ኢኮኖሚ
ዶክተር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት የአረንጓዴ ስምምነት ልዑክ ቡድን መሪ ጋር ተወያዩ
Jul 26, 2024 245
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት የአረንጓዴ ስምምነት ልዑክ ቡድን መሪ ሮቤርቶ ስኪሊሮ ጋር ተወያይተዋል፡፡ በውይይቱም የኢትዮጵያ ቡና በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ገበያ በስፋት እንዲቀርብ ለማድረግ በትብብር እንደሚሰራ ተመላክቷል። የቡና ምርትን እሴት ሰንሰለት ለማሳደግና የውጭ ገበያ አማራጮችን ለማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መክረዋል። በኢኮኖሚና ሌሎች ጉዳዮች በትብብር እየሰሩ የሚገኙት ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት በተለይ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በትብብር እየሰሩ መሆናቸው ተገልጿል። የኢትዮጵያ ቡና በህብረቱ አባል ሀገራት ገበያ በስፋት ለማቅረብ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት በጋራ እየሰሩ ሲሆን በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የቡና የአቅርቦቱና እሴት ሰንሰለቱ ከአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ ነጻ ደንብ ጋር መጣጣም እንዳለበትም ተገልጿል።
በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት የቅድመ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በምሳሌነት የተነሳበት ነው - አቶ   አሕመድ ሽዴ
Jul 26, 2024 225
በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት የቅድመ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በምሳሌነት የተነሳበት ነው - አቶ አሕመድ ሽዴ አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ በ4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት የቅድመ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የለውጥ እርምጃ በምሳሌነት የተነሳበት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ገለጹ። በአዲስ አበባ ከሐምሌ 15 እስከ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ሲካሄድ የቆየው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ተጠናቋል። ጉባኤውን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፤ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በመዲናዋ "የአዲስ አበባ አክሽን አጀንዳ" ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ማስተናገዷን አስታውሰዋል። ኢትዮጵያም የዘንድሮውን 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ የተደረሱ ውሳኔዎችን በመገምገም በስፔን ለሚካሄደው ጉባኤ የቅድመ ዝግጅት ስራዋን በስኬት አስተናግዳለች ብለዋል።   በጉባኤው ላይ የመንግስታቱ ድርጅት አባል ሀገራት፣ የድርጅቱና የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች በተሳተፉበት በስኬት ተካሂዶ መጠናቀቁን አስታውቀዋል። በዚህም ቅድመ ጉባኤው በስፔን ለሚካሄደው የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የታዳጊ ሀገራትን ዕድገት ታሳቢ በማድረግ የለውጥ እርምጃ መወሰድ እንዳለባቸው ተመላክቷል። የውሳኔዎቹ አተገባበርና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የታዳጊ ሀገራት ውክልና እና ለልማት የሚቀርበው የገንዘብ ድጋፍ ማደግ እንዳለበት ዋና ዋና የቅድመ ጉባኤው የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ተናግረዋል። ታዳጊ ሀገራትም ምቹ የልማት ምህዳር በመፍጠር የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በማሳደግ የገቢ አቅማቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው በቅድመ ጉባኤው ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል። የአፍሪካንና ታዳጊ ሀገራትን ድምጽ በማሰማት ሂደትም ኮንፍረንሱ ስኬታማ ነበር ብለዋል። አዲስ አበባም በስኬታማ የኮሪደር ልማት የቱሪዝም መዳረሻ ስራዎቿ ተውባና ደምቃ እንግዶቿን በልዩ ሁኔታ ማስተናገድ እንደቻለች አስረድተዋል። የቅድመ ጉባኤው ተሳታፊዎችም በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን የመዲናዋን የአፍሪካ ማዕከልነት ታሳቢ በማድረግ የተከናወኑ መሆናቸውን በአድናቆት እንደገለጹ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የወሰደችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጠናክራ በመቀጠል የተሻለ ለውጥ የምታመጣ ሀገር መሆኗን በምሳሌነት የተነሳበት እንደነበር አስታውቀዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ተቋማት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ልዑልሰገድ ታደሠ፤ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ሥርዓት የታዳጊ ሀገራትን የልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ማሻሻያ ማድረግ እንዳባቸው ታምናለች ብለዋል።   የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍም ዘላቂ ልማት ግቦችን መፈጸም በሚያስችል መልኩ አሳታፊና ሁሉን ዓቀፍ መሆን እንዳለበት ድምጿን ስታሰማ እንደቆየች ገልጸዋል፡፡ "በአዲስ አበባ አክሽን አጀንዳ" ፍትሕዊ የዓለም አቀፍ ገንዘብ ሥርዓት እንዲፈጠር መወሰኑን አስታወሰው፤ በኮንፍረንሱም ፍትሕዊ የገንዘብ ተቋማት ሥርዓት መዘርጋት እንዳለባቸው በአጀንዳነት ተይዟል ብለዋል። በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ፤ በስኬት ለተጠናቀቀው 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ስኬት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ የተቋማት ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።   የቅድመ ጉባኤው ተሳታፊዎችም በአዲስ አበባ በመንቀሳቀስ በመዲናዋ የተመዘገበውን ተጨባጭ የኮሪደር ልማት ለውጦች በአድናቆት ምላሽ መስጠታቸውን አንስተዋል። የኢትዮጵያ ትክክለኛ መገለጫ ልማትና ብልጽግና ነው ያሉት አምባሳደር ተስፋዬ፤ የቅድመ ጉባኤው ተሳታፊዎችም የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ተገንዘብው እንደሚሄዱ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል። በጉባኤው ላይ የመንግስታቱ ድርጅት የምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሃፊ ሊ ጁንዋ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ክላቨር ጋቴቴ ጨምሮ ከ850 በላይ የድርጅቱ አባል ሀገራት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል። የተጠናቀቀው 4ኛው የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ልማት የቅድመ ጉባኤ እ.አ.አ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 3/2025 በስፔን ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ የተዘጋጀ መድረክ አካል መሆኑ ተገልጿል።    
በክልሉ በከተማ ልማት ክላስተር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ውጤት ተመዝግቧል-አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር )
Jul 26, 2024 114
ደሴ ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በከተማ ልማት ክላስተር የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በማከናወን አበረታች ውጤት መመዝገቡን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተሞች ልማት ክላስተር አስተባባሪና የከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር ) ገለጹ። የአማራ ክልል ከተሞች ልማት ክላስተር የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ በደሴ ከተማ ተካሄዷል።   አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የከተማ ልማት ክላስተሩን በመደገፍና በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ኢኮኖሚውን ያነቃቃ ተግባር ተከናውኗል። በዚህም በስራ እድል ፈጠራ፣ ከተሞችን በሁለንተናዊ መንገድ በማልማት፣ ገበያውን በማረጋጋት የኑሮ ውድነትን በመከላከል፣በኢንቨስትመንትና ሌሎች ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በከተማ ልማት ክላስተር የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በማከናወን አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ/ር)በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ገበያውን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል። በዚህም መንግስት በመደበው 689 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር እና ዩኒየኖችና ህብረት ስራ ማህበራት በራሳቸው በመደቡት 420 ሚሊዮን ብር የተለያዩ ምርት ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰዋል። በዚህም 713 ሺህ ኩንታል በላይ ኢንዱስትሪና የግብርና ምርት እና አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት በማቅረብ ገበያውን የማረጋጋት ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል። አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ አዳዲስ ባለሃብቶችን ወደ ክልሉ መሳብ መቻሉን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ናቸው። በዚህም ከ564 ሺህ ቶን በላይ ተኪ ምርት በማምረት ከውጭ የሚመጣውን ምርት በአገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን አብራርተዋል። በተለይም ''የኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ ውጤት እንዲመዘገብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ በዘርፉ ከ44 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል። እንደ አቶ እንድሪስ ገለጻ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ437 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 2 ሺህ 650 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷል። የክልሉ መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ፤ በክልሉ የመሬት አያያዝና አስተዳደር ስርዓቱን በማዘመን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የተደረገው ጥረት አበረታች ነው ሲሉ ገልጸዋል። በዚህም ከ388 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠቱን ጠቅሰዋል። በተሰጣቸው የይዞታ ማረጋገጫ ደብተርም 3 ሺህ 200 የሚበልጡ አርሶ አደሮች ከአበዳሪ ተቋማት ከ161 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንዲወስዱ መመቻቸቱን ተናግረዋል። በመድረኩ የክልል ከፍተኛ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።  
በኢትዮጵያ የተካሄደው 4ኛው የፋይናንስ ለዘላቂ ልማት ጉባዔ የቅድመ ዝግጅት ስብሰባ ተጠናቀቀ
Jul 26, 2024 126
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016 (ኢዜአ):- በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 4ኛው አለምአቀፍ የፋይናንስ ለዘላቂ ልማት ጉባዔ የቅድመ ዝግጅት ስብሰባ ተጠናቀቀ። እ.ኤ.አ. ከጁላይ 22-26 ቀን 2024 ሲካሄድ የቆየው ጉባኤ ሲጠናቀቅ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ባለፉት አምስት ቀናት የተካሄዱት ውይይቶች ጥልቅ ሀሳቦች የተነሱበት መሆኑን ጠቁመው፣ መንሸራሸር ያለባቸው ሀሳቦችም በጉባዔው ለውይይት መቅረባቸውንም ጠቅሰዋል።   በኮንፈረንሱ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት፣ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያሉ የስርዓት ችግሮችን ለመፍታት እና በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ አለምአቀፍ ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ለመዘርጋት ያስቻለ መድረክ መሆኑንም ተጠቅሷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሃፊ ጁንዋ ሊ በመዝጊያው ላይ በሰጡት አስተያየት ጉባኤው በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ለመወያየት እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለመፍጠር መምከሩን አመልክተዋል። ምክትል ዋና ጸሃፊ ጁንዋ ሊ ለጉባኤው ስኬታማነት የኢትዮጵያ መንግስት ላደረገው ደማቅ አቀባበል እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ምስጋና ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
በሲዳማ ክልል ህዝቡ የሰላም እሴቶቹን አጠናክሮ በመቀጠሉ በልማት ተጠቃሚ ሆኗል-ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
Jul 26, 2024 81
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል ህዝቡ የቆዩ እሴቶቹን በመጠቀም የጸጥታ ኃይሉን የሰላም ግንባታ ስራዎች አጠናክሮ በመቀጠሉ በልማት ተጠቃሚ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ። የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው፥ የክልሉ ፖሊስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታገዘ የወንጀል መከላከል ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል። የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የክልሉ መንግስት ከአራት ዓመት በፊት በይፋ ስራውን ሲጀምር ተቋማትን ከማደራጀት ጎን ለጎን ህዝቡን ለሰላም ዘብ እንዲቆም ተደርጓል። የሲዳማ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ የጸጥታ ችግሮች ሲፈጠሩ በውይይት የሚፈታባቸው እንደ "አፊኒ" ያሉ ባህላዊ ስርዓቶች አሉት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በዚህም ሰላምንና መረጋጋትን በማፅናት ሂደት አይተኬ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።   አሁን ላይ በክልሉ ምንም ዓይነት የጸጥታ ስጋት የለም ያሉት አቶ ደስታ፥ ህዝቡ ጠንካራ የጸጥታ ተቋማት እንዲፈጠሩ በማድረግና የሰላም ዘብ በመሆን በዕለት ተዕለት ህይወቱና በልማት ተጠቃሚ እንደሆነም ገልጸዋል። የክልሉ መንግስትም ሙሉ ትኩረቱን ወደ ልማት ማዞሩን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ፍሰትን እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው ከጥቂት ዓመታት በፊት በክልሉ ውስጥና በአዋሳኝ አካባቢዎች የግለሰቦችን ጸብ የብሔር መልክ በመስጠት ከግጭት ሊያተርፉ በሚፈልጉ ሃይሎች ምክንያት ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር አውስተዋል።   የክልሉ መንግስት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሰላም ወዳዱ ህዝብ ባደረጉት ጥረትም ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ወደ አስተማማኝ ሰላም ተሸጋግረናል ነው ያሉት። በሲዳማ ክልል በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እንደሚኖሩ ያነሱት አቶ አለማየሁ፥ በህዝብና በፀጥታ ሃይሎች የተቀናጀ ስራ ሁሉም ብዝሃነትን ጠብቆ በአንድነትና በፍቅር የሚኖርበት ክልል ፈጥረናል ብለዋል። ህብረተሰቡ ወንጀልን ለመከላከል ከሚያደርገው ርብርብ ባሻገር በየወረዳው ለወንጀል መከላከል የሚያገለግሉ ፖሊስ ጣቢያዎች እንዲገነቡ ትልቅ አሻራ ማሳረፉን አንስተዋል። ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት የመጨረሻ ሩብ ዓመት ብቻ በህብረተሰቡ ተሳትፎ በ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ 44 የፖሊስ ጽህፈት ቤቶች ግንባታ በመጀመር የ32ቱን ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል። የቀሪዎቹ ግንባታም በተያዘው ወር መጨረሻ ይጠናቀቃል ያሉት አቶ አለማየሁ፥ በ58 ቀበሌዎች ፖሊሳዊ ስምሪት መስጫና መረጃ መቀበያ ማዕከላት መገንባታቸውንም አመላክተዋል።   የቢሮ ኃላፊው አክለውም የክልሉ ፖሊስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታገዘ የወንጀል መከላከል ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለአብነትም የብዝሃ ኢትዮዮጵያውያን መኖሪያ በሆነችው ሀዋሳ ከተማ 889 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደህንነት ካሜራዎችን በመግጠም ስውር ወንጀሎችን የማስቀረት ስራን እያገዙ ነው ብለዋል። በቀጣይም በዞን ከተሞች የፖሊስና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በቴክኖሎጂ የማደራጀት ስራ ይሰራል ብለዋል። የፀጥታ ኃይሉ ሙያዊ ስራውን በዲሲፕሊን እንዲፈጸም የአቅም ግንባታ ስራዎች መቀጠላቸውን ያነሱት ኃላፊው፥ የስነምግባር ጉድለት በታየባቸው አመራሮች ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።  
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ 57 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ
Jul 26, 2024 70
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016 (ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ 57 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር ገቢ በመሰብሰብ ከ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ። ኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፤ በ2016 በጀት ዓመት በተቋሙ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትንና የ2017 ዓ.ም እቅድን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህም የገቢ መጠን ማሳደግ፣ የመርከቦችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን የመጫን አቅም መጨመር፣ ፈጣንና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠትና በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን ማጎልበት በበጀት ዓመቱ በትኩረት የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል። ከዚህ አንጻር ተቋሙ 51 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን በማስታወስ፤ አፈጻጸሙ ግን ከፍተኛ እመርታ በማሳየት 57 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉንም አክለዋል። በተመሳሳይ በ2016 በጀት ዓመት 6 ነጥብ 70 ቢሊየን ለማትረፍ አቅዶ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ መገኘቱንም ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ የተገኘው የገቢም ሆነ የትርፍ ምጣኔ ከእቅዱ አንጻር መቶ በመቶ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑንም አክለዋል። ይሁንና በዓለም ላይ ባሉ በተለያዩ ግጭቶች ሳቢያ መርከቦች በታለመላቸው ልክ እቃዎችን እንዳያጓጉዙ እንቅፋት መሆኑን አስታውሰዋል። በዚህም ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ተለዋዋጭ የሰላም ሁኔታዎች ባልተረጋገጡበት ወቅት ይህ ውጤት መመዝገቡ የሚበረታታ መሆኑንም በመግለጫቸው አብራርተዋል። በተያዘው በጀት ዓመት የተቋሙን የሪፎርም ስራዎችን ማጠናቀቅ፣ ዲጂታላይዝ አገልግሎቶችን በሁሉም መስክ ተደራሽ ማድረግ፣ የተሽከርካሪ የመጫን አቅም መጨመር ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አንስተዋል። እንዲሁም የመርከቦችን ብዛት በቁጥር መጨመርና ተጨማሪ የኮንቴነር ግዢ መፈጸም በቀጣይ በጀት ዓመት የሚከናወኑ ተግባራት ስለመሆናቸው አብራርተዋል።    
የኢትዮጵያንና የሩሲያን ወዳጅነት የሚመጥን ኢንቨስትመንት በኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን እንዲኖር እንፈልጋለን- ፍስሃ ይታገሱ(ዶ/ር)
Jul 26, 2024 68
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦የሩሲያንና የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚመጥን የሩሲያ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር እንፈልጋለን ሲሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብር ኮሚቴ ልዑካን ቡድን አባላትን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከልዑካን ቡድኑ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኮርፖሬሽኑ ስር በሚተዳደሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ስለሚገኙ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎች ፤ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችና ዝግጁ ስለተደረጉ መሰረተ ልማቶች ዝርዝር ገለጻ አድርገዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ ከኤምባሲዎች ፤ ከአለም አቀፍ ማህበራትና ልማት ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ዶክተር አለሙ ስሜ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ባሉት የኢንቨስትመንት እድሎች ዙሪያ ከተለያዩ ሀገራት ባለሃብቶች ጋር ተወያዩ
Jul 26, 2024 75
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ባሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ዙሪያ ከተለያዩ ሀገራት ከተውጣጡ የዓለም አቀፍ የንግድና ፋይናንስ ተቋም ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ በውይይቱም ዶክተር አለሙ ስሜ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ 27 የሚሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች ተለይተው የአዋጭነት ጥናት እና ወጪ ግምት ስራ መሰራቱን አስረድተዋል፡፡   ሚኒስትሩ አክለውም በዘርፉ ካሉት የኢንቨስትመንት መስኮች ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እና የኃይል መሙያ ማሽን ቅድሚያ የሚሰጠው እና የመንግስት ተቀዳሚ የትኩረት መስክ መሆኑን ገልጸዋል። በውይይቱ ላይ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እና የኃይል መሙያ ማዕከል፣ በሎጂስቲክስ፣ በባቡር እና መንገድ መሰረተ ልማት እንዲሁም ተጨማሪ የደረቅ ወደብ ግንባታ የኢንቨስትመንት እድሎች ዙሪያ ለባለሃብቶቹ ገለፃ ተደርጓል፡፡ የባለሀብቶቹ ቡድን በኢትዮጵያ ባለው ምቹና አዋጭ የቢዝነስ ከባቢ መሳባቸውን እና በትራንስፖርትና ሊጂስቲክስ ዘርፍ ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለቸው መግለጻቸውን ከሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በኦሮሚያ ክልል በየደረጃው ያለው አመራር በተገኙ ስኬቶች ሳይዘናጋ ለተሻለ ውጤት መረባረብ አለበት - አቶ ሽመልስ አብዲሳ
Jul 26, 2024 94
አዳማ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በየደረጃው ያለው አመራር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተገኙ ስኬቶች ሳይዘናጋ ለተሻለ ውጤትና ለውጥ መረባረብ እንዳለበት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አሳሰቡ። የኦሮሚያ ክልል ላለፉት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የክልሉን መንግስት የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት አጠናቋል።   በማጠናቀቂያ መርሃ ግብሩ ላይ በሰላምና ፀጥታ፣ በልማት ስራዎች፣ በአገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር ማስፈን የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ከቢሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ላሉ የአስተዳደር መዋቅሮች እውቅና ተሰጥቷል። በዚህ ወቅት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደገለፁት፤ በተያዘው በጀት ዓመት የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል። የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ የተለጠጠ በመሆኑ አመራሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተገኘው ውጤት ሳይዘናጋ እቅዱን ለመፈጸም ከአሁኑ ርብርቡን ማጠናከር አለበት ብለዋል። የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ክፍተቶችን በማስተካከልና ጠንካራ ጎኖችን እንደ ግብዓት በመጠቀም ሁሉም አመራር በሙሉ ወደ ስራ መግባት አለበት ሲሉም አሳስበዋል። የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገብ ዕውቅና የተሰጣቸው ቀበሌዎች፣ ወረዳዎች፣ ከተሞች፣ ዞኖችና የክልሉ ተቋማት የቤት ስራቸውን በተሻለ ደረጃ በመፈፀም ምሳሌነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። በተያዘው በጀት ዓመት በሁሉም የልማት መስኮች አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረገም ገልጸዋል።   በእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብሩ በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ የሸገር፣ የአዳማ እና የቢሾፍቱ ከተሞች፤ ከዞኖች ደግሞ ምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ ሐረርጌ እና ምስራቅ ሐረርጌ ከ1ኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ወጥተዋል። ከክልሉ መንግስት መስሪያ ቤቶች ደግሞ ጤና ቢሮ፣ ግብርና ቢሮ እና የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እንደ ቅደም ተከተላቸው እውቅና ተሰጥቷቸዋል። እውቅና ለተሰጣቸው ሁሉም ተቋማት ተሽከርካሪ፣ ሞተር ብስክሌት እንዲሁም የምስክር ወረቀትና ሜዳልያ ተበርክቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ  በ2016 በጀት ዓመት ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ
Jul 26, 2024 74
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ በ2016 በጀት ዓመት ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ። በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ 57 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉንም ገልጿል። የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ ፤ በ2016 በጀት ዓመት በተቋሙ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህም የገቢ መጠን ማሳደግ፣ የመርከቦችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን የመጫን አቅም መጨመር፣ ፈጣንና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠትና በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን ማጎልበት በበጀት ዓመቱ በትኩረት የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል። ከዚህ አንጻር በ2016 በጀት ዓመት 6 ነጥብ 70 ቢሊየን ለማትረፍ ታቅዶ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ መገኘቱን ገልጸዋል። በተመሳሳይ ተቋሙ 51 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን በማስታወስ አፈጻጸሙ ግን ከፍተኛ እመርታ በማሳየት 57 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉንም አክለዋል።          
ግብርና ሚኒስቴር ወጣቶችን በንብ ማነብ ሥራ በብዛት ማሳተፍ የሚያስችል ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ
Jul 26, 2024 72
አዳማ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ ግብርና ሚኒስቴር ወጣቶችን በንብ ማነብ ሥራ በብዛት ማሳተፍ የሚያስችል ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን በሚኒስቴሩ የእንስሳትና አሣ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፅጌረዳ ፍቃዱ ገለጹ። የአምስት ዓመት የማርና የንብ ሀብት ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብርና የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው። በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሣ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፅጌረዳ ፍቃዱ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በዓመት ከ500 ሺህ ቶን በላይ ማር ማምረት የሚያስችል እምቅ አቅም አላት። በ2014 ዓ.ም የማር ልማት ኢንሼቲቭ ተግባራዊ ማድረግ ስንጀመር 146 ሺህ ቶን የማር ምርት በዓመት አምርተን ነበር ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 276 ሺህ ቶን ማምረት ተችሏል ብለዋል። በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 473 ሺህ ቶን ማር ለማምረት ግብ የተቀመጠ ሲሆን ለዚህም 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ጥራቱን የጠበቀ ዘመናዊ የንብ ማነቢያ ቀፎ ይሰራጫል ነው ያሉት።   የማር ምርት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና ለአርሶ አደሮች ገቢ ማግኛ ምንጭ እንዲሆን ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩንም ገልጸዋል። የዛሬው መድረክ ዓላማም በንብ ማነብ ሥራ አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑ ወጣቶች በዘርፉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ባለድርሻ አካላትን በስፋት ለማሳተፍና የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ነው ብለዋል። ከሚኒስቴሩ ጋር ከሚሰሩ ባለድረሻ አካላት መካከል አንዱ ዓለም አቀፍ 'ኢንሴክት ፊዚዮሎጂና ኢኮሎጂ' ማዕከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። የማዕከሉ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ታደለ ተፈራ እንደገለጹት በቀጣይ አምስት ዓመታት አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶችን በማር ልማት ለማሰማራት 80 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መመደቡን አስታውቀዋል።   ገንዘቡ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን መገኘቱን ገልጸው፣ በፕሮግራሙ 80 በመቶ የሚሆኑ የገጠር ሴት ወጣቶች በስፋት በማር ልማት እንዲሳተፉ በማድረግ የስራ አጥነት ችግርን ለማቃለል ያግዛል ብለዋል። በፕሮግራሙ የፋይናንስና የአቅም ግንባታ ድጋፍ፣ የገበያ ትስስር መፍጠር እና በገበያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የክህሎት፣ የኢንተርፕርነርሽፕና የገበያ ስልጠና ለወጣቶች እንደሚሰጥ ገልጸዋል። በዚህም የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ውጤታማነትን ከማረጋገጥ ባለፈ በዓለም አቀፍ ገበያ ኢትዮጵያን በማር ምርት ተደራሽና ተወዳዳሪ ለማድረግ በምርት ጥራትና ብዛት ላይ የሚሰራውን ስራ ይደግፋል ብለዋል። በተጨማሪም የማር አምራች የእሴት ሰንሰለት ለማሳደግ፣ የማር ምርት ጥራትና የማር አልሚ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎን ለማጠናከር ከሚኒስቴሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ነው ያሉት። ፕሮግራሙ በ11 ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል። አዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች የመጡና በማር ልማት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አጋር አካላት ተሳትፈዋል።  
የጋምቤላ ክልል ዋና ኦዲተር የገንዝብ ጉድለትና ያልተወራረደ የሰነድ ክምችት ማግኘቱን አስታወቀ
Jul 26, 2024 66
ጋምቤላ ፤ ሐምሌ 19/2016 (ኢዜአ)፦የጋምቤላ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ባካሄደው የፋይናንስ ኦዲት የገንዝብ ጉድለትና ያልተወራረደ የሰነድ ክምችት ማግኘቱን አስታወቀ። የመስሪያ ቤቱ ዋና ኦዲተር አቶ ኡጁሉ ኡጁሉ ለክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመለከቱት፤ የጥሬ ገንዘብ ጉድለቱ፣ ያልተወራረደ የሰነድ ክምችቱና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ወጪዎች የተገኙት በ57 የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና ድርጅቶች በተካሄደ የፋይናንስ ኦዲት ነው። በመስሪያ ቤቶቹ ላይ የተመላከተው ግኝት በ2014/2015 በጀት ዓመታት በነበራቸው የፋይናንስ አፈፃፀም ላይ በተካሄደ የሒሳብ ምርመራ መሆኑን አመልክተዋል። ከግኝቶች መካከል ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ከ83 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ ያልተወራረደ ሰነድ ክምችት እንዲሁም ከ24 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ደረሰኝ ያልተቆረጠለት ተንጠልጣይ ሰነድ መገኘቱን ተናግረዋል። ዋና ኦዲተር አቶ ኡጁሉ እንደገለጹት፤ ከአገልግሎት ክፍያ ታክስ ተቀናሽ ሆነው ለሚመለከተው መስሪያ ቤት ፈሰስ ያልተደረገ ከሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ለብክነት ተዳርጓል። የመንግሥት የግዥ መመሪያን ባልተከተለ መልኩ ደግሞ ከ19 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አመልክተዋል። እንዲሁም ከመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ተቀናናሽ መዋጮ ከስድስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ ለሚመለከታቸው ተቋማት ፈሰስ ሳይደረግ መገኘቱንም አቶ ኡጁሉ ተናግረዋል። መስሪያ ቤቱ ግኝቶችን ለማስመለሰ ከፍትህ ቢሮ፣ ለክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን ከክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።   የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የኦዲት ሪፖርትን አስመልክተው የኦዲት መስራያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል። ''በተለይም ግኝቶችን ለማስመለስ ከፍትህ ቢሮ ጋር የጀመራቸው ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው'' ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአዲሱ በጀትም ጅምር ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል። ''ኦዲት መስሪያ ቤቱ በሒሳብ ምርመራ ያገኛቸውን ግኝቶች ተመላሽ በማያደርጉ አካላት ላይ በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራዎችን ሊከናወን ይገባል'' ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ቢይ ኡጌቱ ናቸው። ምክር ቤቱ በእስካሁኑ ሂደት የክልሉን የ2016 በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር ፣የኦዲትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የእቅድ ክንውን ሪፖርቶችና እንዲሁም የ2017 የልማትና የመልካም አሰተዳደር እቅድ ላይ ከተወያየ በኋላ አጽድቋል። ጉባኤው በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ውይይት እንደቀጠለ ነው።      
የባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ተኪ ምርት በማምረት ከውጭ የሚገባውን ለማስቀረት የድርሻውን እየተወጣ ነው
Jul 26, 2024 116
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 19/2016 (ኢዜአ)፦ የባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ለተለያዩ አልባሳት አገልገሎት የሚውሉ ተኪ ምርቶችን በማምረት ከውጭ የሚገባን ለማሰቀረት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አስታወቁ። ፋብሪካው ለአንድ ሺህ 200 ሠራተኞች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑም ተገልጿል። ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ መንግስቱ አረጋ እንዳሉት፤ ፋብሪካው ቀደም ሲል ኪሳራ ውስጥ ገብቶ የነበረበትን አሰራር ለይቶ በማሻሻል አመርቂ የማምረት ደረጃ ላይ ይገኛል። በዚህም 90 በመቶ የሃገር ውስጥ የጥጥ ምርት በግብዓትነት በመጠቀም የማምረት ስራውን መቀጠሉን ለኢዜአ ተናግረዋል።። በዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ ከጥጥ የተሰሩ አንሶላና የተለያዩ አልባሳትን በጣቃና ያለቀላቸውን ተኪ ምርቶች በማምረት ለአገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም ከፖሊስተር የሚመረቱ ክሮችን በማምረት ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል። ፋብሪካው እያደረገው ባለው የማምረት እንቅስቃሴ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አሰረድተዋል። በዚሁ ጥረትም አገራዊ ''የኢትዮጵያ ታምርት'' ፕሮግራም ተሸላሚ መሆን እንደቻለም ጠቅሰዋል። ጨርቃጨርቅ ፋብሪካው ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሜትር የአልባሳት ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልጸው፤ ባለፈው ዓመት በተደረገ የስራ እንቅስቃሴም 114 ሚሊዮን ብር የምርት ሽያጭ ማከናወኑን አስረድተዋል። ከዚህም 81 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘት መቻሉንም አስታውቀዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም 600 ሚሊዮን ብር ድረስ ሽያጭ ለመፈጸም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ፋብሪካው ለአንድ ሺህ 200 ሠራተኞችን የስራ እድል በመፍጠር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አመልክተዋል። ፋብሪካው አካባቢያዊ ብክለተን ለመጠበቅም ደረጃውን የጠበቀ የፍሳሽ ማስወገጃ /ትሪትመንት/ ገንብቶ እየተጠቀመ እንደሆነም ገልጸዋል።   በፋብሪካው የስራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አቶ አዲሱ መኮንን በሰጡት አስተያየት፤ ፋብሪካው የሠራተኛውን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያተጋ ነፃ ህክምናን ጨምሮ የሚገባውን ጥቅማ ጥቅም በማመቻቸት እየደገፋቸው መሆኑን ተናግረዋል።   ስራቸውን በአግባቡ በማከናወን ድርጅቱም መብትና ጥቅማቸውን እያከበረላቸው ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ የስራ እድል ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ ገበያነሽ አረጋው ናቸው። የባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ከተቋቋመ ከ60 ዓመት በላይ እንዳስቆጠረ ከፋብሪካው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።    
በክልሉ ከ207 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማ ጤፍ እየተሰበሰበ ነው 
Jul 26, 2024 70
ሮቤ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በበልግ አዝመራ ከ207 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማ የጤፍ ሰብል በኮምባይነር በመታገዝ እየተሰበሰበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች በምሥራቅ ባሌ ዞን በመካናይዜሽን ታግዞ እየተሰበሰበ የሚገኘውን የጤፍ ሰብል በስፍራው ተገኝተው ተመልክተዋል። በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳሬክተር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ በበልግ አዝመራ የለማ ከ207 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማ ጤፍ እየተሰበሰበ ነው።   የጤፍ ሰብሉ የለማው በባሌና ምስራቅ ባሌ ዞኖች እንዲሁም በሌሎች በልግ አብቃይ የክልሉ አካባቢዎች መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይ የምሥራቅ ባሌ ዞን ከክልሉ በልግ አብቃይ አካባቢዎች አንዱ ሲሆን የእዚህ አካባቢ የበልግ ወቅትም ከግንቦት መጀመሪያ እስከ ሀምሌ መጨረሻ መሆኑን አንስተዋል። የምሥራቅ ባሌ ዞን አርሶ አደሮችም ዘንድሮ በበልግ አዝመራ ያለሙትን ጤፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ኮምባይነር ተጠቅመው ምርት እየሰበሰቡ ሲሆን ይህም ለሌችም አካባቢዎች በተሞክሮነት የሚወሰድ እንደሆነ ገልጸዋል። አቶ ሙስጠፋ እንዳሉት በክልሉ እስከ አሁን በተደረገው ጥረት በበልጉ ወቅት በጤፍ ሰብል ከለማው ከ207 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ምርት ተሰብስቧል። ሰብልን በቴክኖሎጂ ታግዞ መሰብሰብ ሊደርስ የሚችለውን የምርት ብክነት ከማስቀረቱም በላይ ጥራቱ የተጠበቀ ምርት በጊዜ ሰብስቦ ለገበያ ለማቅረብ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው አክለዋል። በምሥራቅ ባሌ ዞን የደረሰ ሰብልን ከኮምባይነር በተጨማሪ በጥቃቅን መሽኖችና በሰው ጉልበት የመሰብሰቡ ሥራም ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሰብሪያ አብዱቄ ገልጸዋል።   በዞኑ በበልጉ ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘሮች ከለማው 152 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 18 ሺህ ሄክታር የሚጠጋው በጤፍ የለማ መሆኑን አመልክተዋል። ከከምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል በከር አህመድ፣ በበልግ አዝመራ ያለሙትን የጤፍ ሰብል በኮምባይነር በመታገዝ እየሰበሰቡ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም ይደርስ የነበረውን ብክነት በማስቀረት ከአንድ ሄክታር 28 ኩንታል ምርት ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል። በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የበልግ ምርት ወቅት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መልማቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።  
የአፍሪካ አገራት ከብሉ ኢኮኖሚ ትሩፋቶች ለመቋደስ ለውሃ ሀብቶች ጥበቃ በልዩ ትኩረት መስራት አለባቸው - የአፍሪካ ሕብረት  
Jul 25, 2024 102
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦የአፍሪካ አገራት ከብሉ ኢኮኖሚ ትሩፋቶች ተቋዳሽ ለመሆን የውሃ ሀብቶች ጥበቃ ላይ በተለየ ትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የአፍሪካ ሕብረት አሳሰበ። አራተኛው የአፍሪካ የባህርና የውቅያኖስ ቀን ዛሬ በአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተከብሯል። የአፍሪካ ሕብረት የዘላቂ ከባቢ አየርና ብሉ ኢኮኖሚ ዳይሬክተር ሃርሰን ንያምቤ ንያምቤ ብሉ ኢኮኖሚ (ውቅናኖስ፣ባህርና ሌሎች የውሃ ሀብቶች) ለአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ዘርፍ ነው ብለዋል። የአፍሪካ ሕብረት የብሉ ኢኮኖሚና የማሪታይም ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ወደ ትግበራ ማስገባቱን አንስተው ለአባል ሀገራትም ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል። ለትራንስፖርት፣ ለንግድና ለአገልግሎት ዘርፍ እድገት እንዲሁም ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ ውጤታማነት ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል። ይሁንና የአየር ንብረት ለውጥና በውሃ ብዝሃ ሕይወት ላይ የሚያጋጥም አሲዳማነት በብሉ ኢኮኖሚ ልማት ትልቅ ፈተናና ከጋረጡ ጉዳዮች መካከል እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል። በዘርፉ ያሉ ፈተናዎች መፍትሔ ለማበጀት የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግና ሀገራት ዘላቂነት ያለውን የውሃ ሀብት አጠቃቀም ለማሳካት ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።   የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የአፍሪካ ቀጣናዊ አገልግሎት ማዕከል ተጠባባቂ ዳይሬክተር ኖኒ ማፋቡኔ በበኩላቸው የብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ ለአፍሪካ ብዙ እድሎች ይዞ ቢመጣም የተለያዩ ፈተናዎች እንዳሉበት ገልጸዋል። ሕገ ወጥ ዓሳ ማስገርና ብክለት የውሃና ውሃ አዘል ሀብቶችን ሕልውና አደጋ ላይ እንዳይጥሉ የክብካቤና የጥበቃ ስራ ትኩረት እንደሚያሻውና ለዚህ የጋራ ትብብር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። ዩኤንዲፒ ለአፍሪካ ብሉ ኢኮኖሚ እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።   የአፍሪካን የግሉ ዘርፍ ወክለው ንግግር ያደረጉት የዓሳና አሳ ውጤቶች አምራች የሆነው የካቲ ፋርምስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሎቪን ኮቡሲንግዬ አፍሪካ በብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ በጥሩ መንገድ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል። የብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ አጀንዳ 2063ን ጨምሮ በአፍሪካ ደረጃ የተያዙ አጀንዳዎችን ከዳር ለማድረስና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል። የግሉ ዘርፍም አፍሪካ የውሃ ሀብቶችን በዘላቂነት ተጠቅማ በኢኮኖሚ ለማደግ የያዘችውን ውጥን እውን ለማድረግ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።   በአፍሪካ ሕብረት የኖርዌይ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ ሲን ኤሚሊ ብዮርንራ፤ ከዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጋር የተሳሰሩት የውሃ ሀብቶች ረሃብን፣ ድርቅንና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል እድገትና ልማትን ለማምጣት ወሳኝ ናቸው ብለዋል። ኖርዌይ በብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ የአፍሪካ አጋር መሆኗን ጠቅሰው አህጉሪቷ በዘርፉ ለማሳካት የያዘቻቸውን ግቦች መደገፏን እንደምትቀጥል አመልክተዋል። በአፍሪካ የባህርና ውቅናያኖስ ቀን አከባበር ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አመራሮች፣ የሕብረቱ አባል ሀገራት ተወካዮች፣ የዘርፉ ተዋንያንና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል። የአፍሪካ የባህርና ውቅያኖስ ቀን የአፍሪካ ውሃማ አካላት ሳምንት መርሐ ግብር አካል ነው። ቀኑ በአፍሪካ ያሉ ውሃና ውሃ አዘል ሀብቶች ዘላቂ በሆነ መንገድ መጠቀም ከተቻለ ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለከባቢ አየር ጤናማነት ያለውን ጠቀሜታ ማስገንዘብን አላማ አድርጓል። በተጨማሪም የብሉ ኢኮኖሚ ሀብቶችን ለመጠቀም የጋራ ትብብር ማሳደግ እንዲሁም ሴቶችና ወጣቶችንን ጨምሮ ሁሉን አሳታፊ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቶታል። የአፍሪካ ባህርና ውቅያኖስ ቀን ከእ.አ.አ 2021 አንስቶ በመከበር ላይ ይገኛል። "የአፍሪካ ብሉ ኢኮኖሚ ሕዳሴን ማረጋገጥ" በሚል መሪ ቃል ከሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ ሲከበር የቆየው የአፍሪካ ብሉ ኢኮኖሚ ሳምንትም ዛሬ ተጠናቋል። ሳምንቱን በማስመልከት ላለፉት ቀናት ብሉ ኢኮኖሚን የተመለከተ አውደ ጥናት ተካሄዷል። ብሉ ኢኮኖሚ የውቅያኖስ፣ የባህርና ሌሎች የውሃ ሀብቶችን ለኢኮኖሚ እድገት መጠቀም ላይ ትኩረቱን ያደረገ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው።  
በአማራ ክልል ህብረተሰቡን በማስተባበር ሰፋፊ  የመሰረተ ልማት ስራዎች ተከናውነዋል- ዶክተር አህመዲን መሐመድ 
Jul 25, 2024 107
ደሴ፤ ሐምሌ 18/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ህብረተሰቡን በማስተባበር ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተሞች ልማት ክላስተር አስተባባሪና ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ገለጹ። ዶክተር አህመዲን መሐመድና ሌሎች ከፍተኛ አመራር አባላት በደሴ ከተማ የተለያዩ መሰረተ ልማት እንቅስቃሴዎችን ዛሬ ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ወቅት ዶክተር አህመዲን እንደገለጹት፤ በክልሉ በተለያዩ ከተሞች ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። ህብረተሰቡን በማስተባበር ጭምር በከተሞች መሰረተ ልማት በማሟላትና በማዘመን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተከናወኑት ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አስታውቀዋል።   በዚህም የመንግስትን ከፍተኛ ወጪ ሳይጨምር በህብረተሰቡ ተሳትፎ ብቻ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል። በተለይም በከተሞች የተጀመረው የኮሪደር ልማት አበረታች መሆኑን ጠቅስው፤ ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠልም የክልሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ዛሬ በደሴ ከተማ የተመለከቱት ልማትም ይህንኑ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ልማቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል። በከተሞች እየተሰሩ ያሉ ልማቶች ከተሞችንን ከማዘመንና ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለህብረተሰቡ የስራ እድል መፍጠራቸውንና የኢኮኖሚ ምንጭም እየሆኑ እንደሚገኝም አብራርተዋል።   ዶክተር አህመዲን፤ ህብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ ልማቱን በመደገፍ የጀመረውን ሁለተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል። የደሴ ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረት ልማት መምሪያ ስራ አስኪያጅ አቶ ቃሲም አበራ በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡን በማስተባበር የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እየተሰሩ ነው ብለዋል። በዚህም ውጤት በመመዝገቡ የከተማውን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለህብረተሰቡ የስራ እድል በመፍጠር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል። በጉብኝቱ የክልል፣ የዞንና የከተማው አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም