በታዳጊው የተሰራችው መኪና - ኢዜአ አማርኛ
በታዳጊው የተሰራችው መኪና
ለአዳዲስ ፈጠራ የማይታክተው ልጅዓለም ንጉሱ ትውልድና እድገቱ በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ወረዳ ፀመራ ቀበሌ ነው።
ከሕጻንነቱ ጀምሮ ፈትቶ መግጠምና አፍርሶ መስራትን እየተለማመደ የመጣው ልጅዓለም፤ ከቤት እስከ ትምህርት ቤት ያልተቋረጠ ፈጠራውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ከዚህ ቀደም ለሚማርበት ፀመራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከወዳደቁ ቁሶች የተለያዩ ቅርፃ ቅርፆችን በመስራት የፈጠራ አሻራውን አኑሯል።
በትምህርትና በፈጠራ ሥራው ገፍቶበት አሁን ላይ የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ልጅዓለም እንጨት ገጣጥሞ መኪና በመስራት ያለውን የጥበብና ፈጠራ ክህሎት አሳይቷል።
በታዳጊው የተሰራችውና በፔዳል የምትነዳው መኪና ሁለት ሰዎችን የማያዝ አቅም አላት።
በቀጣይ ተጨማሪ ቁሶችን በማቅረብና በተለያየ መንገድ የሚያግዘው ካገኘ መኪናዋ በዲናሞ እንድትንቀሳቀስ ለማድረግ መዘጋጀቱን ተናግሯል።
የተሽከርካሪውን አካል የገጣጠመው በአካባቢው አጠራር "እንቋ" የተሰኘ ዛፍ እንጨትን በመጠቀም ሲሆን የተሽከርካሪውን እግር ለማዘጋጀት ደግሞ የዋርካ ዛፍ ተጠቅሟል።
በዚህም መሰረት የልጅዓለም መኪና የመብራትና የመሪ ስራዋ ተጠናቆ ሁለት ሰዎችን ጭና መንቀሳቀስ እንደምትችል በተግባር አሳይቷል።
"በቀጣይ የሚያግዘኝና የሚደግፈኝ ካገኘሁ በዲናሞ የሚሰራ ተሽከርካሪ ለመስራት ዝግጁ ነኝ" ያለው ጥበበኛው ተማሪ ወደ ፊት ለሀገሬ ብዙ የመፍጠር ህልም አለኝ ብሏል።
የፀመራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ግርማ ጌቴ፤ ከዚህ በፊት ተማሪ ልጅዓለም በትምህርት ቤቱ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች እንዳሉት አስታውሰው ትምህርቱንም ፈጠራውንም አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የፈጠራ ክህሎቱን፣ ተሰጥኦውንና ፍላጎቱን ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ ተከታትያለሁ ያሉት መምህሩ የሳይንስ ትምህርቱንና የግል ክህሎቱን ደምሮ ለአዳዲስ ሥራዎች እየተጋ መሆኑን አንስተው፣ የመኪና ፈጠራውም ይህንኑ በተግባር ያሳየበት ነው ብለዋል።
የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ ከተደረገለት የተሻለና ውጤታማ ሥራ መስራት እንደሚችል ገልጸው ለሚፈጥሩ ወጣቶች በጥሩ ምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
በእንጨት የተገጣጠመችው መኪና በሁላችንም ድጋፍ የዲናሞ፣ የብረትና ሌሎች አስፈላጊ ቁሶች ከተሟሉላት በታዳጊው ጥበብ የተሻለች መኪና ሆና ልትሰራ ትችላለች ሲለም እምነታቸውን ገልጸዋል።