በመዲናዋ ዘመኑን የዋጁ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ልማት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ዘመኑን የዋጁ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ልማት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 17/2018 (ኢዜአ)፡- በመዲናዋ ዘመኑን የዋጁ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት በከተማዋ የመጀመሪያ የሆነውን የስማርት ፖሊቴክኒክ ግንባታን በለሚ ኩራ ከፍለ ከተማ ተገኝተው በይፋ አስጀምረዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፥ የስማርት ፖሊቴክኒክ ግንባታው ወጣቶችን በክህሎት በማልማት የሀገርን እድገት ለማፋጠን ያለመ ነው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ አመታት በመዲናዋ ወጣቶች የክህሎትና የቴክኖሎጂ ልማት ላይ ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።
እነዚህ በክህሎትና በቴክኖሎጂ የበቁ ወጣቶች አሁን ላይ ከራሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው አልፈው በሀገር ሁለንተናዊ እድገት ላይ የበኩላቸውን አሻራ እያሳረፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ወጣቶችን ዘመኑ በደረሰበት የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ልክ የማብቃት ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
አዲሱ ስማርት ፖሊቴክኒክ የጀርመንን የቴክኒክና ሙያ ልምድ መነሻ በማድረግ፣ በከተማዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገነባና ትውልድ ተሻጋሪ እውቀት የሚገበይበት ማዕከል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኮሌጁ ወጣቶች እውቀትን የሚታጠቁበት፣አዕምሮ እና የሚሰሩ እጆች ተጣጥመው ሀሳብ የሚያፈልቁበት መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሌጁ በአመት በርካታ አዳዲስ ሰልጣኞችን የመቀበል አቅም እንደሚኖረው ጠቁመው፤ በዘመናዊ ማኑፋክቸሪንግ፣ በአውቶሞቲቭ፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በኮሙኒኬሽንና በቴክስታይል ቴክኖሎጂ መስኮች ያሰለጥናል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ፣ በጀትና ጥራት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ከተማ አስተዳደሩ በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው፤ የሚገነባው ኮሌጅ ወጣቶች በስልጠና ወቅት የሚያመጧቸውን የቴክኖሎጂ ሀሳቦችና የምርምር ውጤቶች ወደ ተግባራዊ ቢዝነስ እንዲቀይሩ፣የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ እንዲመሰርቱና ለሌሎችም የስራ እድል እንዲፈጥሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።