በልጆቿ የጀግንነት ተጋድሎ ነፃነትን ሳትራብ ዘመናትን የተሻገረች-ኢትዮጵያ

10423

በቀደሰ ተክሌ (ሚዛን አማን ኢዜአ)

ነፃነት የሰው ልጅ ከፈጣሪ ከተቸሩት ፀጋዎች አንዱና ዋነኛው ነው፤ በራስ ፈቃድ መወሰን፣ በራስ መሻት መከወንና በራስ ማንነት መኖር የሰው ልጅ የነፃነት አብነቶች ናቸው።

ፈጣሪ ይህን ፀጋ የቸረው ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ነው።

ይሁን እንጂ ይህን ከፈጣሪ የተቸረውን ነፃነት በራሱ በወገኑ የመነጠቅ ዕጣ ፈንታ መግጠሙ አልቀረም፤ ነፃነቱን በራሱ ወገን እየተነጠቀ በራስ ፈቃድ መወሰን የማይችል እንዲሆን ተደረገ።

ጥቁር ሕዝቦች በተለይም አፍሪካውያን በነጮች ዘንድ የባርነት ግብር ተሰጣቸው። ቅኝ መግዛት ለእነሱ የኃያልነት መገለጫ አድርገው መረጡ።

በዚህም አፍሪካን ተቀራምተው የራሳቸው አደረጉ። ያኔ ቅኝ ግዛት አስተዳደር ዘመናቸው በራስ እምነት መቆም፣ በራስ ባህል፣ ወግና ማንነት መኖር አይታሰብም።

የሰው ልጅ ከቆዳ ቀለም ልዩነት በስተቀር በራሱ አምሳል ለተፈጠረው ሰው ተገዥ ይሆን ዘንድ አውሮፓውያን ከእኛ ውጭ ሰው ብለው በግዞት የያዟቸውን አገሮች ዜጎች የስቃይና የመከራ ህይወት እንዲያሳልፉ ፈረዱ።

ከባዱን የባርነት ቅንበር በጫንቃቸው ላይ ጫኑ። ማንነታቸውን አስረስተው ያሻቸውን አደረጉ። የቅኝ አገዛዝ ገፈት ቀማሽ እንድትሆን ፅዋ የደረሳት የጥቁሮች ፈርጥ ኢትዮጵያ ግን እንዲህ በቀላሉ ለቅኝ ገዥዎች እጅ አልሰጠችም።

ሰውን በሰውነቱ ብቻ የምታከብረው ኢትዮጵያ የልጆቿ ነፃነት በማንም ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ አልፈቀደችም።ኢትዮጵያን አፅንቶ ያቆማት በመከባበርና በአብሮነት ላይ የታነፀ ባህል፣ እሴት፣ ወግና ሥርዓት በባዕዳን እጅ ወድቆ ከሚከስም ''እኛ እንቅደም'' የሚል ጠንካራ የሀገር ፍቅርና ወኔ በአበራኮቿ ክፋይ ልብ ውስጥ እንደ አቶን እሳት ተንቀለቀለ።

በፈጣሪያቸው እንጂ በምድራዊ ኃይል የሚመኩ አይደሉምና ቅኝ ሊገዛቸው የመጣን የውጭ ወራሪ ኃይል በጀግንነት ታግለው የኢትዮጵያን አንድነት፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅና ለማስከበር በአንድ ልብ ወስነው ቀፎው እንደተነካበት ንብ ወደ አውደ ገባሩ ተመሙ። ኢትዮጵያዊ አንድነትን ኃይል፤ ወኔና ሞራልን ትጥቃቸው አድርገው በዓድዋ ተራራ እስከ አፍንጫው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የኢጣሊያ ጦር ገጠመ።

ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው ተፋለሙ፣ ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ለእኛ ለልጆቻቸው ነፃነትን አወረሱ፤ ለምንምና ለማንም የማይበገረው ኢትዮጵያዊ አንድነትን ትጥቅና ስንቃቸው ያደረጉትን የኢትዮጵያውያንን ከብረት የጠነከረ ክንድ መቋቋም የተሳነው ወራሪ የኢጣሊያ ኃይል ገሚሱ የጎራዴ እራት ሲሆን፤ ቀሪው ቁስለኛና ምርኮኛ ሆነ፤ ሌላው ደግሞ እግሬ አውጣኝ ብሎ ህይወቱን ለማትረፍ እግሩ ወደመራው ፈረጠጠ። ጅግኖች አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው፣ አጠንታቸውን ከሰክሰው የኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት አስጠብቀውና አስከብረው የፈጣሪ ልዩ ፀጋ የሆነውን "ነፃነት" ለዛሬው ትውልድ አስረከቡ። ኢትዮጵያም በትውልድ ቅበብሎሽ ሉዓላዊነቷምን አፅንታ የቆመች ነፃ አገር ሆና ቀጠለች።

በዘመኑ የነበረውን ጥቁር ነጭን ማሸነፍ አይችልም የሚለውን አስተሳሰብ በሀገር ፍቅርና ወኔ ወራሪውን የፋሽሽት ኢጣሊያ ኃይል በጦር በጎራዴ አርበድብደው ድል በመንሳት ጥቁር ነጭን ማሸነፍ እንደሚች በቅኝ ገዥዎች የአገዛዝ አስተዳደር ስር ወድቀው ለነበሩ የዓለም ጭቁን ሕዝቦች በተግባር አረጋገጡ።

በደማቸው ዘመን ተሻጋሪ ደማቅ የአርነት የታሪክ ድርሳን ጻፋ። በዘመን ጅረት የማይወይብ ታሪክ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በዓድዋ ተራሮች ላይ ተጻፈ። ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነትና የጀግንነት ተጋድሎ ነፃነት ሳትራብ ዘመናትን ተሻገረች። የነፃነት ዓርማ ሆና ለአፍሪካውያን ታየች።

የዓድዋ ድል በቅኝ አገዛዝ አስተዳደር ስር ወድቀው ይሰቃዩ የነበሩ የዓለም ጭቁን ሕዝቦች በተለይም አፍሪካውያን የአርነት ትግል አድርገው የግፍ፣ የስቃይና የመከራ ቀንበርን ከጫንቃቸው ላይ አሽቀንጥረው እንዲጥሉ የፃነት ተምሳሌት ሆነ። በኢትዮጵያ የተለኮሰውን የነፃነት ችቦን አቀጣጥለው ብርቱ የአርነት ተጋድሎ አደረጉ፤ በዓድዋ ድል ከቅኝ ገዥዎች መዳፍ አፈተለኩ። የጥቁር ጭቁን ህዝቦች ነፃነት በዓድዋ የድል ገድል ለዓለም ታወጀ።

አፍሪካውያን በራሳቸው ቋንቋ በነፃነት መናገር፣ በራሳቸው ባህል፣ወግና ሥርዓት እንዲሁም በራሳቸው መሪ ወደ ሚተዳደሩበት ምዕራፍ ተሸጋገሩ።የዓድዋ ድል ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነው በቀላሉ የተገኘ አይደለም።

ኢትዮጵያውያውያ ለሀገራቸው ባላቸው ቀናሂነትና ከብረት በጠነከረ አንድነትና በጀግንነት ተጋድሎ ተጋምዶ በተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግል እንጂ። የዓድዋ ድል ዛሬም ወደ ጀመርነው የልማት፣የዕድገትና የብልፅግና ማማ ላይ የሚያደርሰን መሰላል ነው። ይህ የሚሆነው ግን የአንድነት ኃይል ከጀግንነት ወኔ ሳይነጣጠል ፀንቶ ሲቆይ ብቻ መሆኑ እሙን ነው።

ቀደምት አባቶቻቸን የዓድዋ ከፍታን በክብር መቆናጠጥ የቻሉት ዘር እየቆጠሩ ሳይሆን በኢትዮጵያዊ አብሮነትና አንድነት ተጋምደውና ተሰናስለው ነው። ያላቸውን የአንድነት ኃይል ተጠቅመው ድልን ተጎናጸፉ። በየዓመቱ ዓድዋን መዘከር ራስን ''እኔስ ምን ማድረግ እችላለሁ?'' በሚል እሳቤ ከሆነ ዓድዋ ህያው ነው፤ ወደ አለምነው የስኬትና የብልፅግና ከፍታ ላይ የአንድነታችን ኃይሉ እንደሚያደርሰን እሙን ነው።

እንደ ቀደምት አባቶቻችን በተጋመደ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር በኢኮኖሚው፣ ማኅበራዊ፣ በፖለቲካው ያሉ ፈተናዎችን በሀሳብ ልዕልና በማሸነፍ ለሌላ ድል መትጋት አለብን።

አንድነታችንን በማፅናት በኅብረት ለኢትዮጵያ ከፍታ መትጋት ከሁላችንም ይጠበቃል።"ድር ቢያብር አንበሳ ያስር" እንዲ ሀገራዊ ብሂሉ ከተባበርን የማናልፈው ፈተና አይኖርም።

አንዴ በጦርነት ሌላ ጊዜ በድርቅና በሌሎች መንስኤዎች ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች በአብሮነት ተጋፍጠን ድል እያደረግን መጥተናል። ፈተና ሁሌም ይኖራል፤ ማሸነፍና መሸነፍ ግን በእኛ ፅናትና ጥንካሬ ይወሰናል። ለወደፊትም የሚያጋጥመንን ፈተና አንድነታችንን አፅንተን ኅብረታችን ለሀገራችን ልማት፣ ዕድገትና ብልፅግና በማዋል በርካታ ዓድዋዎችን እንሰራለን።

የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ጥቁር ጭቁን ህዝቦች የኩራት ምንጭ የነፃነት ዓርማ ነው። የዓድዋን ታሪክ መጠበቅና መደጋገም የእኛ የኢትዮጵያውን ኃላፊነትና ግዴታ ነው። ልዩነትን መስበክ ከኢትዮጵያዊ ከፍታ መሸራተት ነው።

እኛነትን ረስቶ እኔ ማለት የዓድዋን ታሪክ መሸጥ ነው። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን እንጂ ተከፋፍለን የሰራነው ታሪክ የለም።

የትናንት መልካም ስምና ዝና ከዘመኑ ጋር አብሮ ከፍ ከፍ እያለ አብቦ ማፍራት እንጂ፤ በልዩነት አስተሳሰብና አመለካከት ሊኮሰምን አይገባም። የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የሉዓላዊነት መገለጫ፣ የዓለም ጭቁን ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌ-ዓድዋ ለዘላለም በክብር ሲዘከር ይኖራል‼  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም