መጣጥፍ
በአንድነት የመምከር ብሩህ ተስፋ! 
May 13, 2024 350
በአንድነት የመምከር ብሩህ ተስፋ! በቀደሰ ተክሌ (ከሚዛን አማን) ሀሳብ ያፋቅራል፤ ሀሳብ ያቃርናል። በማንኛውም ጊዜ የሚነሳ ሀሳብ በውይይት ዳብሮ በሰዎች የሕይወት ኡደት ውስጥ መግባባት፣ መተማመን እና መስማማት የሚሉ መሠረታውያንን ሲያስከትል ሰዎችን ልብ ለልብ በማገናኘት አንድ የማድረግ ኃይሉ ከፍያለ ይሆናል። ያን ጊዜ ሰላምና ፍቅር በአብሮነት ታጅቦ በጋራ ማንነት ይደምቃል። በተቃራኒው ሀሳብ በልዩነት የተወጠረ ከሆነ በጊዜ ሂደት እየከረረ ወዳጅነትን የመበጠስ አቅም ያገኛል። ይህ እንዳይሆን ሀሳቦችን በውይይት ማቀራረብ የመጀመሪያ ጉዳይ የመጨረሻም መፍትሄ ነው። ሰው እንደመልኩ አስተሳሰቡና ግንዛቤው ቢለያይም ዙሮ አንድ የሚሆንበት ሰብዓዊ ፀጋ ተችሮታል። ይህም ከራስ በተጨማሪ የሌሎችንም ሀሳብ አዳምጦ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ የሚያስችል ማስተዋል ነው። ማስተዋል ደግሞ ግራ ቀኝን የመቃኘትና የመመዘን ጥበብ ሲሆን፤ የሌሎችን ሀሳብ ከእውነታ ጋር ለማጤን ይረዳል። መነጋገር በብዝኃ አስተሳሰብ እና ማንነት ውስጥ የመከባበር እሴትን በማጉላት በሕዝቦች መካከል አንድነትንና መቀራረብን ይፈጥራል። ፍቅር ሰብኮ፣ ሰላም ዘርቶ አብሮነትን ለማጨድ የሚያስችል ከጥንትም በማህበረሰቡ ወስጥ ያለው ጥበብ ውይይት ነው። ማህፀነ ለምለሟ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ከብዝሃ ባህልና እምነት ጋር አቅፋ ይዛለች። ብዝኃነት ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊነት ስሟን በአብሮነት የመኖር ተምሳሌት የሚያስጠራ ነው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሚያዘጋጀው ምቹ ሁኔታ ኢትዮጵያዊያን በችግሮቻቸው ላይ በጋራ ሊመክሩ ነው። በምክክሩም "የኢትዮጵያዊነት ቀለም፣ የአብሮነት መንፈስ፣ የመከባበር እና የሰላም እሴት አብቦ ፍሬው በምድሪቱ እንዲታይ ያደርጋል" የሚል ብሩህ ተስፋን ሰንቀዋል። ለችግሮቻቸው መፍቻ ቁልፍ ውይይት መሆኑን ስለተረዱትም ምክክሩን አጥብቀው ሽተዋል። በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት መምህር እንዳለ ንጉሴ እንደሚሉት፤ በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ችግሮች ሲፈጠሩ ለመፍትሄው አፈ ሙዝ እንጂ ጠረጴዛ አይታሰብም። ለችግሮች መፍትሄ በሀይል ይገኝ ይመስል ከሰላማዊ ውይይት ይልቅ ጉልበትን መርጠው ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ የገቡ አገራት ጥቂት አይደሉም። በዚህም ወደ መፍረስ አልያም ወደ መዳከምና አቅም አልባ የመሆን ደረጃ ላይ የደረሱ አገራት አሉ። ኢትዮጵያ ግን ከዚህ በመሻገር የውይይት ዐውድ በማዘጋጀት ልጆቿ በችግሮቻቸው ላይ በአንድነት እንዲመክሩ ተግታ እየሠራች ነው። ኢትዮጵያዊያንም በአንድነት ተወያይተው ከልዩነቶቻቸው ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸውን አጉልተው ለማውጣት ጫፍ ላይ ደርሰዋል። ሀገራዊ ምክክሩ ደግሞ በአንድ ሀገር ውስጥ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ በመንግስትና በሕዝብ መካከል መተማመንና ግልጽነትን ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንዳለው ነው መምህር ንጉሴ የገለጹት። እንደመምህሩ ገለጻ፤ ከውይይቱ እንደ ሀገር ፖሊሲ ሊቀረጽባቸው በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን በገብዓትነት ለመሰብሰብ ይቻላል። በምክክሩ በዋናነት የሰላምም ሆነ የግጭትን ውጤት የሚቀምሰውን ማኅበረሰብ ማሳተፍ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ልምድ እንዲዳብር ያደርጋል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በዚህ ረገድ አካታች መርህን መከተሉ በዜጎች ውስጥ ጥሩ ተስፋ እንዲፈጠር አድርጓል። የሕዝብን ፍላጎት አዳምጦ ምላሽ የሚሰጥ አካልን ፊት ለፊት አስቀምጦ ምክክር መደረጉ ከውይይት ማግስት አዎንታዊ ምላሽ ለማግኘት ያስችላል። በሁሉም ዘንድ ተቀባይነቱ ከፍ ያለ መንግስት የመፍጠር ዕድልን ከማስፋት ባለፈ ልዩነትን የሚያሰፉ ችግሮችን ከስር መሠረቱ የመንቀል አጋጣሚን እንደሚያመጣ ነው መምህር ንጉሴ የገለጹት። የምክክር ኮሚሽኑ ዜጎችን አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮችን በማንጸባረቅ የጋራ እሴት የመገንባት ኃላፊነት ተጥሎበታል። ይህ እውን በሚሆነበት ጊዜ የእኔነት ስሜት ተመናምኖ የእኛነት የሚለመልምበት አስተሳሰብ በዜጎች ውስጥ ይሰርጻል ተብሎም ይጠበቃል። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ዘላቂ ሰላም፣ አብሮነትና በጋራ ሀገር በአንድነት ተባብሮ መስራትና በፍቅር የመኖር እሴት እንዲለመልም ምክክሩ መሠረት ይጥላል። የኢትዮጵያውያን እሴትና የኮሚሽኑ ቅቡልነት! ኢትዮጵያውያን የሀሳብ ልዩነቶችን በምክክር መፍታት የሚያስችል ባህላዊ እሴት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው። ምንም እንኳ ከቦታ ቦታ ቢለያይም እያንዳንዱ ብሔረሰብ ግጭት የሚያስወግድበት ባህላዊ ሥነ ሥርዓት አለው። የአፈጻጸሙ ሂደት ጉራማይሌ ሊሆን ቢችልም እንኳ የሰላም ግንባታ ሂደት መሠረቱ ውይይት ነው። ይሁንና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልምዳችን በዘመናት ሽግግር ውስጥ የመደብዘዝ ዕድል ገጥሞታል። ይሁንና ከማኅበረሰቡ ማንነት ውስጥ ጨርሶ ስላልጠፋ ይህ በጎ እሴት አሁን እየታየ ላለው የሰላም እጦት ሁነኛና አስተማማኝ መፍትሄ ስለሚያመጣ ምክክሩ ተቀባይነት አግኝቶ በተስፋ ሊጠበቅ ችሏል። በሌላ በኩል የምክክር ኮሚሽኑ የሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ዜጎች ችግሮቻቸውን ተናግረው ሊደመጡ የሚችሉበት ሰፊ መድረክ በመሆኑ ከሕዝቡ ዘንድ አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል። መምህር እንዳለ እንደሚሉት፤ ውይይት ለሰላም ግንባታ ብቸኛ አማራጭ ሲሆን፤ መንግስትም የሕዝብን ሀሳብ ለመስማት ዕድል ያገኛል። በእዚህም የምክክር ኮሚሽኑ ተቀባይነት መጉላቱን ነው የገለጹት። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኢትዮጵያውያን በችግሮቻቸው ላይ መክረው ለመግባባት የሚያስችላቸው ነው። የውይይት መድረኩ አንዱ የሌላውን ችግር በመረዳት ሀገራዊ እይታውን የሚያሰፋበት መነጽር ይፈጥርለታል። ለመፍትሄ ከመነሳት በፊት ችግሮችን ማወቅ ይቀድማልና በምክክር ወቅት ኢትዮጵያ ምን መልክ እንዳላት ዋና ዋና ችግሮቿስ ምንድን ናቸው? የሚሉት በተወያዮች በኩል ይንጸባረቃሉ። የተወያዮች ኃላፊነት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ውጤታማነት በተወያዮች የሚወሰን ነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አደረጃጅቶች ሀሳቦቻችንን ያደርሱልናል ብለው የወከሏቸው ግለሰቦች አሉ። በመሆኑም እነዚህ የህብረተሰብ ተወካዮች ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ዋና ዋና ችግሮችን ለውይይት ይዞ ለመቅረብ ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ሀሳብ የሚያንጸባርቁት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሰቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አጥናፉ ምትኩ ከማህበረሰብ ተወካዮች በሳል ሀሳብ ይዞ መቅረብ እንደሚጠበቅ ይገልጻሉ። የግል ሀሳብን ሳይሆን የወከሏቸውን ህዝቦች ፍላጎትና አስተሳሰብ ማንጸባረቅ የተወያዮች ግዴታ ነው። በውይይት ወቅትም የራስን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ሀሳብ የማድመጥ ባህልን አጉልቶ ማንጸባረቅ ይጠበቃል። በሌላ በኩል ተወያዮች ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ የጋራ መፍትሄ የማፍለቅ ሃላፊነትም አለባቸው። የመቻቻል እና የመከባበር ልምድ በውይይት ወቅት ጎልቶ እንዲወጣ ከማድረግ ባለፈ ወደ ማኅበረሰቡ ማዛመትም አስፈላጊ ነው። ያለፈውን በማንሳትና በመቆስቆስ አንዱ ሌላውን የሚከስ ሳይሆን ቁስሉን ለማከም መፍትሄ የሚፈልግ ስብዕናን መላበስ ያስፈልጋል። በእዚህ መንፈስ ለውይይት ከቀረብን ለዘመናት ሳያግባቡን የቆዩ ችግሮችን ፈትቶ እንደ ሀገር ለመሻገር አቅም መፍጠር ይቻላል። የዜጎች ድርሻ ተስፋ የነገ ብርሃን ጮራ ነው፤ ነገን የመመልከት መነጽር። ተስፋ ስኬታማ የሚሆነው ደግሞ ዛሬ በሚሠራው ሥራ ነው። እንጀራ ተጋግሮ ከመበላቱ በፊት ጤፍ ተፈጭቶ መቦካት አለበት። እንጀራ የመብላት ተስፋ ጤፍ ከመዝራት ጀምሮ የማስፈጨትና የማቡካት ሂደትን ይጠይቃል። የምክክር ኮሚሽን ፍሬያማ ውጤት በቅድመ ዝግጅት ምዕራፉ የጠራ ግንዛቤ መያዝና ቀና አመለካከት መላበስን ይጠይቃል። ይሆናል፤ ይሳካል ብሎ አዎንታዊ እንቅስቃሴ ማድረግና ከአላስፈላጊ ትችት መራቅም እንዲሁ። መምህር አጥናፉ እንዳሉት የምክክር ኮሚሽኑ ዓላማ ግቡን እንዲመታ በተለይ የአገር ሽማግሌዎች አገር በቀል እውቀቶችን በማቀበል፤ ምሁራን የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመቀመር እና የምርምር ሥራዎችን በማቅረብ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። አካታችነቱን ተጠቅመው ሀሳብ ለማዋጣትና ለመደገፍ ለዜጎች የተሰጠ እድል በመሆኑ በአገባቡ በመጠቀም ተባብሮ እውን ማድረግ ይገባል። ኢትዮጵያ ብሩህ የአብሮነትና የሰላም ተስፋን በምክክር ኮሚሽኑ ላይ የመጣሏ ምሥጢር የቤት ገበናን በቤት ውስጥ መፍታት የሚችል ቁልፍ ይዞ ስለተነሳ ነው። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሀገር በቀል እውቀቶችን ተንተርሶ ከባዳ ዐይንና ጆሮ የራቀ ሁነኛ መፍትሄን እንካችሁ እያለ ነው። ዜጎችም ለመቀበል እጃቸውን ዘርግተው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ይሄን ደግሞ በየአካባቢው ለኮሚሽኑ እየተደረገ ያለው የህዝብ አቀባበልና ድጋፍ ያረጋግጣል። ኮሚሽኑ አሁን የቀረውን የቅድመ ውይይት ሂደት ጨርሶ ወደዋናው ምክክር ሲገባ ከአንደበት ይልቅ ለጆሮ ቦታ ሰጥቶ በሰከነ መንፈስ ውይይቱን የማስኬድ ኃላፊነት መሸከም ከሁሉም ይጠበቃል። ሰላም !!!
ከፈተናዎች ባሻገር . . . !
May 4, 2024 557
ከፈተናዎች ባሻገር . . . ! (በቀደሰ ተክሌ ከሚዛን አማን ኢዜአ) በዓለም ውስጥ ሆኖ በአንዳች ምክንያት የወደቀ ይነሳል፤ የታመመ ይድናል፤ የፈረሰ ይጠገናል፤ የደከመ ይበረታል፤ የተኛ ወይም ያንቀላፋም ይነቃል። ይህን እውነት ሰው በልቡ ተስፋ አድርጎ ውሎ ያድራል።ነገን ያልማል። "ሲጨልም ይነጋል" እያለ ለራሱ ይጽናናል። መከራ ሲበዛበት "ሊነጋ ሲል ይጨልማል" በሚል አዲስ ተስፋን በውስጡ ይዘራል። ከእነዚህ ተቃራኒ የሰው ልጅ ከህይወት ዑደት ኩነቶች ባሻገር በተለያዩ የእምነት ተቋማት አስተምህሮ ደግሞ የሞተ የሚነሳበት መንፈሳዊ ተስፋ አለ። ይህም ትንሣኤ ይባላል- ከሞት በኋላ የሚኖር ሕይወትን የሚያሳይም መነጽር። "ትንሣኤ" ማለት የግዕዝ ቃል ሲሆን፤ ቀጥተኛ ትርጉሙ መነሳት ነው። መነሳት የሚነገረው ለወደቀ፤ ለደከመ እና ለሞተ ነው። እንዲሁም ከነበረበት ከፍ ማለት ቀና ማለት መለወጥና ወደ አዲስ መልካም ነገር መሸጋገርን ያመለክታል። በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትንሣኤ የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሳትን መሠረት በማድረግ ነው። ክርስቶስ በምድር ሲመላለስ የሰው ልጆች ማድረግ ስለሚገባቸው በጎ ምግባራት እርሱ በመተግበር አስተምሯል። የበጎ ተግባራት ውጤት ደግሞ ከሞት በላይ ራስን ከፍ አድርጎ በሕይወት ዙፋን ላይ መቀመጥ እንደሆነ አሳይቷል። ፍቅር እንዲጎለብት ለሌላው መኖርና አልፎም መስዋዕት መሆንን በግልጽ አንጸባርቋል። እርሱ መልካም ነገር አድርጎ "እናንተ እንዲሁ አድርጉ" ብሏል። ለአብነትም ፍቅር በቀዳሚነት የሚጠቀስ ትምህርቱ ነው "እርስ በእርስ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት" ብሏል። ፍቅሩን ለሰው ልጆች ራሱን አሳልፎ በመስጠት ገልጧል። ነገ ምን እንዲያውም ከደቂቃዎችና ሰዓታት በኋላ ምን እንደሚፈጠር በማናውቀው ተገድቦና ተተምኖ በተሰጠን የህይወት ዑደት ውስጥ በምናልፋቸው የትኞቹም ጎዳናዎች ምህረትን፣ ይቅር ባይነትን ይጠየቃል። ለሰው ልጅ ለራሱም ቢሆን ቂምና ቁርሾ ያላደረበት ልብ ያስፈልገዋል። የወደደንን ወይም የሰበሰበንን ሳይሆን ተቃራኒውን የፈጸመብንን የመውደድና ፍቅርን በተግባር የማሳየት ልምምድ እንዲኖረን ያስተምራል። ይህም ከራሳችን ጀምሮ ለአካባቢያችን ሁሉ ሰላምና መረጋጋትን ይፈጥራል። ሌላው የተግባር ትምህርቱ ትህትና ነው። የሰው ልጆችን ለማክበር ራሱን ዝቅ አድርጓል። የደቀ መዛሙራቱን እግር ተንበርክኮ አጥቧል። "እናንተም እንዲሁ ለሌሎች አድርጉ" ሲልም አስተምሯል። የዚህ ዓይነቱ ተግባር ዛሬም በኢትዮጵያውያን እሴት ውስጥ ይስተዋላል። በትውፊት ከትውልድ ወደ ትውልድ በመተላለፉ መጥቷል። ቤታችን የወላጆቻችንን አልፎም የመጣን እንግዳ እግር ማጠብ የመልካም ሥነ ምግባር ምገለጫችን ሆኖ ቆይቷል። ይህ እርስ በርስ መከባበር እያጠነከረ ይመጣል፤ ውሎ ሲያድርም በስነ ምግባር የታነጸ የጠንካራ ማህበረሰብ መገለጫም ይሆናል። ትህትና ከአንገትን ጎንበስ ብሎ ሰላምታ መሰጣጣት ብቻ አይደለም። ሌሎች የተሻሉ እንዲሆኑ ማሰብን ያካተተ ከልብ የሚፈልቅ ተግባር ነው። በትዕቢት አውቃለሁ ባይነት ሳይሆን ራስን ዝቅ በማድረገ መንፈስ የተገዛ ማንነት ማዳበርን ይጠይቃል። ድርጊት የሀሳብ ውጤት ነው። ስለሆነም እርስ በርሳችን ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ እንዲሁም በስራ ቦታችን ካሉ ባልደረቦቻችንን ከልብ በመነጨ ትህትና መቀበልና ማስተናገድ አልፎም መታዘዝ ይጠበቅብናል። ይህ ነው የትህትና ጥቅ እሴቱ። በጎነት፣ ፍቅር፣ ትህትና፣ ለጋስነትና ቅንነትን የሰው ልጅ ገንዘቡ ቢያደርግ ሞትን አሸንፎ ይከብራል። ከመውደቅ ባሻገር መነሳት አለ። ከጨለማ በኋላ ብርሃን ይኖራል። ይህም ከጽልመትና ከአስቸጋሪ ነገሮች አልፈን ብርሃን ማየት እንደሚቻል የጸና ተስፋ በመያዝ ነጋችንን ማየት ይኖርብናል። ትንሣኤ ደስታ ነው፥ ከድቅ ድቅ ጨለማ በኋላ የሚገኝ ልዩ ብርሃን፤ ከመቃብር በላይ የሚገኝ ሐሴት ነው። የትላንት መከራ ላይ የታነጸ ጽኑዕ ደስታ፤ የትላንት መልካም ነገርን መነሻ አድርጎ የሚገኝ ክብር ነው። የሰው ልጅ በፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ነገን ተስፋ አድርጎ ጠንክሮ መስራት ከቻለ መልካም ነገር ሁሉ ማግኘት ይችላል። ዛሬም ዓለም ብዙ ውጣ ውረዶችን ታስተናግዳለች። እንደ አገር ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች እያጋጠሟት ነው። ችግሮቹና መከራው ማብዛቱ የነገን ትንሣኤ ለማምጣት ነው። ከፈተናዎች ባሻገር ድል አለ፤ ትንሣኤ ይገለጻል። ለዚህም ነው ምንም ፈታኝ ነገር ቢኖር፣ ችግሮች ቢደራረቡም ተግቶ ሰርቶ ወደ ብርሃኑ መውጣት ይቻላል የምን ለው። የትንሣኤ በዓል ከበዓል ባሻገር በበጎ እይታ በመቃኘት፣ በፍቅር በመታነጽና የቅንነት ጎዳናን በመያዝ ለአገር እና ለራሳችን ክብርን ለመጎናጸፍ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት መሆን አለበት።      
በድላችን ሐውልት ክላሽንኮቭ መሳሪያ ይዘው ሐውልት የተቀረጸላቸው የካራማራው ዘማች አቶ በቀለ ገመቹ 
Mar 5, 2024 4088
አቶ በቀለ ገመቹ ወይም በቅፅል ስማቸው አሚኮ ይባላሉ፤ በሙያቸው ኤሌክትሪሺያን ናቸው። በ1969 ዓ.ም በዚያድባሬ የሚመራው የሶማሊያ አገዛዝ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ሀገር ስትደፈር ቁጭት ተሰምቷቸው ወደ ጦር ሜዳ መዝመታቸውን ይናገራሉ። ጦር ሜዳ ከመዝመታቸው ባሻገር የኤሌክትሪክ ባለሙያ በመሆናቸው "በራ በራ የድል ጮራ" የተሰኘውን ዓርማ በመቅረጽ በ14ቱ ክፍላተ ሀገር እንዲበራ ማድረጋቸውንም ያነሳሉ። በዚህም ከወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እና ከኩባው ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮ መሸለማችውን ያወሳሉ። ታንክ ማራኪው አሊ በርኬ ጓደኛቸው እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ በቀለ፤ በተለያዩ ዐውደ ግንባሮች መሳተፋቸውን አስታውሰዋል። አቶ በቀለ ጥቁር አንበሳ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ በሚገኘው የድላችን ሐውልት ላይ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ይዘው ሐውልት ተቀርጾላቸዋል። ሐውልት እንዲቀረጽ የተደረገበት ፎቶግራፍ በያኔው ሶስተኛው አንበሳው ክፍለ ጦር በኋለኛው ምሰራቅ ዕዝ በር ላይ በቀኝ እጃቸው መሳሪያ ከፍ አድርገው ይዘው የተነሱት ፎቶ ግራፍ እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ። ከእርሳቸው ጎንም መንበረ የምትባል ሌላ ኢትዮጵያዊ ዘማችና መትረጊስ ተኳሽ ሴት ባደረገችው አስተዋፅኦና በደረሰባት አካል ጉዳት ሐውልት እንደተቀረጸላት ያነሳሉ። የካራማራ ድል ታላቅ ድል ነው የሚሉት አቶ በቀለ ገመቹ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ከፍለውበት የተገኘና ሀገርን ያስከበረ መሆኑንም ይገልጻሉ። የካራማራ ዘማቹ አቶ በቀለ ገመቹ አሁናዊ ኑሯቸው ችግር ላይ እንደሚገኙና ድጋፍ እንደሚሹም ተናግረዋል። ሶማሊያን ለ21 ዓመታት ያስተዳደሩት ዚያድባሬ 'ታላቋን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመስረት' በሚል "ድንበራችን እስከ አዋሽ ይደርሳል" እያሉ በመዛት የጦርነት ነጋሪት መጎሰማቸው የሚታወስ ነው። ይሄን እውን ለማድረግ በ1969 በኢትዮጵያ ላይ ግልጽ ወረራ ፈጸሙ። የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር የእብሪተኛውን የዚያድባሬ ጦር ካራ ማራ ላይ ድል አደረገ፤ የኢትዮጵያ አሸናፊነትም በአደባባይ ታወጀ። ድሉ በየዓመቱ የካቲት 26 ቀን የሚታሰብ ሲሆን ዘንድሮም 46ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል።    
የአፍሪካ ዋንጫን በመሀል ዳኝነት  የመራችው ብቸኛዋ ሴት ዳኛ
Jan 28, 2024 3733
  በይስሐቅ ቀለመወርቅ እንደ መነሻ፡- በእግር ኳስ ውድድሮች የመሃል ዳኝነቱን ቦታ በብዛት የሚይዙት ወንዶች ሲሆኑ፤ አሁን ላይ አልፎ አልፎ ሴቶች ትልልቅ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ሲዳኙ አስተውለናል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 በኳታር አስተናጋጅነት በተከናወነው 22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ፤ ፈረንሳዊቷ ስቴፋኒ ፍራፓርት፤ ኮስታሪካ እና ጀርመን ያደረጉትን ጨዋታ በመሀል ዳኛነት መርታለች። በዚህም በወንዶች ዓለም ዋንጫ ታሪክ በመሀል ዳኝነት የእግር ኳስ ጨዋታን የመራች የመጀመሪያዋ ሴት በመሆን ታሪክ ሰርታለች ። ዘንድሮ ደግሞ በኮትዲቯር አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሞሮኳዊቷ ቦችራ ካርቡቢ፤ ውድድሩን እንዲመሩ ከተመረጡት 32 የመሀል ዳኞች መካከል ብቸኛዋ ሴት ናት። በዚህም በውድድሩ በጊኒ ቢሳውና በናይጄሪያ መካከል የተከናወነውን ሦስተኛ የምድብ ጨዋታ፤ በመሀል ዳኝት በመምራት፤ ታሪክ ጽፋለች። የሞሮኮ ዓለም አቀፍ ማኅበር የእግር ኳስ ዳኛ የሆነችው ቦችራ ካርቡቢ፤ በወንዶችም ሆነ በሴቶች አህጉራዊ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ በርካታ የመጨረሻ ምዕራፍ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ዳኝታለች። 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫን ብቸኛ የሴት ዳኛ ሆና የመራችው ቦችራ ካርቡቢ ማናት? ቦችራ ካርቡቢ በሞሮኮ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው "ታዛ" ከተማ፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1987 ተወለደች። የዘር ግንዷ በሰሜን ምሥራቅ ሞሮኮ ከሚገኙት ሪፊያን ከሚባሉት የበርበር ጎሳ ዝርያ ካላቸው ሕዝቦች የሚመዘዝ ሲሆን፤ ለቤተሰቦቿ አምስተኛና የመጨረሻ ልጅ ነች። ገና በልጅነቷ ለእግር ኳስ ፍቅር ያደረባት ቦችራ ካርቡቢ፤ ኳስ መጫወት የጀመረችው በአንድ ትንሽ የወጣቶች ቡድን ውስጥ ነበር። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2001 በተወለደችበት ከተማ "ታዛ"፤ ለወንዶችና ለሴቶች የእግር ኳስ ዳኝነት ሥልጠና የሚሰጥበት ትምህርት ቤት ተከፈተ ። ይኼ ትምህርት ቤት ቀልቧን የሳበው ቦችራ፤ ሥልጠናውን መውሰድ ጀመረች። "እግር ኳስን እወዳለሁ፤ ራሴንም ላስተምር ፈለኩ።ለምን አላደርገውም ብዬ ፍላጎቴን በመከተል የእግር ኳስ ጨዋታን ደንብ መማር ጀመርኩ" ስትል የእግር ኳስ ዳኝነት ትምህርት የጀመረችበትን ጊዜ ታስታውሳለች። ይኼ ድርጊቷ ካልተዋጠላቸውና፤ በበጎ ጎኑ ካልተመለከቱት ውስጥ ደግሞ፤ ወንድሞቿ ቀዳሚዎች ነበሩ። "በምኖርበት ከተማ አንድ ሴት አጭር ቁምጣ ለብሳ ከወንዶች ጋር ሥልጠና ስትወስድ መታየቷ፤ እንደ አሳፋሪ ድርጊት ስለሚታይ መነጋገሪያ ሆኜ ነበር" ትላለች። የቦችራ ካርቡቢ የዳኝነት ጉዞ እንደ አውሮፓውያን ቆጣጠር በ2007፤ ሞሮኮ ብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ሻምፒዮናን ጀመረች። ይህ መሆኑ ቡችራ ካርቡቢ ብሔራዊ ዳኛ እንድትሆን ዕድል የፈጠረላት ሲሆን፤ መኖሪያዋንም ከትውልድ ሥፍራዋ "ታዛ" ወደ ሞሮኮ ሌላኛዋ ከተማ "ሚከንስ" እንድትቀይር አደረጋት። "ይህን ዕድል ማግኘቴ ቤተሰቦቼ እንዲረዱኝና ሙያዊ ለሆነ ጉዳይ እንደምሄድ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል" በማለት የዳኝነት ሙያዋን በመጨረሻ እንደተቀበሉት ታስረዳለች። በሚከንስ ከተማ በእግር ኳስ ዳኝነት ሥልጠና ላይ እያለች፤ አንድ ቀን አባቷ መጥቶ እንደተመለከታትና፤ ወንድሞቿ ምርጫዋን ሊያከብሩላት እንደሚገባ እንደነገራቸውም ገልፃለች። የ19 ዓመት ወጣት እያለችም፤ በሞሮኮ የሴቶች አንደኛ እና ሁለተኛ የሊግ ውድድር በመዳኘት፤ የዳኝነት ሥራዋን አንድ ብላ ጀመረች። ይህ ከሆነ ከ10 ዓመት በኋላ፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 ደግሞ፤ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ዳኛ በመሆን ራሷን ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋገረች። ከሁለት ዓመት በኋላም በ2018 በጋና አስተናጋጅነት በተከናወነው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ፤ በዛምቢያና በኢኳቶሪያል ጊኒ መካከል የተደረገውን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት አጫወተች። ይህም በአህጉራዊ የውድድር መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሀል ዳኝነት ያጫወተችው ጨዋታ ሆኖ ተመዘገበላት። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020፤ "ቦቶላ" እየተባለ በሚጠራው በሞሮኮ የወንዶች ከፍተኛ የሊግ ውድድር ላይ በመሀል ዳኝነት በመዳኘት፤ የመጀመሪያዋ ሴት ሆነች ። ከአንድ ዓመት በኋላም በካሜሮን አስተናጋጅነት በተከናወነው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፤ ሴኔጋልና ግብፅ ባደረጉት የፍፃሜ ጨዋታ የቫር ዳኛ (video assistant referee) በመሆን ሰርታለች። ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊትም የሞሮኮ የንጉሱ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታን በመዳኘትም ቀዳሚዋ ሴት ናት። አሁን ላይ እየተከናወነ ባለው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወድድርም፤ በጊኒ ቢሳውና በናይጄሪያ መካከል የተከናወነውን ሦስተኛ የምድብ ጨዋታ በመሀል ዳኝት በመምራት፤ የመጀመሪያዋ ሰሜን አፍሪካዊት የአረብ ሴት ሆናለች። ቡችራ ካርቡቢ ከእግር ኳስ ዳኝነት ሥራዋ በተጨማሪ፤ የፖሊስ ኦፊሰር በመሆን ሀገሯን እያገለገለች ትገኛለች።      
ዕልፍ ውበት ከኮይሻ ዕልፍኝ
Dec 23, 2023 2323
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የቱባ ውበቶች መገለጫ ናት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉትም ፈጣሪ በሰጣት የተፈጥሮ ሀብት የታደለች ናት በተለይም በተራሮች፣ በሸለቆዎች፣ በወንዞችና በሐይቆች፣ የተሞላች ሀገር ናት። በአንድ በኩል ተፈጥሮ በብዙ ያደላት፣ ልጆቿም በትጋታቸው በየዘመናቱ ያደመቋት ብትሆንም በሌላ በኩል በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች እንዲሁም በመሰረተ ልማት መጓደል ፀጋዎቿን በአግባቡ ሳታስተዋውቅና ሳትጠቀምበት ቆይታለች። ከአምስት ዓመታት በፊት የመጣውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ መንግስት ለብዝሃ ኢኮኖሚ በሰጠው ትኩረት ቱሪዝም አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ሆኖ ብቅ ማለቱን ተከትሎ ጸጋዎቿ እየተገለጡ ይገኛሉ። በዚህም የአገሪቱን የቱሪዝም አለኝታዎች በአግባቡ መለየትና ማልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መሠረተ-ልማት ማጠናከርና ተጨማሪ አዳዲስ መሠረተ-ልማቶችን መገንባት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ሆነዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሸገርና በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ውጤታማ የቱሪዝም ልማት ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውን ሆነዋል። በገበታ ለሸገር ከተገነቡና ለአገልግሎት ከበቁ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል የእንጦጦ፣ የአንድነትና የወዳጅነት ፓርኮች ይጠቀሳሉ። በወንዝ ዳርቻ ልማትም ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በገበታ ለሀገርም ጎርጎራ፣ ወንጪ-ደንዲና ኮይሻ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው። የኢትዮጵያን ውብ የተፈጥሮ ብልጽግና ሰዎች አይተው ይረኩ ዘንድ የኮይሻ ፕሮጀክት ውብ ሆኖ መሰናዳቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አጋርተዋል።   የኮይሻ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የብዝኃ-ቱሪዝም ባለቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው። የኮይሻ ኢኮ-ቱሪዝም በውስጡ ከያዛቸው በርካታ ሀብቶች መካከል የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ አንዱ ሲሆን በማራኪ ጥብቅ ደን የተሸፈነ ብሔራዊ ፓርክ ነው። በገበታ ለአገር በኮይሻ ፕሮጀክት ውስጥ ከሚለሙ የቱሪዝም መስህቦች አንዱ የሆነው ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ለአረንጓዴ ቱሪዝም ሁነኛ ማሳያ የሚሆን የሀገሪቱ ታላቅ የመስህብ ስፍራ ነው። የመካከለኛው ኦሞ ሸለቆ አረንጓዴያማው ጌጥ ጨበራ ጩርጩራ ወደ 50 የሚጠጉ ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ወንዞች መነሻ ሲሆን በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ጨምሮ አያሌ የዕፅዋት ብዝኃ ሕይወትን የለበሰ ተፈጥሯዊ ፀጋ ነው። የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ዝርያው እየተመናመነ የመጣው የአፍሪካ የዝሆን ዝርያን ጨምሮ እንደ ጎሽ፣ ዲፋርሳ፣ ከርከሮ፣ ሳላ እና አጋዘን ያሉ የዱር እንስሳት የሚገኙበት ነው፡፡ ፓርኩ በደን ሽፋኑ ይበልጥ ጎልቶ ስሙ የሚነሳ ሲሆን፤ በፓርኩ ውስጥ የሚያቋርጡ በርካታ ወንዞችና አምስት ሃይቆችም ይገኛሉ። በጉያው ካቀፋቸው ፏፏቴዎች መካከል ባርቦ ፏፏቴ አንዱ ሲሆን የፏፏቴው ድምጽ ለፓርኩ ተጨማሪ ድምቀት ሆኖታል። የገበታ ለአገር ፕሮጀክት አካል በሆነው የኮይሻ ፕሮጀክት ፓርኩን ለመጎብኘት የሚያስችል መሰረተ ልማት በማሟላት የአካባቢውን የቱሪዝም ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል። የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ የፓርኩን ተፈጥሮ ሳይረብሽ ከፓርኩ ውጪ የሚከናወን ሲሆን ይህም ቱሪስቶች ፓርኩን በቀላሉ እንዲጎበኙት የሚያስችል ነው።   ሌላው የኮይሻ ውብት የግልገል ጊቤ ሶስት ግድብ የፈጠረውን ሰው ሰራሽ ሀይቅ ተንተርሶ የሚገኘው ሀላላ ኬላ ነው። ሀላላ ኬላ በዳውሮ ዞን በኮረብታዎች፣ ሰንሰለታማ ተራራዎችና በግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብ የተከበበ ስፍራ ነው። በዳውሮኛ ቋንቋ "ኬላ" ማለት የድንጋይ ካብ ማለት ሲሆን ሃላላ ኬላ በ1532 ዓ.ም ተጀምሮ በ10 የዳውሮ ነገስታት ለ200 ዓመታት የተገነባ ነው። ስያሜውንም በመጨረሻው ንጉስ ሃላላ ስም ያገኘ ሲሆን ቅርሱ 500 ዓመታትን አስቆጥሯል። ስፍራው ፀጥታ የሰፈነበት፣ የተረጋጋና መንፈስን የሚያድስ እንዲሁም ታሪክ፣ ባህልና መልከዐ ምድርን ማድነቅ ለሚፈልጉ ማረፊያና ማራኪ የቱሪስት መስህብ እንደሆነ ይነገርለታል። ሀላላ ኬላ ሪዞርት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማጎልበትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መዳረሻ ለመክፈት በማሰብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አማካኝነት በ2013 ዓ.ም ይፋ በሆነው የገበታ ለአገር ፕሮጀክት ስር ከሚገኙ የኮይሻ ቅርንጫፍ ስራዎች መካከል አንዱ ነው። በርካታ የተፈጥሮ በረከቶች በአንድ ቦታ የሚገኙበት ሀላላ ኬላ ጎብኚዎች የሚመኙት አይነት አካባቢ፤ የሚውዱት አይነት የተረጋጋ የአየር ጠባይ ያለው ነው፤ የሀላላ ኬላ ሪዞርት። ሪዞርቱ የተገነባው ኢትዮጵያ ያሏትን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶች በማጎልበት ማራኪነታቸውንና መስህብነታቸውን በመጨመር እንዲሁም ተደራሽነታቸውን በማስፋት ለእይታ እንዲበቁ ለማድረግ ነው። በተጨማሪም ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ጎብኚዎች በእንቅስቃሴያቸው ሁሉ እንዲደሰቱና አዲስ ቆይታ እንዲኖራቸው ጥሩ እይታን ፈጥሮ አካባቢውን በሚገባ የሚያስተዋወቅ ነው። የሪዞርቱ ንድፈ ሀሳብ የሃላላ ኬላ ግንብና የአካባቢውን ሕዝብ ታሪክ እንዲሁም የቱሪዝም ሀብትን ከማክበርና ከመጠበቅ ጋር የተቆራኘ ነው። ቱኩል በመባል በአካባቢው ነዋሪ የሚታወቀውን ባህላዊ የስነ ሕንጻ አሰራር ጥበብ በመከተል የቤቱ ውስጣዊ ክፍል አየር በደንብ እንዲያገኝ፣ ጣሪያቸው ከፍ ብሎ ተሰርቷል። የሃላላ ኬላ ሪዞርት በሚያዚያ ወር 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶችና እንግዶች በተገኙበት መመረቁ የሚታወስ ነው። የኮይሻ እልፍኝ ሌላው ውበት የሆነው የልማት ስራ የኮይሻ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነው። የፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት 62 በመቶ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል፡፡ "በቅርብ ርቀት በጨበራ ጨርጩራ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘውን የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅን በምንመርቅበት በአሁኑ ወቅት የኮይሻ ግድብ ለአካባቢው የቱሪዝም ዕድል ተጨማሪ አስተዋፅኦ ያደርጋል" በማለትም በኮይሻ እልፍኝ ዕልፍ ውበት ዕልፍ ዕድል መኖሩን ተናግረዋል፡፡  
የዱርና የቤት እንስሳቱ ቤተሰባዊ ፍቅር
Dec 3, 2023 1318
በፍሬዘር ጌታቸው (ወላይታ ሶዶ ኢዜአ) አብዛኛውን ጊዜ አንዳንድ የዱር እንስሳት ለሥጋቸው፣ ለቆዳቸው፣ ለጥርሳቸው ወዘተ እየተባለ እንደሚገደሉ የአደባባይ ምስጢር ነው። መንግሥት ይህንን ጥቃት ለመከላከል የተለያዩ የዱር እንስሳት ፓርኮችን በማቋቋም ጭምር የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ይታያል። እርምጃው የዱር እንስሳቱን ከመጥፋት እንዲሁም መንግስት ዘርፉን በማስጎብኘት የሚያገኘውን ጥቅም ከመጨመር ባሻገር ሊኖረው የሚችለው ፋይዳ ብዙ ነው። የዱር እንስሳቱ ለአካባቢ ሥነ-ምህዳር የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ሳይዘነጋ ማለት ነው። ሆኖም ግን አሁንም በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም የዱር እንስሳት በሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ ስጋት ላይ ናቸው። ለዛሬ የፅሁፌ ማጠንጠኛ የዱር እንስሳቱ ስጋትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን እነሱን በማላመድ ያልተለመደ ተግባርን እየፈፀመ ባለ ግለሰብ ላይ ይሆናል። ግለሰቡ ወጣት በረከት ብርሃኑ ይባላል፤ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ ነው። ወጣት በረከት አዘወትረን የምንሰማውን 'እንኳን ሰው ወፍ ያለምዳሉ' የሚለውን ብሂል በሚያስረሳ መልኩ እሱ አባባሉን 'እንኳን ሰው አውሬ ያለምዳሉ' ወደሚለው ቀይሮታል ማለት ይቻላል። በረከት “በጎሪጥ የሚተያዩ የዱር እንስሳትን በፍቅር እንዲኖሩ ያደረገበትን ሁኔታ በርካቶች በግርምት ሲመለከቱት ይታያል። የሰው ልጆች በተፈጥሮ ክፉ ሆነው አይወለዱም ዳሩ ግን በህይወት አጋጣሚ ከሚቀስሙት ክፉ ባህሪ የሚማሩትና የሚዋሃዱበት እንጂ ይላል በረከት። ''አብሪያቸው ለመሆን በመወሰኔ እውነተኛ ፍቅርን ከዱር እንስሳቱ ተምሬያለሁ'' የሚለው ወጣት በረከት ከሰባት ዓመት በፊት የዱርና የቤት እንስሳትን በተለይም ሰው ለመቅረብ የሚፈራቸውን ጭምር እንደ ዘንዶ፣ ጅብ፣ ዝንጀሮ፣ አዞ፣ ጦጣ፣ አሳማ እንዲሁም ውሻና የመሳሰሉትን በማሰባሰብ በአንድ ላይ እንዲኖሩ እያደረገ በአንድ ላይ ማኖር እንደጀመረ ይናገራል።   በዚህም ምክንያት ሰው ሰራሽ ሐይቅን በውስጡ የያዘ የወጣቶች መዝናኛ ፓርክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ማቋቋሙን ገልጿል። የዱር እንስሳቱን ከአባያ ብላቴ እንዳመጣቸው የሚናገረው በረከት በይበልጥ ግን በመኪናና መሰል አደጋዎች የተጎዱ የዱር እንስሳትን ከወደቁበት በማንሳት እንዲያገግሙ ለማድረግ በሚያደርግላቸው የእንክብካቤ ቆይታ ታዲያ የዱር እንስሳቱ ከቤት እንስሳት ጋር አብረው የማደር፣ አብረው የመዋል፣ አብረው የመብላት፣ በአንድ ላይ የመጫወት ዕድሉን እንዳገኙ ነው ለኢዜአ የተናገረው። የቤትና የዱር እንስሳቱ ህብረትና አንድነት የሚያስቀና እንደሆነም ወጣት በረከት ገልጿል። ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የዱር እንስሳት ሀብት እንዳለ የሚናገረው ወጣት በረከት በውስጡ ለተፈጥሮ ያለውን ፍቅር ወደ ስራ መቀየሩን ነው የገለፀው። ከሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጋር በመሆን ስራውን ለመሥራት ወስነው በመግባታቸው የከተማው አስተዳደር የሥራ ቦታና መነሻ ካፒታል እንደረዳቸው ገልፆ በዚህም በመበረታታት ያልተለመደ የስራ ዘርፍ ለመፍጠር ወጥነው መጀመራቸውን ይናገራል። ስራውን ሲጀምር ቀላል ሁኔታ እንዳልገጠመው ያስታወሰው በረከት "ካባ ድንጋይ የሚፈነቀልበትን ስፍራ አልምቶና ችግኝ ተክሎ ወደ ዛፍ መቀየር እንዲሁም የሰው ሰራሽ ሐይቅ እንዲያመነጭ ማድረግ የማይቻል ይመስላል" ይላል። ቦታውን በባለሙያ በማስጠናትና ደባል አፈር ከሌላ ቦታ በማስመጣት ህልማቸውን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን አውስቶ ዓላማቸውን ለማሳካት የሄዱበት ርቀት ለሌሎች አስተማሪ መሆኑንም ይናገራል። ቦታውን አሁን ላይ የተለያዩ የዱርና የቤት እንስሳት በጋራ የሚኖሩበትና በርካታ የአገር ውስጥና ከሌላው ዓለም የሚመጡ ጎብኚዎች የሚዝናኑበትና የሚያርፉበት "ጁኒየር የወጣቶች መዝናኛ ፓርክ" መክፈት መቻላቸውን ነው የተናገረው። እንስሳቶች የሚሰጣቸውን ስያሜ ሳይሆን ተቀራርበው የሚኖሩበትን የፍቅር ህይወት ለማየት የሚመጣው ጎብኚ የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ እንዳለበት በማመን የማረፊያ ቤቶች እና ተጨማሪ መዝናኛዎችን በማስፋፋት አሁን ላይ ጥሩ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አብራርቷል። በዚህም ''በፓርኩ ግቢ ውስጥ የወላይታ ሶዶ ከተማን ገጽታ የሚያሳይ ባለ ሰባት በር መግቢያና መውጫ ያለው ሆቴልና የጀልባ መዝናኛ አገልግሎት ለተጠቃሚዎች በመስጠት የተሻለ ስራ በመስራት ላይ እንገኛለን'' ብሏል። ፓርኩን ለመጎብኘት ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ለአንድ ሰው 30 ብር፣ ለውጭ ዜጋ ደግሞ 100 ብር በማስከፈል አገልግሎት እየሰጡ ያነሳው ወጣቱ በአዘቦት ቀናት በቀን ከ400 በላይ ጎብኚ ፓርኩን እንደሚጎበኙ ፣ በሰንበት ቀናት እና በበዓላት ወቅት እስከ 1 ሺህ ድረስ ጎብኚዎች እንደሚመጡ ነው የተናገረው። ያንን ሁሉ አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ባደረጉት ብርቱ ጥረት ከቤተሰብና በጥቂቱም ቢሆን ከመንግሥት ጥገኝነት መላቀቃቸውን የሚናገረው ወጣቱ በህይወታቸው ጥሩ ኑሮ መኖር ከመጀመራቸውም በዘለለ በፓርኩ ውስጥ ላለው የእንስሳት እንክብካቤና ጎብኚዎችን የማስተናገድ ስራን ለሚያሳልጡ 22 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር በመቻላቸውም ስኬታማ እንደሆኑም ያነሳል። "አሁን እንስሳቶቹ ቤተሰቦቼ ሆነዋል በአንድ ቅጥር ግቢ ውስጥ አብሬያቸው ውዬ ነው የማድረው ይላል። ስራ ሩቅ አይደለም አጠገባችን እንዲያውም እጃችን ላይ ነው ያለው የሚለው ወጣት በረከት ሆኖም ሌላ አካል መጥቶ እንዲሰጠን እንጠብቃለን፣ ይኸ አስተሳሰብ የእድገታችን ፀር ነው '' ሲልም አፅንኦት ሰጥቶታል። ኢትዮጵያ በዱር እንስሳት ሀብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ የሚነሳ መሆኑን ጠቁሞ ሀብቱን ለማሳደግና ሳቢ በማድረግ ተደራሽነቱን ለማስፋት እንዲያመች የሎጅ ግንባታ ስራ እንቅስቃሴ ጀምሬያለሁ ባይ ነው። ፓርኩ ውስጥ 62 ምንጮች እንደሚገኙ የገለፀው ወጣት በረከት ማስፋፊያ ቦታ ቢሰጠው የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት እቅድ እንዳለው ተናግሯል። በሰዎች ዓለም ውስጥ ገዢ ሀይል ፍቅር ሊሆን እንደሚገባ ፓርኩ ትልቅ የፍቅር ተምሳሌት ፓርክ ‼ ነው የሚሉት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ታዲዮስ ታንቱ ናቸው። ፓርኩ በሂደት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ እንዲጠራ ጉልህ ሚና ይኖረዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው በመግለጽ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ትኩረትና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ፓርኩን ሲጎበኙ ያገኘናቸው የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ለገሰ ቶማስ በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመነመነ ለመጣው የዱር እንስሳት ሀብት ማገገም የራሱን አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ፓርክ መሆኑን ተናግረዋል። "ሁላችንም እንደዚሁ በእጃችን ያለውን ሀብት መጠቀም ካልጀመርን በቀር ሊለውጠን የሚመጣ ተዓምር አይኖርም'' ያሉት አስተያየት ሰጪው ከወጣት በረከት ሁሉም ብዙ ሊማር እንደሚገባም ጠቁመዋል።  
“ዮ-ማስቃላ''- ሁሉም የሚደሰትበት በዓል
Sep 23, 2023 1433
በሳሙኤል አየነው የሰላም፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የመቻቻልና የአንድነት ተምሳሌት የሆነው የጋሞ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል “ዮ-ማስቃላ” ከወርሃ መስከረም አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች በድምቀት ይከበራል ። በተለያየ ምክንያት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ተራርቀው የነበሩ ወገኖች ወደ የአካባቢያቸው በመመለስ ከቤተሰቦቻቸው ብሎም ከቀየው ህብረተሰብ ጋር አብረው የሚያከብሩት የዓመቱ ታላቅ በዓል ነው ። ታዲያ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ወንዶች ሰንጋ በሬ ለመግዛት እንዲሁም ለትዳር አጋሮቻቸውና ለልጆቻቸው ልብስና ጌጣ ጌጥ የሚሆን ገንዘብ መቆጠብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ሴቶችም ለባህላዊ ምግቦች፣ ለቅመማ ቅመም፣ ለቅቤና ለባህላዊ መጠጦች እህል ግዥ የሚሆን ገንዘብ ዓመቱን ሙሉ ሲቆጥቡ ይከርማሉ። መስከረም ወር ከገባበት ዕለት አንስተው ወንዶችም ሆኑ ሴቶቹ በቆጠቡት ገንዘብ በየፊናቸው ለበዓሉ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ይጀምራሉ። ይህም የዝግጅት ጊዜ “እንግጫ” በመባል ይጥራል። በ”ዮ--ማስቃላ” ጊዜ አብሮነት እንጂ ግለኝነት የሚባል ነገር በጋሞዎች ዘንድ ፈጽሞ አይታሰብም፤ አብሮ እርድ ማካሄድ፣ አብሮ መመገብ፣ አብሮ መጠጣት፣ አብሮ መጫወት የጋሞዎች መገለጫ ነው። እንደ ሌሎቹ በዓላት ሁሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችም በዓሉን እንዴት እናሳልፍ የሚል ስጋት አያድርባቸውም። ምክንያቱም የሌለውም ካለው ጋር አብሮ የሚቋደስበት፣ የሚደሰትበት፣ የሚተሳሰብበትና የሰብአዊነት ልክ የሚንጸባረቅበት ልዩ ድባብ ያለው በዓል ነውና ዮ-ማስቃላ ። የጋሞ የሀገር ሽማግሌ አቶ አመሌ አልቶ ስለ “ዮ--ማስቃላ” በዓል በትንሹ እንዲያወጉን ጠይቀናቸው በዓሉ ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን እንስሳትና አዕዋፋት ሁሉ የሚደሰቱበት እንደሆነ ነግረውናል። በአካባቢው ቋንቋ ተፈጥሮ ሁሉ በዓሉን በደስታ እንደሚያሳልፍ ለመግለጽ “ካፎስ ካናስ ማስቃላ” በማለት የሚገለጽ ስሆን “ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም መስቀል ነው” እንደማለት ነው ብለዋል። በዓሉ ከመድረሱ ከሶስት ወራት አስቀድሞ በየአካባቢው ለእንስሳት የግጦሽ ሥፍራ ተከልሎ የሚዘጋጅ ሲሆን ችቦው በሚለኮስበት በደመራው ዕለት የቤት እንስሳት በሙሉ በዚያው የሚሰማሩ ይሆናል። ዓመቱን ሙሉ ሲያርሱ የነበሩ የእርሻ መሣሪያዎችም በበዓሉ ጊዜ ታጥበውና በቅቤ ታሽተው በክብር ይቀመጣሉ። ክብር ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትና ለእርሻ መሣሪያዎችም ይሰጣል። በባህሉ መሠረት ችቦ በሚወጣበት ሰዓት አባት የራሱን ችቦ ለኩሶ የቤቱን ምሰሶ፣ የከብቶችን ጋጣና የበር ጉበኖችን ግራና ቀኝ በችቦው ጫፍ በማነካካት ወደ ውጭ ካወጣ በኋላ ወንድ ልጆች የየራሳቸውን ችቦ ተራ በተራ እየለኮሱ አባታቸውን ተከትለው “ዮ---ማስቃላ” እያሉ ወደ ደመራ ቦታ ያመራሉ። ከዚያም አባት በቅድሚያ ችቦውን ከለኮሰ በኋላ ልጆች ደግሞ ተከትለው ደመራውን ይለኩሳሉ። ከዚህ ፕሮግራም መልስ ወደ ቤት ተመልሰው የተዘጋጀውን ገንፎ በአንድ ወጭት ላይ “ዮ--ማስቃላ”እያሉ ሁሉም የቤተሰብ አባላት፣ ዘመድ አዝማድና ጎረቤት ተሰባስበው በጋራ ይመገባሉ። በ”ዮ--ማስቃላ” በዓል በዋናነት እርድ የሚከወን ሲሆን ቁርጥ፣ ጎረድ ጎረድ፣ ክትፎና የወጣ ወጥ ዓይነቶች ተሠርተው ለምግብነት ይቀርባሉ። ከባህላዊ ምግቦች ደግሞ የገብስ ቅንጬ፣ የቆጮና ገብስ ውህድ ቂጣ፣ የቡላ ፍርፍር፣ ሀረግ ቦዬ፣ እንዲሁም ከመጠጥ አይነቶች ደግሞ ቦርዴ፣ ጠላ፣ የማርና የቦርዴ ጠላ ውህድና ሌሎች ተወዳጅ ምግቦችና መጠጦች ይዘጋጃሉ። በ”ዮ--ማስቃላ” በዓል ዕለት የሚቀራረቡ ጎረቤታሞች በጋራ ሆነው አማካይ በሆነ ሥፍራ ላይ የእርድ ሥነሥርዓት ያከናውናሉ። የእርድ ሥነ-ሥርአቱም በደመራው ዕለትና ማግስት እንደ ህብረተሰቡ ይሁንታ የሚፈጸም ይሆናል። ከማግስቱ ጀምሮ የተዘጋጀውን ሥጋ በጋራ እየበሉና እየጠጡ የበዓሉን ድባብ የሚያስቀጥሉ ሲሆን “ዱንግዛ” በተሰኘው የጋሞ ባህላዊ ጥበብ ልብስ ደምቀው በጌጣጌጥ አሸብርቀው ሁሉም በየአደባባዩ በባህላዊ ጫዋታዎች እየተደሰተ በዓሉን ያከብራል። ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና አብሮነት ካለ በአዲሱ ዓመት ምድሪቱ ተገቢውን ምርት እንደምትሰጥ ሁሉም ሰው በተሰማራበት መስክ ውጤታማ እንደሚሆን ይታመናል። ከዚም የተነሳ በአሮጌው ዓመት ሃዘን ላይ የነበሩ ወገኖች ሙሉ በሙሉ ሀዘናቸውን በመተው በአዲስ መንፈስ ወደ መደበኛው ህይወት ይመለሳሉ። የተጣሉ ወገኖች ቂም ይዘው አዲስ ዓመትን መሻገር በጋሞዎች ዘንድ ነውር በመሆኑ በባህላዊ ሸንጎ ሥርአት /ዱቡሻ/ በጋሞ አባቶች አሸማጋይነት እርስ በርስ ተነጋግረው በመታረቅ አዲሱን ዓመት በጋራ ያበስሩታል። በሌላ መንገድ “ዮ..ማስቃላ” በዓል ተጠብቆ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ የተጫጩት ደግሞ ጋብቻ የሚከውኑበት እንዲሁም ያገቡት በየገበያው ዕለት “ሶፌ” የሚባል ሥነ-ሥርዓት በማከናወን በማህበራዊ ህይወት ማህበረሰቡን በይፋ የሚቀላቀሉበት መሆኑን ጋሽ አመሌ አውግተውናል። ጋሞዎች ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን በአብሮነት ለሁለት ሳምንታት በደስታ ካሳለፉ በኋላ ወደ ግብርና ሥራቸው በመመለስ ቀደም ሲል በክብር ያስቀመጧቸውን የእርሻ መሣሪያዎች በማንሳት ወደ እርሻ ሥራ ይገባሉ። እስከ ታህሳስ ወር መውጫ ድረስ የበዓሉ ድባብ ሳይጠፋ ይቆይና በመጨረሻም የመሰናበቻ ድግስ ወይም “ጮዬ ማስቃላ” በማዘጋጀት በህብረት ከተመገቡና ከጠጡ በኋላ የዓመት ሰው ይበለን፣ ዓመቱ የሰላም፣ የጤና፣ የበረከት ይሁን በማለት በመመራረቅ “ዮ--ማስቃላ”ን ይሸኛሉ። በዓሉ የህዝቡን ሰላም ፣አንድነትና አብሮነት የሚያንጸባርቅ ልዩ በዓል ነው በማለት የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ሞናዬ ሞሶሌ የጋሞ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት የአቶ አመሌ አልቶን ሃሳብ ይጋራሉ። ባህላዊ እሴቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተጠብቆ እንዲቆይ “ዮ--ማስቃላ” ትልቅ ድርሻ አለው። የባህል እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ በጥናትና ምርምር በማስገፍና የቋንቋና ባህል አውደ ጥናት በየዓመቱ እየተደረገ እንደሆነም ነግረውናል። አባቶች በልዩነት ውስጥ ያለንን አንድነት እንዳቆዩልን ሁሉ ወጣቶችም ኢትዮጵያዊ ለዛ ያላቸው የጋራ እሴቶች ሳይበረዙና ሳይከለሱ ጠብቀው ለትውልድ የማስተላለፍ ሃላፊነት አለባቸው የሚለውን የንግግራቸው ማሳረጊያ አድርገዋል።              
የዕልፍ ሕጻናትን ዕጣ ፈንታ ከሞት ወደ ሕይወት የለወጠው ወጣት ላሌ ላቡኮ 
Sep 8, 2023 1638
በሀገራችን በርካታ አካባቢዎች የታዳጊዎችን ተስፋና ህልም ብቻ ሳይሆን ሕልውና የሚገዳደሩ ከባህላዊ እምነት ጋር የተቆራኙ አይነተ ብዙ ጎጂ ባህላዊና ልማዳዊ ድርጊቶች እና ክዋኔዎች አሉ። ለአብነትም ደቡብ ኦሞ ዞን እንደ ካራ፣ ሀመርና ቤና ህዝቦች ዘንድ የተለመደው እና ከህጻናት ጥርስ አበቃቅል ጋር የተያያዘው ’ሚንጊ' የሚሰኘው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ይጠቀሳል። በአካባቢው ልማድ በታችኛው ድድ ጥርስ የሚያበቅሉ እንስሳት ቅዱስ፣ በላይኛው ድድ ጥርስ የሚያበቅሉ እንስሳት ደግሞ ርኩስ የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል። ከዚህ ጋር በማገናኘትም የሚወለዱ ህጻናት የላይኛው የወተት ጥርሳቸው ቀድሞ የሚበቅል ከሆነ እንደ እርኩሳን እንስሳት ከመጥፎ መንፈስ ጋር ተቆጥሮ ለማህበረሰቡ የማይበጅ፣ አድጎም ለቤተሰቡ ጠንቅ ተቆጥሮ የመገደል ዕጣ ፈንታ ይገጥመዋል። ይህ ልማድ “ሚንጊ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን አያሌ ህጻናትን ቀጥፏል። ይህ ብቻም ሳይሆን የማህበረሰቡ አባል ሴት ከትዳር በፊት ልጅ ከወለደች የተወለደው ሕጻን በ'ሚንጊ'ነት ይፈረጃል። ሚንጊ ተብለው የተፈረጁ ህጻናት በማህበረሰቡ ዘንድ መርገምት፣ ቁጣ፣ ርሀብ በሽታ… እንደሚያመጡ ስለሚቆጠር ከጥልቅ ወንዝ መጣል፣ ወደ ገደል መወርወር አልያም በጫካ ውስጥ የመጣል ዕጣ ይገጥማቸዋል። ሚንጊንና መሰል በየማህበረሰቡ ዘንድ ለዘመናት የተለመዱ ጎጂ ድርጊቶችን ለማስቀረት እና ማህበረሰብ አቀፍ ለውጥ ለማምጣት ግን ውስብስብ እና ጊዜ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ላሌ ላቡኮና መሰል ብርቱና አርቆ አሳቢ ሰዎች ግን ባደጉበት ብርቱ ጥረት የማህብረሰብን አስተሳስብ በመለወጥ ለዘመናት ለሚከወኑ ውስብስብ ችግሮችን መፍትኤ መስጠት ችለዋል። ላሌ ላቡኮ በተወለደበት ቀዬ እና አባል በሆነበት ደመ ከልብ ሆነው የሚቀሩ ህጻናትን ዕጣ ፈንታ ከወንዝ፣ ከገደልና ከጫካ ከመጣል ተርፈው ለወግና ማዕረግ እንዲበቁ አስችላል። በአጉል ባህል ሕይወታቸውን የሚነጠቁ ዕልፍ አዕላፍ ህጻናት ነፍስ እንዲዘሩ በማድረግ ትውልድ ያሻገረ፣ ማህበረሰብን የለወጠ አርበኛ ነው። ላሌ ላቡኮ ይህን ነባር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለመቃወምና መፍትሄ ለማምጣት ያነሳሳው ሁለት እህቶቹን ጨምሮ ምንም ነፍስ ያላወቁ ሕጻናት በሚንጊነት ተፈርጀው ሲቀጠፉ በማየቱና በመስማቱ እንደሆነ ይናገራል። ከ17 ዓመታት በፊት ‘ኦሞ ቻይልድ’ በሚል ባቋቋመው ድርጅት 'ሚንጊ' የተባሉ 58 ሕፃናትን ከገዳዮች ፈልቅቆ ከሕልፈት ወደ ሕይወት ለውጧል፣ ለቁም ነገር ለማብቃትም እያስተማራቸው ይገኛል።   እህቶቹን ጨምሮ የትውልድ መንደሩ ሕጻናትን ሕይወት ለመቀጠፍ የዳረጋቸው የሚንጊ ድርጊት የሚፈጸመው፣ በማህበረሰቡ ዕውቀት ማነስ ነው ብሎ ያምናል። በዚህም ይህን አስከፊ ድርጊት እና አስተሳሰብ ለመቀየር ቆርጦ በመነሳቱ ቤተሰቡን ጨምሮ ከማህበረሰቡ መገለል እስከ ማስፈራሪያ ጥቃቶች አስተናግዷል። እርሱ ግን ፈተናዎች ሳይበግሩት በዓላማው ጸንቶ፣ ትዕግስትና ብልሃት ተላብሶ ሸውራራ ማህበረሰብ አቀፍ አመለካከቶችን መስበር ችሏል። የሚንጊ ባህል አሁንም ሙሉ ለሙሉ እንዳልተቀረፈ የሚናገረው ላሌ፣ ስር ነቀል የአስተሳስብ ለውጥ ለማምጣት ለህብረተሰቡ አሁንም ብርቱ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እንደሚገቡ ገልጿል። ላሌ በመሰረተው ድርጅት ከሚማሩ ሕጻናት ባሻገር ከ300 በላይ ህጻናት ከቤተሰባቸው ዘንድ ሆነው ለመማር እንዲችለኩ ማድረጉንም ይናገራል። ሕፃናቱን ከሞት አፋፍ ታድጎ ከራሳቸው ሕልውና ባለፈ ለቁም ነገር እንዲበቁና ለሀገርና ለወገን የሚበጁ ሰዎች እንዲሆኑ በመስራቱ አዕምራዊ እርካታ እንደሚሰማው ይገልጻል። ላሌ የሚንጊን ጎጂ ድርጊት ከመታደጉ በተጨማሪ በደቡብ ኦሞ ትምህርት ቤት ገንብቶ ከ700 በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል። ናሽናል ጂኦግራፊ፣ ቴድ ቶክ፣ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም እና የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት የላሌን ትውልድ የመታደግ ተግባር ዕውቅና ከሰጡት ወስጥ ይጠቀሳሉ።
የ19ኛ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዎና ደጋሹ የቡዳፔስት ስታዲየም
Aug 22, 2023 1436
  የቡዳፔስቱ ናሽናል አትሌቲክስ ሴንተር ስታዲየም 700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በሚጠጋ ገንዘብ ተገንብቶ ዝግጅቱን አሟልቶ እንዲያስተናግድ በሚያስችል ቁመና ላይ የደረሰው ከ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዎና መጀመር ቀደም ብሎ ነው። የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከኦሊምፒክ ጨዋታዎች ቀጥሎ የሚጠቀስ ግዙፍ የሆነ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነት ነው። “የስፖርቶች ንጉስ” የሆነ ውድድር ነው የሚሉትም አልጠፉም። አገራት ለሻምፒዮናው ከሚያደርጉት ሽር ጉድ ባለፈ እንደዚህ ዓይነት ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት የሚያደርጉት ፉክክር ቀላል የሚባል አይደለም። ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነቶችን ለማዘጋጀት ሚሊዮኖችን አለፍ ካለም ቢሊዮኖችን ወጪ ያደርጋሉ። አገራት ውድድሩን ከማስተናገድ ባለፈ ታሪካቸውንና ባህላቸውን ጨምሮ ያላቸውን መልካም ገጽታ ለመገንባት ይጠቀሙበታል ። 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከቀናት በፊት በማዕከላዊ አውሮፓዊቷ አገር ሃንጋሪ ተጀምሯል። በሻምፒዮናው ላይ ከ200 አገራት በላይ የተወጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ አትሌቶች እየሳተፋ ይገኛሉ። ሻምፒዮናው ቡዳፔስት በሚገኘው ናሽናል አትሌቲክስ ሴንተር ስታዲየም በመካሄድ ላይ ይገኛል። ነሐሴ 13/2015 የሻምፒዮናው ደማቅ የመክፈቻ ስነ ስርዓት በዚሁ ስታዲየም ተከናውኗል። በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን፣የሀንጋሪ ፕሬዝዳንት ካታሊን ኖቫክ፣ የተርኪዬ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይብ ኤርዶጋን፣ የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሰባስቲያን ኮ፣የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት አሌክሳንዳር ሴፈሪንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸው ይትወሳል። እኛም ሻምፒዮናው እየተካሄደበት ስላለው ስታዲየም መረጃዎችን ልናካፍላችሁ ወደናል። ናሽናል አትሌቲክስ ሴንተር ስታዲየም የግንባታ መሰረት ድንጋይ እ.አ.አ በ2020 ተጥሎ ግንባታው የተጀመረው እ.አ.አ 2021 መግቢያ ላይ ነበር። ስታዲየሙ ግንባታው ከመጀመሩ በፊት 40 ሺህ ተመልካች እንደሚያስተናግድ ይፋ ተደርጎም ነበር። ይሁንና የግንባታው ስራ ሲጀመር በሚይዘው የተመልካች ብዛት ላይ ክለሳ ተደርጎ ስታዲየሙ 36 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግድ መልኩ ግንባታው እንደሚቀጥል ተገለጸ። በዚሁ መሰረት የላይኛው የስታዲየም ክፍል 22 ሺህ እንዲሁም የታችኛው ክፍል 14 ሺህ ተመልካች እንዲደሚይዝ የሃንጋሪ መንግስት አስታወቀ። የስታዲየሙ ግንባታ ከእ.አ.አ 2022 አጋማሽ ዓመት በኋላ ተጠናቆ በዛው ዓመት ማብቂያ ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው የትኬት ሽያጭ መከናወን ጀመረ። ስታዲየሙ እ.አ.አ ሰኔ 16/2023 የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሰባስቲያን ኮን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቆ በይፋ ስራ ጀመረ። አጠቃላይ ለስታዲየሙ ግንባታ 700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ወጪ መደረጉንና ይህም ሀንጋሪ ለስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ ያወጣችው ትልቁ ገንዘብ ሆኖ ተመዝግቧል። ከዚህ ቀደም ሀንጋሪ ለስፖርት መሰረተ ልማት ያወጣችው ትልቁ ወጪ ከ67 ሺህ በላይ ተመልካች ለሚያስተናግደው ፑሽካሽ አሬና ስታዲየም ሲሆን ለስታዲየሙ ግንባታ 600 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ እንደተደረገበት መረጃዎች ያመለክታሉ። የውድድሩ መሮጫ መም “The Crown of the Queen of Sports” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ስያሜው የመነጨው አትሌቲክስ የሁሉ ስፖርቶች ቁንጮ ነው ከሚል እሳቤ መሆኑን ተገልጿል። ናሽናል አትሌቲክስ ሴንተር ስታዲየምን የገነቡት ‘ዛኤቭ ኢፕቶይፓሪ ዜድአርቲ’ (ZÁÉV Építőipari Zrt) ‘ማግያር ኢፒቶ ዜድአርቲ’ (Magyar Építő Zrt) የተሰኙ ተቋራጮች ናቸው። ስታዲየሙ የሚገኘው በደቡብ ማዕካላዊ ቡዳፔስት እና በአውሮፓ በትልቅነቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የዳኑብ ወንዝ ምስራቃዊ አቅጣጫ ነው። ከዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በኋላ የስታዲየሙ የመያዝ አቅም ወደ 14 ሺህ ዝቅ እንደሚልና በተመልካቾች በኩል ያሉ ጊዜያዊ የስታዲየሙ የላይኛው ክፍል መሰረተ ልማቶች እንደሚነቀሉም ተገልጿል። የዓለም የአትሌቲክስ አፍቃሪያን በስታዲየሙ በቀጣይ ቀናት በሚካሄዱ የአትሌቲክስና የሜዳ ተግባራት ውድድሮችን በጉጉት መከታተላቸውን ይቀጥላሉ። የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው እስከ ነሐሴ 21/2015 ይቆያል። በሃንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ በሚገኘው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የአራተኛ ቀን ውሎ የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ከምሽቱ 4 ሰአት ከ30 የ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት ብርቄ ኃየሎም እና አትሌት ድርቤ ወልተጂ ይሳተፋሉ። አትሌት ብርቄ 3 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ ከ94 ማይክሮ ሴኮንድ እና አትሌት 3 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ ከ8 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ ያላቸው የግል ምርጥ ሰዓት ነው። በ3 ደቂቃ ከ49 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነችው የ29 ዓመቷ ኬንያዊ አትሌት ፌዝ ኪፕዬጎን ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝታለች። አትሌቷ የ1 ማይል እና የ5 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤትም ናት። በዚህ ውድድር ላይ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው አትሌት ሲፋን ሀሰን ትወዳደራለች። ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ42 ደቂቃ በ3 ሜትር መሰናክል ወንዶች ፍጻሜ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት አትሌት ለሜቻ ግርማና አትሌት ጌትነት ዋለ ይወዳደራሉ። አትሌት ለሜቻ በሰኔ ወር 2015 በፓሪስ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል 7 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በኳታሩ አትሌት ሳይፍ ሰኢድ ሻሂን ለ19ኝ ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ክብረ ወሰን በ1 ሴኮንድ ከ52 ማይክሮ ሴኮንድ ማሻሻሉ ይታወቃል። አትሌት ጌትነት 8 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ15 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ ይግል ምርጥ ሰአቱ ነው። በውድድሩ አትሌት ለሜቻ እና የሞሮኮው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ የሚያደርጉት ፉክክር በስፖርት ቤተሰቡ ከወዲሁ በጉጉት ይጠበቃል። ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው እስከ አሁን 1 የወርቅ፣1 የብር እና 2 የነሐስ በአጠቃላይ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ቡሄ እና ትውፊቱ
Aug 19, 2023 1194
  በአየለ ያረጋል "ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት" ዛሬ ማታ ለጠበል ጠዲቅ እንዳትቀር ሲሉኝ ጎረቤቴ ደብረ ታቦርን አስታወሱኝ። እኔ ባደኩበት ገጠራማ አካባቢ ዛሬን (ነሐሴ 13) ደብረ ታቦር እንለዋለን። ይህ ዕለት በአብዛኛው ኢትዮጵያ አካባቢ 'ቡሄ' በሚል ይታወቃል። የክረምት ወቅት ሦስተኛው ወርኅ ነሐሴ ነው። ቡሄ ደግሞ ከወርኅ ነሐሴ ውብ መልኮች አንዱ ነው። ትውፊታዊ አንድምታው ከክረምት ወደ ጥቢ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከጭጋግ ወደ ወገግታ...የመሸጋገር ምኞት ጋር ይቆራኛል። "ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት" የሚባለውም ለዚህ ይመስላል። በገጠር በእርሻ ሲማስን የከረመ ለገበሬ እና በሬ ከቡሄ በኋላ እፎይታ ማግኘት ይጀምራል። የክረምቱን ከባድ ወቅት አልፎ ጳጉሜን ተሻግሮ ተናፋቂው ወርኅ መስከረም ለመድረስ ('ነይ ብራ ነይ ብራ' እንዲሉ) የቡሄ ወቅት የጉጉት ሰሞን ነው። አዲስ ዓመትን ለማየት የመሻት ምልክት ነው። በነሐሴ አጋማሽና መገባደጃ የአርሶ አደሩ ማሳ ቡቃያ ይለብሳል። ቡሄ መሠረቱ ሃይማኖታዊ ቢሆንም እንደየአካባቢው መልከ-ብዙ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎች አሉት። ቡሄ ታዳጊዎች ይናፍቁታል። በሃይማኖታዊ አስተምህሮው ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር (ታቦር ተራራ) ክብረ-መንግሥቱን እና ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ትዕምርት እንደሆነ ሊቃውንተ- ቤተክርስቲያን ይገልጻሉ። የቡሄ ክዋኔዎች እና ስነ-ቃሎች ሆያ…. ሆዬ….!ሆ….! ቡሄ መጣ በዓመቱ፣ ኧረ እንደምን ሰነበቱ እዛ ማዶ ጭስ ይጨሳል፣ አጋፋሪ ይደግሳል፤ ... የቡሄ ዕለት ማታ ችቦ ይበራል፡፡ ሕፃናቱ ጅራፍ ገምደው ያጮሃሉ። እናቶችም ስንዴ አጥበው እና ፈትገው ዳቦ ይጋግራሉ። ሙልሙል ያዘጋጃሉ። ቀዬው በሕፃናቱ ዜማ ድባብ ይሞላል። መንደሩ በ"ሆያ ሆዬ" ሕብረ- ዝማሬ ይደምቃል። "ቡሄ ና በሉ፤ ቡሄ በሉ ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ …" በሚለው። ይህ ትውልድ ተሻጋሪ ትውፊት እሴቱና ልማዱ ቢለዋወጥም ዛሬም ይከወናል። ቡሄ ትርጉሙ 'ብራ' ማለት ነው። ከሙልሙል ዳቦ በማቆራኘትም 'መላጣ" ማለት ነው የሚሉም አሉ። የቡሄ ጭፈራ በሁሉም አካባቢዎች የተለመደ ነው። ሕፃናቱ ጨፍረው ሙልሙል ዳቦ ይቀበላሉ። ሙልሙል ሲሰጣቸው ምስጋና፣ ሙልሙል ካልተዘከሩ ደግሞ የሐሜት ስነ-ቃሎችን ያስከትላሉ። ለምሳሌ በቡሄ ጭፈራ ዳቦ ከቀረበላቸው "... ሐሚና ሚና፤ ዘነዘነና የበር ዘነዘና ጌታዬን ያማ ሰው፤ እከክ ይውረሰው..." ሲሉ ሙልሙል ያልጋገረች ሴት የተገኘች እንደሆነም "የቡሄ ዕለት ያልጋገረች ሴት፤ አንድ እግሯ ከቆጥ አንድ እግሯ ከረመጥ..." ይላሉ። በነገረ ትውፊት ጽሑፎች የሚታወቁት ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር ስለ 'ብሂለ ወራት' ከጠቀሷቸው ስነ-ቃሎች መካከል ወርኅ ነሐሴ እንዲህ ተጠቅሷል። ... " በሐምሌ እንዴት እከርማለሁ ደግሜ በነሐሴ ነፍሴን እዣለሁ በጥርሴ .... ነሐሴን በእንጥርጣሪ፣ ሐምሌን በብጣሪ ነሐሴ እግር በረቱ፣ መስከረም ዳገቱ በግንቦት አተላ፣ በነሐሴ ባቄላ ..." የቡሄ በዓል የብርሃን በዓል ማለት ነው። የብርሃኑ መገለጥ ዕለት ነው። በዚህም ነሐሴ 13 አመሻሽ ችቦ ይለኮሳል። የችቦው ትዕምርት ደግሞ አንዱ ለሌላው መካሪ አስተማሪ፣ አርዓያ፣ ምሳሌ፣ ብርሃን መሆኑን ያመላክታል። የጅራፍ ትውፊታዊ መልኩ ሁለት ዓይነት ምስጢር ይሰጠዋል። ቀዳሚው ምስጢር የኢየሱስ ክርስቶስን ግርፋትንና ሞቱን ሲሆን ሁለተኛው የጅራፍ ነጎድጓድ ድምፁ የባሕርይ አባቱን (የአብን) ምስክርነት ይወክላል። ነገረ-ሙልሙልም የራሱ ትውፊታዊ ትርጓሜ አለው። በችቦ ብርሃን ወላጆች እረኝነት የወጡ ልጆቻቸውን ለመፈለግ ሲወጡ ለልጆቻቸው በያዙት ስንቅ ይመሰላል። የሙልሙል ዳቦ ዝክሩ መተሳሰብን፣ ፍቅርንና አብሮነትን ይወክላል። ዛሬም ዳቦ የሚጋገረው ለዚህ ትውፊት ነው። ታዳጊዎች 'ሆያ ሆዬ' እያሉ ሙልሙል ዳቦ የሚጠይቁትም ከዚህ ትውፊት የመነጨ ነው። በሌላ ጎኑ ሕፃናቱ በደቀመዛሙርት፣ ዝማሬያቸው ደግሞ በ 'የምሥራች' እንዲሁም ስጦታው በምርቃት ይመሰላል። በዓለ-ደብረ ታቦር ወይም በቡሄ ትውፊታዊ ክዋኔዎች የየራሳቸው ትርጓሜ እና እሴት ቢኖራቸውም አልፎ አልፎ ከትውፊት ያፈነገጡ ክዋኔዎች ይስተዋላሉ። በዚህም ነባሩ ትውፊት ወደ ትውልድ ወግና ሥርዓቱን ሳይለቅ በቅብብል መተላለፍ እንዳለበት የሚሞግቱ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። ለምሳሌ ጅራፍን በርችት መተካት 'የምስጢር ተፋልሶ አለው፤ ማኅበራዊ ገጽታው አይበጅም' የሚሉ ወገኖች አሉ። በሆያ ሆዬ የሚሰሙ ግጥሞች ከግብረ-ገብነት ያፈነገጡ፣ ዓለማዊ መልዕክት ያላቸው፣ ስድብ፣ ፌዝና ሥላቅ ይዘት ያዘሉ ሆነው እንደሚስተዋሉ በመጥቀስ ይህን ተግባር አጥብቀው ይተቻሉ። በሌላ በኩል በሙልሙል ዳቦ የተጀመረው እና ሃይማኖታዊ አንድምታ የነበረው የታዳጊዎች 'ሆያ ሆዬ' ትውፊታዊ ሥርዓቱን እየለቀቀ ገንዘብ መሰብሰቢያ መሆን እንደሌለበት ይነሳል። በቡሄ ምሽት በከተሞች አካባቢ የሚስተዋል የመጠጥና ስካር ድባብም እንዲሁ። ይልቁንም ለነዳያን እየዘከሩ እና እየዘመሩ በሰፈር ማኅበራዊ አብሮነት የሚያሳዩ ወጣቶችን ማበረታታት እንደሚገባ ይመክራሉ። መልካም ቡሄ!!          
“አዲስ አበባ” በሞስኮ:- ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ 27 ዓመታት የዘለቀ ጉዞ
Aug 18, 2023 756
  በአየለ ያረጋል ጊዜው በሞስኮ ሰዓት አቆጣጠር ቀትሯል። ‘ጋርደን ሪንግ’ ጎዳና ማዕከላዊ ሞስኮ ከተማን (የሩስያ ርዕሰ መዲና) እንደ መቀነት ይጠመጠማል። በዚህ ጎዳና ከሚገኝ አንድ ተቋም ለብርቱ ጉዳይ ለመግባት የጎግል ካርታ ተከትዬ ከሜትሮ (ምድር ባቡር) መውጣቴ ነበር። በዚህ ቅጽበት ነበር ‘አዲስ አበባ ሬስቶራንት’ የሚለውን ስፍራ አቅጣጫ በድንገት ያስተዋልኩት። በሞስኮ ጎዳናዎች የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ቀርቶ ኢትዮጵያዊ ማግኘት እንደ ምዕራብ ሀገራት ተራ ነገር አይደለም። ብርቅ ነው ማለት ይቀላል። እናም የኢትዮጵያ ሬስቶራንት በድንገት ማግኘቴ ለእኔ ‘ድንገቴ ፈንጠዝያ’ ሆነብኝ። ከሄድኩበት ቢሮ መግባቱን ትቼ በጎግል ካርታ እየተመራሁ ወደ ፊት ገሰገስኩ። ወደ አዲስ አበባ ሬስቶራንት። በ‘ጋርደን ሪንግ’ ጎዳና የአምስት ደቂቃ ርምጃ የጎግል ካርታው ‘ርቀቱ’ ዜሮ ሆነ። ቀና ስል በሀገሬ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት የቀለሙ ፊደላት አነበብኩ። የሩስኪ ቋንቋ ፊደላት ቢሆኑም ደጉ ነገር የማውቃቸው ፊደላት ነበሩ። ‘አዲስ አበባ’ ደረስኩ!! (የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሞስኮ ቢሮም ከአዲስ አበባ ሬስቶራንት ፊት ለፊት ይገኛል) ገርበብ ያለውን በር ገፍቼ ገባሁ። ከገባሁ ጀምሮ አዲስ አበባ እንጂ ሌላ ሀገር መሆኑን ዘነጋሁ። የሀበሻ ዘፈን ይደመጣል። ግድግዳው በሀበሻ ስዕላት ተሞልቷል። ጣሪያው በእንስሳት ቆዳ ተጊጧል። ባንኮኒው የብዝሀ-ኢትዮጵያ መልክ ይዟል፤ በቅርጻ ቅርጾች እና አልባሳት ደምቋል።   ባንኮኒው ውስጥ ያገኘሁትን ሰው ተዋወቅሁ። ዶክተር ጥላሁን መኮንን ነው-የሬስቶራንቱ ባለቤት። የወገን ወግ ተጨዋወትን-አልፎ አልፎ ወደሩሲያኛ ቋንቋ እየተሰረቀ። በዚህ ቅጽበት ብቻ አይደለም። ሌላም፤ ሌላም ቀን እስከ ሞስኮ ቆይታዬ ድረስ። በመጨረሻም ‘አዲስ አበባ በሞስኮ’ን መጣጥፍ ለመጻፍ ወደድኩ። የእህል ውሃ ነገር ሆኖ እዚህ ቦታ ብንገናኝም ጥላሁን መኮንን የተዋጣለት የሚባል ጎበዝ ሙዚቀኛ ነበር-ፒያኒስት!! ጥላሁን እና ሞስኮ- ከልጅነት እስከ ዕውቀት ጥላሁን መኮንን ትውልዱና ዕድገቱ አዲስ አበባ ነው። የሞስኮ እና የጥላሁን ትውውቅ ግን በዕድሜው ማለዳ የተጀመረ ነው። ሞስኮን የረገጠው ገና በለጋነት ዕድሜው ነው። “በ1976 ዓ.ም ሕጻን እያለሁ ሞስኮ መጥቻለሁ። የሙዚቃ ፌስቲቫል ነበር። ስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ይመስለኛል” ይላል። ጥላሁን ከልጅነቱ ጀምሮ የሕጻናት ኪነት ቡድን አባል ነበር። በ1978 ዓ.ም የነ ጥላሁን የኪነት ቡድን በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበረ ውድድርን በማሸነፍ በቀድሞዋ ሶቬት ሕብረት ለሕፃናት በዓል ተጋበዘ። ጥላሁን እና ሌሎች አራት ጓደኞቹም ኢትዮጵያን ወክለው ወደ ሞስኮ ተጓዙ። ጥላሁን ለሁለተኛ ጊዜ ሞስኮን ረገጠ ማለት ነው። “በዚህ ወቅት ሚኒስትሪ (የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና) የተፈተንኩት እዚሁ ነበር” ይላል። ሙዚቃ የጥላሁን የልጅነቱ የነፍስ ጥሪ ነበረች። በትምህርቱም ቀለሜ ነበር። በብዙ ሙዚቀኞች እንደሚስተዋለው ወላጅ አባቱ የሙዚቃ መክሊቱን እንዳያጣጥም ሳንካ አልሆኑበትም። ከልጅነቱ ጀምሮ አይረሴ የኪነት ትውስታዎችን ሰንቋል። በዘመነ ደርግ የአብዮት ዓመታት በሕጻናት ኪነት ቡድን ውስጥ ትልልቅ ሀገራዊ መድረኮች ላይ ተሳትፏል። ጥላሁን እና ጓደኞቹ በሶማሊያው ዜያድባሬ ወረራ ጊዜ ሰራዊቱን ለማነቃቃት በሚደረጉ መድረኮች፣ በአብዮት በዓላት እና ዓለም አቀፍ በዓላት አከባብር ላይ በሕጻናት ኪነት ውስጥ ዘምሯል። በተለይም በኢሕዴሪ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) ፓርቲ ምስረታ ወቅት የብሔር ብሔረሰቦችን ሙዚቃ እንዲገነዘብ ያስቻለውን ዕድል አግኝቷል። “አያሌ የአብዮት መዝሙሮችን ዘምረናል። በብስራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ የሚተላለፍ የኛ መዝሙር ነበር። ለምሳሌ ‘አይዞን ተነሺ ኢትዮጵያ፤ አለን ልጆችሽ’ የሚለው አይረሳኝም። ሁልጊዜ ቅዳሜ፣ ቅዳሜ እንቀረጽ ነበር። ትልልቅ የመንግስት መድረኮች የኛ ኪነት በድኑ ስራዎችን ያቀርባል። የዕድገት በሕብረት ዘመቻ መዝሙርና አርማ የተቀበልነው እኛ ነበርን። የሚገርምህ በቅርቡ ስለዕድገት በሕብረት ዘመቻ ታሪክ ሲተረክ የልጅነት ፎቶየን (የስምንት ወይ የሰባት ዓመት ልጅ ሆኜ) በቴሌቪዥን አይቼው ደስ ብሎኛል” ይላል። ጥላሁን የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን በጥሩ ውጤት አጠናቆ በፒያኖ የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል። ለመመረቂያም ትልቅ ኮንሰርት አዘጋጅቷል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ለሁለት ዓመታት አስተምሯል። የዛሬው የኢትዮጵያ ሙዘቃ ዘርፍ ማህበራት ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩን ከተማሪዎቹ መካከል ይጠቅሳል። ከአስተማሪነቱ ጎን ለጎንም ፒያኖና አኮርዲዮ በመጫወት ብዙ መድረኮች ላይ ይሳተፍ ነበር። ጥላሁን ገሰሰ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ መሀሙድ አህመድ እና መሰል ዝነኛ ድምጻዊያን በተሳተፉበት መድረክ ሙዚቃ ተጫውቷል። የሙዚቃ ቡድን መሪ ሆኖም ነበር። በሀገር ውስጥ የህዝብ ለህዝብ መድረኮችን በማደራጀትም ተሳትፏል። ከሁለት ዓመታት የመምህርነት ቆይታ በኋላ ነበር የውጭ ትምህርት ዕድል ያገኘው። በወቅቱ ምሥራቅ ጀርመን፣ ቡልጋሪያ እና ሩስያ ምድቦች ነበሩ። ግርማ ይፍራሸዋ፣ ይገዙ ደስታ፣ መታሰቢያ መላኩና መሰሎቹ በሶስቱ ሀገራት ትምህርት የተማሩበት ዘመን ነው። ጥላሁንም ከአንድ ሺህ ተወዳደሪዎች መካከል በነበረው ውጤት ቀዳሚ ተመራጭ ሆኖ ለሁለተኛ ዲግሪ ሩስያ ተላከ። የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህራንም “እናት ሀገርህን እንዳትረሳ አደራ” ብለው ‘የኢትዮጵያ ካርታ’ ሰጥተው ላኩት። በሞስኮ ሁለተኛ ድግሪውን በከፍተኛ አፈጻጸም (በሀገሪቷ አገላለጽ ቀይ ዲፕሎማ) ይዞ ከመመረቁ ያለምንም ፈተና የሶስተኛ ድግሪ (ዶክትሬት) ትምህርት እንዲቀጥል ዕድል ተመቻቸለት። በኦርኬስትራ መሪነት (ኮንዳክተር) ሙያ ሶስተኛ ዲግሪውን ያዘ። የሩስያ ቋንቋ አስተርጓሚነት ዲፕሎማም ወሰደ። ከሞስኮ ዩኒቨርሲቲ ኦርኬስትራ ጋር ትልቅ ኮንሰርት አካሄደ። በሞስኮ ትምህርት ካልቸራል የኒቨርሲቲ መምህርነት ተቀጠረ። “አስተማሪነት በወቅቱ የኑሮ ደረጃው ከባድ ነበር” ይላል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የመንግስት ስርዓት ለውጥ ተደረገ። ታላቋ ሶቬት ሕብረትም ተበታተነች። ፒያኒስቱ ጥላሁን ቀስ በቀስ ወደ ንግዱ ዓለም ተቀላቀለ። ‘አዲስ አበባን በሞስኮ’ ከፍቶ ኑሮውን ቀጠለ። አዲስ አበባ በሞስኮ አዲስ አበባ ሬስቶራንት በሞስኮ ከተማ ውስጥ በብቸኝነት አለ የሚባል የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ነው። ጥላሁን እንደሚለው ሬስፖራንቱ በቤተሰብ የተጀመረ ነው። ከቤተሰብ ተረክቦ ‘አዲስ አበባ በሚል ስያሜ አስቀጠለው። ዘንድሮ 27 ዓመት አስቆጥሯል። የሬስቶራንቱ አገልግሎት ከምግብና መጠጥ ሽያጩ ይልቅ የኢትዮጵያን ገጽታ እና ባህል በመሸጥ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ያምናል። የደንበኞቹ ማንነት እና የሚቀርቡ ምግቦች አይነት ይህን ያረጋግጣል።   “አዲስ አበባ የሩስያዎች ምግብ ቤት ነው። ደንበኞቻችን የውጭ ዜጐች ናቸው-በአብዛኛው ሩስያዎች። የዲፕሎማቶች ማረፊያ ነው። በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ሩስያዊያን መሰባሰቢያቸው ነው” ይላል። ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱ ቱሪስቶችም ከመሄዳቸው በፊት የኢትዮጵያን ምግብ እና ባህል የሚለማመዱት አዲስ አበባ ሬስቶራንት ነው። የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ለማስለመድ ገጠመኞችንም ያነሳል።“አንድ ቀን እንጀራ ምግብ ታዝዘን እንጀራ ቁርጥ በጎን አቅርብንላቸውና ‘ናፕኪን’ መስሏቸው ነበር። የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ መሆኑን እና እንዴት መበላት እንዳለበት አሳየናቸው። አሁን አዲስ አበባ ውስጥ የገባ ደንበኛ እንጀራ ሳይበላ አይሄድም። ምግቡ ማቀዝቀዣ ውስጥ የገባ ሳይሆን ፍሬሽ ነው። ኬሚካል የለውም። ቡናው ቀጥታ ከኢትዮጵያ እናስመጣለን-የሀረር ቡና። በኢትዮጵያ ቡና አፈላል ስርዓት ከነ ጭሱ እየተፈላ ይቀርባል። ይህን ይመርጡታል። እንጀራ፣ ስጋ ወጥ፣ የበግ ጥብስ፣ ዶሮ ወጥ… ለምደዋል” ይላል። ሶቬት ሕብረት ስትፈራርስ ከባድ የፈተና ጊዜ እንደነበር ያነሳል። በርካታ የአፍሪካ ሬስቶራንቶች ቢከፈቱም እንደ አዲስ አበባ መቀጠል ሳይችሉ እንደተዘጉ ያነሳል። ነገር ግን በአውሮፓዊያኑ አቆጣጥር 1998 ጀምሮ ሁሉም ነገር መስመር እየያዘ ስለመምጣቱ ይገልጻል። አዲስ አበባ ሬስቶራንት በሞስኮ የሚገኙ ሀበሾች ብቻ ሳይሆን መላ አፍሪካዊያን የሚገናኙበት ስፍራ ጭምር ነው። ተጠቃሽ የጥቁሮች ሬስቶራንት ነው። “ብዙ የአፍሪካ ሬስቶራንት የለም። የሩስያና የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆን ሚናውን እየተወጣ ነው ማለት እንችላለን። የአፍሪካ ኤምባሲዎች በሬስቶራንቱ ውስጥ ዝግጅት ያደርጋሉ። በፈረንጆች አቆጣጠር እስከ 2000 ድረስ ሬስቶራንቶች ነበሩ። አሁን የሉም። እኛ ኢትዮጵያን ብቻ ነን።” በሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን በሬስቶራንቱ ያዘጋጃል። ከኢትዮጵያ ወደ ሞስኮ ያቀኑ እንግዶች (ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ) ወደ አዲስ አበባ ሬስቶራንት ጎራ እንደሚሉ ይገልጻል። “ወደ ሩስያ የሚመጡ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ሬስቶራንትን ሲያገኙ ይደሰታሉ። በ2018ቱ የዓለም ኦሎምፒክ የመጡ እንገዶች ትልቅ ደስታ ነበራቸው። ብዙዎቹ ሚኒስትሮችና ዲፕሎማቶች ይመጣሉ። ይህም አለ ወይ? ይሉናል። ትንሿ ኢትዮጵያ፣ ትንሿ አዲስ አበባ ይሉናል። በጣም ይደሰታሉ። ያበረታቱናል። ከበሩ ጀምሮ አዲስ አበባ የሚለውን ሲያዩ ይደሰታሉ።” በርግጥም በተለያዩ አጋጣሚዎች ያገኘኋቸው አፍሪካዊያን ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲ መምራን ‘እንጀራ’ እና የኢትዮጵያውያን ‘ውዝዋዜ’ እንደሚያስደስታቸው ገልጸውልኛል። አንዳንዶቹም ከትክሻቸው ወዝወዝ እያሉ ውዝዋዜን በቀልድ መልክ ለማሳየት ሞክረውልኛል። ይህን ያወቁት ‘በሞስኮዋ አዲስ አበባ’ ነው።   የሬስቶራንቱ እንግዶች ስለኢትዮጵያ መልካም ዕይታ እንዲኖራቸው ጥረት ያደርጋል። ጥላሁን የኢትዮጵያ ስም እንዲጎድፍ አይፈልግም። የኢትዮጵያ ምግብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ነው የሚከፈተው። ሬስቶራንቱ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ እንዲሸት እንደሚሰራ ይናገራል። አዲስ አበባሬስቶራንት በሩሲያን መሰል በውጭ ሀገራት የተከፈቱ፣ የኢትዮጵያን ስምና ገጽታ የሚሸጡ፣ የሀገር ባህልና ወግ የሚያስተዋውቁ ባህላዊ ምግብ ቤቶችን ኤምባሲዎች ሊደግፏቸው እንደሚገባ ያምናል። “ኤምባሲዎችም ሊደግፉን ይገባል። ሬስቶራንቱ የኢትዮጵያን ኤምባሲ ነው የሚያገለግለው። የኢትዮጵያ በዓል ሲኖር ምግብ ሰርተን እናስደስታለን። ባህላችን እንሸጣለን። ዓላማችን ይህ ነው። ብዙ ሊከታተሉን ይገባል። ኢትዮጵያን እናስተዋውቃለን። ይበልጥ ማስተዋወቅ እና አስፈላጊውን ነገር መደገፍ ይገባል ብዬ አምናለሁ። የኢትዮጵያንን ባህል እንሸጣለን። ገፅታዋን እንገነባልን። ኢትዮጵየን ያላዩ እንዲያዩ እናደርጋለን። ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱ ሰዎች መጀመሪያ ስለኢትዮጵያ ባህልና አመጋግብ ይለምዳሉ። ጥናትም ያደርጋሉ።” ጥላሁን በሞስኮ ቆይታውና ኑሮው ደስተኛ ነው። ከሙዚቃ ሙያው መነጠሉን እንደ ዕድለ-ቢስነት ቢቆጥርም አዲስ አበባ ሬስቶራንትን ከፍቶ የሀገሩን ስም በማስተዋወቁ ግን ደስተኛ ነው። የሩስያዊያን ባህል እና የህዝቡ ማህበራዊ ውቅር ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳስሎሽ መኖሩም ሌላው የሚደሰትበት ጉዳይ ነው። አሁን የሩስያ ዜግነትም ተቀብሏል። ሁለት ልጆችን ለአካለ መጠን አድርሷል። ሩስያዊያን ስለኢትዮጵያ ያላቸው መልካም ዕይታም ይገርመዋል።   “ብዙዎቹ ሩስያዊያን የኢትዮጵያ ወዳጆች ናቸው። ለኢትዮጵያ ያላቸው ወዳጀነትና ቅርበት ሲናገሩ አታምንም። በኢትዮጵያ የነበሩ ወታደሮች ሁሉ ይመጣሉ። ስለኢትዮጵያ ህዝብ ደግነትና የዋህነት ያወሩኛል። አሁን አዲስ አበባ ደርሰው የሚመጡም አሉ። የድሮዋ አዲስ አበባ አይደለችም እያሉ ለውጡን ይተርኩልኛል። የዋህ ናቸው። በባህልም እንመሳሰላለን። ቅዳሜና እሁድ ቤተ ክርስቲያን ስሄድ እንደ ኢትዮጵያ ሰንበት ይሰማኛል። በጥምቀት በዓል ትዕይንት ልዩ ነው” ይላል። ኢትዮጵያና ሩስያ የሚመሳሰል ተከታታይ ስልጣኔ የነበራቸው ታሪካዊ ሀገራት ናቸው። ለብዙ ዘመናትም መልካም ግንኙነት አዳብረዋል። ሩስያ ብዝሀነት ያለባት ሀገር ብትሆንም ከዕድገት እንዳላገዳት ያነሳል። በኢትዮጵያ የሚስተዋለው በጎጥ እና ብሔር እርስ በርስ መናቆር ያሳዝነዋል። ለሀገር ዕድገትና አንድነት ከሩስያ መማር እንደሚገባ ያነሳል። ከምንም በላይ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ባይ ነው።
የሩቅ ቅርቧ ሞስኮ!
Jul 27, 2023 1518
(በአየለ ያረጋል)       ወትሮን ከዘንድሮ ያዋደዱ ሰማይ ታካኪ ሕንፃዎች መካከል ነው። እንደ ባሕር የተዘረጋው አርበ-ሰፊ ወንዝ እንደ ዝናር እየዞረ ይጥመለመላል። አይነተ ብዙ አያሌ ጀልባዎች በወንዙ ላይ ተሳፍረው ይርመሰመሳሉ። ሰዎች ደግሞ በጀልባዎቹ ተሳፍረው የወደዱትን ዕህል ውሃ እየተቋደሱ ይጓዛሉ። በወንዙ ግራ ቀኝ የሚገኙ ጥቅጥቅ ደን የሚመስሉ ዛፎች ሐመልማላዊ ገጽታ ለስፍራው ልዩ ውበት ደርቦለታል። ከላይ የመኪና፣ ከስር ፈጣን ባቡርን የሚሸከም ግዙፍ ድልድይ በወንዙ ላይ ተዘርግቷል። ከወንዙ ሰማይ ላይ የኬብል መኪናዎች ይከንፋሉ። የሰዎች የሐሴት ጥግ ይነበባል። ትዕይንቱ በወፍ በረር ዕይታ ሲቃኝ ዕፁብ ድንቅ ነው። ተለምዶ ከተፈጥሮ ተዛምዶ ሲታይ በአግራሞት ዕጅን በአፍ ያስጭናል። ይህ ውበት ያለው የሩቅ ቅርቧ ሩስያ ርዕሰ መዲና ሞስኮ ነው። ወንዙም ሞስኮቫ ነው! ሞስኮ አምባ ላይ ነኝ-መሀል ከተማ። ሁሉም ወለል ብሎ በሚታይበት አምባ ላይ በተተከለው አጉሊ መነፀር ሞስኮን እስከ ዕይታ አድማሷ በቀላሉ መቃኘት ይቻላል። የአያሌ ክፍል ዓለማት ስፍር ቁጥር አልባ ጎብኝዎች ስፍራው ላይ የተኮለኮሉት ለዚህ መሆኑ ነው። እኔም ወጉ ደርሶኝ ሞስኮቫ ወንዝ ራስጌ ተገትሬ ነገረ ሞስኮን ኪነ-ሕንፃ፣ ኪነ-ውበት፣ ስነ-ታሪክ መቃረም እና ሀሳብ ማውጠንጠን ቻልኩ። በሞስኮ ሰማይ ስር፤ ከሞስኮ አምባ በስተሰሜን ምዕራብ ክሬምሊን ቤተ መንግስት ግርማውን ተላብሷል። ብርቱ ውሳኔዎች መጸነሻና መወሰኛ ቁልፉ ቦታ-ክሬምሊን። ከክሬምሊን በስተቀኝ በኪነ ሕንፃው የሚወደሰው ባለወርቃማ ዕንቁላል መሰል ጉልላት የተጌጠው ቅዱስ ቤዚል ካቴድራል ይታያል። ከቀዩ አደባባይ ራስጌ! እነሆ ከሩቋ የሕልሜ ከተማ በአካል ተገኝቼ ሁለንተናዊ መልኳን በስሱ እየቃኘሁ ነው። አጋጣሚዎች የመንደር መፃዒ ዕድል ይወስናሉ-እንደ ሞስኮ። የግዙፉ ግዛተ-አፄ ሩስያ ርዕሰ መዲናነት ከታሪካዊቷ ቅዱስ ፒተርስበርግ ወደ ሞስኮ የዞረው ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በፈነዳው አብዮት አጋጣሚ ነበር። አብዮቱ ለሀገሪቷ ብቻም ሳይሆን ለዛሬዋ ሞስኮም አብዮት ወለደ። ሞስኮ ከተቆረቆረች 876 ዓመት ሆኗታል። በ1147 ነበር ምስረታዋ። ስሟም እንደ መቀነስ በታጠቃት ’ሞስኮቫ’ ወንዝ የተወሰደ ነው። በሂደት ሞስኮ መባሏን አስጎብኚዎቼ አጫውተውኛል። ክሬምሊን የሞስኮ አስኳል ነው። ትርጓሜውም የከተማ ውስጥ ምሽግ ማለት ነው። የሩስያ መዲናዋ ሞስኮ ከክሬምሊን ምሽግ ተነስታ ለዘጠኝ ክፍለ ዘመናት ተጉዛለች። ሞስኮ የሮማን ግዛተ-አጼ ዘመነ መንግስትን ስነ መለኮታዊ፣ ስነ መንግስታዊና ባህላዊ አሻራዎችን በማስቀጠሏ በታሪክ ሊቃውንት ዘንድ ከሮማን እና ከኮንስታንቲኖፕል ስልጣኔ ቀጥሎ ‘ሳልሳዊት ሮም’ የሚል ተቀጽላ ስም ተችሯታል።   ከሞስኮ ውብ መልኮች መካከል ‘ሰባቱ እህትማማቾች’ (The Seven Sisters) ይጠቀሳሉ። በኪነ-ሕንጻ ጥበባቸው የሚያስደንቁ ሰባት ቦታ ላይ የተገነቡ ሰባት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ናቸው። ከአስጎብኚዎቹ እንደተረዳሁት ሕንጻዎቹ በታላቋ ሶቬት ህብረት በዘመነ ዮሴፍ ስታሊን ከ1947 እስከ 1953 (እ.አ.አ) በአራት ዓመታት ብቻ የተገነቡ ናቸው። በወቅቱ በአውሮፓ ረጅም ሕንጻዎች ነበሩ። ትዕምርታቸውም የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ዘላለማዊነት መጠቆም ነበር። በርግጥም ዛሬም የሶቬት ሕብረት ጉልህ አሻራዎች ናቸው። ዛሬም የሚሰሩ በርካታ ኪነ-ሕንፃዎች እህትማማቾችን ለመምሰል ይጥራሉ። ሰባቱ እህትማማች ለተለያዩ ተቋማት ቢሮነት፣ በአፓርታማነት እና በሆቴል አገልግሎት እያገለገሉ ይገኛሉ። ለአብነም በ1755 የተመሰረተው ስመ ጥሩ የሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሌኒንግራድስኪያ (ሒልተን ሞስኮ) እንዲሁም ዩክሬን ሆቴል (ዛሬ ራዲሰንብሉ ሞስኮ) በእህትማማቾች ሕንጻዎች ላይ ይገኛሉ። ከሞስኮቫ ወንዝ ባሻገር ሉዥንኪ ኦሎምፒክ ኮምፕሌክስ ከነሞገሱ ይታያል። ስቴዲየሙ በ2018 ሞስኮ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ስታስተናግድ ቁልፍ ሚና ነበረው። ከስቴዲየሙ ባሻገርም 72 ሜትር የሚረዛዝሙ ወርቃማ ሚናሮዎች የተጌጠው የሞስኮ ካቴድራል መስጊድ ይስተዋላል።   መልክዓ-ሞስኮ ትዕይንቶች ለዕይታ አይሰለቹም። በሞስኮቫ ታሪካዊና ባለግርማ ሞገስ ድልድዮች፣ የቀዳማዊ ፒተር(ታላቁ ፒተር) ሰማይ ጠቀስ ሐውልት፣ ጎርክና መሰል ሰፋፊ የመሃል ከተማ ፓርኮች፣ ወጥ ከፍታ ያላቸው ውብ መኖሪያ ሕንጻዎች… ብቻ መልከ-መልካም ናት። ሩስያ በ20ኛው ከፍል ዘመን መባቻ የሶቫሊዝም አብዮት ከመፈንዳቱ በፊት በቄሳሮች (ጻሮች) በሚመራ ዘውዳዊ ስርዓት ለዘመናት ተዳድራለች። የፈረንሳይ መሪ ናፖሊዎን ቦናፓርት ሞስኮን በአንድ ወቅት በቁጥጥር ስር አድርጓት እንደነበር አስጎብኚዎች ይናገራሉ። በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነገሰው ቀዳማዊ ፒተር (ቀዳማዊ ጴጥሮስ) የሁሉም ሩስያ መስራች እና የመጀመሪያው አጼ ነው። የዘመናዊት ሩስያ መሀንዲስ ተደርጎ ይወሳል። ከቀዳማዊ ፒተር እስከ ዳግማዊ ኒኮላስ የሩስያ አፄዎች ዋና ቤተ መንግስት ቅዱስ ፒተርስበርግ ነበር። ድሕረ አብዮት የመንግስት መቀመጫ ሞስኮ ሆነች። አሁናዊ ሞስኮ በከተማ መሰረተ ልማቷና ስርዓቷ ከዓለማችን ውብ ከተሞች አንዷ ናት። የሩስያ ታሪክ ማዕከል፣ የቢሊየነሮች መደብር፣ የዝነኛ ጠቢባን፣ ሳይንቲስትና ታዋቂ ሰዎች መገኛም ናት። በመሰረተ ልማት እና በኑሮ ጥራቷም በፈረንጆቹ 2022 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዓለማችን ምርጥ ግዙፍ ከተሞች መካከል በምርጥነት መርጧት ነበር። ሞስኮ ከ13 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በመያዝ በህዝብ ብዛቷ ከዓለም ስምንተኛዋ ከተማ ናት። ምስጋና ለኢንተራሺያ (InteRussia Program 2023) የኢንተርሽፕ ስልጠና ይሁንና የሩቅ ቅርቧን ሞስኮ በቅጡ ተዘዋውሮ የመጎብኘት፣ ከጥበብ ድግሷ የመቋደስ፣ በውበቷ የመመሰጥ፣ ከታሪኳ የመቃረም ዕድል አገኘሁ። የሩስያው ዜና አገልግሎት ‘ስፑትኒክ’ ከአጋሮቹ ጋር ባመቻቸው በዚህ ፕሮግራም ከአፍሪከ ሀገራት 10 ወጣት ጋዜጠኞች ተሳትፈናል። እኔ ከሌሎች በተለየ ለሩስያ ቀረቤታ ያለኝ ያህል ይመስል ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የታላቁ ሩስያዊ ደራሲ አሌክሳንደር ፑሽኪን ቅድመ አያት በቀዳማዊ ፒተር ዘመን በጀግንነቱ በተመለመለው አብርሐም ሃኒባል ኢትዮጰያዊ መሆኑ ነው። በርግጥም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከሩስያ ጋር ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት በ1960ዎቹ የተጀመረ ሲሆን የኢትዮጵያ ግን ብዙ ዘመናት ወደኋላ ይርቃል። ሩስያን በስማበለው የመናፈቅ ጠኔም ነበረብኝ።   ለምን ሩስያን ለማየት ናፈቅሁ? ከታሪካዊ አጋጣሚዎች ተነስቼ ለሩስያ አወንታዊ ስሜት ካደረብኝ ውሎ አድሯል። በዘመናት ሸለቆ በዘለቀ የኢትዮ- ሩስያ ጽኑና ጥልቅ ወዳጅነት እና የሁለቱ ሀገራት የታሪክ ሂደቶች ተመሳስሎሽ ጥቂት ግንዛቤ ነበረኝና። ሁለቱ ጥንታዊ ሀገራት በዘውዳዊ ስርዓት (ሩስያ በቄሳር፤ ኢትዮጵያም በአጼዎች) ለዘመናት ተዳድረዋል። በየዘመናቱ አያሌ ኅይሎች ሁለቱንም ሀገር በተደጋጋሚ አጥቅተዋል። በአንድ ክፍለ ዘመን ውስጥ (ዓመቱ ቢለያይም) የሁለቱ ሀገራት ባላባታዊ ስርዓት በስር ነቀል አብዮት ተገርስሷል። አብዮቱ የንጉሳዊያን ቤተሰቦችን ለስደትና ለጉዳት በመዳረግ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ አድርሷል። ድሕረ አብዮት የእርስ በርስ ደም አፋሳሽ ዕልቂት ሩስያ በቦልሸቪክ እና መንሸቪክ (Bolshevik and Menshevik)፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በቀይና ነጭ ሽብር መልከ ብዙ ግፎች አስተናግደዋል። የሁለቱ ሀገራት ነገስታት ግንኙነት ለመመስረት ፅኑ መሻት እንደነበራቸው ይወሳል። ቀዳማዊ ፒተር ወደ ኢትዮጵያ መልክተኛ ለመላክ ሞክሮ እንዳልተሳካለት ይወሳል። ከኢትዮጵያ ወገንም ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ታሪካዊ የ’ሴቫስቶፖል’ መድፍን ስያሜ የሰጠው በክርሚያ ጦርነት መነሻ ነበር። አጼ ዮሐንስ አራተኛ በተመሳሳይ በተለይም ከክርስትና እምነት ጋር በተያያዝ ከሩስያ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ለመመስረት ፍላጎት እንደነበራቸው ይወሳል።   በመጨረሻም በ19ኛው ክፍል ዘመን መገባደጃ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና በቄሳር ዳግማዊ ኒኮላስ ዘመነ መንግስት ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተወጥኗል። በተለይም በ1880ዎቸ መጨረሻ ማሽኮቭ፣ ኤሊሴቭና ሌዎንቴቭ፣ አሌክሳንደር ቭላቶቪችና መሰል ሩስያዊ ተጓዦችና የስነ መልክዓ ምድር አጥኝዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሀገራቱን ግንኙነቱን ፈር አስይዟል። የኢትዮጵያና የሩስያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ትብብርም በ1880ዎቹ ጀምሮ እየተጠናከረ መምጣት ለባህል ዲፕሎማሲው የማይናቅ ሚና ነበረው። በአድዋ ድል ማግስት በ1897(እ.አ.አ) ሩስያ ኤምባሲዋን አዲስ አበባ ከፈተች። በ1895(እ.ኤ.አ) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩስያ የዲፕሎማሲ ልዑክ በፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ (የራስ ደስታ ዳምጠው አባት እና በኋላም በአድዋ ጦርነት የተሰዉ) የተመራ ልዑክ ልካለች። ፊታውራሪ ዳምጠው የሩስያ አጼዎች መናገሻ በሆነችው ቅዱስ ፒተርስበርግ ሲደርሱ ደማቅ መስተንግዶ ተደርጎላቸው ለአንድ ወር ቆይተው ቀጣይ ግንኙነት መሰረት መጣል ብቻ ሳይሆን ለአድዋ ጦርነት ወሳኝ ድጋፍ ሰንቀው ተመልሰዋል። በኋላም በኒኮላይ ሌዎንቴፍ (በኋላ ደጃዝማች) መሪነት አድዋ ጦርነት ላይ አይተኬ ሚና የተጫወቱ ከ40 በላይ የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኞች እንዲመጡ አስችሏል። በበርሊኑ ጉባዔ መላው የአውሮፓ ኅያላን አፍሪካን ለመቀራመት ሜዴትራኒያንን ሲያቋርጡ ሩስያ ግን በተዘዋዋሪም ቢሆን ከኢትዮጵያ ጎን ቆማ ደገፋለች። ይህ የሩስያ ቀዳሚው ውለታ ነበር። አጼ ምኒልክ በአውሮፓዊያኑ 1898 በፒዮተር ቫስሎቭ የሚመራ የሩስያ ልዑክ ደማቅ አቀባበል አደረጉ። ጄኔራል ኮንስታንቲን ሊሸን የተባሉት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሩስያ አምባሳደር (በወቅቱ ካውንስለር) አዲስ አበባ ውስጥ ሕይወታቸው እስኪያለፍ ድረስ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በጸና መሰረት ላይ እንዲቀጥል አይተኬ ሚና ተጫውተዋል። መካነ ቀብራቸው አዲስ አበባ ይገኛል። በርግጥ የዳግማዊ ምኒልክ እና የዳግማዊ ኒኮላስ ግንኙነት ሙሉ መተማመንና ልባዊ ወዳጅነት እንደነበረው የተለዋወጧቸው ደብዳቤዎች ዋቢ ናቸው። የደስታና ሀዘን ስሜቶችን ተጋርተዋል። ለአብነትም ዳግማዊ ኒኮላስ በራስ መኮንን ድንገተኛ ሕልፈት ማዘናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ልከዋል። በተመሳሳይ ዳግማዊ ምኒልክ በጦርነት በሩስያዊያን ላይ የደረሰ ጉዳትን አስመልክቶ በጀኔራል ሊሸን በኩል የማጽናኛ ሀዘናቸውን ልከዋል። ሀዘን ብቻም ሳይሆን ተጎጂዎችን ለመደገፍ በሚል ለሩስያ ቀይ መስቀል ገንዘብ ድጋፍ ልከዋል። ‘የአጼ ምኒልክ የውጭ ሀገር ደብዳቤዎች’ በተሰኘው የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ እንደተጠቆመው ዋና ፍሬ ነገሩ ይነበባል። “ሰላም ላንተ ይሁን፡፡ በሩቅ አገር የመስኮብ መንግሥት ልጆች ለንጉሣቸውና ለአገራቸው ደማቸውን በማፍሰሳቸው ብዙ አሳዘኑኝ፡፡ ጥቂትም እንኳን ቢሆን ለእነዚያ ለተጐዱት ልጆች ለመርዳት ብዬ ከዚህ ደብዳቤ ጋር አንድ አክሬዲልዩን ቼክ ስለመቶ ሺ ፍራንክ ልኬልሃለሁና ይህንን ቼክ ከመልካም ምኞቴ ጋር ለመስኮብ የቀይ መስቀል አለቃ እንድታደርስልኝ ይሁን።ይህን አሁን በመስኮብ መንግሥት የተነሳውን ጦር ጠላታቸውን አሸንፈው በቶሉ እንዲያልቅ እጅግ የከበሩ ታላቅ ወዳጃችን የመስኮብ መንግሥት ንጉሠ ነገሥት በጤና በሀብት እንዲያኖራቸው፣ለመስኮብ መንግሥት ሰላምና ረፍት እንዲሰጥ እግዚአብሔርን እንለምናለን”፡፡ የሁለቱን ሀገራት መልክዓ ምድራዊ ርቀት ያልገደበው መተሳሰብ ስሜት ያንጸባረቀ፤ የጋራ ዕጣ ፈንታ እንዳላቸውም የሚያመላከት ይመስላል። አጼ ምኒልክ ከሩስያ በስተቀር ኢትዮጵያ ሁነኛ ወዳጅ እንደሌላት እስከ መግለጽ ደርሰው ነበር። ይህ የኢትዮ-ሩስይ ወዳጅነት እስከዛሬ ሳይዛነፍ በመልካም ትብብርና መደጋገፍ ቀጥሏል። ሩስያዊያን ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታልን ጨምሮ በተቋማት ግንባታ አሻራቸውን አሳርፈዋል። በሁለተኛው የፋቪስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅትም በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ሲጣል የተቃወመች ሩስያ (የወቅቱ ሶቬት ህብረት) ነበረች። ከነጻነት በኋላም በሶቬት ህብረት ሩስያና ኢትዮጵያ ወዳጅነት ዳግም ተጠናክሯል። በአጼ ኅይለስላሴ ዘመነ ምነግስት በሰው ሀብት ልማትና መሰረተ ልማት ላይ መልካም የትብብር ጅምሮች ነበሩ። በዘመነ ደርግ ደግሞ ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ጋር ተዳምሮ ሁሉን አቀፍ ትብብር ነበር። በዘመኑ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በቀድሞዋ ሶቬት ህብረት ዘመን የነጻ ትምህርት ዕድል አግኝተው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።   እነዚህ ጥልቅ ታሪካዊና መንፈሳዊ ትስስሮች ሩስያን እንድናፍቅ ያደርገኛል። በሌላ በኩል ስለሩስያ ትልቅ ክብር እንዲኖረኝ ያደረገኝ በቁንጽል ንባቤ እንዲሁም በየዘመናቱ ሩስያ የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ስለሩስያ የሚሰጡት ፍቅርና አክብሮት ነበር። ለአብነትም ፊታውራሪ ተክለሐዋሪያት ተክለማርያም ይጠቀሳሉ። በራስ መኮንን ቤት ያደጉት ፊታውራሪ ተክለሀዋሪያት ገና በልጅነታቸው (በ19ኛው ክፍል ዘመን መጨረሻ) በራስ መኮንን አደራነት እንዲማሩ በሚል ከአንድ ሩስያዊ ጋር ወደ ቅዱስ ፒተርስበርግ አቅንተው ያደጉ፣ የተማሩና የኖሩ እንዲሁም በኋላ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካና ሀገር መንግስት ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና የነበራቸው፣ ከቀደምት ዘመናዊ ትምህርት ፈር ቀዳጆች መካከን የሚጠቀሱ ጉምቱ አሰላሳይ ምሁር ሰው ናቸው። በሩስያ እናቶች ቤት ያደጉት እነሁ ሰው ‘አውቶባዮግራፊ’ በተሰኘው ግለ ታሪክ መፅሐፋቸው እንደከተቡት ስለሩስያ ህዝብ ፍቅርና የሀገሩ ኅያልነት አንስተው አይጠግቡም። “ሩስያ ሁለኛ ሀገሬ ናት። ለእኔ የዋሉልኝ ውለታ መቼም ልረሳው አልችልም። ሩሲያኖች ሐሳባቸው ሰፊ፣ ሥራቸው ጠንካራ ነው: በማንኛውም ሙያ የሚያሽንፋቸው ኃይል ሊኖር አይችልም"ብለዋል። የቀድሞ ተማሪዎችም ቢሆኑ ስለሩስያ ህዝብ ያላቸው አክብሮት ልዩ ነው። በሩስያ አይረሴ ትዝታ የቋጠሩበት፣ ወጣትነታቸውን ያጣጣሙበት፣ ታሪክ፣ ስነ ጥበብና ስነ ጽሁፍ ከፍታቸው የሚደንቃቸው፣ የሀገር ፍቅር ስሜታቸው የሚያስቀናቸው ናቸው። ካነጋገርኳቸው መካከል ደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላቱ፣ አንጋፋው ዲፕሎማት በላይ ግርማይ፣ የእርሻ ባለሙያው አለማየሁ አሊ እና ዕውቁ ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ የሩስያ አየር ጸባይ ፈተናን ባይዘነጉም የሰዎችን ፍቅር፣ የሀገሩን ጥበብና ኅያልነት ግን አውስተው አይጠግቡም። ዛሬም ይናፍቃቸዋል። የተናፋቂዋ ሞስኮ ልዩ መልኮች የሚዲያ ትርክቶች እና የሞስኮ ዕውነታ ሞስኮ ከመምጣቴ ጥቂት ቀናት በፊት ዋግነር ቅጥረኛ ወታደሮች ሞስኮን ሊቆጣጠር እያመሩ ነው፤ የመንግስት ወታደሮችም በሞስኮ ጎዳናዎች እየተውረበረቡ ነው የሚለው ዜና የምዕራባዊያን ሚዲያዎች ሰበር ወሬ ነበር። ከአዲስ አበባ-ዶሞዴዶቮ አየረ ማረፊያ ደርሼ፣ ወደ ማረፊያ ሆቴል ሳመራ ያየሁት መልክ የጠበቅሁት አልነበረም። ወሬና ዕውነታው ፍጹም የተለየ ነበር። በሞስኮ ጎዳናዎች ቅንጡ ተሽከርካሪዎች፣ ጥቅጥቅ ጫካ የሚመስሉ ዛፎች፣ ቆነጃጅት ልጃገረዶች እንጂ ወታደር አልነበረም። (ከዚያም በኋላ አላየሁም)። ይልቁኑም በዕለቱ የገጠር ሰዎች (አርሶ አደሮች) ለመዝናናት ወደ ከተማ እየመጡ በመሆኑ ሞስኮ የቅንጡ መኪኖች ትራፊክ መጨመሩን ሰምቼ፤ የሀገሬን አርሶ አደር ሕይወት ሀሳብ አቃጭሎብኝ በቁጭት አስፈግጎኛል። የሞስኮ መልክና የመጀመሪያ ግምት ልዩነት የእኔ ብቻ ሳይሆን የሌሎች አፍሪካዊያን ጓዶቼም ትዝብት ነበር። የዚምባብዌ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ ሞቢሌ ችሊ ለረጂም ዓመታት በተለያዩ የምዕራባውያን የቴሌቪዥን መስኮቶች ስለሩስያ የሰማሁት ነገር አሉታዊ ነበር። በአካል ሩስያ መጥቼ ያረጋገጥኩት ነገር ቢኖር ግን የሩስያዊያን በጎ ማንነታቸው አለመተረኩም ነው” ይላል። የሞስኮ ሰላማዊነትና የንግድ ማዕከላት ድምቀት ጦርነት ውስጥ ያለች ሀገር አትመስልም። ‘እውን በሁለንተናዊ ማዕቀብ ያለች ሀገር ናት’ አሰኝቶኛል። የሶስት ሳምንታት ቆይታዬ ሞስኮ ቱሪስቶች መነሃሪያ መሆኗን ታዝቢያለሁ። በየመዝናኛ ቦታዎችና ታሪካዊ ስፍራዎች የሚርመሰበስ የተለያዩ ሀገራት ጎብኚዎች ብዛት የትየለሌ ነው። የአንድ ወገን የዓለም የሚደያ ቅኝት ወደ ብዝሀ ድምጽ ዓለም መለወጥ የሚሻበት ወቅት መሆኑን አፍሪካዊያን ጓደኞቼ ሲነግሩኝ ነበር። ተዓምረኛዋ ሞስኮ መልክዓ-ሞስኮ አጃይብ ነው። ‘አዲስ እረኛ’ እንዲሉ ከተማዋ ከመግባቴ በከተማዋ ስልጣኔ በመደመም ያስደነቀኝን ነገር ሁሉ በፎቶ ለማስቀረት እየሞከርኩ ነበር። ጠለቅ ባልኩ ቁጥር ግን አግራሞቴ እየጨመረ መጣና ሰለቸሁ። በየዕለቱ የሚወለወሉ ጎዳናዎች፣ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የፈሰሰባቸው አፓርታማዎች፣ በየፊናው የሚስተዋሉ ታሪካዊ ስፍራዎች፣ ድልድዮች፣ አዕዋፍት የሚርመሰመሱባቸው አረንጓዴ ስፍራዎችን ያስቀናሉ። ሞስኮ ተፈጥሮን፣ ታሪክን፣ ትውፊትንና ስነ ጥበብን አሰናስላ ያቃፈች ከተማ ናት። የምድራዊ ገነት ሽርፍራፊ ሳትሆን አትቀርም። አያሌ ታሪካዊና ውብ ከተሞች ሊኖሩ ቢችሉም እንደሞስኮ በተፈጥሮ የታደለ፣ በታሪክ የከበረ፣ በጥበብ የተቸረ ኩሉ በኩለሔ አይነት ከተማ ማግኘት ሊያዳግት ይችላል። ሞስኮ የሩስያ የባህል ሙዳይ፣ ሞስኮ የስነ ጥበብ ማዕከላት ማህደር፣ የቅርስና ታሪክ ቤተ መዘከር፣ የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት ማዕከል ናት። ሞስኮ በስርዓትና በቅጥ የተገነባች፣ በመገንባት ላይም ያለች፣ ትናንቷን በቅጡ የምትዘክርና የምታድስ ከተማ ናት። ዕጹብ ድንቅ ኪነ ሕንጻ ጥበብ ያላቸው የሞስኮ አብያተ ክርስቲያናት ብዛት ይገርማል። የቀዩ አደባባይ ወርቃማ ሽንኩርት ቅርፅ ጉልላት ተምሳሌትነት የያዙ አብያተ ክርስቲያናት የሞስኮ ድምቀት ናቸው። በየስጦታ ዕቃ ቤቶች እንደ ብሔራዊ ትዕምርትነት ይሸጣሉ። ኪነ ጥበብ እና ሩስያ በታሪክ ዘውድ እና ጎፈር ይመስላሉ። በ10ኛው ከፍለ ዘመን ክርስትና እምነት መስፋፋትን ተከትሎ መፋፋት የጀመረው የሩስያ ኪነ ጥበብ በቀዳማዊ ፒተር ዘመን ጀምሮ ያለማቋረጥ እምርታ እያሳየ ቀጥሏል። እናም በዘመናት የሩስያ ኪነ ጥበብ ቱርፋቶች ከመላው ዓለም የጥበብ ቤተሰቦችና ጎብኚዎችን መስህብ ሆነዋል። ሩስያዎች ደግሞ ታሪካቸውንና ባለታሪኮችን ያከብራሉ፤ በቅጡም ይዘክራሉ። ካስነደቁኝ የሞስኮ የኪነ ጥበብ ማዕከላት መካከል ትሬትያኮቭ ጋለሪ (Tretyakov Gallery) አንዱ ነው። 11ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ ከ180 ሺህ የሩስያ ስዕላት፣ ቅርጻ ቅርጾችና ግራፊክ ስራዎች የሩስያ የስነ ጥበብ ስራዎችን ያቀፈ ተቋም ነው። አስጎብኚዎቹ እንደሚሉት ጋለሪው ከ150 ዓመታት በፊት ፓቬል ትሬትያኮቭ በተባለ አንድ ባለጸጋ የስዕል ስብስቦች ቤት የነበረ ሲሆን በኋላ በባለቤቱ ፈቃድ ለመንግስት ተላልፎ የሩስያ የስዕል ጥበብ ማህደርነት ተደራጅቶ የዛሬውን ቅርጽ ይዟል። ጋለሪው የሩስያን ጥንተ ነገር፣ የሶቫሊስት እሳቤን፣ ተፈጥሮን፣ ስነ መለኮትን እንዲሁም ነገን በሚተነብዩ ጠቢባን የተሰሩ ኦርጅናል ስራዎች አቅፏል። የመላው ሩስያዊያን ኤግዚቪሽን ማዕከል (All Russian Exhibition of Achievements of National Economy) ሌላው አጃይብ ያሰኘኝ ተቋም ነው። በ1940ዎቹ የተገነባ በስፋት፣ በግንባታ ጥራትና ስነ ውበት ለመግለጽ ቃላት የሚያንስበት ማዕከል ነው። የቀድሞዋ ሶቬት ሕብረት ታሪክና ባለታሪኮች፣ የሀገሪቷን የቴክኖሎጂ ምጥቀት ቁልጭ ብሎ ይታያል። የሩስያ የሥነ ሕዋ ቤተ መዘከርም ከዚሁ ማዕከል ፊት ለፊት ይገኛል። ለዚህም ይሆናልይህ ስፍራ በጎብኚዎች ማዕበል ሲታመስ የሚውል ነው። ሞስኮ ዕልቆ መሳፍርት የሌለው የሐውልት ከተማም ናት። በሞስኮ ጎዳናዎች፣ አደባባዮች፣ በኪነ ጥበብ ማዕከላትና በንግድ ማዕከላት አካባቢዎች ሁሉ መልከ ብዙ የቅርጻ ቅርፅ ጥበብ ከፍታን የሚዋጁና ሞገስ ያላቸው ሐውልቶች ማየት ብርቅ አይደለም። ይህም የሥነ ጥበብ ከፍታቸውን ብቻ ሳይሆን የሩስኪዎችን የሀገር ፍቅር፣ ታሪክና ባለታሪክ የማክበርና የመዘከር ጽኑ መሻትን የሚያሳይ ነው። እናም ከሩስያ ሀገረ መንግስት ምስረታ ጀምሮ አሻራ ያላቸው መሪዎች፣ ጠቢባን፣ ሳይንቲስቶችና ምሁራን ስራቸውን የሚመጥን መታሰቢያ ቆሞላቸዋል። በርግጥ ሐውልት ብቻ ሳይሆን በጎዳናዎች፣ በሜትሮ (በከተማ ባቡር) ጣቢያዎች፣ በተቋማት ስም መሰየምም የተለመደ ነው። የሞስኮ ጎዳናዎች የአዘቦት ትዕይንቶች መቼስ የጎዳናዎች ስፋት፣ ጥራት፣ ውበት፣ የመሬት ስር እግረኛ ማቋረጫዎች፣ አረንጓዴያማ ተክሎች ለዐይን አይጠገቡም። ዋው! ብሎ ማለፍፍ ይቀላል። ከጎዳናዎች ውበት ባሻገር ግን መሰረተ ልማቱ ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የተቆራኘበት ከፍታ ጥግ ግሩም ነው። ሞስኮ ዲጂታላይዜሽን የአገልግሎትና ንግድ ስራና ኑሮን ያቀለለባት ከተማ ናት። ሞስኮ ውስጥ ከግለሰብ እስከ መንግስት ሕንጻዎች፣ መሰብሰቢያ ስፍራዎች፣ ጎዳናዎች በደህንነት ካሜራ አላቸው። ከ70 በመቶ በላይ የጸጥታ ችግፍ የሚፈታው ካሜራዎች ከቀረጹት ግብዓትን በመጠቀም ነው። በሞስኮ ጎዳናዎች የሲጋራ ጭስና አጫሽ ማየት አያስደንቅም። ሴትና ወንዱ፣ ወጣትና ሽማገሌ ብሎ በዕድሜና ጾታ ሳይገደብ ያጨሳል። ይህ ወቅቱ ክረምት ስለሆነ (በእነርሱ የፀሐይ ወቅት) እንጂ በበጋ የጭስ ምጣኔው በጣም እንደሚጨምር ሰማሁ። ግን ህዝቡ ስርዓት አለው፤ በማይጨስበት ክልክል ስፍራ ማንም አያጨስም። በኤሌክትሪክ ኅይል የሚሰሩ አይነተ ብዙ መንቀሳቀሻዎች (ስኮተርና ስኬች)፣ ባይስክሎች እና ሞተርሳይክሎች የሞስኮ መለያዎች ናቸው። የሞስኮ ከተሜዎች አጫጭር ርቀት ለመሄድ ከባስና ሜትሮ(ባቡርይ ይልቅ እነዚህን መንሸራቻዎች ይመርጣሉ። እነዚህ መሳሪያዎች የራሳቸው ፓርኪንግስ ስፍራም አላቸው። ከሌሎች ተከራይቶ ተጠቅሞ መመለስ ይቻላል። በተባበሩት መንግስታት የመሰረተ ልማት ጥራት ተመራጭ ከተሞች መካከል የተጠቀሰችው ሞስኮ፤ ‘የስማርት ሲቲ’ ምሳሌም ሳትሆን አትቀርም። ሩስያዊያን ባህሪያቸው ይገርማል። አብዝቶ ጭምቶች ናቸው። በፍጥነት ይጓዛሉ። ተሰባስበው አያወሩም። ቢያወሩ እንኳ ሳቅ፣ ሁካታ፣ ጫጫታና ጩኸት አያሰሙም። ሽማግሌ ባለበት መድረክ እንደማያወራ የሀበሻ ልጅ እንቅስቃሴያቸው ስነ ስርዓታዊ ነው። በሞስኮ ሜትሮ ውስጥ ቡድን ጮኸ ብሎ የሚስቁና የሚጫወቱ ሰዎች ካሉ ምናልባት እኛ አፍሪካዊያን ነን። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ከአናስታሲያ ጋር ስናወራ (በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሞስኮ ቅርንጫፍ ቢሮ ባልደረባ ናት) “እኛ ሩስያዊያን ሲያዩን ቁጡ እንመስላለን። ብዙ ደማቆች አይደለንም። ግን ከሳቅን ዕውነተኛ ሳቅ ነው የምንስቀው። አናስመስልም” ነበር ያለችው። ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ያረጋገጥኩትም ነገር ቢኖር ሩስኪዎች ከወደዱ ወደዱ ነው፤ ማስመሰል አያውቁም። ሩስኪዎች ዝምታ ብቻ ሳይሆን ሰው ላይ ትኩረት አያደርጉም። ከወጣት እስከ ሽማግሌ ጆሯቸው ላይ ማዳመጫ ሰክተው፤ ሌሎቹ ስልካቸው ሏይ አፍጥጠው ይንቀሳቀሳሉ። የሩስያዎች የስነ ጽሁፍ እና የስነ ጥበብ አሻራ መዳበር መሰረት የሆነው የማንባብ ባህላቸው ዛሬም አልጠፋም። በትራንስፖርት ቦታዎችን ጨምሮ ሩስኪዎች መፅሐፍትና ጋዜጣ ያነባሉ። በሆቴሎች ሳይቀር እንደ ቤተ መፃሕፍት በየሕንጻ ወለሎች ኮሪደር ትልልቅ የመፅሐፍት መደርደሪያዎች ተቀምጠዋል። የሆቴል ደንበኛ የፈለገውን መፅሐፍ ወስዶ አንብቦ መመለስ ይችላል። በጎዳናዎችና ሜትሮ ጣቢያዎች ሙዚቃ እየተጫወቱ ገንዘብ የሚሰጣቸው ሰዎች በብዛት ይታያሉ። ሰዎች ገንዘባቸውን የሚለግሱት የሙዚቃ ጥበቡን አድንቀው ወይስ ድጋፍ ጠያቂዎችን ተቸግረዋል በሚል ለልመና የሚሰጥ ይሆን የሚለውን አላረጋገጥኩም። ሌላው የሞስኮ ቆይታዬ አይጠበቄ ክስተት የቀኑና ሌሊቱ ርዝመት ወይም የፀሐይ ሥርቀትና ግባት ሁኔታ ነው። ሰዓቱ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ነው። በክረምትና በጋ ባህሪያት ግን የተገላቢጦሽ ነን። እናም ወቅቱ ክረምት መሆኑ ትልቅ አጋጣሚ ነበር። የሩስያ መለያ የሆነው አስቸጋሪ ቅዝቃዜ በበጋ ወቅት እንጂ በክረምት የለም። በክረምት ወቅት የሞስኮ ፀሐይ የምትጨልመው ዘግይታ፣ የምትሠርቀው ደግሞ ፈጥና ነው። ሞስኮ ብርሃኗ ሰፊና ረጅም ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባ ዶሮ በሚጮኸበት ከሌሊቱ አስር ሰዓት የሞስኮ ሰማይ የአህያ ሆድ መስሏል። አስር ሰዓት ተኩል ገዳማ የሩስያ ፀሐይ በሞስኮ ውብ ሕንጻዎች ላይ ጮራዋን ትፈነጥቃለች። ይህ ብቻ አይደለም። አዲስ አበባ ሕልም ላይ በሆነችበት፣ የአራዳ መንገዶች ኦና በሆኑበት ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ሞስኮ ምሽት ዓይን መያዝ ይጀምራል። ወደ ቤት ለመግባት የሚደረግ የሞስኮ ሰላማዊ ትርምስምስ ይጀምራል። በርግጥ የሞስኮ ሱፐርማርኬቶች 24 ሰዓት ክፍት ናቸው። በክረምት የሞስኮ ፀሐይ ሌሊት ወጥታ ሌሊት ትጠልቃለች። አንዱ ግርምቴ ነው። በተለይም ከሌሊቱ አስር ሰዓት ከእንቅልፌ ስባንን መስኮት ከፍቼ ቴራስ ላይ ቁጭ ብሎ ትዕይንተ ሞስኮን መቃኘት አስደስቶኛል።   ሰዓት አክባሪው ‘ሜትሮ’ የስርቻው ቤተ መንግስት ሜትሮ ማለት በሩስያኛ ከመሬት ግርጌ (ስርቻ) ወይም ባንቧ ማለት ነው። ይሄውም ከመሬት በታች በጥልቀት ተቆፍሮ የተገነባው የከተማ ውስጥ ባቡር መጠሪያ ቃል ነው። ሜትሮ የሞስኮ ሁለንተና ነው። በዕለታዊ ኑሮ ውስጥ በስፋት የሚወሳ ቃል ነው። የሜትሮ ተዘውታሪነት በመጓጓዣነት የአንበሳውን ድርሻ መያዙ ብቻ አይደለም። መሰረተ ልማቱ የተገነባበት መንገድ ከአገልግሎት ባሻገር ለከተማዋ ቅርስና መስህብ እንደሚሆን እሙን ነው። የሞስኮ ህዝብ ሜትሮን ከመኪናው ወይም ከከተማ ባስ ይልቅ በብዙ እጥፍ ይመርጠዋል። ምክንያቱም ሜትሮ በአማካይ 90 ሰከንዶች ልዩነት እየተጥመለመለ ይደርሳል። በመሳፈሪያ ቦታ የቆመን ተሳፋሪ በሙሉ አንዴ ጎርሶት እልም ብሎ በ90 ሰከንድ ልዩነት ሌላው ይከተላል። አገልግሎት ከጀመረ 70 ዓመታት ያስቆጠረው የሞስኮ ሜትሮ ሰዓት አክባሪና አስተማማኝ የትራንስፖርት ድርጅት ነው። ከመሬት በታች የሚርመሰመሰው ሜትሮ አስደናቂው ነገር መስመሮችን እና መሳፈሪያ ጣቢያዎች ግንባታ ጥራትና ውበት ነው። የሜትሮ ስነ ሕንጻ ጥበብ ግሩም ነው። ሜትሮ በንጹህነቱ፣ በስነ ጥበባዊ ውበቱ፣ በአጠቃላይ ገጽታው የተነሳ ‘የስርቻው ስር የሰፊ ህዝብ ቤተ መንግስት’ ይሰኛል። ሰዓት አክባሪው የስርቻው ቤት መንግስት ያልኩትም ለዚህ ነው። ታሪካዊ ዕውነታዎች እንደሚያስረዱት የመጀመሪያው ሜትሮ መስመር አገልግሎት ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን ዲዛይኑም የወደፊት ሶቬት ሕብረትን ፍላጎት ለማንፀባረቅ እንደሆነ ይወሳል። እንደ ክር የተጥለፈለፈው የዛሬው ሜትሮ ስራ ሲጀምር ‘ከሶኮልንኪ እስከ ፓርክ ኩልተሪ’ ጣቢያዎች የሚያካልል ቀይ መስመር ሲሆን ቀጥሎም ስሞሌንስካያ እስከ ኦክታኒ ሪያድ ባቡር ጣቢያዎች የሚሸፍን ሰማያዊ መስመር ነበር። እንደ ዕድል ሆኖ ካረፍኩበት ሆቴል እስከ ስልጠና ቦታዬ ለመድረስ ቀዩ መስመር ስለነበር የሜትሮ ጣቢያዎችን በቅጡ ለመጎብኘትና ለመደነቅ ችያለሁ። በርካቶቹ ቀደምት ጣቢያዎች ከዲዛይናቸው፣ ከታሪካቸው፣ ከቅርጻ ቅርሶች፣ ስዕላትና አጠቃላይ ስነ ውበት ሲታይ ‘የስርቻው ስር ቤተ መንግስት’ ብቻ ሳይሆን ቤተ መቅደስ የሚመስል ግርም ሞገስ አላቸው። እያንዳንዱ ጣቢያዎች የራሳቸው ልዩ አስደማሚ መልክና ማንነት አላቸው። ሜትሮ ግንባታው ጥልቀት ምስጢር የአፈሩ ሁኔታ እንደሆነ ይነገራል። በመስመር ቁፈራው ወቅትም በርካታ የከርሰ ምድር ወንዞች ተገኝተዋል። በርግጥም እንደ ጸበል የሚፈስ ውሃ ከአንድ ጣቢያ ላይ አይቻለሁ። ሜትሮን ለመጀመሪያ ጊዜ ለተመለከተ ዓይኑን መጠራጠሩ አይቀርም። ሜትሮ ውጫዊ ውበቱ ብቻም ሳይሆን ቴክኖሎጂካል ስርዓቱ አስደናቂ ነው። ከመካከላችን የተወሰኑት በተደጋጋሚ የመጥፋት ችግር አጋጥሟቸዋል። ምክንያቱም ሜትሮ ጣቢያዎች አንድ መውጫና መግቢያ ብቻ ሳይሆን እጅግ ውስብስብ የተሳሰሩ መንገዶችና አቅጣጫዎች አሉት። በተለይም አብዛኛው ጣቢያዎች ከሌሎች ጣቢያዎች ውስጥ ለውስጥ የተሳሰሩ በመሆኑ ነው። ይህን ለመለየት ሜትሮ ብዙ አማራጮች አሉት። ሜትሮ የተሰኘው የሞባይል አፕሊኬሸን (እንደ ጎግል ካርታ) ትልቁ መሳሪያ ነው። ከየት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት ከነአጭር አማራጮች የሚናገር። በየትኛው በር መስመር መቀየር እንደሚገባ፣ መስመሩ ምን አይነት ቀለም እንዳለው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በየፌርማታ ጣቢያዎች ላይም አቅጣጫ ጠቋሚ አማራጮች ያሉ ሲሆን ባቡሩ ውስጥ በራሱ በዲጂታል ስክሪን አመላካች አማራጮች አሉት። በዚህ ካልሆነ ግን ሜትሮ ከተማዋን በሶስት ቀለበት ይዞራታል። እያንዳንዱ ቀለበት ከሌላው እንደ ቀለበት በሁሉም አቅጣጫ እንደ ሸረሪት ድር የተሳሰሩ ነው። 397 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የሞስኮ ሜትሮ በስም፣ በቁጥርና በቀለም የሚለዩ 17 የሜትሮ መስመሮች፣ 265 የሜትሮ ጣቢያዎች(ፌርሜታዎች) አሉት። ወደ ሜትሮ ለመሳፈር እስከ 126 ሜትር የሚረዝሙ (740 ደረጃዎች) አሳንሰሮች (ኢሊቨተርስ) አሉት። የሞስኮ ሜትሮ በቀን እስክ 7 ሚሊዮን ሰዎችን እንደሚያጓጉዝ መረጃዎች ያሳያሉ። በነገራችን ላይ ሞስኮን ከሌሎች ከተሞችና ጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያስተሳስሩ ባቡር ሌሎች ናቸው። ለነዚህ ፈጣን ባቡሮች ስምንት የባቡር ጣቢያዎች ሞስኮ ውስጥ ይገኛሉ። ሞስኮ ሜትሮ ከሌሊቱ 11፤30 እስከ ሌሊቱ 7 ሰዓት የሚያገለግል፣ በሰዓት 42 ኪሎሜትር የሚሸመጥጥ ነው። ለአንድ ጉዞ ትኬት 60 ሩብል (0 ነጥብ 6 ዶላር ገዳማ) ይከፈላል። ክፍያውን በራስ አገዝ ማሽኖች ወይም በስልክ መክፈል የሚቻል ሲሆን ለሜትሮና ለህዝብ ባስ ለሁለቱም የሚያገለግል አንድ ካርድ አለ። ያ ካርድ ያልያዘ ሰው ወደ ሜትሮ ለመግባት መሿለኪያ በሮች አይከፈቱለትም። በርግጥ ሞስኮ እንኳን ሜትሮ የትም ቦታ ገንዘብ ክፍያ በጥሬ ሳይሆን ገንዘብ በተሞላ ካርድ (ከባንክ ሂሳብ ተቆራጭ በሚያደርግ) በኩል ነው። ለሻይ ሂሳብም በካርድ መክፈል ይሻላል። ዲጂታላይዜሽን ማለት እንዲህ ነው። መውጫ ስለሞስኮ መተረክ ‘ዓባይን በጭልፋ’ ነው። ከተማው ጥልቅና ሰፊ ነው። ይህ የእኔ ቁንጽል ማስታወሻ ነው። አፍሪካዊያንን ያስደነቀን፣ በቁጭት ያነደደን ጉዞ ነበረን። ሞስኮ የሀገር ፍቅርና ኩራት፣ ብሔራዊ ትዕምርት ፈጠራን፣ የቴክኖሎጂና ፈጣራ ከፍታና ሚናን፣ በራስ ባህልና ታሪክ መኩራትን ታስተምራለች። የዲጂታላይዜሽን ደረጃና የሩስያ የኢንቮርሜሽን ኮሚዩኒኬሸን ቴክኖሎጂ ምጥቀት ያስገርማል። ይህ በቢሮክራሲና በሙስና የታጠረ ኅላቀር አሰራር ላይ የተቸከለውን የአፍሪካ ሀገራትን አሰራር ለማዘመን ትልቅ የቤት ስራ የሚሰጥ ነው። ብዝሐ-ማንነት ቀጣይነት ያለው ስልጣኔ፣ ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ እንቅፋት አለመሆኑን አያሌ የብሔር ማንነቶችን ያቀፈችው ኢትዮጵያን መሰል በማንነት ተኮር ግጭት ሰለባ ለሆኑ ሀገራት ትልቅ ትምህርት ይሰጣል። ሀገር ዘላለማዊ ክብሯንና ሉዓላዊነቷን ለማስቀጠል በኢኮኖሚ መደርጀት፣ የጦር አቅሟን ማፈርጠም እና የሰው ሀብቷን በዕውቀትና ክህሎት ማልማት እንደሚገባት ከሩስያ በላይ ምሳሌ የለም። ሩስያ በራስ መልክ መዘመን፣ በራስ ጥበብ መራቀቅ፣ በራስ ፈጠራ የሰው ልጅን እንከን መቅረፍ እንደሚቻል በቋንቋቸው አሳይተዋል። በዓለም አቀፍ ስነ ፅሁፍ ምህዳር ውስጥ በመልማቱ የሚታወቀውና የራሱ ፊደል ያለው ሩስያኛ ቋንቋ ከቋንቋ ዕድገት ባሻገር ከቴክኖሎጂ ጋር እንዴት የተጣጣመበት ርቀት ያስቀናል። ኢትዮጵያን መሰል የራሳቸው ፊደል ያላቸው ሀገራት ቋንቋቸውን እንዴት ማልማት እንደሚችሉ ቁምነገር የሚያስጨብጥ ይመስለኛል።
በልጆቿ የጀግንነት ተጋድሎ ነፃነትን ሳትራብ ዘመናትን የተሻገረች-ኢትዮጵያ
Mar 1, 2023 12773
በቀደሰ ተክሌ (ሚዛን አማን ኢዜአ) ነፃነት የሰው ልጅ ከፈጣሪ ከተቸሩት ፀጋዎች አንዱና ዋነኛው ነው፤ በራስ ፈቃድ መወሰን፣ በራስ መሻት መከወንና በራስ ማንነት መኖር የሰው ልጅ የነፃነት አብነቶች ናቸው። ፈጣሪ ይህን ፀጋ የቸረው ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ከፈጣሪ የተቸረውን ነፃነት በራሱ በወገኑ የመነጠቅ ዕጣ ፈንታ መግጠሙ አልቀረም፤ ነፃነቱን በራሱ ወገን እየተነጠቀ በራስ ፈቃድ መወሰን የማይችል እንዲሆን ተደረገ። ጥቁር ሕዝቦች በተለይም አፍሪካውያን በነጮች ዘንድ የባርነት ግብር ተሰጣቸው። ቅኝ መግዛት ለእነሱ የኃያልነት መገለጫ አድርገው መረጡ። በዚህም አፍሪካን ተቀራምተው የራሳቸው አደረጉ። ያኔ ቅኝ ግዛት አስተዳደር ዘመናቸው በራስ እምነት መቆም፣ በራስ ባህል፣ ወግና ማንነት መኖር አይታሰብም። የሰው ልጅ ከቆዳ ቀለም ልዩነት በስተቀር በራሱ አምሳል ለተፈጠረው ሰው ተገዥ ይሆን ዘንድ አውሮፓውያን ከእኛ ውጭ ሰው ብለው በግዞት የያዟቸውን አገሮች ዜጎች የስቃይና የመከራ ህይወት እንዲያሳልፉ ፈረዱ። ከባዱን የባርነት ቅንበር በጫንቃቸው ላይ ጫኑ። ማንነታቸውን አስረስተው ያሻቸውን አደረጉ። የቅኝ አገዛዝ ገፈት ቀማሽ እንድትሆን ፅዋ የደረሳት የጥቁሮች ፈርጥ ኢትዮጵያ ግን እንዲህ በቀላሉ ለቅኝ ገዥዎች እጅ አልሰጠችም። ሰውን በሰውነቱ ብቻ የምታከብረው ኢትዮጵያ የልጆቿ ነፃነት በማንም ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ አልፈቀደችም።ኢትዮጵያን አፅንቶ ያቆማት በመከባበርና በአብሮነት ላይ የታነፀ ባህል፣ እሴት፣ ወግና ሥርዓት በባዕዳን እጅ ወድቆ ከሚከስም ''እኛ እንቅደም'' የሚል ጠንካራ የሀገር ፍቅርና ወኔ በአበራኮቿ ክፋይ ልብ ውስጥ እንደ አቶን እሳት ተንቀለቀለ። በፈጣሪያቸው እንጂ በምድራዊ ኃይል የሚመኩ አይደሉምና ቅኝ ሊገዛቸው የመጣን የውጭ ወራሪ ኃይል በጀግንነት ታግለው የኢትዮጵያን አንድነት፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅና ለማስከበር በአንድ ልብ ወስነው ቀፎው እንደተነካበት ንብ ወደ አውደ ገባሩ ተመሙ። ኢትዮጵያዊ አንድነትን ኃይል፤ ወኔና ሞራልን ትጥቃቸው አድርገው በዓድዋ ተራራ እስከ አፍንጫው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የኢጣሊያ ጦር ገጠመ። ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው ተፋለሙ፣ ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ለእኛ ለልጆቻቸው ነፃነትን አወረሱ፤ ለምንምና ለማንም የማይበገረው ኢትዮጵያዊ አንድነትን ትጥቅና ስንቃቸው ያደረጉትን የኢትዮጵያውያንን ከብረት የጠነከረ ክንድ መቋቋም የተሳነው ወራሪ የኢጣሊያ ኃይል ገሚሱ የጎራዴ እራት ሲሆን፤ ቀሪው ቁስለኛና ምርኮኛ ሆነ፤ ሌላው ደግሞ እግሬ አውጣኝ ብሎ ህይወቱን ለማትረፍ እግሩ ወደመራው ፈረጠጠ። ጅግኖች አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው፣ አጠንታቸውን ከሰክሰው የኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት አስጠብቀውና አስከብረው የፈጣሪ ልዩ ፀጋ የሆነውን "ነፃነት" ለዛሬው ትውልድ አስረከቡ። ኢትዮጵያም በትውልድ ቅበብሎሽ ሉዓላዊነቷምን አፅንታ የቆመች ነፃ አገር ሆና ቀጠለች። በዘመኑ የነበረውን ጥቁር ነጭን ማሸነፍ አይችልም የሚለውን አስተሳሰብ በሀገር ፍቅርና ወኔ ወራሪውን የፋሽሽት ኢጣሊያ ኃይል በጦር በጎራዴ አርበድብደው ድል በመንሳት ጥቁር ነጭን ማሸነፍ እንደሚች በቅኝ ገዥዎች የአገዛዝ አስተዳደር ስር ወድቀው ለነበሩ የዓለም ጭቁን ሕዝቦች በተግባር አረጋገጡ። በደማቸው ዘመን ተሻጋሪ ደማቅ የአርነት የታሪክ ድርሳን ጻፋ። በዘመን ጅረት የማይወይብ ታሪክ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በዓድዋ ተራሮች ላይ ተጻፈ። ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነትና የጀግንነት ተጋድሎ ነፃነት ሳትራብ ዘመናትን ተሻገረች። የነፃነት ዓርማ ሆና ለአፍሪካውያን ታየች። የዓድዋ ድል በቅኝ አገዛዝ አስተዳደር ስር ወድቀው ይሰቃዩ የነበሩ የዓለም ጭቁን ሕዝቦች በተለይም አፍሪካውያን የአርነት ትግል አድርገው የግፍ፣ የስቃይና የመከራ ቀንበርን ከጫንቃቸው ላይ አሽቀንጥረው እንዲጥሉ የፃነት ተምሳሌት ሆነ። በኢትዮጵያ የተለኮሰውን የነፃነት ችቦን አቀጣጥለው ብርቱ የአርነት ተጋድሎ አደረጉ፤ በዓድዋ ድል ከቅኝ ገዥዎች መዳፍ አፈተለኩ። የጥቁር ጭቁን ህዝቦች ነፃነት በዓድዋ የድል ገድል ለዓለም ታወጀ። አፍሪካውያን በራሳቸው ቋንቋ በነፃነት መናገር፣ በራሳቸው ባህል፣ወግና ሥርዓት እንዲሁም በራሳቸው መሪ ወደ ሚተዳደሩበት ምዕራፍ ተሸጋገሩ።የዓድዋ ድል ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነው በቀላሉ የተገኘ አይደለም። ኢትዮጵያውያውያ ለሀገራቸው ባላቸው ቀናሂነትና ከብረት በጠነከረ አንድነትና በጀግንነት ተጋድሎ ተጋምዶ በተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግል እንጂ። የዓድዋ ድል ዛሬም ወደ ጀመርነው የልማት፣የዕድገትና የብልፅግና ማማ ላይ የሚያደርሰን መሰላል ነው። ይህ የሚሆነው ግን የአንድነት ኃይል ከጀግንነት ወኔ ሳይነጣጠል ፀንቶ ሲቆይ ብቻ መሆኑ እሙን ነው። ቀደምት አባቶቻቸን የዓድዋ ከፍታን በክብር መቆናጠጥ የቻሉት ዘር እየቆጠሩ ሳይሆን በኢትዮጵያዊ አብሮነትና አንድነት ተጋምደውና ተሰናስለው ነው። ያላቸውን የአንድነት ኃይል ተጠቅመው ድልን ተጎናጸፉ። በየዓመቱ ዓድዋን መዘከር ራስን ''እኔስ ምን ማድረግ እችላለሁ?'' በሚል እሳቤ ከሆነ ዓድዋ ህያው ነው፤ ወደ አለምነው የስኬትና የብልፅግና ከፍታ ላይ የአንድነታችን ኃይሉ እንደሚያደርሰን እሙን ነው። እንደ ቀደምት አባቶቻችን በተጋመደ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር በኢኮኖሚው፣ ማኅበራዊ፣ በፖለቲካው ያሉ ፈተናዎችን በሀሳብ ልዕልና በማሸነፍ ለሌላ ድል መትጋት አለብን። አንድነታችንን በማፅናት በኅብረት ለኢትዮጵያ ከፍታ መትጋት ከሁላችንም ይጠበቃል።"ድር ቢያብር አንበሳ ያስር" እንዲ ሀገራዊ ብሂሉ ከተባበርን የማናልፈው ፈተና አይኖርም። አንዴ በጦርነት ሌላ ጊዜ በድርቅና በሌሎች መንስኤዎች ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች በአብሮነት ተጋፍጠን ድል እያደረግን መጥተናል። ፈተና ሁሌም ይኖራል፤ ማሸነፍና መሸነፍ ግን በእኛ ፅናትና ጥንካሬ ይወሰናል። ለወደፊትም የሚያጋጥመንን ፈተና አንድነታችንን አፅንተን ኅብረታችን ለሀገራችን ልማት፣ ዕድገትና ብልፅግና በማዋል በርካታ ዓድዋዎችን እንሰራለን። የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ጥቁር ጭቁን ህዝቦች የኩራት ምንጭ የነፃነት ዓርማ ነው። የዓድዋን ታሪክ መጠበቅና መደጋገም የእኛ የኢትዮጵያውን ኃላፊነትና ግዴታ ነው። ልዩነትን መስበክ ከኢትዮጵያዊ ከፍታ መሸራተት ነው። እኛነትን ረስቶ እኔ ማለት የዓድዋን ታሪክ መሸጥ ነው። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን እንጂ ተከፋፍለን የሰራነው ታሪክ የለም። የትናንት መልካም ስምና ዝና ከዘመኑ ጋር አብሮ ከፍ ከፍ እያለ አብቦ ማፍራት እንጂ፤ በልዩነት አስተሳሰብና አመለካከት ሊኮሰምን አይገባም። የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የሉዓላዊነት መገለጫ፣ የዓለም ጭቁን ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌ-ዓድዋ ለዘላለም በክብር ሲዘከር ይኖራል‼  
ሽሬ ወአክሱም (የአልፎ ሂያጁ ማስታወሻ)
Jan 25, 2023 9719
ሽሬ ወአክሱም (የአልፎ ሂያጁ ማስታወሻ) አየለ ያረጋል (ኢዜአ) መዳረሻዬ ሽሬ እንዳስላሴ ነው። ለዘገባ ሥራ ከባህርዳር- ጎንደር- ደባርቅ- ሸሬ መንገድ ከሚዲያ ባልደረቦች ጋር እየተጓዝኩ ነው። የጥምቀት ሙሽራዋ ጎንደር እየተኳኳለች ነበር። ደባርቅ ከመድረሴ በፊት ዳባት ትገኛለች-የደጃች አያሌው ብሩ ቁርቁር ከተማ። ደጃች አያሌው ትውልዳቸው በጌምድር ጋይንት ቢሆንም ግዛታቸውና ኑሯቸው ዳባት ነበር። ሞገደኛው ደጃዝማች አያሌው ብሩ በጎንደር ማኅበረሰብ ዘንድ ዝናቸው የናኘ ነው። ደጃዝማች አያሌው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ (ከልጅ ኢያሱ እስከ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥት) ታሪካዊ ክንውኖች ጉልህ ተሳትፎ አላቸው። አንዷን ብቻ ልምዘዝ። ራስ ተፈሪ ‘ንጉሠ-ነገሥት አጼ ኃይለሥላሴ’ ደጃች አያሌው የቅርብ ዘመዳቸውን ራስ ጉግሳ ወሌ ብጡልን (የንግሥት ዘውዲቱን ባለቤት) ወግተው የጎንደር ግዛት ‘ራስ’ ተብለው ለመሾም ቃል ቢገባላቸውም፤ ተልዕኳቸውን ተወጥተው ቃሉ ባለመፈጸሙ ደጃዝማቹ ከአጼው ጋር መቀያየማቸው አልቀረም። በዚህም:- "አያሌው ሞኙ፣ ሰው አማኙ ሰው አማኙ፣ የአያል ጠመንጃ፣ ስሟን እንጃ ስሟን እንጃ…” በማለት የጎንደር አዝማሪ አዚሟል። ዛሬም ይህ ግጥም የብዙ ባህላዊ ዘፈኖች አዝማች ነው። ደጃች አያሌው ብሩ ደፋር ናቸው ይባላል። ከአጼ ኃይለሥላሴ ጋር ቢቀያየሙም በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ሲመጣ ቅድሚያ ለአገሬ ብለዋል። ‘የተደበቀው ማስታወሻ’ በተሰኘው የዶክተር ሀራልድ ናይስተሮም (ትርጉም ገበየሁ ተፈሪ እና ደሳለኝ አለሙ) መጽሐፍ እንደተጠቀሰው ደጃች አያሌው “ንጉሡ እንደኛ ሰው ናቸው። ኢትዮጵያ ግን የሁላችንም ናት" ብለው ጦራቸውን መርተው በሽሬ ግንባር ዘምተዋል። ጉዟችን ቀጥሏል። ደባትን እያለፍን ነው። ‘እንኳን ደህና መጡ፤ ወደ ጭና ታሪካዊቷ ሥፍራ’ የምትለዋን ታፔላን በስተግራ እያየን ወደ ደባርቅ ገሰገስን። የሰሜን ተራሮች የብርድ ወጨፎ ያረሰረሳትን ደባርቅን ከማለፋችን ሊማሊሞ ጠመዝማዛ ቁልቁለት ተቀበለን። አስፈሪ የሊማሊሞ መልክዓ ምድር የደጋው ሰሜን ውርጭ እና የተከዜ በርሃ ኬላ ነው። ባለቅኔው ጸጋዬ ገብረመድህን “የሰማይ የምድሩ ኬላ፣ የየብስ የጠፈሩ ዋልታ አይበገር የዐለት ጣራ፣ አይመክተው መከታ ሊማ-ሊሞ አድማስ ሰበሩ፣ በጎማ ፈለግ ይፈታ? በትሬንታ እግር ይረታ?…” ብሎ የመኪና መንገድ ተገንብቶበት በማየቱ ግርምቱን የተቀኘለትም ለዚህ ይመስላል። ከሊማሊሞ ቁልቁለት በኋላ አዲ-አርቃይ፣ ዛሪማ፣ ማይፀብሪ እና ሌሎች የጠለምት ወረዳ ከተማዎችን አልፈን፤ የዋልድባ ረባዳማ አካባቢዎችን ተሻግረን ተከዜ ወንዝ ደረስን። የዚህን መንገድ እና ተከዜ ወንዝን ሳስብ የሀዲስ ዓለማየሁ ትዝታ አስተከዘኝ። የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ጦር የወገንን ጦር ፊት ለፊት መቋቋም ሲሳነው በሰው ልጆች ላይ ተደርጎ የማያውቅ መርዝ በጅምላ የፈጀበት አሳዛኝ ታሪክ ነበር። በተከዜ ወንዝ ውሃን በመመረዝ የወገን ጦር ያለቀበት ሥፍራ ነው። የተከዜ ሸለቆ በኢትዮጵያዊያን ደምና አጥንት ዋጋ የተከፈለበት ነው። ሀዲስ ዓለማየሁ በአንድ ዕለት የተመለከቱትን እንዲህ ጽፈውታል። “የተከዜ ውሀ እመሻገሪያው ላይ ሰፊና ፀጥ ያለ ነው። ታዲያ ያ ሰፊ ውሀ፤ ገና ከሩቅ ሲያዩት ቀይ ቀለም በከባዱ የተበጠበጠ ይመስላል። “ምን ነገር ነው፤ ምን ጉድ ነው?” እየተባባልን ቀረብ ስንል መሻገሪያው በቁሙም በወርዱም ከዳር እስከ ዳር ሬሳ ሞልቶበት የዚያ ሬሳ ደምና ፈርስ ነው። የሰው ሬሳ፣ የፈረስ እና የበቅሎ ሬሳ፣ ያህያ ሬሳ፣ ያውሬ ሬሳ፥ ሬሳ ብቻ! እግር ከራስ ራስ ከእግር እየተመሰቃቀለ እየተደራረበ ሞልቶበት፥ የዚያ ሁሉ ሬሳ ደምና ፈርስ ነው”። ይሉናል። ቀጥለውም “በእውነቱ እንዲህ ያለውን መሳሪያ ምንም ጠላት ቢሆን በሰው ላይ ለማዋል የሚጨክን ሰው፥ ሰብዓዊ ስሜት የሌለው፣ አለት ድንጋይ የተፈጠረበት መሆን አለበት፤ እንዲህ ያለውን መሳሪያ በሰው ላይ ማዋል ሰብዓዊ ህሊና ሊሸከመው የማይችል እጅግ ከባድ መሆኑን ዓለም ሁሉ ያወቀውና ያወገዘው በመሆኑ የኢጣሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ከማድረጉ በቀር “ሌላ መንግሥት በሌላ አገር ላይ አደረገ’ ሲባል ተሰምቶ የሚያውቅ አይመስለኝም” ብለዋል። ከተከዜ ባህር ማዶ ጉዞዬ ያገኘኋት ሌላዋ ታሪካዊ ሥፍራ እንዳባጉና ናት። እንዳባጉና የወገን ጦር ትልቅ ገድል የፈጸመበት ነው። ጀግኖች አባቶቻችን የጠላት ታንክ ሳያስፈራቸው የጠላት ጅምላ ጨራሽ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ተቋቁመው ጠላትን ድባቅ የመቱበት፤ ወደ አክሱም እንዲያፈገፍግ ያደረጉበት ሥፍራ ነው። “የጠላት ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በጦር ሜዳው ትንንሽ ቦምቦች አውቶማቲክ ጠመንጃ ይተኩስ ነበር። አቢሲኒያኖች ደግሞ ከጠላት ጋር ግብግብ ገጥመው ጉዳይም አልሰጡትም ነበር…” ይላል ዶክተር ሀራልድ ‘የተደበቀው ማስታወሻ’ በተሰኘ መጽሐፉ። ይህ አካባቢ በሀገር ፍቅር የነደዱ ኢትዮጵያዊያን ደም ያፈሰሱበት፣ አጥንት የከሰከሱበት፤ ለኢትዮጵያ መስዕዋትነት የከፈሉበት ነው። ይህ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዋጋ የተከፈለበት ቀጣና ነው። ቀኑ ተገባዷል። ጉዟችን እንደቀጠለ ነው። እኔም የማሽላ ማሳዎችን ግራ ቀኝ እየተመለከትኩ ለዕለቱ መዳረሻችን ወደሆነችው ሽሬ ከተማ ገባን። ሽሬ በትግርኛ ‘ሽረ’ ሲሉት ይደመጣሉ። በእርግጥ ሽሬን ለመጀመሪያ ጊዜ መርገጤ ነው። ዕለቱም ጥር ሥላሴ ነው። ሽሬ በጥር ሥላሴ ትደምቃለች፤ ሙሉ ስሟም ሽረ እንዳስላሴ ነው። የሽሬ ሥላሴ ጠበል ሽሬ ደርሰን ማረፊያችንን ያዝን። ጊዜው በጣም አልመሸምና ከተማዋን በቀላሉ መቃኘት ይቻላል። ሽሬ ሰፊና ደማቅ የዞን ከተማ ናት። ከመካከላችን የአንደኛው ባለሙያ ቤተሰቦች ሽሬ ነበሩና አስጠሩን። ለሥላሴ ጠበል ግብዣ። ባል እና ሚስቱ ከልክ በላይ መስተንግዶ አደረጉልን። ‘ጠብ እርግፍ አድርገው አስተናገዱን’ ማለት ይቀላል። እንግዳ መቀበል ነባር ኢትዮጵያዊ እሴታችን ቢሆንም ጦርነት ውስጥ ለቆየ አካባቢ የተለየ መልክ ነበረው። እንግዳ አቀባበላቸው በእርግጥም የመሃል አገር ሰው የናፈቃቸው ይመስላል። የተትረፈረፈ እህልና ውሃ አቅርበው በ’ብሉልን፤ ጠጡልን’ ተማጽኗቸው የተነፋፈቀ ቤተ-ዘመድ ግብዣ አስመሰሉት። የሥላሴው ጠበል የሸሬ ጠላ ቀረበ። የሸሬ ጠላ ሳስታውስ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ታወሱኝ። የወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምሀሩ ፕሮፌሰር ሽብሩ በዘመነ ደርግ በዕድገት በሕብረት ዘመቻ ተማሪዎቻቸውን ይዘው ሽሬ ዘምተው ነበር። በወቅቱ ታዲያ የሸሬ ጠላ ፍቅር ይዟቸው በየጊዜው ሲኮመኩሙ የተመለከቱ ሰዎች ‘ፕሮፌሰሩ ከጠፉ የሚገኙት ጠላ ቤት ነው’ ሲባሉ እንደነበር ‘ከጉሬ ማርያም እስከ አዲስ አበባ’ በተሰኘው ግለ ታሪካቸው አስፍረዋል። ከግብዣ መልስ ከማረፊያ ሆቴል ላይ ሆኜ ከተማዋን ስቃኛት ከጦርነት ድባቴ የተላቀቀች ይመስላል። የአመሻሽ ሕዝቡ እንቅስቃሴም ሆነ እስከ ሌሊቱ አጋማሽ የሚሰሙ የመዝናኛ ቤቶች ሙዚቃዎች የከተማዋን አሁናዊ መልክ የገለጠልኝ ነበር። ንጋት ላይ በቁርስና ቡና ሰዓታት ከሰዎች ጋር መስተጋብሬ ጀመረ። በጦርነት አዙሪት የከረመችው ሽሬና አካባቢው ኑሮ እጅጉን የከበደ ነበር። መልከ-ብዙ ማህበራዊ ቀውሶች አስተናግደዋል። አሁናዊ ምላሻቸው “ተመስገን፤ ያ ሁሉ አለፈ” የሚል ነው። ገበያው ተረጋግቷል፤ ማህበራዊ ኑሮ ተመልሷል። ድህረ-ሰላም ስምምነት ለሽሬ ነዋሪዎች ሁለንተናዊ እፎይታን አንብሯል። ከቀናት በኋላ በአክሱም የታዘብኩትም እንዲህ ነው። ኑሮን ያቀለለው የተቋማት አገልግሎት ጅማሮ በመጀመሪያ ዘገባ ስራዬ መሰረተ ልማትን አገልግሎት ቃኘሁ። ባንክ፣ ቴሌ፣ ሆስፒታል… መሰሎቹን። ተጠቃሚዎችንም፣ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ስራ ሃላፊዎችንም አነጋገርሁ። ከሰላም ስምምነቱ ማግስት ጀመሮ ተቋማቱ ወደስራ መመለሳቸው ከሁለንተናዊ ችግር እንደታደጋቸው ያነሳሉ። በትራንስፖርት እየተንቀሳቀሱ፣ በኤሌክተሪክ ስራዎቻቸውን እየከወኑ ነው። ለሁለት ዓመታት የተቋረጠው አገልግሎት አቅርቦት እና የአገልግሎት ፈላጊዎች ፍላጎት ግን አሁንም ሙሉ በሙሉ ተመጣጣኝ እንዳልሆነ የተጠቃሚዎችም፤ የአገልግሎት ሰጭዎችም ሀሳብ ነው። በሽሬ ስሁል ሆስፒታል የተመለከትኳቸው፤ ያነጋገርኳቸው፤ ከታዳጊዎች እስከ አዛውንት ዕድሜ ያሉ ህሙማን የሰላም አየር ማግኘታቸው የሕይወታቸው ዑደት እንዲቀጥል አድርጓል። ድንገተኛም ሆነ ነባር ህመም ያለባቸው ሰዎች በነጻ እየታከሙ ነው ያገኘኋቸው። ሰላም ከሌለ መታከም ቀርቶ በቅጡ ማስታመም፤ በወጉ መቀበርም እንደማይቻል ገልጸውልናል። የጤና፣ የባንክና የቴሌኮም አገልግሎት የግብዓት ክፍተቶች የማሟላት ሰራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም በፌዴራል ደረጃ በየተቋማቱ የተመደቡ አስተባባሪዎች አረጋግጠውልኛል። የጸጥታ አካሉና የህብረተሰቡ ትብብርም የሚያስቀና እንደሆነ ግለሰቦችም፤ የጸጥታ አካላትም ነግረውኛል። አክሱም ጺዮን ማርያም፣ ሽሬ ስላሴ ንግስ፣ የጥምቀት በዓላት ከሶስት ዓመታት በኋላ በአደባባይ ታቦት ወጥቶ ተከብሯል። የፌዴራል ፖሊስ ተወካዮችም ይህንኑ ነው ያረጋገጡልኝ። የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከከተማ ነዋሪዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ቤተሰባዊ የሆኑ ይመስላል። እንቅስቃሴያቸውም የሰላማዊ ቀጠና መልክ ያለው ነው፤ ዩኒፎርም ከመልበሳቸው በስተቀር ጀሌያቸውን ይንቀሳቀሳሉ። ይህ ደግሞ መተማመን ከመፍጠር ባለፈ ጦርነት ውስጥ ለቆየ ማህበረሰብ ከስነ ልቦና ጫና እንዲላቀቅ አይነተኛ ሚና እንደላው ይሰማኛል። ኢ-መደበኛ የሽሬና አክሱም ወጎች ያረፍኩበት ሆቴል ባለቤት ‘አደይ’ ተግባቢ ናቸው። ደግ እናት ይመስላሉ። ከገባን ጀምሮ ‘ጠላ ተጎንጩ፤ ቡና ጠጡ’ ጭንቃቸው ነው። ሁለት ቀን ቡና አስፈልተውልናል፤ ጠላ አቅርበው ዘክረውናል። ይህ ሁሉ ሲሆንም ለከተማው እንግዳ መሆናችንን እንጂ ስለሙያችንም ሆነ ስለሌላ ማንነታችን አያውቁም ነበር። ብዙ መጨዋወትና ውሎ አዳር በኋላ ነው ጋዜጠኛ ስለመሆናችን ያወቁት። አደይ ተጨዋች ናቸው። አማርኛ ያዝ ቢያደርጋቸውም ጨዋታቸው ‘ኩርሽም’ ነው- ተሰምቶ የማይሰለች። በአጋጣሚ ‘ሰለክላካ’ ስለምትባለዋ ታሪካዊ ሥፍራ ጠይቄያቸው እያወጋን ነበር። ‘እንደእናንተ ወጣቶች ሳለን ‘ሰለክላካን ያላዬ ሸዋን ያመሰግናል’ ይባል ነበር። ታዲያ አንድ የሸዋ ሰው መጣና ሰለክላካን አየና ‘በቃ ይቺ ናት’ ሰለክላካ’ ብሎ ተገረመ” ብለው አሳቁን። (የፍቅር እስከ መቃብር መሪ ገጸ-ባህሪው ‘በዛብህ’ ወደ ዲማ ጊዮርጊስ ሄዶ ‘የዲማ መልኳ እና ዝናዋ’ ተጣርሶበት እንደተገረመበት ቅጽበት መሆኑ ነው)። አደይ የተጀመረው ሰላም ፍጹም ምሉዕ ሆኖ ወደ ቀደመ ኢትዮጵያዊ መልካችን የምንመለስበት ጊዜ እንዲመጣ ይሻሉ። ከጦር-ነት ወደ ሰላም-ነት! ቆንጂዬዋ ፊዮሪ የኮሌጅ ተማሪ ነበረች። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ጀምሮ በኋላም በጦርነት ሳቢያ ትምህርቷን ካቆመች ሦስት ዓመታት ሆኗታል። ጦርነቱ ከቆመ በኋላ የጀበና ቡና ጀምራለች። ደንበኞቿ ሰብሰብ ብለን እንቀመጣለን። ፊዮሪ ከስኒ ማቅረቢያዋ ላይ አነስተኛ ጀበናዋን፤ የሚያማምሩ ስኒዎቿን እና መዓዛው ከሚያውድ የዕጣን ማጨሻዋ ጋር ሰድራ ይዛ ትቀርባለች። ከመካከላችን ካለው ጠረጴዛ ላይ ታስቀምጥና እርሷም ወንበር ይዛ ከመካከላችን ትቀመጣለች። ቡናው እስኪሰክን ጨዋታዋን ታስኮመኩመናለች። ቡናው ከሰከነ በኋላ ቡናዋን ቀድታ ለእያንዳንዳችን በእጃችን እያነሳች ትሰጣለች። በሽሬ ቡና የሚቀርበው በዚህ መልክ ነው። ለፊዮሪ እና መሰሎቿ ጦርነቱ ክፉ ጠባሳ መጣሉ፤ ተስፋቸው ላይ መጥፎ አሻራ ማስቀመጡን ታነሳለች። አሁን ግን ብሩህ ተስፋ ሰንቃለች። ስለነገዋም “ሰላሙ ይዝለቅልን፤ ትምህርቴን ለመቀጠል እመኛለሁ” ትላለች። አክሱም ከሽሬ በስተሰሜን 60 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ከሽሬ አክሱም ስንንቀሳቀስ ከጥምቀት ዕለት በስተቀር ገበሬው የግብርና ሥራዎቹን እየከወነ ነበር። አርሶ አደሩ ያርሳል፤ መስኖውን ያለማል። የተዘራውን ውሃ ያጠጣል። የበቀለ ቡቃያውን ይኮተኩታል። ከጦርነት ወደ ልማት መዞሩን ዐይኔ ታዝቧል። በጥምቀት ዋዜማ፤ የከተራ በዓል ዕለት ሁለት ጎራማይሌ የረፋድ ትዕይንቶችን ላንሳ። ከአክሱም ከተማ ወደ አድዋ እና ሽሬ መገንጠያ አካባቢ ሰፊ የቀንድ ከብት ገበያ ነበር። እውነተኛ የዓመት በዓል ገበያ መልክ ያለው ትዕይንት ነበር። በተለይም የፍየል ዋጋ በተመጣጣኝ ዋጋ እየተገበያዩ እንደነበር ሰምቻለሁ። ታሪካዊቷን አክሱም ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ የረገጥኳት/የተሳለምኳት ከአራት ዓመት በፊት በ2011 ዓ.ም ይመስለኛል። ከገበያው ቀጥሎ በታቦተ-ጽዮን መገኛዋ ርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ደጅ፣ በጥንታዊያኑ የአክሱም ሐውልት መገኛ አደባባይ ነበር። ከጽዮን በስተምዕራብ በአርባቱ እንሰሳ በኩል፤ በቅዱስ ያሬድ ዋርካ… አድርጌ በጽዮን ዋናው በር ደረስኩ። ማራኪ የአክሱም የኮብልስቶን መንገዶች ኦና ናቸው። የወትሮው ግርግር ናፍቋቸዋል። ከጽዮን ቅጥር ግቢ በዋናው በር በስተውጭ አነስተኛ እና ብቸኛ ዋንዛ በኮብልስቶን መሃል ነበረች። ዛሬም ለምልማ አለች። በዚህ አካባቢ ድሮ የነጭ ጎብኚ ጋጋታ፣ የጽዮን ደጅ ጠኚ ምዕመን… የተጨናነቀ ነበር። እንደ ድሮው የፎቶ አንሺ ግርግር፣ የአክሱም መስቀል ቀርጸው የሚሸጡ ወጣቶች ጫጫታ የለም። ይልቁንም እርጥባን የሚሹ አቅመ ደካሞችና ህፃናት ነበሩ። ጦርነት የሥፍራዋን መልክ አጠይሞታል። ያም ሆኖ ከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ በኩሉሄ ባይባልም ወደነበረበት እየተመለሰ ነው። የግልም ሆነ የመንግሥት ባንኰች ሥራ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ከአክሱም ሐውልት ወደ ሌላ ሰፈር አቀናሁ። ትርሐስ ገና ታዳጊ ልጅ ነች። ጠይም፤ ስርጉድ፣ ሳቂታና ተረበኛ አይነት ልጅ ነች። እንደ ሽሬዋ ፊዮሪ መንገድ ዳር የጀበና ቡና እየሰራች ነው። ከሩቅ የመጣን እንግዶች መሆናችንን ስታውቅ፤ ደስታዋ ከገጿ ይነበብ ነበር። ያለፉ ጊዜያትን ሰቆቃ አጫወተችን። ስለቀጣይ ዕጣ ፈንታዋ እና ዕቅዷ ስታወራ ትቆይና “የሰው ልጅ ግን በጣም ከሃዲ ነው። ከወራት በፊትኮ ስለቢዝነስ አላስብም ነበር። መቼ እሞታለሁ እንጂ” ብላ ራሷን ትወቅሳለች። ወደ ሰማይ አንጋጣ ፈጣሪዋን ታመሰግናለች። ጦርነት ተራውንም ሕዝብ ለመልከ-ብዙ ቀውስ ዳርጎት እንደቆየ ታነሳለች። ዛሬ ሁሉ አልፎ ሰላም መውረዱ ለመጨዋወት መብቃቷ ለእርሷ ትልቅ ብሥራት ነው። ይህ ለትርሐስ ብቻ ሳይሆን ለመላው አክሱማዊያን መሆኑ እሙን ነው። አክሱም ከተማ በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ከዋለችበት ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ በሻለቃ አዛዥነት የተሰማራ የፌደራል ፖሊስ አባልም ያጋጠመውን አሳዛኝ ገጠመኞች አጫውቶኛል። ጦርነቱ ቢራዘም ኖሮ በተራው ሕዝብ ላይ ምን ያህል የከፋ ጉዳት ይደርስ እንደነበር በአሳዛኝ ሁኔታ ገልጾልኛል። አክሱሞች ያን ሁሉ አልፈው ሰላም አየር ነፍሶ፣ ከስጋት ቆፈን ተላቀው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሰዋል። የዛሬ ሳምንት ሰርክ(11 ሰዓት) ላይ አክሱም የከተራ በዓል በድምቀት አክብራለች። ታቦተ-ጽዮን ወደ ባህረ- ጥምቀቱ ስትወርድ፤ ወግና ሥርዓቱ ተጠብቆ፣ ሕዝቡ በሀበሻ ነጫጭ አልባሳት፣ ካህናት በልብሰ ተክህኖ ደምቀው … እየተከወነ ነበር። አንዲት እናት ለአማርኛ ተናጋሪ በቀረበ አነጋገር እያለቀሱ ታቦት እየሸኙ ነው። ትኩር ብዬ ሳያቸውም ዕንባቸው ዱብ ዱብ ይላል። “ከዚያ ሁሉ መከራ አልፎ ለዚህ በቃን፤ ተመስገን” እያሉ እልልታውን ያቀልጡታል። በደስታ እያነቡ ነበር። ይህ ስሜት የብዙኃኑ አክሱማዊያን እናቶች እንደሆነ መገመት ቀላል ነው። አክሱም በኮቪድ እና በኋላም በጦርነቱ ምክንያት ባህረ-ምቀት ታቦት ወጥቶ ሲከበር ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። ከወትሮው በተለየ ድምቀትና ውበት በሰላምና በደስታ፤ በአደባባይ እልልታና ሆታ በማክበራቸው ልዩ ስሜት ፈጥሮባቸዋልና! እናም በአክሱም የከተራ ሆነ የበዓለ-ጥምቀት ክብረ-በዓላት በሰላም ስምምነቱ ማግስት በድምቀት ተከውኖ አለፈ። የሃይማኖት አባቶቹም ሆኑ ምዕመኑ በሰጡት ቃለ መጠይቅም የዘንድሮው ክብረ-በዓል ካለፉት ዓመታት ነባራዊ ሁኔታ ጋር እያነጻጸሩ፤ ትልቅ ብሥራትና መልክ እንዳለው ገልጸዋል። ሰላም እንዲጸና፤ ነባር ኢትዮጵያዊ አንድነትና መተባበር እንዲመለስ ጽኑ መሻታቸውን ነግረውናል። በበጎ ቀን የማውቃትን አክሱም፤ ከረዥም ጊዜ በኋላ አሁናዊ መልኳን ታዝቤ፤ የነገ ትዝታ ሰንቄ ተመለስኩ!! ሰላም ለኢትዮጵያ!!
ገና እና ላሊበላ
Jan 5, 2023 1137
(ብርሃኑ አለማየሁ) በኢትዮጵያ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ወይም ገና አንዱ ነው። በዓሉ በሃይማኖት ተቋማቱ ሃይማኖታዊ ስርዓትና ትውፊት መሰረት ይከበራል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በሚከናወኑ የዝማሬና የመንፈሳዊ የጸሎት መርሐ ግብሮች አማካኝነት በዓሉ በልዩ ሁኔታ ይከበራል። የገና በዓል በቤተክርስትያኗ ስርዓትና ትውፊት በተለየ ሁኔታ ከሚከበርባቸው ስፍራዎች ቀዳሚው በሰሜን ወሎ ዞን አገረ ስብከት ስር የሚገኘው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ነው። የላሊበላ አካባቢ የመሬት አቀማመጡ ለግብርና ባይጋብዝም፤ ፍሬያማነቱ  በታላላቆች የጥበብ ንቃት የሚለካና ምርታማነቱም ባኖሩት የኪነ-ህንጻ ርቀት የሚመነዘር እንዲሆን አድርጎታል። ጥልቅ የኪነ ህንጻ ጥበብ ያረፈባቸው ዘመን ተሻጋሪዎቹ  የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ፤ የቆየውን ሀይማኖታዊ ህይወትና ክንዋኔ ፈጣን በሆነው የዓለም ለውጥ ሳይበረዝ እንዲቀጥል ጠባቂ በመሆንም ወደር አይገኝላቸውም ፡፡ ቅዱስ ላሊበላ /ከ1180­-1207 ዓ.ም/ ከአባቱ ጃን ስዩም እና ከእናቱ ኪርወርና ይባላሉ። በተወለደም ጊዜ በንብ ስለ ተከበበ እናቱ ማር ይበላል ለማለት "ላል ይበላል" ብላለች። በአገውኛ “ላል” ማር ማለት ነው። ከዚህ የተነሳ ስሙ “ላልይበላ” ተባለ። ቀደም ሲል ሮሀ በአሁኑ አጠራር ላሊበላ በመባል የሚታወቀው ቦታም ስያሜውን ያገኘው እንደ እ.ኤ.አ ከ1181-1221 ነግሶ ከነበረው የመጀመሪያው የዛግዌ ስርወ - መንግስት ንጉስ ላሊበላ መሆኑ ይነገራል፡፡   በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት መሰረት የቅድስና ማዕረግ ከተሰጣቸው ነገሥታት መካከል አጼ ላሊበላ አንዱ ሲሆን፤ የተወለደበት ዕለት ታህሳስ 29 መሆኑን ገድሉ ይገልጻል። በዚህም የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላልይበላ የልደት በዓል በላልይበላ በጥምረት ይከባራል። የበዓሉ በጥምረት መከበርን አስመልከቶ ከታህሳስ 28 ከምሽት 2 ሰዓት ጀምሮ የሚካሄደው ሰርዓተ ማኅሌትና ዝማሬ ከዓለት ወደታች በሰው እጅ የተፈለፈሉትን አብያተ ክርስትያናት በተመስጦና በአድናቆት ለሚመለከተው ጎብኚ ሌላ ማራኪ ትዕይንት ይሆንበታል። በዓሉ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ በሆነው ቤተ መድኃኔዓለም የሚከበር ሲሆን፤ የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች በተባለው መጽሐፍ እንደተገለጸው  ይህ ቤተ መቅደስ ቅዱስ ላሊበላ በሮሐ ከዓለት ከፈለፈላቸው አብያተ ክርስቲያናት አንዱ ነው። በዓሉም በዚህ ቤተ መቅደስ በአካባቢው ካሉ አብያተ ክርስቲያናት ከተውጣጡ ከ500 በላይ አገልጋዮች ህብረ ዝማሬ ማህሌት (ምስጋና) የሚታሰብ ይሆናል። አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ መጽሐፋቸውና በዓሉን አስመልክቶ ከታተመው ሐመር መጽሔት እንደተመለከተው የገና በዓል አከባበር የሚጀምረው ከታህሳስ 23 (በዓለ ጊዮርጊስ) አንስቶ ሲሆን፤ እስከ ታህሳስ 29 ድረስ ይቀጥላል። የማኅሌቱን ስነ ስርዓት ስንመለከት አንድ ጊዜ 12 ገደማ ጥንግ ድርብ የለበሱ በአንድ በኩል ደግሞ ጥቁር ካባ የለበሱ ማኅሌታውያን እያሸበሸቡ ስርዓተ ማኅሌቱን ያከናውኑታል። ማዕጠንት የያዙ 4 ካህናትና ከ8 ያላነሱ ዲያቆናት ወርቅ ካባ ለብሰው፣ የወርቅ አክሊል ደፍተው፣ የወርቅ መስቀል ይዘው መለከት እየነፉ ዙሪያውን በመዞር ማህሌቱን ያጅቡታል። ይህ ታህሳስ 28 ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀመሮ የሚከናወነው የማኅሌት ሰርዓት ሌሊት 10 ሰዓት ላይ በሰርዓተ ቅዳሴ ይተካና ታህሳስ 29 ቀን ከ12 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ ከ11ዱ የላልይበላ ቤተ መቅደስ የተውጣጡ ሊቃውንት የበዓሉን ያሬዳዊ ዜማ ለማጀብ ወደ ማሜ ጋራ /ቤዛ ኩሉ ዓለም ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበት ቦታ/ ይወጣሉ። ልክ አንድ ሰዓት ሲሆን፤ ከላይና ከታች የሚሰለፉ ካህናት ቦታቸውን ይይዙና እስከ 4 ሰዓት በሚፈጅ ክንውን እየተቀባበሉ ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ' የዓለም መድሃኒት ዛሩ ተወለደ የተባለውን ወረብ ያቀርባሉ። የበዓሉን አከባበር በላሊበላ ልዩ የሚያደርገው አንዱ ይህ “ቤዛ ኩሉ ዓለም" የሚባለው የቀለም ዓይነት ሲሆን፤ በወረቡ ትርጓሜ መሰረት ዝማሬው ለአገር፣ ለወገን፣ ለምድር ሰላም በረከት የሚጸለይበት ነው። ከትርክቱም በላይ ዛሬም ድረስ ተአምራዊ ጥበባቸው ያልተፈታው የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ዓለምን ማስደመማቸው እንደቀጠለ ፤ ታላቅነታቸው እንደቀደመ፤ ቅድስናቸው እንደጸናና  የበርካታ ሰዎችን የመንፈስ ቀልብ እንደገዙ ከሚታሰበውም በላይ ልቀው የዘለቁ ናቸው።  የገናን በዓል በላሊበላ ለመታደም እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናቱንና መንፈሳዊ የበዓል ሥርዐቱን ለመጎብኘት  የሃይማኖቱ ተከታዮችና በርካታ አገር ውስጥና የውጭ አገር ጎብኚዎች ወደ ላሊበላ ያቀናሉ። ላሊበላ ከተማ አብዛኛውን የኢኮኖሚ ምንጯንና ማህበራዊ መስተጋብሯን መሰረት ያደረገቸው ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጎብኚዎችና እሱን ተከትሎ ባሉ የማህበራዊ ትስስር ጉዳዮች ነው ቢባል ማጋነን አየሆንም። በርካታ ጎብኚዎችም የአብያተ ክርስቲያናቱን የኪነ ህንጻ ልህቀት ከሀይማኖታዊ ክንዋኔው ጋር ለማጣጣም ገናንን ተከትሎ የሚመጣውን የጥምቀት በዓል ተመራጭ ያደርጋሉ፡፡ በዓላትን ተከትለው በሚቆሙት ገበያዎቹ ፤ ከመቶ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠሩ በሚነገርላቸው ልዩ ባለአንድ ፎቅ መኖሪያ ቤቶች በአካባቢው ነዋሪዎች አጠራር “ህድሞ” በሚባሉት ሳይቀር መስህብነቱን ከፍ ያደረገ ነው፡፡ በዓሉን ለመታደምና ስለታቸውን ለመፈጸም የሚመጡ እንግዶች ላሊበላ የምትጠቀምበት መንገድም ሌላኛው አስደናቂ መስህብ ነው። የገና በዓል ከመከበሩ ሳምንታት በፊት አስቀድመው ወደ ላሊበላ የሚመጡ ሰዎችን እግር በማጠብ፣  ቤት ያፈራውን በማቅረብ ለዘመናት ያካበተ እሴት በአደባባይ ይገለጣል። በስፍራው ከሚገኙ ሁቴሎች ጀምሮ ቅርጻ ቅርጽ ሻጮችና ሌሎች ዘርፎች በገና ወቅት ገበያ የገበያ አድማሳቸው የሚሰፋ ይሆናል። ነዋሪውም ቢሆን በወደደው የእጅ ጥበብ የተካነ ፤ ከአባቶቹ በወረሰው ጥንታዊ የብራና ላይ ጽሁፎቹና ስዕሎቹ የደመቀና ከዘመናት በፊት ከጥበበኞቹ የወረሰውን ጥበብ በስጦታዎቹ ላይ የራሱን አሻራ ጨምሮ ይታያል፡፡ በላሊበላ በገና ሰሞን ከሚታዩ አስደናቂ ሁኔታዎች መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው ደግሞ በዓሉን አስታኮ የሚከናወነው የሰርግ ስነ ስርዓት ነው። የላሊበላ ጎብኚና ተሳላሚ እድምተኛ የሚሆንበት ሰርግ። በሰርግ ስነ ስርዓቱ ቤተ ዘመድ ተሰባስቦ ፍቅርን የሚለዋወጥበት፣ ስለ ማህበራዊ ጉዳዮች የሚመክርበት ብሉልኝ ጠጡልኝ የሚልበት የላሊበላን እንግዳ በፍቅር ማዕድ የሚያስቀድስበትም ነው። ይህም የገና በዓል በላሊበላ ሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ትውፊታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አገራዊ ፋይዳ እንዳለው የሚያመለክት ነው። ዓለምን በአንድ የሚያናግሩት ቅርሶች መገኛ የሆነው ላሊበላ ለነዋሪውም፡ ለመላው ህዝብም ለጎብኚዎችም ተመችቶ እያስደመመ እንዲቀጥል ቅርሶቹን መጠበቅና የአካባቢውን መሰረተ ልማት ማሟላት ያሻል፡፡
ቻይናን ሳስባት
Dec 22, 2022 502
(በረከት ሲሳይ) አፈሩን ያቅልልላቸውና በቅርቡ በሞት የተለዩን አምባሳደር እምሩ ዘለቀ ከዓመታት በፊት በአንድ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ቀርበው በ1960ዎቹ ወደ ቻይና በማምራት፤ ሆንግ ኮንግን ጨምሮ የተለያዩ የቻይና ከተማዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን በመግለጽ፤ በዚያን ጊዜ ቻይና የነበረችበትን የድህነት ሁኔታና አሁን ላይ የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ በማነጻጸር የነበራቸው አድናቆትና ግርምት አሁንም ይታወሰኛል። አለፍ ብለውም ቻይና ከ1970ዎቹ ጀምሮ ባልተቋረጠ የዕድገት ምህዋር ውስጥ በመግባት ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበችበትን ሂደት ከኢትዮጵያ ጋር በትይዩ በማነጻጸር “እኛን ምን ነክቶን ነው?” በማለት አምባሳደሩ በቁጭት ያነሱት ጥያቄ ከዓመታት በኋላ ዛሬ ላይ እኔ በድጋሚ ላነሳው እወዳለሁ። ለአምስት ወራት ገደማ ለሙያ ሥልጠና በከረምኩባት የሩቅ ምስራቋ “ቻይና” በእውነቱ! ዕድገቷን አይቶ “እኛስ መቼ ነው እንዲህ የምንሆነው?” ብሎ አለማሰብ ከቶ አይቻልም። በዚህ ተጠየቅ፤ በቻይና በሄድኩባቸውና በደረስኩባቸው ከተሞች እንዲሁም በጎበኘኋቸው ተቋማት ሁሉ በዓይነ-ህሊናዬ ኢትዮጵያን እያሰብኩኝ ቆይታዬን አገባድጄ በቅርቡ ወደ አገሬ ተመልሻለሁ። ወረርሽኙና ቆይታዬ በቻይና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሥር በሚንቀሳቀሰው የቻይና ዓለም አቀፍ የፕሬስ ማዕከል ጋባዥነት ነበር ለአራት ወር ተኩል የሥልጠና ቆይታ ወደ ቻይና ያመራሁት። ሥልጠናው እኔን ጨምሮ ከ60 በማደግ ላይ ያሉ አገራት የተውጣጡ 75 ጋዜጠኞችን ተሳታፊ ያደረገ ነበር። ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለበርካታ ተጓዞች ወደ ቻይና መግባት ከባድ በሆነበት ወቅት ሥልጠናው መካሄዱ አንዳንድ ሁኔታዎችን እንድጋፈጥ አስገድዶኛል። ቻይና ከመግባቴ በፊት በአዲስ አበባ ለአምስት ቀናት እንዲሁም ቻይና ከደረስኩ በኋላ ሥልጠናው በዋነኝነት ወደሚካሄድባት የቻይናዋ ርዕሰ ከተማ ቤጂንግ ከማቅናቴ በፊት ደግሞ በደቡባዊ ቻይና በምትገኘው ጓንዙ ከተማ ለአሥር ቀናት በድምሩ ለ15 ቀናት ተከታታይነት ያለው የኮሮና ምርመራ በማድረግ ወሽባ (ኳራንቲን) ውስጥ ማሳለፌ ከገጠሙኝ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አንደኛው ነው። ምንም እንኳን ከኮቪድ ነፃ መሆኔ ተረጋግጦ ወደ ቤጂንግ ባቀናም አገሪቱ ወረርሽኙን ለመከላከል ያወጣችውን ፖለሲ ተከትሎ ሥልጠናውን አጠናቅቄ እስከምመለስበት ጊዜ ድረስ በየሁለት ቀናት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለማድረግ መገደዴም ሌላው የገጠመኝ ፈተና ነበር። ቻይና ከመግባቴ አስቀድሞ በተለይም ስለ ወረርሽኙ ሁኔታና ቁጥጥር በተመለከተ ከነበረኝ ግንዛቤ በተጨማሪ ከሚመለከታቸው አካላት ገለጻ ቢደረግልኝም፤ በመጀመሪያዎቹ ቀናት መደናገር አልቀረልኝም። ነገሮች አዲስ ሆነውብኛል፤ በየሁለት ቀናቱ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በመደበኛነት ማድረግ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ማድረግ፤ ወደየትኛውም የሕዝብ መገልገያ ሥፍራ ማለትም መዝናኛ ቦታዎች፣ ሱፐር ማርኬትና ሌሎች ሥፍራዎች ለመገኘት በእጅ ስልክ ላይ ባለው መተግበሪያ (ቢጂንክ ሄልዝ ኪት) አማካኝነት የምርመራ ውጤት በር ላይ ላሉ አሳላፊዎች ማሳየት በግዴታነት መቀመጡ ከነበረኝ ልምድ ጋር ፍጹም የተለየ ነው። ነፃ የምርመራ ውጤትን ሳያሳዩ የትም መግባትም ሆነ መንቀሳቀስ አይታሰብም። ጎን ለጎንም በርካታ ለወረርሽኙ አጋላጭ ናቸው የተባሉ የሕዝብ መሰብሰቢያ ሥፍራዎች ዝግ ናቸው፤ መዝናኛ ቦታዎችና የሕዝብ መገልገያ ማዕከላት ከመደበኛው ታዳሚዎቻቸው በእጅጉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ብቻ እንዲያስተናግዱ ተገደዋል፤ በአገሪቱ የሚካሄዱት እንቅስቃሴዎች ላይም እገዳ ተጥሏል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች አገራት ወደ ቻይና የሚጓዙ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ወደ ቻይና የሚያደርጉት ጉዞ በወረርሽኙ ሳቢያ መስተጓጎል ገጥሞታል። በውጭ የሚኖሩ ቻይናውያንም በወረርሽኙ ምክንያት እንደልባቸው ተመላልሰው የአገራቸውንና የወገናቸውን ናፍቆት መወጣት እንዳይችሉ ሆነዋል። በተለያዩ አጋጣሚዎች ቀርበን ያወጋናቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት ቻይና ቁጥጥሩን በእጅጉ ብታላላው በርካታ ዜጓቿን በሞት ልታጣ እንደምትችል ጥናት አጣቅሰው አስረድተውናል። በመሆኑም ወረርሽኙን ለመከላከል የተተገበረው ፖሊሲ አገሪቱ ውድ የሆነውን የዜጎቿን ህይወት እንድታተርፍ ከማስቻሉ ባለፈ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገቷ ተጽዕኖዎችን ተቋቁሞ በአዎንታዊ የዕድገት ምህዋር ውስጥ እንድትገሰግስ እንዳስቻላትም ያትታሉ። ያም ሆኖ አገሪቱ ወረርሽኙን ለመከላከል የመደበችው የሰው ኃይልና የምታፈሰው ገንዘብ እጅግ በርካታ መሆኑን ሳስብ እንዲሁም ሕዝቡም ሳያወላውል ወረርሽኙን ለመግታት የወጡ ደንቦችን በማክበርና በመተግበር የተወጣው አስተዋፅኦ እጅግ ያስገርማል። ወረርሽኙን ለመከላከል የሄዱበት ርቀት ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት ለመከወን የሚቻልም አይደለም። ወደ ቀድሞ ነገር ስንመለስ- በዚህ አውድ ውስጥ የተካሄደው ይህ የጋዜጠኞች ሥልጠና በመደበኛነት የቻይና ታሪክ፣ ባህል፣ ማኅበራዊ አወቃቀር፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ፖለቲካዊ ሥርዓትና በአንዳንድ የጋዜጠኝነት ርዕሰ- ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። በተለይም የቻይናን አሁናዊ ሁኔታ እንድንረዳ ያለመ ሲሆን ወረርሽኙን ታሳቢ በማድረግም በሰሜኑና ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ አምስት ግዙፍ ከተሞች ጉብኝት አድርገናል። በጎበኘናቸው እያንዳንዱ ከተሞች እጅግ የሚያስደምሙ የመንገድ፣ የወደብ፣ የኤርፖርት፣ የባቡር መስመርና ጣቢያ፣ መዝናኛ ሥፍራዎችና ሕዝባዊ ተቋማት የመሰሉ አስደማሚ መሰረተ-ልማቶችን ተመልክተናል። የኢንዱስትሪ ልማትና ስፋት፣ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትና የተቋማት ግንባታው ቀልብን ይገዛል። የከተሞቻቸው ስፋትና መሰረተ-ልማት እንዲሁም ሌሎች የአገልግሎት አቅርቦቶች ዜጎቻቸው በምቹ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ አስችሏቸዋል። በጎበኘናቸው የገጠር አካባቢዎችም ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዜጎች ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምሩ የሚሰራውን ሥራ በዚያው ልክም ገቢያቸው እያደገ የተሻለ ህይወት እየመሩ መሆኑን ተመልክተናል። በሌላ በኩል በቴክኖሎጂ ዘርፍ በተለይም በፈጠራ ሥራ አስደማሚ ሥራዎችን በመሥራት አገራቸው ሌላ ገጽታ እንዲኖራት ማስቻላቸውንም እንዲሁ። የቻይና ዕድገት የቻይና ዕድገት ከማንም የተሸሸገ ባይሆንም “ማየት ማመን ነው” እንደሚባለው በአካል ተገኝቶ አሁን ላይ አገሪቷ የደረሰችበትንና ቀድሞ የነበረችበትን ሁኔታ ማነጻጸር መቻል በራሱ ብዙ ያስተምራል። ቻይና ባለፉት 40 ዓመታት 800 ሚሊዮን ሰዎችን ከድህነት በማላቀቅ ቀዳሚ ተደርጋ የምትነሳ አገር ናት። በ1960ዎቹ አገራዊ ጠቅላላ ምርቷ ከጎረቤት አገራችን ከኬንያ በታች የነበረ ሲሆን፤ ከ1970ዎቹ ጀምሮ በአማካኝ 9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2021፤ 17 ነጥብ 73 ትሪሊየን ዶላር ጠቅላላ አገራዊ ምርት በመያዝ ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛዋ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን በቅታለች። እጅግ የከፋ ድህነት ውስጥ የነበሩት ቻይናውያን አሁን ላይ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው 10 ሺህ ዶላር ደርሷል። ቻይና በቀጣይ 13 ዓመታት የዜጎችን ገቢ 20 ሺህ ዶላር ለማድረስ ያለመታከት እየለፋች ትገኛለች። ቻይና አሁን እየሄደች ያለችበት የዕድገት ፍጥነት በተለይም ጠቅላላ የአገራዊ ምርት ደረጃዋ አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአንደኝነት ደረጃን ከአሜሪካ እንድትረከብ ያስችላታል የሚሉ በርካታ ተንታኞች አሉ። በተቃራኒው በ1990ዎቹ ጃፓንም አሜሪካን በዕድገት ትቀድማለች ተብሎ ሳይሳካ መቅረቱን አንስተው፤ ይህንን መላምት ውድቅ የሚያደርጉ ተከራካሪዎችም አሉ። የቻይና ምጣኔ ሀብታዊ ግስጋሴ በጣም ፈጣን የሚባልና ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ መሆኑ በዘርፉ ብቸኛዋ አገር ያደርጋታል። በተለይም ከሁለት ዓመታት በፊት የተቀሰቀሰው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምጣኔ ሀብቷን እስኪፈትነው ድረስ የአገሪቱ የዕድገት ሂደት ወጥ የሚባል ነበር ማለት ይቻላል።  ቻይና እንዴት አደገች? ለሚለው ጥያቄ በርካታ የመስኩ ተንታኞች እንደሚያስቀምጡት፤ የቻይና ዕድገት “የኢንዱስትሪ መር” መሆኑን ያለልዩነት ይስማሙበታል። የቻይና መንግሥት አገሪቱን ለውጭ ገበያ እንዲሁም ለውድድር ክፍት ካደረገበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1978 ጀምሮ ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ጀምሮ አሁን ላይ እስከተገነቡ ግዙፍ ኩባንያዎች ድረስ ለኢንዱስትሪ ልማት የተሰጠው ትኩረት እጅጉን የሚያስገርም ነው። አገሪቱ በተለይም በገጠሩ የማኅበረሰብ ክፍል የግብርና ምርትን በማስፋፋት ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የምርት ሽያጭ ዋጋን ከፍ በማድረግ ትልቅ ሥራ ሰርታለች። በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች የተጀመረው የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ መርሃ-ግብርም ትልቅ እመርታን ማስመዝገብ አስችሏል።  የኢንዱስትሪ ምርቶች የገበያ ተደራሽነታቸውን በማስፋት መንግሥት የሰጠው ከለላም ኢንዱስትሪዎቹ በእጅጉ እንዲያድጉ አድርጓል። ከዚያ በመለስ የቻይና የልማት ዕቅድ ውስጥ “ፈጠራ” ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን የኢንዱስትሪና የምርምር ተቋማት በዚሁ ጉዳይ ላይ እንዲሰሩና የተሻሉ ውጤቶችን እንዲያመጡ አስችሏቸዋል። ዛሬ ላይ የቻይና ኢንዱስትሪዎች የውስጥ ፍላጎትን ከማዳረስ አልፈው ለሌሎች የዓለም አገራትም ተርፈዋል። በፈጠራ ሥራ ላይ ያስመዘገቧቸው ለውጦችም በተለይም በታዳጊ አገራት ላይ ቻይና ያላት ተጽዕኖ ከፍተኛ እንዲሆን አስችሏል። በሌላ በኩል ቻይና ጠንካራ መንግሥታዊ አመራርና ተከታታይነት ያለው ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረጓ ለዚሁ መብቃቷም ይጠቀሳል። የሕዝቡ ፅናትና ቆራጥነትም ለዚህ ውጤት ጉልህ ሚና አለው። በተለይም ከ1970ዎቹ በፊት በነበሩት ጊዜያት የነበረው ድህነት ከባድ መሆኑን በማንሳት ቻይናውያን አንድም ወደ እዚያ ሕይወት ዳግም ላለመመለስና ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር የነበራቸው ተነሳሽነት በሌላ በኩል ደግሞ ለቀጣይም ትውልድ የተሻለ አገር ለማስረከብ የነበራቸውን ቁርጠኝነት ለዕድገታቸው በምክንያትነት ያነሳሉ። ምን እንማር መቼም ከድህነት እስካልወጣንና የራሳችንን ዕድገት በራሳችን ጥረት እስካላረጋገጥን ድረስ ከአደጉ አገራት የመማራችን ሂደት ቀጣይነት ይኖረዋል። በእርግጥ አድገንም ቢሆን እስከጠቀመ ድረስ ከሌላ መማሩ አይጎዳም። ኢትዮጵያ የ3 ሺህ ዓመታት ታሪክ እንዲሁም ረዥም የመንግሥት አስተዳደር ታሪክ ያላት መሆኑን የራሳችንም የውጭ መጻህፍት ድርሳናትም ያስረዳሉ። በአንጻሩ ድህነትና ኋላቀርነትም ለበርካታ ዘመናት አሁንም ድረስ እግር በእግር እየተከተለ የዛሬይቷን ኢትዮጵያ መፈተኑ አልቀረም። በተለይም ለዘመናት የዘለቁ የጦርነት ጊዜያትና በፖለቲካው መስክ ያሉ ስንጥቃቶች ዛሬም ድረስ ተጽዕኗቸው እጅግ የጎላ ነው። ምንም እንኳን እንዲህ ያሉ የተዋረሱ ችግሮች አሉታዊ ተጽዕኗቸው በሁሉም ዘርፎች ላይ ቢሆንም በተለይም በምጣኔ ሀብት ረገድ አገሪቱ ፈቅ እንዳትል አድርጓታል። ያለፈው ታሪካችን አሁን ላይ ተጽዕኖው እንዳለ ሆኖ መጪው ጊዜ በሕይወታችን የሚያጓጓና ትልቁን ሥፍራ መያዙ አይቀሬ መሆኑን በመረዳት የተሻለች ኢትዮጵያን በኅብረት ለመገንባት ቆርጦ መነሳት ያሻል። በዚህ ረገድ በተለይም የቻይና ዕድገት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገራትም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ምንም እንኳን የተከተሉትን የኢኮኖሚ ሞዴል ጠቅልሎ ገቢራዊ ማድረግ ባይቻልም ቢያንስ ለበርካታ አገራት ሊሰራ የሚችለውንና የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ላይ ተግባራዊ በማድረግ ላይ የሚገኘውን በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል። በተለይም ግብርናውን ማዘመንና የኢንዱስትሪ ልማትን ሊያስፋፉ የሚችሉ እንደ ጥቃቅንና አነስተኛ የመሰሉ ተቋማት በስፋት ማደራጀትና ወደ ተግባር ማስገባት ያስፈልጋል። በውስጣቸውም የሕዝቡን ህይወት ሊቀይሩ የሚችሉ ተጨባጭ የፈጠራ ሥራዎች እንዲስፋፉ የሚያስችሉ በፖሊሲ የተደገፉ ሥራዎችን መሥራት ግድ ይላል። ጎን ለጎንም ሕዝቡን በማንቃትና በማደራጀት ለአንድ አገራዊ ዓላማ እንዲሰለፍ ማድረግ ሌላው ከቻይና የምንማረው ጉዳይ ነው እላለሁ። አሁን ላይ በተለያዩ የፖለቲካ አጀንዳዎች ተጠምዶ ቀን ከሌት የሚያሰላስለውን ወጣት ወደ ልማት ፊቱን እንዲያዞር የሚያስችሉ ሥራዎች መሥራት ያሻል እላለሁ። በዚህ ላይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የአሁኗና የወደፊቷ ኢትዮጵያ የምትገዳቸው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የወል ኃላፊነት መሆኑንም ልብ ይሏል። አብዝተው ስለ ራሳቸውና ስለቤተሰባቸው ከፍ ሲልም ማኅበረሰብንና አገራቸውን በሚጠቅሙና የጋራ ረብ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ባለ ራዕይ ወጣቶች ያስፈልጉናል። በበርካታ ጉዳዮች ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም ጽሑፌን እዚህ ጋር ገትቼ ኢትዮጵያም እንደ እስያ ቻይና አድጋ ተመንድጋ እንድናያት እወዳለሁ።
የኤሌክትሪክ ኃይል-አንድም ብርሀን አንድም ቀጣናዊ ትስስር መፍጠሪያ መሳሪያ
Dec 5, 2022 407
የኤሌክትሪክ ኃይል አንድም ብርሀን አንድም ቀጣናዊ ትስስር መፍጠሪያ መሳሪያ (በሰለሞን ተሰራ) የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት የሚስተዋልበት በመሆኑ በአካባቢው በሚገኙ አገራት መካከል ጠንካራና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለመመስረት አዳጋች ሆኖ ቆይቷል። አካባቢው ለዘመናት የዘለቀ አለመረጋጋት የሰፈነበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ደካማ የሆነ የፖለቲካ አብሮነት ሲንጻባረቅበት የቆየ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይስማሙበታል። ቀጣናው ከኢኮኖሚ ትብብር ይልቅ ወታደራዊ ትብብር የሚጎላበት፣ የአንድን አገር የውስጥ ሰላም ለማደፍረስ የተለያዩ አገራት ረጃጅም እጆቻቸውን የሚዘረጉበት፣ አገራት በጎረቤቶቻቸው ላይ ሴራ የሚጠነስሱበት እንደነበርም በቻታም ሀውስ የአፍሪካ ፕሮግራም ተባባሪ ተመራማሪና የጥናት ተንታኝ የሆኑት ሳሊ ሄሊ የተባሉ የፖለቲካ ምሁር ይጠቅሳሉ። በዚህም በቀጣናው የሚስተዋለው የእርስ በርስ ግጭት፣ አለመረጋጋትና የኢኮኖሚ ዕድገት ከማጓተቱ ባለፈ አገራቱ እርስ በርሳቸው እንዳይተማመኑ አድርጓቸው ቆይቷል። ሳሊ ሄሊ እንደሚሉት በአገራቱ ውስጥ የሚኖሩ ተመሳሳይ ማህበረሰቦች በርካታ በመሆናቸው በአንዱ አገር የሚፈጠረው የደህንነት ስጋት ሌላኛውን በቀጥታ ይጎዳዋል። ማህበረሰቦቹ አንድ አይነት የአኗኗር ባህል የተላበሱ በመሆኑ የመኖር ህልውናቸውም ሆነ ብልጽግናቸው ተነጣጥሎ የሚታይ አይደለም። ኢትዮጵያ በቀጣናው ከሚገኙ ሁሉም አገራት ጋር ድንበር የምትጋራ በመሆኑ የስጋቱ ቀጥተኛ ተጠቂ ናት። ይህን ተከትሎ ስጋቱን ወደ መልካም ዕድል ለመቀየር የተለያዩ የዲፕሎማሲ መስመሮችን በመዘርጋት የቀጣናውን ትስስር ጠንካራና ዘላቂ ለማድረግ እየሰራች ትገኛለች። በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠርና የአፍሪካ ሕብረት ለአህጉሪቱ ልማት፣ ሰላምና ውህደት መሳሪያ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንዲጠናከር ለማስቻል በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ኢትዮጵያ በ”ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ” ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖርና የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በመትጋትም አርአያነቷን እያሳየች ትገኛለች። ከጎረቤቶቿ ጋር በወደብ፣ በባቡርና በየብስ ትራንስፖርት እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብቱ አያሌ መሠረተ ልማቶች ከመተሳሰር ባለፈ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የምታደርገው ጥረት በአርአያነት እንድትጠቀስ አድርጓታል። ነገር ግን ከአፍሪካ ቀንድና ከጎረቤት አገራት ጋር ቀጣናዊ ትስስር ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ያልተዋጠላቸውና የቀጣናው መረጋጋት ጥቅማችንን ያሳጣናል ብለው የሚያስቡ አንዳንድ ኃያላን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን በማሳደር አገሪቱ ከያዛቸው ግብ ወደ ኋላ ለመሳብ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ በግልጽ ይስተዋላል። ጫናዎቹ እንዳሉ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ከትብብርና አብሮ መልማት አካሄዷ ዝንፍ አላለችም። ቀጣናውን በኢኮኖሚ ልማትና ዕድገት ለማስተሳሰር የወጠነችውን ግብ ለማሳካት ያግዛት ዘንድ ለጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የጀመረችውን ጥረት ገፍታበታለች። ለአብነትም የውሃ፣ ነፋስ፣ እንፋሎትና የጸሃይ ብርሃን በመጠቀም ኃይል አምራች በመሆን ከምስራቅ አፍሪካ ባሻገር የአፍሪካ የኃይል ምንጭ ማዕከል ለመሆን ግብ ጥላ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። የኃይል አቅርቦት ጅማሮው በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ድንበር ዘለል የሃይል ንግድ እንዲሁም ትስስርን ለማጎልበት ያግዛል። ይህም በአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጣር 2005 የተቋቋመው ኢስተርን አፍሪካ ፓወር ፑል እንቅስቃሴ ተግባራዊነት የሚያረጋግጥ ነው። ኢስተርን አፍሪካ ፓወር ፑል ምስራቅ አፍሪካን በአስተማማኝና ዘመናዊ የኃይል አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ በዓለም ላይ ካሉ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች አንዱ ተብሎ ወደሚታወቅ ቀጣና የመቀየር ራዕይ አለው። በአጠቃላይ የኃይል ልማትን የማስተባበር ስልጣን የተሰጠው የተቋሙ ዋና ፅህፈት ቤት በአዲስ አበባ የሚገኝ ሲሆን አስራ አንድ አባል አገራት አሉት። አገራቱም ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሊቢያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ናቸው። ይህን የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ፖል ኢኒሸቲቭን መሰረት አድርጋ የምትንቀሳቀሰው ኢትዮጵያ በቀጣናው ለሚገኙ በርካታ አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ በማድረግ ላይ ትገኛለች። አሁን ላይ ለኬኒያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ ኃይል የምታቀርብ ሲሆን በቀጣይ ለታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን ኃይል በማቅረብ ምስራቅ አፍሪካን በልማት ለማስተሳሰር እየተጋች ነው፡፡ በቀጣይ ዓመታትም የኃይል ምርትና የአቅርቦት ምጣኔዋን በማሳደግ የምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ የኃይል አቅራቢ ለመሆን እየሰራች ነው። ኢትዮጵያ ለጂቡቲ፣ ኬንያና ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል የምትሸጥበት ታሪፍ ተቀራራቢነት ያለው ሲሆን በዋናነት የጋራ የልማት ትስስርን መሰረት ያደረገ ነው። በ2014 ዓ.ም. ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለጅቡቲ 527 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማቅረብ ታቅዶ 611 ጊጋ ዋት ሰዓት ማቅረብ የተቻለ ሲሆን ለሱዳን ደግሞ 1 ሺሕ 93 ጊጋ ዋት ሰዓት ማቅረብ መቻሉን መረጃዎች ያመለክታሉ። መንግስት ለጅቡቲና ሱዳን ካቀረበው የኃይል ሽያጭ ያገኘው 95 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን፤ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀርም የ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም የ5 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ እንዳለውና የአገራቱ ትስስር እየጎለበተ መምጣቱን ያሳያል። አገራቱ ካለባቸው የኃይል እጥረት አኳያ የኢትዮጵያ በጋራ የመልማት አካሄድ ተጠቃሚ እያደረጋቸው ይገኛል። በተለይ ጅቡቲ ኃይል ለማመንጨት ለድንጋይ ከሰልና ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ከስምምነቱ በእጅጉ ተጠቃሚ ያደርጋታል። ሱዳን ከዚህ ቀደም ወደ 200 ሜጋ ዋት የሚጠጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ እንደገዛችና ይህም የሱዳንን 10 በመቶ የኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎትን እንደሚሸፍን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያና ኬንያ በኃይል ለመተሳሰር የጀመሩት ጉዞ በቅርቡ ለፍሬ በቅቷል። በ2008 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው የኢትዮ-ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ 1 ሺ 068 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ሲሆን፣ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ 1 ነጥብ 26 ቢሊዮን ዶላር ወጥቶበታል። የማስተላለፊያ መስመሩ በኢትዮጵያ በኩል 437 ኪ.ሜ በኬኒያ በኩል ደግሞ 631 ኪ.ሜ. ርዝመት አለው። በኢትዮጵያ በኩል የተዘረጋው መስመር ከወላይታ-ሶዶ ማከፋፈያ ጣቢያ ጀምሮ አርባ ምንጭ፣ ኮንሶ፣ ብርንዳር፣ ያቤሎና ሜጋንን አቋርጦ ኬንያ የሚዘለቅ ሲሆን ግንባታው በመጠናቀቁ ኢትዮጵያ ለኬኒያ ኃይል ማቅረብ ጀምራለች። ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት ለሩዋንዳ፣ ለታንዛኒያና ለብሩንዲ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ውይይት የጀመረች በመሆኑ የኬንያው መስመር ዝርጋታ ለኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። አዲስ የተገነቡትና በመገንባት ላይ የሚገኙት እንደ ግልገል ጊቤ 3፣ ኮይሻና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬቱን ለማፋጠን አጋዥ ተደርገው ይቆጠራሉ። የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ቀጣናውን በኃይል ከማስተሳሰር ባለፈ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ስጋት የሆነውን የአየር ፀባይ ለውጥ ለመከላከል የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። ወደ ጎረቤት አገር የሚላኩት የኤሌክትሪክ ኃይልና የወጭ ንግድ ምርቶች ኢትዮጵያ በኢጋድ አገሮች ውስጥ ለሚኖረው አካባቢያዊ ትስስር የሰጠችውን ከፍተኛ ትኩረት ያመለክታል። በዚህም ከኃይል አቅርቦቱ ባለፈ በኢትዮጵያ በኩል አልፈው ወደ ኬንያ፣ ሶማሌላንድ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ጂቡቲ የሚዘልቁ ከ13 በላይ የመገናኛ ኮሪደሮች ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ረገድ የምታደርገውን እንቅስቃሴ በሚያግዝ አግባብ ሰፊ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች። በመንገድ፣ በባቡር፣ በነጻ የንግድ ቀጣና፣ በኃይል ትስስር እየሰራቻቸው ያሉ ስራዎች በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። አገሪቷን በአገር ውስጥና በክፍለ አህጉሩ ደረጃ ለማገናኘት የሚያግዝ 4 ሺ 744 ኪሎ ሜትር የሃዲድ መስመር የሚሸፍን ስምንት የባቡር መንገድ ኮሪደሮች በሁለት ምዕራፍ ለመገንባት የተያዘው ዕቅድ ሌላው ማሳያ ተደርጎ ሊነሳ ይችላል። የኢትዮጵያ የገቢ ሸቀጥ 90 በመቶ በጅቡቲ ስለሚገባ የኃይል አቅርቦቱ ይህንኑ የወደብ እንቅስቃሴ ለማሳለጥና የህዝቦችን ኢኮኖሚያዊና የአገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለው ሚና ወሳኝ ነው። ቀጣናው በአየር ጸባይ ለውጥ የተነሳ ለተደጋጋሚ ረሃብ፣ ድርቅ፣ ጎርፍና የአንበጣ ወረረርሽኝ የተጋለጠ በመሆኑ የታዳሽ ኃይል ግንባታ ጥረቱ በመጠንም ቢሆን እነዚህን ስጋቶች እንደሚያስወግድ ታምኖበታል። ኢትዮጵያ ለአየር ጸባይ ለውጥ ምክንያት ባትሆንም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ ግንባር ቀደም የምስራቅ አፍሪካ አገራት አንዷ ናት። የታዳሽ ኃይል አቅርቦቱ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የስራ ዕድል በመፍጠር፣ ከባቢያዊ ሁኔታን በመጠበቅና የደን ሃብትን ከውድመት በመታደግ የራሱ የሆነ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ከዚህ ባለፈ ትስስሩ የአገራቱ የፖለቲካና የለውጥ መሰረት ለሆነው አገር ተረካቢ ወጣት ዘርፈ ብዙ የስራ ዕድል በመፍጠር ትውልዱን ከስጋት ምንጭነት ወደ ልማት ፊት አውራሪነት ለመቀየር ያስችላል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢነርጂ ማዕከል ለመሆን በያዘችው እቅድ የውሃ፣ የነፋስ፣ የእንፋሎት እና የጸሃይ ብርሃን ሀይል የማመንጨት አቅሟን ለማሳደግ እየሰራች ትገኛለች። ይህም ንጹህ ኢነርጂን በመጠቀም ረገድ በዓለም ላይ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥን የሚያሳይ እንዲሁም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ንጹህ ኢነርጂን በመጠቀም ቀዳሚ እንድትሆን እንደሚያስችላት ተገልጿል። ይህም ከቀጣናው ባለፈ አፍሪካን በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር የጀመረችውን ቁርጠኛ አካሄድ ያረጋግጣል። በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተዘጋጀው የ2013-2022 የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ እንደተመላከተው በአገር ውስጥ ያለውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የጥራት መስፈርቶችን የሚያሟላ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለጎረቤት አገራት ማቅረብን ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ጎረቤትን ያስቀደመ በጋራ የመልማት አካሄዷ ማሳያ ብቻ ሳይሆን ማረጋገጫ መሆኑን ከልማት ዕቅዱ ተጨልፈው በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑና ለውጤት የበቁ የልማት ስራዎች ምስክሮች ናቸው። እነዚህን ትስስሮች በማጎልበት መተማመንን የሚፈጥሩ ተግባራት ማጠናከርና በጋራ በመልማት መርህ ላይ ተመስርቶ መስራት የሁሉም አገራት ቀዳሚ አማራጭ ሊሆን ይገባል።
ለዓለም ዋንጫ ባታልፍም በውድድሩ ሁሉም ጨዋታዎች ላይ የምትሳተፈው ኢንዶኔዢያ
Nov 28, 2022 452
ኢንዶኔዢያ በ22ኛው የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ካልተሳተፉ ሀገራት መካከል ብትሆንም በውድድሩ ሁሉም ጨዋታዎች በሚባል ደረጃ እየተሳተፈች ነው። በዓለም ዋንጫ ውድድሩ ሳይሳተፉ ኢንዶኔዢያን በውድድር በመወከል ታሪክ የሰሩት ዜጎቿም “በጣም ኩራት ተሰምቶናል” ሲሉ ለሀገራቸው ክብር የበኩላቸውን በማድረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። ለኢንዶኔዢያ ኩራት የሆነውን ጉዳይ በተመለከተ ዘገባ የሰራው አልጀዚራ የኢንዶኔዢያ ልጆች ሀገራቸውን ለዓለም ዋንጫ ማሳለፍ ባይችሉም በኳስ ምርታቸው ግን በውድደሩ ተፋላሚ ሆነዋል ብሏል። ሀገሪቷ የውድድሩ ተሳታፊነትን ያገኘችው በምሥራቅ ኢንዶኔዢያ ማዲየም በተባለች ግዛት በሚገኘው ፒቲ ግሎባል ዌይ በተሰኘ ኩባንያ አማካኝነት ነው። ኩባንያው በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ላይ “አል ሪህላ” በሚል ስያሜ የሚቀርበውን ኳስ እንደሚያመርት እ.አ.አ በ2020 መገለጹ ይታወቃል። በዛው ዓመት ኩባንያው ቅርንጫፉን በግዛቲቱ በመክፈትም በዓለም ዋንጫው ያልተሳተፉ ኢንዶኔዢያውያን በኳታሩ የዓለም ዋንጫ አሻራቸውን እንዲያኖሩ እድል ፈጠረላቸው። የማዲየም ግዛት አስተዳዳሪ አህመድ ዳዋሚ በሰጡት አስተያየት” አል ሪህላ የኩራት ምንጭ ሆኖናል በተጨማሪም ወደ ኳሱ ምርት ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ ለሀገር ውስጥ የገቢ ምንጫችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል” ብለዋል። የኢንዶኔዢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የማዲየም ግዛት ነዋሪዎች “በኳታሩ ዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ሀገሪቱን በኳስ ምርት በማሳተፍና ገቢን በማመንጨት የዓለም ኢኮኖሚ አንድ አካል ሆነዋል” ሲል ኢንዶኔዢያ ከተሳትፎ ባሻገር ከዓለም ዋንጫው ያገኘችውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና ለውድድር ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ገልጿል። ጉዞ የሚል ትረጉምን የያዘው የዓለም ዋንጫው ኳስ “አል ሪህላ” ከአዲዳስ ኩባንያ ጋር በጥምረት የሚመረት ሲሆን በፊፋ የደረጃ ምደባም 14ተኛው ይፋዊ የዓለም ዋንጫ ኳስ መሆኑም ተመልክቷል። አል ሪህላ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአካባቢ ብክለትን መከላከል አንዲችል ሆኖ ውሃማ መሠረት ካለው ሙጫና ቀለም የተሰራ መሆኑ በዘገባው ተካቷል። በቅርብ ዓመታት በተካሄዱ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ጥቅም ላይ ከዋሉት ኳሶች መካከል የ2006ቱ ቴሜጊይስት በርሊን፣ በ2010 ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ጥቅም ላይ የዋለችው ኳስ ጃቡላኒ የሚል ስያሜ የተሰጣት ሲሆን በሴቶች ብቻ የተመረተ ስፒድ ሴል፣ የ2014 ቱ ብራዙካ እና የ2018 ቱ ቴልስታር ይጠቀሳሉ።
ከስደት መልስ - አገር አቀፍ የግብርና ዘር አምራች ካምፓኒ የመመስረት የታታሪነት ጉዞ
Nov 12, 2022 510
ዑመር መሀመድ አወል ይባላሉ፤ ውልደትና እድገታቸው ወልቄጤ ከተማ ሲሆን በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ቦረር ሜዳ ቀበሌ የሚገኘው የ"መሀመድ አወል እርሻ ልማት" ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ናቸው። በአገራቸው ላይ ሙአለ ንዋይ አፍስሰው መስራት ከመጀመራቸው በፊት ለ10 ዓመታት በስደት ኖረዋል። ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዑመር መሀመድ በ1987 ዓ.ም ወደ አሜሪካ በማቅናት በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰዋል። በአገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በማመንም በ1999 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በቅተዋል። ትኩረታቸውንም አባታቸው መሀመድ አወል በ1985 ዓ.ም ያቋቋሙትን የእርሻ ልማት ድርጅት በማጠናከርና በማስፋፋት አገርና ወገናቸውን መጥቀም በሚችሉበት ጉዳይ ላይ አደረጉ። ጊዜ አልፈጁም ወዲያው ወደ ሰብል ልማትና ምርጥ ዘር ማምረት ተሸጋገሩ። ቀጥለውም በስራ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶችን በመቋቋም በአገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ የሆነ የባለ ግዙፍ ምርጥ ዘር አምራች የእርሻ ልማት ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ለመሆን እንደበቁ ይገልፃሉ። ከ30 ዓመታት በፊት 160 ሄክታር መሬት ከመንግስት በመረከብ የሰብል ልማት ስራውን አንድ ብሎ የጀመረው የእርሻ ልማት ድርጅት ዛሬ ላይ ከ1ሺ 400 ሄክታር በላይ መሬት ላይ በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ጤፍ፣ ሽምብራ እና ስንዴ በማምረት ላይ ይገኛል። በቅርቡም በደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ርስቱ ይርዳው የተመራ የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች ቡድን በእርሻ ልማቱ እየተከናወነ የሚገኘውን የምርጥ ዘር ሰብል ልማት እንቅስቃሴ ጎብኝቷል። የእርሻ ልማቱ አገር ከምትሻው ሰፊ የምርጥ ዘር አቅርቦት በተጨማሪ 2ሺህ ለሚደርሱ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አቶ ዑመር ተናግረዋል። ለሰራተኞቹም እስከ 2 ሚሊየን ብር የሚደርስ ወርሃዊ ክፍያ እንደሚፈጸም ጠቅሰው ጠንክሮ መስራት ለዛሬ ውጤት እንዳበቃቸው ይናገራሉ። ከ2ሺህ ዓ.ም ጀምሮ ያካበቱትን የምርጥ ዘር ሰብል ልማት ተሞክሮ በበቆሎ ምርጥ ዘር ማሻሻያ ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ። በተያዘው ዓመትም የእርሻ ልማት ድርጅቱ መንግስት በምርጥ ዘር ሰብል ልማት እያከናወነ የሚገኘውን ስራ ለማገዝ "ሊሙ" የተሰኘን የበቆሎ ምርጥ ዘር እያለሙ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በምርጥ ዘር ማሻሻያ ልማት ስራውም በሄክታር እስከ 50 ኩንታል የሚደርስ የበቆሎ ምርጥ ዘር ምርት ለመሰብሰብ እየጠበቁ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የኢትዮጵያን የሰብል ምርጥ ዘር እጥረት ለመሙላት ድርጅቱ እያደረገ ባለው ጥረት የመንግስት እገዛ እንዳልተለያቸውም ያነሳሉ። በዚህም የተሻሻለ የበቆሎ ምርጥ ዘርን በማልማት የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት ለመሙላት ሰፊ ስራ እያካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በእርሻ ልማት ድርጀቱ እየተካሄደ ከሚገኘው ሰፊ የበቆሎ ሰብል ምርጥ ዘር ብዜት በተጨማሪ ለ14 ሺህ አርሶ አደሮች የሚውል 7ሺህ ኩንታል የቀይ ቦለቄ ምርጥ ዘር ማምረት እንደተቻለ ጠቁመዋል። የአረንጓዴ አሻራ ልማትም ሌላኛው በድርጅቱ እየተከናወነ የሚገኝ የልማት ስራ እንደሆነ አንስተዋል። በቀጣይም አኩሪ አተርን ለማልማት እቅድ እንዳላቸው ጠቁመው፤ በመጪው የበጋ ወራትም ስንዴን በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ሌሎች ባላሀብቶችም በእርሻ ኢንቨስትመንት ስራ በሚደረግ ጥረት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አማራጩን ማየት እንዳለባቸው መክረዋል። የመንገድ እና መሰል በልማት ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቋቋም ለአገራቸው ምርጥ ዘር አቅርቦት አሻራቸውን እያኖሩ እንዳሉ ተሞክሯቸውን በማጋራት። በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ "የመሀመድ አወል እርሻ ልማት" ድርጅት ግንባር ቀደም አገር ዓቀፍ የምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅት ለመሆን እየተጋ እንደሚገኝም አመላክተዋል። ድርጅቱ እያበለጸጋቸው የሚገኙ የሰብል ልማቶችም ትልቅ የተሻሻለ ምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅት እንደሚሆን አረጋግጠዋል።
አሊ ቢራ - የጸደይ ብርሃን አብሳሪ
Nov 7, 2022 635
(በአሸናፊ በድዬ) "ሰምቼ የማልጠግበው ድምጽ 'ዛሬ ዝም አለ' የሚል ዜና ሰማሁ። እንደሌላ ጊዜው ውሸት በሆነ ብዬ ተመኘሁ። ግን መራራ እውነት ነው። ባለወርቃማ ድምጹ አሊ ቢራ ትቶልን የሄደው ብዙ ነው።" ይህ አንድ የአንጋፋው አርቲስት አድናቂ ሀዘኑን የገለጠበት መንገድ ነው። እውነትም ክቡር ዶክተር አርቲስት ዓሊ ቢራ ከሙዚቃ ጋር ከስድስት አስርታት የበለጠ እድሜ የተቆራኘ መጠሪያውን ጭምር በጥበብ ስራው የተካ ድንቅ ሰው ነበር። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ባለውለታ ከሆኑ አንጋፋ ድምጻዊያን መካከል ዓሊ ቢራ በቀዳሚነት ከሚቀመጡት ይመደባል። በተለይም የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃዎች ከፍ ብለው እንዲደመጡና በርካታ ሰዎች ጋር ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር አሊ ቢራ የነበረው ሚና እጅግ ላቅ ያለ ነው፡፡ ሙዚቃ ቋንቋ ነው የሚለውን ብሂልም በተግባር አሳይቷል። ለአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የሙዚቃ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በበርካታ ቋንቋዎች ሙዚቃን የሚጫወተው አሊ ቢራ በአፋን ኦሮሞ በተጫወታቸው በርካታ ሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን በመቻሉ ትልቅ ስፋራ ይሰጠዋል፡፡ ይህ የሙዚቃ ሰው በድሬደዋ ገንደ ቆሬ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ከአባቱ መሐመድ ሙሳ እና ከእናቱ ፋጡማ አሊ በ1940 ዓ.ም ነው የተወለደው። ከህጻንነቱ ጀምሮም የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችን እያደመጠና እያንጎራጎረ ማደጉ ይነገራል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በድሬዳዋ ከተማ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ካቴድራል ትምህርት ቤት ተከታትሏል። አሜሪካ አገር በሚገኘው የሳንታ ሞኒካ ኮሌጅም የሙዚቃ ትምህርት ተምሯል። አርቲስት ዓሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም ገና በ13 ዓመቱ የኦሮሞን ሙዚቃ ለማስተዋወቅ ዓላማ አድረጎ የተቋቋመውን ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን “አፍረን ቀሎ”ን በመቀላቀል ነው የሙዚቃ ስራውን አንድ ብሎ የጀመረው። አሊ ቢራ በዚህ የባህል ቡድን ተቀላቅሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረክ ያቀነቀነው ሙዚቃም የዛሬው የስሙ መጠሪያ የሆነው "ቢራ ዳ በሪኤ" የሚለው ሙዚቃ ነው፡፡ "ቢራ ዳ በሪኤ" የሚለው ሙዚቃ ከባዱ ክረምት አልፎ አዲስ ብርሃን መውጣቱን ገና በለጋ እድሜው በማብሰር የሙዚቃ ተስፋውንም አብሮ ያለመለመበት ነው። በዚህ ሙዚቃ ምክንያትም "አሊ መሐመድ ሙሳ" የነበረው ስሙ "አሊ ቢራ" ተብሎ እንዲጠራ አድርጎታል፡፡ ድምጻዊ ዓሊ ቢራ ከአፍ መፍቻ ቋንቋው ከአፋን ኦሮሞ በተጨማሪ በአማርኛ፣ በአረብኛ፣ በሃረሪ እና በሶማሊኛ ቋንቋዎች የመዝፈን ችሎታ አለው። በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ተቀጥሮ ለሦስት ዓመታት የሰራ ሲሆን ‘አይቤክስ’ ባንድን በመቀላቀል ለስምንት ዓመታት የሙዚቃ ስራዎቹን በዲ አፍሪካ ሲያቀርብ መቆየቱም ይነገራል፡፡ ከ267 በላይ ሙዚቃዎች ያበረከተው ድምጣዊው በአፋን ኦሮሞ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የሆነውን አልበሙን በ1971 ዓ.ም ከመስራቱ በተጨማሪ ለገበያ የቀረቡ 13 አልበሞች እንዳሉትም በአንድ ወቅት ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል፡፡ የክብር ዶክተር አሊ ቢራ የሙዚቃ ስራዎች አፋን ኦሮሞ በማይሰሙ ሰዎች ዘንድም ጭምር እጅግ ተቃባይነት ያላቸው መሆኑን ባለቤቱን ጨምሮ በርካቶች ምስክርነት ሰጥተዋል። እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ ስራዎቹ መካከልም:- "Birraa dhaa Barihe" የመጀመሪያ ስራው፣ " Waa Malli nu dhibe"፣ "Jaalaluma teeti"፣ "Barnootaa"፣ "Ushuruururuu"፣ "Karaan Mana Abbaa Gadaa"፣ "Nin deema"፣ "Dabaala Keessan" የሰርግ ሙዚቃ፣ "Amalele" ከብዙዎቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ድምጻዊ አሊ ቢራ "Waa Malli nu dhibe" በሚለው የሙዚቃ ስራው እናታችን አንድ ናት ምንድነው የሚያለያየን በማለት ኢትዮጵያዊያን አንድ መሆናቸውን እና መቼም መለያየት የማይችሉ የአንድ እናት ልጆች መሆናቸውን በሙዚቃ ስራው በማቀንቀን ከመለያየት ይልቅ አንድነት ፍቱን መፍትሄ መሆኑን አንጸባርቆበታል፡፡ "Karaan Mana Abbaa Gadaa" በሚለው የሙዚቃ ስራውም ፍትሃዊነት፣ እኩልነት፣ አንድነት፣ መልካምነት፣ ግልፀኝነት፣ ሀቀኝነት የገዳ ስርዓት መገለጫዎች ስለመሆናቸው አቀንቅኗል፡፡ "ትምህርት የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፍ ነው" ብሎ እንደሚያምን የሚናገረው ድምጻዊ አሊ ቢራ ትውልዱ ትኩረቱን ትምህርት ላይ ብቻ ማድረግ እንዳለበትም "Barnootaa ammas Barnootaa" በሚለው ሙዚቃ ስራው አስተምሯል፡፡ "Amalele ……….. an yaada keen takka hin bule" በማለት ስለፍቅር ሃያልነት ባቀነቀነው ሙዚቃ ፍቅር የሁሉም ነገር ማሰሪያ፣ ከደስታዎች ሁሉ በላይ ደስታ መሆኑም ለትውልዱ አስተምሯል፡፡ ድምጻዊ ዓሊ ቢራ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮነትና ማህበራዊ ትስስር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክቶችን በማስተላለፍ መልካም ትውልድ እንዲቀረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። የተለያዩ ፈተናዎችን ተሻግሮ በከፍተኛ ጽናትና ብቃት ለረጅም ዓመታት በኪነ ጥበቡ ውስጥ ያሳለፈ መሆኑ ደግሞ አሁን ላለው ትውልድ ታላቅ ተምሳሌት ያደርገዋል። በርካታ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የሚጫወተው አሊ ቢራ ከአርባ በላይ በሆኑ አገራት እጅግ በርካታ የመድረክ የሙዚቃ ስራዎችን ተጫውቷል። ባለፉት 60 ዓመታት በኦሮሞ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ እንቁ ሆኖ የቆየ፣ በርካታ ወጣቶችን ማፍራት የቻለ፣ ትውልዱ በእውቀት እና በስነ-ምግባር እንዲቀረጽ በሙዚቃ ስራው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ነው፡፡ ድምጻዊ ዓሊ ቢራ “Birra Children’s Education Fund” የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከባለቤቱ ጋር አቋቁመው ለሕፃናት ትምህርት ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በዘርፉ ላበረከተው ታላቅ አስተዋፅኦ ሁለት የክብር ዶክተሬት የተሰጠው አርቲስት ዓሊ ቢራ፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ተቋማት የተለያዩ እውቅናዎችን እና ሽልማቶችን አግኝቷል። ለአብነትም ከድሬዳዋ እና ከጅማ ዩኒቨርስቲዎች የክብር ዶክትሬት ተበርክቶለታል፤ በድሬደዋ ከተማ ፓርክ እንዲሁም በአዳማ መንገድ በስሙ ተስይሟል፣ የኦሮሚያ ክልል በሙዚቃው ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ ልዩ የኒሻን ሽልማት አበርክቶለታል፤ የመጀመሪያው የኢሬቻ የሰላም ሽልማት ተሸላሚም ሆኗል፤ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ የኪነጥበብ ሽልማት የህይወት ዘመን ተሸላሚ ለመሆንም በቅቷል፤ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከፍተኛ ሽልማት አግኝቷል፤ በካናዳ ቶሮንቶ የአፍሪካ የምንጊዜም አንጋፋ ሙዚቀኛ ሽልማት አግኝቷል፤ የኦዳ አዋርድ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ መሆን ችሏል፤ ሌሎችንም ከፍተኛ ማዕረጎችንና ሽልማቶች አግኝቷል፡፡ የአንጋፋውን አርቲስት የክቡር ዶክተር አሊ ቢራን ህልፈት ህይወት አስመልክቶ ብዙዎች ሀዘናቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የሙያ አጋሮቹ አገር ትልቅ ባለውለታዋን ማጣቷን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ "የአንጋፋው ድምጻዊ ዓሊ ቢራ ህልፈት ለኢትዮጵያ ጉዳት ነው፤ በዜማዎቹ ኅብረትን፣ ጽናትንና ባህልን አቀንቅኗል፤ ለብዙዎችም አርአያ ሆኗል፤ ላደረግከው ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግንሃለች" በማለት ሀዘናቸውን ገልጸዋል። ይህ አንጋፋ አርቲስት በህይወት ቢለየንም ህያው ስረዎቹ ግን አብረውን ይዘልቃሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም