ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል በበልግ እርሻ ተዘርተው የደረሱ ሰብሎችን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በበልግ እርሻ ተዘርተው የደረሱ ሰብሎችን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ የእንክብካቤና የክትትል ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ የክልሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በበልግ ወቅት በተለያዩ ሰብሎች የለሙ ማሳዎችን እየገበኙ ነው።

በጉብኝቱ ወቅት የቢሮው ኃላፊ መምሩ ሞኬ እንዳሉት፤ በሲዳማ ክልል በበልግ እርሻ ተዘርተው የደረሱ ሰብሎችን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በክልሉ በበልግ እርሻ በቆሎ፣ ቦሎቄና ሌሎች ሰብሎችን ጨምሮ 152 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ለምቷል ብለዋል፡፡

ከዚህም 24 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተው፤ በምርት የተሸፈነውን ማሳ ውጤታማ ለማድረግም የእንክብካቤና የክትትል ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አመልክተዋል፡፡

በበልግ ወቅት የመስኖና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም የለማው ሰብል የሚጠበቀውን ምርት እንዲሰጥ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም