ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ ነው-ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሂደት በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ዋናውን የምክክር ጉባኤ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፣ ምክክሩ አጀንዳዎችን በማብላላትና በምሁራን ገለጻዎች ተደግፎ በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል።

ባለፉት ቀናት በተከናወኑ የምክክር መድረኮች ተመካካሪዎች በቡድን ተከፋፍለው የተሰጧቸውን አጀንዳዎች በጥልቀት በማብላላት፣በመደማመጥና በመከባበር ወደ ሐሳብ ማጠናቀር ሂደት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደው የምክክር ጉባኤም ተመካካሪዎች በ50 እና በ10 አባላት በመከፋፈል የመጀመሪያውን የሐሳብ ማመንጨትና ማጠናከር ሂደት ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

በ10 አባላት በመደራጀት የተካሄደው ውይይት በተመካካሪዎች መካከል የልብ ቅርርብ በመፍጠር እንዲተዋወቁና በተሰጧቸው አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት እንዲመክሩ ማስቻሉን አስረድተዋል።

በዚህም ሂደት ተመካካሪዎች እርስ በእርሳቸው እንዲቀራረቡና አጀንዳዎችን በጥራት እንዲያብላሉ በተዘረጋው አሠራር መሠረት ውጤታማ ሥራ መሠራቱን አመልክተዋል።

10 አባላት ባሏቸው ቡድኖች በተካሄደው ምክክር የተጠናቀሩ ሪፖርቶች ላይ ከነገ ጀምሮ 50 አባላት ባሏቸው ቡድኖች በመሰባሰብ ውይይት እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

በዛሬው ዕለትም ሙያተኞች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በስምንት ቡድኖች ለተከፋፈሉ ተመካካሪዎች ሰፊ ማብራሪያዎችንና መረጃዎችን መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በሀገር ግንባታ፣ በታሪክ፣ በፌዴራሊዝምና በማንነት ጉዳዮች ላይ በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ለተመካካሪዎች ልዩ ግብዓት የሚሆን ገለጻ በማቅረብ፣ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ መስጠታቸውን አስረድተዋል።

ከነገ ጀምሮም 10 አባላት ባሏቸው ቡድኖች በተካሄደው ምክክር ያጠናቀሯቸውን ሪፖርቶች ለ50 አባላት ባሏቸው ቡድኖች በማቅረብ የቀጣዩ የውይይት ሂደት እንደሚጀመር ገልጸዋል።

በምክክር ጉባኤው 4 ሺህ ተመካካሪዎችን ማስተናገድ ሰፊ ዝግጅት የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የጤና፣ የጸጥታና ደህንነት፣ እንዲሁም የትራንስፖርት ተቋማት እያደረጉት ያለውን የተቀናጀ ድጋፍ አድንቀዋል።

የተከናወኑት የውይይት ሂደቶች በስምንቱም ቡድኖች ውስጥ በ500 ተሳታፊዎች ተደራጅተው ሲካሄዱ ቆይቷል ብለዋል።

ከነገ ጀምሮ 50 አባላት ያሏቸው ቡድኖች ያጠናከሯቸውን ሪፖርቶች ለቡድኖቻቸው በማቅረብ ወደ 250 አባላት ባሏቸው ሃምሳ ቡድኖች የሚደረገው ቀጣይ የውይይት ሂደት እንደሚሸጋገር ገልጸዋል።

በቀጣይ ሳምንት ደግሞ 4 ሺህ ተሳታፊዎች በ16 ቦታዎች ተከፋፍለው የምክክር ሂደቱን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

በውይይቱ ወቅት ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ተሳታፊዎች በፌዴራልና በክልል ሆስፒታሎች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም የጸጥታና ደህንነት፣ የትራንስፖርትና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ለተሳታፊዎች አስፈላጊውን አገልግሎት በተቀናጀ መልኩ እየሰጡ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም