹ በዓሉን ከመዘከር ባሻገር ተማሪዎችን፣ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ እንዲሁም የቀድሞ የዩኒቨርሲቲውን ምሩቃንን የማገናኘት፣ የማስተዋወቅ እና የማወያየት ዕቅድን ያካተቱ ናቸው ብለዋል። የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እና አጋር አካላት ዩኒቨርሲቲው ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላ የት ደርሶ ማየት እንደሚፈልጉ መልካም ምኞታቸውን በፅሁፍ በአንድ መዝገብ የሚያኖሩበት ዝግጅት መኖሩንም ጠቅሰዋል። የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች ኔትወርክ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር መሳይ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ ከታህሳስ 18 እስከ 24/2018 ዓ.ም ባሉት ቀናት የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን እና ቤተሰቦች ወደ ዩኒቨርሲቲያቸው እንዲመጡ መጋበዛቸውን አስታውቀዋል።   ከመምህሮቻቸው ጋር እንዲገናኙ፣ የተማሩባቸውን ቦታዎች እንዲጎበኙና ዩኒቨርሲቲውን ማገዝ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ መታቀዱን ገልፀዋል። የዩኒቨርሲቲው የቴአትር መምህር ዘርይሁን ብርሃኑ፤ የዩኒቨርሲቲውን የ75 ዓመታት ጉዞና ውጣ ውረድ ሰንዶ የያዘ መፅሐፍ በዩኒቨርሲቲው እውቅ ምሁራን መጻፉንና በቅርቡ እንደሚመረቅ ተናግረዋል።   ዩኒቨርሲቲው እንደ አንድ የትምህርት እና ምርምር ተቋም ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያሳረፈውን አሻራ የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልም መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል። የ75ዓመት ልህቀት በ75 ሴኮንዶች የሚል የተማሪዎች የአጭር ፊልም ውድድር እንደሚካሄድም ነው የገለጹት።  
በከባድ የሙስና ወንጀል ምርመራ የተጣራባቸው አሥራ አንድ ተጠርጣሪዎች ክስ ተመሰረተባቸው
Nov 27, 2025 195
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ በከባድ የሙስና ወንጀል ምርመራ የተጣራባቸው አሥራ አንድ ተጠርጣሪዎች ክስ እንደተመሰረተባቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል። ክስ የተመሰረተባቸውም ‎1ኛ ተከሳሽ አቶ ክፍሌ ወ/ማርያም ጋዎ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበረ፤ ‎2ኛ ተከሳሽ አቶ ወልደአብ ደምሴ ክብረት በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ግብዓት ምርትና አቅርቦት ዐብይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበረ፣ ‎3ኛ ተከሳሽ አቶ ተንሳይ ሜጫ ወ/ስላሴ በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ሀብት አመራር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ኮሚቴ አባል የነበረ፤ ‎4ኛ ተከሳሽ ወ/ሪት መንበረ ኃ/ማርያም ነጋሳ በኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የኮርፖሬሽኑ የግዢ ኮሚቴ አባል የነበረች፤ ‎5ኛ ተከሳሽ አቶ ሚሊዮን ገረመው እሸቱ በኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የግዢ ባለሙያ እና የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ኮሚቴ አባልና ፀሀፊ የነበረ፤ ‎6ኛ ተከሳሽ አቶ ሰለሞን ገብሬ መላክ በኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ፣ የኮርፖሬሽኑ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ኮሚቴ አባል፣ የብሄራዊ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ኮሚቴ ፀሀፊ የነበረ፤ ‎7ኛ ተከሳሽ አቶ መንግስቱ ተስፋ ላቀ በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የግብዓት አቅርቦት መሪ ሥራ አስፈጻሚ፣ የብሄራዊ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ቴክኒካል ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበረ፤ ‎8ኛ ተከሳሽ አቶ ዘላለም ዳኜ ሮሪሳ በኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የግብዓት ግዢ እና ትራንዚት ክፍል ስራ አስኪያጅ የነበረ፤ ‎ ‎9ኛ ተከሳሽ ካፒቴን ወንድወሰን ካሳ አሰፋ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ የነበረ፣ ‎10ኛ ተከሳሽ አቶ ጸጋዬ በርሀ ኪዳኑ በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበረ፤ ‎11ኛ ተከሳሽ አቶ አለባቸው ሞልቶት ዳኜ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የጅቡቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የነበረ ‎በወንጀል ድርጊቱ ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ‎እነዚህ ተከሳሾች በጋራና በተናጠል የተሰጣቸውን ስልጣን ያለ አግባብ በመጠቀም የክልል መንግስታት ለኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የዓለም አቀፍ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ እንዲፈፅም የሰጡትን ውክልና እና የኮፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ውሳኔዎች፣ የግዢ መመሪያዎችን፣ ውሎችና ድንጋጌዎችን በመጣስ ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል። ተከሳሾቹ የተጋገረውን ማዳበሪያ ማስከስከሻ ወጪ 204 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ያለአግባብ በመክፈል፣ ከመቀሌ መርከብ ጊር ተነቀለ በማለት ኮርፖሬሽኑ 100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ የማጓጓዣ ወጪ እንዲያወጣ በማድረግ፤ ጥራት የሌለው ማዳበሪያ የተጓጓዘበት ወጪ 39 ሚሊየን 992 ሺህ 860 የአሜሪካን ዶላርን ጨምሮ በድምሩ 40 ሚሊየን 296 ሺህ 860 የአሜሪካን ዶላር ወይም 5 ቢሊየን 681 ሚሊየን 857 ሺህ 260 በመመዝበር በሕዝብና በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዋናነትም በወንጀል አድራጊነት እና ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከባድ የሙስና ወንጀል የምርመራ መዝገብ አጣርቶ በፍትሕ ሚኒስቴር ለዐቃቤ ህግ ከላከ በኋላ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ እንደተመሰረተባቸውም አስታውቋል። መንግስት በሰጠው አቅጣጫ እና በተደረገ ሰፊ ጥናት ‎በአጭር ጊዜ ውስጥ ወንጀሉን አጣርቶ ተከሳሾች ለሕግ እንዲቀርቡ ያደረገው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቀጣይም በከባድ የሙስና ወንጀሎች ላይ የጀመረውን ክትትልና ምርመራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የህዝቦችን አብሮነት እያጠናከረ ነው
Nov 27, 2025 85
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ባህልን ከማስተዋወቅ ባሻገር የህዝቦችን አብሮነት እያጠናከረ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ፋይዛ መሃመድ ገለጹ። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ 20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር እያካሄደ ይገኛል። ከጥያቄና መልስ ውድድር ባሻገር በዓሉን ምክንያት በማድረግ የፓናል ውይይት የሚካሄድ ይሆናል። የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ፋይዛ መሃመድ 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርኃ ግብሮች በመከበር ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ባህል ከማስተዋወቅ ባሻገር የህዝቦችን አብሮነት እያጠናከረ መሆኑን ገልጸው፤ ዜጎች በብሄራዊ ጉዳይ የጋራ ዓላማ እንዲኖራቸው አድርጓል ብለዋል። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የዘንድሮ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሀገራችን ግዙፍ ልማቶችን ማሳካት በቻለችበት ወቅት መከበሩ ልዩ ደስታ እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ ለአብነትም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አንስተዋል። በዓሉ የህዝቦችን ባህልና ወግ በማስተዋወቅ ለዲሞክራሲያዊ መግባባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል። በተለይ የትምህርት ማህበረሰቡ የተማረና ብቁ የሆነ ዜጋን ለማፍራት ሚናቸውን ማጠናከር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል። 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ ይከበራል፡፡
ኢትዮጵያ ፍትሕን በማስፈን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሕጎችን በማውጣት በቀጣናው የመሪነት ሚና አላት
Nov 26, 2025 120
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በምሥራቅ አፍሪካ ፍትሕን በማስፈን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ሕጎችን በማውጣት የመሪነት ሚና ያላት ሀገር መሆኗን የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ፕሬዝዳንት ረመዳን አቡበከር ገለጹ፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ከፍትሕ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ፈዴራል ጠበቆች ማህበር ጋር በመተባበር 30ኛ ዓመት የምሥረታና ዓመታዊ ጉባኤውን በመጪው ዓርብ በአፍሪካ ህብረት ያካሂዳል፡፡ በዚህ ጉባኤ የቀጣናውና የሌሎችም ሀገራት ተጋባዥ የህግ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ በስካይ ላይ ሆቴል እየተካሄደ ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ፕሬዝዳንት ረመዳን አቡበከር በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ጉባኤው የአፍሪካ ህብረትና የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ አባልነትን የተቀላቀለችው ባለፈው ዓመት እንደነበር አስታውሰው፤ በቀጣናው ፍትሕን በማስፈን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለፍትህና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ መሰረታዊ እና ሌሎች ሀገራት የሚማሩባቸው ህጎችን በማውጣት የመሪነት ሚና ያላት ሀገር ነች ብለዋል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ሀገራት ትብብራቸውን በማጠናከር ፍትሕን የማስፈን ግብ እንዳለው ገልጸው፤ በቀጣናው ጠንካራ የፍትሕ ተቋማትን መገንባት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ በቀጣናው የተለያዩ ክህሎት እውቀትና አቅም ያላቸው የህግ ባለሙያዎችና ማህበራት እንዳሉ በመጥቀስ፤ ሕጎችን ገቢራዊ ለማደረግ የመማማሪያ መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ተቋማት መገኛ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መስራች መሆኗን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተደረገው ሀገራዊ ሪፎርም የፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 መጽደቁን በማንሳት፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ከአምስቱ መሰረታዊ የፍትህ ተቋማት አንዱ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ አባል መሆን በቀጣናው ፍትሕን ለማስፈንና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚኖራትን ሚና ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ጉባኤ በሀገራት የሕግ ባለሙያዎችና ተቋማት መካከል የተሳለጠ የመረጃ ልውውጥ በመፍጠር ቀጣናዊ ትብብርን ያሳድጋል ብለዋል፡፡  
ረቂቅ አዋጁ የግብርና ዘርፉን ለማሸጋገርና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል
Nov 26, 2025 85
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንቲን ረቂቅ አዋጅ የግብርና ዘርፉን ለማሸጋገርና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ፋየዳ እንደሚኖረው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብና የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ አካሂዷል። በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃና ቁጥጥር ጉዳዮች አማካሪ ተክሉ ባይሳ፤ በዕፅዋትና እንስሳት ሃብት የሚከሰት ተባይና በሽታ ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖ አላቸው ብለዋል። በዕፅዋትና እንስሳት ላይ የሚደርሱ የተባይና በሽታዎችን ለመከላከልም የዕፅዋት ጥበቃና የእንስሳት ማቆያ ማዕከል ረቂቅ አዋጅ በርካታ ሂደቶችን አልፎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅ ስራ ላይ ሲውል በዕፅዋትና እንስሳት ሃብት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል። በዚህም ረቂቅ አዋጁ ዘመናዊ የተባይና በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በመረጃና ጥናት ላይ የተመሰረተ የምርታማነት ሥርዓት ለመፍጠር እንደሚያግዝ አስረድተዋል። የውይይቱ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላትም፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ የዕፅዋትና እንስሳት ደኅንነትና ቁጥጥር፣ የሕግ ተጠያቂነትና ዓለም አቀፍ የሰብል ጥበቃ መርሆችን መካተት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ(ዶ/ር)፤ ከዚህ ቀደም የዕፅዋትና እንስሳት ምርታማነትን ለማስጠበቅ ለ55 ዓመታት ያህል ያገለገለ ሕግ በስራ ላይ መኖሩን አስታውሰዋል። በዕፅዋት ጥበቃና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅ በምርምር የተደገፉ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም በሚያስችል መልኩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጭምር ተካተውበት መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በቀጣይም ባለድርሻ አካላት ለረቂቅ አዋጁ ግብዓት እንዲሆኑ ያቀረቧቸውን ምክረ ሃሳቦች ከከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ጋር ጭምር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል። የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን የግብርና መዋቅራዊ ሽግግር በማሳለጥ ምርታማነትን ለማስቀጠል በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅም በዕፅዋትና እንስሳት ላይ የሚያጋጥም ተባይና በሽታን በተሻለ አሰራር በመምራት የግብርና ምርት ጥራትና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል። በግብርናው መስክ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ወደ ውጭ የሚላክ ምርት በመጠንና በጥራት ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሊ ረቂቅ አዋጁ የዕጽዋት ጥበቃ እና ኳራንታይን ስራዎችን ለማጠናከርና ምርታማነትን ለማሻሻል ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል። የግብርና ዘርፉን ለማሸጋገርና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።  
ኢትዮጵያ በዘላቂ የእንስሳት ሃብት ልማት በአርዓያነት የሚወሰድ ውጤት እያስመዘገበች ነው -የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት
Nov 26, 2025 96
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዘላቂ የእንስሳት ሃብት ልማት በመገንባት ረገድ በአርዓያነት የሚወሰድ ውጤት እያስመዘገበች እንደምትገኝ የዓለም እንስሳት ጤና ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ባባ ሱማሬ ገለጹ። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ኑሮና ኢኮኖሚ በአብዛኛው ከእንስሳት ሃብት ልማት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የእንስሳት ሃብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በአርብቶ አደር አካባቢዎች እንስሳት ሃብት ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ በአረንጓዴ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ የተደገፈ የመቋቋም አቅም እየገነባች ትገኛለች። ለአብነትም በእንስሳት መኖና ውሃ ልማት፣ በዝርያ ማሻሻያና ጤና ጥበቃ፣ በማቆያና ገበያ ማዕከላት ግንባታ እንዲሁም በቅድመ ማስጠንቀቂያ የአየር ንብረት ተፅዕኖን የመቋቋም ሥርዓት እየዘረጋች ነው። የዓለም እንስሳት ጤና ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ባባ ሱማሬ ለኢዜአ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ በዘላቂ የእንስሳት ሃብት ልማት አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ነው። በእንስሳት ሃብት ጥበቃና ምርታማነት ላይ የተተገበሩ የአሰራር ሥርዓቶች የዘርፉን ውጤታማነት በማሻሻል የሚታይ ለውጥ ማስገኘታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት እንቅስቃሴና ልማት ላይ በትብብር ለመስራት ያላት ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም በግጦሽ መሬትና በውሃ ሃብቶች ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት ይገባል ብለዋል። በቀጣይም በእንስሳትና በሰው ጤና እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት መርህን በመከተል ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት ልማት ላይ የወሰደችው የፖሊሲ ማሻሻያ ለሌሎች ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡ ማሻሻያዎቹ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመቀነስ የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል። የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በእንስሳት ሃብት ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የማርበርግ ቫይረስን በአጭር ጊዜ ውስጥ መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
Nov 26, 2025 171
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ የማርበርግ ቫይረስን በአጭር ጊዜ ውስጥ መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ። የማርበርግ ቫይረስን ወቅታዊ ሁኔታና እየተሰሩ ያሉ የመከላከል ስራዎችን በተመለከተ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ መግለጫ ሰጥተዋል።   በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እንዳሉት የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከሰቱ ከተገለፀበት ጊዜ አንስቶ የክትትል ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ቫይረሱን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር የሚያስችሉ የልየታ፣ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በባለሙያዎች የተደራጀ የምላሽ ሰጪ ቡድን የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልፀዋል። እስከዛሬ ጠዋት ባለው ሰባ ሶስት ሰዎች ምርመራ ተደርጎ አስራ አንድ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡንና የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን አስረድተዋል። ከታማሚዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሶስት መቶ አርባ ዘጠኝ ሰዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀው አንድ መቶ አስራ ዘጠኝ ሰዎች የክትትል ጊዜ ገደብ ጨርሰው ከልየታ ማቆያ መውጣታቸውን ተናግረዋል። በተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የላቦራቶሪ ምርመራዎችን ለማጠናከር በስፋት እንደሚሰራም ነው የገለፁት። በሽታው ተከስቶባቸው ከነበሩ ሀገራት ጋር ልምድ ልውውጥ በማድረግ ተጋላጭነትን የሚቀንሱና ለህክምና የሚሆኑ አስፈላጊ መድኃኒቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ተደራሽ መደረጉንም አብራርተዋል።   የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፤ የማርበርግ ቫይረስን የመከላከል፣ ቅኝት፣ ምላሽና ህብረተሰቡን የማስገንዘብ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቤት ለቤት ቅኝት እየተካሄደ መሆኑንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ተግባራት ተከናውነዋል
Nov 26, 2025 87
አዳማ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በሩብ ዓመቱ የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ የማጎልበት ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ የማጎልበት ተግባራት ተከናውነዋል። በተለይም የሴቶችን መንግስታዊ የስራ ኃላፊነት በማሳደግ ለሀገር ልማት የሚተጉበትን እድል ለማስፋት መሰራቱን አክለዋል። የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማጉላት ያለሙ ስልጠናዎችን በመስጠት በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ በመምረጥም ሆነ በመመረጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከወዲሁ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል። የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም በሩብ ዓመቱ ሦስት ሺህ ሴቶች በከተማና ገጠር ግብርና እንዲሰማሩ በማድረግ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ከዚህ ባለፈም በቦረና ዞን ያቤሎ ከተማና በምእራብ ሸዋ ኤጀሬ ወረዳ አነስተኛ ገቢ ያላቸው እናቶችን በእንስሳት ማድለብና በወተት ላሞች እርባታ ስራ ላይ እንዲሰማሩ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል። በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ሴቶች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል። የሴቶችን መብትና ደህንነት ለማረጋገጥም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መሰራቱን አንስተዋል። የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን የጥቃት አድራሾችን ጥቆማ ለመቀበል 919 ነጻ የስልክ መስመር መዘርጋቱን አንስተዋል። በጥቃት አድራሾች ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን ከፖሊስና ከፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። የሴቶችን ጥቃት የማይቀበል ማህበረሰብን ለማፍራትና የ''ነጭ ሪቫን'' ቀንን በማስመልከት የአንድ ወር ንቅናቄ እንደሚካሄድም ተናግረዋል። ይህም ለጥቃት የተጋለጡ ወገኖች የስነ ልቦናና የህግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲያገኙ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም አክለዋል።
በሽሬ እንዳስላሴና አካባቢው የኃይል መቆራረጥን ማስቀረት የሚያስችል የትራንስፎርመሮች ተከላ ተከናወነ
Nov 26, 2025 74
ሽሬ እንዳስላሴ ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል ሽሬ እንዳስላሴና አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ማስቀረት የሚያስችል የትራንስፎርመሮች ተከላ እና የኃይል ተሸካሚ መስመሮች ዝርጋታ ማከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሽሬ ሪጅን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ኪዳኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሽሬ እና አካባቢው የኃይል መቆራረጥን ለማስቀረት የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል።   በሪጅኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋትና የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት ከ984 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ መከናወናቸውን ተናግረዋል። በሪጅኑ በሚገኙ ሽሬ እንዳስላሴ፣ በአክሱም፣ በአድዋ እና በሌሎች ስምንት ከተሞች የኃይል መቆራረጥን ለማስቀረት የሚያስችሉ አዳዲስ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች፣ የትራንስፎርመር ተከላና ያረጁ የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት የመተካት ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። በዚህም የ108 ኪሎ ሜትር መካከለኛና ዝቅተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመር ዝርጋታ፣ የ119 ትራንስፎርመሮች ተከላና የ55 ኪሎ ሜትር የእንጨት ምሰሶዎች በኮንክሪት የመተካት ሰራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።   እንዲሁም የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ለማዘመንም ጊዜ ቆጣቢ የተለያዩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ መፈፀሚያ አማራጮች በሪጅኑ ስር በሚገኙ 15 የአገልግሎት መስጫ ማእከላት መዘርጋቱንም ተናግረዋል። ሪጅኑ በተያዘው የበጀት ዓመት የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካትና አገልግሎቱን ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።   ከሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ በላይ ኃይሉ እና አቶ ጌታቸው ካህሳይ፤ አገልግሎቱ የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋትና ዘመናዊና ቀልጣፋ አሰራርን ለመዘርጋት የጀመረው ስራ የሚደነቅ ነው ብለዋል።   የቆዩ ምሰሶዎችን የተሻለ ደረጃ ባላቸው የመቀየር እንዲሁም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች በአዲስ መልክ መቀየራቸው የኃይል መቆራረጥን የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል።
በጤና መድህን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እያገኘን ነው-ተጠቃሚዎች       
Nov 26, 2025 141
ሮቤ ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦ የጤና መድህን አገልግሎት ጤናችንን ለመጠበቅና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንድናገኝ አግዞናል ሲሉ በባሌ ዞን የዲንሾ ወረዳ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ ። በወረዳው የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑ አባላት መካከል ወይዘሮ ሙኒራ ኡስማን እንዳሉት አንድ ጊዜ በከፈሉት አነስተኛ ገንዘብ የህክምና አገልግሎትን በማግኘት የቤተሰባቸውን ጤና መጠበቅ ችለዋል።   የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች በመርሃ ግብሩ እንዲታቀፉ በፈጠሩላቸው ግንዛቤ በአባልነት ተመዝግበው ያለ ስጋት የህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል። አስቀድመው በከፈሉት የአባልነት መዋጮ ዓመቱን ሙሉ ሳይጉላሉ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ በመርሐ ግብሩ የታቀፉት የወረዳው ነዋሪ አቶ ሱሌይማን አብዱረህማን ናቸው።   በማሳያነትም ባለቤታቸውንና ልጃቸውን ለማሳካም የተጠየቁትን ከፍተኛ ወጪ አገልግሎቱ በመሸፈኑ ከስጋትና እንግልት እንደታደጋቸው ገልጸዋል። የዲንሾ ወረዳ ጤና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ወርቁ እንደገለፁት፤ የህብረተሰብ ተሳትፎና ግንዛቤን በማሳደግ ከወረዳው 10 ሺህ አባወራዎች መካከል ከ9 ሺህ በላይ የሚሆኑትን የማህበረሰብ የጤና መድህን አባል ማድረግ ተችሏል።   የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባላትን የመረጃ አያያዝን ዲጂታላይዝ በማድረግም ተጠቃሚዎቹ ሳይጉላሉ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን አስረድተዋል። ይህም ወረዳው በጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ሞዴል ሆኖ እንዲመረጥ ማድረጉን አክለዋል። የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ዘገየ ዘውዴ በበኩላቸው፤ በዞኑ 10 ወረዳዎች ውስጥ በ2017 የበጀት ዓመት ከ763 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።   ዞኑ ከጤና መድህን አገልግሎት አባላቱ የሚሰበስበውን ገንዘብ በአንድ ቋት በማድረግ ተገልጋዩ የተሻለ ህክምና እንዲያገኝ ማድረጉን ተናግረዋል። በኦሮሚያ ክልል ከ30 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች በጤና መድህን ስርዓት መታቀፋቸውን ከክልሉ ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር የክስተት አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት እየተሰራ ነው - ኢንስቲትዩቱ
Nov 25, 2025 253
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2018(ኢዜአ)፦ የማርበርግ ቫይረስን በራስ አቅም መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል ሀገር አቀፍ ግብረ ኃይል በማቋቋምና የክስተት አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የማርበርግ ቫይረስ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሀገራት የተከሰተ መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጂንካ ከተማ የተከሰተው የማርበርግ ቫይረስ ከታማሚ ሰው ከሚወጣ ፈሳሽ ጋር በሚኖር ቀጥታ ንክኪ የሚተላለፍ መሆኑንም አንስተዋል። በቫይረሱ የተያዘ ሰው ምልክቶች ትኩሳት፣ የሰውነት መቆረጣጠም፣ ደም መፍሰስ መሆናቸውን ጠቁመው፤ መሰል ምልክቶች የታዩበት ሰው ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደሚገባው አስገንዝበዋል። ቫይረሱ መከሰቱን ተከትሎ በጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የሚመራ ሀገር አቀፍ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጸው፤ ግብረ ኃይሉ በየቀኑ በሽታው ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ግምገማ እያካሄደ እንደሚገኝ አብራርተዋል። በተጨማሪም ሀገር አቀፍ የክስተት አስተዳደር ሥርዓት ተዘርግቶ የቅንጅትና የማስተባበር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ የማከም፣ ቅኝትና ልየታ የማድረግ ስራ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ምርመራ የሚደረግበት ተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪ ወደ ጂንካ ተልኮ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለህክምና የሚያስፈልጉ የሎጂስቲክስ አቅርቦት ተደራሽ መደረጉንም ገልፀዋል። በሽታውን ለመከላከል ከትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል። ኮቪድ-19 በተከሰተበት ወቅት ዝግጅት ላይ መስራት ከምላሽ ስራ ይልቅ ውጤታማ እንደሚያደርግ ግንዛቤ በመወሰዱና ልምድ በመቀሰሙ የሰው ኃይል ስልጠና፣ የህክምና ተቋማትን የማስፋፋትና አቅማቸውን የማሳደግ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል። ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተከታታይነት ያለው መረጃን በመስጠት የተግባቦት ስራን ለማጠናከር እንደሚከናወን ጠቁመዋል። ማህበረሰቡ ከሚመለከታቸው አካላት ብቻ የሚወጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበር በሽታውን መከላከል እንዳለበት ገልፀዋል። ጥያቄ ያላው ሰው በነፃ የስልክ መስመር 8335 አሊያም 952 በመደወል በማንኛውም ሰዓት አስፈላጊውን መረጃ ማግኘት እንደሚችልም ነው የጠቆሙት። እስከትናንት ባለው መረጃ አስር ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም መካከል አምስቱ በጤና ተቋም ህክምና እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት በጋራ መስራት ያስፈልጋል
Nov 25, 2025 183
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 16/2018(ኢዜአ)፦ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት አዲስ ከተካተቱ ተቋማት መሪዎችና ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ጋር በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ ላይ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ማህበራት እና የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ጥምረት ምክር ቤት እንዲሁም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ አመራር አባላት ተሳትፈዋል። ከዚህ በፊት ከነበሩ አባላት በተጨማሪ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መንግስታዊ ያልሆኑ ማህበራት አመራር አባላት በምክር ቤቱ እንዲካተቱ ተደርጓል። የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል። የአይበገሬነት አስተሳሰብ በመገንባት ከተረጂነት አመለካከት ለመላቀቅና በራስ አቅም ለመደጋገፍ በተለይ የምክር ቤቱ አባላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል። በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚከሰቱ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት በራስ አቅም ለአደጋ ምላሽ የመስጠት አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል። የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጉዳይ ከብሔራዊ ደህንነት አጀንዳ፣ ከማህበራዊ ዋስትና፣ ከዘላቂ ልማትና ሰላም ማስፈን ጋር የተያያዘ መሆኑን አስታውቀዋል። በመድረኩ በኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲና አዋጅ፣ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፍን የተቋማት ተሳትፎና ሚናቸውን እንዲወጡ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል። በውይይቱ የተሳተፉ የምክር ቤቱ አባላት እንደገለጹት፤ በራስ አቅም የሚከናወን የሰብዓዊ እርዳታ ምላሽ አሰጣጥ ለሉዓላዊነት መከበር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።   የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሓፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት፤ በሃይማኖት ተቋማት በተናጠል የሚደረጉ እርዳታዎች በቅንጅት ስራ ላይ ቢውሉ ለሰብዓዊ ምላሽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው። ኮሚሽኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ላይ ማሳተፉ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሓፊ አበራ ሉሌሳ በበኩላቸው፤ ማህበሩ ኮሚሽኑ የያዛቸው እቅዶች እንዲሳኩ ባሉት መዋቅሮች በመታገዝ ትብብሩን እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።   መንግስት ጠባቂነትን በማስቀረት ለአደጋ ስጋት በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የያዘው አቋም ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰብዓዊ ድጋፍ ሲቪል ማህበረሰብ ፎረም ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲሳይ ደረጀ በበኩላቸው፤ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማቀናጀት ለአደጋ ስጋት በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።   ፎረሙ ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግና በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ላይ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም