አካባቢ ጥበቃ
የመዲናዋን ለውጥ የሚመጥኑ ህንጻዎች እንዲገነቡ ከቅድመ ግንባታ ጀምሮ ቁጥጥር እየተደረገ ነው
Dec 6, 2024 316
አዲስ አበባ፤ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፥የመዲናዋን ለውጥ የሚመጥኑ ህንጻዎች እንዲገነቡ ከቅድመ ግንባታ ጀምሮ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የኮሪደር ልማትና የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በመከናወን ላይ ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ደሲሳ፤ መስሪያ ቤታቸው የመዲናዋን ስማርት ሲቲ ፕሮጀክትና የኮሪደር ልማት ለማሳካት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል። በኮሪደር ልማት ከተማዋ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቷን አንስተው፥ ይህም ለሀገር ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አመላክተዋል፡፡ የኮሪደር ልማት ስራው ከመንገድ መሰረተ ልማት ባለፈ የከተማዋን የህንጻ ግንባታና አጠቃላይ ገፅታ የሚቀይር እንዲሁም ደረጃዋን የጠበቀች ማድረግን ያለመ ነው ብለዋል። ባለስልጣኑም የሚገነቡ ህንጻዎች እንዲሁም የአጥርና የመንገድ ዳር ማስታወቂያዎች የከተማዋን ለውጥ የሚመጥኑ መሆናቸውን የማረጋገጥና የመከታተል ስራ በትኩረት እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።   የህንጻዎችን የግንባታ ቦታ ተገቢነትና ህጋዊነት ማረጋገጥ፣ ከዋና መንገድ ተገቢውን ርቀት ጠብቀው እንዲገነቡ ማድረግ እና የግንባታ ጥራትና የህንጻ ከፍታቸው ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል አሰራርን እየተገበረ ነው ብለዋል። ህንጻዎቹ በሚገነቡበት ጊዜ እና የግንባታ ተረፈ ምርት በሚጓጓዝበት ጊዜ የከተማዋን ውበትና ፅዳት በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ባለስልጣኑ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የከተማዋን የህንጻ መስፈርቶች ያላሟሉ ግንባታዎች ሲገኙ የህንጻው ባለቤት፣ ተቋራጭ፣ አማካሪና የግንባታ ሂደቱን የሚከታተል የባለስልጣኑ ባለሙያ ጭምር ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር መኖሩንም አስረድተዋል። ከተማዋን ውብና ጽዱ ለማድረግ የግንባታ ተረፈ ምርቶች አያያዝና አወጋገድ ስርዓት በቅርቡ በከተማ አስተዳደሩ ተግባራዊ መሆን መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ
Dec 6, 2024 329
አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ። የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (ኢ/ር) በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በቁልፍ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር አላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል። ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው በልምምድ ልውውጥ፣ በስልጠና መርሃ ግብሮች፣ የብክለት አስተዳደር፣ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር፣ የስነ ምህዳር ጥበቃ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ጠንካራ የከባቢ አየር ሪፎርም ኢኒሺቲቮችን በጋራ በመተግበር ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። በተጨማሪም የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከሩሲያ መንግስት አቻ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን እና የምርምር ተቋማት ጋር ትስስር እንዲፈጥር በማድረግ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር እንዲሰራ ገልጸዋል። ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በአጋርነትና ኢኖቬሽን አማካኝነት ዘላቂ የከባቢ አየር መፍትሔዎችን ለማምጣት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።    
በአማራ ክልል ለዘንድሮው የበጋ ወቅት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ስራ ዝግጅት እየተደረገ ነው 
Dec 4, 2024 348
ባህር ዳር ፤ ህዳር 25/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወራት ለሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ስራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። ከዝግጅቱ መካከል ለ280 ሺህ 700 ቀያሽ አርሶ አደሮች ስልጠና መስጠት መጀመሩ ተጠቅሷል። የክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንዳመለከቱት፤ ባለፉት ዓመታት በክልሉ የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የአካባቢው ስነ-ምህዳር ወደነበረበት እየተመለሰ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ይህም የአፈር ክለት እንዲቀንስና ለምነቱ እየጨመረ እንዲመጣ ከማድረግ ባለፈ ተፋሰሶቹ በቂ የእንስሳት መኖ መገኛ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል። ስራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል በዘንድሮው የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራው በዘጠኝ ሺህ 67 ተፋሰሶች እንደሚከናወን ገልጸዋል።   ይህም መላ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በመጪው ታህሳስ ወር መጨረሻ ለሚጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። የልማት ስራውም በተራቆተ 366 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን፣ እንዲሁም የተለያዩ የውሃ ማስረጊያ " ስትራክቸሮች " ይከናወናሉ ብለዋል። በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ቀበሌዎች በሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በልማት ስራው እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ መሆኑን አመልክተዋል። ለዚህም ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከሰብል ምርት ስብሰባው ጎን ለጎን የተጀመረው የቀያሽ አርሶ አደሮች ስልጠና እስከ ቀጣዩ ወር አጋማሽ ተጠናቆ ወደ ተግባር ስራ እንደሚገባ አብራርተዋል። ለልማት ስራው ከሚያስፈልገው እስካሁን ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ አካፋ፣ ዲጅኖና ሌሎች የስራ መሳሪያዎች መለየታቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደር አላምረው ሞላ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት ዓመታት ያከናወኑት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።   በእርሻ ማሳቸው ላይ የተከናወነው የዕርከን ስራ የአፈር ክለትና መሸርሸር እየቀነሰ እንዲመጣ ከማድረግ ባለፈ የምርት ጭማሪ እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል። በያዝነው የበጋ ወቅት በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ያለማንም ቀስቃሽ ግንባር ቀደም ሆነው በስራው ለመሳተፍ እንደተዘጋጁም ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት ባከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ተጠቃሚ ሆነናል'' ያሉት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ አርሶ አደር መንጌ መንግስቴ ናቸው። የመሬቱ ለምነት በየጊዜው አየተሻሻለ መምጣቱ ምርታማነት እንዲጨምርና ከተፋሰሶች በቂ የእንስሳት መኖ እንዲያገኙ እያስቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል። በያዝነው ዓመትም ስራውን በእኔነት ስሜት ለማከናወን ተግባሩ የሚጀመርበትን ቀን እየተጠባበቁ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በውጤታማ መሆኑን ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ለማግኘቷ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል -  የደን አስተዳደር ምክር ቤት የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አናህ አጋሻ 
Dec 3, 2024 345
አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ለማግኘቷ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የደን አስተዳደር ምክር ቤት የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አናህ አጋሻ ገለጹ፡፡ እ.አ.አ በ1993 የተቋቋመው ዓለም አቀፉ የደን አስተዳደር ምክር ቤት ለኢትዮጵያ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያም በምክር ቤቱ የአስተዳደር ማረጋገጫ ከተሰጣቸው ከ85 በላይ አባል ሀገራት መካከል አንዷ መሆን ችላለች፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ40 ቢሊዬን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋኗን ከ23 በመቶ በላይ አድርሳለች፡፡ የደን አስተዳደር ምክር ቤት የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አናህ አጋሻ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለደን ልማት ምቹ ሥነ ምህዳር ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ለአየር ንብረት፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ጥቅም የሚውሉ ሀገር በቀል ዛፎች ጭምር ያሉባት መሆኗንም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ምክር ቤቱ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ለመስጠት ያወጣችውን ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ለማሟላት ያደረገችውን ጥረት እናደንቃለን ብለዋል፡፡ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተራቆቱ መሬቶችን በደን ለመሸፈንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብዙ መስራቷንም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ የደን አስተዳደር ደረጃ ለመካተቷ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የጎላ አስተዋፅኦ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም የኢትዮጵያ የደን ልማት ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በትብብር እንሰራለን ብለዋል፡፡   በፎሬስት ኦፍ ዘ ወርልድ የደን አስተዳደር ቴክኒካል ኤክስፐርት ጀንስ ካንስትራፕ ኢትዮጵያ ያገኘችው የአስተዳደር ደረጃ የአካባቢ ጥበቃን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የደን ልማት አስተዳደር ምክር ቤቱን ደረጃ ያሟለ መሆኑን ገልጸው፤ ከደን ልማት የሚገኙ ምርቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላታል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የደን ልማት መርኃ ግብር የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋገጠዋል፡፡      
በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ለመኸር ሰብል ስብሰባ አመቺ ደረቅ የአየር ሁኔታ ይኖራል - የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
Dec 2, 2024 232
አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2017(ኢዜአ):- በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ለመኸር ሰብልና ድህረ ሰብል ስብሰባ አመቺ የሆነ ደረቅ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሚቀጥሉት ቀናት ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ የቦረናና ጉጂ ዞኖች፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ እና የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ዞኖች ከቀላል እሰከ መካከለኛ የዝናብ መጠን እንደሚያገኙ ጠቁሟል። በአጠቃላይ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች በሚቀጥሉት 10 ቀናት የሚኖረው ደረቅ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብና ለድህረ ሰብል ስብሰባ አመቺ መሆኑን ገልጿል። ከሳምንቱ አጋማሽ በኋላ በተለይም በሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እሰከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ በትንበያው አመላክቷል። በመሆኑም አርሶ አደሮች ይህንኑ በመረዳት ሳይዘናጉ በማሳ ላይ የሚገኙ የደረሱ ሰብሎችን ባሉት ደረቅ ቀናት እንዲሰበስቡ ጥሪ አቅርቧል። በሌላ በኩል አልፎ አልፎ ባሉት ቀናት በደቡብና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚጠበቀው ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት የበጋ ወቅት ሰብል ለሚያመርቱ ጥቂት የደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጿል። በተጨማሪም ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት። በትንበያው መሰረት የሀገሪቱ የአየር ሁኔታ የገፀ ምድርና የግድቦችን የውሃ መጠን በማሻሻል ለበጋ መስኖ ውሃ አቅርቦት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል።
 የደን አስተዳደር ምክር ቤት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ማግኘቷን ይፋ አደረገ
Dec 2, 2024 235
አዲስ አበባ፤ህዳር 23/2017(ኢዜአ)፦ የደን አስተዳደር ምክር ቤት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ማግኘቷን ይፋ አደረገ። የደን አስተዳደር ምክር ቤት የደን ልማት አስተዳደርን በማሳደግ ምርታማና ምቹ ዓለምን ለመፍጠር እንደ እ.አ.አ በ1993 የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው። ተቋሙ ከ150 ሚሊየን ሄክታር በላይ የምስክር ወረቀት የተሰጠው የደን መሬትንም ያስተዳድራል። ዛሬ ይፋ የተደረገው የደን አስተዳደር ስታንዳርድ የኢትዮጵያን የደን ልማት ዘርፍ በማጠናከር ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ የደን ልማት ምርቶችን ጥራትና ተፈላጊነት ያሳድጋል ተብሏል። በተለይም የሥነ ምህዳር ተጽፅኖን ለመቀነስ እንደ ዉሀ፣ ካርበን፣ ብዝሀ ህይወት እና መሰል ዘርፎችን ለመጠበቅ ያግዛል። ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ የመሰለፍ እቅዷን እውን ለማድረግ በ2025 ዓ.ም 15 ሚሊየን ሄክታር የተራቆተ መሬት በደን ለመሸፈን እየሰራች ነው። የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም፤ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል። የደን ልማት አስተዳደር ደረጃው የተጠናከረ የአስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት የደን ጭፍጨፋን ማጥፋት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የተጠናከረ የደን ልማት አስተዳደር እና ቁጥጥር ስርዓትን በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል ብለዋል። የኢትዮጵያን የደን ጥበቃ ከማጠናከር ባለፈ ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ የደን ልማት ምርቶችን በጥራትና በብዛት ማቅረብ እንደሚያስችል ጠቁመዋል። በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ በብዛት የሚመረቱ የቀርከሃ ምርቶችን በተሻለ ጥራትና ተወዳዳሪነት ወደ ዓለም ገበያ ለማውጣት እድል ይፈጥራል ነው ያሉት። የደን አስተዳደር ምክር ቤት የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አናህ አጋሻ፤ ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ የደን አስተዳደር ደረጃ ስር መካተቷ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ የደን አስተዳደር ደረጃ መፅደቁ ኢትዮጵያ እና የደን አስተዳደር ምክር ቤቱ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ትብብር እና የጋራ ራዕይ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል። የደን አስተዳደር ምክር ቤቱ ለአስተዳደር ደረጃው ገቢራዊነት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ኮፕ 29 ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታከናውናቸውን ተግባራት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስገንዘብ አስችሏል
Nov 29, 2024 286
አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦ 29ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 29) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን ተግባራት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስገንዘብ እንዳስቻላት ተመላከተ። 29ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከሕዳር 2 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም በአዘርባጃን በባኩ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል። በጉባኤው ኢትዮጵያም በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተመራ ሉዑክ ቡድን ተሳትፎ አድርጋለች። የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሥዩም መኮንን በጉባኤውና በተጓዳኝ በተካሄዱ ስብሰባዎች የኢትዮጵያን ተሳትፎ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም፤ በጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ጉዳትና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በተመለከተ ውይይቶችና ድርድሮች ተካሂዷል ብለዋል። ኢትዮጵያ በጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገች ያለውን ጥረት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳየት መቻሉን ገልጸዋል። በጉባኤው በነበረው የኢትዮጵያ መካነ ርዕይ (ፓቪሊዮን)፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በተፈጥሮ ቱሪዝም፣ በአረንጓዴ ከተማ ልማት፣ በታዳሽ ኃይልና በሌሎች ዘርፎች የሰራቻቸውን ሥራዎች ማሳየት መቻሏን አብራርተዋል። የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከሌሎች አገራት ጋር አጋርነት በመፍጠር የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችል ሥራ መሠራቱን አመላክተዋል። በተለይም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሰራችውን ሥራ በቅጡ ማስገንዘብ በመቻሉ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከፍተኛ አድናቆት እንድታገኝ ማስቻሉን ጠቅሰዋል። ይህንንም ተከትሎ በርካታ አገራት ከኢትዮጵያ ልምድ ለመውሰድ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውን አመላክተዋል። ከጉባኤው ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር 19 የሁለትዮሽ ውይይቶችን ማድረጓንና ከሩሲያና ዴንማርክ ጋር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ሥምምነቶች መደረጋቸው ተመላክቷል።
መዲናዋን ውብና ፅዱ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ለአካባቢ ብክለት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል
Nov 26, 2024 357
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ ፅዱና ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ ለሚሰራው ስራ ውጤታማነት ባለድርሻ አካላት ለአካባቢ ብክለት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ ። የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተቋማት ቅንጅታዊ ስራዎችን እቅድ አፈፃፀም በጋራ ገምግሟል።   የባለሥልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ እንዳሉት አዲስ አበባ ከተማን ከብክለት የጸዳች እንደስሟ ዉብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚሰራው ስራ የአንድ አካል ተግባር ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተቋማት ርብርብ የሚጠይቅ ነው። ባለስልጣኑ ከበርካታ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ቅንጅታዊ አሰራሩ ተቋማት ያለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አስችሏል ነው ያሉት። ከብክለት የፀዳችና ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ከተማ ለመፍጠር በሚሰራው ስራ ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል። እንደምክትል ስራ አስኪያጁ ገለፃ የአካባቢ ጥበቃ ስራ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ በመሆኑ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። ካሁን ቀደም ተቋማት በግላቸው ሲያከናውኗቸው የነበሩ ስራዎች ውጤታማ እንዳልነበሩ ገልፀዋል። ባለስልጣኑ ይህንን በመመልከት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል ስምምነት በመፈራረም ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል። በዚህም ካሁን ቀደም ከነበረው የተሻለ ውጤታማ ስራ ማከናወን መቻሉን ነው የገለፁት። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት እውን በሆኑት የአረንጓዴ አሻራ፣ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ላይም በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። ቅንጅታዊ አሰራሩ የተቋማት የቁጥጥርና የመከታተል አቅም እንዲጨምር ማድረጉንም ነው የጠቀሱት። ባለፋት ስድስት ወራት "ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል የተከናወነው የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደጉ በመድረኩ ተነስቷል።    
በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማጠናከር የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተስፋፋ ነው
Nov 25, 2024 459
አዲስ አበባ፤ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማጠናከር የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተስፋፋ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ። በነገው ዕለት በይፋ የሚከፈተው የአፍሪካ መሰረተ ልማት መርኃ ግብር ሣምንት አካል የሆኑ የውይይት መድረኮች በአፍሪካ ኅብረት እየተካሄዱ ነው። "ለችግሮች የማይበገሩ አካታች መሰረተ ልማት ማስፋፋት ለአፍሪካ ዘላቂ ዕድገት" በሚል መሪ ኃሳብ ከተደረጉ መድረኮች የኢትዮጵያ የግሪን ሞቢሊቲ ተሞክሮ ላይ የመከረ የፓናል ውይይት ይገኝበታል። የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በረኦ ሀሠን በዚሁ ጊዜ፥ የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ፖሊሲ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልፀዋል። በታዳሽ ኃይል ተሽከርካሪዎች ላይ በተሰጠው ትኩረትም የከተማ ትራንስፖርት ሥርዓት ለዚህ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሰረት ልማቶች ግንባታዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ ገልፀዋል። ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ እንዲሁም የመንገድ ደኅንነት አገራዊ ስትራቴጂ መቅረጿንም አንስተዋል። የነዳጅ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎችን ለመቀነስና በኤሌክትሪክ ለመተካት በተሰጡ ትኩረትም ባለፉት ዓመታት በታዳሽ ኃይል ለተሰማሩ ኩባንያዎች ከፍተኛ ማበረታቻ እየተደረገላቸው ስለመሆኑ ጠቁመዋል። ለአብነትም ባለፉት ዓመታት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በመገጣጠም የተሰማሩ ኩባንያዎች እየተበራከቱ መሆኑን ገልፀዋል። ይህም ለግሪን ሞቢሊቲ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየች መሆኑን ተናግረዋል። የመንገድ፣የባቡርና የአየር ትራንስፖርት ማስተሳሰር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል። የግሉ ዘርፍ በሕዝብ የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት ዘርፍ እንዲሰማራ በተሰራው ሥራም አሁን ላይ በርካታ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በአገር ውስጥ እንደሚንቀሳቁሱ ገልፀዋል። በዓለም አቀፉ ትራንስፖርት ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ክሪስ ኮስት፤ በከተሞች ግሪን ሞቢሊቲ በተመለከተ የኢትዮጵያ ተሞክሮ አድንቀዋል። መንግሥታት ተደራሸና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባቸው አንስተዋል። በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር ልማት ሥራዎች ጥራታቸውና ደኅንነታቸው በተጠበቀ ተደራሽ ትራንስፖርት ሥርዓት እየተገነባች ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ከተማ መሰረተ ልማት ጅምሮች ጥራት ያላቸውና ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሆኑ ገልፀው፥ የከተማ ስትራቴጂ ቀርፃ ወደ ተግባር መግባቷ በአርዓያነት የሚወሰድ እንደሆነም ነው ያነሱት። የእግረኛ፣የሳይክልና ተሽከርካሪዎች ጎዳናዎች ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞችም በምሳሌነት የሚወሰዱ እንደሆኑ ገልፀዋል።            
ኮፕ 29 ለኢትዮጵያና አፍሪካ የካርቦን ሽያጭን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ ተስፋ ሰጪ ስምምነቶች የተገኙበት ሆኖ ተጠናቋል - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር
Nov 25, 2024 383
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ 29ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ የካርቦን ሽያጭን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ ተስፋ ሰጪ ስምምነቶች በመፈራረም መጠናቀቁን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ። ከሕዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ጉባዔ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል። በጉባዔው የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ልዑካን ቡድን ተሳትፎ አድርጓል። የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አንቀፅ 6.2 እንዲሁም 6.4 መሰረት የካርቦን ሽያጭ ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህም ለኢትዮጵያና ለቀረው የአፍሪካ ክፍል በጎ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በዚህ ስምምነት ጥላ ስር ኢትዮጵያ አስቀድማ የዘላቂ አረንጓዴ ልማት ትብብር መመስረትና አማራጭ ገቢ ማስገኛ ዕድሎቿን ማሳየቷን ገልጿል። አረንጓዴ አሻራን ለማጠናከር ፣ የታዳሽ ኃይል ልማትና አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም የግብርና ዘርፍን ለማትጋት የሚያግዝ አቅምን የሚያልቅ እንደሚሆንም ታምኖበታል። ስምምነቱ ኢትዮጵያ ምሳሌ በሆነችበት የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ በሀገራት መካከል ያለው ትብብር እንዲጠናከር በር እንደሚከፍት ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው። ለዚህም ኢትዮጵያና አፍሪካ የጀመሯቸውን ጥረቶች በማጠናከር ቀሪ የቤት ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባቸው ተመላክቷል። በተጨማሪም በኮፕ 29 ጉባዔ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋሚያ የሚውል የ300 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ አቅርቦት ስምምነትም ፀድቋል። በጉባዔው ላይ 200 አገራት የሚጠጉ ተሳታፊዎች ተካፍለዋል። 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) እ.አ.አ በ2025 በብራዚል ቤሌም ከተማ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ በ10 አመታት ውስጥ 95 በመቶ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለመጠቀም እየሰራች ነው
Nov 24, 2024 400
አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመጪው አስር አመታት ውስጥ 95 በመቶ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራች መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ። በአዲስ አበባ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮ- ግሪን ሞቢሊቲ ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም ዛሬ ተጠናቋል። የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በረኦ ሀሠን በዚሁ ወቅት፣ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም ረገድ ሰፊ እቅድ ይዛ እየሰራች ነው ። በትራንስፖርት ዘርፍ የኤሌክትሪክ መኪና ምርትን በማፋጠን የነዳጅ ወጪን ለመቀነስና አረንጓዴ ከባቢን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።   ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሚመጡት 10 ዓመታት ከ 432 ሺህ እስከ 500 ሺህ የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች 95 በመቶ የሚሆኑት የኤሌክትሪክ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ መንግስት ከፍተኛ እገዛና ክትትል የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል። በዚህም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በዘርፉ ላይ የፖሊሲ ምላሾች የተሰጡበት፣ ሙሉ በሙሉ የስትራቴጂክ አቅጣጫ የተቀየረበትና ለኤሌክትሪክ መኪኖች ምቹ መዳላድል የተፈጠረበት እንደነበር አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅትም ከውጭ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው የሚገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች ቀረጥ 5 በመቶ ብቻ ሲሆን በከፊል ተገጣጥመው የሚገቡት ደግሞ ምንም አይነት ቀረጥ እንደማይከፈልባቸው አብራርተዋል። በዘርፉ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች መኪኖቹን በጋራ በመሆን በስፋት እንዲያመርቱ ለማስቻል የፋይናንስ አማራጮችን ከማፈላለግ አንስቶ ሰፊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አንስተዋል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ 15 የሚጠጉ የግሉ ዘርፍ ባለሃብቶች የኤሌክትሪክ መኪኖችን በመገጣጠም ለአገልግሎት እያቀረቡ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።
የአካባቢና ማህበራዊ ተፅእኖ ግምገማ በማድረግ ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች ፈቃድ ተሰጥቷል
Nov 24, 2024 220
አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2017(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች የአካባቢና ማህበራዊ ተፅእኖ ግምገማ በማድረግ ፈቃድ መስጠቱን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለፀ። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሚ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ‘‘ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ‘‘ የአካባቢ ብክለት መግቻ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በሁሉም አካባቢዎች ተከናውኗል። የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄውን መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ማስጀመራቸውና ለተከታታይ ስድስት ወራት መካሄዱ ይታወሳል። የንቅናቄው ዓላማ የከተሞችን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን የተከተለ በማድረግ ውብና ምቹ ከተማ መገንባት እንዲሁም የድምጽ ብክለትን መከላከል ነው። በዚህም ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ለሚሆን ህዝብ በአካባቢ ብክለት ተፅእኖ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት። በተጨማሪም በባለስልጣኑ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ለሚቀርቡ የፕሮጀክት ጥናቶች የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማ መስራትና ማጽደቅ ይገኝበታል ብለዋል። በዚህም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ለ2 ሺህ 026 የፕሮጀክት ጥናቶች የአካባቢ እና ማህበራዊ ተፅእኖ ግምገማ በማድረግ ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል። እንዲሁም በአፈር፣ በውሃ፣ በድምፅ እና በአየር ብክለት ከማህበረሰቡ ሲነሱ ለነበሩ ከ356 በላይ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት መቻሉንም ጠቁመዋል። እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ የቆሻሻ መልሶ መጠቀም ልምድን በመገምገም የታዩ ክፍተቶችን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ በ29 የመልሶ መጠቀም ዘርፍ ላይ ለሚሰሩ ተቋማት ድጋፍና ክትትል ተደርጓል። በዚህም 347 ሺህ 329 ቶን ቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ እንደዋለም ጠቅሰዋል። ኢንቨስትመንት ለሀገር እድገት አስፈላጊ ቢሆንም የአካባቢንና የህብረተሰቡን ሰላም እና ጤንነት በጠበቀ መልኩ ሊከናወን እንደሚገባ አንስተዋል። ይህንን መሰረት በማድረግም ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች፣ የአበባ እርሻዎች እንዲሁም ሆቴሎች አካባቢን ከመጠበቅ ጋር ተያይዞ የማሻሻያ ስራ እንዲሰሩ ተደርጓል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር(P4G) በ2027 የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ ተመረጠች
Nov 18, 2024 449
አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር(P4G) በ2027 የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ ተመርጣለች። የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ስዩም መኮንን ከዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር ዳይሬክተር ሮቢን ማክጉኪን ጋር መምከራቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል። የኮፕ 29 ዓለም አቀፍ ጉባዔ እየተካሄደ ባለው የአዘርባጃን ባኩ መድረክ ጎን ለጎን የተካሄደው የስራ ኃላፊዎቹ ውይይት የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመመከት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የግሉ ዘርፍ ስለሚወጣው በጎ ሚና ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።   በዚህ ረገድ ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር(P4G) እያደረገ ላለው ተሳትፎ ሚኒስትር ዴዔታው አመስግነዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የአየር ንብረት ተፅዕኖ ለመከላከል ድጋፍ ለማድረግ በሀገራት መካከል ትብብር እንዲጎለብት የማድረግ ተልዕኮ ያለው የአረንጓዴ ልማት ትብብር(P4G) በ2027 የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ ኢትዮጵያ መመረጧ ተመለክቷል። ውሳኔው ኢትዮጵያ በዘላቂ የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲጎለብት እየተወጣች ላለው ጉልህ ሚና ዕውቅና የሰጠ ሆኗል። የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ስዩም መኮንን ከዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር ዳይሬክተር ሮቢን ማክጉኪን ጋር ባደረጉት ምክክር በዘላቂ የልማት ዕቅዶች ውስጥ የጅምር ፈጠራ ሀሳቦች(startups) ሚናን ማላቅ እንዲሁም ለአካታች የኢኮኖሚ ሽግግር ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያም መክረዋል። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመቋቋምና ዘላቂ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ለመገንባት ለሚደረግ ዓለም አቀፍ ጥረት የበኩሏን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗንም ሚኒስትር ዴዔታው አረጋግጠዋል። አለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ትብብር(P4G) እ.አ.አ 2017 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ዴንማርክ፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ሜክሲኮ እና ቬትናም መንግሥታት የተመሰረተ አጋርነት ነው።
በአማራ ክልል ህብረተሰቡን ባሳተፈ የደን  ልማትና ጥበቃ ስራ አበረታች ውጤት ተገኝቷል 
Nov 17, 2024 404
ባህር ዳር ፤ህዳር 8/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወነ የደን ልማትና ጥበቃ ስራ አበረታች ውጤት መገኘቱን የክልሉ አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ። አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ሃብትን በራሱ አያያዝና እንክብካቤ ስልት መጠበቅ የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና በባህር ዳር ከተማ ተሰጥቷል። የባለስልጣኑ ምክትል ሀላፊ አቶ በልስቲ ፈጠነ እንደገለጹት፤ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን በአግባቡ ማከናወን መቻል የአርሶ አደሩ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ትልቅ አቅም ይሆናል። የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ወንዞችና ሀይቆች በደለል እንዳይሞሉ፣ የመሬት መራቆት እንዳይከሰትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለመከላከል አይነተኛ መፍትሄ እንደሆነ ገልፀዋል። ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በአረንጓዴ አሻራና በመደበኛ የችግኝ ተከላ በተከናወነ ተግባር የክልሉ የደን ሽፋን 18 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን ጠቅሰዋል ። ከዚሁ ጎን ለጎን የተፈጥሮ ደንን በመጠበቅ እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ህብረተሰቡን በየአካባቢው በማደራጀትና የደን ቦታዎችን በመለየት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አመልክተዋል። በክልሉ አሁን ላይ 13 ጥብቅ የደን ቦታዎች እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በአንድ ተቋም ብቻ የሚከወን እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ የአጋርና ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። በዚህ ረገድ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው ሰብዓዊ ተግባራት በተጨማሪ ለጉዳዩ ትኩረት በማድረግ ለአርሶ አደሩ በቅርበት ሙያዊ እገዛ ለማድረግ እያከናወነ ላለው ተግባር ምስጋና አቅርበዋል። በወርልድ ቪዥን ኢትዮጰያ የሰሜን ምእራብ ሪጅን ሀላፊ አቶ ቴዎድሮስ አባተ በበኩላቸው፤ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ስራዎችን ከማከናወን በተጨማሪ በመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሰረት የልማት ስራዎችን እያገዘ ይገኛል። የተፈጥሮ ሃብትን ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ተሳትፎ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተው፤ የስልጠናው ዓላማም ይህን ለማጠናከር እንደሆነ አስገንዝበዋል።  
ኢትዮጵያ በሊቀመንበርነት የምትመራውና በከባቢ አየር ላይ ያተኮረ የአፍሪካ ሚኒስትሮች ኮንፍረንስ በአዘርባጃን ባኩ እየተካሄደ ነው
Nov 17, 2024 405
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በሊቀመንበርነት የምትመራውና በከባቢ አየር ላይ ያተኮረ የአፍሪካ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ በአዘርባጃን ባኩ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ከ29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(ኮፕ 29) ጎን ለጎን እየተካሄደ ያለውን ኮንፈረንስ በፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ሊቀመንበርነት የሚመራ ነው። በኮንፈረንሱ ላይ የአፍሪካ ሚኒስትሮች፣ባለሙያዎች እና የልማት አጋሮች ተሳታፊ ሆነዋል። በኮንፈረንሱ ቁልፍ በሆኑ የከባቢ አየር ጉዳዮች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮች እና የአፍሪካ የዘላቂ ልማት ዋንኛ ትኩረቶች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል። የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪ ቡድን ስራዎች፣ አፍሪካውያን በአየር ንብረት ለውጥ እና በሳይንስ ምርምር ያላቸው ሚና እና በቀጣይ በሚካሄደው 20ኛው የአፍሪካ ሚኒስትሮች የከባቢ አየር ኮንፈረንስ ላይ የውይይቱ አጀንዳዎች መሆናቸውን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ እና ቻይና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ
Nov 17, 2024 384
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 8/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቻይና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ። 29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(ኮፕ 29) በአዘርባጃን ባኩ መካሄድ ከጀመረ ዛሬ ሰባተኛ ቀኑን አስቆጥሯል። ከጉባኤው ጎን ለጎን ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ (Belt and Road Intiative) የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና ተፅዕኖ መቋቋም አላማው ያደረገ ውይይት ተካሂዷል። በኢትዮጵያና ቻይና የጋራ መድረክ ሁለቱ አገራት ያላቸውን የቆየ ወዳጅነት በአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ላይም በሰፊው በጋራ ለመስራት የሚያግዝ እንደሆነ ተገልጿል። በጉባኤው ላይ እየተሳተፋ የሚገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የተሻለች ሀገርና ዓለምን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የኢትዮጵያን ልምድና ውጤቶች አቅርበዋል። ሚኒስትሯ በተለይም ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 40 ቢሊዮን ችግኞች እንዲተከሉ ማድረጉን አንስተዋል። በዚህም መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ሀገራዊ የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደግ መቻሉንና ለበርካታ ዜጎችም አማራጭ የስራ ዕድል መፍጠር እንደታቻለም አመልክተዋል። ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልን እንደ ኬንያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ ላሉ ጎረቤት ሀገራት በማዳረስም ቀጣናዊ የአረንጓዴ ልማት ትብብር ለማጎልበት ጉልህ አበርክቶ እየተወጣች ነው ብለዋል። በአዘርባጃኑ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የቻይናን ልዩ ልዑክ የመሩት ሊዩ ዠንሚን ቤጂንግ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በኩል ለአረንጓዴና ለአነስተኛ የበካይ ጋዝ ልማት የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ሀገራት ከአየር ንብረት ጋር ለተስማሙ የልማት ግቦቻቸው ስኬት ከቀረጿቸው ፕሮጀክቶች ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል። ኢትዮጵያና ቻይና በፓሪሱ የአየር ብክለት መጠን ቅናሽ ስምምነት መሰረት ምሳሌ የሚሆን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ትብብር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።        
ኢትዮጵያ ቃል የገባችባቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶች እየፈጸመች ነው - የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም
Nov 14, 2024 376
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ቃል የገባችባቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶች በሙሉ የምትፈጽም ሀገር እንደሆነች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ገለፀ፡፡ ከዱባይ እስከ ባኩ ያለፈውን አንድ አመት ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሰራቻቸውን ስራዎች በተመለከተ በኢትዮጵያ ፓቪሊዮን ከአጋር ድርጅቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከፖሊሲ ለውጥ ጀምሮ በአረንጓዴ አሻራ፣ በታዳሽ ሀይል እንዲሁም በምግብ ሰብል እራስን ለመቻል በርካታ ስራዎችን እየሰራች እንደሆነ ገልጸዋል።   ባለፈው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ኮፕ28 ቃል የተገቡ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶችንም መፈፀሟን ተናግረዋል ፡፡ የልማት አጋር ድርጅቶቹ በበኩላቸው ዓለም የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን ለመሸፈን የሀይል አማራጮችን ሙሉ በሙሉ በታዳሽ ሀይል ለመተካት የያዘውን እቅድ ኢትዮጵያ ቀድማ ጀምራለች ነው ያሉት፡፡ በተለይም በአረንጓዴ አሻራ እየተሰራ ያለው ስራ ለተቀረው ዓለም ምሳሌ መሆን የሚችል መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ እየሰራችው ላለችው ስራ ድጋፍ እናደርጋለን ማለታቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት ያላት ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው- ታሪዬ ባድጌሲን
Nov 13, 2024 414
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2017(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት ያላት ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ሲሉ የ“ክላይሜት ኢንቨስትመንት ፈንድ' ዋና ስራ አስፈጻሚ ታሪዬ ባድጌሲን ተናገሩ። 29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) በአዘርባጃን ባኩ መካሄድ ከጀመረ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል። ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴን (ዶ/ር) ጨምሮ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጉባዔው ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። ፕሬዝዳንት ታዬ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና በአካባቢ ጥበቃ እየሰራች ያለችውን ስራ የሚያሳይ መካነ ርዕይ (ፓቪሊየን) መርቀው መክፈታቸው ይታወቃል። የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔው ተሳታፊዎች መካነ ርዕዩን በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ። በ “ክላይሜት ኢንቨስትመንት ፈንድ” (Climate Investment Fund) ዋና ስራ አስፈጻሚ ታሪዬ ባድጌሲን የተመራ ልዑካን ቡድንም በመካነ ርዕዩ ጉብኝት አድርጓል። የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጋር በደን ልማት ላይ ያተኮረ የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል። ባድጌሲን ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት አድንቀዋል። የግብርና ሚኒስትሩ፥ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ እና ልዑካቸው መካነ ርዕዩን በመጎብኘታቸውና ውይይት በማድረጋቸው ምስጋና ማቅረባቸውን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነትን እና የባለፈውን አመት የCOP28 ኃላፊነቶቿን በሶስት ሥራዎች እየተገበረች ትገኛለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
Nov 13, 2024 356
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነትን እና የባለፈውን አመት የCOP28 ኃላፊነቶቿን በሶስት ሥራዎች እየተገበረች ትገኛለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ። ቀዳሚው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ 40 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋን ከነበረበት በ6 በመቶ እንዲያድግ አድርጓልም ብለዋል።   ሌላው በ2015 የምርት እጥረትን ወደ ትርፍ ምርት የለወጠው በመስኖ የለማ ስንዴ መርሃ ግብር ሲሆን በታዳሽ የኃይል ምንጭ የታገዙ የእግረኛ መንገዶች ያሏቸው እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የቀረቡባቸው ዘላቂና አረንጓዴ ከተሞችን የፈጠሩ ለአየር ንብረት ጥበቃ ምቹ የሆኑ ዘመናዊ የከተማ ልማት ፕሮጀክቶች ሌላዎቹ ሥራዎች ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።   ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት #COP29 እየተካሄደ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ቀውስ ጉዳይን መፍትሔ ለማስገኘት የሚከናወኑ ተግባራት ፋይናንስን ኢላማ ከማድረግ ባሻገር ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያራምዱ የጋራ ግን በነፍስ ወከፍ የተለዩ ኃላፊነቶችን ብሎም ታሪካዊ ተጠያቂነትን የሚያጠይቁ መሆን እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥታለች ብለዋል። ግልፅነት ያላቸው የአየር ንብረት የገንዘብ ድጋፍ ብያኔዎች እድገትን እንደ አፍሪካ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ዝቅተኛ የልማት መጠን ያላቸው ሀገራትን በተጨባጭ ለመከታተል አስፈላጊ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም