“የመደመር ትውልድ” መጽሐፍን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የማስተዋወቅ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
“የመደመር ትውልድ” መጽሐፍን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የማስተዋወቅ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ መጋቢት 12/2015(ኢዜአ)፦“የመደመር ትውልድ” መጽሐፍን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የማስተዋወቅና የሽያጭ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በሸራተን አዲስ ሆቴል እየተካሄደ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በባሌ ዞን ለሚገኘው የሶፍ ዑመር ዋሻ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ማስገንቢያ እንደሚውል ተገልጿል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተጻፈው "የመደመር ትውልድ" መጽሐፍ በአፋን ኦሮሞ፣ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ሲሆን ሶስት ክፍሎች እና አስር ምዕራፎችም አሉት።
እየተካሄደ በሚገኘው መርሐ-ግብር ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳና የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረህማንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ዲፕሎማቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የ"መደመር ትውልድ" መጽሐፍ ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሌሎችም እንግዶች በተገኙበት መመረቁ ይታወሳል።