ሳይንስና ቴክኖሎጂ
የልማት ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ከመከታተል ባሻገር ዲጂታል የግዥ ስርዓትን በማጠናከር የሙስና ተጋላጭነትን መቅረፍ ይገባል
May 29, 2024 77
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ የልማት ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ከመከታተል ባሻገር ዲጂታል የግዥ ስርዓትን በማጠናከር የሙስና ተጋላጭነትን መቅረፍ እንደሚገባ የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ። ፌዴራል የሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን በፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ዙሪያ ያደረገውን የስጋት ትንተና ጥናት በሚመለከት ከሚኒስቴሩና ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው በዚሁ ጊዜ ፤በፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ስር ያሉ ስነ ምግባር መከታተል ክፍሎች የተጠናከረ አደረጃጀት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።   ይህም የጸረ ሙስና ትግሉን ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርገው ነው የገለጹት፡፡ በተለይ የመንግስት የግዥ ስርዓትን በዲጂታል አሰራር በማጠናከር ለሙስና እና ብልሹ አሰራር በር ሊከፍቱ የሚችሉ ጉዳዮችን ማስወገድ እንደሚገባ በጥናቱ መመላከቱንም ነው ያነሱት፡፡ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ክትትልና ቁጥጥር ዙሪያ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ መሰል ችግሮችን በማስተካከል ዙሪያ ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት፡፡ የስነምግባር መከታተያ ክፍሎችን በሚገባ ማጠናከር እና አፈፃፀማቸውን በመገምገም የተደራጀ የጸረ ሙስና ትግል እንዲኖር መስራት እንደሚገባም እንዲሁ፡፡ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው የተቋማቱን አሰራር ዲጂታል በማድረግ ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡   ይህም ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመቅረፍ ምቹ እድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ በጥናቱ የተቀመጡ ምክረ ሃሳቦችን ገቢራዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ነው ያነሱት፡፡ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር)፤ የኮሚሽኑ የስጋት ተጋላጭነት ጥናት ውጤታማ የጸረ ሙስና ትግል ለማከናወን አንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡   በቀጣይም ጥናቱን መሰረት በማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚያደርጉበት መተግበሪያ ይፋ አደረገ
May 29, 2024 97
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መተግበሪያ ይፋ አድርጓል። "itismydam" የተሰኘው መተግበሪያ ይፋ የማድርጊያ መርኃ-ግብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መስሪያ ቤት እየተካሄደ ሲሆን የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ በዚህ ወቅት ባንኩ ለግድቡ ግንባታ መሳካት ጉልህ ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል።   ባንኩ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ካሉበት ሆነው ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መተግበሪያ አበልጽጎ ይፋ ማድረጉንም ተናግረዋል። በዚህም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር "itsmydam" የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል። መተግበሪያው ዓለምአቀፍ ተደራሽነት ያለው፣ ለአጠቃቀም ቀላል እና አስተማማኝ መሆኑንም ጠቁመዋል። በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመተግበሪያው አማካኝነት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርኼ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስም ዛሬ ይፋ በሆነው መተግበሪያና ከዚህ ቀደም በተዘረጉ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ስልቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።  
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ብክለትና የውሃ ብክነትን መከላከል የሚችል ቴክኖሎጂ እያበለፀገ ነው
May 29, 2024 62
ጂንካ ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ብክለትና የውሃ ብክነትን መከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ እያበለፀገ መሆኑን ገለጸ። የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች እና የአመራር አባላት በዩኒቨርሲቲው የበለጸገውንና ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በማከምና በማጥራት ለግብርና አገልግሎቶች ለማዋል የሚያስችል ቴክኖሎጂን ጎብኝተዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩሴ ጉዲሼ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ቴክኖሎጂው የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።   ቴክኖሎጂው በቀን እስከ 300 ሜትር ኪዩብ የማጣራትና የተጣራ ውሃን የማከም አቅም ያለው ሲሆን ከአምስት ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት ያስችላል ብለዋል። ቴክኖሎጂው የውሃ ብክነትን እና የአከባቢ ብክለትን የመከላከል አቅም ያለውና የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት ሚዛን በጠበቀ መልኩ የሚሰራ ነው ያሉት። ግንባታው ከተጀመረ ስድስት ወራት ያስቆጠረው ፕሮጀክቱ የማስፋፊያና የመስመር ዝርጋታዎችን ጨምሮ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለታልም ብለዋል። አሁን ላይ ፕሮጀክቱ በከፊል አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ሁለት ዓመታት ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ነው ያሉት። በቀጣይም በቴክኖሎጂው ላይ ተግባር ተኮር ስልጠና በመስጠት በስፋት በማበልፀግ የቴክኖሎጂ ሽግግር ይደረጋል ብለዋል። የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዓለሙ አይላቴ በበኩላቸው ቴክኖሎጂው የአፈር ለምነትን የሚጠብቁ የአፈር ማዳበሪያዎችን የማምረት አቅም አለው ብለዋል። ይህም ዩኒቨርሲቲው ለሚያከናውነው የተቀናጀ የግብርና ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል። ጂንካ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ብክለትና የውሃ ብክነትን መከላከል ከሚችል ቴክኖሎጂ በተጨማሪ በምርምር ያላመዳቸውን የተሻሻሉ የእንስሳትና የሰብል ዝርያዎችን ዛሬ አስጎብኝቷል።        
በክልሉ የፈጠራ ስራዎችን  በመደገፍ ከዘርፉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ 
May 29, 2024 60
ሆሳዕና ፤ ግንቦት 21 ቀን 2016 (ኢዜአ) ፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን በመደገፍና በማጠናከር ከዘርፉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ ። "አዲስ አስተሳሰብ ለዲጅታል ለውጥ" በሚል መሪ ሀሳብ በሀዲያ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን መምሪያ የተዘጋጀ የምርምርና ፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕይ በሆሳዕና ከተማ ተከፍቷል። የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በወቅቱ እንዳሉት፤ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን መደገፍ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎትና ምርታማነት ለማጎልበት እድል ይፈጥራል። በክልሉ ይህንን በማጠናከር ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን በመደገፍና በማብቃት ከዘርፉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። ለዚህም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች እንዲበራከቱ በግብአትና በሰው ሀይል እንዲሁም በስልጠናና መሰረተ ልማት ተደራሽነት የመደገፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ በበኩላቸው ፤ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ማዳረስ እንደሚገባ ተናግረዋል።   ለዚህም ስኬት የዞኑ አስተዳደር የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶችን በመደገፍና በማብቃት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል። በዞኑ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በግልና በቡድን የሚሰሩ አበረታች የሆኑ የፈጠራ ስራዎች መኖራቸውን የተናገሩት ደግሞ የሀዲያ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ታምራት አኑሎ ናቸው ። የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎቹን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀትና በመደገፍ ለስኬት እንዲበቁ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። የአውደ ርዕዩ ዓላማም የፈጠራ ስራዎች ለዕይታ ቀርበው ይበልጥ እንዲጎለብቱ ለማስቻል፣ ተሞክሮን ለማስፋፋትና መነሳሳትን ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ርዕይ ላይ የተለያየ የፈጠራ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።      
የኢትዮጵያ  የቴክኒክና ሙያ አመራሮች ካውንስል ተመሠረተ
May 29, 2024 67
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ አመራሮች ካውንስል ተመሠረተ። በዚሁ ወቅት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደተናገሩት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለሀገራዊ ልማት በመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። ተቋማቱ የክህሎትና የዕውቀት ሽግግር በማድረግ ተልዕኮአቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተመሳሳይ ተልዕኮ ካላቸው ተቀማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተደራጀ መልኩ ለማሳለጥ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ዘርፉን ለማስተሳሰር የሚያስችል የቴክኒክና ሙያ አመራሮች ካውንስል "ብቁ መሪነት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት'' በሚል መሪ ሃሳብ በይፋ መመስረቱን ገልጸዋል፡፡   ካውንስሉ ተቋማቱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት እንዲወጡ እንዲሁም ስራቸውን ተናበው የሚሰሩበት ወጥ የሆነ የአደረጃጀት ስርዓት ለመገንባት የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል። የአመራር ካውንስሉ ጥናትና ምርምር በማድረግ ልዩነት መፍጠር የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት ይጠበቅበታል ብለዋል። ካውንስሉ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ገበያ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ከማፍራት አንጻር ከምንጊዜውም በላይ ፍጥነትን፣ ፈጠራን ፤ጥራትንና ብዛትን ማዕከል አድርጎ እንዲሰራ አሳስበዋል።   የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ከድር በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከ 2 ሺህ በላይ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በመንግሥትና በግል ባለቤትነት ስራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ከእነዚህም መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑት የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ኮሌጆቹ የበርካታ ወጣቶችን ክህሎት በማበልጸግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ስራ እያከናወኑ መሆኑን አንስተዋል። የበለጸገ ክህሎት የማስጨበጥ ስራው በተለይ ወጣቶች ከራሳቸው ባለፈ ለሀገራቸው ኢኮኖሚ የማይተካ ሚና እንዲጫወቱ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።  
ኢትዮጵያዊያን የቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች በአለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ለመሳተፍ ሞሮኮ ገቡ
May 27, 2024 96
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦ 40 የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን የቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች የልኡካን ቡድን አባላት በአለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ለመሳተፍ ሞሮኮ ገብተዋል። የልዑካን ቡድኑ አባላት በማራካሽ በሚኖራቸው ቆይታ በምርምር ያበለፀጓቸውን የጤናና የኢንቨስትመንት አዋጭ መተግበሪያዎችን ጨምሮ አምስት የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከተለያዩ የአለም ሃገራት ለተውጣጡ ተመራማሪዎችና የቢዝነስ ሰዎች ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዱባይ የንግድ ማዕከል አማካኝነት በሞሮኮ ማራካሽ በተዘጋጀው በዚህ ልዩ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ አፍሪካን ከተቀረው አለም ሊያገናኝ የሚችል አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች ይፋ እንደሚደረግበት የልዑካን ቡድኑ አስተባባሪ ፣ የአብርሆት ቤተመፅሐፍት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ውባየሁ ማሞ ገልፀዋል። ተመራማሪዎቹ ለሁለት ዓመት በአብርሆት ቤተመፅሐፍት ሲሰለጥኑ እንደነበርም ኢንጂነሩ ገልፀዋል። የቴክኖሎጂ ተመራማሪ የልዑካን ቡድኑ አባላት በከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም በአብርሆት ቤተመፅሐፍት እና በA2SV አስተባባሪነት የሚሳተፉ ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል።        
መንግስት ለፈጠራ ስራ የሰጠው ትኩረት ፈጠራን በማስተዋወቅ የአገርን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ዕድል የሚፈጥር ነው - የፈጠራ ባለቤቶች
May 27, 2024 102
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦መንግስት ለፈጠራ ስራ የሰጠው ትኩረት ፈጠራን በማስተዋወቅ የሀገርን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የፈጠራ ባለቤት መምህራን እና ተማሪዎች ገለጹ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ "በፈጠራ ሥራ የዳበረ ትውልድ ለሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ ከተማ አቀፍ የተማሪዎች የሳይንስና የፈጠራ ውድድር አውደ ርዕይ ማካሄዱ ይታወሳል።   አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሳይንስና የፈጠራ ውድድር አውደ ርዕይ ተሳታፊ እና የፈጠራ ባለቤት መምህራን እና ተማሪዎች እንደሚሉት ፈጠራ የሀገርን ዕድገትና ብልጽግና ለማሳለጥ የማይተካ ሚና ይጫወታል። መንግስት ለፈጠራ ስራ የሰጠው ትኩረት ፈጠራን በማስተዋወቅ የሀገርን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል። የጂቫ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ክርስቲና ጳውሎስ መንግስት ለፈጠራ ስራ የሰጠው ትኩረት የፈጠራ ስራዋን እንድታስተዋውቅና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንድታደርግ እድል እንደፈጠረላት ተናግራለች። የከተማ ግብርናን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መስራቷን በመግለፅ ወደ ተግባር ለመቀየር መዘጋጀቷን ገልፃለች። ቴክኖሎጂው ውሃ ቆጣቢና የተፈጥሮ ማዳበሪያን ለማዘጋጀት እንደሚያስችልም ገልጻለች።   የአቡነ ባስሊዎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነጋ ፀጋየ የበጋ መስኖ ምርታማነትን ማሳደግ የሚችል በትንሽ ኃይል የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ቴክኖሎጂ መስራቱን ተናግሯል። የውሃ መሳቢያው በኤሌክትሪክና በታዳሽ ኃይል የሚሰራ በመሆኑ የአየር ብክለት የማያስከትል የፈጠራ ስራ መሆኑን በመግለፅ ከውጭ የሚገባ ምርት የሚተካ መሆኑንም አስረድቷል። በቀጣይ ፈጠራውን ማሳደግ የሚችልበት የገንዘብ ድጋፍ ከተደረገለት ቀጥታ ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚችል ገልጿል።   የገዳምስታዊያን ማርያም ፅዮን ካቶሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሃይሉ ካሴ የመማር ማስተማር ስርዓቱ የንድፈ ሀሳብ ትምህርትን ከተግባር ትምህርት ጋር በማቀናጀት እንዲያስተምሩ ዕድል በመፍጠሩ የፈጠራ ባለቤት የሆነ ትውልድ ማፍራት መቻላቸውን ተናግረዋል። ሁሉም የፈጠራ ስራዎች የሀገር ልማትንና እድገትን የሚያፋጥኑ መሆናቸውን ተገንዝቦ መደገፍና ማበረታታት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ መምህር ዘውዱ ዘነበ ናቸው።  
ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በቻይና በተካሄደው የሁዋዌ ዓለም አቀፍ የአይ ሲ ቲ ፍጻሜ ውድድር አሸነፉ
May 27, 2024 117
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በቻይና በተካሄደው የሁዋዌ ዓለም አቀፍ የአይ ሲ ቲ ፍጻሜ ውድድር ሶስተኛውን ሽልማት አሸነፉ። ኢትዮጵያን ወክለው የሁዋዌ ዓለም አቀፍ አይ ሲ ቲ ውድድርን በቻይና ሼንዘን ከተማ በኮምፒውቲንግ ትራክ የተሳተፉት 3 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ሶሰተኛውን ሽልማት ከማሌዢይ፣ ሜከሲኮ እና ኬንያ ቡደን ጋር መጋራታቸው ተጠቁሟል። ውድድሩ ከግንቦት 14 እስከ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ከመላው ዓለም የተውጣጡ ተማሪዎች በተሳትፉበት በሶስት የውድድር ትራኮች (Innovation, Network and Computing) ተካፋፍሎ የተካሄደ መሆኑም ተገልጿል።   የኢትዮጵያ ቡድን የተወከለው ከአርባ ምንጭና ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በተገኙ ተማሪዎች መሆኑን አመላክቶ በኮምፒውቲንግ ትራክ ውድድር ሶስተኛውን ሽልማት አሸንፎ ዛሬ ወደ ሀገሩ መመለሱም ተጠቁሟል። ትምህርት ሚኒስቴር በተማሪዎቹ ውጤት የተሰማውን ደስታም በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ ገልጿል። ወደፊትም የተማሪዎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እድል የሚፈጥሩ ውድድሮች ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ከመሰል ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ጋር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
የስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በምርምርና ኢኖቬሽን የተከናወኑ ተግባራትን በስፋት ያስተዋወቀ ነው- በለጠ ሞላ (ዶ/ር)
May 26, 2024 116
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2016(ኢዜአ)፦የስትራይድ ኢትዮጵያ 2024 ኤክስፖ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በምርምርና ኢኖቬሽን የተከናወኑ ተግባራትን በስፋት ያስተዋወቀ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ። ከግንቦት 11 እስከ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ የቆየው ስትራይድ ኢትዮጵያ 2024 ኤክስፖ የማጠናቀቂያ ፕሮግራም ተካሂዷል። የኤክስፖው መክፈቻ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአይሲቲ ፓርክ የተካሄደ ሲሆን በሳይንስ ሙዚየም ደግሞ ለእይታ ክፍት ሆኖ ቆይቷል። ኤክስፖው "ሳይንስ በር ይከፍታል፤ ቴክኖሎጂ ያስተሳስራል፤ ፈጠራ ወደፊት ያራምዳል" በሚል መሪ ሃሳብ" ተካሂዶ በዛሬው እለት ተጠናቋል። በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ ኤክስፖው ኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በምርምርና ኢኖቬሽን የተከናወኑ ተግባራትን በስፋት ያስተዋወቀ ነው ብለዋል።   በኤክስፖው በርካታ ልምዶች የተገኙበት በቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች የታዩበትና የተበረታቱበት መሆኑንም ጠቅሰዋል። የግል ድርጅቶች ተሳትፎ የታየበት ኤክስፖ እንደነበር ጠቅሰው ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሰራል ብለዋል። የስራና ክሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብረሃኑ ነጋ እና ሌሎችም የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመዝጊያ ስነ ስርአቱ ላይ ተገኝተዋል። በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ ለዘርፍ አስተዋጽኦ ላደረጉና ተጨባጭ ውጤት ላስገኙ ሽልማትና ዕውቅና ተሰጥቷል።
ሀገራዊ ልማትና እድገትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የወጣቶች የፈጠራ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
May 26, 2024 94
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2016 (ኢዜአ):- ሀገራዊ ልማትና እድገትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የወጣቶች የፈጠራ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ "በፈጠራ ስራ የዳበረ ትውልድ ለሁለንተናዊ እድገትና ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው 9ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስና የፈጠራ አውደ ርዕይ ማጠቃለያ ፕሮግራም ተካሂዷል። በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ፤ የወጣቶች ሳይንስና ፈጠራ ለሀገር እድገትና ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም የተማሪዎች የፈጠራ ሥራዎች ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ መሰረቶች መሆናቸውን ጠቅሰው በፈጠራና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ሀገራዊ ልማትና እድገትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። የትምህርት ቤቶችን ደረጃና ጥራት ማሻሻል፤ የትምህርት ቤት የምገባ ሥርዓት፣ የመማር ማስተማሪያ ግብዓትና የንድፈ ሀሳብ አቅም የፈጠራ አቅምንም የሚያሳድጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡   ከተማ አስተዳደሩ ንድፈ ሀሳቦችን ከተግባር ትምህርት ጋር በማቀናጀት የተማሪዎችን የመፍጠር አቅም ለማሳደግ የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የትምህርት ቤቶች የፈጠራና የምርምር ውጤቶች የሀገር እድገት መሆናቸውን ገልጸው፤ የምርምር ሥራዎች ወደ ተግባር እንዲለወጡ የጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፤ አውደ ርዕይው የተማሪዎችን የፈጠራ ክህሎት ለማሳደግ፣ ልምድ ለመጋራትና ስራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም የተማሪዎችን የፈጠራ አቅም የሚያጎለብቱ መርሃ ግብሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡ በዛሬው መርሃ ግብር የላቀ የሳይንስና የፈጠራ ውጤቶችን በማቅረብ አሸናፊ ለሆኑ ትምህርት ቤቶች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ ለምርታማነት እድገት ሚናውን እየተወጣ ነው
May 25, 2024 116
ደሴ ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ)፦ መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ አርሶ አደሮችን በምርምር በማገዝ ለምርታማነት እድገት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገለጸ። ዩኒቨርሲቲው ሁለተኛውን አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው። የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጥናትና ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ስለሺ አቢ እንደገለጹት ተቋሙ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ነው።   በግብርና፣ ቴክኖሎጂ ፣ ማዕድንና ቱሪዝም ሀብቶች ላይ 75 ጥናትና ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመው ከእነዚህ ውስጥ በተጠናቀቁት 13 ጥናቶች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል። ከዚህም በተለይ በሰብል ልማት የስንዴ፣ ሽምብራና ምስር እንዲሁም በደጋ ፍራፍሬዎች ዝርያዎችን በማሻሻልና በማላመድ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ተናግረዋል። በእንሰሳት ዘርፍም የበግና የዳልጋ ከብት ማድለብና እርባታ ላይ የተጀመሩ ጥናቶች አዋጪና የአርሶ አደሩን ኑሮ የሚያሻሽሉ ናቸው ብለዋል። ከዚህም ሌላ በወሎ አካባቢ የሚገኙ በርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን ለይቶ በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው የተጀመሩ የምርምር ስራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።   በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የእጽዋት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር በቃሉ አበበ በበኩላቸው በባቄላ ሰብል ላይ ባደረጉት ምርምር የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም አሲዳማ አፈርን በማከም የአረምና የተባይ ቁጥጥር ስራ በማከናወን ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ማረጋገጥ እንደቻሉ ገልጸዋል። የስጋ፣ የወተትና የእንቁላል ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ባቀረቡት ጥናት ያመላከቱት ደግሞ በኢትዮጵያ በዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የለማዳ እንስሳት ተመራማሪ አቶ ተስፋለም አሰግድ ናቸው።   ለዚህም መንግስት በሌማት ትሩፋት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠር ምርታማነትን ማሳደግና አርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ በተመረጡ 24 ማዕከላት የተለያዩ እንስሳት ዝርያዎችን በምርምር የማሻሻልና የማላመድ ተግባራት እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የተሻለ ምርት የሚሰጡ አዳዲስ ዝርያዎች እየተገኙ ነው ብለዋል። በኮንፈረንሱ በአገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን እየተሳተፉ ሲሆን፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ነገ በሚኖረው ቆይታ 35 የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ የሚጠበቅ መሆኑ ተገልጿል።  
ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው የማዕድን ልማት ስራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በጥናትና ምርምር እያገዘ ነው
May 25, 2024 104
ነቀምቴ ፤ ግንቦት 17/2016 (ኢዜአ)፡- ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በወለጋና አካባቢው የማዕድን ልማት ስራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በጥናትና ምርምር ለማገዝ እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን የሱፍ ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው ''የአመራረት ቴክኖሎጂዎች፣ ማዕድን ማውጣትና ግኝት ለዘላቂ ልማት" በሚል ሀሳብ ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስና አውድ ርዕይ እያካሄደ ነው። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን የሱፍ፣ ዩኒቨርሲቲው የማዕድን ሀብት ልማት በእወቅትና በቴክኖሎጂ ታግዞ ጥቅም ላይ እንዲውል የጥናትና ምርምር መድረክ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።   በተለይም ዩኒቨርሲቲው በሚገኝበትና ወለጋና አካባቢው በርካታ የማዕድን ሀብት መኖሩ በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ጥናቶች መረጋገጡን ተናግረዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የማዕድን ሀብት ልማት በባህላዊ መንገድ የሚከናወን በመሆኑ ሀብቱ በአግባቡ ለሀገር ጥቅም እየዋለ አለመሆኑን አንስተዋል። ዩኒቨርሲቲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በአካባቢው ያለው የማዕድን ሀብት በዘመናዊ መንገድ እንዲለማ በጥናትና ምርምር ለማገዝ የጀመረውን ስራ ያጠናክራል ብለዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎችም በአካባቢው ያለውን ጸጋ ተረድተው በጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።   በዩኒቨርሲቲው የጂኦሎጂ መምህር ደግፍ ተመስገን፣ በወለጋና አካባቢው የተለያዩ የተፈጥሮ ማዕድናት ይገኛሉ ብለዋል። በአካባቢው ዜጎች ለአመታት በባህላዊ መንገድ እንደ ወርቅ የመሳሰሉ ማዕድናትን ሲያወጡ እንደነበረ ጠቅሰው፣ አመራረቱን ለማዘመን ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ሌላዋ ዩኒቨርሲቲው የጂኦሎጂ መምህርት ሀና ታምሩ፣ የማዕድን ልማት ስራ ቅንጅታዊ አሰራርን የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።   ይህም በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ከመንግስት፣ ከባለሀብቶች እና የማዕድን ሀብት በሚገኝባቸው አካባቢው ያሉ ዜጎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በሁሉም አካባቢ ያሉ ምሁራን ኢትዮጵያ ካላት የማዕድን ሀብት በአግባቡ ተጠቃሚ እንድትሆን የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ አለባቸው ሲሉም መክረዋል። በዩኒቨርሲቲው የተዘጋጀው የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የኢኖቬሽን ተግባራትን በትብብር ማከናወን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ
May 25, 2024 94
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ)፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከጅማ፣ ድሬድዋ፣ ሐዋሳ እና ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የኢኖቬሽን ተግባራትን በትብብር ማከናወን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። በዝግጅቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ስምምነቱ በኢኖቪዝ-ኬ ኢንኩቤሽን ማዕከል እና በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ አቅሞችን አቀናጅቶ በመጠቀም በዘርፉ ውጤት ማምጣት አላማ ያደረገ ነው ብለዋል።   የሚከናወኑ የምርምር፣ የኢኖቬሽን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ስታርታፖችን የመደገፍ ብሎም ምቹ ስነ-ምህዳር ከመፍጠር አንጻር ያሉ ስራዎችን በጋራ በመስራት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ዘርፉ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ለማበርከት ያግዛል ብለዋል። በፊሪማ ስነ-ስርአቱ ላይ ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ኡባህ አደም(ዶ/ር) ስምምነቱ ዩንቨርሲቲዎች የሰው ሃይል ልማት ስራቸውን በተቀናጀ መንገድ ለመስራት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት። ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን አቅም በሀገር ኢኮኖሚ ልማት ለማዋል በዚህ መልኩ ተባብሮ መስራት ፈጥኖ ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀማል አባ ፊጣ(ዶ/ር) ናቸው። የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ታፈሰ ማትዮስ(ዶ/ር) ዩንቨርሲቲው በፈጠራ በምርምር እና በቴክኖሎጂ ስራዎችን ለመስራት ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ጠቅሰው ይህን መሰል ቅንጅት መፈጠሩ ያሉ አቅሞች እንዳይባክኑ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል። የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት አዝመራው አየሁ(ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ከሚኒስቴሩ ጋር በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል። ይህ ስምምነትም የነበሩ ሰራዎችን ከማጠናከር ባለፈ ዩኒቨርሲቲው አቅሙን እንዲጠቀም ያግዘዋል ብለዋል። ከስትራይድ ኢትዮጵያ 2016 ኤክስፖ (STRIDE Ethiopia 2024 Expo) ጎን ለጎን በዘርፉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ከምሁራን፣ ከአጋር የልማት ድርጅቶች፣ ከፈጠራ ባለሞያዎችና የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ጋር ዘርፉን ለማጠናከር የሚረዱ ግብአቶችን ለማሰባሰብ ያለሙ ውይይቶች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የጀመረችው ጉዞ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-የልማት አጋሮች
May 24, 2024 129
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የጀመረችው ጉዞ ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የልማት አጋሮች ገለጹ። የስትራይድ ኢትዮጵያ 2024 ኤክስፖ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ መከፈቱ ይታወቃል። በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ካለው ኤክስፖ ጎን ለጎን "የኢትዮጵያ ሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ እና ዘላቂ የልማት ግቦችን" በተመለከተ ከልማት አጋሮች ጋር የፓናል ውይይት ተደርጓል። በውይይቱ የተገኙት በኢትዮጵያ የተመድ የልማት ፕሮግራም የአካታች ኢኮኖሚ ልማት ቡድን መሪ አቶ ግዛቸው አስናቀ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ የልማት ስራዎች እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዋናነት ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲጂታላይዜሽን ጎዞ መሳካት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህንን የትብብር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ባለሙያ ማክስም ሄንዲሪክስ በበኩላቸው የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ጎዞ ውጤታማ እንዲሆን እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።   ወደ ተግባር የሚገቡ እቅዶች እንዳሉ የጠቀሱት ባለሙያው፥ በአውሮፓ በዲጂታል መሰረተ ልማት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም የቴክኖሎጂ፣ የእውቀትና የክህሎት ሽግግርን ለማሳካት ያግዛል ነው ያሉት። በኢትዮጵያ የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ(ኮይካ) ምክትል ኃላፊ ሹንዮንግ ሊ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በአቅም ግንባታ ዘርፍ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።   ለስታርአፖች መጎልበትና ለመሰረተ ልማት መሟላት ኮይካ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ መንግስት ፈጠራን የሚያጎለብት እና የቴክኖሎጂ ስነ-ምህዳር እድገትን የሚደግፉ ፖሊሲዎችና ህግጋትን እየተገበረ ነው።   ይህም የሀገር ውስጥ ተሰጥኦዎችን በማጎልበት በቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚመራ ዘላቂ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላል ብለዋል። በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።  
በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችል ውሳኔ ተላልፏል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
May 24, 2024 84
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦ በዲጅታል መር የኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያሳድጉ ውሳኔዎች ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት መተላለፋቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጡ የዲጂታል እና ቴክኖሎጂ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎችን ተፈፃሚነት በየጊዜው በመከታተልና በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጥ ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። ምክር ቤቱም ዛሬ ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ሚያዚያ 4/2016 ዓ.ም ባካሄደው የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አፈጻጸም በመገምገም ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህ፥ ውሳኔዎቹን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ምክር ቤቱ በመጀመሪያ ስብሰባው በዲጂታል ስርዓተ ምህዳር ያሉ ህጎች፣ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ተጠንተው እንዲቀርቡ ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር አውስተዋል። በዛሬው ስብሰባ በሀገሪቱ ዲጂታል ዘርፍን የተመለከቱ በርካታ ህጎች፣ መመሪያዎችና ስትራቴጂዎች ያሉ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል። ሆኖም እነዚህ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ያላቸው ተግባራዊነት እንዲሁም ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ክፍት ናቸው ወይ የሚለው በዝርዝር በባለሙያዎች ተጠንቶ እንዲቀርብ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል። በተለይም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና በዲጂታል ስርዓቱ ውስጥ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚና እንዲጫወት ከማድረግ አኳያ ነባር ህጎች ምን ያህል ክፍት ናቸው የሚለው እንዲታይና አዳዲስ ህጎች እንዲዘጋጁም አቅጣጫ መቀመጡን ነው ያነሱት። ሌላኛው ምክር ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ ከኢኮኖሚና ከዲጂታል እድገት አኳያ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ለማድረግ የምክር ቤቱ አባል እንዲሆን ውሳኔ መተላለፉን ገልጸዋል። በመሆኑም ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከግሉ ዘርፍ ማህበራት ጋር በመሆን የግሉን ዘርፍ ወክለው የምክር ቤቱ አባል የሚሆኑ አካላትን እንዲያሟላ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል። ምክር ቤቱ በቨርቹዋል እየተገናኘ መወያየት እንዳለበት በመጀመሪያ ስብሰባው ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በዛሬው ስብሰባ ለቨርቹዋል የተግባቦት ስራዎች የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን በመለየት ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አክለውም የምክር ቤቱ አባላት በኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ውስጥ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ የሚያሳኩ መሰረተ ልማቶች መኖራቸውን እንደተመለከቱ ገልጸዋል። ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤቱ ለፓርኩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ እንዲሰራ ይደረጋል ብለዋል። የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ለዲጂታል ሽግግሩ ወሳኝ የሆኑ የዳታ ማዕከላትና ወጣቶች የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩባቸው ምቹ የልምምድ ስፍራዎችን ያካተተ መሆኑን አንስተዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ፓርኩ በኢትዮጵያ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራና በምርምር ታላቅ ሀገር እንድትሆን ይሰራል ብለዋል።   የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው የኢኮኖሚ ግንባታን ለማፋጠን የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ወሰኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰው፥ ሚናው እንዲጎለብትም በህግና በፖሊሲ ደረጃ መንግስት ትኩረት ሰጥቷል ነው ያሉት።   የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፥ በፓርኩ የሚገኙ የዳታ ማዕከላት የመንግስትና የግል ተቋማት መረጃዎችን በማከማቸትና በመጠቀም ሀገርን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።   አስተዳደሩም የመረጃና የቴክኖሎጂ ደህንነትን ለማስጠበቅ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል። ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ ያቀደቻቸውን ግቦች ለማሳካት ቅንጅታዊ አሰራርን በመዘርጋትና አስፈላጊ ስራዎችን በመለየት የፖሊሲ ምክረ ሃሳብ ያቀርባል።  
ብሔራዊ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የግል ዘርፉን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ውሳኔዎችን አሳልፏል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
May 24, 2024 114
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦ ብሔራዊ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የግል ዘርፉን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ። ምክር ቤቱ ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ በኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ አካሂዷል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክርቤቱ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህ፥ውሳኔዎቹን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ምክርቤቱ በመጀመሪያ ስብሰባው በዲጅታል ስርዓተምህዳር ያሉ ህጎች፣ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ተጠንተው እንዲቀርቡ ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር አውስተዋል። በዛሬው ስብሰባው በሀገሪቱ ዲጅታል ዘርፍን የተመለከቱ በርካታ ህጎች፣መመሪያዎችና ስትራቴጂዎች ያሉ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል። ሆኖም እነዚህ ህጎች፣ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ያላቸው ተግባራዊነት እንዲሁም ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ክፍት ናቸው ወይ የሚለው በዝርዝር በባለሙያዎች ተጠንቶ እንዲቀርብ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ዲጅታል ስርዓት ውስጥ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚና እንዲጫወት ከማድረግ አኳያ ነባር ህጎች ምን ያህል ክፍት ናቸው የሚለው እንዲታይና አዳዲስ ህጎች እንዲዘጋጁም አቅጣጫ መቀመጡን ነው ያነሱት። ሌላኛው ምክር ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ ከኢኮኖሚና ከዲጅታል እድገት አኳያ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ለማድረግ የምክር ቤቱ አባል እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን፤ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከግሉ ዘርፍ ማህበራት ጋር ሆኖ ሊወከሉ የሚችሉ የግሉ ዘርፍ አባላትን እንዲያሟላ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል። ምክር ቤቱ በቨርቹዋል እየተገናኘ መወያየት እንዳለበት በመጀመሪያ ስብሰባው ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በዛሬው ስብሰባ ለቨርቹዋል የተግባቦት ስራዎች የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን በመለየት ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል።  
በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዲፈቱ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ
May 24, 2024 103
አዳማ፣ግንቦት 16/2016 (ኢዜአ)፡-በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ወደ ተግባር ተቀይረው የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዲፈቱ በቅንጅት መስራት ይገባል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ። በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 3ኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው። የኢንዱስትሪ ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ እውቀትና ቴክኖሎጂ ያልታከለበት ልማት ውጤታማ አይሆንም። በዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ተቋማት የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችም ጥራታቸውን የጠበቁ ከመሆን ባለፈ ሀገሪቷ ለያዘችው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና እድገት ግብዓት መሆን አለባቸው ብለዋል። የጥናትና ምርምር ስራዎች ምርታማነት፣ ለቴክኖሎጂ፣ ለእውቀትና ክህሎት ማበልጸግ አስተዋጽኦ በሚያበርክት መልኩ ሊከናወኑ እንደሚገባም ጠቅሰዋል። በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር የሚኖራቸው ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው ለዚህ ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲፈቱ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል። የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲም በዚሁ ቅኝት የጀመራቸውን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎች የበለጠ ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል። የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለሚ ጉታ(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ለማፍራት ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።   በዚህም የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የባዮ ቴክኖሎጂ፣ የህዋና የድሮን ቴክኖሎጂን ጨምሮ የተለያዩ የልህቀት ማዕከላት መክፈቱን ተናግረዋል። በተጨማሪም በከተማ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ጥራት ማማከር እንዲሁም በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዙሪያ ትኩረት ያደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያወጣ መሆኑን አስረድተዋል። በአውደ ጥናቱ ላይ የሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ስራዎች የሀገሪቱን ልማትና እድገት ለማፋጠን የተሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዓለሙ ዲሳሳ(ዶ/ር) ናቸው።   እነርሱም የኢንዱስትሪ፣ የአካባቢ ጥበቃና የአገልግሎት ዘርፍን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ያለሙ የጥናትና ምርምር ስራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። ቴክኖሎጂ በሁሉም ዘርፎች ውስጥ ያለው አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲውም ለቴክኖሎጂ እድገት ትኩረት ሰጥቶ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት ላይ ጥናትና ምርምሮች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ተገልጿል።  
ለዲጂታል ምህዳሩ የወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ እና ዲጂታል ቴክኖሎጂ  ዕድገት ጋር መጣጣማቸው እንዲጠና  ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀመጠ
May 24, 2024 64
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦ የብሄራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት በዲጂታል ምህዳሩ የወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ እና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸው እንዲጠና አቅጣጫ አስቀምጧል። ምክር ቤቱ መደበኛ ሁለተኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት ያደረገ ሲሆን በአንደኛ መደበኛ ስብሰባው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ትግበራ መገምገሙን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አመልክተዋል ፡፡   ፓርኩ ያሉበትን ውስን ተግዳሮቶች በመፍታት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ እና ከመንግስት ጋር ያለውን ትብብር የሚያጠናክር ቁመና እንዲላበስ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል። በፓርኩ በዳታ ሴንተር ዘርፍ የተሰማሩ ሁለት ድርጅቶችን እና የኢንኩቤሽን ማዕከልን መጎብኘታቸውንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።   የተመለከትናቸው ድርጅቶች በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት አስፈላጊውን መሰረተ ልማት አሟልተው ዝግጅት ከማጠናቀቃቸውም በላይ ለደንበኞቻቸው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተመልክተናል ብለዋል። በአጠቃላይ በፓርኩ ያየነው የስራ እንቅስቃሴ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂን ዕውን ለማድረግ ትልቅ ተቋም እየተገነባ መሆኑን ነው ሲሉም ገልጸዋል።  
አዲስ አበባን ትውልድ የሚገነባባት፣ ለሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና የሚተጉ ጥበበኛ ወጣቶችን የምታፈራ ከተማ ለማድረግ የጀመርነው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
May 24, 2024 143
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባን ትውልድ የሚገነባባት፣ ለሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና የሚተጉ ጥበበኛ ወጣቶችን የምታፈራ፣ የሀገራችን የብልጽግና ተምሳሌት ከተማ ለማድረግ የጀመርነው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። ከንቲባዋ “በፈጠራ ስራ የዳበረ ትውልድ ለሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ዘጠነኛውን ከተማ አቀፍ የሳይንስና ፈጠራ የተማሪዎች ዓውደ ርዕይ በወዳጅነት አደባባይ መክፈታቸውን አስታውቀዋል።   ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እያከናወንናቸው ያሉ ስራዎች ፍሬ እየሰጡ መሆናቸውን በዓውደ ርዕዩ የተመለከትናቸው የተማሪዎች የፈጠራ ስራዎች አስገንዝበውናል ብለዋል። ለትውልድ ግንባታ የላቀ ትኩረት በመስጠት የተማረውን በተግባር የሚያሳይ ችግር ፈቺ ትውልድ ለመገንባት እና አዲስ አበባን ትውልድ የሚገነባባት፣ ለሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና የሚተጉ ጥበበኛ ወጣቶችን የምታፈራ፣ የሀገራችን የብልጽግና ተምሳሌት ከተማ ለማድረግ የጀመርነው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ገልጸዋል።
የ2016 ብሔራዊ የሳይበር ተሰጥኦ ውድድር ምዝገባ ተጀመረ
May 24, 2024 74
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦የ2016 ዓ.ም ብሔራዊ የሳይበር ተሰጥኦ ውድድር ምዝገባ ከዛሬ ግንቦት 16 ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 እንደሚካሄድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ። አስተዳደሩ የ2016 ብሔራዊ የሳይበር ልዩ ተሰጥኦ ውድድር ፕሮግራም ምዝገባን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር ቢሻው በየነ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ታዳጊ ወጣቶችን በመመልመል ስልጠና ሰጥቶ አስመርቋል፡፡ የ2016 ብሔራዊ የሳይበር ተሰጥኦ ውድድር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሶስተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ ተናግረዋል። የዘንድሮው ብሔራዊ የሳይበር ልዩ ተሰጥኦ ውድድር ከዛሬ ግንቦት 16 ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 ድረስ ምዝገባው እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡ ለምዝገባው እድሜያቸው ከ11 ዓመት ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል አቅምና ፍላጎት ያላቸው መመዝገብ እንደሚችሉ ተናግረዋል። የሳይበር ሴኪዩሪቲ ዘርፍ ከፍተኛ የሰው ሀይል እጥረት ያለበት መሆኑን ገልጸው ተሰጥኦ ላይ መስራት የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸዋል። መገናኛ ብዙሀን፣ የትምህርት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም ቁልፍ የመንግስት ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም