ዓለም አቀፍ ዜናዎች
የአፍሪካ ህብረት እና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በአህጉራዊ ትስስር ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ
Aug 26, 2025 502
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) በአህጉራዊ ትስስር አጀንዳ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማላቅ እንደሚሰሩ አስታወቁ። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በዓለም የንግድ ድርጅት(ጄኔቫ) የአፍሪካ ህብረት ቋሚ መልዕክተኛ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሴኤ) ዋና ፀሐፊ ክላቫር ጋቴቴ ጋር ተወያይተዋል።   ሁለቱ ወገኖች አፍሪካ በዓለም መድረክ አንድ የጋራ ድምጽ እንዲኖራት ማድረግ ያለውን ወሳኝ ጠቃሜታ አጽንኦት ሰጥተው መክረውበታል። የአፍሪካ ህብረት እና ኢሲኤ በንግድ፣ቀጣናዊ ትስስር እና የአፍሪካ የአዕምራዊ ንብረትን የበለጠ አጀንዳ ማራመድ ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ከኢሲኤ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።   ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በዓለም የንግድ ድርጅት(ጄኔቫ) የአፍሪካ ህብረት ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው በሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም መሾማቸው የሚታወስ ነው። የአፍሪካ ህብረት እና ኢሲኤ ትብብራቸውን እ.አ.አ በ1960ዎቹ መግቢያ ላይ መጀመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
አፍሪካ ህብረት እና ጃፓን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት በትብብር ይሰራሉ
Aug 24, 2025 454
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 18 /2017 (ኢዜአ)፦አፍሪካ ህብረት እና ጃፓን ያላቸውን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት በትብብር እንደሚሰሩ አስታወቁ። ዘጠነኛው የጃፓን አፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ፎረም(ቲካድ) በዮካሃማ መካሄዱን ቀጥሏል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከፎረሙ ጎን ለጎን ከጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ፕሬዝዳንት አኪሂኮ ታናካ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።   የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር የጃይካ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንዲሁም ኢኮኖሚና ማህበራዊን ጨምሮ በአፍሪካ ቁልፍ ዘርፎች እያደረገ ያለውን ኢንቨስትመንት አድንቀዋል። ሊቀ መንበሩ እና ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ ህብረት እና ጃፓን ያላቸውን የጋራ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ዘጠነኛውን የቲካድ ፎረም መንፈስ ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ ለውጥ በጋራ የመፍጠር ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚገባም አንስተዋል። ከነሐሴ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ፎረም የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ፤ የአህጉር በቀል መፍትሄዎች መድረክ 
Aug 23, 2025 458
በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አፍሪካውያን የአየር ንብረት በርቀት የሚያዩት ስጋት ሳይሆን የዕለት ተዕለት እውነታቸው ነው። በጎርፍ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች እና ተጠራርገው የሚወሰዱ ንብረቶች፣ በተከታታይ ድርቆች ምክንያት የሚያጋጥመው የምርታማነት መቀነስ የአየር ንብረት ለውጥ ከወለዳቸው ቀውሶች መካከል ይጠቀሳሉ። እነዚህ በተጨባጭ የዜጎችን ኑሮ እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች በአፍሪካ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስነ ምህዳር ላይ ለውጥ እንዲመጣ አስገድደዋል። የድህነት ምጣኔ እና የተፈናቃይ ዜጎች እየጨመረ መምጣት የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽእኖዎችን በተግባር የገለጡ ጉዳዮች ሆነዋል።   አፍሪካ ለዓለም የበካይ ጋዝ ልቀት ከአራት በመቶ በታች ድርሻ ቢኖራትም የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ከፍተኛ ቀንበር የሚያርፍባት አህጉር ሆናለች። ከሳህል ቀጣና የበረሃማነት መስፋፋት እስከ ምስራቅ አፍሪካ ኃይለኛ ጎርፎች የአህጉሪቷ ዜጎች በጣም ውስን ድርሻ ባላቸው ጉዳይ የቀውሱ ከፍተኛ ሰላባ እየሆኑ ነው። አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም። እንደ ዓለም አቀፉ የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት መረጃ ከእ.አ.አ 1991 እስከ 2022 ባለው ሶስት አስርት ዓመታት ባሉ እያንዳዱ አስርት ዓመታት በአፍሪካ በአማካይ የ0 ነጥብ 3 ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት ጭማሪ ተመዝግቧል። እ.አ.አ በ2024 የዓለም ሙቀት በ1 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሺየስ ጨምሮ በዓለም ታሪክ ከፍተኛው ሙቀት የተመዘገበበት ዓመት ነበር። 2024 በአፍሪካ የሙቀት መጠን 0 ነጥብ 86 በመቶ በመጨመር በአህጉሪቷ ታሪክ ከፍተኛው ሙቀት የተዘመገበበት ዓመት ሆኖም ተመዝግቧል። ከሙቀቱ በአሳሳቢ ሁኔታ መጨመር ባሻገር ድርቅ፣ ጎርፍ እና የምግብ ዋስትና ስጋት ላይ መውደቅ ሌሎች የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች ናቸው። እ.አ.አ 2024 ደቡባዊ አፍሪካ ክፍል በቅርብ አስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ድርቅ አጋጥሟታል። በድርቁ ምክንያት ዛምቢያ እና ዚምባቡዌ የሰብል ምርታቸው በ50 በመቶ ቀንሷል። በምስራቅ እና ማዕከላዊ አፍሪካ በቅርብ ጊዜ የተከሰቱ ከባድ ጎርፎች ሚሊዮኖችን አፈናቅለዋል፤ የዜጎች ህይወት አመሰቃቅላዋል መሰረተ ልማቶችንም አውድመዋል። የዓለም አቀፉ ሜትሮሎጂ ድርጅት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪካን ከሁለት እስከ አምስት በመቶ ጥቅል ዓመታዊ ምርት (ጂዲፒ) ወጪ እየወሰደ ይገኛል። አንዳንድ ሀገራት ለአየር ንብረት አስቸኳይ ምላሽ ዘጠኝ በመቶ ጥቅል ሀገራዊ ምርታቸውን ፈሰስ ያደርጋሉ። አፍሪካ በየዓመቱ ከ30 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ለአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ አቅዶች ትግበራ ቢያስፈልጋትም ከዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ውስጥ የምታገኘው ገንዘብ ከአንድ በመቶ በታች ነው። የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት የ2024 የአፍሪካ ሪፖርት የአፍሪካ የግብርና ምርታማነት ከእ.አ.አ 1961 በኋላ በ34 በመቶ መቀነሱን ይገልጻል። የአፍሪካ ሀገራት ከውጭ ሀገራት ምግብ ለመግዛት የሚያወጡት 35 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ወጪ እ.አ.አ በ2025 ማብቂያ ወደ 110 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ከፍ እንደሚል ገልጿል። የበረሃማነት መስፋፋት፣ የብዝሃ ህይወት መመናመን፣ የጤና እክሎች፣ መፈናቀል እና የታሪካዊ ቅርሶች አደጋ ላይ መውደቅ አፍሪካ እየገጠሟት ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽእኖዎች ውጤት ናቸው። አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት በየዓመቱ 250 ቢሊዮን ዶላር ቢያስፈልጋትም እያገኘች ያለችው 30 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት አፍሪካ የጥያቄ አምሮት ኖሮባት የምታነሳው አጀንዳ ሳይሆን የፍትህ እና የህልውናዋ ጉዳይም ጭምር ነው። በአዲስ አበባ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አህጉሪቷ እየገጠሟት ካሉ አንገብጋቢ ፈተናዎችን በዘላቂነት መሻገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራል። የሀገራት መሪዎች፣ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ወጣቶች እና የግሉ ዘርፍ በአንድነት ይወያያሉ። በጉባኤው ላይ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በታዳሽ ኢነርጂ፣ ዘላቂ ግብርና እና ተፈጥሮ ተኮር መፍትሄዎች ጨምሮ በአፍሪካ ያሉ አረንጓዴ የመፍትሄ ሀሳቦች የበለ ማላቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሀገራት ተሞክሯቸውን ያቀርባሉ። አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ በየዓመቱ የሚያጋጥማትን የ220 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ አቅርቦት ክፍተት መሙላት እና አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀም ላይ ምክክር ይደረጋል። በብራዚል ቤለም በሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) ጨምሮ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ድርድሮች ላይ የአፍሪካን ፍላጎቶች እና ጥቅሞች ማስጠበቅ የሚያስችል የጋራ እና ጠንካራ አቋም መያዝ ከጉባኤው የሚጠበቅ ውጤት ነው። የአፍሪካ ሀገራት በጉባኤው ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የሚያስችሉ ተጨባጭና መሬት ላይ የወረዱ እቅዶቻቸው ላይ የሚያቀርቡ ሲሆን የገቡትን ቃል ኪዳን ወደ ተግባር መቀየራቸውን የሚከታተል የቁጥጥር ስርዓት ትግባራትን የሚያጠናክሩባቸው መንገዶችን በማቅረብ በአጠቃላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን ቃልኪዳናቸውን ዳግም ያድሳሉ።   አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ገፈት ቀማሽ ሳትሆን የመፍትሄዎች እና የአይበገሬነት ስራዎች ማሳያም ናት። የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ እና አከባቢ ጥበቃ ስራዎች፣ የኬንያ የእንፋሎት እና የፀሐይ ኃይል ኢንሼቲቮች እንዲሁም የሞሮኮ ኑር ኦውርዛዛቴ የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አረንጓዴ ልማት ሊሆን የሚችል ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ የሚሳካ መሆኑን አፍሪካ ማረጋገጫ እንደሆነች በግልጽ የሚያመላክት ነው። አፍሪካ ከዓለም ዋንኛ በካይ ጋዝ ለቃቂ ሀገራት ገንዘብ በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሀገር በቀል የፋይናንስ እና ሀብት ማሰባሰብ አቅማቸውን የበለጠ ማሳደግ ይጠበቅባታል። የአዲስ አበባው ጉባኤም የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አቅርቦታቸውን እንዲጨምሩ ጥሪ የሚቀርብበት ነው። አፍሪካውያን እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ከንግግር ያለፉ ሀገር በቀል መፍትሄዎችን በመተግበር አይበገሬ አቅም ሊገነቡ ይገባል። የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎችን ከዓለም አቀፍ አጋርነት ጋር ከማዛመድ አኳያ ያላው ሚና ወሳኝ የሚባል ነው። ጉባኤው አፍሪካ ከአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ትርክት ወደ መፍትሄ አፍላቂነት እና የግንባር ቀደም ሚና አበርካችነት ለመሸጋገር እንደ መስፈንጠሪያ የሚያገለግል ትልቅ እድል ነው። የአዲስ አበባው ጉባኤ ከስብስባ ባለፈ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ቆርጣ ለተነሳችበት የተግባር ምላሽ ጉዞ እና የዓለም አቀፍ ተጠያቂነት መረጋገጥ የጋራ ትግል ውስጥ ትልቅ እጥፋት ሊሆን ይችላል።  
በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የአንድ ሀገር የመልማት እና የማደግ ፍላጎት ሊገደብ አይገባም - አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
Aug 5, 2025 893
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2017(ኢዜአ)፦መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የአንድን ሀገር የመልማት እና የማደግ መብት በፍጹም መወሰን የለበትም ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ። ሶስተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ኮንፍረንስ ዛሬ በተርኪሚኒስታን መካሄድ ጀምሯል።   በኮንፍረንሱ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ፣እስያ፣አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ የሚገኙ 32 ሀገራት ተሳታፊ ሆነዋል። ከተሳታፊዎቹ ሀገራት መካከል 16 ከአፍሪካ ናቸው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኮንፍረንሱ ላይ ባደረጉት ንግግር የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ያሉባቸውን የልማት፣የኢኮኖሚ እና የእድገት ፈተናዎችን አንስተዋል። በማደግ ላይ የሚገኙ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የመልማት አቅማቸው ባሉበት መልክዐ ምድራዊ ስፍራ ምክንያት ሊገደብ እንደማይገባ አመልክተዋል። ዋና ፀሐፊው የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የዓለምን ሰባት በመቶ ህዝብ የያዙ ቢሆንም በዓለም ኢኮኖሚና ንግድ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከአንድ ፐርሰንት ጥቂት ሻገር ያለ መሆኑን ገልጸው ይህ ትልቅ ኢ-ፍትሃዊነት ነው ሲሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ሀገራቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸው ድርሻ ዝቅተኛ ቢሆንም የጉዳቱ ዋንኛ ሰለባ መሆናቸውን አንስተዋል። የዓለም ማህበረሰብ ሀገራቱ በዓለም ኢኮኖሚ እና የንግድ ስርዓት ውስጥ ያላቸው ድርሻ እንዲያድግ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።   የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በዓለም የንግድ እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲጨምር የሚያስችል መዋቅራዊ ለውጥ ያሻል ያሉት ዋና ፀሐፊው፥ ይህም ሀገራት ጥሬ ምርቶችን ከመላክ ከፍተኛ እሴት ያለው ምርት ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ያደርጋል ነው ያሉት። የባለብዙ ወገን የልማት ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት አነስተኛ ወለድ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት ለሀገራት ተደራሽ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ከትስስር ጋር በተያያዘ የሚገጥማቸውን የመሰረተ ልማት እና መዋቅራዊ ችግሮች መፍታት እንደሚገባ አመልክተዋል። ለዚህም ድንበር ተሻጋሪ አሰራሮችን ማቅለል፣የተለያዩ የመመዘኛ ደረጃዎችን ማጣጣም እንዲሁም የተሳለጠ ንግድና ትራንዚት እንዲኖር የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ነው ያነሱት። ጉቴሬዝ በመሰረተ ልማት መጠነ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ይገባል ያሉ ሲሆን የባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የማይበገር የትራንስፖርት መተላለፊያ መስመር፣ ድንበር ተሻጋሪ የእርስ በእርስ የኢነርጂ ትስስር፣ ሰፊ የአየር ትስስር እና በቴክኖሎጂ የታገዙ የሎጅስቲክስ አውታሮች እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝበዋል። ሀገራቱ ያለባቸውን የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እክሎች ምላሽ ለመስጠት ፍትሃዊ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፈን እንዳለባቸው አሳስበዋል።   ኮንፈረንሱ ላይ ኢትዮጵያ እና የባህር በር የሌላቸው ሌሎች ሀገራት በዓለም የንግድ ስርዓት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ በትስስር፣ በፍትሃዊ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነት እና ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲያድግ ግፊት እንደሚያደርጉ ተመላክቷል። ሶስተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ኮንፍረንስ እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኤርትራ በአፋር ህዝብ ላይ እየፈጸመች ያለውን ግፍ የተሞላበት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሊያስቆም ይገባል -  የአፋር ቀይ ባህር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት 
Jul 22, 2025 819
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/ 2017 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኤርትራ በአፋር ህዝብ ላይ እየፈጸመች ያለውን ግፍ የተሞላበት የዘር ማጥፋት ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲያስቆም የአፋር ቀይ ባህር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ጥሪ አቀረበ። በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው በዳንካሊያ ክልል የሚገኙ የአፋር ህዝቦች የተቀናጀ የዘር ሽብር ዘመቻ መክፈቱን አመልክቷል። ድርጅቱ ኤርትራ በአፋር ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለው ያልተቋረጠ የጭካኔ ተግባር የዓለምን አስቸኳይ ትኩረት ይሻል በሚል መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫው የኤርትራ መንግስት መጠነ ሰፊ ግድያዎች፣ በግዳጅ ለውትድርና መመልመል፣ አስገድዶ መሰወር፣ ማሰቃየት እና ሆን ብሎ የአፋር ማህበረሰቦችን ማፈናቀል ጨምሮ የተለያዩ ግፎችን እየፈጸመ መሆኑን አመልክቷል። ድርጅቱ ኤርትራ የምትፈጽማቸው ድርጊቶች በመንግስት ደረጃ የተቀነባበረ የባህል እና የዘር ማጥፋት ዘመቻ አካል ነው ሲል ገልጿል።   እየፈጸሙ ያሉ በደሎች የአንድ ጊዜ ብቻ ክስተቶች አይደለም ይልቁንም በተጠና ፖሊሲ አፋርን ከኤርትራ ለማጥፋት በመንግስት እየተፈጸመ ያለ ተግባር ነው ብሏል። ድርጅቱ ጉዳዩን አስመልክቶ በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም ለአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝብ መብቶች ኮሚሽን በይፋ አቤቱታ ማቅረቡን ገልጾ በአፍሪካ ቻርተር የተቀመጡ 25 የመብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን አመልክቷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና ለዔሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት በኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት እና ተቋማት ማዕቀብ እንዲጥሉ ጥሪ አቅርቧል። ተቋማቱ ዓለም አቀፍ የሕግ እርምጃ እንዲወስዱ እና የአፋር ህዝብ የፍትህ፣ የመጠበቅ እና በራሱ የመወሰን መብት እውቅና እንዲሰጡ ጠይቋል። ኤርትራ በአፋር ህዝብ ላይ እየፈጸመች ያለው ግፍ እና በደል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች እና በሰብዓዊ መብት ተቋማት በሰፊው በማስረጃ ተሰንዶ ያለ ጉዳይ መሆኑን አመልክቷል። በኤርትራ መንግስት ላይ እርምጃ ካልተወሰደ የዜጎች ህይወት መቀጠፉን እንደሚቀጥል እና ሊቀለበስ የማይችል የባህል ውድመት እንደሚፈጥር ድርጅቱ አስጠንቅቋል።
በህንድ የአውሮፕላን አደጋ የ204 ዜጎች ህይወት አልፏል- የሕንድ ፖሊስ
Jun 12, 2025 1874
አዲስ አበባ፤ሰኔ 5/2017 (ኢዜአ)፦በህንድ የአውሮፕላን አደጋ የ204 ዜጎች ህይወት ማለፉን የሀገሪቷ ፖሊስ አስታወቀ። በሕንድ 242 መንገደኞችን ይዞ በህንድ ሰሜን ምዕራባዊ ክፍል አህመዳባድ ከተማ ከሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ለንደን ጋትዊክ ለማምራት በተነሳበት ቅፅበት በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ማረፊያ ላይ ተከስክሷል። በቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር አውሮፕላን ውስጥ 169 ህንዳውያን፣ 53 የብሪታኒያ ዜጎች፣ 7 ፖርቹጋላዊ እና አንድ ካናዳዊ ነበሩ።   በአደጋው የተረፈ ሰው ለማግኘት የሚቻልበት እድል እጅጉን የጠበበ ነው ሲል የአህመዳባድ ፖሊስ ኃላፊ ለአሶሲዬትድ ፕሬስ ገልጾ ነበር። ይሁንና ማምሻውን በወጣ መረጃ የ40 ዓመት የህንድ እና ብሪታኒያዊ ጥምር ዜግነት ያለው ቪሽዋሽ ኩማር ራሜሽ ከአደጋው መትረፉ ተጠቁሟል። እስከ አሁን የ204 ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል። የአውሮፕላኑ አካል የህክምና ባለሙያዎች ማረፊያ ላይ ወድቆ ቢያንስ አምስት የህክምና ተማሪዎች መሞታቸውን እና 50 ገደማ የሚሆኑት መጎዳታቸው ተገልጿል። የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት የሀዘን መግለጫ መልዕክት አደጋው ቃል ከሚገልጸው በላይ ልብ የሚሰብር ነው ሲሉ ገልጸዋል። በአደጋው ለተጎዱ በሙሉ ልባዊ ሀዘናቸውን በመግለጽ መጽናናትን ተመኝተዋል።
ኮሚሽኑ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ማስፈን ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ ይሰራል- መሐሙድ አሊ ዩሱፍ
May 12, 2025 1819
አዲስ አበባ፤ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዲሱ አስተዳደር በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ማስፈን ዋንኛ የፖሊሲ የትኩረት አቅጣጫው በማድረግ እንደሚሰራ የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዲሱ ሊቀ-መንበር መሐመድ አሊ ዩሱፍ ከሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋር ዛሬ ትውውቅ እና ቆይታ አድርገዋል። ሊቀ-መንበሩ በስልጣን ጊዜያቸው ሊያሳኳቸው ስላቀዷቸው ተቋማዊ ግቦችና ቅድሚያ ሰጥተው ለመፈጸም ያሳቧቸውን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዲሱ አስተዳደር በሰላም፣ ደህንነት፣ ልማትና ዓለም አቀፍ ትብብር ላይ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል። መሐመድ አሊ ዩሱፍ ሰላምና ደህንነት የኮሚሽኑ ዋንኛ የትኩረት ማዕከል መሆኑን አመልክተዋል። ኢ-ሕገ መንግስታዊ የመንግስት ለውጦች በአፍሪካ መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀናቸውን ተናግረዋል።   የአፍሪካ ህብረት መሰል ችግሮችን በመፍታት እንዲሁም ሰላምን በማስፈንና የዴሞክራሲ ስርዓትን በማረጋገጥ የህብረቱ አባል ሀገራትን ሉዓላዊነት እና ደህንነት መጠበቅ ላይ አበክሮ ይሰራል ነው ያሉት። ሊቀ-መንበሩ በገለጻቸው ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ መድረክ የአፍሪካን ድምጽ የበለጠ ለማጉላት እንደሚሻ ገልጸዋል። በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ የአፍሪካ ህብረትን ሚና ማጠናከር ቁልፍ ግብ መሆኑን ጠቅሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግበት በጽኑ ሁኔታ እንደሚሟገት አመልክተዋል። ሊቀ-መንበሩ የፀጥታው ምክር ቤት አሁናዊ መዋቅር የታሪክ ኢ-ፍትሃዊነት በማለት የገለጹት ሲሆን አፍሪካ በዓለም አስተዳደር የሚገባትን ትክክለኛ ስፍራ በሚገልጽ ሁኔታ ምክር ቤቱ ማሻሻያ ሊደርግበት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። በሌላ በኩል በዲጂታል ኢኮኖሚና ሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት በአፍሪካ ፈጠራ እና ዘላቂ ልማትን ማሳለጥ ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ነው ብለዋል። የህብረቱ ኮሚሽን ከቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ በማጠናከር ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ወጥነት ባለው መልኩ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ሊቀ-መንበሩ በአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል አማካኝነት ወረርሽኝን የመከላከል ዝግጁነት እና ምላሽ አቅም ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱንም አንስተዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዲሱ ሊቀ-መንበር መሐመድ አሊ ዩሱፍ በቀጣይ ከሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋር በየሶስት ወር ጊዜ ቆይታ እንደሚያደርጉ ለማወቅ ተችሏል። በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ መሐመድ አሊ ዩሱፍ ሙሳ ፋቂ ማህማትን በመተካት የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በባንጁል ቻርተር እና በማፑቶ ፕሮቶኮል ያላትን የአፈጻጸም ሪፖርቶች ማቅረብ ጀመረች
May 10, 2025 1320
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2017(ኢዜአ)፦ በፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ የተመራ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በአፍሪካ የሰዎችና ህዝቦች መብቶች ቻርተር ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ነው። በጋምቢያ ባንጁል የአፍሪካ የሰዎችና ህዝቦች መብቶች ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት እየተካሔደ ባለው ስብሰባ ላይ በአፍሪካ የሰዎችና ህዝቦች መብቶች ቻርተር (ባንጁል ቻርተር) ወቅታዊ የኢትዮጵያ አፈጻፀምና በአፍሪካ የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል (ማፑቶ ፕሮቶኮል) መነሻ ወቅታዊ አፈጻፀም ላይ ልኡኩ ሪፖርቶችን ማቅረብ ጀምሯል።   ሚኒስትር ዴኤታው ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በሪፖርት ዘመኑ በቻርተሩና ፕሮቶኮሉ መሰረት ያሉባትን ግዴታዎች ለመወጣትና የሰብአዊ መብቶችን ከማስጠበቅ አንጻር የተወሰዱ የፖሊሲ፣ የህግ እና ተቋማዊ እርምጃዎችን የሚመለከቱ ለውጦች ሪፖርት በዝርዝር ቀርቧል። በኮሚሽኑ መርሃ-ግብር መሰረትም ሪፖርቱን ተከትሎ ከኮሚሽነሮች ለተነሱ ጥያቄዎች ኢትዮጵያ በልዑካን ቡድኑ አማካኝነት ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ምላሾችን ትሰጣለች ተብሎ እንደሚጠበቅም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል። መድረኩ ኢትዮጵያ በባንጁል ቻርተር እና በማፑቶ ፕሮቶኮል ስምምነቶች መሰረት በአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶችን እና የፆታ እኩልነትን ለማጎልበት ያላትን ቁርጠኝነት የምታሳይበት እንደሆነም ተገልጿል።
በቱርኪዬ ኢስታንቡል በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 2 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ
Apr 23, 2025 1884
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2017(ኢዜአ)፦በዛሬው እለት በቱርኪዬ ኢስታንቡል በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 2 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል። እንደ አናዶሉ የዜና ወኪል ዘገባ ዛሬ ቀትር ላይ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የኢስታንቡል እና ጎረቤት አካባቢ ነዋሪዎች በፍርሃት የመኖሪያ ህንጻቸውን ለቀው እንዲወጡ አድርጓቸዋል። በሌላም በኩል ረፋዱ ላይ በኢስታምቡል አቅራቢያ የባህር ዳርቻ ቡዩኪክሚ የተባለ ስፍራ ላይ በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 9 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አናዶሉ የዜና ወኪል የሃገሪቱን የድንገተኛ አደጋ መቆጣጠር ባለስልጣን ጠቅሶ ዘግቧል። በአደጋው ምንም የተመዘገበ ጉዳት እንዳልተከሰተ የጠቀሰው ዘገባው ነዋሪዎች የዚህ ዓይነት አጠራጣሪ ሁኔታ ሲገጥም የተጎዱ ሕንጻዎች ውስጥ እንዳይገቡ የግድ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ተሽከርካሪዎችን እንዳይጠቀሙና ሌሎች የጥንቃቄ መልዕክቶችን ባለስልጣኑ ማስተላለፉም ተገልጿል። የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉ መሆናቸውንና ለዜጎችም መልካም ሁኔታ እንዲገጥማቸው መመኘታቸው ተገልጿል። ፕሬዝዳንቱ ከሃገሪቱ የድንገተኛ አደጋ መቆጣጠር ባለስልጣንና ከሚመለከታቸው አካላት መረጃዎችን በመቀበል በቅርበት እየተከታተሉ እንደሚገኙም ተገልጿል።
አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት ይኖርብናል - የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ
Apr 15, 2025 1512
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 7/2017(ኢዜአ)፦አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ሁሉን አቀፍ አቅም መገንባት ይኖርብናል ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ። የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት 24ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ዛሬ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል። ምክር ቤቱ በስብሰባው የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት የአንድ አባል ምርጫ ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል። በተመሳሳይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የዓለም አቀፍ ህግ አማካሪ አደረጃጀት (AUCIL) አንድ አባል እንዲሁም የአፍሪካ የህዋ ምክር ቤት (AfSC) አንድ አባል ምርጫ ይከናወናል ። በተጨማሪም ምክር ቤቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት፣ ቱሪዝም፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽን እና የትምህርት ፣ሳይንስ ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር የምርጫ ሂደት አስመልክቶ የተዘጋጀ ረቂቅ ሪፖርት ያዳምጣል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የአፍሪካ አህጉር በርካታ ውስብስብ ችግሮች እየገጠሙት ይገኛል። የአንዳንድ እርዳታ ሰጭ ተቋማት ድጋፍ መቋረጥ በጤናና በምግብ ዋስትና ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን ጠቅሰው፤ አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችል ሁሉን አቀፍ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የመሳሰሉ ዘዴዎችን ለመተግበር በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የወቅቱ የምክር ቤቱ ሊቀ-መንበር ቴቴ አንቶኒዮ በበኩላቸው፤ ሰላም እና መረጋጋት ለእድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። አህጉራዊ ተቋማት የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮችን ለመቋቋም የሚያስችል ጠቃሚ ግብዓት እንዳላቸው ጠቁመው፤ ይህም የውሳኔ ሰጭውን አካል መፍትሄ የሚፈለግ መሆኑን ተናግረዋል። የአፍሪካ ህብረት እነዚህን ተግዳሮቶች በጥበብ እና አርቆ አስተዋይ አመራር በመምራት ረገድ ንቁ መሆን አለበት ያሉት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተወካይ አምባሳደር ሒሩት ዘመነ ናቸው። የ2063 አጀንዳን ራዕይ ለማሳካትና የበለፀገች አህጉርን ለመፍጠር አህጉራዊ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ቀልጣፋ ስራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብስባ እየተካሄደ ያለው በየካቲት 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተደረገው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት ነው።  
ስድስተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ውይይት እና የዘላቂ ልማት ግቦች ፎረም ተጀመረ
Apr 7, 2025 994
አዲስ አበባ፤መጋቢት 29/2017(ኢዜአ)፦ ስድስተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ውይይት እና የዘላቂ ልማት ግቦች ፎረም ዛሬ በዩጋንዳ ካምፓላ መካሄድ ጀምሯል። ውይይቱ እየተካሄደ የሚገኘው “ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እርምጃዎችን በፋይናንስ መደገፍ ለአፍሪካ ዘላቂ አረንጓዴ እድገት እና ልማት፤ የፍትህ ጉዳይ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው። በመክፈቻው ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ፣ የህብረቱ አመራሮች፣ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በአዘርባጃን ባኩ የተካሄደው 29ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) የተላለፉ ውሳኔዎች በአፍሪካ ላይ የሚኖራቸውን አንድምታ በተመለከተ ምክክር እንደሚደረግ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው ያመለክታል። በኮፕ 29 ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አስመልክቶ ውሳኔ የተደረሰባቸው ጉዳዮች ለአፍሪካ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ አለመስጠታቸውን የገለጸው ህብረቱ በጉዳዩ ሀገራት ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ ገልጿል። በብራዚል ቤለም በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) የአፍሪካ የጋራ አቋም ምን መሆን አለበት? በሚለው ጉዳይ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል። እ.አ.አ በ2024 አፍሪካን የተመለከቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች እና በ2025 በሚኖሩ አጀንዳዎች ላይም ምክክር ይደረጋል። በአዲስ አበባ በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚቴ (CAHOSCC ) በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ይገመገማሉ። የአፍሪካ የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችም ሌላኛው የውይይቱ አጀንዳ ናቸው። በንጹህ መጠጥ ውሃ እና በማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የዋሽ ፕሮጀክት (WASH) አፈጻጸም ለተሳታፊዎች ቀርቦ ምከረ ሀሳብ ይሰጥበታል። በስብሰባው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና የዘላቂ ልማት ግቦችን የተመለከተ የውሳኔ ሀሳብ እንደሚጸድቅ የህብረቱ መረጃ ያመለክታል። ስድስተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ውይይት እና የዘላቂ ልማት ግቦች ፎረም እስከ ነገ ይቆያል።  
የአፍሪካ የውቅያኖስ አስተዳደር ስትራቴጂ ወደ ትግበራ ሊገባ ነው 
Mar 31, 2025 976
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፡- የአፍሪካን የባህር እና የመጠጥ ውሃ ሀብቶች ያለውን ቀጣናዊ ትብብር ማጠናከርን ያለመው የአፍሪካ የውቅያኖስ አስተዳደር ስትራቴጂ ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑ ተገለጸ። ስትራቴጂውን ለማፅደቅ የተዘጋጀ አውደ ጥናት ከነገ ጀምሮ በታንዛንያ ዳሬ ሰላም ይካሄዳል። ስብሰባውን ያዘጋጁት የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም በጋራ በመተባበር ነው። የአፍሪካ የውቅያኖስ አስተዳደር ስትራቴጂ የአፍሪካን የባህር እና የመጠጥ ውሃ ሀብቶች የሀገራት እና የዘርፉ ተዋንያን ትብብርን ለማጠናከር ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ ውይይት እንደሚደረግ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል። የስትራቴጂው ተቋማዊ ማዕቀፍ፣ የክትትል ስርዓትና የድርጊት መርሃ ግብር ውይይት የሚደረግባቸው ዋነኛ አጀንዳዎች ናቸው። የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ስትራቴጂውን ከብሄራዊ እቅዶቻቸው ጋር አጣጥመው በሚተገብሩበት ሁኔታ ላይም ይመክራሉ። የውቅያኖስ አስተዳደር ስትራቴጂው ከአፍሪካ የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ ከዘላቂ ልማት እና ዓለም አቀፍ ግቦች ጋር ያለው ትስስርም ውይይት ይደረግበታል። እ.አ.አ በ2023 በአሜሪካ ኒው ዮርክ የተፈረመው ዓለም አቀፍ የባህር ብዝሃ ህይወት ዘላቂ አጠቃቀም ስምምነት (BBNJ Agreement) የትግበራ አፈጻጸም ሌላው የአውደ ጥናቱ የመወያያ አጀንዳ ነው። የአፍሪካ ሀገራት እ.አ.አ ጁን 2025 በፈረንሳይ ኒስ በሚካሄደው ሶስተኛው የተባበሩት መንግስታት የውቅያኖስ ኮንፍረንስ ላይ ይዘው የሚቀርቡትን የጋራ አቋም ይፋ እንደሚያደርጉም የህብረቱ መረጃ ያመለክታል። የአፍሪካ የውቅያኖስ አስተዳደር ስትራቴጂ ለማፅደቅ የሚደረገው አውደ ጥናት እስከ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በማጽደቅ 48 ሃገራት ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል
Mar 25, 2025 620
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ጨምሮ እስካሁን 48 ሀገራት የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በማጽደቅ ለትግበራው ቁርጠኛነታቸውን ማሳየታቸውን የአህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣናው ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ ገለጹ። የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና በአፍሪካ አጀንዳ 2063 የልማት ማዕቀፍ ከተያዙ ግዙፍ አህጉራዊ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ስር ከሰደደ ድህነት እንደሚያላቅቅ ይጠበቃል። የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና መመስረቻ ስምምነትን እ.ኤ.አ. በ2018 በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ መፈረማቸው ይታወቃል። ኢትዮጵያም ስምምነቱን በወቅቱ ከመፈረም ባለፈ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል መጋቢት 12/2011 ዓ.ም አፅድቃለች። ዋና ጸሐፊው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነቱን 48 የአህጉሪቱ አባል ሀገራት አጽድቀውታል። እነዚህ ሀገራት ስምምነቱን ለመተግበር ያላቸውን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን የሚያሳልጡ ጠንካራ የህግ ማዕቀፎች እያዘጋጁ ነው ብለዋል። ከዚህም ባለፈ 19 አባል ሀገራት የቀረጥ መርሃ ግብር በማውጣት የንግድ ግብይት ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። አክለውም የአነስተኛና መካከለኛ አርሶ አደሮችን ምርት በማሰባሰብ አህጉራዊ የንግድ ትስስርን የሚያጠናክሩ ድርጅቶችን ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የንግድ ድርጅቶችን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረትም የአፍሪ-ኢግዚም ባንክ ለነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱ የ750 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም አስረድተዋል። የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደትና ዕድገት በማረጋገጥ የህዝቧን ተጠቃሚነት ማጎልበት የህልውና ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቀድሞ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዬሚ ኦሲንባጆ ናቸው። የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በጠንካራ የፖለቲካ አመራር መተግበር የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል። ከአህጉራዊ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት መካከል አንዱ የሆነው ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ፤ የአፍሪካን የወደፊት የኢኮኖሚ እጣ ፋንታ የሚወስን መሆኑንም ተናግረዋል። የአፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደትና ዕድገት የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ መታየት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለስኬቱም ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል። የአፍሪካን አህጉራዊ ውህደት ራዕይን እውን ለማድረግ እ.ኤ.አ በ1963 ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቋቋም ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። ለአብነትም የአፍሪካ መሪዎች እ.አ.አ በ2012 በአዲስ አበባ በተካሄደው የህብረቱ 18ኛ መደበኛ ጉባኤ አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና እንዲመሰረት ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም እ.ኤ.አ በ2015 ድርድሩን በይፋ በመጀመር በ2018 አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና መመስረቻ ስምምነቱ በይፋ ተፈርሟል። የአፍሪካ የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት 55 የአፍሪካ ሀገሮችን በአንድነት ያካተተ የነጻ ንግድ ስርዓት የፈጠረ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ስምምነት ነው፡፡ የአፍሪካ ሀገራት በአብዛኛው እቃዎች ላይ በሂደት ታሪፍን ለማስወገድ፣ የአገልግሎት ንግድን በሂደት ክፍት ለማድረግ እና የንግድ መሰናክሎችን ለማስወገድ የተስማሙበትም ነው፡፡
ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት ይሰራል - ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር)
Mar 14, 2025 575
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የተቋሙ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ገለጹ። ዋና ፀሐፊው ከወቅቱ የኢጋድ ሊቀ መንበር እና የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱ የደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ በተካሄደው 43ኛው የኢጋድ አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ ውጤቶች ላይ ያተኮረ ነበር።   ዋና ጸሀፊው ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) በውይይቱ በጉባዔው ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች ተግባራዊነት እና ኢጋድ ቀጣናዊ ፈተናዎችን ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት ላይ ከሊቀመንበሩ ጋር ሀሳቦች እንደተለዋወጡ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በሙሉ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል። አስቸኳይ ጉባኤውን ተከትሎ የደቡብ ሱዳን ኃይሎች አለመግባባቶችን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ ኢጋድ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ መሻሻል አለባቸው
Feb 12, 2025 893
አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2017(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ መሻሻል እንዳለባቸው በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ። 46ኛው የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሔደ ይገኛል። በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በዚህ ወቅት፤ አፍሪካውያን የተፈጥሮ ሀብታቸውን በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም ብለዋል። አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምታሳድረው ተፅዕኖ ጥቂት ቢሆንም የጉዳቱ ገፈት ቀማሽ መሆኗን ገልጸዋል። በመሆኑም የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ ሪፎርም መደረግ አለባቸው ብለዋል። የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት በመሰረታዊነት መቀየር እንዳለበትም ገልጸዋል። አፍሪካውያን አህጉራዊ ሀብታቸውን እሴት ጨምረው መጠቀም እንዲችሉ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። በአህጉሪቱ ጥሬ ምርትን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ በምርቶች ላይ እሴትን ጨምሮ የመላክ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። አፍሪካውያን ለደረሰባቸው ግፍና በደል ተገቢ የፍትሕ ካሳ ሊያገኙ እንደሚገባም ገልጸዋል። ይህ ችግር የዓለም የንግድ ስርዓትን በማዛባት የአፍሪካውያንን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በእጅጉ የጎዳ መሆኑን ተናግረዋል። አፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላት አሉታዊ ተፅዕኖ ውስን ቢሆንም የጉዳቱ ሰለባ ከመሆን አልዳነችም ብለዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ አፍሪካን የአህጉራዊ ጥቅል ምርቷን አምስት በመቶ እንደሚያሳጣት በመጥቀስ፣ በዓለም ዙሪያ ለኢንቨስትመንት ከሚመደበው ሀብት የአፍሪካ ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ይሄ የአፍሪካን ጥቅም የሚጎዳ ኢፍትሃዊነት በቃህ ሊባል ይገባል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት መሰረታዊ ሪፎርም ሊደረግባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።  
የቀድሞው ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ የ11 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው
Jan 30, 2025 780
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በሙስና በመደለል ከግብፅ መንግስት ጉቦ የተቀበሉት አሜሪካዊው የቀድሞው የኒው ጀርዚ ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ የ11 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል። በኒው ዮርክ በ12 ዳኞች የተሰየመው ችሎት የፍርድ ውሳኔውን ትናንት ማስተላለፉን የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኤንቢሲ ዘግቧል። ችሎቱ ከዚህ ቀደም የ71 ዓመቱን የሕግ ባለሙያና ፖለቲከኛ በ16ቱም የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ብሏቸዋል። የአሜሪካ ፌደራል ዐቃቤ ሕጎች የቀድሞውን ሴናተር ጉቦ ተቀብለው የግብጽ ወኪል ሆኖ በመስራት፣ ፍትሕ እንዲዛባ በማድረግና የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወንጀል መክሰሳቸው ይታወቃል። ዐቃቤ ሕጉ ሜኔንዴዝ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት የግብጽን ፍላጎት በማንጸባረቅ፣ ለዚህም ከግብጽ መንግስት ገንዘብ ማግኘታቸው በሰነድና በሰው ማስረጃ አረጋግጧል። የቀድሞው ሴናተር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ በኒው ጄርሲ በንግድ ስራ ላይ ከተሰማሩ 3 የግብጽ ሰዎች እጅ ወርቅ እና ጥሬ ገንዘብ ጉቦ ተቀብለዋል። ይህም ሴናተሩ ራሳቸውን ለግብጽ መንግሥት ወኪል አድርገው በመቆም ሰርተዋል የሚል ክስ ሲቀርብባቸው እንደነበረ ይታወቃል። በዚህም በዘረፋ፣ ጉቦ በመቀበል፣ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ በሴራ፣ ፍትህን በማደናቀፍና መሰል 16 ወንጀሎች ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸው ተገልጿል። በ16 የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ የተባሉት ሜኔንዴዝ የግብፅ መንግስት በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአሜሪካ መንግስት ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ረድተዋል የሚል ክስ እንደቀረባበቸውም እንዲሁ። ሜኔንዴዝ የውጪ መንግስታትን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተቀበሏቸው ስጦታዎች መካከል 100 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ወርቅና ቅንጡ መርሰዲስ መኪና የተጠቀሱ ሲሆን፣ በመኖሪያ ቤታቸውም 480 ሺህ ዶላር ጥሬ ገንዘብ በቤታቸው መገኘቱን የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከዚህ ቀደም በስፋት ዘግበውታል። የቀድሞው ሴናተር ከግብጽ የንግድ ባለቤቶች ጋር የጥቅም ትስስር እንደነበራቸው ተጠቁሟል። በክሳቸው ላይ ከግብጽ በተጨማሪ ከሌሎች የውጭ መንግስታት ጉቦ መቀበላቸው በምርምራ እንደተረጋገጠም ተመላክቷል። እ.አ.አ በ2021 የ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ የተዘጋጀው በ70 ዓመቱ ፖለቲከኛና የሕግ ባለሙያ ቦብ ሜኔንዴዝ ዋና አርቃቂነት ነው። በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ረቂቅ ሕጎቹ በሕግ አውጪው አካል ድምጽ ተሰጥቶባቸው እንዳይጸድቁ ለማድረግ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላትን በማናገር፣ደብዳቤ በመጻፍ፣ፊርማ በማሰባሰብና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ በማድረግ ጥረት አድርገዋል። ሕጉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት የሚጎዳና ሉዓላዊነቷን የሚጥስ እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል። እነዚህ ሕጎች እንዲፀድቁ ግብጽ ግፊት ስታደርግ እንደነበር ይታወቃል።
አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት የመውጣቷን ውሳኔ ማጤን አለባት - የአፍሪካ ህብረት
Jan 22, 2025 893
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት የመውጣት ውሳኔዋን እንድታጤነው ጠይቀዋል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ አውጥተዋል። በመግለጫቸውም አሜሪካ ከድርጅቱ አባልነት ለመውጣት መፈለጓ እንዳሳዘናቸው ሙሳ ፋኪ ገልጸዋል። ውሳኔውን መለስ ብሎ በማጤን በአባልነቷ ትቀጥላለች የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አስታውቀዋል። አሜሪካ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል(አፍሪካ ሲዲሲ) መስረታ ላይ ቀደምት እና ጠንካራ ደጋፊ ነበረች ሲሉም በመግለጫቸው አስታውሰዋል፡፡ አሁን ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዓለም አቀፉን የህብረተሰብ ጤና ደህንነት እንደ አንድ የጋራ ጥቅም የማረጋገጥ ተልዕኮውን ለመወጣት በዓለም ጤና ድርጅት ላይ ጥገኛ መሆኑን የገለፀው ህብረቱ፤ የድርጅቱ ቁልፍ መስራች አባል የሆነችው አሜሪካ ከተቋሙ የመውጣት ውሳኔዋን በድጋሚ እንድታጤነው ጠይቋል።
26ኛውን የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤን ኢትዮጵያ ታዘጋጃለች - ግብርና ሚኒስቴር  
Jan 15, 2025 827
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ 26ኛውን የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤ ልታስተናግድ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ጉባኤ በየዓመቱ በግንቦት ወር በፈረንሳይ ፓሪስ የሚካሄድ ሲሆን በየሁለት ዓመቱ ደግሞ በየአህጉራቱ እንደሚካሄድ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ 25ኛው ጉባኤ እአአ በ2023 ቦትስዋና ያስተናገደች ሲሆን 26ኛውን ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ መመረጧንም አስታውቋል። ጉባኤው "የእንስሳት ጤና ለምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ለሕብረተሰብ ጤና" በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 27 እስከ 30/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡ ለጉባኤው መሳካት ከዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ዋናው ጽህፈት ቤት፣ የአፍሪካ እና የምስራቅ አፍሪካ ተወካዮች ጋር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውም ተገልጿል። የግብርና ሚኒስቴርም ግብረ-ሃይል በማቋቋም ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡ በጉባኤው ከየአፍካ ሀገራት የጤና ኃላፊዎችና ቋሚ ተወካዮች፣ ከዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት፣ በየአህጉሩ ያሉ የእንስሳት ጤና አመራሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች እንደሚታደሙም ተጠቁሟል። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) በጉባኤው በአፍሪካ የእንስሳት ጤና አገልግሎት፣ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን መቆጣጠርና መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ብሎም ከበሽታ ነጻ የሆነ አህጉር ለመፍጠር የሚረዱ ውይይቶች ይደረጋሉ ብለዋል። በጉባኤው በእንስሳት ጤናና ልማት፣ በምግብና ስነ-ምግብ ዙሪያ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚገኙና የተለያዩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት ገልጸዋል። በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እየተሰሩ ያሉ እንደ ዝርያ ማሻሻል፣ መኖ፣ የእንስሳት ጤና እና የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ በስፋት ውይይት ይደረግባቸዋል፤ አቅጣጫዎች ይቀመጡበታል ሲሉም ተናግረዋል። የእንስሳት ጤና በንጥረ ነገር የበለጸገ ምግብ ለማምረት እንደሚረዳ፣ መቀንጨርን ከመከላከል አንጻር የእንስሳት ጤና ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳለውም የምናይበት መድረክ ነው ሲሉም ገልጸዋል። ጉባኤው ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራትና በአህጉር ደረጃ ካሉ ሀገራት ጋር ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን ለመቆጣጠር፣ የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ብለዋል። ሀገራት ያላቸውን የእንስሳት በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስትራቴጂና ተሞክሮ፣ ኢትዮጵያም በእንስሳት ጤና፣ መሰረተ ልማት እና ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን ለዓለም የምታስተዋውቅበት፣ ልምድ የምንጋራበት መድረክ ነው ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። ከመቶ ዓመት የዘለለ የእንስሳት ጤና አገልግሎትና የምርምር ተቋማት፣ በእንስሳት ጤና ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ፣ ክትባትና መድሃኒት የሚያመርቱ፣ በእንስሳት ጤና የሰው ሃይል የሚያፈሩ ተቋማት መኖራቸው መልካም አጋጣሚዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የሚካሄደው የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ ጉባኤ የእንስሳት ጤና እንዲጠበቅ ብሎም ዘርፉ እንዲነቃቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለታቸውም በመረጃው ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም