ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክር የጋራ አሸናፊነት ማብሰሪያ፤ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ማሳለጫ ነው-የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 16/2018 (ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ምክክር የጋራ አሸናፊነት ማብሰሪያ፤ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ማሳለጫ መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በማወያየት ምክክር የሚደረግባቸው ስምንት አጀንዳዎችን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በአጀንዳዎቹ ላይም አራት ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ምክክር ማድረግ ጀምረዋል።

በዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አመካካሪ አቶ አህመድ ሁሴን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ምክክሩ አንዱ የሌላውን ፍላጎት እና አተያይ በአግባቡ እንዲረዳ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው።

ከዚህ ቀደም ሩቅ ሆኖ በአጀንዳዎች ላይ የግል ምልከታን ማንጸባረቅ የተለመደ ነበር ያሉት አመካካሪው፤ አሁን ግን የሌሎችን ስጋት እና ፍላጎት በደንብ ለማየት ልዩ የሆነ እድል መፈጠሩን አንስተዋል።

ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በኢትዮጵያ አዲስ ባህል እና ልምምድ መሆኑን የገለጹት አቶ አህመድ፤ በምክክር ጉባኤው ለሀገር ግንባታ ገንቢና ጠቃሚ ሀሳቦች እየተነሱበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የምክክር ጉባኤው አሳታፊ እና አካታች መሆኑ የዜጎችን መተማመን እንደሚያሳድገው ጠቅሰው፤ ይህም ለሀገር መንግሥት ግንባታ እንዲሁም ለሀገር ግንባታ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከተመካካሪዎቹ መካከል አቶ መልካሙ ጸጋዬ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በተቃርኖ ጫፍና ጫፍ ሆነን ስንወጋገዝ ኖረናል ብለዋል።ምክክሩ ለኢትዮጵያ ሁሉም የድርሻውን የሚያበረክትበት አውድ የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

በምክክሩ ልማትን ለማፋጠን የሚረዱና የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ሀሳቦች እንደሚፈልቁበት ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ ለዚህም እንደ አንድ ተመካካሪ የድርሻዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

ምክክር የሁሉ ነገር መፍቻ ቁልፍ በመሆኑ ልዩነትን በኃይል ሳይሆን በምክክር የመፍታት ግብ ይዘን ወደ ምክክሩ መጥተናል ያሉት አቶ መልካሙ፤ የጋራ አሸናፊ የሚያደርገን ይሄው መንገድ ብቻ መሆኑን ገልጸዋለ።


 

ሌላው ተመካካሪ ወጣት ዮሴፍ አበራ በበኩሉ፤ በምክክሩ ላይ በመሳተፌ ብዙ ልምድ አግኝቻለሁ ያለ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉ ሀሳቦች እየመነጩበት መሆኑን መታዘቡን ገልጿል።

ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር ወሳኝ እርምጃ ላይ ነን ያለው ወጣት ዮሴፍ፤ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ ሀሳብ ይዘን ተነስተናል እንደሚሳካም ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም