ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክር፡ለተሻለች ኢትዮጵያ የተከፈተ በር

በኢትዮጵያ ለዓመታት የቆዩ አለመግባባቶችና ችግሮች ብዙ ናቸው።እነዚህ አለመግባባቶች የሀገር ሰላም፤አንድነት፤ልማት እድገትና የዜጎችን የወደፊት ተስፋ የሚፈታተኑ ሆነው ቆይተዋል።

አለመግባባቶችን በኃይል ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎች ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጡ አልቻሉም። ስለዚህ የጥላቻን፣የበቀልንና የመከፋፈልን ዑደት ለማቆም የሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ውይይት፣መደማመጥና መግባባት መሆኑ በስፋት እየታመነ መጥቷል።

በዚህ መነሻ፣ኢትዮጵያ በታሪኳ ታላቅ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እያካሄደች ትገኛለች።ይህ ምክክር ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበትና የጋራ መፍትሄ የሚፈልጉበት መድረክ ሆኗል።

የሀገራዊ ምክክሩ አሸናፊና ተሸናፊ መፍጠር ሳይሆን፣ የሁሉንም ወገን ድምጽ በማዳመጥ የጋራ መግባባት መፍጠር ነው።

ይህ ምክክር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተወከሉ ዜጎች ድምጽ የሚሰማበት፣አመለካከቶች የሚተነተኑበትና የጋራ መፍትሄዎች የሚፈለጉበት ታሪካዊ አጋጣሚ ሆኗል።

ሀገራዊ ምክክሩ የተለያዩ ወገኖችን በአንድነት በማሰባሰብ፣የከረሙ ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ በመፍታት፣ የፖለቲካዊ፣የኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ ለውጦችን ለማምጣት ይረዳል።

እንዲሁም ኢትዮጵያን ወደ አንድነት፣ሰላምና ብልጽግና ለማሸጋገር የሚያገለግል ታላቅ መድረክ ነው።

ሀገራዊ ምክክር ማድረግ ብቸኛው መንገድ ነው ብለው ያመኑ ኢትዮጵያዊያንም ከሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ እና ከውጭ ጭምር በመምጣት በአዲስ አበባ ተገናኝተው ስለሀገራቸው እየመከሩ ይገኛል።

በሁሉም ክልሎች፣በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች ሕዝብ የወከላቸው ተመካካሪዎችም በንዑስ ቡድኖች በመከፋፈል በተመደቡበት አጀንዳ ላይ መመካከር መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ሂደት ጠንካራ መግባባትን የሚፈጥር ግልፅና ተስፋ ሰጪ ምክክር እያደረግን ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመካካሪዎች በበኩላቸው ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የአንድ ተቋም ወይም የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ከመላው ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ ጋር የሚያያዝ ነው።

ዛሬ በምክክር የምንገነባው መግባባት፣ነገ ለመጪው ትውልድ የተረጋጋች፣የተባበረች፣ሰላማዊና የበለፀገች ኢትዮጵያን የሚያስረክብ መሠረት ይሆናል።

ይህ ሀገራዊ ምክክር የጋራ መግባባት ባህልን ለማጠናከር፤ለፀናችና ለተሻለች ኢትዮጵያ የተከፈተ ትልቅ በር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም