የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት የላቀ አገልግሎት ለመስጠት የቴክኖሎጂና ዲጂታል መሰረተ ልማት ይገነባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት የላቀ አገልግሎት ለመስጠት የቴክኖሎጂና ዲጂታል መሰረተ ልማት ይገነባል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ተቋማዊ አቅምና ዝግጁነትን ለማሳደግ፣ ዜጋ ተኮር የላቀ አገልግሎት ለመስጠት የቴክኖሎጂና ዲጂታል መሰረተ ልማት ለመገንባት ይበልጥ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት የመንግስት አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ዜጋ-ተኮር ማድረግ የሚያስችል የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድና ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርጓል፡፡
ፍኖተ ካርታው የ«ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» ስትራቴጂን መነሻ በማድረግ፣ የዜጎችን የአገልግሎት ተደራሽነት፣ ጥራትና ቅልጥፍና ማሳደግ የሚያስችሉ ቁልፍ የለውጥ አቅጣጫዎችን አካቷል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አለማየሁ በመድረኩ እንደገለጹት፤ ፍኖተ ካርታው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቀጣይ ሶስት ዓመታት ምን ዓይነት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መገንባት እንዳለበት በግልጽ የሚያመላክት ሰነድ ነው።
የስትራቴጂክ ዕቅዱ መሠረትም መሶብ ባለፈው አንድ ዓመት ያከናወናቸውን ሥራዎች በመገምገም፣ በቀጣይ የሚከናወኑ የዲጂታል ሽግግር፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እና ተቋማዊ አቅም ግንባታ ሥራዎችን የሚመራ ይሆናል ብለዋል።
ዕቅዱ ከ«ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» ራዕይ፣ ከሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም አቅጣጫዎች እና ከሀገራዊ የዲጂታል ልማት ግቦች ጋር ተጣጥሞ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በአገልግሎቱ የእቅድና ፕሮግራም ዳይሬክተር ደሳለኝ ድንገታ ባቀረቡት ጽሁፍ፤ በመሶብ የተዘጋጀው ስትራቴጂያዊ ፍኖተ ካርታ በሶስት ዋና ዋና የትኩረት መስኮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የመጀመሪያው ተቋማዊ አቅምና ዝግጁነትን ማሳደግ መሆኑን ጠቅሰው የመሶብን የመፈጸም አቅም ማጎልበት፣ ዘመናዊ የአፈጻጸም አመራር ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም የሰው ኃይል ብቃትን ማሳደግና ውጤታማ የሥራ ባህል መገንባት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃም ዜጋ ተኮር የላቀ አገልግሎት መስጠት ሲሆን የመሶብ አገልግሎቶችን ተደራሽ፣ ፍትሃዊና ዲጂታል ማድረግ፣ የዲጂታል አገልግሎት አጠቃቀምን ማስፋፋት ብሎም የጥሪ ማዕከል አገልግሎትን ማጠናከርና የተገልጋዮችን እርካታ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን መዘርጋት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በሶሰተኛ ደረጃም የላቀ ቴክኖሎጂና ዲጂታል መሰረተ ልማት መገንባት መሆኑን ጠቅሰው የሳይበር ደህንነትን ማጠናከርና ዘመናዊ የዲጂታል አገልግሎት ሥርዓቶችን ማልማት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
የፍኖተ ካርታው ዝግጅት የተመሠረተው በሀገራዊ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ፣ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ፣ በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ እንዲሁም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ላይ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ዛሬ ይፋ የተደረገው ፍኖተ ካርታ፤ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋና ዜጋ ተኮር የመንግስት አገልግሎት ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተመላክቷል፡፡