በመደመር የተቃኘ ኢትዮጵያን የሚመጥን የከተሜነት ጉዞ - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር የተቃኘ ኢትዮጵያን የሚመጥን የከተሜነት ጉዞ
በዮሐንስ ደርበው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ጥቅምት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተገኙ ጊዜ፤ የኮሪደር ልማት ዓላማ ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማ ሲለማ ደግሞ ለነዋሪም ሆነ ለጎብኚ፤ ለዐይንም፣ ለጤናም ለእንቅስቃሴም ውበትና ምቾት ማላበሱ አይካድም።
የኮሪደር ልማት ጽዱ ከተሞችን ይሠራል፤ከትራንስፖርት፣ ከትራፊክ ምልክቶች፣ ከብስክሌትና እግረኛ መንገድ ደኅንነት ጋርም ተጣጥሞ ተሠርቷል። በዚህ ዐውድ የኮሪደር ልማት ውበትም ምቾትም ነው።
መሠረተ-ልማት ተጠብቆ ለረጅም ጊዜ እንዲጠቅምም የኮሪደር ልማት ሚና የላቀ ነው።
ኢትዮጵያ በከተሞቿ እና ገጠራማ አካባቢዎቿ የኮሪደር ልማት እያከናወነች ነው። ይህ በኢትዮጵያ ከውበት በላይ ነው።
· ማኅበራዊ መሥተጋብርን በመጠገን፡- ኢትዮጵያውያን ከሚታወቁባቸው አንዱ በየዐውዱ የሚገለጠው ጥብቅ ማኅበራዊ መሥተጋብራቸው ነው። በጋራ መንቀሳቀስ፣ መጫወት፣ ከቤት ወጣ ብለው መመካከር የኑሯቸው አካል ነው።
ይሁን እንጂ በተለይም ከተሜው ከወዳጅ ጋር በኅብረት በእግር ወይም በብስክሌት ለመንቀሳቀስ፣ አረፍ ብሎ የሚያወጋበት በቂ አረንጓዴ ስፍራና ፓርኮች ባለመኖራቸው ማኅበራዊ መሥተጋብሩ እየላላ የመጣ ይመስላል።
አሁን የኮሪደር ልማት በደረሰባቸው ከተሞች፤ሰዎች ሲያሻቸው በእግር አሊያም በብስክሌት ከወዳጆቻቸው ጋር የልባቸውን እያወጉ ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ሰዎች በእንቅስቃሴያቸው መሐል ዐረፍ ማለት ቢሹም ችግር የለም፤ አሁን እንደ ድሮ አይደለምና። አረንጓዴ መናፈሻ ስፍራ ፍለጋ ከከተማ መውጣት አያሻም።
በሌላ በኩል ወጣቶች እና ሕጻናት ኳስ የሚጫወቱበት ስፍራ መመቻቸቱ ጤናን ከመጠበቅ ባሻገር፤ ማኅበራዊ መሥተጋብራቸውን ያጠናክራል።
· ጤናማ አከባቢን በመፍጠር፡- የኮሪደር ልማት ለሰው ልጆች ከቸራቸው ጥቅሞች አንዱ፤ ጤናማ ከባቢን መፍጠር ነው።
በተለይም በደካማ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ለሚታሙ ከተሞች የኮሪደር ልማት ሁነኛ መፍትሔ ሆኗል።
ይህ ደግሞ በቀጥታ ከነዋሪዎች ጤና ጋር ይገናኛል። ደግሞም በንጹህ አካባቢ የመኖር መብትን ማስጠበቅ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በኮሪደር ልማት ሰፋፊ መንገድ ከመሥራት ባለፈ ታዳጊዎች እግር ኳስ የሚጫወቱባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና የእግረኛ መንገዶች ተሠርተዋል ያሉትም ለዚሁ ነው።
· በሥራ ዕድል ፈጠራ፡- የኮሪደር ልማት የዘመቻ ሥራ አይደለም።በትንሹ በአንድ ከተማ ወይም አካባቢ ተጀምሮ እየሰፋ ይቀጥላል። በዚህ ሂደት የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል ማሰብ አያዳግትም።
እንዲሁም የኮሪደር ልማት ሥራዎች ሲከናወኑ፤ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያገለግሉ የመኪና ማቆሚያ፣ ሱቆች እና መሰል ለንግድ ተግባራት እንዲበጁ ተደርገው ነው።
የኮሪደር ልማት ከከተሜነት ዕድገት ጋር የተሣሠረ ልማት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መናገራቸው ይታወሳል።
· በገጽታ ግንባታ ረገድ፡- ከተሞች ሲጸዱና ምቹ ሲሆኑ በዓለም ዘንድ መታወቂያ ይሆናሉ። ነዋሪም በኩራት ስለአካባቢው በየሄደበት አምባሳደር ሆኖ ይመሠክራል።
ቱሪስቶችንም ይስባሉ። የቆይታ ጊዜያቸውንም ለማራዘም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታሉ። ዓለም አቀፍ፣ አኅጉር አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ጉባዔዎች እንዲካሄድባቸውም እንዲመረጡ ያስችላል።
በከተሞች ከሚሠራው የኮሪደር ልማት ባሻገር፤ የገጠር ኮሪደር ልማት በውጤታማነት እየተሠራ ነው። ይህም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሐዊ መሰረተ-ልማት ለዜጎች መቅረቡን ያሳያል።
ኮሪደር ልማት ኢትዮጵያውያን የተሻለ ኑሮ ይገባቸዋል በሚል የተጀመረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ተናግረዋል። የተሟላ ብልጽግና የምናረጋግጠው በዚሁ መንገድ ነውም ብለዋል።
የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት በመቀነስ የተመጣጠነ ዕድገት በሁሉም አካባቢ ለማምጣት የገጠር ኮሪደር ልማት መጠናከር ጠቀሜታው የጎላ ነው። የገጠር ኮሪደር ልማት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ-ምኅዳራዊ ፋይዳን ጨምሮ ብዙ ጥቅም አለው፤ ይህም ዘላቂ ልማትና የተረጋጋ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
የከተሞች መዋብና ምቹ መሆን ለነዋሪው ነው፤ በቀጥታ ተጠቃሚውም ሕዝቡ። ስለዚህ መንግሥት ከሚያከናውናቸው በተጨማሪ ባለሃብቱ፣የመንግሥትም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ኅብረተሰቡ የኮሪደር ልማትን በተነሳሽነት ለማስፋፋት መትጋት ይጠበቅበታል።