ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ ነጻ የሕክምና አገልግሎት የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ማህበረሰብ ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ የበጎ ፈቃድ ነጻ የሕክምና አገልግሎት የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ማህበረሰብ ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ ብቁና ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡

«በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ» በሚል መሪ ሐሳብ የጤና ሚኒስቴር ከቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በጋራ ያዘጋጀው የክረምት የበጎ ፈቃድ የነፃ የጤና ምርመራ፣ ምክርና ሕክምና አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በጉለሌ ክፍለ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።


 

መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወነው የክረምት የበጎ ፈቃድ ሕክምና አገልግሎት ዋና ዓላማ በሽታዎችን ቀድሞ መከላከልና መለየት ላይ ያተኮረ ነው።

ይህ አገልግሎት ዜጎች ቀድመው ሕክምና የሚያገኙበት ትልቅ ዕድል መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አብረሃም እሸቴ በበኩላቸው፣ ሆስፒታሉ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በየዓመቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚያካሂድ ጠቁመዋል።

በዘንድሮው የክረምት መርሃ ግብርም ከ120ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የተለያዩ ነፃ የሕክምና አገልግሎቶችን ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸዋል።


 

አገልግሎቱም ከተለመዱት መደበኛ ምርመራዎች ባሻገር የቀዶ ሕክምና፣ የስፔሻሊቲ ሕክምናዎች እንዲሁም እንደ ሲቲ ስካን (CT Scan) እና ኤም አር አይ (MRI) ያሉ የላቁ የዲያግኖስቲክ ምርመራዎችን ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።

የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከሕክምና ሥራዎች ጎን ለጎን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኞችን መተከል፣ የአቅመ ደካሞች ቤቶችን ማደስ፣ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግና የማዕድ ማጋራትን እንደሚያካተት ተጠቅሷል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም