አፍሪካ ለ2030 እና አጀንዳ 2063 ግቦች የሚያስፈልጋትን የልማት ፋይናንስ ለማግኘት የራሷን የብድር ደረጃ መመጠኛ ተቋም ለማቋቋም ወሰነች - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ ለ2030 እና አጀንዳ 2063 ግቦች የሚያስፈልጋትን የልማት ፋይናንስ ለማግኘት የራሷን የብድር ደረጃ መመጠኛ ተቋም ለማቋቋም ወሰነች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፦ አፍሪካ ለ2030 እና አጀንዳ 2063 ግቦች የሚያስፈልጋትን የልማት ፋይናንስ ለማግኘት የተዛባውን የዓለም የፋይናንስ ስርዓት የሚያጣጥም የራሷን የብድር ደረጃ መመጠኛ ተቋም (African Rating Agency) ለማቋቋም መወሰኗን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።
የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 10ኛ ዓመታዊ ኮንፍረንስ በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መድረኩ በአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ፣ ዘላቂ ልማት፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አስተዳደርና በተለዋዋጭ ዓለም የአፍሪካ ፈተናዎች ዙሪያ የሚያተኩር ነው።
የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትን ጨምሮ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ በአሕጉሪቱ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚደረግ ጥረት ቢኖርም በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሰቃዩበትና የሚሰደዱበት አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
ይሄውም በአፍሪካ አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከጸጥታ ባለፈ በመልካም አስተዳደር፣ በልማትና የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት አስቻይ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በአፍሪካ የልማት ፋይናንስ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር፤ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ አስተዳደር የአጀንዳ 2063 እና 2030 ግቦችን ለማሳካት እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል።
በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋሙና አሁንም ያለው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ለአፍሪካ ፍላጎትና እውነታ ምላሽ የማይሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም አፍሪካን ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት ጋር ለማጣጣም የራሷን የብድር ደረጃ መመጠኛ ተቋም (Africa Rating Agency) ለማቋቋም መወሰኗን ገልጸዋል።
ይሄውም የአፍሪካ ሕብረት በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ሲሰራ ቆይቶ እ.አ.አ በመጪው ሰኔ ወር 2026 በሞሪሼስ በይፋ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በአፍሪካ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸው፤ በብዙ ሀገራት የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ንሯል፤ በአንዳንድ ሀገራት የነዳጅ ዋጋ ከ100 እስከ 150 በመቶ ጨምሯል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ሕብረት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በትብብር ሲሰራ መቆየቱን በመጥቀስ፣ የእርስ በርስ ትብብሩን ለማጠናከር በቅርበት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ተቋማት አጋርነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው በመግለጽ፤ በተቋማቱ መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ ትብብር ወደፊት ማሻገር ያስፈልጋል ብለዋል።